fredag 15. februar 2013

ሟች አና ገዳይ ፤ የጊዜአቸው ሰለባዎች



የመምህር ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ አና የመምህር በላይነህ ገ/ማርያም አሳዛለኞችኝ ታሪክ

በኤፍሬም የማነብርህን
ሰሞኑን “በኢሕአፓ የዲሲና አካባቢው ደጋፊ አካል” ብሎ በሚጠራ ድርጅት በሚታተመው “ኢትዮጵያ” በተሰኝው መጽሔት የኅዳርና ታህሳስ 2005 (ኖቬምበር አና ዲሴምበር 2012) ሕትመቶቹ ላይ “መምህር በላይነህ ገ/ማርያም በሞቱ ጠላቶቹን ድል የነሳ የኢሕአፓ ኮከብ” ብሎ ያወጣውን ምንባብ በአጋጣሚ አግኝቼ በከፍተኛ ድንጋጤ አነበብኩት፡፡  በመጽሔቱ ላይ እንደተገለጸው ጽሑፉ የተወሰደው በሚያዝያና ግንቦት 1993 ዓም (አፕሪል እና ሜይ 2001) ታትሞ ከወጣው የጎሕ መጽሔት መሆኑንም ይኸው “ኢትዮጵያ” በመንደርደርያው ላይ ገልጾታል፡፡
የጽሑፉ ይዘት ባጭሩ፣ የኢሕአፓ አባል የነበረው መምህር በላይነህ በመስከረም 23 1969 (ኦክቶበር 2 1976) ዓም በመምህር ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ ላይ ስለፈጸመው አሳዛኝ “ጀብዱ” ግድያ ነው፡፡ የግድያው ጥንስስ  ከተነደፈበት ጊዜ ጀምሮ በተግባር እስከተከናወነበት ድረስ እና መምህር በላይነህ በደርግ ተይዞ እስከተገደለበት ድረስ የሆነውን ሁሉ በዝርዝር የመጀመርያ ደረጃ እውቀት ያለው በሚመስል ጸሓፊ ታሪኩ ቀርቧል፡፡  የሚከተለውን ጥቅስ ከጽሑፉ ቀንጨብ አድርጌ አቅርቤዋለሁ፡፡
ግዳጃቸውን በሚወጡበት ዕለት ወደ ወሳኙ ተልኮ ከመሰመራታቸው በፊት ስፕሪንግ ሆቴል ተገናኝተው  ሻይ ቡና አዘዙ፡፡ ያን ዕለት ዶ/ሩን ከቢሮው ሲወጣ ጀምሮ መከታተል አላሻቸውም፡  ዒላማቸው ከቢሮው ከወጣ ጥቂት ደቂቃዎች ያለፉት መሆኑን ለማወቅ ሰዓታቸውን መመልከት ብቻ ይበቃቸው ነበር፡፡ ሂሳብ ከፍለው ከሆቴሉ በመውጣት ወደመኪናቸው አመሩ፡፡ መከላከያ ሚኒስቴር ሲደርሱ፣ የዶ/ር ፍቅሬን መኪና ተመለከቷት፡፡  ከኋላው ሆነው ተከተሉት . . . .  መምህር በላይነህ ከመኪናው ወርዶ እጆቹን ኪሶቹ ውስጥ በመክተት ከሞርጌጅ ባንክ ፊት ለፊት የኮሜርስን ግንብ ጥግ  ተከትሎ ወደፊት ተረማመደ፡፡ የዶ/ር ፍቅሬ ባለቤት ከተለመደው ሥፍራ ቆማ ባሏን በመጠባበቅ ላይ ነበረች፡፡ ወዲያውኑም ዶ/ሩ ደረሰና መኪናዋን ወደ ሚስቱ አስጠግቶ አቆመና አሳፈራት፡፡ በዚያን ቅጽበት በላይነህ ዶ/ሩ በተቀመጠበት በኩል ወደ መኪናዋ ተጠጋ፡፡  ሰላምታ የሚሰጠውም በማስመሰል የመዘዘውን  ነጥብ  ስላሳ ስምንት ኮልት ሽጉጥ አነጣጥሮ ቃታውን በመሳብ ጭንቅላቱን በአረር ተረከከለት፡፡ ወዲያውኑም መኪና ይዞ ወደሚጠብቀው ይትባረክ በሩጫ ተፈተለከ። . . .የባሏን በጥይት ተመትቶ መውደቅ ያስተዋለችው የዶ/ሩ ሚስት ከመኪናዋ ወርዳ ልትከተለው ሞክራ ነበር፡፡ ይሁን  እንጅ፣ ትቅርና ባለረጅም ታኮ ጫማይቱ ሴት፣ የባንኩ ጥበቃ ወታደሮች እንኳ ሮጠው ሊደርሱበት አልቻሉም፡፡
መምህር ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድን እኔ ሳውቅው
ጊዜው መስከረም ወር 1966 (ሴፕቴምበር 1973) ነበር።  በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት የመጀመሪያ ዓመት ተመድበን ትምሕርት ከጀመርነው 50 ያህል ተማሪዎች አንዱ ነበርኩ፡በሕግ ት/ቤት ካሪኩለም መሰረት የመጀመሪያውን ዓመት የመተዋወቂያ ኮርስ እንዲያስተምር የተመደበው መምህር በቅርብ ከፈረንሳይ የሕግ ዶክትሬቱን አግኝቶ፣ ለሃገሩ ካለው ፍቅር የተነሳ ወደአገሩ በመመለስ፣ በዓለም ዙሪያም ሆነ በአገር ውስጥ የተሻለ ደሞዝ ሊያገኝ የሚችልበትን ሥራ ትቶ በጣም በትንሽ ደሞዝ ወገኖቹን ለማስተማር የወሰነ ገና ትኩስ መምህር ነበር፡፡  ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ ቀላ መልከ መልካም፣  ጸጉሩ ከግንባሩ ትንሽ ገባ ማለት የጀመረው አጠር ያለ ባለአፍሮ ጸጉር፤ ካላወቁት በቀር፣ በአለባበሱ ሆነ በባሕርይው ከአካቢቢው ለየት ብሎ የሚታይ በወቅቱ ዕድሜው ቢበዛ ከመጀመሪያዎቹ ሰላሳዎች ያልበለጠ ወጣት መምህር ነበር፡፡
መምህር ፍቅሬ መርዕድ በትምህርትና በዕውቀት የላቀ በመልካም ሥነ ምግባር የታነጸ፣ በላዩ ምንም ትዕቢትም ሆነ ትምክህት የማይታይበት በአነጋገሩም ሆነ በአረማመዱ ቁጥብ፣ ኩሩና ጨዋ፣ ወንድ ሴት፣ ትልቅ ትንሽ ሳይል፣ ሁሉንም በአክብሮት የሚያስተናግድ፣ በተማሪዎቹ ሁሉ የተከበረ ሰው ነበር፡፡ እኛ ተማሪዎችም ይህን በመሰለ በዕውቀቱም በባሕርይውም ምሳሌ የሆነ መምህር በማግኘታችን፣ የሱን የማስተማሪያ ክፍለ ጊዜ ሁሌም በናፍቆት ነበር የምንጠብቀው።
ስለ ፍቅሬ  መርዕድ ዕድገትና ሥረ መሰረት ብዙ አላውቅም፡፡ የሚያውቁ ካሉና ስለዚህ ትልቅ መምህር የተጻፈ ካለ፣ ጽሑፉን የሚጠቁመኝ ሰው ትልቅ ባልውለታዬ ይሆናል፡፡  ከማውቀው በትንሹ፡ ፍቅሬ መርዕድ የግርማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ ባለ ሥልጣን የነበሩት የጀነራል መርዕድ መንገሻ ልጅና ከንጉሳውያኑ ቤተሰብ አካባቢ እንደሆነ፤ ለረጂም ዓመታት በፈረንሳይ ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶ አገሩን ለማገልገል የተመለሰ መሆኑን፣ ትዳርም መስርቶ ከሚወዳት ሚስቱ ጋር በሰላምና በፍቅር ይኖር የነበረ መሆኑን ነበር የማውቀው፡፡ ምንም እንኳን ቤተሰቡ ትልቅ ሃብትና ንብረት የነበራቸው ቢሆኑም በወቅቱ በሱ ደረጃ ከነበሩ ሌሎቹ መምህራን ብዙም በማይለይ አፓርትመንት ተከራይቶ ከሕዝብ ተቀላቅሎ የሚኖር ሰው ነበር፡፡
ዶ/ር ፍቅሬ በክፍል ሲያስተምር ረጋ ብሎ፣ ለእያንዳንዷ ንግግሩ ክብደት የሚሰጥ መምህር ነበር፡፡  ብዙ ጊዜ ቁጭ ብሎ ማስተማርን ይመርጥ ስለነበረ፣ አንዳንዴ ተነስቶ በጣም በሚያማምር ካሊግራፊው ሰሌዳው ላይ ሲጽፍ፣ እንዲሁም ለማስተማሪያ የሚያዘጋጃቸው ጽሑፎቹ የነበራቸው ጥራትና ጥንቃቄ፣ መምህሩ ለንዝህላልነት ምንም ቦታ ያልነበረው ሰው እንደነበረ በቂ ማስረጃ ነበሩ፡፡  በአውሮፓ በከፍተኛ ደረጃ የተማራቸውን የሕግና ሕብረተሰብ፣ የአስተዳደርና ፖለቲካ ፍልስፍናዎችን ለእኛ ጨቅላዎቹ ሊገባን በሚችል ቋንቋ በመተርጎም ሲያስረዳን፣ የማይረሳ ትዝታ ያልጣለበት ተማሪ አልነበረም፡፡  በተለይ ዘመኑ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ፍልስፍና ሊነቀፍ በማይታሰብበት ዘመን ቢሆንም፣መምሕር ፍቅሬ መርዕድ ግን ሁሉንም ፍልስፍና በእኩል በማስቀመጥ የአንድ ቲዎሪ ወይም ፍልስፍና ባሪያ መሆን እንደማይግባን ነበር የሚያስተምረን፡፡
ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ ይህን በመሰለ ችሎታውና የማስተማር ዘዴው ለአንድ ዓመት ካስተማረን በኋላ፣ በርሱ ሥር ለመማር ሌላ ዕድልም ሳናገኝ በሚቀጥለው ዓመት አብዮት ፈነዳ፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ከሥልጣን ወረዱ፡፡ የመሬት ይዞታም ታወጀ፡፡ ተማሪም ዘመቻ ተሰማራ፡፡ ኢሕአፓና መኢሶንም ተመስረተው ብዙ ሳይቆዩ ጎራ ለዩ፡፡ መንግስት የሚያደርግበትን ፕሮፓጋንዳና የእሥራት ጥቃት ለመቋቋም በማለት፣ ኢሕአፓ በመሳርያ የታገዘ የከተማ ሽምቅ ትግል በመጀመር ከደርግ ጋር ባበሩት ላይ ሁሉ ዒላማውን አነጣጠረ፡፡  ተወዳጁ መምህሬ ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድም ገና በአብዮቱ ጥዋት፣ መስከረም 23 1969 ዓም (ኦክቶበር 2 1976) የመጀመርያው የኢሕአፓ የምሁር ሰለባ ሆነ፡፡
የመምህር ፍቅሬ መርዕድን ሞት የሰማሁበት ቀንና ሰዓት፣ ቦታውም ጭምር፣ ገና ትላንት የሆነ ይመስል በግላጭ አሁን ድረስ ይታየኛል፡፡ ዜናውን የነገረኝ የሕግ ት/በት ጓደኛዬ ዘመቻ ለመዝመት ቤትሰቦቼ ዘንድ ናዝሬት በነበርኩበት ወቅት ሊጎበኘን መጥቶ ብነበረ ጊዜ ነበር፡፡ ዜናውን በሰማሁ ጊዜ ያልታሰበ ዕንባ ተናነቀኝ፡፡ የማደርገው ጠፋኝ፡፡ በወቅቱ በአባልነት የመመልመል ፍላጎቱ ባይኖረኝም፣ ኢሕአፓን ተስፋ ሰጭ ድርጅት አድርጌ እቆጥረው ነበር፡፡ ወንድም እህት ጓደኛ፣ አፈሩ ቅጠሉ ኢሕአፓ ስለነበር ሙሉ እምነቱ በሌላቸው አካባቢ እንኳን ኢሕአፓ መሆን ፋሽን ነበር፡፡ እንደኔ ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድን ላላወቁት፣ በዚያ አስከፊ ሰዓት የሱ በአሳዛኝና በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል ብዙም አልተሰማችው ይሆናል፡፡ በዚህም አልወቅሳቸውም፡፡  ለኔና ለጓደኞቼ ግን ያች ክስተት ላንዴም ለመጨረሻም አቅጣጫ ያስቀየረችን ነበረች፡፡ ከዚያች ቀን በኋላ ኢሕአፓን ዞር ብለን አላየነውም፡፡
የነበረው በነበር አልፎ አሁን ከአንድ ሳምንት በፊት ከላይ የጠቀስኩትን ጽሑፍ አነበብኩት፡፡  ስለ ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድም አገዳደል ዝርዝር ያነበብኩት ለመጀመርያ ጊዜ ነበር፡፡  ዜናው የቀድሞ ሃዝኔን ቀሰቀሰብኝ፡፡ አስደንጋጩ ጽሑፍ የወጣውም በዚች በአሜሪካ፣ እንዲያውም በዋሽንግተን ዲሲ መሆኑ በጣም ረበሸኝ፡፡  ጽሑፉን ደግሜ ደጋግሜ አነበብኩት፡፡ ነገር ግን ብዙ ባነበብኩት ቁጥር ገዳዩ ራሱ. መምህር በላይነህ ያሳዝነኝ ጀመር፡፡ መምህር በላይነህ ራሱ ቀላል መምህር አልነበረም፡፡  የሃገር ፍቅር የሚያቃጥለው ኢትዮጵያዊ እንደነበር ተረዳሁ፡፡ የሚከተለው ስለ መምህር በላይነህ በ“ኢትዮጵያ” መጽሄት ከወጣው በአጭሩ የቀረበ ነው፡፡
መምህር በላይነህ ገ/ማርያምን ሌሎች እንደሚያውቁት
በ “ኢትዮጵያ” መጽሄት ላይ እንደተገለጸው፣ መምህር በላይነህ በደብረ ብርሃን ተወልዶ በአዲስ አበባ መድሃኒ ዓለምና በአምቦ የእርሻ ት/ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በዓለማያ እርሻ ኮሌጅ የእርሻ ምህንድስና ትምሕርት ወስዶ ዲግሪውን ከማግኘቱ በፊት በስብስቴ ነጋሲ አስተማሪ በመሆን ሲያስተምር የነበረ ፤ በኋላም በአሜሪካ ከሚገኝ ኮሌጅ በመጻጻፍ የሕግ ትምሕርት ይከታተል የነበረና፣ አነስተኛ መጠን ያላቸውን የማስፈልፈያና የማሞቂያ መሳሪያዎችን በመጠቀም የዶሮ እርባታና የከብት እርባታ ያካሂድ የነበረ ሰው ነበር፡፡  በኑሮውም ቅንጡነትን የማያበዛ፣ አልጋና ፍራሽ ሳይኖረው፣ ኬሻና ካሊም አንጥፎ ወለል ላይ የሚተኛ፣ ነገር ግን ለአካባቢው አርሶ አደርና የቀን ሰራተኞች በራሱ ወጭ ጥቁር ሰሌዳ ጠመኔና ማሾ ገዝቶ ማታ ማታ በማስተማር መሃይምነትን ያላቀቀ ሰው ነበር፡፡ በግል ጸባዩም ጥብቅ የመጻሕፍት ጓደኛና፣ ትጉህ መምህር ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ያልታደለው ትውልድ
ከላይ የተቀመጠው የመምህር ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድና የመምህር በላይነህ ታሪክ እንደሚያሳየው፣ ሟችና ገዳይ ከሚያለያያቸው ይልቅ የሚያቀራርባቸው በርካታ መመሳስሎች ነበሯቸው፡፡  ሁለቱም ትጉህ መምህራን ነበሩ፡፡ ሁለቱም የኢትዮጵያ ነገር ያንገበግባቸው ነበር፡፡  አካባቢያቸውንና ወገናችውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘር ሳይለዩ ለማሻሻል ሁለቱም ራሳቸውን ለመስዋዕትነት ያቀረቡ ነበሩ፡፡  አንዱ ገዳይ አንዱ ሟች መሆኑን ለጥቂት ወደጎን ብናስቀምጠው፣ በተለየ ጊዜና ቦታ በፍቅርና ወንድማማችነት ለአንድ የጋራ ዓላማ ተቃቅፈው ሊሰሩ የሚችሉ ሰዎች እንደነበሩ መገመት አያዳግትም፡፡ ያች ሁለቱ መምህራን፣ አንዱ በሟችነት ሌላው በገዳይነት የተቆራኙባት ሰዓት የመጭውን አመላካች የነበረች፣ ገና አሁንም ሊያስተውል ለፈለገ ከስህተት ለመማሪያ ምሳሌ የምትሆን ክስተት ናት፡፡
የአገሪቱ ብርቅዬ ወጣቶችና ምሁራን አዲስ ሥርዓት በኢትዮጽያ ለማስተዋወቅ በነበራቸው ጉጉት ሳቢያ፣ ወደ ተሳሳተ የትግል ጎዳና ያመሩበት የታሪክ ነጥብ ነበር፡፡ ምናልባት ብዙዎች ይህን ሀተታ ለቀባሪው እንደማርዳት ሊቆጥሩት ይችሉ ይሆናል፡፡ነገርግን ከላይ የጠቀስኩትን በኢትዮጵያ መጽሔት ገዳይን በማወደስ እንደ ጀግና የቀረበው ጽሑፍ በዚህ ባለንበት ቦታና ጊዜ መውጣቱ ያ ስሕተት እንዳይደገም ለሚሻ ሁሉ የማስጠንቀቂያ ጥሪ ይመስለኛል፡፡  መምህር ፍቅሬ መርዕድና መምህር በላይነህ በአካል ከተገናኙባት ክስተት በኋላ የተከተለው ጊዜ ወንድም ከወንድሙ፣ እህት ከእህቷ፣ ወዳጅ ከወዳጁ፤ ወገን ከወገኑ ጦር የተማዘዘበት፣ የተጨካከነበት፣ጠላትን ከወገን ለመለየት የሰው ዓይን የታወረበት፤ በአገር ደረጃ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ያበደበት ወቅት ነበር፡፡ ባሕልና ወግ የተገረሰሰበት፣ ሃይማኖት የተናቀበት፣ ጭፍራ መሪውን፣ ወጣት ሽማግሌውን፣ ታናሽ ታላቁን የናቀበት ዘመን ነበር፡፡  ነገር ግን ይህ አባባል ያለፉትን ዞሮ በማየት የመጣ ግምገማ እንጂ በወቅቱ እንኳን ለዳኝነት ለመደማመጥም ፋታ አልነበረም፡፡
ያ ያለፈው ክፉ ዘመን አገሪቱን ያለ መልካም መሪ አስቀርቶ፣ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ የጎሳ አባልነትን ቅድሚያ ለሚሰጡ የሁለተኛ ረድፍ መሪዎች፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚልን ሁሉ በውሸታምነትና በድብቅ አማራና ነፍጠኛነት ለሚፈርጁና እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ሲባል ለሚስቁና ለሚሳለቁ መሪዎችና ካድሬዎች፣ እንዲሁም እናት አገርን ወደብ አልባ ላደረጉ ከሃዲዎች፤ እና ሕዝቦቿም በጎሪጥ እንዲተያዩ ሌት ተቀን የጣሩ መሪዎች ሲሞቱ ግን መልካም ሥራ ሰርተው ያለፉ ይመስል ካላተለቀሰላቸው አገር ይያዝ ለሚሉ ካድሬዎች ተክቶና ሕዝቡንና አገሪቱን ለአደጋ አጋልጦ አልፏል፡፡
መልካሙ የቀረው ነገር ግን፣ እነኚህ ሁለተኛ ረድፍ መሪዎች የሕዝቡን ልብ መስረቅ አለመቻላቸው ነው፡፡  ሊፈጥሩት እየሞከሩ ያሉት ሥርዓት በአሸዋ ላይ እንደተሰራ ግንብ ይዋልላል፡፡  ለኢትዮጵያውያን ይህ ሌላ አጋጣሚ ነው ከተጠቀምንበት፡፡ ባለፈው የሰራነውን ስህተት ተገንዝበን ከሚለያየን የሚያገናኘንን፣ ከሚያራርቀን የሚያቀራርበንን፣ ከሚያጣላን የሚያስታርቀንን ምርጫ የመለየት እውቀቱን ማጎልበት ይኖርብናል፡፡
ኢትዮጵያ” መጽሄት ላይ ስለ መምህር በላይነህ ስለወጣው ጽሁፍ
የኔ ክርክር ታሪኩ ይደበቅ አይደለም፡፡ በታሪኩ ይዘትና ዓላማ ላይ ነው እንጂ፡፡ እሺ ይሁን፤ መምህር በላይነህን የጊዜው ሰለባ እንበለው፡፡ የዶ/ሩን ሚስትና ልጆቹን እንዲሁም የቅርብ ዘመዶቹንና ጓደኞቹን ቁጭትና ብሶት ትተን እኛ የሩቆች መምህር በላይነህ የፈጸመው ወንጀል በዕብደት ዘመን የሰራው ስሕተት ነው ብለን ነፍስ ይማር እንበል፡፡ በ1993 ዓም የጎሕ መጽሄትን ያዘጋጁትን ይቅርታ ለማለት ቢከብድም እሺ ይሁን መቼስ ምን ይደረግ ያለፈው አልፏልና ምንም ማድረግ አንችልም፤ እንተወው እሱን፡፡
ነገርግን ያሁኑ ይባስ፡፡ በዚች የዲሞክራሲ ቁንጮ በሆነችው በአሜሪካ ግዛት፣ ብሎም በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ርዕሰ ከተማ በዋሽንግተን ዲሲ የሚታተም መጽሔት ይህንን አስነዋሪ በወገን ላይ የተፈጸመ ደባ በ2012 እንደጀብዱ ቆጥሮ ለንባብ ሲያበቃው እንዴት ዝም ብሎ ማየት ይቻላል? ይህን የመሰለ ቅጥ ያጣ ገድለ አራዊት በመልካም ሕዝቦችና ከስሕተታቸው ተምረው ለመታረም ዝግጁ በሆኑ ወገኖች መሃል ቦታ እንደሌለው በግልጽ ሊነገር ይገባል፡፡ ከ“ኢትዮጵያ” መጽሔት እርማት እንጠብቃለን፡፡
እግዚአብሔር አሁንም ኢትዮጵያን ለዘለዓለም ይባርክ፤ ሕዝቦቿንም ይጠብቅ፡፡
ዋሽንግተን፣ ዲ ሲ  የካቲት 2005

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar