lørdag 2. februar 2013

መቀሌ ዉስጥ ህወሀት ለሁለት መሰንጠቁን የሚጠቁሙ ወረቀቶች መበተናቸዉ ተሰማ


ላለፉት ስድስት ወራት በተለይ ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ በአባላቱ የእርስ በርስ ሽኩቻና የቃላት ጦርነት ሲታመስ የከረመዉ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ግንባር ጭራሽ ለይቶለት ሁለት ቦታ የመሰንጠቅ አደጋ ላይ መዉደቁ የማይቀር መሆኑን የሚጠቁሙ በራሪ ወረቀቶች መቀሌ ዉስጥ በመበተን ላይ መሆናቸዉን ዉስጥ አዋቂ ምንጮቻችን ከመቀሌ በላኩልን ዜና ገለጹ። ባለፈዉ ረቡዕና ሀሙስ መቀሌ ዉስጥ ለህወሀት አባላትና ለከተማዉ ህዝብ በትግርኛ ቋንቋ ተጽፎ የተበተነዉ ወረቀት ስዩም መስፍንን፤ አባይ ፀሐዬንና ፀጋዬ በርሔን ከነባለቤቱ ከህወሀት እንዲባረሩ የሚጠይቅ ሲሆን ለህወሀት ክፍፍልና ያለመስማማት ዋና ምክንያት ነዉ ያላቸዉን የድርጅቱን መስራቾች ስብሐት ነጋንና አንዳንድ ጓደኞቹን ደግሞ እርምጃ እንዲወሰድባቸዉ ይጠይቃል። በትናንትናዉ ዕለት ከወደ መቀሌ በደረሰን ዜና መሠረት ወረቀቱን የበተኑት እነ ቴውድሮስ ሃጎስ፣አዜብ መስፍንና በረከት ስምኦን መሆናቸዉን ለማወቅ ተችሏል።
የተበተነዉ ወረቀት “ሕዝባችን አስተውል” የሚል ሀይለ ቃል ያለበት ሲሆን ሆኖም ወረቀቱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠዉ እነሱ ህዝብ የሚሉት የትግራይን ህዘብን ብቻ ነዉ። ወረቀቱን የበተነዉ ቡድን ለህዝብ ባስተላለፈዉ መልዕክት ዉስጥ «ተቆርቋሪ ለሆናችሁ የትግራይ ተወላጆች በሙሉ፤ «ድርጅታችሁ ህወሀት እስከ ዛሬ ታግላ እዚህ ደረጃ አድርሳችኋለች። በተለይም የሁሉም ነገር አድራጊና ፈጣሪ የነበረውን ባለ ራዕይ መሪያችንን በቅርብ ጊዜ አጥተናል። ዛሬ እነዚህን ደካማ ጐኖች ተጠቅመው ለጠላት አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ያውም ደግሞ ህዝብ የኔ የሚላቸው ጅቦች ተነስተውብናል የሚሉና የትግራይ ህዝብ ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጠላትነት እንዲተያይ የሚገፍፋፉ ቃላቶች ተደርድረዉበታል።

ይህ ህዝብን ከሀዝብ ጋር በሚለያይና ለጥፋት በሚዳርግ መልከ ተጽፎ የተበተነዉ ጽሁፍ “እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል መስራቾች ነን” ብሎ እራሱን ካወደሰ በኋላ ህወሀት ወደኋላ መገፍተሩን ብሎም በአንፃሩ ሌሎች ህወሀት ያሳደጋቸዉ ድርጅቶች መጠናከራቸዉንና ይህም የትግራይን ህዝብ ጥቅም እንደጎዳዉ ያለምንም ሀፍረት በመዘርዘር ከዚህ አደጋ ዉስጥ መውጣት ካለብን ከድርጅቱ የተወገዱትን የቀድሞ አባላት መልሰን ወደ ፓርቲው ማስገባት አለብን። ይህ ካልሆነ ግን የሕዝብ ትግል አውላላ ሜዳ ላይ ጅብ በልቶት ሊቀር ነው በማለት ከጠላቶቻችን ጋር እንታረቅ እያሉን ነውና “ሕዝባችን አስተውል” እያለ አንደኛዉን አንጃ ይከስሳል። ከላይ ከፍ ሲል አንደተጠቀሰዉ ክሱን የሚያቀርበዉ የአዜብ መስፍን፤ በረከት ስምኦነና ቴዎድሮስ ሀጎስ ቡድን ሲሆን ክሱ የሚቀርበዉ ደግሞ በነስዩም መስፍንና አባይ ጸሐዬ ቡድን ላይ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ጽሁፉ ስብሀት ነጋን የዚህ ሁሉ አፍራሽ ሴራ ጠንሳሽና አራማጅ ነዉ በማለት ይኮንነዋል።
ህወሀት ኢትዮጵያ ዉስጥ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋል የመከፋፈል አደጋ ሲገጥመዉ ይህ ሁለተኛ ግዜዉ ሲሆን የመጀመሪዉን አደጋ መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎቹን በማሰርና ከድርጅቱ በማባረር ማሰታገስ መቻሉ የሚታወስ ነዉ። አሁን ግን ህወሀት ይህ ነዉ ተብሎ የሚታይና የሚፈራ መሪ ስለሌለዉ ይህ መከፋፈልና መባላት ለ38 አመቱ ድርጅት የመጨረሻዉ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል ሲሉ ብዙዎች አስተያየት በመስጠት ላይ ናቸዉ።
  • facebook
  • google_buzz
  • twitter
  • rss
  • print
  • bookmark
  • email

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar