fredag 29. november 2013

ገኔን አያችሁ?!
ከአስራ-ሶስት ወራት የብርሃን ጸጋ፣
ከአዝርዕት እናት ከለምለሟ ምድር..፣
 ተፈጥሮ ሲቸገር!
 ወገኔን አያችሁ?!
 አባይ፣ አዋሽ፣ ኦሞ — አንገረብ፣ ተከዜ፣
 ጊቤ፣ ዋቤ፣ ባሮ - አትባራ፣ ገናሌ...፣
 ጀማ፣ ሮቤ፣ ሙገር - ደዴሳ፣ ቀበና...፣
 ጎጀብ፣ ሚሌ፣ ጉደር፣ - በለስ፣ መረብ፣ ዳዋ...፣
 ጨፌ የሕይወት ምንጭ አቋርጦ ተሻግሮ፣
 በምድረ-በረሃ በውሃ ጥም አሮ፣
 በረሃብ በጠኔ አንጀቱ ተቋጥሮ?!
 ወገኔን አያችሁ?!
 ባረመኔ ጥይት ልቡ ላይ ተመቶ፣
 በጨካኞች በትር አናቱ ተፈልጦ፤
 በስጋት በጭንቀት ሰርክ ተወጥራ፣
 በውራጅ ቦዘኔ ንጹኋ ተደፍራ፤
 በበረሃ በረት እንደ ከብት ታጉረው፣
 በቀቢጸ-ተስፋ ፍጡራን ተሞልተው...፣
 ወገኔን አያችሁ?!
...እናስ ምናላችሁ?
 እናንት ደላሎች የሰው ፍጡር ሻጮች፣
 በነሱ ላብና ደም “ሚሊዮን” ቆጣሪዎች፣
 እብነ-በረድ ሕንፃ ፎቅ ቤት አሰሪዎች፣
 ጮማ ሰልችቷችሁ “ቃተኛ” በሊቶች፣
 ቬርሙጥ፣ ኮኛክ፣ ውስኪ፣ እንደ ወሃ ቀጂዎች...፣
 እናስ ምናላችሁ?
 ሲራብ፣ ሲጠማ.. ምስኪን ወገናችሁ፤
 የገንዘብ ምንጫችሁ!
እናንተስ “ክቡራን” የተኮፈሳችሁ፣
በንቀት ጥላቻ የተበከላችሁ፣
በዘር በሃይማኖት ...ሕዝብ እያመሳችሁ፣
በጉልበት በብረት አፈና የገዛችሁ፤
ከንቱ ጸረ-ዜጋ “ልማታዊ መንግሥት” እኛን ወደ “አሸዋ” - “ለነሱ” ለም- መሬት...፤
ምንድን ተሰማችሁ?
ሲናድ ሰብዕናችን—ሲነካ “ክብራችሁ”?
እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም...ዘመዳሞች፣
አልቅሶ ተቀባይ... አልቅሶ ሸኚዎች፣
በጣርና ስቃይ ከሚያገኟት ጥሪት እሚያካፍሏችሁ፣
ሲራቡ፣ ሲጠሙ፣ በግፍ ሲሰቃዩ.. እስኪ ምን አላችሁ?
 በሃዘን መኮራመት— ሁለተኛ ጉዳት?
 ወይስ ተጠያቂን አፋጦ መሟገት?!
 ስንት ዓመት ይቆጠር ስንት ዘመን ይለፍ፣
 በግፍ በሰቆቃ ስንት ወጣት ይቀጠፍ፣
 እንደ አገር ኢትዮጵያ— እንደ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ተከብሮ ለመኖር፣
 ስንት ጊዜ ይክነፍ? — ስንት ሽበት ይብቀል?
 ግፈኛውን ቡድን፣ ዘረኛውን ሥረዓት ከስሩ ለመንቀል?!
ከዚያም የሆናችሁ — ከዚህም ያላችሁ
ሁላችን! ሁላችሁ!
ወገኔን አያችሁ?! አናስ ምን አላችሁ?!
 ጌታቸው አበራ
ሕዳር ፳፻፮ ዓ/ም
(ኖቬምበር 2013)

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar