tirsdag 18. juni 2013

ፌዴሬሽኑ የፊፋን ክስ አመነ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምንያህል ተሾመ ሁለት ቢጫ ካርድ አይቶ ሳለ ሰኔ 1/2005 ከቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን ጋር በተደረገው ጨዋታ መሰለፉ ስህተት እንደሆነ አመነ፡፡
ፌዴሬሽኑ ብሄራዊ ቡድኑ ከደቡብ አፍሪካ  አቻው ጋር ከመጫወቱ በፊት ችግር ስለመፈጠሩ ፊፋ አሳውቆት እንደነበር ገልጿል፡፡
ሆኖም ይህ ችግር በቡድኑ ተጫዋቾችና በደጋፊዎች ላይ ያልተፈለገ የመንፈስ ጫና እንዳይፈጥር በመስጋት መረጃውን ይፋ ሳያደርግ ቆይቷል፡፡
ፌዴሬሽኑ በፈጠረው ችግር ዙሪያ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ መሰረት ፊፋ ተጫዋቹ ሁለት ቢጫ ካርድ በማየቱ የተነሳ ከቦትስዋና ጋር በሚካሄደው ጨዋታ እንዳይሰለፍ የሚገልፅ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ልኳል፡፡ ይሁንና የፌዴሬሽኑ አመራሮች ይህን የፊፋ ውሳኔ በመዘንጋታቸው ተጨዋቹን አሰልፈውታል፡፡
የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለችግሩ ተጠያቂ ያላቸውን ግለሰቦች ዝርዝርም ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህ መሰረት የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንትና የብሄራዊ ቡድኑ ቡድን መሪ አቶ ብርሀኑ ከበደ፣ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ ረዳት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፣ የቡድኑ ተጨዋች ምንያህል ተሾመና ሌሎች የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤቱ ኃላፊዎች በጥፋተኝነት ተፈርጀዋል፡፡
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጥፋተኞቹ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት እንደሚገባቸው የተስማማ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ የቅጣት ውሳኔውን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የፌዴሬሽኑ በተፈጠረው ችግር ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማው ገልፆ ለኢትዮጵያ ህዝቦችም ይቅርታ ጠይቋል፡፡
በፊፋ ህግ መሰረት ተገቢ ያልሆነ ተጨዋችን ማሰለፍ በጨዋታው የተገኘውን ነጥብ የሚያሳጣና ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣትም የሚያስጥል ነው፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በተፈጠረው ስህተት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው ጳጉሜ 2/2005 ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ለሚካሄደው ጨዋታ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ጨዋታ አሸንፈን ወደ አለም ዋንጫ እንደምንሳተፍ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል አሰልጣኙ፡፡
ተጨማሪ መረጃዎች ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ እናቀርባለን፡፡
 ሪፖርተር- ሰይፉ አለምሰገድ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar