tirsdag 5. februar 2013

“አቦይ ስብሀት ምን እያሉ ነው?!”



አቶ ስብሀት ነጋ ባለፈው ከኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንደተለመደው ብዙ ሊያነጋግሩ የሚችሉ ነገሮች ያሉት ነው። ያም ሆኖ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ደግሞ ቅጥፌትና ሴራ የተሞላበት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይህም እዚያው ጋዜጣ ላይ “እኛ ኢትዮጵያውያን የአስተሳስብ ድህነት አለን” ብለው እንደተናገሩት “የፈለኩትን ብል ምንም አያመጡም” ብለው ሊሆን ይችላል።
አቶ ስብሀት ነጋ በዓረና አባላት ላይ በትግራይ ስለሚደርሰው ከፍተኛ ወከባ፣ እስር፣ አፈናና ግድያ የሚነገረው እንዴት ያዩታል ተብለው ሲጠየቁ የመለሱት መልስ የሚያዛዝን ነው።
ከሁሉም የሚገርመው “ህወሀት ዓረናን ይቀናቀነኛል ብሎ የሚፈራው አይደለም። ምንም ወከባም የደረሰባቸው የለም።” ማለታቸውን ነው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት አንድ እውነት ህወሀት አንድን ተቃዋሚ ለማጥፋት የሚነሳው ይቀናቀነኛል፣ ለህልውናዬ ስጋት ይፈጥራል ብቻ ብሎ አይደለም፤ በተፈጥሯዊ ባህሪው ልዩነት የሚባል ነገር ማየትና መሸከም ስለማይወድ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን የህወሀት ልደት በዓል 35ኛ ዓመት ሲከበር የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስተር አቶ መለስ ዜናዊ “በትግራይ ውስጥ ምንም ዓይነት ክፍተት፣ ምንም ዓይነት ስንጥቅ መኖር የለበትም። እነዚህ እሾሆች፣ እነዚህ የጭቃ ላይ እሾሆች መጥፋትና መወገድ አለባቸው” ብለው መናገራቸው ነው። ይህ ንግግር ሲደረግ አቦይ ስብሀት እዚያው ቁጭ ብለው ያዳምጡ ነበር። ስለዚህ በዓረና መኖር ህወሀት የማይሰጋ ከሆነ አቶ መለስ
በዚያን ቀን ያን ያህል የከረረ ንግግር ማድረግ ለምን አስፈለጋቸው?!

ህወሀት በዓረና ስጋት ከሌለው ፓርቲው እንደተመሰረተ ዓረናን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል የሚያሳይ ባለ አስራ ስምንት ገፅ ያለው ፅሁፍ አዘጋችቶ ለአባላቱና ታች ለመቃቅሩ ማህተም ባለው ደብዳቤ ማሰራጨት ለምን አስፈለገው?! ህወሀት በዓረና ምንም ዓይነት ስጋት ከሌለው በመንግስት መስራያ ቤት ያሉ የመንግስት ሰራተኞች የህወሀት አባላት የሆኑና ያልሆኑ ተለይተው እንዲታወቁ የሚገልፅ ደብዳቤ በሲቪል ሰርቪስ ቢሮ በኩል ማሰራጨት ለምን አስፈለገው?!
የዓረና አባላት ከስራ በየጊዜው ይባረራሉ፣ ወደ አዲስ አበባና ወደሌሎች ክልሎች ሄደው ለመኖር የተገደዱ በጣም ብዙ ናቸው። ከእነዚህ ወስጥ ሴቶችም ይገኙበታል። የዓረና አባላት በልማት ፓኬጅና በእርዳታ እንዲታቀፉ አይደረግም። ሌላው ሁሉ ይቅር አረጋዊ ገብረዮሐንስ
የተባለው አባላችን ለምርጫ በሚወዳደርበት ጊዜ ለምን ተገደለ? ባለፈው ሳምንት እንኳ በሁመራ አከባቢ መደባይ በሚባለው የገጠር ከተማ የነበረው ፅሕፈት ቤታችን በቡልዶዘር እንዲፈርስ ተደርጓል። የፓርቲው ንብረት ወደ ቀበሌ ተወስዷል። ይህ ሁሉ የሚሆነው
እርስዎ እንዳሉት “ዓረና የተቆጣን ህወሀቶች ስለሆን” ይሆን ሌላው “ዓረና በፕሮግራም ደረጃ ከህወሀት ምንም ልዩነት የለውም።” በለዋል። እስኪ የእናንተን ፕሮራም እና የእኛ ፕሮግራም ምንና ምን እንደሆኑ ለመየት እንዲቻል በጋዜጣ ጎን ለጎን እናውጣው! ለነገሩ አቦይ ስብሀት ለማንበብ የሚሆን ጊዜ ስለሌላቸው የእኛ ፕሮግራም ያውቁታል ብዬ አልገምትም። እርግጥ ነው ዓረና ኢዮጵያዊነትን ለድርድር የሚያቀርበው ጉዳይ አይደለም፤ የትግራይ ህዝብ ችግር
በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ለመፍታት ነው የሚታገለው። እንደ ህወሀት በትግራይ ህዝብ ህይወት ላይ ፈፅሞ አይደራደርም።
የትግራይን መሬት አሳልፎ የሚሰጥም አይደለንም። እኛ እንደ ህወሀት በትግራይ ህዝብ ስም እየነገድን የትግራይ ህዝብ ሳይበላ እንደበላ፣ ሳያልፍለት እንዳለፈለት ተደርጎ እንዲታይ፣ በስጋት እንዲኖር አናደርግም። የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢዮጵያውያን ወንድሞቹ በእኩልነትና በፍቅር ተከባብሮ እንዲኖር ነው የምንታገለው። እኛ የምንታገለው ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት፣ ህዝቦቿ ሁሉ እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ፤ የፖለቲካና የማህበራዊ ሁኔታ የሚያረጋግጥ ስርዓት ለማምጣት ነው። የድሮ ስርዓቶችም እንዲመለሱ፣
ተመልሰውም በህዝቦች ላይ ተጨማሪ ግፍ እንዲፈፅሙ የምንፈቅድ አይደለንም። “ባንዴራችን አረንጋዴ ብጫ ቀይ ነው፤ ስርዓታችን ራሳችን በራሳችን ለማስተዳደር የሚስችለን ስርዓት ዓረና ገረብ ነው። ራሳችን በመረጥነው እንጂ በንጉሱ አንገዛም” የሚለው የቀዳማይ ወያኔ መፈክር ለዓረና እንደመነሻ ሆኖ አገልግለዋል። ዓረና ማለት በራሱ ራስ በራስ የማስተዳደር ፅንሰ ሀሳብ ያለው “አንድ ሆነን እንነሳ፣ ተደራጅተን መብታችንን እናስከብር” የሚል ትርጉም ያለው ነው። ዓረና፣ ዴሞክራሲ ለሚለው ቃል ልከኛ ትርጉም የሚሰጥ አገርኛ ቃል ነው።
ሌላው የአቶ ስብሀት ነጋ ስህተት ሁሉም ዓረና ውስጥ ያለው ከህወሀት የተባረረ “ህወሀት” ነው ማለታቸውን ነው። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ዘጠና በመቶ የሚሆነው የዓረና አባል ወጣት ነው። ይህ ወጣት ደግሞ ፈፅሞ የህወሀት አባል ሆኖ የሚያውቅ አይደለም።
ደግሞስ ህወሀት የነበረ ሰው ቢሆንስ ምን ችግር አለው! “ያለሁበት ሁኔታ የተሳሳተ ነው። የህወሀት መንገድ የሚያዋጣ አይደለም” ብሎ ካመነና አቋሙ ከቀየረ ምንድ ነው ችግሩ? እነ ገብሩ አስራት፣ እነ አውዓሎም ወልዱ፣ እነ አረጋሽ አዳነ፣ እነ አስገደ ህወሀት የነበሩ ናቸው።
እነዚህም ቢሆን ግን ራሳቸው ናቸው ፓርቲው አያስፈልገንም ጥለው የወጡት እንጂ የተባረሩ አይደሉም። ለዚያውም ለምን እኛን ትታችሁ ትሄዳላችሁ ተብለው እየተለመኑ፤ አትሂዱብን ተብለው በለቅሶ እየተለመኑ ነው ድርጅቱን ጥለው ወጡት። በመሰረቱ አቶ ስብሀት ነጋ
ከህወሀት የወጣ ሁሉ ዓረና ነው የማለት ዝንባሌም ያላቸው ይመስላሉ። ይህን እንድል ያደረገኝ “ተወልደ ወልደማርያምም ከእነርሱ ጋር ነው” በማለታቸው ነው። አቶ ተወልደ ወልደማርያም ዓረና አይደሉም፤ ዓረናም ሆነው አያውቁም። ዓረናን ከመሰረቱና ከመጀመሪያ ጀምሮ ከነበሩ ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ፤ አንድ ቀንም አቶ ተወልደን አይቻቸው አላውቅም። እንግዲህ አቦይ ስብሀት ከየት አምጥተው አቶ ተወልደ ዓረና ውስጥ እንደጨመሩት እራሳቸው ናቸው የሚያውቁት።
እኔስ የገረመኝ፤ (መቼም የአቦይ ስብሀት ነገር ሁሌም የሚገርም ነው) ስለመደብ ፖለቲካ የሰጡት ትንተና ነው። እኔ አቦይ ስብሀት ኮሚኒስት ናቸው ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ምክንያቱም ስለኮሚኒዝም ሲያወሩ ሰምቼ ስለማላውቅ ነው። አሁን ግን “ክላስ ቤዝድ
ያላደረገ ፓርቲ በዓለም ላይ የለም። አሁን አሜሪካ ክላስ ቤዝድ ነው፤ ለእኛ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ነው። የአሜሪካው ሪፐብሊካን ፓርቲ የሀብታሞቹ ነው። ዲሞክራት ደግሞ የመካከለኛው መደብ ነው። ስለዚህ መካከለኛውና የላይኛው ነው የተወከሉት።” ሲሉ ጊዜ የኤፈርት የበላይ ሀላፊ እንደነበሩ ሳስታውስ ተውኩት እንጂ “ኦ አንጋፋው ኮሚኒስት!” ልላቸው ፈልጌ ነበር።
መቼም ይህ አተናተናቸው ግራ ዘመም የሆነው የኮምኒዝምን ርዕዮተ ዓለም ቤዝድ ያደረገ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ይህ “ሁሉም ፓርቲ በመደብ ነው የሚመሰረተው” የሚለው ነገር እውነትነት ያለው አይመስለኝም። እውነት እንዲሆን በጣም የተለጠጠ ነገር ይመስላል እንጂ።
ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar