fredag 8. februar 2013

ፍቅርና አንድነት ያለው ህዝብ ጠላቱን ያሸንፋል


ባለፈው ሂትለርና የወያኔን መሪዎች ባነጻጸርኩበት ጽሁፍ ላይ መለስ ስብሀት በአማራው ህዝብ ላይ በሰፊው ሊያንቀሳቅሱ የሞከሩት እልቂት አንዴት በሚፈልጉት ልክ እንዳልገፋላቸው ሗላ ላይ እናወጋለን ብየ ነበር።
በአለማችን ያሉ ጤናማ መንግስታት በዜጎቻቸው መካከል የመብት ልዩነትና የዘር የቀለም መለያየት፤ ግጭት እንዳይኖር ያለመታከት ይሰራሉ። ይተጋሉ። በኢትዮጵያ ያለው የዲያቢሎሶች መንግስት፤ ሰው በዘሩ ተለይቶ እንዲታወቅ፤ እንዳይስማማም እንዲበላላም ለማድረግ በትጋት ሲሰራ ሀያ ሁለት አመታትን አስቆጠረ።
ስርአትን መቃወም አንድ ነገር ነው።ስርአቱን ወደ ጎን አድርጎ አንድን ክፍለ ህዝብ እንደስርአት ስሎ፤ የመደብ ጠላት አድርጎ፤ አእላፍ ቋንቋ የሚናገርን ሕዝብ ለድህነትህ፤ ለሗላቀርነትህ፤ ተጠያቂ፤ ጠላትህ፤ ያንን ቋንቋ የሚናገረው ዘር ነው ብሎ፤ ባንድ ወገን ላይ የጥላቻ ዘመቻ ማንቀሳቀስ ዘርን ለማጽዳት ከሚደረግ ትልምና እቅድ የተለየ አላማ አለው ማለት ያስቸግራል።
  • ገዢ መደቦች ለፈጠሩት ስህተት ወይም ወንጀል፤ እነዚያ ገዢዎች የወጡበት ክፍለ ህዝብ እንደ ጠላት ተቆጥሮ ትውልድ በማያቀው ጉዳይና  በማይደግፈው ድርጊት እዳ የሚከፍልበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም። ባለፉት ሀያ ሁለት አመታት የህውሀት መሪዎች ስልጣኑን በጠመንጃ ተቆጣጥረው በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እያደረሱት ላለው በደልና ወንጀል፤ ለራሱም የችግሩ ሰለባ የሆነው የትግራይ ህዝብ ተጠያቂ ነው የሚል አስተሳሰብ ያለው፤ የሀያ አንደኛው ክፍለዘመንኢትዮጵያዊ ይኖራል ብየ አላምንም። ምንጊዜም በሀገርና በህዝብ ላይ ለሚፈጸሙ አስተዳደራዊ ወንጀሎች፤ ተጠያቂው በአፈሙዝም ይሁን በምርጫ ስልጣን የተረከበውን ቡድን በበላይነት የሚመሩት፤ የህጉም የፖሊሲውም፤ አውጪዎችና አስፈጻሚዎች በጣት የሚቆጠሩት መሪዎች ናቸው እንጂ፤ ያመሪ የወጣበት የህብረተሰብ ክፍል አይደለም። በተዋረድ እንደየስልጣን ደረጃቸውና ሀላፊነታቸው እስከታች አርከን የወንጀሉ ተሳታፊዎች በህግ ይጠየቃሉ። ሕዝብ ከደሙ ንጹህ ነው።

1983 ወደ ሗላ መለስ ብየ ልጀምረውና በአርሲ አርባ ጉጉ፤ በአሰቦት ደብረወገግ ገዳም፤ በበደኖ፤ እና በሌሎቹም አካባቢዎች ህውሀት ወደ ስልጣን አንደመጣ በአማሮች ላይ ሊያንቀሳቅስ የሞከረው ፍጅት የተፈለገውን ያህል ውጤት ሊያመጣ ያልቻለው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለምእተ አመት ያካበተው ውህደት የፈጠረው፤ የወንድማማችነትና የአንድነት መንፈስ፤ አሸናፊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ህብረተሰቡ ለዚያ መተላለቅ በቀላሉ ተነሳስቶ  እነ መለስ ስብሀት ሚፈልጉትን  ባለማድረጉ ነበር። ሌላው ምክንያት ታላቁ ያገር ልጅ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የመሩት እንባ ጠባቂ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት፤ በዚህ ክፍለ ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ሰቆቃና በደል፤ ወያኔ ይዞት የመጣውን የዘር ማጥፋት እቅድ፤ በያለሙ እንዲስተጋባ በማድረጉ፤ አሁን ያለው የአለም ተጨባጭ ሁኔታ ያንን ሊያስቀጥል የሚችል አለመሆኑን ጌቶቻቸው ስለ ነገሯቸው ሊቀጥሉበት አልቻሉም።
ወደ መጀመሪያው ሙከራቸው ልሂድና የመጀመሪያውን እልቂት ሊያንቀሳቅሱ የሞከሩት የህውሀትንና የኦነግ ወታደራዊ ካድሬዎችን በማሰማራት ነበር። ህውሀትና ኦነግ ያሰማሯቸው የሁለቱ ቡድን መልከተኞች ናቸው አንጂ በአርሲም በሀረርጌም ያን መተላለቅ የፈጠሩት አብሮ የሚኖረው ህብረተሰብ አልነበረም።
ለዚህም ማስረጃ በወቅቱ እዚያው አካባቢ ስለነበርን ሀረርጌ በአካል ህብረተሰቡ ውስጥ ተገኝተን በተለይም ህውሀት ግጭቱን ለማንቀሳቀስ ኢላማ ያደረጋቸው አማሮችና ኦሮሞዎች እንዴት በመተሳሰብ ያንን ሁኔታ እንዳሳለፉት እንድ ተጨባጭ ታሪክ አቀርባለሁ።
ሐረርጌ አንድ ገጠር አውራጃ ውስጥ አማሮች እየታደኑ በሚገደሉበት ሰሞን የህውሀትና የኦነግ ካድሬዎች ባንዲት ገበሬዎች መንደር አንዱን ኦሮሞኢትዮጵያዊ ጎልማሳ በገዳይነት ሊመለምሉት እቤቱ ይመላለሳሉ። አስፈላጊ ነው ብለው ያመኑበትን የፖለቲካና የዘር ጥላቻ ትምህርት ለሳምንታት በቤቱ እየተመላለሱ ከሰጡት በሗላ መሳሪያ ያስታጥቁታል። ልብ ይሏል በዚያን ጊዜ እነሱን መቃወም የኦሮሞን ነጻነት መቃወም ተደርጎ እርምጃ ያስወስዳል። ያ ድሀ አርሶ አደር አስፈላጊው የፖለቲካ ትምህርትና መሳሪያ ከተሰጠው በሗላ የተነገረው ተልእኮ ባካባቢው የሚኖሩ አማሮችን ስለሚያውቅ እያደነ እራሱ እንዲገድል ነበር።እዚያው አጠገቡ አብሮ አደግ ጉረቤቱ የሆነ ሰው ይኖር ስለነበረ ሄዶ እንዲገለው ትዛዝ ይሰጠዋል። ይህን ብለውት ከቤት እንደወጡ እሱም አብሮ ይወጣና ቆይቶ ወደቤቱ ተመልሶ ይመጣል። ከሰአታት በሗላ ተመልሰው ግዳጁን ተወቶ እንደሆነ ይጠይቁታል። እቤቱ የለም ይላቸዋል። አብሮ አደግ ጎረቤቱ ግን ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር እሳት ዳር ቁጭ ብለው ይጫወቱ ነበር። እነዛ የኦነግ እና የህውሀት አረመኔዎች  ሲመጣ ጠብቆ እንዲገለውና ሪፖርት እንዲያደርግ ማስጠንቀቂያም ጭምር ሰተውት ይሄዳሉ። አሁንም ይህ አርሶ አደር  ከቤት ወቶ እነሱ ሲሄዱ ተመልሶ ከቤቱ ይቀመጣል። በድጋሜ ተመልሰው መጡና ትዛዛቸው መፈጸሙን ሊያረጋግጡ “ገደልከው?” አሉት።
ያ ቅዱስ የኦሮሞ አርሶ አደር እንባውን እያፈሰሰ “…እባካችሁ ተውኝ .. ይህን ድሀ አብሮ አደግ ወንድሜን ግደል አትበሉኝ ። ይህንን የኔቢጤ ሚስኪን ብገድለው ድህነቱና ቅማሉ አንጂ ምን ይተርፈኝ መሰላቸሁ። ግደሉኝ ብትፈልጉ… አልገለውም..፡ “ በማለት ያሸከሙትን መሳሪያ ወዲያ ወረወረው። እነዚያ ካድሬዎች ያንን ድሀ አማራ ያን እለት ከነልጆቹ ይዘውት ሄዱ። ወዴት እንዳደረሷቸው ግን አይታወቅም።
በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን ከሀያ ሁለት አመታት በሗላ ወያኔዎችም ሆኑ የተወሰኑ ኦነጎች ችግራቸው ለራሳቸው ተጭነውት የሚሰቃዩበትን በሽታ በቀጥታ በህብረተሰቡ ላይ ለማራገፍ ከመጣደፍ በቀር እዚያ የደረሱበት አካባቢም ሆነ በማናቸውም ጥግ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ “በእንዴት ያለ ሁኔታ ነው አብሮ መኖር የያዘው? ትስስሩና ፍቅሩ እምን ድረስ ነው? ውህደቱና ስምምነቱ እምንድረስ ነው ?” ብለው የህብረተሰቡን ሁኔታ ለማጥናት ጊዜ አይወስዱም። የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱ በታወሩበት የዘረኝነት በሽታ ታውሮ የሚኖር ነበርም ነውም የሚመስላቸው።
በወቅቱ የታዘብኩትን ሌላ ገጠመኝ ላውጋ። እዚያው ሀረርጌ ውስጥ ነው። ጊዜዋም ያችው ቀውጢዋ ነበረች። አንዲት የወረዳ ከተማ ውስጥ ልዩ ልዩ ብሄረሰቦች ይኖራሉ። አብዛኛው ኦሮሞ ይሁን እንጂ አማራ፤ ጉራጌ፤ አፋር፤ከሶማሌ ብሄረሰብ ኢሳ የሚኖሩበት ከተማ ነች። እነዚህ ክፉ ሰዎች ገና ሁሉንም ተቆጣጥረው እንደጨረሱ ቢሆንም በደንብ አልተረጋጋም። ኦነጎችም እስር እስራቸው ይሉ ነበር። በዚች በማወሳት ትንሽ ከተማ ውስጥ አስተዳዳሪዎች ነን ብለው ኦነጎች ቢሮ ገባ ገባ ብለው የነበረበትና አለቆቻቸውም ከወያኔ ጋር ሽግግር ምክር ቤት ሽር ጉድ ይሉ የነበረ ጊዜ ነው። ክልሉ የኦሮሞ ስለሆነ እናስተዳድራለን ይሉን የነበሩት የኦነግ ታጣቂዎች አምስት ስድስት ትላልቅ የኝነት መኪና ሞልተው፤ ጠመንጃ ተሸክመው፤ ላይ ታች በከተማው ዥው ዥው ይሉ የነበሩቱ እያስተዳደርን ነው ብለው ቢሮ በገቡ በሶስተኛው ቀን፤ ኦሮምኛና ትግርኛ እንጂ አንዲት የአማርኛ ዘፈን እንዳንሰማ በማለት  “ይህንን ግም አፍ” ከእንግዲህ ሲያዘፍን የተገኘ እርምጃ ይወሰድበታል ብለው ሖቴሎችና ሻይቤቶች ሳይቀሩ አማርኛ እንዳያዘፍኑ ትዛዝ አስተላለፉ። ጠቅላላው የከተማዩቱ ነዋሪ ፈራ። ወዲያው ደግሞ ቀጠሉና በአራተኛው ይሁን በአምስተኛው ቀን የአማርኛ ቋንቋ እንዳይነገር መመሪያ ሰጡ።
በዚህን ጊዜ ነው የከተማዩቱ ኦሮሞ ነዋሪዎች ከሌሎቹ ነዋሪዎች ጎን በመቆም “አይዞአችሁ። እነዚህ ኦሮሞዎች አይደሉም። ምን እንደሆኑም አናውቅም። ተረጋጉ ።” ብለው በቀጥታ ከነዚያ ሰዎች ጋር መላተም የጀመሩት። በከተማዩቱ የኢሳ ብሄረሰብም ይኖራል ብያለሁ። ለገበያ ይመላለስባታል። እነሱም ክልሉ የኛነው ይሉ ነበረና ይህ ሁሉ ሲሆን ለካንስ ኢሳዎች በጥሞና እየተከታተሉ “ምንድናቸው?” ብለው ይጠይቃሉ። “ኦነግ” ይሏቸዋል። “ኦነግ ምንድነው? ምን ያደርጋሉ እዚህ?” “የኦሮሞ ነጻ አውጭ ናቸው ያስተዳድራሉ” ተባሉ።
በመሰረቱ ከጥንት ጀምሮ የኢሳ ብሄረሰብና ኦሮሞ ይጣላሉ። ልማዳዊ አለመግባባት አለ። የኢሳ ብሄረሰብ ዘላን ከብት አርቢ ስለሆነ ሳር ፍለጋ ከብቶቹን ከቦታ ቦታ በሚያንቀሳቅስበት ጊዜ ኦሮሞዎች የሚኖሩበትንም አካባቢ መድረሱ ስለማይቀር፤ የተሰማሩ ከብቶችን ካገኘ እየቀማም እየዘረፈም ከመንጋው ቀላቅሎ ይዞ መሄድ የተለመደ ነገር ነው። ለማስመለስ መሳሪያ ሳይቀር ይመዘዛል። ሰውም ይሞታል።
እና ታዲያ አሁን በማወሳት ከተማ ውስጥ ሕዝቡን መከራ እያበሉ ያሉትን የኦነግ ተዋጊዎች “ይህ ክልሉ የኛ ስለሆነ ለቃችሁ ውጡ” ብለው ሽማግሌ ይልኩባቸዋል። ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ደጅ ታሳድራለች እንደተባለው ወይም ወያኔ አለልን ብለው ወይም ደግሞ ኢሳ ተዋጊ መሆኑን አለማወቅ፤ ማስጠንቀቂያውን ከእቁብ ሳይቆጥሩ ሰዉን ማሸበራቸውን ቀጠሉ። በዚህን ጊዜ ኢሳ ጦርነት ሊከፍት ከየገጠሩ እየተጠራራ በከተማዩቱ ሰፍሯል። እነ ኦነግም በበርካታ የጭነት መኪኖች ሞልተው ላይ ታች ይላሉ። ጥቂት የወያኔ ወታደሮች ከተማው ጥግ ሰፍረው የሚሆነውን ይከታተላሉ። ጣልቃም አይገቡም።
አንድ ቀን ጠዋት ማለዳው ላይ ያቺ ትንሽ ከተማ በቀላል ነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያ ተኩስ ልትፈነዳ ደረሰች። ለሁለት ሰአት አካባቢ ሞቅ ያለ ተኩስ ከተሰማ በሗላ፤ መልሶ ጸጥ ለጥ ረጭ አለ። እስከቀትር ድረስ ሰውም ከቤት አልወጣ ከተማዋ ጭር እንዳለች ዋለና ሗላ ላይ የኢሳ ብሄረሰብ ወዲያ ወዲህ ሲል ሁላችንም ከተሸሸግንበት ወተን የሆነውን እናጠያይቅ ጀመር። አዎ እነዚያ ሰዉን ያምሱት የነበሩ የኦነግ ጂሎች መሬት ይግቡ ሰማይ የደረሱበት አይታወቅም። የሞተው ሞቶ የቀሩት ድራሻቸው ጠፍቷል። ወዲያውኑ በየሆቴሉ በየሻይቤቱ የአማርኛ ዘፈን ይሰማ ጀመር። ሰውም ጮክ ብሎ አማርኛ ያወራ ጀመር። የከተማዪቱ ኦሮሞኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በዚያን ሰሞን ለቀረው ህዝብ ያሳዩት አጋርነትና ተቆርቋሪነት፤ ያሳዩት ወገንተኝነትና አብሮነት የዘር ድርጅት መሪዎች እጅግ ብዙ ሊማሩበት የሚያስችል ክስተት ነበር።
ታዲያ ግጭቱ ከተከሰተ በሗላ ምን ይሆን ትተው የሄዱት፤ በየቢሮው ጥለውት የሄዱ ሰነድ ካለ ምን ይሆን እቅዳቸው አልንና የተወሰንን ሰዎች በየቢሮው ገብተን መበርበር ጀመርን። ያገኘነው አስደንጋጭ ነገር ቢኖር በከተማዋ ነዋሪ የሆኑ፤ ነዋሪው በጠቅላላ የሚያከብራቸው፤ የሚወዳቸው፤ ያገር ሽማግሌዎች የሞተን የሚቀብሩ፤ የታመመን የሚያስታምሙ፤ የተቸገረን የሚረዱ፤ አስራ ስድስት ነዋሪዎች ስም ዝርዝር እንዲገደሉ በቃለጉባኤ ተፈርሞበት ተቀምጧል። ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነፍጠኞች ስምዝርዝር ይላል። የሚደንቀው ደግሞ ከነዚያ ሰዎች አራቱ ኦሮሞዎች ነበሩ።
ያቺ የኢሳ ብሄረሰብ ያስነሳት አጭር ጦርነት የነዚያን ንጹሀን ዜጎች ህይወት ለማትረፍ በቃች።ሕህቡንም ከመራር ሀዘን አዳነችው።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንደነዚህ አይነት በሽተኞችን ይዞ ነው የሚጓዘው። ይህ የዘር ጥላቻ፤ ይህ የዘር ፖለቲካ፤ የወያኔን መሪዎችና መሰሎቻቸውን ለጊዜው ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ይችላል። በረጅም ጊዜ ጦሱ ግን የሚያጠፋቸው ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ያካባተው፤ ያዳበረው አብሮ የመኖር የአንድነትና የመተሳሰብ መንፈስና ባህል ምንጊዜም በውስጡ ያለ በመሆኑ አንድ ቀን እነዚህን የዘር ልክፍተኞች በቃችሁ እንደሚላቸው ጥርጥር የለውም። የኢትዮጵያን ሀብት ዘርፈን የኢትዮጵያን ህዝብ በትነን የራሳችን መንግስት እናቆማለን ብለው ለሚቧችሩ ወዮ ለነሱ ይህ ሕዝብ አንድ ሆኖ በቃ ያለቀን።በመጨረሻዋ ሰአት ወዮ ለዘረኞች!
በስደት በምንኖርበት የባእድ አገር ጽንፈኛ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች ለልጆቻቸው እንዴት ጥላቻን እንደሚያስተላልፉ የሚያመለክት አንድ ገጠመኝ ላክል።ይህንን ታሪክ ያጫወተኝ ሰው ነገሩ ለርሱ ብዙም ክብደት አልሰጠውም። የልጅ ነገር ብሎ እየሳቀ ነው የነገረኝ። እኔ ግን ከልጅ ነገርነቱ ባሻገር ነው የከፋ ነገር የታየኝ። ላንባቢያን ባካፍለው ሁላችንም እንማርበታለን ብየ አሰብኩ።
ሁለት ህጻናት ወንዶች ልጆች እድሜያቸው አስራ አንድ አመት የሆኑ ትምህርት ቤት ተከፍቶ አንድ ክፍል ይመደባሉ። ሁለቱምኢትዮጵያውያን ናቸው። ያንኑ እለት በእፈፍት ሰአታቸው እግር ኳስ ሊጫወቱ እየተሯሯጡ ኳስ ሜዳ ገብተው ጥቂት እንደተጫወቱ ለማረፍ ወደሜዳው ጥግ ሄደው ሳር ላይ ቁጭ እንዳሉ ይተዋወቁና ጎን ለጎን ተንጋለው ወሬ ይጀምራሉ። ከየት እንደመጡ ይጠያየቃሉ። አንደኛው ከኢትዮጵያ አንደመጣ ሲነግረው ሌላኛው ከኦሮሚያ ነው የመጣሁት ይለዋል። ሁለቱም የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጆች ናቸው። ይህ ከኢትዮጵያ ነው የመጣሁት የሚለው ልጅ “ ኦሮሚያ የት ነው” ይለዋል አዲሱ ጓደኛውን።
“ እሩቅ አፍሪካ ውስጥ ነው።” ይመልሳል የኦሮሚያው ልጅ
“ እዚህ አገር ከመጣህ ተመልሰህ ሄደሀል?”
“ አዎ ሰባት አመት የነበርኩ ጊዜ ሄጄ ነበር”
“ እኔም ስድስት አመት የነበርኩ ጊዜ አባቴ ወስዶኛል።ኢትዮጵያ ብዙ ደስ ብሎች አሳለፍኩ…ኦሮሚያ ከኢትዮጵያ በየት በኩል ነው?”
ተጠያቂው ህጻን ኦሮሚያ በየት በኩል ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ከመስጠቱ በፊት “አማራ ነህ?” ይለዋል። ከኢትዮጵያ መጣሁ የሚለው ልጅ ብሄሩንም አያውቅምና “ እኔ አንጃ “ ይላል።
ያም ቀበል ያደርግና “ኢትዮጵያ የአማራዎች አገር ነው። ጥሩ አይደለም። ኦሮሚያ ጥሩ ነው። “ ይላል።
ብዙም አልተግባቡ ወደጨዋታቸው ይመለሳሉ። ይህ ከኢትዮጵያ ነው የመጣሁት የሚለው ልጅ ይህንን ታሪክ ለወላጆቹ ይነግርና “ኦሮሚያ የት ነው አዲስ ጓደኛ አገኘሁ” ይጠይቃል አባትን። አባትም ኦሮሚያ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ አንድ ክልል መሆኑን ያስረዳና የሚኖሩበት አገር ካናዳን እንደምሳሌ አድርጎ ፕሮቪንሶቹን እየጠራ እንደ አንዱ እንደማለት ነው ካለ በሗላ “ሁለታችሁምኢትዮጵያውያን ናችሁ። ወንድማማቾች ናችሁ። ጥሩ ጓደኛ አግኝተሀል እንኳን ደስ ያለህ” ይለዋል።
ልጅ ይህንኑ ካባቱ የተነገረውን በሁለተኛው ቀን ትምህርት ቤት ሲሄድ ለአዲሱ ጓደኛው ያስረዳና በጓደኝነታቸው እንደሚቀጥሉ ይነግረዋል።
ያኛው ህጻን ግን ባልተጠበቀ መልኩ የሚያስከፋ መልስ ይሰጠዋል። “…ኖ!..ኖ! ከንግዲህ አንተ የኔ ጓደኛ አትሆንም አንተ….ነህ ..I hate…..” እያለ ጥሎት ይሄዳል።
በሁኔታው ግራ የተጋባው ልጅ እንደገና ይህንኑ ታሪክ ላባቱ ይወስድና አማራ ምንድነው? ብሎ ይጠይቃል። አባት ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሊገባ አልፈለገም። “ ጓደኛ አልሆንህም ካለህ ምርጫውን አክብር። አትረብሸው። ሌላ ጊዜ በደንብ ስትተዋወቁ ጓደኛ ትሆናላችሁ “ በማለት ልጁን ያጽናናል።
ይህ ቡቃያ ከእናቱ ወይም ከአባቱ የዘር ፖለቲካ ልክፍተኛ እንዳለበት ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ መልኩ ነው የጥላቻ በሽታ ከቤተሰብ ወደ ልጆች የሚተላለፈው፤ የሚጋባው። አሁን በሀገራችን ስልጣኑን የተቆጣጠሩት የሕውሀት መሪዎች የዚህ አይነት አስተዳደግ ውጤቶች ናቸው ብየ ነው የማምነው።
መልካሙ ነገር እነዚህ ህጻናት እኛ ካደግንበት ወይም ሀገርቤት ያሉት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ከሚያድጉበት የተሻለ አለም ውስጥ ስለሆነያሉት፤ ነገ ጠዋት ሁላችንንም ወላጆችን እንደሚያርሙንና እንደሚተቹን የሚያጠራጥር ነገር የለውም፤ ምክንያቱም መንግስታቸው “በቆዳ ቀለምና በዘረኝነት አትታወር” እያለ ነውና የሚያሳድጋቸው።
በዛሬዪቱኢትዮጵያ በወያኔ ዘረኛ ገዢ ቡድን አስተዳደር ስር ያሉት ሕጻናቶቻችን አየሩ ሁሉ በዘር ፖለቲካ ሰበካ፤ በጥላቻ ወሬ፤ በልዩነት ፕሮፓጋንዳ ጩኸት በተወረረበት፤ ንጹህ አየር ተንፍሰው ለማደግ ፋታ ባጡበት ሁኔታ ሬዲዮ፤ ቴሌቪዥን ወያኔያዊ ሀሰተኛ የውንጀላ ድራማና ወሬ ብቻ በሆነበት ዘመን፤በሀሰት፤ በክህደት የሀገርን ታሪክ፤ የህዝብን አንድነት የሚያረክስ ሴጣናዊ ወያኔያዊ የቁራ ጩኸት ብቻ በሆነበት ምድራችን ለሚያድጉት ህጻናቶቻችን የወደፊት እጣፈንታ መጨነቅ ያስፈልገናል።
ባለፉተ ሀያ አመታት ውስጥ በሀገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምናየው አንዳንድ ምልክት ወያኔ የዘራው በሽታ የሚፈልገውን ፍሬ እያፈራለት መሆኑን ያመለክታል። በዘር ተለያይተው የሚደባደቡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማየት ችለናል። ነገ ሀገሪቱን የሚረከቡ ዜጎች ናቸው። ወያኔ እያሳየን ያለው ምን ያህል ትውልዱን እያዘቀጠልን እንዳለ ነው። ተበልጠናል። ልጆቻችንን ለወያኔ የዘረኝነት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ከመሆን ልናድናቸው አልቻልንም። አንድ ሆነው እንዲቆሙ ወላጆች ማስተማር አልቻልንም። ከህብረተሰብም ከትምህርትቤትም በፊት ሰው የሚቀረጸው በቤት ውስጥ ነው።ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን፤ ህብር ህዝብነታቸውን፤ የባህል የቋንቋ የስነልቡና ውህደታቸውን አያት ቅድም አያቶቻው ከባእዳን ወራሪዎች ጋር ተፋልመው ያቆዩአት አንዲት የጋራ ሀገር እንዳለቻቸው፤ ባለመጠራጠር እንዲያውቁ አላደረግንም። ለዚህም ነው ከአንድነታቸው ይልቅ ልዩነታቸው እየጎላ የታያቸው ልጆች ወያኔ መፍጠር የቻለው።ለዚህም ነው የወያኔን ሴራና ተንኮል መረዳት አቅቶአቸው አንዲህ ተባልን እንዲህ ሆን ብለው ሆብለው ለጅምላ ድብድብ መፍጠን የቻሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማየት የቻልነው።
ለራሳችንም የዘር በሽታ ልክፍተኛ የሆን ወገኖች በሽታችንን፤ ህመማችንን፤ዋጥ አድርገን ለልጆቻችን ደግደጉን መንገር አልቻልንም።
የኢትዮጵያ ልጆች እጣ ፈንታ በኛ በወላጆቻቸው ትከሻ ላይ ነው ያለው አንጂ በመርዘኛው የወያኔ ገዢ ቡድን እጅ ውስጥ አይደለም። ወያኔ እየጋታቸው ያለውን የመጥፊያ መርዝ እንዳይውጡ ማድረግ የኛ ፋንታ ነው። እያንዳንዱኢትዮጵያዊ ወላጅ በቤቱ ውስጥ የኢትዮጵያዊያንን እኩልነት ብዛትና አይነት ባህላችንን ቋንቋችንን አንድነታችንን የምድራችንን ልክ ማስተማር ይጠበቅብናል።
ከውጭ ወራሪ ጠላት የከፋ ጠላት ከውስጥ ስለተቆጣጠረን፤ በዘር በሽታ የተለከፍን ሁሉ አማራውም፤ ኦሮሞውም፤ ትገሬውም፤ አፋሩም፤ ሶማሌውም…ሁሉም!…. ካባቶቻችን የወረስነው የመጠላላት በሽታ ካለ ዋጥ አድርገን፤ ነገ አብረው መኖር ስላለባቸው ልጆቻችን፤ ቡቃዮቻችን እናስብ።
የሚቀጥሉት ሰላሳና አርባ አመታት ነገሩ ሁሉ አሁን አንዳለው ከቀጠለ፤ልጆቻችን እርስበርስ ሲናቸፉ፤ ወያኔና ከውጭ በገፍ እያስገቡአቸው ያሉት ባእዳን ባለሀብቶች ይህችን ሀገር ይቆጣጠሯታል። ይቀራመቷቷል። እነዚህ ከውጭ እያስገቡ መሬት የሚያድሏቸው ባእዳን ሁሉም ሀብታምና ትልልቅ መንግስታት ከጀርባ አላቸው። ቻይና፤ ሳውዲአረቢያ፤ አሜሪካ፤ እንግሊዝ፤ ሕንድ፤ወዘተ…ለህዝባቸው የተትረፈረፈ ምግብ፤ ለኢንዱስትሪአቸው ጥሬ ሀብት፤ ለሸቀጣቸው ማራገፊያ ሰፊ ገበያኢትዮጵያ እየተበለተችላቸው ነው።
መሬትን ለማረስ መጀመሪያ ደኑን መመንጠር እንደሚገባ መሬቱን ለባእዳኑ ለመሸጥ መጀመሪያ ወያኔ ዜጎቻችንን በመግደል እየመነጠረ የሚሸጠውን ቦታ እያመቻቸላቸው ነው። በቅርቡ የሱሬ ብሄረሰቦች መቶ ሀምሳ የሚሆኑ ከመሬታቸው ከቀያቸው ውስጥ ተሰብስበው በመትረየስ ተጨፍጭፈው ተጥለዋል። አሁን መሬቱ ተመንጥሯል። ባእዳኑ ገንዘቡን ከፍለው መረከብ ይችላሉ።የኢትዮጵያ ህዝብ ምን አይነት የማደንዘዣ መርፌ እንደወጉት አይታወቅም፤ ተራ በተራ እየገደሉ እስኪጨርሱት ተቀምጦ እየጠበቃቸው ነው።
ዛሬ እንዲጠላሉ አድርገን ያሳደግናቸው ልጆቻችን ነገ ምድራቸውን የተቀራመቷት ባእዳንና ወያኔዎች በሚያቀርቡላቸው ጠመንጃ ስራቸው መዋጋት ይሆናል። የምድሪቱን ቱሩፋትና በረከት በብዙ ሺህ ማይልስ ርቀት ላይ ያሉ ህዝቦች ይኖሩበታል። በብዙ ሺህ ማይልስ ርቀት ላይ የሚገኙ የሀብታም ልጆች ይፋፉበታል ያድጉበታል። ይህችው ምድር ያበቀለቻቸው ዜጎቿ ያልታደሉቱ፤ ይራቡባታል። እርስበርስ እየተታኮሱ ይገዳደሉባታል።በወያኔና መሬቱን በተሸለሙት ሀብታም መንግስታት ወታደሮች ይገደሉባታል።
ልጆቻችንን ከመጠላላት ፖለቲካ እናድን። ለማናችንም አይበጅም። እኛም በሽታው ካለብን ዋጥ አናድርገው። ቀጠሮ የምንሰጠው ጉዳይ አይደለም። ዛሬ!..ዛሬ!..ዛሬ ነው ጊዜው። ፍቅርና አንድነት ያለው ህዝብ ያሸንፋል።የጋራ ጠላታችን ወያኔን አምርረን እንዋጋ።እርስበርስ መጠላለፉ እልቂታችንን ያቀርበዋል።ለመዳን አንድ እንሁን!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar