onsdag 26. juni 2013

የኢትዮጵያዊያን ትግል – ( ክፍል ሶስት ) digg


የሁለት ደረጃ ትግላችን፤
ሰኔ ፲፰ ቀን ፳ ፻ ፭ ዓመተ ምህረት – June 25, 2013
ከአንዱ ዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ፤ Facebook እና Twitter 
http://nigatu.wordpress.com/
በዚህ ርዕስ በተከታታይ በቀረበው ባሁኑ የሶስተኛው ክፍል፤ በቀጥታና በግልፅ ቋንቋ ምን ማድረግ እንዳለብን አብራራለሁ። በመጨረሻውና አራተኛው ክፍል ደግሞ ከዚህ ወዴት? በሚል መዝጊያን አቀርባለሁ። ኢትዮጵያዊያን አሁን ባለንበት የፖለቲካ ሀቅ፤ ሁለት ደረጃ ያለው ትግል ማድረግ የግድ አለብን። እኒህን በቅደም ተከተል መደረግ ያለባቸው ትግሎች፤ በግልፅ ተረድተንና ተከትለን ካልሄድን፤ ትግላችን የእሬያ ታጥቦ ጭቃነት ነው። እኒህ ትግሎች በፊታችን የተጋረጡ ለመሆናቸውና የግድ ማድረግ ያሉብን ለመሆናቸው፤ ማናችንም ብንሆን ጥርጣሬ የለንም። አንጥረን የለየናቸውና በዚያ ስሌት ያስቀመጥናቸው ለመሆናቸው ግን፤ ጥያቄ አይጠፋም። እንዲያውም ዝብርቅርቅ ያለ ጭጋግ ወጥሮ ይዞናል። ይህን ለማሳየት መጀመሪያ ኢትዮጵያዊያን ያለንበትን ሁኔታ እንመልከት።

ኢትዮጵያዊያንን የማይወክል መንግሥት አዲስ አበባ ላይ ተቀምጧል። ይህ መንግሥት ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ አስቀድሞ፤ ሀገራችንን ከአንድነት ወደ ልዩነት በመንዳት፤ ለርስ በርስ ትልቅልቅ እያዘጋጀን ነው። በውልድ ኢትዮጵያዊ ይሁኑ እንጂ በተግባር ፀረ-ኢትዮጵያዊ ለመሆናቸው መረጃ የሚጠይቀኝ የለም። ግልፅ ነውና! በእርግጥ እስካሁን በተለያዩ ወገኖቻችን መካከል መጠፋፋቱ አልተከሰተም ብዬ አይደለም፤ መጪው መለኪያ የሌለው የከፋ መሆኑን ለመጠቆም ነው። ድህነቱ፣ በበሺታ ማለቁ፣ ያልተመጣጠነ አስተዳደርና እድገት በተለያዩ ቦታዎች መከሰቱና መደልበቱ፣ የአስተዳደር በደል ጣራ መንካቱ፣ የኑሮ ውድነቱ ማሻቀቡ፣ . . . ወዘተ፤ ባጠቃላይ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ መሄዱ የተዘገበ ነው። ይኼን እንደ አስተዳደር ብልጠት የተሞሽረበት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ በዕብሪትና ባለው አቅም እየገፋበት ነው።
በተጓዳኝ የተቃዋሚዎቹን ወገን የተመለከትን እንደሆን ደግሞ፤ አንድ ማዕከል የሌለው፣ አንድ የትግል ራዕይ የሌለው፣ እጅግ በጣም የተበታተነ ክፍል እናያለን። በነዚህ የተለያዩ የተቃዋሚ ወገኖች ውስጥ፤ እጅግ በጣም ቆራጥና ሕይወታቸውን ለወገናቸውና ላገራቸው ለመሥጠት ወደ ኃላ የማይሉ ታጋይ ወጣቶች ሞልተውባቸዋል። የአብዛኛዎቹ የነዚህ ወጣቶች ፍላጎት፤ የኢትዮጵያዊያን ነፃነት፣ የሀገራቸው ብልፅግናና እድገት ብቻ ነው። እነዚህ ወጣቶች፤ ማን ነገ በሕዝቡ ተመርጦ መሪ ይሆናል? ማን ይቸነፋል? የሚሉት በአእምሯቸው ቦታ የላቸውም። በመሪዎቻቸው በኩል የተገላቢጦሽ ነው። አሁንም እነኚህ ወጣቶች በአንድነት ለኢትዮጵያ ለመሠለፍ ዝግጁ ናቸው። መሪዎቻቸው ግን አጥር አበጅተውባቸዋል። የነሱ ድርጅት፣ የነሱ ፍልስፍና፣ እነሱ አጥቂና የበላይ ካልሆኑ፤ ትግሉ አፍንጫውን ይላስ ያሉ ይመስላሉ። እናም “ሌሎቹ ስህተተኞች ናቸው” ብለው ይስብኳቸዋል። ይህ ሊፈርስ የሚችለውና ባንድ ላይ ተሰባስበን ልንታገል የምንችለው፤ የትግሉን ምንነትና መንገድ በአደባባይ ተወያይተንበት ግልፅ ግንዛቤ ስንይዝ ነው። በዚህ ለይስሙላ የተዘረጉት አጥሮች በሙሉ ይፈራርሳሉ። ለዚህም ነው አሁን ካለንበት የፖለቲካ አረንቋ ወጥተን ነገ ትሆን ለምንፈጋት ኢትዮጵያ መንገዱ ሁለት ደረጃ ያለው ትግል ነው የምለው። የተጋዮች በአንድ ወገን መሠለፍ ግዴታ ነው። እነሆ ሁለቱ የትግል ደረጃዎች።
ሁለቱ የትግል ደረጃዎች ምንድን ናቸው?
መልካም። በሁለቱም የትግል ደረጃዎች ውስጥ የአስተሳሰብና የሃሳብ ልዩነቶች አሉ። የሚለያዩበት ቢኖር፤ እንዴት ይስተናገዳሉ በሚባልበት ጊዜ የሚሠጣቸው መፍትሔ ላይ ነው። የመጀመሪያዉን ከመዘርዘሬ በፊት ሁለተኛውን ማስቀደሙ፤ ለግንዛቤ ይቀላልና በሱ ልጀምር።
ሁለተኛው የትግል ደረጃ፤
የሁለተኛው የትግል ደረጃ፤ የእኔ አምራለሁ፣ እኔ አምራለሁ፣ ውድድር ነው። በኔ አምራለሁ አኔ አምራለሁ ውድድር፤ ከፈራጅ ፊት ቀርቦ መልስ መጠበቅ እንጂ፤ እርስ በርስ ማማርን ለማሻሻል ሆነ ለማሳየት ፍጥጫ የለበትም። የሌላውን አለማማር ለማሳደግ ሲሮጡ የራስንም አለማማር ስለሚያባብሱት ሁሉም በዚያ ጎዳና መጓዙን አይወድም። ከጎኑ ያለውን እንዳያምር አደርጋለሁ ብሎ የሚነሳ፤ የራሱ አለማማር ከመጉላቱ ሌላ፤ ያልተነኩት ማማራቸው ወደ ላይ ስለሚወጣ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ይሆናል። እዚህ ላይ አምራለሁ ባዮች የፖለቲካ ድርጅቶች ፈራጅ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ትግሉም የሰላምና የሃሳብ ትግል ነው። እንግዲህ በዚህ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ፤ የርዕዩተ ዓለም ልዩነት በሕዝቡ ፊት እየቀረበ፤ የምንፋረጅበት ነው ማለት ነው። የዴሞክራሲ ትግል ነው። ሕጋዊ ትግል ነው። ሕጉም የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ነው። በሀገሪቱ ያለው መንግሥት ከተወዳዳሪዎቹ የተለዬና ነፃ የሆነ ነው። እናም በመንግሥቱና በወቅቱ የመንግሥቱን በትር በጨበጠው የፖለቲካ ድርጅት መካከል ግልፅ የሆነ ልዩነት አለ። ይህ እንግዲህ የዴሞክራሲያ አሠራር የሠፈነበት ኅብረተሰብ መኖሩን ያሳያል። ይህን አሠራር የሚያራምዱትና የሚጠብቁት፤ ሕገ መንግሥቱ፤ መንግሥታዊ መዋቅሩና እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ ናቸው። በዚህ ደረጃ ላይ ከተደረሰ፤ ወደ ኋላ የመጓዝ ዕድሉ ሙሉ በሙሉ ይጠፋል ባይባልም፤ በጣም ጠባብ ነው። መብቱን በተረዳ ሕዝብ መካከል፣ ይኼንን መብት በግልፅ ያስቀመጠ ሕገ መንግሥት ባለበት ሀገርና መንግሥታዊ መዋቅሩ ለዚህ አመቺ ሆኖ በተዘረጋበት እውነታ፤ አምባገነኖች የመፈልፈላቸውና ፍላጎታቸውን በሕዝቡ ላይ የመጫናቸው ዕድል የጠበበ ነው። በዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ግን ትልቅ አጥር መሻገር ይኖርብናል። ይኼውም የመጀመሪያው ትግል ነው። የመጀመሪያውና አስቸጋሪው ትግል በቅድሚያ መደረግ አለበት።
የመጀመሪያው ትግል፤
ከላይ ባስቀመጥኩት የሁለተኛው ትግል፤ የተለያዩ አመለካከቶች ያሏቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፤ አመለካከታቸውን በሕዝብ ፊት በማቅረብ፤ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚወዳደሩበት እንደሆነ አሳይቻለሁ። ይኼኛው የመጀመሪያው የትግል ደረጃ ከዚያኛው የትግል ደረጃ በጣም የተለዬ ነው። እዚህ ላይ የርስ በርስ ውድድር የለበትም። ይኼ መሠመር አለበት። እዚህ ላይ የርስ በርስ ውድድር የለበትም። ፈራጅ የለም። እዚህ ላይ የኢትዮጵያዊያን የሕልውና ትግል ነው። ይህ ወደ ሁለተኛው የትግል ደረጃ ለመድረስ ጠራጊ ትግል ነው። ይህ እኔ አምራለሁ እኔ አምራለሁ በማለት የሚኮፈሱበት ሳይሆን፤ ለመጠፋፋት የሚነሱበት የትግል ደረጃ ነው። በእርግጥ፤ እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ምርምር ሁሉ አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለው ማለት አልችልም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መሪዎች፤ “ሳንጠፋፋ አብረን እንሥራ ብለው” ሊሠለፉ ይችላሉ ብሎ የሚሞግተኝ እንደማይጠፋ እርግጠኛ ነኝ። እስኪ እኒህን እንመልከታቸው።
በኔ በግል አመለካከቴ፤ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ያለው ቅራኔ የመጠፋፋት ደረጃ ለይ ስለደረሰ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነቱን የሚያገኘው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥትን አወድሞ ነው እላለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ የለም መጠፋፋቱ አያስፈልግም፤ ይህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት፤ ሀገራችን ያለችበትን አደጋ ተረድቶ፣ ፈቃደኛ ሆኖ፣ ከተቃዋሚዎቹ ጋር በመተባበር፣ የዴሞክራሲያዊ አሠራርን ተቀብሎ፤ የሽግግር መንግሥት ይመሠርታል የሚሉ አሉ። አይሆንም ብዬ አልከራከራቸውም። የሚሆንበት መንገድ የለም ብዬም ደረቅ አቋም አልወስድም። የመሆን ዕድል አለው። እኔ ግን በሕልሜም አይመጣልኝም። እናም አላምንም። አሁንም በትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ያው ትግል፤ የጠፊና የአጥፊ ነው እላለሁ። በዚህ ጎን የሚሠለፉ፤ ቅኝ ተገዢዎችና የቅኝ ገዢዎች፣ ተወራሪዎችና ወራሪዎች፤ ትክክለኛ የሆነና ትክክለኛ ያልሆነ ጦርነት አነሳሾች ናቸው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ትክክለኛ የኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሕጋዊ አይደለም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መሪ ሆኖ ከቀጠለ፤ ሀገራችንን ያጠፋታል። ይኼንን እያልኩ፤ ከዚህ መንግሥት ጋር የሰላም ድርድር ይቻላል የሚል ብዥታ አላራምድም። ኢትዮጵያዊያን ለሕልውናችን ስንል ይኼን መንግሥት ማስወገድና ማጥፋት አለብን። የለም ይህ መንግሥት መጥፋት የለበትም የሚሉ ደግሞ፤ ሀገር ውስጥ በሚደረገው ሕጋዊ ትግል ገብተው፤ በሰላማዊ መንገድ፤ ትክክለኛ መንግሥት ለመመሥረት መታገል አለባቸው። ይህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ተደምስሶ ኢትዮጵያዊ መንግሥት መመሥረት አለበት ባዮች ደግሞ፤ ሕጋዊም ሆነ ሕጋዊ ያልሆነ የሚባል ትግል የለንም። የትኛው ሕግ? ማንኛውንም መንገድ በመከተል መታገል አለብን። በአንዳንዶች ዘንድ ሰላማዊ ያልሆነ ትግል መልሶ ሌላ አምባገነን ስለሚያመጣ፤ የትጥቅ ትግል ቦታ የለውም የሚሉ አሉ። ለዚህ እኮ ነው ውይይት አድርገን፤ ሀገር አቀፍ የሆነ አንድ ድርጅት ብቻ መሥርተን፤ በማንኛውም መንገድ እንታገል የምለው። የሚያስፈራው ሰላማዊ ወይንም ትጥቃዊ መሆኑ አይደለም። የሚያስፈራው አንድ የራሱ የሆነ ጉልበታም ድርጅት፤ ሌሎቹን ሁሉ ጠቅጥቆ፤ በራሱ አጀንዳ አዲስ አበባ ላይ የተፈናጠጠ እንድሆነ ወይንም ጠመንጃውን ተመክቶ፤ ተገንጥሎ የሄደ እንደሆነ ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥትን፤ አንድነት ያለውና አንድ ብቻ ኢትዮጵያዊ ኃይል፤ በማንኛውም መንገድ ሊጥለው ግዴታ አለብን። የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው። ስለዚህ፤ የታጠቀ አመፅ ለሚያስፈራችሁ፤ አትፍሩ፤ ኢትዮጵያዊና መላ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚሉ ኢትዮጵያዊያንን ያካተተ ስለሚሆን፤ መቼ ደርሶ በሉ! በነገራችን ላይ ስለትግሉ ጥቅል መልክ ለመሥጠት እንጂ ዝርዝሩን በሚመለከት ገና አልጀመርኩም።
የመጀመሪያው ደረጃ ትግል ዝርዝር፤
እንዲህ ነው። ኢትዮጵያዊያን ለሕልውናችን የምናደርገው ትግል አንድ አጀንዳ፣ አንድ መልክ፣ አንድ ማዕከልና አንድ ግብ ብቻ ነው ሊኖረው የሚገባ። የተለያዩ ማዕከሎች ካሉት፤ ሌላ ትግል በመካከላችን እያዘጋጀን ነው ማለት ነው። አንድ ማዕከል ካላደረግን፤ ተጠፋፊዎች የሆኑ አካላት በመካከላችን አሉ ማለት ነው። ከሁለተኛው ደረጃ ከመድረሳችን በፊት መጠፋፋት ያለብን ክፍሎች አለን ማለት ነው። ይሄ ከታወቀ፤ አጥፊና ጠፊ ባንድ ስለማንሠለፍ፤ ሠፈራችንን ካሁኑ ለይተን መደራጀት አለብን። በዚህ የሕልውና ትግል አንድ ማዕከል ብቻ ሳይሆን አንድ ድርጅት ብቻ እንዲኖር ግዴታ አለ የሚል ነው እምነቴ። ለምን ቢባል፤ የዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጫዬን ነውና! መለያየታችን በሀገር ሕልውና ከሆነ ካሁኑ እንጠፋፋ። የምንለያየው በዴሞክራሲያዊ እምነታችን የመፍትሔ መንገድ ከሆነ በኋላ ከሕዝብ ፊት ስንቀረብ ፈራጁ ስለሚያስተናግደን፤ ቅደም ተከተላችንን እንወቅ። ትግላችን ኢትዮጵያ ሀገራችን ናት ብለን ነው። ትግላችን ኢትዮጵያዊያን ነን ብለን ነው። ትግላችን የሕግ የበላይነት በሀገራችን ይኑር ብለን ነው። ትግላችን የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብት በትክክል ይከበር ብለን ነው። ትግላችን የሀገራችን ዳር ደንበር ይጠበቅና ይከበር ብለን ነው። ትግላችን የኢትዮጵያዊያን አንድነት ይኑር ብለን ነው። ትግላችን ለዚህ ሁሉ ስኬት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ተወግዶ የኢትዮጵያዊያን መንግሥት ይቋቋም ብለን ነው። በዚህና ለዚህ የምንሰባሰበው ደግሞ፤ እያንዳንዳችን በየኪሶቻችን በያዝናቸው ዘውዶች ልክ የተሰፋ ድርጅት ይዘን በመሰለፍ አይደለም። የግድ አንድና አንድ ድርጅት ብቻ ይዘን ነው። ለዚህ ትግላችን ከአንድ በላይ ድርጅት አፍራሽ ነው። ለምን? ከላይ የተዘረዘሩትን የትግል ዕሴቶቻችንን በአንድ ድርጅት ለማሳካት መነሳት አለብን። ከነዚህ አንዷንም አልቀበልም ያለ የትግሉ አካል አይሆንም። በእርግጥ መጨመር ይቻላል፤ ቁም ነገሩ ግን ሁላችንን የሚያስማሙ መሠረታዊ የትግል ዕሴቶችን በመለየት ላይ ነው። በነዚህ ላይ እንስማማለን የሚል እምነት አለኝ።
የሕልውና ጥያቄ ያለው አንድ መልስ ብቻ ነው። መኖር ወይንም አለመኖር። መኖር ደግሞ አንድ ሕይወት ነው ያለው። የኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ መኖር አንድ ነው። የኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ መኖር ሁለትና ሶስት የለውም። አለን ወይንም የለንም ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ አለች ወይንም የለችም ነው። እንድንኖር ደግሞ በአንድነት አለን ለማለት እንድንችል በአንድነት መሠለፍ አለብን። የአኗኗራችንን ሁኔታ፤ ሕይወታችንን ስናረጋግጥ እንነጋገርበታለን። መጀመሪያ ግን ሕልውናችንን እናረጋግጥ። ይህ ማለት ደግሞ፤ ለሕልውናችን አንድ ሆነን በአንድነት እንታገል ማለት ነው። ታዲያ ሁለትና ሶስት ድርጅቶች፣ ሁለትና ሶስት ማዕከሎች፣ ሁለትና ሶስት የአመራር መዋቅሮች ተልዕኳቸው ምንድን ነው? በእርግጥ ይኼ ቀላልና ግልፅ በሆነ መንገድ ስንመለከተው ነው። ለአንዳንዶች የነበራቸው ታሪክ፣ የከፈሉት መስዋዕትነትና የድርጅታቸው ጥንካሬ እየጎተታቸው ይኼንን መቀበል ይገዳቸዋል። ቁም ነገሩ ግን፤ የተዋደቁለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነቱን አግኝቶ የራሱ ምርጫ እንዲኖረው እንጂ፤ የነሱ ድርጅት የግድ የበላይ ሆኖ ገዢ እንዲሆን አልነበረምም፤ አይደለምም። እንግዲህ እዚህ ላይ፤ በትክክለኛ መንገድ ድርጅታቸውን የትግል መሣሪያ አድርገው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታግለውበታል ከሚለው ቅን አስተሳሰብ በመነሳት ነው። በያዙት ርዕዩተ ዓላማ ጠንካራ እምነት ካላቸው፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እምነት ካላቸው፣ ያደረጉት ተጋድሎ የሕዝብ ነው ብለው ካመኑ፤ የድርጅታቸውን ጉዳይ በሁለተኛው የትግል ደረጃ ለማምጣት የሚያግዳቸው የለም። በሌላ በኩል ደግሞ፤ አባሎቻቸው በድርጅቶቻቸውና በርዕዩተ ዓለሞቻቸው ሙሉ እምነት ያላቸው ከሆኑ፤ ድርጅቱ በሰዓቱና በቦታው ሲመሠረት መምጣታቸው አይቀርም። አለያ ፍርሃት አለ ማለት ነው! ያንን ራሳቸው ይመርምሩ። በብልጠት ቦታ መያዣ አድርገው፣ ካሁኑ መረቦቻቸውን ዘርግተው፣ ድርጅታቸውን አጠናክረው፣ የተጠራቀመ ድልብ ሆነው ለሥልጣን ከሆነ ድርጅታቸውን የሚፈልፉት የሕዝብ ክፍል ለመሆናቸው ጥርጣሬ እንዳሳድር ያደርገኛል። ትግሉ ሕዝቡን የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ እስከሆነ ድረስ፤ ቅንነት፣ ቆራጥነት፣ መስዋዕትነት፣ እና ከራስ ወዳድነት የራቀ ኢትዮጵያዊነት ነው የሚጠበቀው ከታጋዮች። በተለይም የተሰው ታጋዮችን የትግል ፍሬ መቁጠር ያለብን በሕዝቡ የሥልጣኑ ባለቤትነት መሆን አለበት።
ከዚህ ወዴት?
ከዚህ በላይ በሠፈሩት ከተስማማን፤ መስማማታችንን መጀመሪያ ማስመር ግድ ነው፤ ቀጥሎ ምን ይደረግ ወደሚለው እንሄዳለን። ነገር ግን፤ ከላይ የሠፈረው ቀላልና እንዲያው ባድ ሰው ጽሑፍ ወይንም ባንድ ምሽት የሚካተት ስላልሆነ፤ ሁላችን በያለንበት እንድናብላላውና የየራሳችን የሆነ አቋም ወስደን እንድንወያይ፤ ጊዜ መሥጠት እፈልጋለሁ። ይኼ የኔ የብቻዬ ወይንም የግሌ ጉዳይ አይደለም። ጉዳዩ የሀገራችንና የሁላችን ነው። ያቀረብኩት የራሴን አቋም ነው። ከኔው የተሻለ ሃሳብ ሊኖር ይችላል። ጥሩ የሚሆነው፤ የለም እንዲያ አይደለም፤ ተሳስተሃል ተብዬ የናንተን ደግሞ ባዳምጥ ስለሆነ፤ ተነጋገሩበት። የሀገር ጉዳይ በአደባባይ እንዲህ ወጥቶ ብንነጋገርበት፤ ወደ ጥሩ መፍትሔ አንሄዳለን። ከዚህ ወዴት? የሚለውን በሚቀጥለው አራተኛውና የመጨረሻው ክፍል አቀርባለሁ።
(ክፍል አራት – የመጨረሻው ይቀጥላል)

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar