lørdag 2. februar 2013

በደል እንዴት ይራሳል?



የኢትዮጵያ ህዝብ መስከረምን ከጥቅምት ወይም ታህሳስን ከጥር ጋር አወዳድሮ ይህ ወር ከዚህ ወር ይበልጣል ወይም ይሻላል ብሎ የሚያምንበት ልዩ ምክንያት ባይኖረዉም እያንዳንዱ ወር በመጣ ቁጥር ግን ይዞት የሚመጣዉ የራሱ የሆኑ ታሪካዊ፤ ባህላዊና ፖለቲካዊ ትዝታዎች አሉት። የቅርቡንም ሆነ ቆየት ያለዉን ታሪካችንን ወደ ኋላ ዞር ብለን ስንመለከት ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀልንና የዚያኑ ያክል ተስፋችንን አጨልሞ ጽልመት ዉስጥ የከተተን ወር ቢኖር ወርሃ ግንቦት ነዉ። አዎ ! . . .  ግንቦት የፖለቲካና የባህል ቁመናችንን የዳሰሱ አያሌ ክስተቶችን ያስተናገደ ጉደኛ ወር ነዉ።  . . .  ግንቦት ልደታ፤ ግንቦት 8፤ ግንቦት 20ና ግንቦት ሰባት በየአመቱ የግንቦት ወር በመጣ ቁጥር የምንዘክራቸዉ አገራዊ ትዝታዎቻችን ናቸዉ። ግንቦትንና እነዚህን ትዝታዎች የብዕር ሰዎቻችን በየዘመኑ ያነሷቸዋል፤ የኪነት ሰዎቻችን ቅኔ ይቃኙላቸዋል የየዘመኑ የታሪክ ድርሳኖቻችንም ይዘግቧቸዋል።
ግንቦት 7 1997 በኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲ ትግል ታሪክ ዉስጥ ልዩ ቀን ናት። ግንቦት ሰባት አንድ ትዉልድ ብቻ ሳይሆን ሁለትና ሦስት ትውልድ የደም ላብ አልቦና የህይወት ግብር ከፍሎ በረጂም ዘመን የትግል ታሪከችን መዝገብ ዉስጥ የጫራት አብሪ ኮከብ ናት። አዎ! ግንቦት ሰባት የዲሞክራሲ ትግላችን  የከተባት ግዙፍ ክታብ ናት። ግንቦት ሰባት የ1940ዎቹ ትዉልድ አስቧት፤የ1950ዎቹና 60ዎቹ ትዉልድ አርግዟት የ1970ዎቹና 80ዎቹ ትዉልድ አምጧት የ1990ዎቹ ትዉልድ በጣር የወለዳት የኢትዮጵያ ህዝብ የበኩር ልጅ ናት። የኢትዮጵያ ሀዝብ ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓም በታሪካችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ያደረገዉ ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ የዘመናት የነፃነትና የዲሞክራሲ ረሀቡ ዉጤት፤የአርቆ ማስተዋሉ ምልክት፤ወይም ከዉስጥ ሆዱ የመነጨ የፍትህ፤ የነፃነትና የእኩልነት ፍላጎት ዉጤት ነዉ እንጂ የመላምት ታሪክ ቱልቱላዎች ሹክ ሊሉን እንደሚፈልጉት የወያኔ በጎ ፈቃድ ገጸበረከት አይደለም። ግንቦት ሰባት የአዋቂዉ መሳሳብ፤ የሀፃናት መተሳሰብ፤የምሁሩ መናበብና የወጣቱ መተሳሰብ “ቱሉፎርሳ” ብሎ ከዘረኞች ጓዳ በገመድ ጎትቶ እዉን ያደረጋት የዲሞክራሲ ትግላችን ተምሳሌት የሆነች ቀን ናት።

ግንቦት ሰባት እዉን እንድትሆን አያሌ ኢትዮጵያዉያን የህይወት፤ የአካልና የንብረት መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ አያሌ ቁጥራቸዉ በዉል የማይታወቅ ዜጎች ታስዋል፤ ተድብድበዋል ወይም ከአገር ተስድደዋል። “ዲሞክራሲ ካለገደብ አሁኑኑ” ብሎ የጮኸዉ የ1970ዎቹ ወጣት በደርግ የቀይ ሽብር ወንጀሎኞች ካለርህራሄ ተጨፍጭፏል፤ ምሁሩ ካለፍርድ ተገድሏል፤ ወታደሩ ተረሽኗል አንዲሁም ብዙ ቤተሰብ ያለ አባትና እናት ተበትኖ ቀርቷል።  ወርሃ ግንቦት በተለይ ግንቦት ሰባት እነዚህን ሁሉ ጀግኖች የምናስታዉስባት ቀን ናት።  ግንቦት ሰባት በየአመቱ ስትመጣ ከምናስታዉሳቸዉ የቅርብ ግዜ ዉድ ሰማእቶቻችን ዉስጥ አንዱ ህጻን ነቢዩ ኃይሌ ነዉ።
ግንቦት ብዙ የሚተረክ ታሪክ፤የሚወሳ ወግና የሚነገር ገድል ያላት ወር ናት። የግንቦትን ጉድና ገድል አዉርተን እንጨርስ ብንል እየመሸ ይነጋብናል እንጂ የግንቦት ወግ ተነግሮ አያልቅም። ስለሆነም ዛሬ የምናወራችሁ ተነግሮ የማያልቀዉን የግንቦትን ታረክ ሳይሆን እቺ ጉደኛ ወር ካፈራቻቸዉ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ጀግኖቻችን ዉስጥ የአንዱን ሰማእት ታሪክ ነዉ። ለወትሮዉ የጀግኖቻችን ገድል ሲነገር ጀግናዉ ደጃዝማች ባልቻ፤ ወጣት ጀግኖቹ ዋለለኝ መኮንንና ማርታ መብርሀቱ፤ የሴት ጀግኖቹ ሸዋረገድ ሐይሌና እቴጌ ጣይቱ እየተባለ ነበር። ዛሬ የምናቀርብላችሁ የግንቦት ሰማእት ግን ደጃዝማችም፤ጎልማሳም፤ ወጣትም አይደለም። ህፃን ነቢዩ ሐይሌ ይባላል። ህፃኑ ጀግና ነቢዩ ሐይሌ እሱ ለራሱ በሚገባ ቀምሶ ያላጣጣመዉን የለጋ ህይወቱን ጣፋጭ መዐዛ እኛ ቋሚዎቹ እየሸተተን እንዲኖር የህፃንነት ለስላሳ ደረቱ በአግዓዚ አዉሬዎች ጥይት ተበጣጥሶ ህይወቱ ያለፈና የታሪካችን ምእራፍ አንዱ አካል የሆነ ህጻን ሰማእት  ሲሆን በዛሬው ትረካችን በዚያን ወቅት ብሩህ ተስፋ ሰንቆ ይጠባበቅ የነበረ የህጻን ነቢዩ የእድሜ አቻ የትናንቱ ለጋ ህጻን የዛሬው የነጻነት አርበኛ ተስፋን የክተት ጥሪ ይዳስሳል።
ግንቦት 6 1997 ዓም ዕለቱ ቅዳሜ ነበር። ቅዳሜ የሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ነዉ። ሆኖም የዚያን ጊዜው ህፃን ተስፋ ቅዳሜን እንደ ሳምንቱ መጨረሻ ቀን አይደለም የሚመለከታት፤ ለተስፋ ቅዳሜ የእረፍቱ የመጀመሪያ ቀን ናት። ተስፋ አባትና እናቱ ኑሯቸዉ ሩጫ ነዉ፤ በአንድ በኩል አባቱ የተቀደደ ለመድፈን በሌላ በኩል ደግሞ እናቱ የተደፈነ ለመክፈት ጎንበስ ቀና እንዳሉ ነዉ የሚዉሉት፤ ስለሆነም ማታ ቤት ሲገቡ ሁለቱም አልጋቸዉ ላይ የሚወጡት በግዜ ነዉ። ተስፋ ግን ወላጆቹ ቴሌቭዢኑን ዝጋ ብለዉት እሱን ሳያስተኙ እነሱ እንደማይተኙ ያዉቃልና እቺን በግዜ መተኛት የሚሏት ነገር አይወዳትም፤ በተለይ አርብ ማታ። በ1997 ዓም በተለይም ከገናዉ ወር ከታህሳስ ጀምሮ ነቢዩ ቤታቸዉ ዉስጥ አንዳንድ ለዉጦችን መመልከት ጀምሯል። ለወትሮዉ በግዜ አልጋቸዉ ላይ የሚወጡት ወላጆቹ ትተዉት የነበረዉ ቴሌቭዢን ፊት መደርደር ጀምረዋል። ተስፋ የወላጆቹን መለወጥ ቢወድደዉም ምክንያቱን አያዉቀዉምና ግራ ግብት ብሎታል። አንዴ ከወላጆቹ ጋር ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥን ሲመለከት ከተቀመጠበት ብድግ ብሎ እናቱን ያቅፋቻዉና ምነዉ አንቺና አባዬ አለወትሯችሁ ቴሌቪዥን ማዘዉተር ጀመራችሁ ብሎ ይጠይቃቸዋል። ትምሀርት ቤት አይነግሯችሁም እንዴ! ዘንድሮኮ ትልቅ ምርጫ አለ ይሉታል እናቱ እጁን ይዘዉ ወደ ጉያቸዉ እየሳቡት። ት/ቤት ስልምርጫዉ በየቀኑ ነዉ የሚነግሩን ግን ምርጫዉንና ቴሌቪዥኑን ምን አገናኛቸዉ ይላቸዋል ፊቱን ወዳእናቱ አዙሮ አይን አይናቸዉን እየተመለከተ። አይ ልጄ! ቴሌቪዥን ላይ የምናየዉ ፉክክር፤እሰጥ አገባ፤ ሽሙጥ፤ ጉንተላና እንተ ትብስ አንተ ትብስ ክርክር ዘንድሮ የድፍን አበሻን ልብ ሰቅዞ ይዞታል። ይህ ምርጫ ደግሞ የዋዛ እንዳይመስልህ፤ የወያኔን የመጨረሻና የኢትዮጵያን ትንሳኤ መጀመሪያ የሚያበሰር ምርጫ ነዉ።ደግሞም ከእኔና ከአባትህ በላይ ይህ ምርጫ የሚጠቅመዉ አንተን ነዉ ብለዉ እናቱ ንግግራቸዉን ሳይጨርሱ አባትየዉ ቀበል ያደርጉና . . . . አየህ ተስፋ ተቃዋሚዎች አሸንፈዉ ስልጣን ከያዙ ከአሁን በኋላ አገራችንን የሚመራት ጠመንጃ የተሸከመ ሀይለኛ ሳይሆን ህዝብ በችሎታዉና በባህሪዩ የመረጠዉ ዜጋ ብቻ ስለሚሆን እንተም እድገትህ አገር ከመምራት ጋር የተያያዘ ነዉ ብለዉ ወደ መኝታ ክፍላቸዉ ገቡ።
ተስፋ አልጋዉ ላይ ወጥቶ አይኑን እየጨፈነ ለመተኛት ቢሞክርም ቡና ሲጠጡ እንደዋሉ ባልቴት እንቅልፍ በአይኑ አልዞር አለ።  ብንን ባለ ቁጥር አሁንም አሁንም ፊቱ ላይ እየመጣ የሚደቀንበት አባቱ “እንተም እድገትህ አገር ከመምራት ጋር የተያያዘ ነዉ” ብለዉ የተናገሩት ንግግር ነዉ።  እኔም ኢትዮጵያን መምራት እችላለሁ እንዴ . . . . ብሎ ተስፋ እራሱን ጠየቀ። በአባቱ ንግግር ግራ ተጋብቶ ወይም የልጅ ነገር ሆኖበት አልነበረም ተስፋ ይህንን ጥያቄ የጠየቀዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ስልጣን የባለጠመንጃ ነዉና ተስፋ እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ህጻን የአገር መሪ የመሆን ህልም ከምኞት ዝርዝሩ ዉስጥ የለም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫዉን ካሸነፉ ግን ከዚህ በፊት ያልተመኘዉንና እሆናለሁ ብሎ ያላሰበዉን ማሰብና መመኘት ይችላል። አዎ! ተቃዋሚዎች ካሸነፉ ህፃን ተስፋ አድጎ አገር መምራት ይችላል።  ብዙ ተንቆራጠጠ፤ አሰበ፤ አለመ. . . . ይበልጥ ባሰበና ባለመ ቁጥር “መሪ መሆን እችላለሁ” የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ መጣበትና የልጅነት አንጎሉ ይህንን ትልቅ ሃሳብ ማስተናገድ አቃተዉ፤ እሱም ቢሆን እዉነትም አንድ ፍሬ ልጅ ነዉና እንቅልፍ ይዞት ጭልጥ አለ። ሲነቃ ወላጆቹ እቤት ዉስጥ የሉም፤ ዬት እንደሄዱ ስለሚያዉቅ ተመልሶ ተኛ። ቀኑ ግንቦት ሰባት 1997 ዓም ነበር።
ተስፋ ከእንቅልፉ ተነስቶ የግድግዳዉን ሰዐት ሲመለከት የምሳ ሰዐት አልፏል . . . . .  .አይመጡም እንዴ አለ ተስፋ መዘግየታቸዉ አስጨንቆት። ተስፋ ተቃዋሚዎች አሸነፉ ሲባል ለመስማት ቸኩሏል፤ ደግሞም የልጅ ነገር ሁሉንም በአንዴ ነዉና  እናቱና አባቱ ሲመጡ ማን እንዳሸነፈ የሚነግሩት መስሎታል። አሁንም ቀና ብሎ ሰዐቱን ሲመለከት ከቀኑ ስምንት ሰዐት አልፏል። ወላጆቹ በቆዩ ቁጥር ተቃዋሚዎች የተሸነፉ እየመሰለዉ  መቁነጥነጥ ጀመረ። የወያኔ ማሸነፍ የወደፊት እድሉን እንደሚያጨልም በዉል የተረዳዉ ተስፋ ሰዐቱ በጨመረ ቁጥር የእሱም ስጋትና ጭንቀት ጨመረ።
የቤታቸው ሰዐት ዘጠኝ ሰዐት ሆኖ ሲደዉል፤ ተስፋ ከእንቅልፉ ሲነቃና የቤቱ በር ሲከፈት እኩል ሆነ።  ተስፋ ከተጋደመበት ፎቴ ተነስቶ “ማን አሸነፈ” እያለ ወደ በሩ ሲሮጥ ለግማሽ ቀን ቤቱን ሞልቶት የነበረዉ ዝምታ ተገፈፈ። አይ ልጄ! የኛ ስራኮ መምረጥ ብቻ ነዉ፤ ህዝብ የሰጠዉን ድምጽ ቆጥሮ ዉጤቱን የሚነግረን መንግስት ነዉ አሉት እናቱ እግራቸዉ ወደ ኩሺናዉ እየቀደመ። እንዴ!  መንግስት ድምጽ ቆጥሮማ እንዴት ተቃዋሚዎች ያሸንፋሉ አለ እናቱን ተከትሎ ወደ ኩሺናዉ እየገባ። እናቱና አባቱ አይናቸዉ ሳያስቡት ገጠመና መልሱን በማያዉቁት የልጃቸዉ ጥያቄ ተገረሙ። የተስፋ እናት ባለሙያ ናቸዉ፤ ይሀንን ደግሞ መንደሩ ሁሉ ያዉቀዋል። ኩሽና ዉስጥ እንደገቡ የጀመሩት ጥብስ ቤቱን አዉዶታል በእርግጥም የጥብሱ ሽታ እንኳን የተራበ ሆድ በልቶ የጠገበን አንጀትም ያስጎመጃል፤ ልጃቸዉ ተስፋ ግን የራበዉ ምግብ ሳይሆን የምርጫዉን ዉጤት ማወቅ ነበረና ሁሉንም ነገር ትቶ ከቴሌቪዥኑ ጋር ተፋጥጦ ቁጭ አለ።
ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 1997 ዓም ረፋዱ ላይ የአዲስ አበባ አየር ሞገዶች ቅንጅት አዲስ አበባን አሸነፈ በሚል ድምጽ ተሞሉ። ተስፋ ቤቱ አልበቃ አለዉ፤ እሱም ሆነ ወላጆቹ ምኞታቸዉ የደረሰ መሰላቸዉና ያንን ከሆድ ዉስጥ ተፈንቅሎ የሚወጣ እዉነተኛ ደስታና ፈገግታ አይቶት የማያዉቀዉን ቤት ሠርግና ምላሽ አስመሰሉት።ተስፋ ኢትዮጵያ የምትመራዉ እናትና አባቱ በመረጡት ፓርቲ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አባቱ የነገሩት የእሱ የራሱ ብሩህ ዘመን መምጣት ወለል ብሎ ታየዉና የልጅነት ፊቱ በደስታ ተሞላ። ሆኖም አየሩን የሞላዉ ተቃዋሚዎች አዲስ አበባም አሸነፉ የሚል ዜና ነዉ እንጂ ምርጫዉን አሸነፉ የሚል ስላልነበረ እሱም፤ ወላጆቹም ሆኑ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሸንፈዉ ወያኔ ተወገደ የሚለዉን ዜና እስኪሰሙ ድረስ ልባቸዉ አላርፍ አለ።
ተስፋ ምድር ላይ ከኖረባቸዉ ጥቂት አመታት ይልቅ ሰኞ ግንቦት ስምንት ማክሰኞና ግንቦት ዘጠኝ ረቡዕ ግንቦት አስር እንደ ገመድ ረዘሙበት። በየደቂቃዉ ከአባቱ፤ ከእናቱና ከመንደሩ ሰዉ ሹክ እያለ ጆሮዉ ዉስጥ የሚገባዉ ዜና “ቅንጅት አሸነፈ” ሲል ፊቱ ላይ የተደቀነዉ ቴሌቪዥን ደግሞ ኢህአዴግ አሸነፈ ይላል። ቅንጅት አሸነፈ ሲባል ፊቱ በደስታ ይፈለቀለቃል፤ ኢህአዴግ አሸነፈ ሲባል ደግሞ ያንኑ ያክል ሰዉነቱ ይፈርሳል። ሁለቱም እንደማያሸኝፉ ያዉቃልና ትክክለኛዉን አሸኛፊ አስከሚያዉቅ ድረስ አንቅልፍ አልወስድህ አለዉ።
ሀሙስ ግንቦት 11 ቀን ጧት ረፋዱ ላይ ተስፋ ከተቀመጠበት ተነስቶ ቴሌቪዥኑን ዘጋዉና … አላልኩሽም . . .  እማይ. . . . አላልኩሽም እያለ ከሳሎን ወጥቶ ወደ ኩሽና ገባ። እናቱ ልጃቸዉ ተስፋ ድምጽ ሰጥተዉ የመጡ ቀን የተናገራቸዉንም ሆነ አሁንም ሊነግራቸዉ የሚፈልገዉን ያዉቃሉና እሳቸዉም ልክ እንደ ልጃቸዉ በቅንጅት ያበበዉ ተስፋቸዉ በወያኔ ሲጠወልግ ታያቸዉ። ከሰዐታት በፊት ሙሉ አካላቸዉ በተስፋ ተሞልቶ የነበረዉ እናትና ልጅ የጫነዉን ጭነት ገልብጦ እንደሚመለስ ገልባጭ መኪና ባዶ ሆኑ። ተስፋ ጆሮዉን ከፍቶ ባዳመጠ ቁጥር “ድዉ ድዉ” የሚለዉ የራሱ ልብ ትርታ አስደነገጠዉና ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደከዳ እሱም ልቡ የሚከዳዉ መሰሎት ግራ ደረቱን በሁለት እጆቹ ይዞ ቆመ።
ግንቦት፤ ሰኔና ሐምሌ እያለ አመቱ እድሜዉ እየጨመረ ሲያረጅ የተስፋና የጓደኞቹ ከቅንጅት ማበብ ጋር አብቦ የነበረዉ ተስፋቸው ጨለመ። እነሱ ባያረጁም ተስፋቸዉና ያለሙት ህልም ዘመን እንደቆጠረ ሰዉ አረጀ። ተስፋ የቆረጡ ጋቢያቸዉን እየለበሱ እቤታቸዉ ተቀመጡ፤ የትግሉ ዉስብስበብነት የገባቸዉ ግን ወያኔን በሚችሉት ዘርፍ ሁሉ ለመታገል ታጥቀዉ ተነሱ። “የህዘብ ድምጽ ይከበር” የሚል ህዝባዊ ጥያቄና ጩኸት አዲስ አበባንና የክልል ከተሞችን አናወጠ። ህዝብና ወያኔ መርጠኸኛል. . . . የለም አልመርጥኩህም ብለዉ ሙግት ዉስጥ ገቡ። አዲስ አበባ ቀዉጢ ሆነች። ህዝብ ለመጮህ ድምጹን አግአዚ ልሳን ለመዝጋት መትረየሱን ተሸክሞ በየአደባባዩ ተፋጠጡ። የመለስ ዜናዊ “በሏቸዉ” የሚል የእብሪትና የበቀል ትዕዛዝ አዲስ አበባን አሸበራት፤ የአዲስ አበባ ሰማይ በሞት ዳመና ተሸፈነ። ከግራዚያኒና ከደርግ እልቂት አገግማ የሰነበተችዉ አዲስ አበባ እንደገና አገረሸባት። ስንት ልግደል እያለ እንዳበደ ዉሻ የሚክለፈለፈዉ አግአዚ በሬሳ ላይ እሬሳ ከመረ። እንደ ሞገስ አስገዶም፤ አብርሃም ደቦጭና እንደ ብዙዎቹ የ1970ዎቹ ሰማዕታት የህፃን ተስፋ ያኢድሜ ጓደኛ የነበረው ህጻን ነቢዩም ያልጠገበዉን ጨቅላ ህይወት ገብሮ አንቀላፋ። ተቃዊሚዎች አሸንፈዉ ዬኔንም የወደፊት የአገር መሪ የመሆን በር ይከፈታሉ ብሎ ሲጠባበቅ የነበረዉ የዚያን ጊዜው ህጻን ተስፋ በፋሺስቶች በግፍ የተጨፈጨፉትን ወገኖቹን በተለይም ምንም በማያውቀው የእድሜ ጓደኛው ህጻን ነቢዩ ኃይሌ አሰቃቂ አገዳደል ስሜቱ በመነካቱ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ ነጻነት ሲል ከአረመኔው የአግአዚ ሓይል ጋር ፊት ለፊት ለመተናነቅና ለመጋፈጥ ወሰነ።አዎ! በ1983 ዓም መለስ ዜናዊ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ዉስጥ ግድያ አብቅቷል ብሎ ከተናገረ ከአመታት በኋላ የተወለደዉ ህፃን ነቢዩ ኃይሌ በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ተገደለ።
ያቺ የቀን ጎዶሎ መጥታ ከሄደች ከሰባት አመት ከመንፈቅ በኋላ ዛሬም ልጆቿን በጠራራ ፀሐይ የተቀማችዉ አዲስ አበባ የፍትህ ያለህ እያለች ነዉ። ልጆቻቸዉ እንደወጡ የቀሩባቸዉ ወላጆች ፊት ዛሬም በእምባ እንደታጠበ ነዉ። ተስፋዉ እንደ መብረቅ ብልጭ ብሎ ድርግም ያለበት የኢትዮጵያ ህዝብም የአግአዚ ጭካኔ ወዲህ ቢለዉ ወድያ ትርጉም አልሰጥህ ብሎት ዛሬም በሀዘን እንደተዋጠ ነዉ። እኛንና ዉድ አገራቸዉን ብለዉ ደረታቸዉ በአግአዚ አልሞ ተኳሾች የተበሳዉ ነቢዩና ጓደኞቹም ከላይ ከሰማይ “በደል ይረሳል…..በደል የለመዳል”  ብለዉ መጠየቅ ከጀመሩ እነሆ ሰባት አመታት አለፉ።  ወገን ለመሆኑ በደል ይረሳል ወይስ ይለመዳል? ህፃኑ ሰማእት ነቢዩ ኃይሌ በደል ስንለምድና በደል ስንረሳ እያየ ምን ይለን ይሆን . . . . እሱማ በመንፈስ እንዲህ ይለናል::

በደል እንዴት ይረሳል   እንዴት ይለመዳል በደል
የኔ የነቢዩ የህጻኑ ደረት በአግአዚ ብረት ሰተረተር፤
ወንድ ሴት ሳይለይ ህዝብ በታንክ ሲገፈተር።

እኮ ንገሩኝ በደል እንዴት ይለመዳል
እናቶች በአረር ሽታ ሲታጠኑ
መንገዶች በወገን ደም ሲታጠቡ።

እባካችሁ አታስጩሁኝ መልሱልኝ ጥያቄዬን
አትብሉት አደራዬን።

በደል እንዴት ይረሳል ልጅ እናቱ ፊት ተረሽኖ
ነብስ ያላወቀ ህፃን እንደ ዲያቢሎስ ተኮንኖ።

በሉኮ ንገሩኝ አናግሩኝ ወይ ላናግራችሁ በተዘጋዉ አንደበቴ
ጎንበስ ብዬ ልማጸናችሁ በህጻንነት በተቀማዉ ህይወቴ።

እዉነት በደል ይረሳል? በይኮ ንገሪኝ ኢትዮጵያ በደል ይለመዳል?
በደል እንዴት ይለመዳል ከጎናችን ሰዉ ሲገደል፤
በደል እንዴት ይረሳል አበሻ ስጋዉ አንደ ነዶ ሲነደል።

አረ ንገሩኝ በደል እንዴት ይረሳል ሴት ልጅ ታስራ ጅማቷ ሲወጠር ፤
ወንድ የፊጥኝ ታስሮ ዉስጥ እግሩ ሰተለተል።

ስማኝ ወገኔ በደል እንዴት ይረሳል እታለም ታስራ ጡቷ ሲቆነጠጥ
ወንድም ጋሻ ታስሮ ብልቱ ሲጎተት።

በልኮ ንገረኝ አንተ ያገሬ ልጅ በደል እንዴት ይለመዳል፤
እህትህ ቁልቁል ስትሰቀል ወንድምህ ወፌይላላ ተሰቅሎ ሲቀቀል፤
እኮ ንገረኝ በደል እንዴት ይረሳል ህዝብ በጅምላ ሲነቀል፤
ወያኔ ወገንህን በዉሸት ቂምበቀል ሲበቀል።

ለመድኩት አልሽኝ እታለም እናቴ ፊት መገደሌን
አንተስ ወንድምዬ ረሳሁት አልከኝ አገዳደሌን
አደባባይ ላይ በጥይት መደብደቤን።

ረሳችሁኝ ወይ እኔን ነቢዩን   ነብስ ሳላዉቅ ጥይት የማዉቅ ምግብ ሳልጠግብ ባሩድ የቃምኩ።
በሉ አሺ እኔንስ ተዉኝ     አንድ ፍሬ ልጅ ነዉ አያዉቅም ብላቸሁ እርሱኝ

ግን . . . . ግን ረሳችሁት ወይ አሰፋ ማሩን
ወገኔን ባለ ስጋዉ ማረሩን።

ተረሳችሁ ወይ የአዋሳ አበሳ . . .
ሲዳማ “ሲዳማ” ልሁን ባለ እራሱን በጥይት ሲበሳ።

ለመዳችሁ ወይ የአኝዋክን እልቂት፤   መሬቴን ባለ ጋምቤላ ሲገፋ   ጎጆዉ ተቃጥሎ እሱ ሲደፋ።

አረ አንዴት . . . .  እኮ እንዴት ይረሳል የሽብሬ ሞት. . . .  ወንድሞቼን አትንኩ ባለች እሷ እንደወጣች የቀረች።
ስንቱን ጠርቼ ልጨርሰዉ    ማንን ጠቅሼ ማንን ልተዉ።
ምስክር ከሆነ ችግራቸሁ
ቃል ብቻ ከሆነ እምነታችሁ …..
ለቃልማ. . . . .ለቃልማ  እኔ አልበቃም ወይ እኔ ነቢዩ የሁሉም ታናሽ ጨቅላዉ ህፃኑ።
በሏ ንገሩኝ ምን ይበጃል ከኔ ሌላ ምስክር፤
እኮ ምን ይባላል እኔዉ ሞቼ ከኔ ጋር ክርክር . . . .
ከተሰዋ ሰዉ ጋር ድርድር ።
ማን አለና ህይወቱን የሰጠ እማኝ ፤
እስኪ ቅረበኝ ወገኔ እባክህ ስማኝ  . . . .
ማን ይምጣልህ ከነቢዩ በላይ እማኝ።
እኔ አይደለሁ ወይ የህጻን ሰማእት ተምሳሌት
አልደፈርም ባይ ኢትዮጵያዊነት።
እኮ እንዴት ይረሱ አግአዚን የተጋፈጡት
ባርነትን እምቢኝ ብለው ደረታቸውን ለፋሺስቶች ጥይት የሰጡት።

በሉ እንገዲህ ስሙኝ በደል አትርሱ በደል አትልመዱ . . . . .
ሞቴን በሞታችሁ ዉለዱ፤ የሞትኩለትን አርማ አንሱ  መስዋዕትነቴን አትርሱ።
በተለይ . . . . .  በተለይ በደል አትርሱ  . . .

እንዴት ይረሳል በደል
እንዴት ይለመዳል ሰዉ ሲገደል።
አረ አንዴት ይረሳል በደል ወጣት እንዳዉሬ ታድኖ ሲታሰር
ኮረዳ ተሰብስቦ ሲደፈር።
በሉኮ ንገሩኝ በደል እንዴት ይረሳል አበሻ እንደጎመን ሲቀቀል
ወገን ባደባባይ በጥይት ሲቃጠል ።

እባካችሁ ንገሩኝ በደል እንዴት ይረሳል አግአዚ ገድሎ ሲወደስ
በደል እንዴት ይለመዳል የሰዉ ልጅ ጥርስ በሽቦ ሲነቀስ

ንጹህ ዜጋ በየመንገዱ ሞቶ ሲለቀስ…….
እኮ እንዴት ይረሳል በደል ወጣት እንደ ምጣድ ሲታመስ
ሀይማኖታችን ሲረክስ አንድነታችን ሲፈርስ።

ስሙኝ . . . . . ስሙኝ …  ወገኖቼ እንደ እባብ ቆዳ ጀርባችሁ የሚላጥ
እንደ ላም ወተት ወዛችሁ የሚናጥ፣

ወያኔ . . . . . ወያኔ . . . .እንደ ብርቱኳን ልጦ ግጦ፣
ወዝ ላባችሁንን መጥጦ፣
ሊዉጣችሁ ነዉ አላምጦ
መተካካት እያለ ትብስን በትባስ ለዉጦ።

ይሉናል ከሰማይ ቤት ፡
ቁልቁል እያዩን በትዝብት።

እኔ ተስፋ ግን ጥሪያቸውን ሰምቻለሁ ፡
በልጅነት እድሜዬ የተቀማሁትን ብሩህ ተስፋ
እውን ላደርግ በሞቴ ፍትህን ለማስፈን ቆርጫለሁ፡

ለሰንደቄ ክብር ለኢትዮጵያ አንድነት
ለህዝቧ እኩልነት
ህይወቴን ልገብር ጉዞ ጀምሬአለሁ ፡
ህዝባዊ ሀይሉን ተቀላቅያለሁ።

ወንድሜ ምን እንዳይቀር በቃህ ተነስ፣
እህቴ ምን እንዳይቀር በቃሽ ተነሽ፣
እስር አለ ታሰሩ፡ ሞትም አለ ሙቱ፣
ከሃዲስ ይሞት የለ ክህደት ሞልቶ ባንደበቱ፣
የእዉነት ሞት ግን
ህይወት ነዉ እስኪ ለህይወት ሙቱ . . .እስኪ ለህይወት ሙቱ!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar