torsdag 20. juni 2013

ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንና የዘረኛው ወያኔ ሹመኞች


በሰው ቁስል ላይ ጨው እየነሰነሱ የክርስቲያን ሥራ እየሰራሁ ነው ማለት አይቻለም።
በስመ አብ፤ ወወልድ፤ ወመንፈስ ቅዱስ፤ አሃዱ አምላክ፤ አሜን።
በ09/06/2013 በዕለተ እሑድ ለንደን በሚገኘው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከቅዳሴ በኋላ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደርና ሹማምንቶች የሚቀጥለውን ማስታወቂያ ለሕዝቡ አስተላልፈዋል።
  1. በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ሦስት ወራት መዘጋቷን፤
  2. ለብጥብጡና ለችግሩ መንስዔ የሆነው ቤተ ክርስቲያኗ ኢትዮጵያ በሚገኘው በቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ባለመመራቷ መሆኑን፤
  3. ቤተ ክርስቲያኗ ላለፉት 7 ዓመታት ኢትዮጵያ ከሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጥላ ብቻዋን ስትንከራተት ከቆየች በኋላ አሁን ተመልሳ መቀላቀሏን። (ማስታወቂያው ከተነገረ በኋላ እንደ ተለመደው ሕዝቡ የሚጠበቅበትን ጭብጨባና እልልታ እንዲያሰማ ተደረገ)
  4. ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ችግር መንስዔ የሆነው ጉዳይ እልባት ሊያገኝ የቻለው ከቅዱስ ሲኖዶስ ተልከው በመጡት በሊቃነ ጳጳሳቱ መሆኑንና የሰጡት መፍትሔም ቤተ ክርስቲያኗ በአቡነ እንጦስና በመጋቢ ተወልደ በሚመራው የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሃገረ ስብከት ሥር እንድትደዳደር መመሪያ ሰጥተው ወደ ኢትዮጵያ መለሳቸው ነው በማለት አብራርተዋል።
በመጨረሻም ርዕሰ አድባ
ራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሃገረ ስብከቱ ሥር እስከሆነች ድረስ ማንኛቸውም ምእመን በቤተ ክርስቲያኗ የመገልገል መብት ስላለው ቤተ ክርስቲያኗ ባስቸኳይ ተከፍታ አገልግሎቷን እንድትሰጥ ሕዝቡ ማመልከቻ (Petition) ላይ እንዲፈርም የተደረገ ሲሆን በገብረኤል ቤተ ክርስቲያንም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደተፈጸመ ለማወቅ ተችሏል።
ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ፡
  1. ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሃገረ እንግሊዝ ከተመሠረተች ከ40 ዓመታት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያ ከሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጥላ አታውቅም፤ አሁን የተፈጠረውም ችግር በቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ትሁን አትሁን ከሚለው ጥያቄ ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም።በእርግጥ ቤተ ክርስቲያኗ ኢትዮጵያ በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ሆና ብትቆይም ቤተ ክርስቲያኗ በውጪ ሃገር የምትገኝ በመሆኗ እና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተፈጠረው ችግርና መከፋፈል የተነሳ ከአንድም ሁለትና ሦስት ጊዜ በአባ ጳውሎስ አማካኝነት ከኢትዮጵያ ተልከው በመጡ እንደ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ፤ አቡነ ኢሳያስና በመጨረሻም በአቡነ ሙሴ አማካኝነት ተደጋጋሚ ችግር ስለደረሰባት የተፈጸመባት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋር ያላትን ግንኙነት ሳታቋርጥ አስተዳደሯንና ንብረቷን በተመለከተ ግን ቃለ ዓዋዲውን መሠረት በማድረግ  በUK የቻሪቲ ሕግ መሠረት ራሷን ችላ ስትተዳደር ቆይታለች። ይህንን አቋሟን ልለውጥ፤ ወይም ላሻሽል ብሎ የተነሳ ክርክርም ሆነ ጸብ የለም።
  2. ከዚሁ ጋር ቤተ ክርስቲያኗ አሁን በህይወት የሌሉት አባ ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያኗም ላይ ሆነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱትን በደልና ግፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት ስማቸውን ቅዱስ ብሎ ላለመጥራትና አመራራቸውንም ላለመቀበል የጠራ አቋም በመያዝ በዛ አቋም መሠረት ስትመራ
ከ7 ዓመት በፊት አቡነ እንጦስ ቤተ ክርስቲያኗን መንበሬ እንዳደርግ በአባ ጳውሎስ ተሹሜአለሁ ብለው በመጡበት ወቅት የቤተ ክርስቲያኗን አቋም ተቀብለው እንዲያገለግሉ ሲጠየቁ የቤተ ክርስቲያኗን አቋም አልቀበልም በማለታቸውና የአባ ጳውሎስንም ሥም ካልጠራሁ ላገለግል አልችልም በማለታቸው ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ሳይመጡ ቀርተዋል። “ቤተ ክርስቲያኗ ኢትዮጵያ ከሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጥላ ለ7 ዓመት ስትንከራተት ነበር” በማለት በስላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አማካኝነት ለሕዝቡ የተላለፈው መልዕክት ከአቡነ እንጦስ ተነጥላ በሚል ቢታረም ምናልባት ከእውነት ጋር ሊገናኝ ይችል ይሆናል እንጂ ቤተ ክርስቲያኗ ኢትዮጵያ ከሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ የተነጠለችበት ወቅትና ጊዜ የለም።
  1.  ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አቋሟንና አሰራሯን በማጥራት  አገልግሎቷ ሰፍቶና ተጠናክሮ ዕድገቷ በመፋጠኑ የቤተ ክርስቲያን ህንፃ ለመግዛት ጥረት በተጀመረበት ወቅት በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ቂምን የቋጠሩት አባ ጳውሎስ ሕዝበ ክርስቲያኑ ህንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገዛ ለማሰናከል ለAnglican Church ደብዳቤ በመጻፍ የቤተ ክርስቲያኑ ህንፃ ለስደተኛው ኢትዮጵያዊ እንዳይሸጥ ተቃውሞ አቀረቡ። ያም ሆኖ ግን ሰው ሳይሆን ፈጻሚው እግዚአብሔር ነውና የአባ ጳውሎስ የጭካኔና የተንኮል ተግባር ከሽፎ በታላቅ ርብርቦሽ የቤተ ክርስቲያኑ ህንፃ ከነ መኖሪያ ቤቱ ሊገዛ ችሏል።
በዚህ አሳዛኝ ተግባር እንኳ ሕዝበ ክርስቲያኑ በአባ ጳውሎስ ላይ እሮሮውን አሰማ እንጂ ኢትዮጵያ ካለው ቅዱስ ሲኖዶስ እንለይ፤ ወይም እንገንጠል የሚል ጥያቄ አላነሳም፤ ከዛም በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ ፀብና ክርክር አንስቶ አያውቅም።
በአሁኑ ወቅት ግን ስላሴ ቤተ ክርስቲያንን በር እረጋጣችሁ ብለው ካህናትን የሚያባርሩትና የሚያግዱት፤ ምእመናንን ስላሴ አትሂዱ በማለት ሲያስፈራሩና ሲያስጠነቅቁ የነበሩት፤ በኢትዮጵያ ባለው ሲኖዶስ ላይ መግለጫና ማስጠንቀቂያ ሲያዘንቡ የነበሩት አባ ግርማ ከበደና ተከታዮቻቸው ኢትዮጵያ ያለው ሲኖዶስ ደጋፊዎች ነን ብለው በመነሳት ሌላው ሕዝብ ኢትዮጵያ ያለውን ሲኖዶስ ተቃዋሚ አድርገው በማቅረብ የችግሩ መነሻም ሆነ ነድረሻ የሲኖዶስ ጉዳይ ነው የሚል አዲስ የቲያትር ደርሰው በተዋናኝነት ሲቀርቡ  ይህ ጉዳይ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንደሆነ የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አባላትና ሹማምንቶች በሚገባ እያወቁ ሕዝብን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ በሚወስድ መልኩ ማቅረባቸው በእጅጉ ያሳዝናል፤ ያስተዛዝባል።
  1. ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በያዘችው የጠራ አቋም በመጽናት ያለማንም የፓለቲካና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በነፃነት በመመራት ቀጥሎ የተመለከቱትን ተግባራት ታከናውን ነበር እንጂ ከቅዱስ ሲኖዶስ ተለይታ ስንትከራተት የኖረች አይደለችም።
  • ኢትዮጵያ ውስጥ ህጻናት፤ ጎልማሶችና አሮጊትና ሽማግሌዎች በመንግሥት ወታደርና የደህንነት ኃይል በግፍ ሲጨፈጨፉ አባ ጳውሎስ ግፍ የተፈጸመበትን ሕዝብ ትተው ለአገዛዝ ሥርዓቱ በመወገን መንፈሳዊነታቸውን ትተው ከፓሊተከኞቹ ብሰው በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ለሞቱት ሰዎች ጸሎት እንዳይደረግላቸው ሲያግዱ ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ግን ክርስቲያናዊ ያልሆነውን የአባ ጳውሎስን ማገጃ በመጣስ በግፍ ለተገደሉት ኢትዮጵያኖች ሙሉ ጸሎት አካሂዳለች።  (ይህም በመፈጸሙ ለሞቱት ኢትዮጵያኖች ጸሎት መደረግ የለበትም የሚሉ ካህናት ከቤተ ክርስቲያኗ ተነጥለው ነው ዛሬ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን መሥርተው የሚገኙት)
  • ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሕግ የበላይነት፤ ፍትሕና ነጻነት በሰፈነበት ሀገር የምትገኝ በመሆኗ በኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ በሌላው ዓለም በክርስቲያኖችና በመላው ሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈጸምን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን፤ ግፍና በደል ሁሉ እንደ ቤተ ክርስቲያን በነፃነት በመቃወምና በማወገዝ የድርሻዋን ስትወጣ ኖራለች፡፤
  • በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ገዳማት ሲጠቁና ሲቃጠሉ ቤተ ክርስቲያኗ ማንኛቸውም መንግሥትና የፓለቲካ ተቋም ጫና ሳይገድባት የተቃውሞ ድምጿን ከፍ አድርጋ አሰምታለች፤ አቅም በፈቀደም ለተጎዱትና ለተጎሳቆሉት ገዳሞችና ቤተ ክርስቲያናት ያለመንግሥት ተጽዕኖና ጣልቃ ገብነት በነጻነት እርዳታና ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች፤
  • በቅርቡ ዋልድባ ገዳም ለሸንኮራ አገዳ ተክል ተብሎ ታሪካዊ ቦታዎች ሲፈርሱ መቃብራት ሲታረሱ፤ መነኮሳት ሲበደሉና ሲሳደዱ ከሲኖዶስ ጀምሮ ወደ ታች ያለው በመንግሥት ተጽዕኖ አፉ ተለጉሞ፤ እግሩና እጁ ታስሮ ሲቀመጥ ሌላው ቀርቶ በዚህ በምንኖርበት በነፃነት ሃገር የሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናት ሳይቀሩ ራሳቸውን ከመንግሥት መዋቅር ጋር በማያያዝ በሃይማኖታቸውና በቤተ ክርስቲያናቸው ላይ የሚደርሰውን ጥቃቅ በጸጋ ለመቀበል ሲገደዱ ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ግን በዓለም ተዋዊ በሆነው በእንግሊዝ ፓርላማ ፊት በመውጣት የተቃውሞ ድምጿን አሰምታለች።
በዚህ መሠረት ውድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሁሉ የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለሕዝብ ከገለጸው ማስታወቂያ ውስጥ የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረጽዮን ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ወር መዘጋት ካልሆነ በስተቀር የተቀረው በሙሉ ሃሰትና ሕዝብን አሳስቶ በፓለቲካ መሣሪያነት ለመጠቀም ሆነ ብሎ የተቀነባበረ የቅስቀሳና የፕሮፓጋንዳ ተግባር ብቻ መሆኑን ልትገነዘቡት ይገባል።
በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠርውን ችገር ለመፍታት ወይም ለማስታረቅ ከኢትዮጵ መጡ የተባሉት ሊቃነ ጳጳሳት ስብስበው ያነጋገሩትና የሥላሴ፤ የገብረኤልና የጸራጽዮን ቤተ ክርስቲያን አባላትን እና ከለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ አባ ግርማንና ደጋፊዎቻቸውን ብቻ ሲሆን ያደረጓቸው ሁሉም ስብሰባዎቻቸው ደግሞ ምእመኑ ተሰብስቦ
  • የሊቃነ ጳጳሳቱን ትምሕርትና መግለጫ ያዳመጠበት፤
  • ቤተ ክርስቲያኗ ኢትዮጵያ በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር እንድትሆንና አስተዳደሯም ሆነ ሃብትና ንብረቷ በሃገረ ስብከቱ ስር ሆኖ አቡነ እንጦስ መንበራቸው በቤተ ክርስቲያኗ እንዲሆን ካህናቱ ተስማምተው መፈራረማቸውን፤ ሲገልጹ እልልታና ጭብጨባውን የለገሰበት፤
  •  አባ ግርማ ከበደ የማይወክሉትን ሕዝብ እወክላለሁ፤ የሌለውን የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ አለ በማለት የስላሴንና የገብረኤልን አብያተ ክርስቲያናት አባላት የውሸት ይቅርታ የሚጠይቁበትን ዲስኩር በመስማት፤ እልልታና ጭብጨባውን ያሰማበት ብቻ ነበር እንጂ ሃሳብና አስተያየቱን የሚሰጥበት ወይም ውሳኔ የሚያስተላልፍበት አልነበረም።
ሊቃነ ጳጳሳቱ አባ ግርማ በሕዝበ ውሳኔ ከሥልጣናቸው መውረዳቸውንና የተቀሩት ሁለት የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ አባላት ካህናት ማሟያ ተመርጦላቸው አብረው እንዲሰሩ ቢጠየቁ አሻፈረኝ በማለታቸው የቤተ ክርስቲያኗ አባላት የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ከካህናት፤ ከምእመናንና ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተውጣጣ አዲስ የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ መርጠው መሰየማቸውን ተገቢው ገለጻ በተደረገላቸው ወቅት የሰጡት ጠንካራ ምላሽ “ከቤተ ክርስቲያን ሕግ አኳያ ቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር ከቤተ ክርስቲያኑ ውጪ የተደረገው ምርጫ ሁሉ ምንም ዓይነት ሕጋዊነት የለውም” የሚል ነበር።
ይህንን ቃል ካረጋገጡና ካስረዱ በኋላ ግን ሊቃነ ጳጳሳቱ ራሳቸው ከአባ ግርማና ደጋፊዎቻቸው በስተቀር የተቀረው የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን  ቤተ ክርስቲያን አባላት ባልተገኙበት ከቤተ ክርስቲያኗ ውጪ ጉባኤ በማካሄድ ይባስ ብለው ለደረሰው ችግር ሁሉ ዋናው መንስዔና የችግሩ ሁሉ ዋና ተጠያቂ አባ ግርማንና ሌሎች የአባ ግርማን ሥልጣን ያጠናክራሉ ያሏቸውን ሰዎች ሥራቸውን በለቀቁት የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ አባላት ምትክ በመሾም ቤተ ክርስቲያኗን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ለሀገረ ስብከቱ እንዲያስረክቡ መመሪያ ሰጥተል።
ይህንን ሹመትና ድልድላቸውን ለማጠናከርና የአባ ግርማና ደጋፊዎቻቸውን ተግባር የተቃና ለማድረግ ሊቃነ ጳጳሳቱ አሁንም አብዛኛው የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ባልተገኙበት በገዛ ፍቃዳቸው ሥራቸውን ለለቀቁት ምእመናን የሰባካ አስተዳደር ጉባኤ አባላት የቤተ ክርስቲያኗን ምሥል የያዘ ፎቶ ግራፍና ምሥክር ወረቀት ሸልመዋል።
ከላይ የተጠቀሰውን ድርጊት ነው የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የሊቃነ ጳጳሳቱ ተልዕኮ ስኬትና የማርያም ቤተ ክርስቲያንም ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የመፍታት ዜና አድርጎ ያቀረበው።
የማርያም ቤተ ክርስቲያን ችግር ቢፈታና ቤተ ክርስቲያኗ ተከፍታ አገልግሎቷን ብትጀምር ከሁሉም በላይ የቤተ ክርስቲያኗን አባላት የሚያስደስት በመሆኑ ማስታወቂያው እውነትነት ቢኖረው ምንም ባላነጋገረ። ነገር ግን ማርያም በተዘጋችና አባላቷም ባዘኑና በተንገላቱ የቤተ ክርስቲያኗን ችግር መጠቀሚያ አድርጎ የራስን ዓላማና ምኞት ማሳኪያ አድርጎ ለመጠቀም መሞከር በቁስል ላይ ጨው እንደመነስነስ ይቆጠራል።
ሌላው ሊቃነ ጳጳሳቱ ከላይ የተዘረዘርውን ተግባር ሲያከናውኑ፡
  1. አባ ግርማ ከበደና የእሳቸው ተከታይ የሆኑትን ጥቂት ካህናትና ምእመናንን ከማየትና ከመቅረብ በስተቀር  ከዛ ውጪ ያለውን አብዛኛውን የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያንን አባላት ስብስቡልንና ችግሩ ምን እንደሆነ ከሁለቱም ወገን እንስማ የሚል ጥያቄ ቀርቶ ዝንባሌም አሳይተው አያውቁም፤
  2. ለሕዝቡ የስብሰባ ጥሪ በሚደረግበት ወቅት የተጣላ ባልና ሚስትን ለማስታረቅ ባልና ሚስቱን ትቶ ጎረቤቱን ሁሉ ሰብስቦ ከማነጋገር ጋር በተመሳሰለ ሁኔታ የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ችግር ለመፍታት በሚል የሚጠሩት የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት አባላትን በመሆኑ፤ ችግሩን ለማወቅም ሆነ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል አንዳችም ሁኔታ አልተፈጠረም ነበር።
  3. ሊቃነ ጳጳሳቱ ባደረጓቸው ጉባኤዎች ሁሉ የነሱንም ሆነ የካህናቱን ውሳኔና መግለጫ እያሰሙ ሕዝቡ ጉዳዩ ይግባውም አይግባው መብቱና ድርሻው እልልታ ማሰማትና በእጁ ማጨብጨብ ብቻ ስለሆነ በየትኛውም ስብሰባ ላይ ሕዝበ ክርስቲያኑ የተወያየበት ወይም ጠይቆ የተረዳበት አንዳችም ጊዜ አልነበረም እንዲኖርም አላደረጉም።
ይህ ሁሉ የሚደረገው አሰራሩም ሆነ እውነታው ሳይታወቅ ቀርቶ ሳይሆን ከኢትዮጵያ የመጡት ሁለት ሊቃነ ጳጳሳትና ለንደን የሚገኙት የሃገረ ስብከት ሊቃነ ጳጳስ ዓላማቸው ቤተ ክርስቲያኗ ከችግሯ ተላቅቃ መልሳ በሁለት እግሯ ሳትቆምና ሳትጠናከር አስተዳደሯንም ሆነ ሃብትና ንብረቷን የ”ሰሜን ምዕራብ አውሮፓ” ተብሎ በተቋቋመው ሃገረ ስብከት ስር ማዋል አለብን የሚለውን ዕቅድ ማራመድ ስላለባቸው ብቻ ነው።
ይህንን ለማስፈጸም የሚቻለው ደግም ቤተ ክርስቲያኗ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር እስከምትውል ድረስ በአሁኑ ወቅት በዋና መሣሪያነት ሊጠቅሙ የሚችሉትን አባ ግርማንና ጥቂት ተከታዮቻቸውን በማጠናከር እነሱን ግንባር ቀደም ተፋላሚ አድርጎ ከነሱ ኋላ ሆኖ በመሥራት ነው።
እዚህ ላይ ከኢትዮጵያ የመጡት ሊቃነ ጳጳሳት አባ ግርማ ከበደ እንዴት ለችግሩ መንስዔና ተጠያቂ እንደሆኑ፤ እሳቸው በአስተዳደር ሥልጣን ላይ እያሉም ችግሩ ሊፈታ እንደማይችል በተጨባጭ ማስረጃ ሲገለጽላቸው ጉዳዩን አምነው በመቀበል መፍትሔውም አባ ግርማንና መሰሎቻቸውን ከቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ማንሳት እንደሆነ በሚገባ ተረድተው ከወሰኑ በኋላ መልሰው ሲገመግሙት ግን የሃገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የበላይ ተቆጣጣሪ አድርጎ ለማስቀመጥ አስተማማኝ መንገድ መስሎ ስላልታያቸው አባ ግርማንና ተከታዮቻቸውን ሥልጣን አጠናክሮ በማቆም በዛ መሸጋገሪያነት ቤተ ክርስቲያኗን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ይቻላል በሚለው ስልት በመለወጥ ምንም ዓይነት ሕጋዊነት የሌለው ሹመትና የስራ ድልድል አድርገው ችግሩ ጭራሽ ወደ ባሰና ወደ ከፋ ደረጃ የሚሸጋገርበትን የችግር ቦይ ቀደው ሊሄዱ ችለዋል።
የስላሴና የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን አባላት በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊነታቸው ከዛም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይነታቸውና በአንዲት የስደት ሀገር የሚገኙ በመሆናቸው ግዙፍ በሆነ አንድነት፤ በወንድምነት፤ በእህትነት፤ በአባትና ልጅነት የሚተያዩ ናቸው እንጂ የፓለቲካና የጎሳ ዘይቤ የተጠናወታቸው ጥቂት አመራሮች በፈጠሯት ጥፍጥሬ በምታክል የአቋም ልዩነት በጠላትነት ሊተያዩ የሚችሉ አይደሉም።
ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ፡ በማርያም ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ችግር መነሻው ውሸት ነው፤ ውሸቱንም የጀመረው አስተዳደሩና አስተዳዳሪው ናቸው፤ ውሸቱ እያደገ በሄደ ቁጥር ችግሩም እየሰፋ ሄደ፤ ውሸቱ ሕዝቡን ሲያጥለቀልቀው ችግሩም ሕዝቡን አጥለቅልቆታል።
ከጅምሩ ገና ውሸቷ ማቆጥቆጥ ስትጀምር በአንድነት ቆመን ብንዋጋና ብንጨፈልቃት አድጋና ተጠናክራ በክርስቲያኖች መካከል ግንብ ሰርታ ሕዝብን የመከፋፈል አቅም ባላገኘች ነበር። ዛሬም በስላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተጀመረው  ውሸት የሃገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ በማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ የሥልጣን መቆናጠጫ መሰላል ለማመቻቸት እንጂ ለሥላሴም ሆነ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚፈይደው ነገር ኖሮ አይደለም።
ይልቁንም ይህንን የመሰለ ችግር በማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲደርስ የሌላው ቤተ ርክስቲያን አባላት በማዘንና በመቆጨት እግዚአብሔር መፍትሔውን እንዲያመጣ በጸሎትና በልመና መርዳት እንጂ ምን ዓይነት መግለጫና ማብራሪያ በፈረማችሁት ማመልከቻ (Petition) ላይ ተጨምሮ እንደሚተላለፍ መተማመኛ ሳይኖርና አንዴ የተፈረመውን አስተዳደሩ ለሌላም ጊዜ እንዳማይጠቀምበት ማረጋገጫ በሌለበት በየዋህነት ብቻ ማመልከቻ (Petition) ላይ መፈረም አንዱን ክርስቲያን በሌላው ላይ በማስነሳትና እርስ በእርስ በማጋጨት ከፍተኛ ጸብና ጥላቻን ቀስቅሶ  ያንዱ ቤተ ክርስቲያን ችግር እንደ ተስቦ ወደ ሌላው ቤተ ክርስቲያን በመዛመት ከፍተኛ መዘዝን ቀስቅሶ ያልታሰበና ያልተገመተ ችግርን ለሚያመጣ ተግባር መሣሪያ እንዳትሆኑ መጠንቀቅ ይገባችኋል።
በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሚችለው እግዚአብሔር  እና የምንኖርበት ሃገር ሕግ ብቻ ነው።
ብልጣ ብልጦችና የውሸት ቋቶች ሃይማኖታችሁን፤ የዋህነታችሁንና ሰው አማኝነታችሁን ተጠቅመው እሬቱን በማር ለውሰው፤ ሃሰቱን የውሸት ቀለም ቀብተው እያቀረቡላችሁ ሳታውቁ በገዛ ጥርሳችሁ ምላሳችሁን እንዳትነክሱ ከማርያም ቤተ ክርስቲያን ችግር በመማር እንደ እርግብ የዋህ ብትሆኑም እንደ እባብ ብልህ መሆን ይጠበቅባችኋል።
ከላይ የተጠቀሰው መልዕክት ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚመለከት ሲሆን የሥለሴ ቤተ ክርስቲያን እና የገብረኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳደሮችና ሹማምንቶች በተመለከተ በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት አንዱን ወገን በመደገፍ ሌላውን ወገን ለመጉዳትና የቤተ ክርስቲያኗን ችግር ወደ ባሰ ደረጃ ለማድረስ የሚደረጉ ተግባራት ሁሉ እስካላቆሙ ድረሥ ይህንን ተግባር በሰላማዊ መንገድ ለመቃወም በሚወሰደው እርምጃና በዚህም ሳቢያ ለሚደርሰው ማንኛቸውም ነገር ተጠያቂ መሆናቸውን ከወዲሁ ለማስገንዘብ እንወዳለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar