ቅኝ ገዥዎችን በማሳፈር በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ነጻነቷን ጠብቃ የኖረችውና በባርነት ስር ለቆዩ ሀገራት ፋና ወጊ የሆነችው ውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ዛሬ በሀገር ውስጥ ወራሪ በሆነው ህወሃት/ወያኔ መዳፍ እጅ ገብታ በሁሉም ረገድ ከኢኮኖሚ እስከ ሰበአዊ መብት አያያዝ በአለም የመጨረሻዋ የሰው ልጅ መብት ረገጣ የሚፈጸምባት ተስፋ አልባ ሀገር ተብላ ተመድባ ትገኛለች።
ይህችው የቀድሞዋ ኢትዮጵያ በክብርና በኩራት የአፍሪካ የነጻነት ፋናወጊ ተብላ የሚነገርላት፤ በዚህ ዘመን በባርነት አረንቋ እየኖረች፣ ህዝቧ የነጻነት ያለህና የትውልድ የድረሱልኝ ጥሪ ኤሎሄ ለወጣት ልጆቿ እያቀረበች፣ እየተማጸነች አለች።
ይህን ተከትሎ በሁሉም ግንባር ሀገር በቀል ወራሪ ህወሃት/ወያኔን ታግሎ ለማስወገድ እየተደረገ ያለው ትብብር የሚበረታታ ቢሆንም የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ ና የአንድ ዘር የበላይነት ርዕዮተ ዓለምን አስወግዶ ነፃነት ከናፈቀው ህዝብ ጎን በመሰለፍ በሀገራችን የሰላም አየር በሁሉም ከተሞች እንዲሰፍን ለሚደረገው እልህ አስጨራሽ ጉዞ የምናደርገው እገዛ በቂ ነው ብለን አናምንም።
ትውልዱ ለውጥ አያመጣም በሚል እስከአሁን የተደላደለውን ወያኔ፤ ከመንበሩ ፈንቅለው ሊጥሉት ዛሬ ራሳቸውን መሰዋእት ለማድረግ ስማቸው ከመቃብር በላይ ሆኖ፣ በታሪክ ማህደር ኢትዮጵያዊ ገድላቸው እንዲቀለምላቸው ቆርጦው የተነሱት የህዝባዊ ሃይል ታጋዮች ፤ የእማማ ኢትዮጵያን እንባ በእንባቸው ሊጠርጉ መከራና ስቃይን መርጠው መሰደዳቸውን ሰሞኑን በድጋሜ አስታውቀዋል።
ህዝባዊ ሃይሉ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ኢትያጵያዊነት እንደ ሸቀጥ የተሸጠበት የክፉ ቀን ውረደት ላይ እንገኛለን እና ከገባንበት የውረደት አዘቅት የመውጫ ጊዜው አሁን ነው፤ ነገም ሳይሆን ዛሬ ነው። ዛሬ በሃገራችን በወያኔ አምባገነናዊ እብሪት ያልታፈነ፣ ያልተዋረደና ያልተዘረፈ የሃገሪቱ ዜጋ አይገኝም። የወያኔ ሹማምንት በሃብት ላይ ሃብት፤ በድሎት ላይ ድሎት ሲጨምሩ፣ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እጣ ፈንታ ግን መፈናቀል፣ መሰደድ፣ መንገላታት፣ መታሰር፣ መደብደብና መገደል ሆኗል” ብለዋል ። ታዲያ እኛ ምን እንጠብቃለን?
ሀገራችን ሀገር ሆና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ግንቦት 7 ለፍትህ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ከማንኛውም ሃይል ጋር ሆኖ ለድረሱልኝ ሀገራዊ ወገናዊ ጥሪ ደራሽ በመሆን በዛች ሀገር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወያኔን በማስወገድ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታን ለማምጣት አምርሮ በመስራት ፍትህና ነፃነትን ከተጠማው ሕዝብ ጋር አብሮ ሊታገል ቃል በመግባት ለጥሪው ምላሽ ይሰጣል፡፡
የማንኛውም የፖለቲካ/የሲቪክ ማህበራት እንዲሁም ወጣቱ፤ በተለይም አደገኛ በረሃዎችንና ባህሮችን በማቋረጥ ለመሰደድ ልብህ እየከጀለ ያለው የሃገራችን ወጣት ሆይ! የመተባበሪያው ጊዜ አሁን ነው። በውርደት እስከ መቼ ? ማንስ መጥቶ ሊታገልልን ይችላል? ስለዚህ በከንቱ ክቡር ህይወትን ከማጣት ስደትን አቁሞ ዘላለማዊ ክብር ወደ ሚያሰገኝለት የትግል ጥሪ ይቀላቀል ዘንድ ግንቦት 7 ንቅናቄም ጥሪውን ያቀርባል።
በርግጥም ነው ድሎት ሳይሆን የህዝብ ስቃይ ጣርን፣ የሀገር ውርደትን ማየት አላስችል ያላቸው የህዝባዊ ሃይሉ የቁርጥ ቀን ወጣቶች፤ የጥቁር ደም ጥቁር አፈር የሰራቸው የአበው ልጆች የውርደትን ወላፈን፤ በማይቆምና በሚያቃጥል የትግል ወላፍን ሊመክቱት፣ ሊያስወግዱት፤ ተራራ፣ ጋራ ሸንተረሩን መርጠው ወያኔንን በሚገባው ቋንቋ ሊያናግሩት ሊጋፈጡት ቀናትን እየቆጠሩ ነው።
የህዝብ ልጆች የከፈሉትና ወደፊትም የሚከፍለው ውድ መስዋእትነት የሌላ አምባገነናዊና ግፈኛ ሥርዓት መቋቋሚያ እንዳይሆን ትግሉ የሚጠይቀውን ማንኛውንም ተግባር በተናጠል ይሁን በ ጋራ በመሆን መሰዋእት በመክፈል አብሮ መስራት የግድ ነው ሲል ግንቦት 7 ንቅናቄም ያምናል።
አምባገነኖች መውደቂያቸው ሲደርስ ሁሉም ነገር በቁጥጥራቸው ሥር ያለ ለማስመሰል መቅበጥበጣቸው የተለመደ ነው። የወያኔም መቅበጥበጥ ምክንያቱ መሠረቱ እየተናደ በመሆኑ ነው። ቢቻለው የተፈጥሮ ቀመርን ሳይቀር በሱ መልካም ፈቃድ የሚከናወን መሆኑን ብናምለት ደስታው ነው። ይህ የሁሉም አምባነኖች የመውደቂያ ወቅት መለያ ባህርይ ነው።
ስለዚህ ወያኔ ከሥልጣን ሳይባረር አንዳችም በጎ ለውጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ማሰብ አይቻልም። ስርአቱ ከገባበት የምቾት ማጥ ውስጥ በስብሶ ስለተቀመጠ ከቶ ጀሮዎቹ ለሰላማዊ ጥሪ ጮኸት የተደፈኑ ስለሆኑ፤ እያንዳንዷን ደቂቃ ሳንዘናጋ በንቃት ሁሉንም የተቃዋሚ ሃይላትን በማስተባበር ትግሉን የማቀጣጠያ ሰአት ላይ ነን።
እኛ ግንቦት 7 ለፍትህ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ከማንኛውም ሃይል ጋር ሆነን ለድረሱልኝ ሀገራዊ፣ ወገናዊ ጥሪ ደራሽ በመሆን፤ በዛች ሀገር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወያኔን በማስወገድ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታን ለማምጣት አምርሮ በመስራት ፍትህና ነፃነትን ከተጠማው ሕዝብ ጋር በመቆም ለመታገል ዝግጁ መሆኑን ዛሬም ያሳውቃል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar