fredag 8. februar 2013

የጀግና ውሎና ምሽት


ፍቅረ ዮሐንስ
fikireyohanis@yahoo.com
…ትውልድ እድገትህም ኢትዮጵያ ሰሜን ምድር ፣
ከመቅደላ አፋፍ ላይ ከጀግና መፍለቂያ ከፋሲል ግንብ ስር ፣
ስለ ጀግንነትህ ትውልድ ቢመሰክር አንዳች ግን ቀርቶሃል…
ከጥበብ መስካሪው ከአባ ተክሌ እግር ስር ፣
በል ጎንደር ግባና ጀግንነት ክብርህን ስራህን አስመስክር!
ይህ መወድስ ግጥም የኔ እንዳይመስላችሁ፣ በፌብሩዋሪ 2 የኢሳት የገቢ ማሰባሰቢያ የአውሮፓ ቱር የመጀመሪያ በሆነችው ስዊዘርላንድ (ጄኔቫ )በተዘጋጀ ዝግጅት ላይ የቀረበ አስደናቂ ግጥም ነው። ግጥሙ ይህ ብቻ አይደለም ሙሉ ዝግጅቱ ላይ ከገጣሚው አንደበት ብትሰሙት እና እናንተም በአዳራሹ እንደነበረው ታዳሚ ተነስታችሁ ብታጨበጭቡለት እመርጣለሁ፣ ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመጣ በዚህ ቀን የተካሄደው ዝግጅት ዝም የሚያሰኝ እጅን በአፍ የሚያስጭን ነው።
በዝግጅቱ መሃል አንዲት በስዊዘርላንድ ላለፉት አመታት (ረዘም ላለ ጊዜ)የቆየች ሴት እንደነገረችኝ (በስሜት ሆና) “ወጣቱን ወያኔ በላችው” እያልኩ እጨነቅ ነበር አሁን ግን የዓመታት ጭንቀቴ ተፈታ “እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን” ብላኝ ሳልጠብቀው ድምፅ አውጥታ አለቀሰች ምን አይነት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ነው?  በጣም ገረመኝ ለቅሶዋን ለኔም ከኔም ጋር ላሉት ጎረምሶች ጉዋደኞቼ አጋባችብን፣ ማንም ማንንም አያይም፣ ሁሉም በራሱ ስሜት ሆኖ ግማሹ ያለቅሳል፣ ግማሹ የመድረኩን ዝግጅት በግርምት ይከታተላል… ቆዩማ ከመጀመሪያው ልጀምርና ላውራችሁ…
እኔ እዛ ቦታ ስደርስ ልክ ከቀኑ 1ሰዓት ገደማ ነበር (ሰዓት አቆጣጠሩ በአውሮፓ ነው) ሩቅ መንገድ በመግዋዜ ጠዋት እንደነገሩ የቀመስኩዋት ቁርስ ሆዴ ውስጥ አልነበረችም፣ ነገር ግን እጄ ላይ ብስኩት ቢጤ ስለያዝኩኝ ረሃቤን በሷ አስታግሻለሁ። ጄኔቫ – ስዊዘርላንድ ልክ ከቀኑ 1 ሰዓት… ከሌሎቹ በሀገሪቱ ካሉ ከተሞች የተለየ የአየር ንብረት ዛሬ ነበራት; ሌሎቹ ከተሞች በበረዶ ፣በቅዝቃዜና በዳመነ አየር የተሸፈኑ ቢሆኑም አሁን ያለንባት ከተማ ግን መካከለኛ ፀሃያማና መጠነኛ ቀዝቀዝ ያለ ነፋስ-ቢጤ ነበራት፣ ጄኔቫ ለስዊዘርላንድ ሁለተኛ ዋና (የዲፕሎማቲክ) ከተማ ተብላ ትጠራለች፣ ከሌሎች ከተሞች በበለጠ በአንደኝነት ማለት ይቻላል ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት ከተማ ነች።
ለማንኛውም እኔ በደረስኩበት ሰዓት የዝግጅቱ ጥቂት የማይባሉ ታዳሚዎች ከአዳራሹ ውጪ እዚም እዚያም ቡድን ሰርተው ይወያያሉ፣ ይሳሳቃሉ የፕሮግራሙን መጀመር በጉጉት እንደሚጠብቁ ከሁሉም አይን መረዳት ይቻላል፣ እኔም ከጉዋደኞቼ ጋር ቡድን ሰርተን ለወትሮው በትምህርት፣ በሥራ፣አልያም በተለያዩ ምክንያቶች እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ስብስብ ስለማናገኘው ሁሉም ነገር በናፍቆት ነበር የሚከናወነው ።መግቢያ በሩ በስተቀኝ ሰንደቅ አላማችን፣ በስተግራ ደግሞ በሀገሩ ባንዲራ አሸብርቆአል፣ ከበሩ አናት ላይ ደግሞ ልዩ የሆነ ግራፊት ፅሁፍ በእንግሊዘኛ ተፅፎ ተሰቅሎአል፣ ፅሁፉን እንደነበረ ለማስቀመጥ ቢከብድም መንፈሱ ግን “Free All Ethiopians, Christians & Muslims” እንደሚል በምርምር ደርሼበታለሁ።
የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ለወራት የደከሙለትን ቀን በመልካም ለማስተናገድ ሽር-ጉዱን ተያይዘውታል፣ በቅድሚያ ከአስተባባሪዎች አንዱ ባጅ አምጥቶ ዝግጅቱ ላይ በቅርበት መስተንግዶ የሚሰጡና የተለያዩ የስራ ድርሻ ላላቸው ሰዎች ሰጣቸው። እኔም ከነዚህ አንዱ ነኝና ይህ ባጅ ደርሶኛል፣ እንግዲህ ይህ ከላይ ያነበባችሁት መወድስ-ግጥም ከባለባጆቹ አንዱ በተሰደሩ ቃላትና ውብ በሆነ ድምፀት አንብቦ ታዳሚውን ያስደመመው። በአዳራሹ ቀድመው የገቡ ታዳሚዎች በሙሉ እንዲወጡ በዕለቱ የተመደቡት የስዊዘርላንድ ዜግነት ያላቸው የፀጥታ አካላት አዘዙ፣ የአዳራሹን ዙሪያ-ገብ አገላብጠው ፈተሹት፣ ታዳሚውም ሲገባ እንዲሁ፣ እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ነገር የወያኔ/ህወሓት ጉዳይ ነው፣ ይህ ቡድን መጥፊያው ቀርቦ ነው መሰለኝ አጥፍቼ ካልጠፋሁ እያለ ነው፣ የሀገር ቤቱ ሳያንሰው በአውሮፓና በአሜሪካ እንዲሁም በግፉ ምክንያት በስደት ሆነው የሚቃወሙትን ጀግኖች ካልገደልኩ ሞቼ እገኛለሁ እያለ ነው፣ ወያኔ ያልገባው ቢኖር “ታጋይ ቢሞትም ትግል እንደማይሞት” ነው። ለማንኛውም ሰርጎ-ገብ የወያኔ ልዑካን ቢኖሩ እንኩዋን መላወሻ እንዳያገኙ ተደርጎ የፀጥታው ሁኔታ ተጠብቆ እስከመጨረሻው የዝግጅቱ ፍፃሜ ድረስ ዘልቆአል።
ባጅ የለጠፉትና ከበርን የመጡት ወጣቶች ከመደበኛ የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ጀግኖቹን ከመጠበቅ አልፎ ታዳሚውም ምቾት እንዲሰማው አድርገውት ነበር፣ ምናልባት እንዲህ አይነቱ ቅንጅት በሌሎቹም ሀገራት በቀጣይ ቢሰራበት ጥሩ ልምድ እንደሚሆን ሳልጠቁም አላልፍም።
ይህ ሁሉ ከሆነ ከጥቂት ደቂቃዎች በሁአላ ጀግኖቹ የመምጣታቸው ዜና ተሰማ፣ ወዲያው ከበርን የመጡት ወጣቶችና አጠቃላይ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ከመግቢያው ጀምሮ ግራና ቀኝ በእናት ሀገር ባንዲራ ከበው በጀግንነትና በክብር ዜማ ተቀበሉዋቸው፣ ጋዜጠኛ ገሊላ መኮንን እና አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ። እውነቱን ለመናገር ሁለቱንም በቴሌቪዥን መስኮት ካልሆነ በቀር በአካል አይቻቸው አላውቅም ነበር… እድሜ ለኢሳት።
ዜማው አቀባበሉ እልልታው በእውነት አስገራሚ ነበር፣ ደስታ ግርምት እንባ… ሁሉም ስሜት እኔም ታዳሚውም ላይ የተንፀባረቀ ነበር፣ ሳላውቀው ሳግ ተናነቀኝ ለጊዜው ወደሁዋላ ሸሸት አልኩኝ ስሜቴን እንደምንም ተቆጣጥሬ መልሼ ተቀላቀልኩ። ውስጥ ሲገባ አዳራሹ አንዳች ስሜት ያጭራል… ኢትዮጵያ… ኢትዮጵያ… ይህን ስሜት በዘመኑ እድለኛ ሆኖ ኢሳት በሁሉም ልብ ውስጥ መፍጠር መቻሉ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በአንድ ላይ ማየቴ ኢሳትን ለፈጠሩ ጀግኖች እድሜ ይስጥልኝ ብዬ ዝም አልኩኝ።
የመድረክ መሪው የፕሮግራሙ ተጀምሮአል ድምፁን አሰምቶ ሁሉም በተዘጋጀለት ቦታ እንዲቀመጥ ተናገረ ሁሉም እንዲሁ ሆነ፣ ጋዜጠኛ ገሊላ እና ጀግናው አክቲቪስት መድረክ ላይ በተዘጋጀላቸው ቦታ ተቀመጡ፣ የቤተክርስትያን አባቶችና የእስልምና እምነት ተወካይ እንደወጉ ፀሎትና መልእክት ካስተላለፉ በሁዋላ ከመድረክ የሃሳብ አለኝ ድምፅ ተሰማ፣ ታማኝ ነበር፣ እኛ እዚህ መቀመጥ የለብንም ከህዝቡ ጋር ከታች እንሆናለን… ታዳሚው በሙሉ አጨበጨበ… ከመድረክ በታች ቦታ ተዘጋጀ… ወረዱ… አሁን ትዕይንቱን ፊት ለፊት ማየት ይችላሉ ።
ብቻ ሁሉም ዝግጅት በተያዘለት ተራ ተስተናገደ፣ ሶስት ገጣምያን የግጥም ስራዎቻቸውን አቀረቡ፣ ቅድም መግቢያዬ ላይ የቀነጨብኩት መወድስ-ግጥምም አንዱ ነበር ታዳሚውን በስሜት ሳግ ያተናነቀ፣ በየመሃሉ ያጨበጭባሉ፣ ግጥሙ እንዳለቀ ሁሉም ከመቀመጫው ተነስቶ ዳግም እጆች ከእጆች ተላጉ… ምስጢራዊና እምቅ መወድስ… በመቀጠል አርቲስትና ጋዜጠኛ ገሊላ መኮንን ያቀረበችው የመድረክ ተውኔትም የታዳሚውን ስሜት የቀሰቀሰ ዝግጅት ነበር… በአርቲስቱዋ ያልተነሳ የኢትዮጵያ ዘመን አልነበረም… የጥንቱ ዘመን፣ መካከለኛው ዘመን እና አሁን… ያሁን ገዢዎቻችን የወደቀ ሞራል ከይሲ አስተሳሰብና ጎጠኝነት እንዲሁም የቀደሙትን ጀግንነት ክብር ኢትዮጵያዊነት… ብቻ በጣም ግሩም ሌላ ምን ይባላል?
አሁን ተራው የጀግናው ነው፣ በሌሎች ሃገራት በአውስትራሊያ እና በደቡብ-አፍሪካ እንዳየነው ስሜትን ሰቅዞ የሚይዝና ከዘመን ዘመን የሚያሻግር ከአንድ የታሪክ ምዕራፍ ወደ ሌላ ይዞ የሚነጉድ፣ በሙሉ ቪዲዮ መረጃዎች የተደገፉ እውነታዎች፣ የኢትዮጵያ አበይት እምነቶችና በአብሮነት በመከባበር የዘለቁት ክፉና መልካም ዘመን፣ የአሁን መሪዎቻችን ግፍ፣ ውሸትና ቅጥፈት እንዲሁም አምባገነንነት፣ ባለፉት ቅርብ የሚባሉ ጊዜያት በስደት ላይ ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሱት አሳዛኝ ግፎች፣ እንደወጡ መቅረት፣ ብቻ እየደረሰብን ያለው መከራ አያልቅም አይደል? ሁሉንም ጀግናው ዳሦታል… ይህንንም ምንም አልል… እጄን በአፌ ጨኘ ዝም…
ቀጣዩ ዝግጅት እራት ነው፣ እኔም ከጉዋደኞቼ ጋር ገበታው ላይ ተሰይሜአለሁ፣ እንጀራ፣ ወጡ ብዙ አይነት፣ ጠጅ፣ ቢራ፣ ወይን፣ ለስላሳ-መጠጦች፣ እንደመድረኩ ዝግጅት ሁሉ ጉዋዳውም ሙሉ ነበር፣ ይህ የዛሬው የጄኔቫው ዝግጅት ለጀግናው የመጀመሪያው ነው፣ ቀጣይ ባለተራዎችም ከዚህ የጀግና አቀባበልና የኢሳት ቀን ትምህርት እንደሚወስዱ ተስፋ አለኝ። ከእራት በሁዋላ ቅልጥ ያለ የሙዚቃና የመዝናኛ ዝግጅት ነበር፣ የቀረ ሰው አልነበረም፣ ወጣት አዋቂ እናቶች አባቶች ሁሉ የውዝዋዜው አካል ነበሩ ኢትዮጵያዊነት እንዴት ያምራል ባካችሁ? ይበላል፣ ይጠጣል፣ ሁሉም ይዝናናል፣ በግሩፕ በግሩፕ ሆነው የሚጨፍሩ፣ ተሰብስበው የሆድ የሆዳቸውን የሚያወሩ ሁሉም በየአይነቱ ነበር–ያልተዳሰሰ የብሄረሰቦቻችን ሙዚቃ ያለ አይመስለኝም።
ከጀግኖቹ ጋር ፎቶ ለመነሳት ያለው ትርምስ፣ አብሮ ለመወዛወዝ ያለው ፍትጊያ፣ብቻ ያስቀናል በዚህ ሁሉ ላይ ግን ባጅ የለጠፉት ወጣቶች ያላሰለሰ ክትትልና ቅንጅት ከመደበኛ የፀጥታ አካላት ጋር ያላቸው ቁርኝት ለሁሉም እንደልቡ እንዲዝናና ምቾት ሰጥቶ ነበር—ምስጋና ይገባቸዋል።
ሌላው ጨረታው ነው፣ ለጨረታው የቀረበው “የምኒሊክ ጥቁር ሰው ” ስነ-ስዕል ሲሆን ከተለያዩ ካንቶኖች (ከተሞች) በመጡ ሰዎች ጨረታው ሲካሄድ ከቆየ በሁዋላ ብዙዎቹ እየተረቱ ዙሪክ፣ ጄኔቫና፣ በርን ከተሞች ቀሩ፣ መካከል ላይ ዙሪኮች በሙሉ ወደመጡበት መሄድ ነበረባቸው፣ ምክንያቱም የተኮናተሩት መኪና ሰዓቱ ስለደረሰ፣ የሚገርመው መንገድ ላይ ሆነው ሁሉ እየተሳተፉ ነበር። በለንደን፣ በጀርመን፣ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ድጋፍ እንዲሁ ከየአቅጣጫው በስልክ… ሌላው በጣም የገረመኝ የኢካድፍ (ECADF) ጉዳይ ነው፣ ይህን ስዕል ያበረከቱትና ለጨረታው ግብአት ጥቂት የማይባል ገንዘብ ሲለግሱ ለነበሩት ጠቅላላ የሩሙ አባላትና አድሚኖች ምስጋና ይገባቸዋል። የጨረታው ፉክክር በስተመጨረሻ በበርንና በጄኔቫ መካከል ሆኖ ለብዙ ሰዓት የቆየ ቢሆንም ሁለቱም አሸናፊዎች ናቸው በሚል ብሂል ስእሉ ግን ለበርን እንደሚሰጥ ተነግሮ የጨረታው ዝግጅት በጥሩ ሁኔታና ውጤት ተጠናቀቀ።
አሁንም ውዝዋዜው ሙዚቃው ቀጥሎአል አሁን ሰዓቱ ከሌሊቱ 2 ሰዓት በአውሮፓ አቆጣጠር… የፕሮግራሙ ፍፃሜ… የኢሳት ምሽትና የጀግና ውሎ በጄኔቫ በድል ተጠናቀቀ… ድንቅ።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar