mandag 19. august 2013

ለነጻነታችንና ለተዋረደው ስብዕናችን መከበር ስንል ልንከፍለው የማንፈልገው መስዋዕትነት እንደሌለ ወያኔን የማሳወቂያ ጊዜው አሁን ነው

በጉልበት በተገኘ ስልጣን የአገሪቱን አንጡራ ሃብት በመዝረፍ የከበረው የወያኔ ቡድን በእብሪት ተወጥሮ ተቃዋሚዎችን “መንገዱን ጨርቅ ያድረግላችሁ” ሲል እንዳልነበረ፤ የአገራቸው በዘረኞችና በአምባገነኖች መዳፍ ስር መውደቅ አንገብግቦአቸው ገና ለትግል ከመሰባሰባቸው በድንጋጤ ድባብ ውስጥ ተዘፍቆ የሚይዘውንና የሚጨብጠውን እንዳሳጣው ከአንተ ከጉዳዩ ባለቤት በላይ ምስክር ሊሆን የሚችል ሌላ ሀይል የለም። ወያኔን ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረገው አንተ በየጊዜው ይምታሳየው ጥንካሬ ነው፤ እየደረሰብህ ባለው እስራትና እንግልት ሳትንበረከክ፤ ወያኔ አንተኑ አፍኖ ለመግዛት ሆን ብሎ በፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳትበገር ወያኔን በህቡና በይፋ ለመታገል መወሰንህ ወያኔን እንቅልፍ አሳጥተህ እንዲደናበር ማድረግህ ማንም የሚስተው አይደለም። የወያኔ መደናበር ከልክ ማለፉን ለመረዳት ሰሞኑን በግንቦት 7 አባላትና ለአገራችው ነጻነት በመቆርቆር ድምጻቸውን በማሰማታቸው የሞትና የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸውን ወታደራዊ መኮንኖች፣ ወ/ት ብረቱካንንና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እሰረኞችን መጥቀሱ በቂ ነው።
የወያኔው የይስሙላ ፍርድ ቤት በ5 ኢትዮጵያውያን ላይ ሞት፣ በ33ቱ ላይ ደግሞ የእድሜልክ እስራት ውሳኔ ማስተላለፉን ሰምተሀል (ሻል)። በውኑ እንዲህ አይነት ፍርድ የሚገባቸው እንማን ነበሩ? ገና ህይወትን ሳያጣጥሙ፣ ለአገራቸውና ለህዝባቸው የሚጠቅም ስራ ሰርተው ለማለፍ ሲያልሙ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በአጋዚ ጥይት የጨፈጨፈው የአውሬው የመለስና የበረከት ቡድን፣ ወይስ ልጆች በነጻነት እንዲማሩና አገራቸውንም እንዲጠቅሙ የነጻነትን ትምህርት ያስተማሩዋቸው የኢትዮጵያ ታጋይ ልጆች? በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ ፣ በሶማሊያ፣ በኦጋዴን፣ በአማራ፣ በደቡብ. በቤንሻንጉል ወዘተ “ኢትዮጵያውያን ተራብን ተጠማን፣ አስተዳደራዊ በደል ደረሰብን፣ እንደ ሶስተኛ ዜጋ እየኖርን ነው፣ በአገራችን የመማር፣ የመስራት መብታችን ይከበርልን፣ በፈለግነው መሪ እንተዳደር” ብለው የጠየቁትን ኢትዮጵያውያንን እንደ ፋሲካ በግ እያረደ በየመንገዱ የጣላቸውን የአውሬዎች ስብስብ ወይስ፣ ለዜጎች እኩልነትና ብልጽግና የሚታገሉት የኢትዮጵያ ልጆች? አገራችን መሬቷ ተቆርሶ ለባእድ አገር እንዲሰጥ፤ ደሀው ገበሬ የሚያርሰው መሬት ባጣበት ሰአት ለግል ሀብት ማካበቻ ሲባል ገበሬውን እትብቱ ከተቀበረበት ቦታ እያፈናቀለ ለቻይና፣ ለህንድና ለአረብ ነጋዴዎች የሚቸበችበው፤ በአገራችን ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአንድን ብሄር አገዛዝ በመላው አገሪቱ ያሰፈነው የወያኔው የሽፍታ ስብስብ ወይስ ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባትና የህግ ልእልና የሰፈነባትን አገርን ለመመስረት የሚታገሉት ኢትዮጵያውያን? ወያኔ ልብ ካለው፣ ልብ ብሎ እንዲሰማ የምንፈልገው፣ የግንቦት 7 አባላት የወያኔው የይስሙላ ፍርድቤት በሰጠው ፍርደ ገምድል ውሳኔ ይበልጥ ለትግል የነሳሳሉ እንጅ ቅንጣት ታክልም ከአላማቸው የማይዘናጉ መሆናቸውን ነው። ውሳኔው አገራችን በቶሎ ነጻ ካልወጣች ከዚህ የበለጠ ጉዳት ሊደርስባት ይችላል ብለው እንዲጨነቁና ትግላቸውን እንዲያፋጥኑ ያደርጋቸውል እንጅ ፣ “ሞት ከተፈረደብንማ አንታገልም” ብለው እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ አያደርጋቸውም ። ግንቦት 7 ለነጻነታቸው ሲሉ ለመሞት የቆረጡ ኢትዮጵያውያንን ያሰባሰበ ፣ አንድ ሞት አይደለም አንድ ሺ ሞት ቢመጣ ሁሉንም እንደ አመጣጡ ለማስተናገድ ውሳኔ አድርገው የሚታገሉ ኢትዮጵያን ያሰባሰበ ንቅናቄ ነው። ይህንን ደግመን ደጋግመን ለወያኔ መንገር እንፈልጋለን።
ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ወያኔ የይስሙላ ፍርዱን ሲያስተላልፍ “ ለሌሎችም መቀጣጫ ይሆናል” ብሎ መናገሩን ሰምተሀል ። ይህ በቀጥታ ለአንተ የተላለፈ መልእክት ነው። መልእክቱ ስለነጻነትህ እንዳትጠይቅ ፣ ኑሮ ተወደደብኝ ብለህ እንዳታማርር ፣ ፍትህ ጎደለብን ብለህ እንዳታጉረመርም በአጠቃላይ በአገርህ ላይ ባለቤትነት እንዳይሰማህ፣ በአገርህ ላይ የመወሰን መብት እንዳይኖርህ ለማድረግ የተላለፈ መልክት ሲሆን፣ ይህን ካደረክም ሞትና የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቅሀል እያለህ ነው። ይህ ስድብ ነው። ይህ ታሪክን ማንቋሸሽ ነው። ይህ ከታሪክ ለመማር አለመቻልን የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ሞትና እስራትን ከነጻነት በላይ አድረጎ የሚመለከት ቢሆን ኖሮ፣ አገራችን ዛሬም ድረስ በጣሊያን አገዛዝ ስር በወደቀች ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ በሞትና በእስራት ነጻነቱን አሳልፎ የማይሰጥ መሆኑን ለማሳየት ታሪክ እንጥቀስ ብንል ወረቀቱም አይበቃንም። ይህን የአገራችን ህዝብ ያውቀዋል፤ ወያን ግን ገና ያወቀው አይመስልም።
ውድ ኢትዮጵያ ህዝብ፣
ወያኔ ዝምታን እንደፍርሀት በመቁጠር መያዢያ መጨበጫ ያጣ እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው። ዛሬ በግንቦት 7 አባላትና በወታደራዊ መኮንኖች ላይ የተላለፈው ውሳኔ አለማቀፍ ትኩረት ይሳብ እንጅ፣ አንተ ባልታወቀ ና ባልተነገረ ፍርድ የሞትና የእድሜ ልክ እስራት ፍርደኛ መሆንክህን ጠንቅቀህ ታውቃለህ። ዛሬ ይህ ዝምታህ ማብቃት እንዳለበት ልናስታውስህ እንወዳለን። ወያኔን እንደማትፈልገው በግንቦት 1997 ምርጫ ወቀት በግልጽ ተናግረሀል። ከዚያ በሁዋላ የምትወስዳቸው እርምጃዎችም ይህን እውነታ የሚያጠናክር ነው። ዛሬ ከአንተ ጋር እጅና ጓንት በመሆን ይህን የአውሬዎች አገዛዝ የምናስወግድበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ስለዚህም አስተዋፅኦህ በሁለም መስክ ይፈለጋል። መደገፍ ያለባቸውን ታጋዮች ደግፍ፣ ለወያኔው አገዛዝ ግብር አትክፈል፣ በቡድን እየተደራጀህ የወያኔ ሰላዮች ከሚያደርሱብህ ተጽኖ ተከላከል። አጋጣሚዎች ሲመቻቹልህም በተለያዩ አካባቢዎች የፈጠርካቸውን ድርጅቶች በአንድ ላይ በማቀናጀት በወያኔ ላይ ያለህን ተቃውሞ አስነሳ። እንደአካባቢህ ተጨባጭ ሁኔታ እያየህ የወያኔ አገዛዝ ተመቻችቶ እንዳይገዛ የሚያደርጉ እርምጃዎችን ውሰድ። ለነጻነታቸው ሲሉ በእስር ላይ የሚገኙ የነጻነት ታጋዮችንና ቤተሰቦቻቸውንም በሞራል፣ በገንዘብና በምትችለው ነገር ሁሉ እርዳቸው። ወያኔ ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ከሚያኮለሽበት መንገድ አንዱ፣ የነጻነት ተጋዮችን ቤተሰቦች ማሰቃየት ነው። ይህን ተረድተህ የነጻነት ታጋዮችን ቤተሰቦች ለመደገፍ ወደ ሁዋላ አትበል።
ለነጻነት የሚደረገው ጉዞ ረጅምና ፈታኝ ሊሆን ይችላል፤ ነጻነትን የሚሹ ግን ሁሌም በአሸናፊነት እንደሚወጡ ታሪክ ምስክር ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar