torsdag 25. juli 2013

በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተነሳው ብጥብጥ እየተካረረ ነው

- ፖሊስ ደቀ መዛሙርቱን ከኮሌጁ ግቢ እንዲያስወጣ የፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት ጠየቀ፤ የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ውሳኔውን በጽኑ ተቃውመዋል
- ኮሌጁ እንዲዘጋ የውሳኔ መነሻ የሰጠው ከአቡነ ጢሞቴዎስ ተጽዕኖ ያልወጣው የኮሌጁ ቦርድ ነው
- የኮሌጁ ምግብ ቤት አገልግሎቱን እንዲያቆም በመታዘዙ ደቀ መዛሙርቱ ምሳና ራት ተከልክለው ውለዋል
ሐራ ተዋሕዶ ብሎግ እንደዘገበው
አቤቱታቸውን ለመንግሥት አካላት ያሰሙት ደቀ መዛሙርቱ ‹‹ቅ/ሲኖዶስ እና ምእመናን የከፈቱት ኮሌጁ የሚዘጋው በመቃብራችን ላይ ነው!›› በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል፤ በአስተዳደር ሕንጻው ዙሪያ የሚያደርጉትን ቁጥጥር አጠናክረዋል
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ ለማስገደድ የፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት የፌዴራል ፖሊስ ኀይልን እገዛ መጠየቁ ተገለጸ፡፡
በልዩ ጽ/ቤቱ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ስም ተፈርሞ የወጣውና ለፌዴራል ፖሊስ እንደተጻፈ በተገለጸው ደብዳቤ÷ ልዩ ጽ/ቤቱ የኮሌጁን ደቀ መዛሙርት በሰላም ነሽነት በመወንጀል ኮሌጁ እንዲዘጋ መወሰኑን ያስታወቀ ሲኾን በዚህም መሠረት ፖሊስ ደቀ መዛሙርቱ ኮሌጁን ለቀው የሚወጡበትን ርምጃ እንዲወስድ እገዛ መጠየቁ ታውቋል፡፡
የልዩ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ የተጻፈው በኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ተጽዕኖ ውስጥ እንዳለ የሚነገረውና በደቀ መዛሙርቱ የችግሩ አካል ተደርጎ የሚተቸው የኮሌጁ ቦርድ ኮሌጁ እንዲዘጋ በሰጠው የውሳኔ መነሻ መኾኑ ተነግሯል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በአቡነ ገሪማ የበላይ ሓላፊነት የሚመራው የፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት የቦርዱን መነሻ በመቀበል ኮሌጁ እንዲዘጋ መወሰኑንና ደቀ መዛሙርቱም ግቢውን ለቀው እንዲወጡ መጠየቁን በጽኑ ተቃውመዋል፡፡
ፓትርያሪኩ ኮሌጁን የመዝጋት ሥልጣን እንደሌላቸው የገለጹት የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሓላፊው ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ‹‹በኮሌጁ ላይ ለመወሰን ሙሉ ሥልጣን ያለው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ነው፤›› በማለት በመንበረ ፓትርያሪኩ ስምምነት በተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ የቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ ተግባራዊ እንዲኾን ተሟግተዋል፡፡ ከኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ጋራ የሚስማማው ይኸው የብፁዕነታቸው አቋም ከፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ጋራ በትይዩ እንዳቋማቸውና የከረረ ውዝግብ ውስጥ እንደከተታቸው ተዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ አኳኋን አምስት አባላት የሚገኙበትን አጣሪ ኮሚቴ በተወካዩ አማካይነት በሰብሳቢነት የመራው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት ኮሌጁ እንዲዘጋ ያስተላለፈው ውሳኔ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ኮሚቴው አጣርቶ ያቀረበውና ፓትርያሪኩም እንደተስማሙበት የተመለከተው የመፍትሔ ሐሳብ ተፈጻሚ እንዲኾን መጠየቁ ተሰምቷል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar