lørdag 29. juni 2013

ባይተዋር መምህር ለማይጨበጠው ሥርዐተ-ትምህርት

ስብሰባ . . . ስብሰባ . . . ስብሰባ! ለኢትዮጵያ መምህራን አዲስ አይደለም። የፖለቲካው ግለት ቢጨምር፣ በኑሮ መጎሳቆል ማኅበረሰቡ ቢያጉረመርም፣ ተማሪዎች በፖሊስ ላይ ድንጋይ ቢወረውሩ ወይም መምህራኑ ራሳቸው በተቃዋሚነት ቢጠረጠሩ አስቸኳይ ስብሰባ አያጣቸውም። ድንገተኛ ጥሪ ከየትኛውም የኢሕአዴግ ካድሬ ሊመጣ ይችላል። ፖለቲከኛ ብርቱካን ሚደቅሳ በድጋሚ ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ሲደረግ ርምጃው “ሕጋዊ ነው” ለማለት መምህራኑ ለስብሰባ እንደተጠሩት ሁሉ፤ አብዛኞቹ የግዴታ ጥሪዎችም ከመማር ማስተማር ጉዳይ ጋር የቀጥታ ግንኙነት የሌላቸው ናቸው።

ዛሬም፣ አዲስ የትምህርት ዘመን ሲመጣ እንደሚኾነው የ2003 መባቻን ተከትሎ ከመስከረም 4 ቀን 2003 ጀምሮ ስብሰባ እንዲቀመጡ ተጠርተዋል፤ “የትምህርት ንቅናቄ” በሚል ጉዳይ። በግልጽ መፈክሩ እንደተቀመጠው የትምህርት ጥራትን በማምጣት የአምስት ዓመቱን የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማገዝ ለስብሰባው በዓላማነት ተቀምጧል። ይኹንና የትምህርት ጥራት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ በመጠመቅ  ይመጣ ይመስል ስብሰባውን የሚመሩ ካድሬዎች እንደተለመደው ከመፈክሩ አፈንግጠው ስለ አዲሱ ዕቅድ “የማይቀር” ስኬት የሚተርኩበት ሌላኛው መድረክ አድርገውታል። መምህሩ ተቀበለም አልተቀበለ ይኼን ዲስኩር የመስማት ግዴታ አለበት።
የአምስት ዓመቱ ሕልም የሚተረክለት መምህር ግን የትምህርት ጥራት ወጉ እንደቀረበት እንጂ ሌላ በቀጥታ እርሱን የሚመለከት ጉዳይ እንደተነፈገ የሰማ አይመስልም። ባለጉዳዩ መምህር አድማጭ እንጂ ተሳታፊ ባልኾነበት መድረክ ያልተነሳው ጉዳይ ግን አድማስን አካሏል። ካድሬዎችም ሰለ“ሰማያዊው” ዕቅድ ደጋግመው ቢሰብኩም በ2003 የትምህርት ዘመን ትምህርት ሚኒስቴር በሁሉም “የሥርዐተ ትምህርት” ለውጥ ማድረጉን ለማስተዋወቅ አልደፈሩም።
ይኹንና መንግሥት ባለፈው ሳምንት በብዙኀን መገናኛ ይፋ እንዳደረገው ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ የሚተገበር በሁሉም የክፍል ደረጃዎች የሥርዐተ ትምህርት ለውጥ አድርጓል። የሥርዐተ ትምህርት ለውጡን ተከትሎ አጋዥ የትምህርት መጻሕፍት የታተሙ ሲኾን በተያዘው ዓመት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ይኾናል ተብሎ ይጠበቃል። ለማስፈጸሚያም 150 ሚልዮን የአሜሪካን ዶላር መመደቡን ትምህርት ሚኒስቴሩ ይገልጻል።
መንግሥት መምህራን ቅድመ ዝግጅት ሳያደርጉ እና በቂ ሥልጠና ሳያገኙ የትምህርትም ጉዳይ እንዳሻው መቀያየሩ የተለመደ ነው። በተለይ ደግሞ የአንድ የትምህርት ዘመን እንኳ ዕድሜ ሳይኖራቸው የሚለዋወጡት መርጃ መጻሕፍት የመምህሩን ይኹንታም ኾነ አስተያየት ሳያገኙ ለትግበራ የሚዘጋጁ ናቸው። በተያዘው ወር የኾነውም ጉዳይ ከዚህ ራቀ አይደለም። ይህም ያለመምህሩ ቅድመ እውቅና እና አስተያየት ያልዳበረ እንዲሁም ለመምህሩ ቅድመ ትውውቅ ያልተደረገለት የትምህርት ሥርዐት የሚያመጣው ለውጥ ለባለሞያዎቹ እንቆቅልሽ እንዲኾን አድርጎታል። የትምህርት ጥራት በተደጋጋሚ የካድሬ ስብሰባዎች ሳይኾን በትምህርት ቤቶች ውስጥ መኾኑን ለሚያውቁት መምህራንም ምንነቱ ያልተብራራውን ለውጥ ከሰማይ እንደወረደ ታምር ከመቀበል ውጪ የለውጥ መሣርያ ማድረግ ፈተናቸው ነው።
በርግጥ የሥርዐተ ትምህርት ለውጥ አለ?
ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የትምህርት ፖሊሲ ነው። አዲሱ የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ የተቀረጸው በ1986 ዓ.ም ሲኾን በወቅቱ አዲስ ሥርዐተ ትምህርት፣  የትምህርት አስተዳደር መዋቅር እና የትምህርት መስጫ ቋንቋ በአዲስ መልኩ ትግበራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል። በለውጡም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ዝግጅት ሥልጣኑን ለክልሎች በመስጠት በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርን እንደ አንድ አማራጭ እንዲጠቀሙም የፈቀደ ነው።
በወቅቱ የትምህርት ፖሊሲው በያዛቸው ዓላማዎችም ይኹን ዓላማዎቹን መሠረት አደርጎ በተቀረጸው ሥርዐተ ትምህርት የተገኘው የባለሞያም ኾነ የተቀረው ሕዝብ ድጋፍ እጅግ ዝቅ ያለ ነበር። ብዙዎች ተቃውመዋል። በተለይም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የኾነው አሃዳዊ (Self-contained) የማስተማር ሥነ-ዘዴ፣ የሁለተኛ ደረጃ የፕላዝማ ትምህርት አሰጣጥ፣ የሲቪክ ትምህርት ይዘት፣ የመጻሕፍት የጥራት ደረጃ እንዲሁም የመምህራን ሥልጠና እና የትምህርት ቤቶች አስተዳደር ኹናቴ ትችት ከቀረበባቸው አጨቃጫቂ ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እስከ አሁንም ትችቱ አልረገበም፤ አጨቃጫቂነቱም አልቀረም።
ከሁሉ በላቀ ግን በቀጥታ ከሥርዐተ ትምህርቱ ጋራ የተያያዙት የባለሞያ ትችቶች የበረከቱ ነበሩ፤ ናቸውም። በተለይም በሥርዐተ ትምህርቱ መሠረታዊ ጽንሠ ሐሳብ ግድፈቶች፣ የመምህራን ሥርዐተ ትምህርቱን አለመቀበል እና ከሥርዐተ ትምህርቱም ጋራ የማይጣጣሙ የመጻሕፍት ዝግጅቶች በተደጋጋሚ መስተዋል የፖሊሲውን የማያዋጣ መንገድ ቀድመው ያመላከቱ ነበሩ። ትችቶቹ የበረከቱ ይኹኑ እንጂ መንግሥት በወቅቱ መፍትሄ ለመስጠት አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ የባለሞያዎቹን ምክር ወደጎን በመተው የሥርዐተ ትምህርት ማሻሻያ ሳያደርግ የመጻሕፍት ለውጥን በተደጋጋሚ ማድረግ እንደ ዋነኛ መፍትሄ ተቀበለው። በዚህም በትምህርት ገበታ ለአንድ ዓመት እንኳ ሳያገለግሉ በሌላ የሚተኩ መጻሕፍት በርካቶች ነበሩ።
በአብዛኛውን ጊዜም መጻሕፍቱ በመምህራን አስተያየቶች ያልዳበሩ፣ ይወክሉታል ተብሎ የታሰበላቸውን የክፍል ደረጃ የማይመጥኑ እና በግድፈት የተሞሉ መኾናቸው የመማር ማስተማሩን ሂደት ወደኋላ ከሚጎትቱ ሰንኮፎች መካከል ዋነኛውን ሚና የሚጫወቱ ናቸው። መንግሥትም በተደጋጋሚ ለሚያሳትማቸው መጻሕፍት የሚያወጣው ወጪ ሌላ የኢኮኖሚው ራስ ምታት በመኾን ችግሩን ይበልጥ አወሳስቦታል።
ይህን የመንግሥት ግትር አቋም በወጉ ለሚከታተሉ ባለሞያዎች ግን አሁንም የሥርዐተ ትምህርት ለውጥ አደርጌያለሁ የሚለው ዜና የሚዋጥ አይደለም። መጻሕፍትን በየትምህርት ዘመኑ መለዋወጥ እና ሥርዐተ ትምህርትን ሙሉ ለሙሉ መቀየር የተለያዩ ጉዳዮች መኾናቸውን ይረዳሉ። እስካሁን ለመምህራን እንኳ ሊገለጽ የተፈራው ጉዳይ ምን ይዘት ቢኖረው ነው የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ቢኾንም መንግስት ሥርዐተ ትምህርቱን ቀይሬያለሁ በሚለው ዜና ላይ ግን እምነቱ የለም።
ሽግግር Vs ባይተዋሩ መምህር
ባለፉት ዐሥራ ዘጠኝ ዓመታት እንደታየው መንግሥት በመምህሩ በኩል ለማስፈጸም ለሚፈልጋቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ካልኾነ በቀር መምህሩን አጥብቆ የያዘበትም ኾነ የፈለገበት ጊዜ ማግኘት ይቸግራል። መምህራን ለማስተማር በሚጠቀሙባቸው መጻሕፍት ዝግጅት ላይ የመሳተፍ ዕድል የላቸውም። በትምህርት ሥራ ላይ ምርምር እና ጥናት በማድረግ የመማር ማስተማር ተግባሩን ሂደት ማገዝ የሞያ ግዴታቸው ቢኾንም የመንግሥትን ድጋፍ እና ይኹንታ በማጣት ከምርምር ተግባር እንዲርቁ ይገደዳሉ። አብዛኛውን ጊዜም መንግሥት ለሚፈልገው ፖለቲካዊ ጉዳይ ካልኾነ በቀር በነጻነት የመሰብሰብ መብትን ስለሚነፈጉ የጠነከረ የሞያ ማኅበር በመመሥረት የሞያቸውን ክብር ለማሰጠበቅ እንኳ አልቻሉም።
ይህም በመኾኑ ምክንያት ትምህርት ሚኒስቴር የመርኀ ትምህርት (Syllaubs) ለውጥ በማድረግ ብቻ ሥርዐተ ትምህርቱ እንደተለወጠ አድርጎ በአደባባይ ሲደሰኩር ተመልካች ከመኾን የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። እነርሱ ባልተስማሙበት ትምህርት ተምረው ወደ ሌላኛው እርከን መሸጋገር ያቃታቸው ተማሪዎች በትዕዛዝ እንዲያሳልፉ ሲገደዱም ድምፅ የማሰማት አቅም እንደሌላቸውም አሳይተዋል።
ይኹንና ሁሉን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገው መንግሥት ከዚህ በፊት ያደርገው እንደነበረው ዛሬም በወጉ ለመምህራን ያላስተዋወቀውን “ሥርዐተ ትምህርት” ለመተግበር እነዚሁኑ ባይተዋር መምህራንን ያሰማራል። በዚህም የአምስት ዓመቱን “ዕቅድ” እውን ለማድረግ እንደሚቻለው ይተነብያል። የትምህርት ሥራ ግን  በክፍል ውስጥ እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አይሠራም። ዋነኞቹ ባለጉዳዮች የኾኑት ተማሪ እና አስተማሪ ክፍል ውስጥ ምን እንደሚሠሩ ያውቁታል። ክፍል ውስጥ ባይተዋር የለም፤ የአምስት ዓመቱ ዕቅድም የለም። ያም ኾኖ የተማሪው ውጤት የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ የሚጠራጠር አይኖርም።http://www.addisnegeronline.com/2010/09/%E1%89%A3%E1%8B%AD%E1%89%B0%E1%8B%8B%E1%88%AD-%E1%88%98%E1%88%9D%E1%88%85%E1%88%AD-%E1%88%88%E1%88%9B%E1%8B%AD%E1%8C%A8%E1%89%A0%E1%8C%A0%E1%8B%8D-%E1%88%A5%E1%88%AD%E1%8B%90%E1%89%B0-%E1%89%B5/

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar