søndag 23. juni 2013

የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ከኃላፊነታቸው ተነሱ


የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ከኃላፊነታቸው ተነሱ

- ከምኒልክ ሆስፒታል ጥገና ጋር በተገናኘ መሆኑ ተጠቁሟል
በቅርቡ የተቋቋመው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ፈለቀ ኃይሌ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ታወቀ፡፡
 ከሰኔ 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውንና በእጃቸው ያለውን ንብረት እንዲያስረክቡ የሚገልጸው ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው ለመነሳት በዋና ምክንያትነት ያስቀመጠው፣ ከዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ሪፈራል ሆስፒታል እድሳት ጋር በተገናኘ ‹‹ሙስና ተፈጽሟል›› በሚል ጥርጣሬ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ለዘመናት ሳይታደስ በመቆየቱ ዋርዶቹ እየፈራረሱና ቅርስነታቸውን እያጡ በመምጣታቸው፣ እንዲሁም የሆስፒታሉ ግቢ ሰፊ ከመሆኑ አንፃር አዳዲስ ሕንፃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ግንባታዎች እንዲካሄድ በሚል፣ አስተዳደሩ ከአራት ዓመታት በፊት በመደበው በጀትና ከተለያዩ ወገኖች በተገኘ ዕርዳታ የተጀመረውን ግንባታ የቦርድ ኃላፊ ሆነው ሥራውን ይመሩት የነበሩት አቶ ፈለቀ ኃይሌ እንደነበሩ ምንጮች አስረድተዋል፡፡
በተያዘለት የጊዜ ገደብ ካለመጠናቀቁም በተጨማሪ፣ ‹‹ታድሷል ወይም ተሠርቷል›› በሚያስብል ደረጃ ሥራው አጥጋቢ እንዳልነበር የገለጹት ምንጮቹ፣ በወቅቱ ለግንባታው ወጥቷል የተባለው ወጪ ከፍተኛ እንደነበርም አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ ኮንትራክተሮች ሥራው ነካ ነካ ተደርጐ ለጊዜው የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ በተለይ በተቆርቋሪ ወገኖችና በአንዳንድ የአስተዳደሩ ኃላፊዎች ቅሬታ ፈጥሮ መክረሙን የገለጹት ምንጮች፣ ከአራት ወራት በፊት በሚስጥር በወቅቱ ተሠራ የተባለውንና የተቀመጠለትን የመቆያ ዕድሜ ከውጪው ጋር በማነፃፀር ጥናት ሲደረግ፣ ያላግባብ ወጪ መውጣቱን ከማመላከቱም በተጨማሪ፣ ዝቅተኛ ወጪ እንደወጣበት ተደርጐ መታለፉን የሚያሳዩ ጠቋሚ ነገሮች መገኘታቸውን ምንጮች አውስተዋል፡፡ በመሆኑም በወቅቱ ኃላፊ ሆነው ሥራውን ሲከታተሉ የነበሩት አቶ ፈለቀና ሌሎች ኃላፊዎች ተጠያቂ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ምንጮች ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን በቀጥታ ተነግሯቸው ሳይሆን ከሦስተኛ ወገን እንደሰሙ የሚናገሩት፣ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈለቀ በበኩላቸው፣ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
አቶ ፈለቀ እንደገለጹት፣ በሥራ ምክንያት ባለፈው ሳምንት ለሥራ ወጣ ብለው ነበር፡፡ የየካ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ በነበሩበት ወቅት የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ሆስፒታል ሲታደስ የቦርድ ኃላፊ ሆነው እድሳቱን የሚያስፈጽሙት እሳቸው ነበሩ፡፡ ከሥራው ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጉዳዮች ከአራት ወራት በፊት እየተጣሩ እንደነበር እንደሚያውቁ ገልጸዋል፡፡
ሥራውን በተመለከተ አንዳንድ ችግሮች አሉ በሚል እየተጣራ መሆኑንና ከሥራው ጋር የተያያዘም ነገር ሊኖር እንደሚችል የገለጹት አቶ ፈለቀ፣ በወቅቱ እሳቸው ኃላፊ ሆነው ሥራውን ቢመሩም፣ ማኔጅመንቱና የዲዛይን ግንባታ ክፍሉም አብሮ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
የግንባታ ሥራው በተለይ ዋርዶች መጠገናቸውን፣ የቆሻሻ ማስወገጃ መሠራቱን፣ ሴፍቲ ታንክና አጥር መገንባቱን የገለጹት አቶ ፈለቀ፣ በወቅቱ ስለተሠራው ሥራ ኦዲት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ የሚገኝ ነገር ካለ መጥራት ስላለበት እስከሚጠናቀቅ መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
‹‹ሆስፒታሉ ባዶ ነበር፤ ሥራ ስትሠራ በየጊዜው የሚኖር ነገር አለ፡፡ ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. በነበርኩበት ጊዜ የተሠራ ሥራ ነው፤›› ያሉት አቶ ፈለቀ፣ የማጣራት ሁኔታው በሚቀጥለው ሳምንት ሊያልቅ እንደሚችልም አክለዋል፡፡ በእነሱ በኩል የሚፈለግባቸውን መረጃ ሰጥተው ውጤቱን እየተጠባበቁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከኃላፊነታቸው የተነሱበትን ደብዳቤ ሰኔ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ሄደው እንደሚወስዱም አስታውቀዋል፡፡
ethiopian reporter

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar