mandag 19. august 2013

የሽብርተኝነት አዋጁ፤ የጠሉትን መምቻ?


ተመስገን ደሳለኝ
ኢህአዴግ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት በስራ ላይ ካዋላቸው አዋጆች መካከል የ‹‹ፀረ-ሽብር ህጉ››ን ያህል
ያጨቃጨቀ የለም ቢባል ከእውነቱ ብዙም አልራቀም፡፡ በርግጥ ከተቃውሞ አቅራቢው አብዛኛው በደፈናው ‹‹ህጉ
አያስፈልግም›› የሚል አልነበረም፡፡ ህጉ ‹‹ሽብርተኝነት››ን የገለፀበት መንገድና አንዳንድ አንቀፆቹ ለትርጉም አሻሚ
በመሆናቸው ከስርዓቱ ባህሪ አኳያ ለፖለቲካ ጥቅም የሚውሉበት ዕድል መኖሩ አይቀሬ ነው የሚል ስጋት ነበር፡፡
የህግ ረቂቁ ለተወሰኑ የምዕራብ ሀገራት ዲፕሎማቶች ይመለከቱት ዘንድ በተሰጣቸው ጊዜም ተመሳሳይ ስጋት
ሲያነሱ፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ደግሞ ‹‹ሽብርተኝነት››ን ከየትኛውም የአለማችን ሀገር እጅግ በሰፋ መልኩ ስለሚተረጉም መሰረታዊ
መብቶችን ሊዳምጥ እንደሚችል ጠቅሶ መጽደቁን ለመቃወም ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡

በጊዜው የግንባሩን ለዘብተኛ አመራሮች ጨምሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ አለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ተቋማት፣ የምዕራብ ሀገራት
ዲፕሎማቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራኖች… ይህ ህግ ፀድቆ በስራ ላይ ቢውል የፖለቲካ መብቶችን እና የዜጐችን ነፃነት ከመገደብ አልፎ
ስርዓቱ በአይኑ መዓት የሚያያቸውን ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች መምቻ (ማጥቂያ) ሊያደርገው ይችላል በሚል ጥርጣሬ ቢያጣጥሉትም
በነሐሴ 22/2001 ዓ.ም በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከመውጣት ሊያስቆሙት አልቻሉም፡፡
…ህጉ ስራ ላይ ከዋለ ሶስት አመት ሞቶታል፡፡ በዚህ ፅሁፍም ህጉ ከመተግበሩ አስቀድሞ የተነሱ ስጋቶች እውን መሆናቸውን እና በተግባር
ከታየው የህጉ ዓላማ ጋር አሰናስዬ ለማየት እሞክራለሁ፡፡
እንደ መግቢያ
የአፍሪካ ቀንድ ከተፈጥሮአዊው ጂኦ-ፖለቲካ አኳያ እና በአካባቢው ያሉ ሀገራትም የፈራረሰችውን ሶማሊያን ጨምሮ ለጽንፈኛ የእስልምና
እንቅስቃሴ የተጋለጡ መሆናቸው ለሽብርተኝነት የተመቻቸ ሜዳን እንዲፈጥር ማድረጉ አያከራክርም፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአሸባሪዎች ቀጥታ ጥቃት የታየው የቀድሞውን የግብፅ ፕሬዘዳንት ሆስኒ ሙባረክን ዒላማው ያደረገ አንድ
ቡድን በ1986 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የግድያ ሙከራ ባደረገበት ጊዜ ነበር፤ ቀጥሎ ደግሞ በ1991 ዓ.ም. በትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትሩ
አብዱልመጅድ ሁሴን ላይ የተሞከረው ግድያ የሽብርተኝነት ጅማሮዎች ሆነዋል፡፡ ይህ ከሆነ ጥቂት ዓመታት ዘግይቶ በተመሳሳይ ሰዓት
በግዮን እና በዋቢ ሸበሌ ሆቴሎች የደረሰው የቦንብ ጥቃት፣ መሀል ፒያሳ ይገኝ በነበረው ትግራይ ሆቴልን የመታው ፍንዳታ የሽብር
አደጋው በቅርብ ርቀት ለመኖሩ አመላካች ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ስርዓቱ ድርጊቱን ለመከላከል በስራ ላይ ከዋሉት ህጎች ተጨማሪ አዲስ አዋጅ
‹‹ያስፈልገኛል›› የሚል ድምዳሜ ላይ አልደረሰም፤ ወይም የመፈለግ ምልክት አልታየበትም፡፡
በግልባጩ ከምርጫ 97 በኋላ የሽብር ጥቃቱ ዒላማውን ከባለስልጣናት እና ሆቴሎች ወደ ህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶች (ሚኒባስ
ታክሲ እና የከተማ አውቶብስ) ያሸጋገረ መሰለ፡፡ በአንዳንድ አካባቢም የተጠመዱ ፈንጂዎች በደህንነት ሰራተኞች ‹‹ቅድመ ንቃት››
የመምከናቸው ዜና የቴሌቪዥን ርዕሰ ጉዳይ እንደነበረ ይታወሳል (በነገራችን ላይ መንግስት ከጥቂት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ሶስት ሰዎች
የገደለውን የፈንጂ ጥቃት የፈፀሙት የኦነግ አባላት ናቸው ቢልም፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጉዳይ ፈፃሚ የነበሩት ቪክ ሀድልስተን
የኢምባሲ ምንጫቸውን ጠቅሰው ወደስቴት ዲፓርትመንት በላኩት ዘገባ ፈንጆቹን ያጠመደው የኢትዮጵያ መንግስት እንደነበረ ዊክሊክስ
መዘገቡ ይታወሳል) አሳዛኙ ጉዳይ የድርጊቱ ትርፍና ኪሳራ የተወራረደው አጀንዳውን (ጥቃቱን መሰንዘር ያስፈለገበት ምክንያት) በጭራሽ
የማያውቁትን እና የማይመለከታቸው በርካታ ንፁሃንን የህይወት ዋጋ በማስከፈል መሆኑ ነበር፡፡
በየትኛውም ሀገር ህዝብን በማሸበር ዓላማቸውን ለማስፈፀም የሚቋቋሙ ቡድኖች የመጀመሪያ ዒላማ የሚያደርጉት ሰላማዊ ዜጎችን ነው፤
የዚህ ምክንያቱ ፍርሃትን ካላነገሱ በቀር ኃይል ያለው ቡድን ፍላጎታቸውን ሊያሟላ ወይም በትይዩ ተቀምጦ ለመደራደር ፍቃደኛ ሊሆን
ባለመቻሉ ይመስለኛል (በቅርቡ የባራክ ኦባማ አስተዳደር በአፍጋኒስታን ህጋዊ ስልጣን የያዘውን መንግስት አውላላ ሜዳ ላይ አስቀምጦ
ለዓመታት በአስቸጋሪው ቶራ ቦራ ተራራ ሳይቀር ዘመን ባፈራው ቴክኖሎጂ ሲያሳድደው የነበረው ታሊባንን ዕውቅና ከመስጠት አልፎ
ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው መግለፁ አንዱ ማሳያ ነው፡፡)
በኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሱት የሽብር ድርጊቶች ቢፈፀሙም በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ‹‹አሸባሪ›› ወይም ‹‹ሽብርተኝነት›› የተባሉ ቃላቶች
የተለመዱ አልነበሩም፤ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትና ታላቋ አሜሪካንን የሚመለከት ብቻ ተደርጎ የተተወ ነበር-የኢትዮጵያ መከላከያ
ሰራዊት ፊቱን የጦር አበጋዞች በታትነው /ከፋፍለው/ ወደ ሚያስተዳድሯት ሶማሊያ የሚመልስበት ምክንያት እስኪያገኝ ድረስ፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar