onsdag 26. juni 2013

“መቶ ሚልዮን የሰረቁና ያስዘረፉ፤ 10ሺህ ብር የሰረቀውን ሲያገላብጡት ሲያስፈራሩት ይታያሉ” – ስብሃት ነጋ (አዲስ ቃለ-ምልልስ)

(በቀጣይ ለዘ-ሐበሻ አንባቢዎች ያቀረብነው ቃለ ምልልስ አቶ ስብሃት ነጋ ሰንደቅ ለሚባለው ጋዜጣ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ነው። ቃለ ምልልሱ ዛሬ በኢትዮጵያ በታተመው ጋዜጣ ላይ ታትሞ ተሰራጭቷል። ጥያቄዎቹ በሰሞናዊዎቹ በሙስና እና በአባይ ጉዳይ ያተኩራሉ። ለግንዛቤዎ በሚል እንደወረደ አቅርበነዋል”")

ሰንደቅ፡- ባለፉት ስርዓቶች ሙስና እንደ አሁኑ ብዙ ጫጫታ አይሰማበትም ነበር። ለምን አሁን?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- ትክክል ነህ። ምክንያቱም በፊውዳሉ ስርዓት መሬቱም ጉልበቱም የባላባቶቹ ንብረት ስለነበረ ቀጣፊ የሚባለው ጭሰኛ ነበር። “ቅጥፈቱም” ለባላባቶች ከሚያርሰው መሬት ትንሽ ለሆዱ የሚሆን በቆሎ ከዘራበት ለምን ቦሎቄ አልዘራህም ተብሎ በቦሎቄ ሂሳብ ይቀጣል። የመንግስት ሰራተኛ የመንግስት ገንዘብ ከሰረቀ ግን ጐደለበት ነበር የሚባለው። በደርጉ ቢሮክራቲክ ሶሻሊዝም ስርዓትም ቢሆን የከተማ ንብረት በመሉ በእጁ ስለነበረ የተገኘችው እንደፈለገ ነበር፤ ለራሱም ለቤተሰቦቹም ሲጠቀምበት የነበረው። ስለዚህ ሁለቱም ሃብት ፈጣሪዎችም አልነበሩም የተፈጠረው ሃብትም በመሰረቱ የራሳቸው ነበር። አሁን በመንግስትም በገበሬም በግሉ ባለሀብትም በፍጥነት ሃብት እየተፈጠረ እያለ ከስርዓቱ ጋር የማይሄድ ሙስና እያጋጠመ ነው።

ሰንደቅ፡- በባህርዳር በተካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ዘመቻ እንዲከፈት ለጉባኤው ጥሪ አቅርበው ነበር። ጥሪውን ለማቅረብ የነበረዎት መነሻ ምን ነበር?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- ኪራይ ሰብሳቢነት የስርዓታችን አደጋ ነው ተብሎ በትክክል የተቀመጠው ገና ኢህአዴግ ስራ ሲጀምር ነው። ስለዚህ ሙስና ያለቅጥ እየተስፋፋና  አደጋ እያደረሰ ሲሄድ ጠ/ሚ/መለስም፤ ጠ/ሚ/ሃይለማርያምም፤ የኢህአደግ ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ሬድዋንም፣ ተራው ህዝብም በየመንገዱ በየመስርያ ቤቱ ለአመታት ሲጮሁበት የነበረ ጉዳይ ነው። እኔም እንደ ሌሎቹ ነው ስለሙስና የተናገርኩት እንጂ የተለየ ነገር የለውም። የተለየ ካለው ሙስና ከውጭ ወራሪ ኃይል የከፋ ጠላት ነውና ሙስና የተወራበት ቦታ ካለ የሚመለከታቸው አካላት ለደቂቃም ሳይዘገዩ ማጣራት ግዴታቸው ነው፤ ስል አሳስቤአለሁ።
ሰንደቅ፡- አሁንበሀገሪቷ ውስጥ ያለውን አደጋስ እንዴት ያዩታል?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሙስና ጠቅላላ የሀገሩና የኀብረተሰቡን ህይወት ወደ ከፍተኛ ምስቅልቅል የሚመራ ተግባር ነው። በመንግስት፤ በግልና በገበሬው የሚካሄደው ልማት ተገቢውን ውጤት ሳያመጣ ሊቀር ይችላል። በሙስና ምክንያት በመንግስት የሚፈፀሙ እቅዶች በተገቢው ወጪ፤ በተፈላጊው ጥራትና ጊዜ እንደማይፈፀም የአደባባይ ሚስጢር ነው። በዚህ ጉዳይ ምን ያህል ጉዳት ደረሰ በጥናትና በምርመራ ነው የሚታወቀው። መንግስት የተቀናጀ ሁሉም ዓይነት ድጋፍ በመስጠት በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ልማታዊ የግል ባለሀብት እፈጥራለሁ ነበር ያለው። አሁን በየሴክተሩ ያለው ባለሀብት እውነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል አቅም አለው ወይ ብለን ብንጠይቅ፣ መልሱ አሉታዊ ነው ሊሆን የሚችለው። ጥገኛውን በተቀናጀ ጫና እያዳከምን አቅመ-ቢስ እናደርገዋለን፤ ያልነውስ የት ደረሰ ብለን ብንጠይቅስ መልሱ ምንድነው? ጥገኛው እየበረታ ልማታዊው ሳይፈጠር የቀረበት ሁኔታ ውስጥ ያለን እንዳንሆን መገመት፤ ከግምት ወጥተንም መገምገም የሚጠይቀን ይሆናል።
ሙስና በልማት ብቻ ሳይሆን በመልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲ ግንባታ ላይም የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ ነው። ህገ መንግስትን በመጣስ የላይኛው የታችኛውን ኃላፊ እያዘዘ ለዚህ አድርግለት፤ ለዚያኛውም ቀማው፤ እሰረው የሚል አለ። ስልጣን የሚቀማው ለኢኮኖሚው /ሙስና/ ጥቅሙ ነው። ስልጣን እየተቀማ ያለውም በዚያች ወንበር ተቀምጦ ለመቆየትና ትርፍራፊ አገኛለሁ ብሎ በማሰብ ነው። በወንበሩ ላይ እስካለ ድረስ ጥቅም ያገኛል። ስልጣን በመንጠቅ በመነጠቅ የሚፈፀም እንዳልሆነ ከፓለቲካዊ ድርጅት ፈንጠር ብለው የድርጅቶችን አባልነታቸው ስም በመጠቀም የራሳቸው ህገ ወጥ ሰንሰለት ፈጥረው ሊዘርፉ ሊያዘርፉ የሚኖሩ ግለሰቦችም የተፈጠሩ ይመስለኛል። ፈንጠር ማለቴ በኔትወርክ ማለቴ ነው። ስለዚህ በመንግስትም በፖለቲካዊ ድርጅቶችም ለስርቆት ተቋማዊ አሰራር ከተጀመረ አደጋ ነው።
የሙስና አደጋ በልማትና በዲሞክራሲ የሚያመጣው አደጋ ብቻ ሳይሆን በሃገር ፀጥታና በሰው ልጆች የሚያመጣው የስነ አእምሮ ጫናና ስጋትም ጭምር ነው። ሌባ የሰላም ሃይል አይደለም። ለውጭ ጠላትና ለሃገር ውስጥ ፀረ ህዝብ ተገዢ ነው። በልማታዊና በፀረ ሙስና ሃይሎች የማይተኛ ፈሪ ጨካኝና ፈጣን አራዊት ነው፤ ሙሰኛ።
በመሰረቱ በጤናማ ሁኔታ የሚገኙ ሰዎችን እንቆርጣለን፤ እናስራለን ወዘተ እያሉ ሲያስፈራሩ የነበሩ የፖለቲካ፤ የመንግስት ሰዎች ነን የሚሉ የፀጥታና የስነ አእምሮ ሁከት ፈጥረዋል። መቶ ሚልዮን የሰረቁና ያስዘረፉ፤ 10ሺህ ብር የሰረቀውን ሲያገላብጡት ሲያስፈራሩት ይታያሉ ይባላል። ጠቅለል አድርገን ስናየው አሁን ያለው የአንዳንድ የመንግስት፤ የፓርቲና የግል ባለሃብቶች ከኢህአደግ መንግስት ስርዓት ፈፅሞ የማይሄድ ፀረ-ልማት፣ ፀረ ዴሞክራሲና ፀረ ሠላም እየሆኑ በመጓዝ ላይ ነው ያሉት። ሙሰኝነት ከኢህአዴግ ስርዓት አኳያ ስናየው ከውጭ ወራሪ ኃይል እጅጉን የከፋ ጠላት ነው። ድንበር የተሻገረ ጠላት ጊዜ የሚሰጥና በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ አደጋ ነው። ስለዚህም ዋናው አደጋ የውጭ ጠላት ሳይሆን በስርዓቱ የሚደርስ አደጋ ነው። የስርዓቱ ባለቤቶችና ስልጣን እየተረከቡ የሚሄድት ልማታዊ ባለሃብት እና ወዝአደሩ ሳይፈጠሩ እየቀሩ፣ ስርዓቱ እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች የጥገኛው ባለሃብትና የቢሮክራቱ ስርዓት ይሆናል።
ሰንደቅ፡- ይህ ስርዓት በኪራይ ሰብሳቢዎች የመጠለፍ አደጋ ይገጥመዋል ብለው ይሰጋሉ?
አቶ ስብሀት ነጋ፡-ያለውንየሙስና ሁኔታ የሚመጥን እርምጃ ካልተወሰደ ስርዓቱ ያለምንም ጥርጥር አደጋ ይገጥመዋል። አደጋውም በልማታዊነት ዴሞክራሲያዊነት ብቻ ላይ አያበቃም። ሰላም በውስጥም ከውጭም አይኖርም። ይህ ሲከሰት ደግሞ የሰላም የልማት የዴሞክራሲ ተምሳሌት የተባልነውን ያህል ወደ ድሮ አሳፋሪ ስማችን እንመለሳለን።
ሰንደቅ፡- ሙስናን ለመታገል በመንግስት በኩል የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነበር ብለው ያምናሉ?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- የሙስና መጀመርና እየተስፋፋ መሄድ ከአስር ዓመታት በላይ ሲነገርለት የነበረ ጉዳይ ነው። እኔ እስከማውቀው አልፎ አልፎ የሚወሰዱ ሁኔታውን የማይመጥኑ የተናጠል እርምጃዎች ነበሩ። ጥራታቸውን ለሚያውቁ እንተወው።
ሰንደቅ፡- የሙስናውደረጃ አሁን ባለበት ደረጃ እስከሚደርስ ለምን ተኛን ብለው ይገምታሉ?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- ሙስናውእዚህ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ለምን ተኛን የሚለው የግምገማ ጉዳይ ስለሆነ ቢቆይ ይሻላል።
ሰንደቅ፡- አሁን መንግስት በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ የጀመረውስ እርምጃ ተመጣጣኝ ነው ብለው ያስባሉ?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- አብረን የሰማነው የጠ/ሚ/ኃይለማርያም ቃል ነው የምደግምልህ። “ፀረ ሙስና እንቅስቃሴ ይቀጥላል፤ ህዝቡ ይሳተፍበታል፤ እኔ ራሴ በቀጥታ እከታተለዋለሁ” ብለዋል። ይህ የእሳቸው ንግግር የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይንፀባረቅበታል። አሁንበሙሰኞች ላይ በተወሰደው እርምጃም ተጠቃሚው ሰፊ ህዝብ ከጫፍ እስከጫፍ እጅግ በጣም የተደሰተ ይመስለኛል። እርምጃ መወሰድ የተጀመረው ህዝቡ ይሳተፋል፤ እኔ እራሴ እከታተለዋለሁ ካሉ በኋላ ነው። ይቀጥላል የሚለው ቃል እርምጃው ከተጀመረ በኋላ የተገለፀ ነው። ስለዚህም የጠ/ሚኒስትሩ ቃልና ተግባር ስለተገጣጠሙ አስተማማኝ ጅምር ነው እየሆነ ያለው። መቆም ወደማይችልበት ደረጃ የደረሰ ይመስለኛል።
ሰንደቅ፡- ይመስለኛል፤ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይንፀባረቅበታል ከሚሉ ለምን በእርግጠኝነት ምላሽ አይሰጡኝም?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- ጠ/ሚኒስትራችን ያለው እንደማይቀለበስ እርግጠኛ ነኝ። አካሄድ ላይ ግን እርግጠኛ ለመሆን አልቻልኩም። በተለይ ኪራይ ሰብሳቢዎችን ለመዋጋት በህዝብ ተሳታፊነት እንዴት ሊሆን እንደሚችል አላወቅኩም። ህዝብ ያለው ኢንፎርሜሽንና በእንቅስቃሲያዊ አካሄድ ያለው ገንቢ አመለካከት ለማን ነው የሚያቀርበው? እንዴት ነው የሚያቀርበው? ካቀረበው በኋላስ በየፈርጁ ተደራጅቶ እንደገና ለውይይት ለጥራት ለህዝቡ እንዴት? መቼ? በማን? ነው የሚቀርበው። ወይስ በተናጠል ከቀረበ በኋላ ወደ ማጣራትና ወደ ምርመራ ወደ ክስ ነው የሚኬደው? ባጭሩ የህዝቡ ተሳትፎ አካሄድ የህዝቡ አቅም በሚያዳብር አግባብና ጥራት ያለው ውጤት መሄድ አለበት የሚል እምነት አለኝ።
እኔ የሚታየኝ አሁን ያለው የኪራይ ሰብሳቢነት ሁኔታ በአጠቃላይ፤ ስፋቱ፤ ጥልቀቱ፤ በየትኛው የመንግስትና የግል አካላት እንደሚታይ በሚመለከተው አካል አማካኝነት ለህዝቡ መቅረብ አለበት። ሁኔታው ከቀረበ በኋላ ህዝብ ያዳብረዋል። ዋነኛው ህዝብ ማለት ደግሞ፣ በአገልጋዩ የመንግስት አካል የሚሰራ ሰራተኛ እና በዚሁ አካል በቀጥታ የሚገለገል ህዝብ ነው። ይህም ሲባል፤ ከሁኔታው ጋር በቀጥታ ዝምድና ያላቸው ህዝቦች ማለት ነው። ሌላውም የኅብረተሰብ ክፍል በሚድያ በመድረክ ሊሳተፍ ይችላል። በዚህ መልኩ ሁኔታው ከታየ በኋላ በቀጣይ መንስኤውን ማስቀመጥ ነው። በሶስተኛ ደረጃ ያስከተለውን ኪሳራ ማየት ነው። በአራተኛ ደረጃ መፍትሄውን ማየት ነው። ባጭሩ ሁኔታ፤ የሁኔታው መንስኤ፤ የፈጠረው ጠንቅ እና መፍትሄው ላይ ነው ህዝቡ መሳተፍ ያለበት። ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ነበረ ወይ የሚለው በዚህ ሂደት ነው የሚመለሰው።
ሰንደቅ፡- ከላይያስቀመጡትን ሂደቶች ማነው የሚያዘጋጀው?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- ይህን መነሻ /መንደርደርያ/ ግምገማ ማን ነው የሚያዘጋጀው የሚለው የእኔም ትልቅ ጥያቄ ነው። በፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቋም ውስጥ ያለውን መረጃ ለዓመታት ከአገርም ከውጭም የተጠራቀመ ኢንፎርሜሽን አሉ። በአሁኑ ጊዜም ህዝቡ ወደዚያው ነው የሚልከው ይባላል። አሁንም ከድሮውም ጀምሮ በሙስና ኢንፎርሜሽን ጉዳይ ሁሉም ነገር ተቋሙ በእጁ ያለ ይመስለኛል። በኢንፎርሜሽን ከመታጠቅ ውጭ የሞራል ወዘተ ትጥቅ አለው ወይ? ምንም አላውቅም። የምገምተው ግን አለን። የሆኖ ሆኖ የዚህ ባለጉዳይ የመንግስት አካል ለህዝቡና ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሙስና ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ መንስኤው እና ያስከተለውን ጠንቅ ለውይይት ቢያቀርብ ህዝቡ ዋናው ባለጉዳዩ የት ነበርክ? በምን ምክንያት ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ማቅረቡ አይቀርም። ስለዚህም ‘ይመስለኛል’ ያልኩት ከመንግስት አቋም ጥርጣሬ ተነስቼ ሳይሆን አካሄዱ እንዴት ነው የሚሆነው? ከሚል መነሻ ነው። አሁንም ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለጉዳይ ሆኖ ነው ወይ የሚቀጥለው የሚሉ ጥያቄዎች ስላሉኝ ነው።
ሰንደቅ፡- አሁን ያለው ስርዓት ለዓብይ ሙስና ለGrand Corruption የተጋለጠ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- የፌደራልየስነምግባርናፀረ ሙስና ኮሚሽን ከአገር ውስጥ እንዲሁም  ከውጭም በPerception ደረጃ ብዙ ኢንፎርሜሽን እንደሚቀርብለት እሰማለሁ። የሙስና ኢንፎርሜሽን ለአመታት የተከማቸው እዚያው ተቋም ውስጥ ስለሆነ ከላይ እንዳልኩት ህዝቡ በሂደቱ እንዲሳተፍበት ከተፈለገ በትክክል በተገቢው የኢንፎርሜሽን /መረጃ/ አደረጃጀት ይቅረብና እነሱና (ተቋሙ) ህዝቡ ይመልሱታል። እኔ ስገምተው ግን ለGrand Corruption የተጋለጥንና በእሱ የተጨማለቅን ጥቂቶች ብቻ አይመስለኝም።
ሰንደቅ፡- የፀረ ሙስና ዘመቻው በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ያጠነጠነ ነው ይባላል። የእርስዎ አመለካከት ምን ይመስላል?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- እስካሁን ከፍተኛ ሙሰኞች ትንሹን ሙሰኛ ከሰው አሳስረው ያስፈርዱና ያሰቃዩ ነበር ይባላል። ከፍተኛ ሙሰኞች ከመርማሪው ጀምረው አቃቤ ህጉም ዳኛውም ምስክሩም ይቆጣጠሩና ትንሽ የሰረቀም ምንም ያልሰረቀም ሲያሰቃዩና ሲያደኸዩ የነበሩም፤ አሉም ይባላል። እንደዚህ ሲያደርጉ እነ እንትና ከክሱ በስተጀርባ አሉበት ብለው ማስፈራርያ /ትክክልም ሊሆን ይችላል/ የፖለቲካ ሰዎች ስም እየጠሩም፣ እየተገናኙም፣ ስልክ እየደወሉም፣ ይፈርዱ ያስፈርዱ ነበር ይባላል። ይህ ትክክል ነው አይደለም ራሱ የቻለ ሰፊ ስራ ነው። ሰው ግን አረፍ ብሎ ሰርቶ መብላት መኖር አለበት። ስለዚህ የአሁኑ ፀረ ሙስና እንቅስቃሴ የፍትህ አካላትም የምርመራ አካላትም፤ የዐቃቤ ሕግ ጉዳዮችም እያጠሩ ህዝባዊ ፍትሃዊ እየሆኑ የሚሄዱበት ጉዞና በትልቁ ደግሞ በጠራራ ፀሃይ ማለት ህዝቡ የሚካፈልበት ስለሚሆን ያላጠፉ ግለሰቦችን የማይነካበት ይሆናል። ይሁን እንጂ ሌባና ሌባ የሁሉም ብሄሮች ሌቦች በአንድነት እየተደራጁም በተናጠልም የዚህ ብሄር ተጠቃ የዚያኛው ብሄር ያለጥፋቱ ታሰረ ማለታቸው አይቀርም። ትርጉም ግን አይኖረውም።
ሰንደቅ፡- የፌደራል ዋና ኦዲት ሪፖርት ለእርስዎ የሚሰጥዎት ትርጉም ምንድነው?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- በዚህ አገር በዚህ ስርዓት በአሁኑ ጊዜ ትልቁና የማያጠራጥር ተስፋ ሰጪ ሁኔታ የፌደራል ዋና ኦዲተር ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ መጀመሩና ከሁሉም በላይ ደግሞ የፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህዝብ ተወካይነቱ ማረጋገጥ መጀመሩ ነው። ይህ ከፍተኛ የስልጣን አካል ስራ መጀመሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ የምስራች ነው። የሾማቸውን አስፈፃሚ አካላት ኦዲት ሪፓርት መሰረት በማድረግ መቆጣጠር መጀመሩ ብቻ ሳይሆን፤ በቀጥታ በመጥራትም ያለወትሮው የስራ ሂደት ማወቅና ማስተካከል ጀምሮዋል። አሁንም ያለወትሮው ወደስራ ቦታው እየሄደ ማጥናትና ማስተካከል ጀምሯል። አሁን የተወካዮች ምክር ቤትን በተገቢው ደረጃ የማይፈራ ፈፃሚ አካል የለም። ኦዲት እየጠራ እንዲቀርብለት በሚቀርብለት ኦዲት ተመስርቶም እርምጃ እንደሚወስድ ምንም ጥርጥር የለውም። ሌሎች ተጠሪነታቸው ለፓርላማ የሆኑም እንደሚንቀሳቀሱ ምንም ጥርጥር ያለው አይመስለኝም። ሌሎች በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችም ማለትም የክልል የወረዳ፤ የቀበሌ፣ የከተሞች ም/ቤቶች የፌዴራል ም/ቤት ፈለግ መከተላቸው አይቀርም። ፓርላመንተሪ ሲስተም የእኛን ሲስተም ማለቴ ነው። ቦታውን እየያዘ ነው። ሌላው የዳኝነት ስርዓቱ ፅዳት በፍጥነት መድረስ አለበት። የጠቅላላ ስርዓቱ አንድ አካል የሆነው ዳኝነት የሚባለው ያለበት ሁኔታ ዓለም ያወቀው ስለሆነ ይስተካከል ከማለት በስተቀር ስለሁኔታው አሁን አለመናገር ይሻላል።
ሰንደቅ፡- ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የግብፅ ፓለቲከኞች የሚሰነዝሩትን ሃሳቦች   እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- የግብፅ ፖለቲካ በወሳኝነቱ በአባይ ወንዝ የተመሰረተ ነበር፤ አሁንም ቢሆን። የግብፅ ፖለቲከኞች ሃገራዊነታቸው ጀግንነታቸውና በስልጣን የመቆየታቸው ጉዳይ በአባይ የተመሰረተ ነው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ አለመረጋጋት አለ። ስለዚህ ማንኛውም የግብፅ ፖለቲከኛ የግብፅ ብሄርተኝነቱ ማረጋገጫ በአባይ ላይ የሚወሰደው አቋም ነው። ለዚህ ተጨማሪ በኢትዮጵያ ህዝቦችና ባለፉት መንግስታት የነበረው ንቀት አለ። ስለዚህ እነዚህ ድክመቶች ተደማምረው እነሱ የፈጠሩትን የህዝቡ ስሜታዊነት ለመቀስቀስ አካኪ ዘራፍ ማለታቸው አያስገርምም። የሚያስገርመው ግን ስለግድቡ እንደማያውቁ መሆናቸው ነው። የሆኖ ሆኖ ታላቁ ቁምነገር ተሳስተናልና ሁሉም ነገር በጋራ እናየዋለን ማለታቸው ነው።
ሰንደቅ፡- በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ጦርነት ይነሳል ብለው ያስባሉ?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- ጠ/ሚ/ኃይለማርያም አይመስለኝም ብሎ መልሶታል። የእኛ መንግስት ኃላፊዎች የግድቡ አጀማመር፤ አካሄድና ይዘት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ የአካኪ ዘራፍ አቋም አልነበራቸውም። ማብራሪያ ነበር የጠየቁት። በታላቅ ትዕግስት ነበር ማብራሪያውን የጠበቁት። በርግጥ አንዳንድ ሰዎች ስለጉዳዩ ምንም አይነት ፍንጭና አጠቃላይ ግንዛቤም ሳይዙ ወደ ወታደራዊ አቅም ግምገማ የሄዱት፤ የተመኙት ጦርነት የሚሆንላቸው እየመሰላቸው ነው። ጦርነት የማይነሳው በወታደራዊ አቅም ሚዛን ብቻ አይደለም። የግድቡ ፍትሃዊነትና ፍትሃዊነቱም ድፍን ዓለም ያወቀው በመሆኑ ነው። በዋናነት ፍትሃዊነቱ የዓለም ኅብረተሰብ ብቻ ሳይሆን የማይናቅ የግብፅ ህዝብም አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ባህሪ የጋራ ጥቅምን ማዕከል አድርጐ እያሰበ የሚሰራ እንጂ የህዝብ ተራ ስሜት እየቀሰቀሰ ጐራዴ ታጥቆ በየመንገዱ የሚፎክርና የሚያስፎክር እንዳልሆነ ማወቅ ጀምረዋል። ስለዚህም ጥንቃቄ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ለጦርነት ምክንያት የለውም።
ሰንደቅ፡- ግብፅ፤ ኤርትራና ሶማሊያን እንዲሁም የሃገር ውስጥ ተቃዋሚዎችን ኢትዮጵያ ለማተራመስ መምረጣቸውን እንዴትን ይመለከቱታል?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- ግብፅ እነዚህን ጐረቤት ሃገሮች ለትርምስ መምረጥዋ አላውቅም። የምትመርጥ አይመስለኝም። ግብፅ የሚጠቅማት የኢትዮጵያ ልማትና መረጋጋት ነው። ይህንን በተሟላ ደረጃ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ የሚወስድባቸው አይመስለኝም። ግብፅ፣ ሶማልያ፣ ኤርትራና የአገር ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለትርምስ  አትመርጥም። ብትመርጣቸውም እንደሃገር ለዚህ ጉዳይ ከግብፅ ጋር የሚሰለፉ አይመስለኝም። አይመስለኝም ያልኩት በሁለት ምክንያት ነው። መጀመርያ ሊያምኑበት አይችሉም። ሁለተኛ እነዚህ ጐረቤቶች አያዋጣቸውም። ዋናው ነገር ግን ግብፅ ይህንን ነገር አትመርጥም። ኢህአዴግ ቢጠሉም ከግብፅ ጋር የሚሰለፉ የሃገር ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አይኖሩም። አንዳንድ ብስጭታቸው ወደ ህመም ደረጃ የደረሰ ካልሆኑ በቀር የሚሰለፍላቸው የለም። ዋናው ነገር ግን ግብፆች ጥቅማቸውን የሚያዋጣቸውን ሳይገነዘቡ አይቀሩም። እየተገነዘቡም ነው።
ሰንደቅ፡- የህዳሴው ግድብ ገዢው ፓርቲ ለራሱ የፖለቲካ ፍጆታ እያዋለው ነው የሚል ክስ ተቃዋሚዎች ያቀርባሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
አቶ ስብሀት ነጋ፡- የህዳሴ ግድብ ይዘትና አካሄድ በጉዳዩ በአለማችን ግሩምና የተዋጣለት ከሚባሉ ታሪኮች አንዱ ነው። የጉዳዩ ውስብስብነት በመረዳት የናይል ተፋሰስ ባለድርሻዎች በማሰለፍ አንዱ ትልቅ የአፍሪካዊነት ኢትዮጵያውነት ህዝባዊነት የፈጠረው ብልህነት ነው። የባለድርሻዎች ሰልፍ ነው። የአባይ ግድብ ለሶስታችን ለጋራ ተጠቃሚነት ለመገደብ ሲታሰብ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፖለቲካዊ፤ ዲፕሎማሲያዊና ቴክኒካዊ ፍተሻና ጥናት እንዲካሄድ ኢትዮጵያ መሪነቱን እየያዘች ቀዳዳ እንዳይገኝ የረጅም ዓመታት ወደፊት እያየች በታላቅ ሃላፊነትና ትዕግስት ሞያ ነው ስራውን ስታራምድ የቆየችው። ይህን ያህል ታላቅ የዘመናችን ስራ አሁንም ለወደፊትም ለጠላት በር እድል እንደማይሰጥ አድርገህ መሄድ እጅግ በጣም አስደናቂ ታሪክ ነው።
በእኛና በታችኛው አባይ የነበረ የዘመናት ውጥረት ወደ ፍቅርና አብሮ የመስራት መንደር የሚከተን ስራ ነው። በአጠቃላይ ለኛ ለአባይ ተፋሰስ አገሮችና በተለይ ግድቡ ለሶስታችን ብቻ አይደለም፤ ጠቃሚነቱና አስተማሪነቱ። እንደኛ ያሉ ድንበር ዘለል ወንዞች ያሉዋቸው አገሮች የእኛ የአባይ ተፋሰስ አገሮች አብሮ ለመስራት መጀመር ታላቅ ትምህርት ነው። ግድቡ ብቻ አይደለም ታላቅ የሃገር ስራ። ዋናው የዓባይ ተፋሰስ ሃገሮች ትብብር መጀመሩ ነው። ይህ ጉዳይ በዓለም እየተነገረ ብቻ ሳይሆን የሚኖረው መልካም ትምህርት ሆኖ እየተኮረጀ የሚኖር ስራ መስራታቸው ነባሪ ነውና መላው ህዝብ እንደ ሃገር ኩራት መውሰድ አለበት። ለቀጣይ ሃገራዊ ስራዎች የህሊና ሃይል በሚፈጥር መንገድ መነገር ብቻ ሳይሆን፣ ተፅፎ ለእንደኛ ያሉ ድንበር ዘለል ወንዞች ያሉዋቸው ሃገሮች መዘርጋት አለበት።¾
(ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር407 ረቡዕ ሰኔ 19/2005)

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar