tirsdag 22. oktober 2013

መንዜው አጉኔ አለቃችንና ተስፋዬ ገ/ አብ


• በተስፋዬ ገ/አብ የስደተኛው ጋዜጠኛ መጽሃፍ ላይ ሰሞኑን ዲያስፖራው ቁርቋሶ ከመጀመሩ በፊት ፣ላይፍ ለተባለ
መጽሄት ተስፋዬ ገ/አብ ቃለ መጠየቅ ሰጥቶ ነበር ፡፡ ኢህአፓ እንደኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም መጽሃፍ አሻጥር
ቢያደርግብህ በምን ትቋቋመዋለህ ተብሎ ሲጠየቅ ? አበጥ አበጥ ያሉ ገታሪ ጠበቆች ፣ አሳታሚውም ድርጅት ሆነ እኔ
ስላሉን በሱ አታስቡ ነበር ያለው ፡፡ ቀስ ብሎ ግን ከወደ አመስተርዳም አንድ ዳጎስ ያለ ዶሴ ፣ በዳኛ ወልደሚካኤል
በኩል ብቅ አለ ፡፡ ዲያስፖራው ተንጫጫ ፡፡ ድሮስ ! ተናግረን አልነበረ? ይህ ደራሲ እንደ ወገምት ይዞናል ! መች
ይለቀንና ! እሱ ምን ያድርግ ! ከውስጣችን የወሸቁት የኛ ሰዎች.... ብዙ አይነት ንዴት ፥እልህ ፥ቁጭት ወዘተ ጨሰ ፡፡
በዚያም ሰፈር በኩል ፣ እነ አይጋ ፥ ትግራይ ኦን ላይን አጫጫሱት ፡፡ አብሪ ባትሪም ወደ ሰማይ አጎኑ ፡፡
• በውጭ አገር ያሉ ፣ በዛ ያሉ ነጻ ድረ ገጾች ነን የሚሉ ሁሉ በዳኛ ወልደሚካኤል አጋላጭ ጽሁፍ ላይም ሆነ ፣
በአሌክስ_ሊክስ የአራዳ ዘበኛ ሚስጢር ጎልጓይነት ሥራ ባለመስማማት ይሁን ወይ ኤዲቶሪያል ቦርዳቸው ባለመፍቀዱ
ምክንያት ዳጎስ ያለውን ጽሁፍ አገዱት ፡፡ ፌስ ቡኮች ነገሩን አቀጣጠሉት፡፡ አካበዱትም፡፡ አጥቅተውም ታትሞ ሊሸቀል
በዝግጅት ላይ የነበረው መጽሃፍ መከነ ፡፡ በመጨረሻም በራሱ በጸሃፊው በፒዲኤፍ በነጻ ተበተነ፡፡

• ብዙ ፓልቶኮች ሳይሆኑ ፣ አንድ የፓልቶክ ክፍል ብቻ ጉዳዩን አጮኽው ፡፡ ከማጮኽም አልፎ ፣የተቃውሞ ደቦ
በማስተባበር የተስፋዬ ገ/ አብን መጽሃፍ አሳታሚው ድርጅት ከህትመት ውጭ እንዲያስወጣው የፊርማ ደቦ
አፋፋመበት ፡፡ ደቦው የሠራ መስሏል ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ከመጽሃፉ ምዕራፍ ሰባትን ካላወጣህ አናትምልህም የተባለው
ተስፋዬ ፣ ጽሁፌን አልቀነጥስም ፣ ባታትሙት ተዉት እንጂ ብሎ ፣ በነጻ በተነው ፡፡
• ነጻነት አሳታሚ ድርጅት የተባለው ድርጅት ፣ ለጊዜው እፎይታ ያገኘ ይመስላል ፡፡ ውሉን ቢያፈርስም ፣ አሳታሚው
ድርጅት ግን አሁንም የአሰፋ አባተን የቀድሞ ዘፈን ከማዜም አላቆመም ይሉታል ተቺዎቹ ፡፡

 ፊርማና ወረቀት ቀሪ ነው ተቀዳጅ፣
 መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ ፡፡

የፌስ ቡክ ነገር ቢነሳ አንድ በአረቡ ዓለም ሰሞኑን የሚቀለደውን ቀልድ ላልሰማችሁ ፣ እንድትሰሙት ፈለግሁ ፡፡ እንዲህ ነው
ቀልዱ ፡፡ ሆስኒ ሙባረክ ሞተና ሰማይ ቤት ሲደርስ ከበር ላይ ጀማል አብዱል ናስር፥ አንዋር ሳዳት ሆነው ፣ ለሙባረክ ሞቅ ያለ
አቀባበል ያደርጉለታል ፡፡ በምን ምክንያት እንደ ሞተ ተራ በተራ ይጠይቁታል ፡፡ የመጀመርያውን ጥያቄ ጀማል አብዱልናስር
ይጠይቃል... አንተንም እንደኔ በመድሃኒት መርዘው ነው የገደሉህ ? ኧረ በጭራሻ ይላል፡፡ ሳዳት ይቀጥላል ፣ እንደኔ በጥይት ነው
የገደሉህ ይላል ? ሙባረክ አሁንም ኧረ በጭራሽ ! ሁለቱም በመጨረሻ በመገረም ታድያ በምንድነው የገደሉህ ቢሉት ? በፌስ
ቡክ! ጀማል አብዱልናስርም ሆነ ሳዳት ፌስ ቡክን አያውቁትም ፡፡

የዛሬ ሶስት ዓመት ግድም ፣ በአመስተርዳም ከተማ በተዘጋጀው የአውሮፓ ኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ላይ የዚህ ጽሁፍ
ጸሃፊ ጋዜጠኛና ደራሲን ተስፋዬ ገ/ አብን እዚያው ስታዲዮሙ ቅጥር ግቢው ውስጥ ባለ መዝናኛ ክበብ ውስጥ ቢራ ሲጎነጭ
አግኝቼው ለመቀላቀል ብዬ በትሪ ቢራ ይዤ ቁጭ አልኩ ፡፡ ተስፋዬ ጀርባውን ወደ በሩ ሰጥቶ ያለምንም ፍርሃት ቢራውን
ይጎነጫል ፡፡ ሁለታችንንም የሚያውቅ አንድ ታላቅ ደራሲ አስተዋወቀንና ጨዋታ ጀመርን ፡፡ ወያኔን የመሰለ ታላቅ ጠላት አለኝ
እያልክ እንዴት ጀርባህን ሰጥተህ ትዝናናለህ ? ነበር የኔ የመጀመርያ ጥያቄ ? ተስፋዬ ወደ ሰማይ እያሳየኝ ... ከገላገሉኝማ እሰየው
አለኝ ፡፡ አልገባኝም ፡፡ ለምን ? የሚል ነገር በውስጤ ተጫረ ፡፡ ጨዋታው ደራ! በቡርቃ ዝምታ ላይ የነበረኝን ብስጭት
ገለጽኩለት ፡፡ አይናደድም እሱ ! ጭራሽ ሰው ያበግናል እንጂ ፡፡ ወደ ታሪክ ገባን ፡፡ ዘራይ ደረስን አነሳን ፡፡ አሁን ጨዋታው ፈረሰ
ዳቦው ተቆረሰ ወደ ሚባል ደረጃ ተዳረስን ፡፡ ዘራይ ደረሰ ለኢትዮጵያ ባንዲራ ሲል ጎራዴውን ከአፎቱ ስቦ ጣልያን አገር ሰው
ጨረሰ የምትሉት ባዶ ተረት ነው ፡፡ ለኢትዮጵያ ባንዲራም ሳንጃውን አልሳበም ፣ ለወደፊቱ በዚህ ላይ እጽፋለሁ አለኝ ፡፡ እኔም
ጻፍ ! ኢትዮጵያ የታሪክ ጸሃፊ መካን አይደለችም ፡፡ የዚያን ጊዜ መልስ ታገኛለህ ብዬ በመከባበር ተለያየን ፡፡

በአንድ ገዥ መደብ ላይ ቂም የያዙ ሰዎች ፣ ጥርስ ሲነክሱ ፣ ገዚዎቹ መደቦች ላይ ብቻ ሳይሆን አገራትም ላይ ጥርስ ይነክሳሉ ፡፡
ለዚህ ደግሞ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ጋዜጠኛ አይናር ሉንድ የተባለው ኖርዌጅያዊ ጋዜጠኛ ልክ እንደ ተስፋዬ ገ/አብ በኢትዮጵያ ላይ
አቂሞ የጻፈው Paradisveien/ የገነት ጎዳና የተባለው እንደ አብነት የሚጠቀስ መጽሃፍ ነው ፡፡ ይህ ጋዜጠኛ እንደ አውሮፓውያን
አቆጣጠር ከ 1973/75 በኢትዮጵያ ብስራተ ወንጌል ተብሎ በሚጠራው ድርጅት ውስጥ በሚሰራበት ወቅት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ
መንግሥት የተገለበጠበት ወቅት በመሆኑ ፣ ከደርጎች ጋር ጸብ ውስጥ ይገባል ፡፡ የጸጥታ ሠራተኞች ዘወትር መውጫና መግቢያውን
እየተከታተሉ መግቢያ መውጫ ያሳጡታል ፡፡ ያስሩታልም ፡፡

አይናር ሉንድ እኤአ. በ-1995 ለኖርዌጅያን አረጋውያን የእንቅልፍ ማስተኛ የጻፈውን ኢትዮጵያውያንን የተመለከተ የተረት
መጽሃፉን እንዲህ ይተርክልናል ፡፡ በቮክስዋገን የፖሊስ መኪና ከሚከታተሉኝ ፖሊሶች ትንሽ ለመገላገል ብዬ ፣ ስዊድኖች ካሰሩት
ህንጻ ኮሌጅ ባሻገር ካለው ሸዋ ዳቦ ተብሎ ከሚጠራው ዳቦ ቤት ተኮልኩለው ሰልፍ ከያዙት ሰዎች ኋላ ሄጄ ተሰለፍኩ ፡፡ሁል ጊዜ
ዳቦ የምገዛው ከዛ ሸዋ ዳቦ ቤት ስለነበረ ፣ ከዚያ ስሠለፍ አንድ ነገር ትውስ ይለኛል ፡፡ ኢትዮጵውያኖች አንድ አፈ ታሪክ አላቸው
የሚመጻደቁበት ፡፡ እንዲህ ይላሉ ፡፡ ፈጣሪ የሰው ልጅን በራሱ አምሳያ ሊፈጥር አሰበና ፣ ሊጥ አቡክቶ ወደ መጋገርያው ምድጃ
ውስጥ አስገባው ፡፡ በመሃሉ ፈጣርያችን ከሚሯሯጡ ጦጣዎች ጋር ሲላፋና ሲቃለድ የዳቦውን የማውጫ ሰአት ስለዘነጋው ፣
ምድጃውን ሲከፍተው ዳቦው አርሮ ድብን ብሎ ጠቁሮ አገኘው ፡፡ ይህን ጊዜ ፈጣሪያችን ኔግሮ ብሎ ጠራው ፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar