onsdag 27. februar 2013

ኢትዮጵያዉያን የእስልምና እምነት ተከታዮች ዋሺንግተን ዲሲ ዉስጥ ታላቅ የተቃዉሞ ሰልፍ አካሄዱ



ባለፈዉ ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓም ዩናይትድ ሰቴትስ አሜሪካ ዉስጥ የሚኖሩ ትዮጵያዉያን የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ በወንድሞቻቸዉና በእህቶቻቸዉ ላይ በማድረስ ላይ ያለዉን ግፍና መከራ በመቃወም  ዋይትሀዉስ ፊትለፊት በሚገኘዉ ላፋየት ፓርክ ዉስጥ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸዉን ዋሺንግተን ዲሲ ዉስጥ የሚገኘዉ የግንቦት ሰባት ድምጽ ዘጋቢ በላከልን ዜና ገለጸ። በዚህ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነጻነት የሚታገሉ ኃይሎች በብዛት በተሳተፉበትና ፕሬዚዳንት ባራክ አባማ በሚወጡበትና በሚገቡበት ዋነኛዉ የአሜሪካ ቤተመንግስት በራፍ ላይ በተደረገዉ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የሐይማኖት አባቶች፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤ የሲቪክ ድርጅቶቸ ተወካዮችና ብዛት ያለዉ የዲሲ፤ የቨርጂኒያና የሜሪላንድ ነዋሪ ህዝብ ተገኝቷል። ሰለማዊ ሰልፉ ከፍተኛ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የነገሰበትና የወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለዘመናት ተከባብሮ የኖረዉን የእስላሙንና የክርስትያኑን ህብረተሰብ ለማጣላት የሚያደርገዉን ሙከራ ያከሸፈ እንደነበር ዘጋቢያችን አክሎ የላከልን ዜና ያስረዳል። በዕለቱ ሰልፈኛዉ ይዞ ከወጣዉ መፈክሮች ዉስጥ “እስላሙና ክርስቲያኑ አንድ ነዉ”  ፤ ‘’የእስላሙ መብት ሳይከበር የክርስቲያኑ መብት አይከበርም”  ኡስታዝ አቡበከር እኛ ነን” የሚሉና ሌሎችም የወያኔን አላማ መክሸፍ የሚጠቁሙና ጠንካራ መልዕክት ያዘሉ መፈክሮች ይገኙበታል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተለያዩ ሰዎች ንግግር ያደረጉ ሲሆን በተለይ የእስልምና እምነት ተወካይ፤የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን አባትና አንድ ከኢትዮጵያ ከመጣ ሳምንት ያልሞላዉ ወጣት የእስልምና እምነት ተከታይ ያደረጉት ንግግር የብዙዎችን ስሜት የኮረኮረና ቀልብ የሳበ ነበር። ሁለቱ የሐይማኖት መሪዎች ባስተለላፉት መልዕክት ዉስጥ በኢትዮጵያዊነት የምንጋራቸዉ ብዙ እሴቶች አሉን ስለሆነም በሐይማኖት ተለያይተን የወያኔን ፍላጎት አናሟላም የሚል ጠንካራና የኢትዮጵያዉያንን ማንነት በግልጽ የሚያሳይ መልዕክት ይገኝበታል።
በየሳምንቱ ቃሊቲ ድረስ እየተጓዘ የትግል ጓደኞቹን ሲጠይቅ እንደነበረ የተናገረዉ ከኢትዮጵያ የመጣዉ ወጣት ደግሞ በእስር ላይ የሚገኙት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴ አባላት ትልቅ ጭንቀት መታሰራቸዉና በወያኔ ወታደሮች መሰቃየታቸዉ ሳይሆን የእነሱ ትልቅ ጭንቀትና ስጋት ይህ የተጀመረዉ ትግል እንዴት ከግቡ ይደርሳል የሚለዉ ጥያቄ መሆኑን ተናግሯል። ይሄዉ ወጣት ንግግሩን በመቀጠል በቅርቡ ወያኔ ክርሰቲያኑንና እስላሙን ህብረተሰብ ለማደናገርና  የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርሱ እንዲጣላ ሆን ብሎ በሰራዉ “ጅሀዳዊ ሃረካት” በሚባል  የማታለያ ወጥመድ ዉስጥ ኢትዮጵያዉያን ተሳስተዉ እንዳይገቡ የትግል ጓደኞቹ ከእስር ቤት ያሰተላለፉትን መልዕክት ለሰላማዊ ሠልፈኛዉ አስተላልፏል። በመጨረሻም ሰላማዊ ሰልፈኛዉ ለአሜሪካ ህዝብ፤ ለአሜሪካ ኮንግሬስ፤ ለዋይትሀዉስና ለአሜሪካ ህዝብ መልእክቱን ካስተላለፈ በኋላ ሳንለያይ እጅ ለእጅ ተያይዝን ይህንን የጀመርነዉን ትግል ከግቡ እናደርሳለን የሚል መልዕክት በማስተላለፍ ወደየቤቱ ሄዷል።
  • facebook
  • google_buzz
  • twitter
  • rss
  • print
  • bookmark
  • email

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar