fredag 8. februar 2013

ታደሰ በዛብህ የመርካቶው አይጥ (ክፍል ሁለት)


ክፍል ሁለት
<<የተረፉት በሞቱት ይቀናሉ. . . 
በልጅግ ዓሊ
ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ የሚገኘውን የመቃብር ቦታ  ግቢ ውስጥ የሚገኝ አዳራሽ አለ። ዜጎቻችንን ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ወቅት አስከሬኑን ወደ ሃገራችን መላክ የተለመደ ቢሆንም፣ አንዳንዴ እንደ ሟች ወይም እንደ ሟች ቤተሰብ ፍላጎት የቀብሩ ሥነ ስርዓት እዚሁ ፍራንክፈርት ውስጥ ይፈጸማል። ቀብሩ ከመፈጸሙ በፊት እዚህ አዳራሽ ውስጥ የቤተ ክርስትያን ሰዎች ትምህርት ይሰጣሉ። ቤተሰብንም ያጽናናሉ። ፍራንክፈርት ውስጥ የቀብር ሥነ ስርዓት ከተፈጸመው መካከል አንድ ውድ ወንድማችን በፍራንክፈርት ነዋሪ በሆኑ ዜጎቻችን ልብ ውስጥ በማይጠፋ ቀለም ተጽፎ አልፏል። በላይ ዳኛቸው። በላይ ዳኛቸው ለሃገሩ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል ብዙ ታግሏል። በላይ ብዙ ያልተነገረለት ጀግና ነበር። ይህንን ጽሁፍ ስጽፍ አስበዋለሁ። ምንአልባትም የበላይና የታደሰ የውስጥ ምሥጢር ተመሳሳይ ይሆን ይሆናል። ምንአልባት ልንደርስላቸው ስንችል አልደረስንላቸው ይሆን?
የፍራንክፈርቱ የመቃብር ቦታ አዳራሽ ውስጥ በበላይ ዳኛቸውን ቀብር ምክንያት ተሰብስበን ትምህርቱ ሲሰጥ ግድግዳው ላይ ከነበሩት ጽሁፎች ሳነብ አንዱ እንዲህ ይላል፡ -

Selig sind, die da Leid tragen, denn sie sollen getröstet werden.
የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው መጽናናትን ያገኛሉና። ማቴ 5፡4
Tadesse Bezabh Ethiopian adopted kid in Germany1ስንት ዜጎቻችንን ልንረዳቸው ስንችል፣ ሳንረዳቸው ቀርተን የመጨረሻውን ውሳኔ ወስደው ይሆን? ይህ ሁሉ ችግራችን መቼ ይሆን የሚቀረፈው? ሕጻናቶቻችን በውጭ ሃገር በዘር ልዩነት መድረሻ አጥተው ራሳቸውን አጥፍተዋል። ሕጻናቶቻቸንን የጠገበ ፈረንጅ የፍትወተ ሥጋ ማርኪያ ሆነዋል። ሕጻናቶቻችን ማንም የማይናገርላቸው፣ ራሳቸውም መናገር የማይችሉ ድምጽ አልባ ናቸው። ዛሬ በማደጎ ስም ስለሚሸጡ ሕጻናት ችግር ከመወያት፣ አዲስ አበባ መንገድ ላይ በልመና  ስለ ተሰማሩት ሕጻናት መፍትሄ ከመሻት፣ ደልቃቆች፣ የወያኔ ሥርዓት አሽቃባጮች፣ አዲስ አበባ ውስጥ ስለለተገተረው ኦና ሕንጻ ሲደለቁ እንሰማለን። ዛሬ  በተወለዱበት ዘር ምክንያት፣  የወያኔ ፖለቲካ በፈጠረው ዘረኝነት፣ ሃገራቸው ውስጥ የተሰደዱ ሕጻናት ቁጥር ትንሽ አይደለም። ሕጻናት በሃገራችን በሁሉም ሥርዓት በጣም የተጠቁ ሲሆን የጮኹላቸው ግን ቁጥራቸው አነስተኛ ናቸው። ከእነዚህ ሕጻናት መሃል አንዱ ታደሰ በዛብህ ዞል ነበር።
Germay country sideታደሰ ከማደጎ ቤተሰቦቹ ጋር ለመኖር ከአዲስ አበባ ከመጣ በኋላ፣ በደቡብ ጀርመን፣ በባደን ቩተንበርግ ክፍለ ሃገር (Baden-Württemberg)ውስጥ በምትገኝ ሚሸልባህ በምትባል  (Michelbach an der Bilz) ትንሽ ከተማ ውስጥ ይኖር ነበር። የዞል ቤተሰቦች ከታደሰ ጋር ስድስት ልጆች ነበሯቸው። እናትየው እርምሂልድ ዞል (Irmhild Söhl) ስትባል አባትየው ደግሞ ፍሬሪሽ  (Frerich  Söhl) ይባላል። ሚሽልባህ በ2010 በተደረገው ቆጠራ 3375 ነዋሪ ሲኖራት ከዚህ ውስጥ  124 የውጭ ሰው ነው። ከዚህ ከ124 ውስጥ ስንቱ ጥቁር እንደሆነ ማወቅ አይቻልም።
የታደሰን መሞት በሚመለከት የማደጎ እናቱ (Irmhild Söhl) <<ታደሰ ለምን?>> <<Tadesse, warum?>>የሚል መጽሐፍ ጽፋለች። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በተለይ እሷ ለልጇ ለታደሰ የነበራትን ፍቅር ፣ እሱም ለእሷ የነበረውን ፍቅር በሰፊው ተገልጿል። በተለይ የታደሰ የመጨረሻው ቀን ለቤተሰቡ ሰቀቀን ሆኖ የቀረ ነው። እሷ ልትረሳው ያልቻለችው እንደሆነ ከጽሁፏ መረዳት ይቻላል። ስለ ታደሰ አሟሟት(Hamburger Abendblattes)የሚባል ጋዜጣ በታህሳስ 1996 እትሙ እንዲህ ብሎ አስቀምጦታል።
Tadesse Bezabh Ethiopian kid from Germany “Feindseligkeiten und Demütigungen, diedem fröhlichen Jungen das Leben schwermachten. ‚Nigger‘, ‚Buschneger‘ oder ‚schwarze Sau‘ nannten ihn seine Schulkameraden.
<<ጥላቻ  የሚፈጥሩና ሞራልን የሚሰብሩ ንግግሮች ደስተኛ የነበረውን ወጣት ሕይወት በጣም አስቸጋሪ አድርገውታል። ኒግር ፣ የጫካ ኒግር ወይም ጥቁር አውሬ ይሉት ነበር የክፍል ጓደኞቹ። >>
እንደዚህ ዓይነት ስድቦች በክፍል ጓደኞቹ ብቻ ሳይሆን በአስተማሪዎችም ደረጃ በተለያየ መልክ ስለሚሰማቸው ሕይወቱን እስከ ማጥፈት ደርሷል።
ታደሰ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት የተቀየረ ጊዜ ትልቅ ችግር እየገጠመው መጣ። የጀርመን ትምህርት አራተኛ ክፍልን ሕጻናት ከጨረሱ በሁዋላ በሁለት ይከፈላሉ። እሱም Hauptschule or Gesamtschule ይባላሉ። Gesamtschule ደግሞ  Realschule እና Gymnasium ያጠቃልላል።  ልዩነቱ የመጀመሪያ ከ10ክፍል አቁመው ወደ ቴክኒክ ትምህርት ቤት የሚወስድ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ያስቻላሉ። ይህ ምደባ በተማሪዎቹ ጉብዝና ይወሰናል። ታደሰ Realschule እንዲገባ ተፈቅዶለት ትምህርት ቤት ቢሄድም አስተማሪው ግን ታደሰን መቀበል አልፈለገም ። በዚህ ምክንያት በሁለቱ መካከል ክርክር ይነሳል።
- << የት ልትሄድ ነው የምትፈልገው?>> አስተማሪው ይጠይቃል።
- <<የትም መሄድ አልፈልግም ?>> ይላል ታደሰ።
- <<ምን ትሰራለህ እዚህ ታዲያ?>> አስተማሪው መጮህ ጀመረ ።
- <<ምንም አልሠራም።>> አለ ታደሰ
- <<ጥፋ ከዚህ ።  (Hauptschule) ነው ላንተ የሚገባው።>> አለ አስተማሪው።
- <<እኔ ( Hauptschule) ተማሪ አይደለሁም። እኔ ( Realschule) ተማሪ ነኝ።>> አለ ታደሰ።
- <<አስተማሪው ተናዶ የታደሰን ትከሻ ይዞ ይንጠው ጀመር። አንተ እዚህ ልትሆን አትችልም። ሂድ ወደ     Hauptschule >>ይለው ጀመር። እየገፋፋ ሊያስወጣው ሞከረ።
- <<እውነቴን ነው። እኔ እዚህ ነው የተመደብኩት>> ብሎ አስተማሪውን ነገረው። አስተማሪው ግን ይበልጥ እየገፋፋ ሊያሰወጣው ሞከረ ። ሌላ ተማሪ መሰከረለትና አስተማሪው ታደሰን ተወው።
ከዚህ ድርጊት እንደምንረዳው አስተማሪው ታደሰ ጥቁር በመሆኑ ብቻ ከፍ ላለው ደረጃ አይደርስም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል ማለት ነው።ይህንን ከላይ የጠቀስኩትን በተለያየ ሃገር የምትኖሩ ስታነቡት ለማመን ያዳግታችሁ ይሆናል። ግን ጀርመን ለኖርነውና ብዙ ላየነው ችግሩን ለመገንዘብ አስቸጋሪ አይደለም። ታደሰ ጀርመን ሃገር እያለ ብዙ ችግሮች ደርሰውበታል።  ችግሮች እናቱ ከጻፈችው በላይ እንደሚሆኑ ደግሞ ጥርጥር የለውም። ታደሰም ሁሉንም ነገር አይናገረም።በተለይ የታደሰ የመጨረሻው ቀኖቹ አስከፊ ነበሩ።
የታደሰ የመጨረሻ ቀን እንዲህ ነበር፡ -
ትምህርት ቤት ከተጀመረ ጥቂት ሳምንታት አልፈውታል። ታደሰ እየሮጠ ወደ ቤት ይመጣል። የማደጎ እናቱ  በማድቤቱ መስኮት በኩል ስትመለከት አንድ ችግር እንደተፈጠረ ገባት። ለእሷ በማይገባት ቋንቋ እየጮኸ ይናገራል። ባርኔ የምትባለው ውሻው እንደለመደችው በራፉ ላይ ብትጠብቀውም ፍቅሩን ሊያሳያት አልቻለም። እንዲያውም  እስክትጮህ ድረስ በንዴት በርግጫ ብሏት በችኮላ ወደ ቤት ውስጥ ገባ። የትምህርት ቤት ቦርሳውን  ጃኬቱንና ኮፍያውንም ጭምር አልያዘም።። ዓይኖቹ በንዴት ፈጠዋል።
<<ምን ሆነሃል ታደሰ? >>ብላ እናቱ ጠየቀችው። እያለቀሰ ወደ ማድቤት እንድትመጣ ከጠየቃት በኋላ ከምድጃው ውስጥ ያለውን የኬክ መሥሪያ እያሳየ ፡ -
<<ትመለከቻለሽ . . .  ይህንን አየሽው ! !>> እያለ ይጮኽ ጀመር።
ነገሩ ስላልገባት <<ምንድነው ማየት ያለብኝ ታደሰ ? >>ብላ ጠየቀችው።
እንደገና  እያሳየ ፡ -
<<ይህ ነው ጥቁር ፣ እኔ ቡናማ ቀለም ነው ያለኝ ። አስተማሪዋ ግን ሁል ጊዜ ጥቁር ነህ ትለኛለች። ዛሬ ስፖርት የምንሠራበት ቦታ ላይ።<< Schwarzer Mann komm mal hier>> <<ጥቁሩ ሰውዬ ወደዚህ አንድ ጊዜ ና>> አለችኝ:: ሌሎቹን በሰማቸው ነው የምትጠራው። ፒተር ፣ ኦሊቨር ፣ ኤልቬራ እያለች። እኔም እንደ ሌሎቹ አንድ ስም አለኝ ። ታደሰ እባላለሁ። ታያለሽ እኔ ቡናማ ቀለም ነው ያለኝ ።>>
እናቱ በፍቅር እቅፍ አድርጋ << አዎ ቡናማ ቀለም ነው ያለህ። ቆንጆ ቡናማ ቀለም . . . >> ብላ አረጋጋችው። ውሻዋ በራፉን እየቆረቆረች ስላስቸገረች እንድትገባ ከፈቱላት። ታደሰም ውሻዋን << ይቅርታ አድርጊልኝ>> በማለት ያሻሻት ጀመር ።ከዛም ወደ ክፍሉ ሄደ።
የታደሰ የማደጎ እናት አዲስ ወደሚሠራው ቤታቸው ለመሄድና አባታቸውና ልጆቹ የመሬቱን ማንጠፍ ጉዳይ ምን እንዳደረሱት ለማየት ስትጣደፍ፣  ታደሰ ክፍሉ ውስጥ እያንኮሻኮሸ ነበር። ከክፍሉ በድንገት ወጥቶ በስፖርት የተሸለመውን የምስክር ወረቀትና አንድ ፎቶ <<ይህ ላንቺ ነው እናቴ>> እያለ በፈገግታ ሰጣት። ከሞተ በኋላ ነበር ይህ የመጨረሻው ስጦታ ከልቡ እንደነበርና የመጨረሻ የመሰነባበቻው ፈገግታው መሆኑ የገባት።
<<አመሰግናለሁ>> ብላ በሩን  ዘግታ  ሄደች ። ያ ነበር በሕይወት ለመጨረሻ ጊዜ ታደሰን ያየችው ።
የአዲሱ ቤት ለግማሽ ሰዓት ከቆየች በኋላ ከታደሰ ታናሽ እህት  ከሮና ጋር ወደ ቤት ተመለሱ። ሮና ወደ ልጆች ክፍል ሄዳ፣ በጣም ደንግጣ እየጮኸች <<እናቴ ቶሎ ነይ! ታደሰ ቁም ሳጥኑ ላይ ተሰቅሏል>> አለቻት። ሮጣ ወደ ክፍሉ ስትገባ ታደሰ ከቁም ሳጥኑ ጀርባ ተሰቅሏል። ታደሰ . . . .  ታደሰ ብላ ጮኸች። ታደሰ ግን ምንም አይሰማም።ታደሰ በተወለደ በአሥራ አንድ ዓመቱ ራሱን ሰቀለ ።
የታደሰን ታሪክ እየፃፍኩ ሳለ በጀርመን ትምህርት ቤት ውስጥ በጥቁር ልጆች ላይ የሚፈጸመውን በደል ለማወቅ ልጄን፡ -
<<ታደሰን አስተማሪው በስሙ ሳይሆን  << schwarzer Mann >> << ጥቁሩ ሰው>> ብላ ነበር የምትጠራው አንቺስ ላይ የደረሰ ነበር ወይ ?>> ብዬ ጠየቅኋት።
<< አንድ ቀን አንድ አስተማሪ ስፖርት በምንማርበት ክፍል ውስጥ አንድ ጨዋታ እንድንጫወት ጠየቀችን። ጨዋታው የሚባለው << Wer hat angst von Schwarzer Mann >> <<ማነው የጥቁሩ ሰው ፍራቻ ያለው >> ይባላል። ጨዋታው ጥቁሩ ሰው መሃል ይቆምና ሌሎቹ ይሸሻሉ። ጥቁሩ ሰው በእጁ የነካው መሮጥ አይችልም መቆም አለበት። ጨዋታውን ካስረዳችን በኋላ ወደ እኔ እየተመለከተች << ይቅርታ ጨዋታው እንደዚህ ስለሚባል ነው አለች >>
<< እና ለምን ለእኔ ነገርሽኝ?>> ብዬ ጠየኳት ።
<< አንቺ ጥቁር ስለሆንሽ ነው >> አለችኝ ።
በዛ ክፍል ውስጥ የውጭ ሰዎች ብዙ ስለነበርን የባሰ ስቀንባት አበሸቅናት። ታደሰ የሚኖርበት አካባቢ እንኳን ጥቁር የውጭ ሃገር ሰው ቢሆን በቁጥር ነው። ለዚህም በጣም ችግር ነው ብላ አስረዳችኝ።
ዘረኝነት ጀርመን ውስጥ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ትልልቅ ከተማዋች የሚኖሩት ብዙም ችግር ላያጋጥማቸው ይችላል። እንደ ታደሰ ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ግን ስቃያቸውን ነው የሚያዩት።
በታደሰ ደብተሮች ውስጥ የተገኙት ይጽፋቸው የነበሩት በሙሉ  ይህንን አጉልተው ያሳያሉ። ለምሳሌ በጎን የምታዩት የታደሰ ጽሁፍ እንዲህ ይላል።
Tadesse Bezabh Ethiopian kid in Germany letterአንዳንድ ልጆች ቢጫ ናቸው ፣
አንዳንዶቹ ነጭ፣
እና እኔ ጥቁር ነኝ፣
አንዳንድ ልጆች ደግሞ ቡናማ፣
እና እኔ ጥቁር ነኝ፣
ስለሆነም እኔ ከሌሎቹ የተሻልኩ አደለሁም፣
ስለሆነም ሌሎቹም ከእኔ አይሻሉም ፣
እኛ የፈጣሪ አምላክ ልጆችህ ነንና ፣
ፈጣሪ አምላክ ጥላቻ እንዳይኖረን እርዳን፣
እርስ በእርስ እንድንግባባ አድርገን፣
እንድንዋደድ እርዳን ፣
ታደሰ እራሱን ያጠፋው ክፍሉ ውስጥ ነበር። በመጀመሪያ ሮና የምትባለው እህቱ አይታ ለእናቷ ነገረቻት። ታደሰ እራሱን የሰቀለው  ቤተሰቦች ሰሜን ጀርመን ከሰሜን ባሕር አካባቢ በሚገኝ ምሥራቅ ፍሪስላንድ (Ostfriesland ) የሚባል ቦታ ለእረፍ ት በሄዱ ወቅት ባሕሩ ገፍቶ የተፋው ቱባ ገመድ አግኝተው ነበር። ግድግዳው ላይ ደግሞ አንድ የአየር ወለድ ፎቶ ያለበት ፖስተር ተለጥፏል። ቁምሳጥኑ ላይ ደግሞ አንድ የጋዜጣ ቁራጭ -  የአውቶሚክ ቦንብን የሚቃወሙ ሐኪሞች የጻፉት << የተረፉት በሞቱት ይቀናሉ>> የሚል ተለጥፏል።
የታደሰ የማደጎ እናት እንዳየችው እግሮቹን አቅፋ . . .  ታደሰ . . .  ታደሰ . .  እያለች ጮኸች።  በአንድ እጇ ደግሞ አንገቱን ከገመዱ ለማለያየት ትጥራለች። ሮና ጎረቤቶችን ለእርዳታ ለመጥራት ሄዳለች። ሲንጂ ሌላዋ እህቱ መጥታ ታደሰ . . . ታደሰ እያለች መጮህ ጀመረች። ቁምሳጥኑ ላይ ወጥታ ገመዱን አስለቀቀችው። ሰውነቱ በሙሉ እናቱ ላይ አረፈ። ፊቱ በጣሞ ገርጥቷል።
እናቱ ቀስ ብላ መሬት ላይ አስተኛችው ። አይተነፍስም ፣ ልቡም አትመታም። ሮጣ ስልኩን አንስታ ዶክተር ጠራች። ተመልሳ አፏን ካፉ ገጥማ እርዳታ አደረገችለት። ጎረቤታቸው ሄዶ አባቱንና ወንድሙን ይዞ መጣ ። እነርሱም የተቻላቸውን ሞከሩ። ታደሰ ግን ምንም አይሰማም። ዶክተሩ ቆይቶ መጣ ። ሁሉም ነገር ማለቁን ነገራቸው ። ታደሰ ላይመለስ ሄዷል።
የጀርመን ፖሊስ ሁሉን ነገር ካጣረ በኋላ <<የሞተው በጨዋታ ላይ እያለ አደጋ አጋጥሞት ነው>> በሚል ፋይሉን ዘጋው። ከጊዜ በኃላ የታደሰ አባት የታደሰን ልብሶች በሚፈትሽበት ወቅት አንድ የተጣጠፈ  ደብዳቤ ከጅንስ ሱሪው ውስጥ አገኘ።
የታደሰ የመሰነባበቻ ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡ -
Liebe Mutti . Lieber Vati
<<Ich mÖchte  euch keinen Kummer machen. Ich gehe dahin zurück,wo ich hergekommen bin>>
ውድ እናቴ ፣ ውድ አባቴ
<< እንድትቸገሩ አልፈልግም ። እኔ ወደ መጣሁበት ተመልሻለሁ>>
አዲዮስ ታደሰ . . .  የጀርመን ፓሊስ ኪሶቹን እንኳን በደንብ ለመፈተሽ ጥረት አላደረጉም።
የሃገራችን ሕጻናት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ያለው። በተለይ በውጭ ሃገር የሚደርስባቸውን ችግር የሚረዳው በጣም አነስተኛ የሆነ የኀብረተሰቡ ክፍል ነው። ይህ ችግር በትክክል ተገልጾ አልተጻፈም። አልተነገረምም። ብዙው ዜጋ ልጆቹ ወደ ውጭ ቢሄዱ የተሻለ ትምህርትና ኑሮ ይገጥማቸዋል በሚል ጥሩ ምኞት ላይ በመመርኮዝ ልጆቹን አሳልፎ ይሰጣል። ግን ሁሉ ጊዜም እንደዚህ አይነት አጋጣሚ ላይኖር ይችላል። የታደሰ አንዱ ሲሆን በተለይ ደግሞ ሕጻናትን ለፍትወት እርካታ የሚፈልጉ ነጮች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ወንጀላቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ መረዳት አለብን። በተለይ በአሁኑ ወቅት ሙስና በተስፋፋበት የወያኔ መንግሥት ልጅን በማደጎ ማግኘት ቀላል ሊሆን ይቻላል። ወደ ዐረብ ሃገር እንደሚጓዙት እህቶቻችን ለዚህም ተግባር አስፈጻሚ ደላላም ሊገኝ ይችላል። ምንአልባት በሃገር ውስጥ ይህንን የመሳሰሉ አስከፊ ታሪኮች በሰፊው ቢነገሩ ትምህርት ሊሰጡ ይችላሉ።
ስለ ሃገራችን ሕጻናት ደህንነት የሚያስቡ በሰላም ይክረሙ !
4. Februar 2013
ለንደን

1 kommentar:

  1. Hi there, its pleasant artifle concerning media print, we all know media is a great source of facts.
    tikus

    SvarSlett