አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ በዜጎች ላይ የሚደርሰዉ ጭቆናና ግፍ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ መጥቶ ዛሬ “ባለራዕዩ” መሪ ህዝብ ላይ የጫነዉ መከራና መአት ወደ ራስ አልባው መሪ በፍጥነት እየተሸጋገረ የግፈኞች ስርዐት አገርንና ትዉልድን እያጠፋ ነዉ። ሻል ያለ ግዜ ይመጣል እያለ የወደፊቱን ብሩህ ዘመን የሚጠባበዉ የኢትዮጵያ ህዝብም ተስፋዉም ትዕግስቱም ተሟጥጠዉ የወያኔን አማራጭ ብቻ ሳይሆን ወያኔን የሚያስወግድበትን አማራጮች ጭምር እየፈለገ ነዉ።
የዘረኛው ወያኔ ስርአት ቁንጮ መለስ ዜናዊን ለይስሙላ የተካዉሃይለማርያም ደሳለኝ በአንድ በኩል የህዝብ መነሳሳት ለመገደብ በሌላ በኩል ደግሞ የራሱን ፍርሃት ለመሸፈን ሀገራችንን ድቅድቅ ጨለማ ዉስጥ በማስገባትና በወገናችን ላይ የሚያደርሰውን በደል አጠናክሮ በመቀጠል ኢትዮጵያውያን ስለ ብርሃን መውጣት እንዳያወሩ፣ እንዳያልሙ፤ ስለ ነገዉ የነጻነት ተስፋ እንዳይተነፍሱ፣ ስለ ነጻነት እንዳያዘምሩ ለማድረግ ልሳን ዘጊ የሆኑ የስርአቱ ጀሌዎችን በመምረጥ ሰቆቃው በከፋና በተጠናከረ መልኩ ህዝብና ሀገርን አውዳሚ የሆነ ሃይላቸውን በመጠቀም በንጹሃን ዜጎች ላይ ኢ-ሰበአዊ የሆነ አስነዋሪ ድርጊት እያስፈጸመ ነው።
የመለስ ዜናዊን ሥልጣን ሳይሆን ወንበር ብቻ የወረሰዉ ሃይለማርያም ደሳለኝ የራሱ ህሊና የሚያዝዘዉን ስራ መስራት ሲገባው የህወሃት አለቆቹን በመፍራትና የነሱን ቡራኬ ለማግኘት ሲል የኢትዮጵያን ህዝብ ለሰዉ በላ የህወሃት ባለስልጣኖች አሳልፎ እየሰጠ ነዉ። ይህ ነዉ እንግዲህ ከመለስ ዜናዊ ወደ ሃይለማርያም ደሳለኝ የተደረገው ሽግግር።
መላው የሀገራችን ህዝብ አዛውንቱ፣ ወጣቱ፣ ምሁሩ፣ ሰርቶ አደሩ ገበሬውና፣ ህጸናት ሳይቀሩ ዛሬ የወያኔ የስቃይ ሰለባ እና ገፈት ቀማሽ ያልሆነ ትውልድ ከቶ የለም።በከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎችና አስተማሪዎች ላይ የሚደርሰው በደል፣ በእምነት ቦታዎች የሚሰማው እሮሮ፣ የማህበረሰባዊ ተቋማትን የማፍርስ አደጋ እና ሌሎችም እኩይ ተግባራት ተጨምረው የስርአቱን የግፍ በትር ያልቀመሰ ዜጋ የለምም።
ይህ የወያኔ ስርአት የጉልቻ መለዋወጥ ከትግላችን ለአንዲት ደቂቃም ቢሆን ሊያዘናጋን አይገባም፡፡ ችግሩን ከማግባባትና መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ማፋፋምን፣ መጨቆንን የመረጠው የህወሃት/ኢህአዴግ ቡድን፤ በፍጹም ሊታመን የማይችል፤ ህዝባዊ ድጋፍ የሌለው፣ ብሄራዊ አንድነትን የማያውቅ፣ ሰበአዊነት የማይሰማው አካል በመሆኑ ዛሬ ልናስወግደው የሚገባ ዘረኛ ድርጅት ስለመሆኑ በአንድ ቋንቋ በቃህ ልንለው ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያችን የሚያስፈልጋት የሰው ለውጥ ሳይሆን ስር ነቀል የሆነ የስርአት ለውጥ ነው፤ ይህ ማለት ደግሞ ከአገራችን ዉስጥ ተነቅሎ መወገድ ያለበት ወያኔ/ኢህአዴግ እራሱ ነው። ሌላው ለውጥ ኢትዮጵያዊው ወጣት ከአበው የተማረውን፣ የወረሰውን አመኔታን በመገንባት የውርደት ዝምታን በእምቢተኝነት በመለወጥ የማያዳግም የስርአት ለውጥ እንዲመጣ አበክሮ በመታገል፤ ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ማምጣት ነው።
ከመለስ ዜናዊ ወደ ሃይለማርያም ደሳለኝ የተደረገው ሽግግር የአንድን ፓርቲ ቡድናዊና ግለሰባዊ ፍላጎትና ጥቅም ማእከል ያደረገ መሆኑ ዛሬ ለምናየዉና ተባብሶ ለቀጠለው አፈና፣ ግድያ፤ ቤተሰብ መፍረስ፤ የኑሮ መገሳቆልና በአጠቃላይ በ የነገ ተስፋው መጨለም ምክንያትሆኗል።
የወያኔ አገዛዝ “በመተካካት” ስም ህወሃት የበላይነቱን እንደያዘ የመቀጠል ህልም ያለው መሆኑን አረጋግጦልናል። ስለዚህ የፍትህ እጦት፤ የውሸት ምርጫዎች መብዛት፤ የሰብዓዊ መብቶች መረገጥ፤ የሥራ አጥነት መበራከት፣ የአግአዚ ጦር ሠራዊትና እና “የጆሮ ጠቢዎች” በወገናችን የሚያደርሱት እልቂትና ስቃይ ሰለባ የሆናችሁና ነጻነትና የአገራችሁ አንድነት የሚያንገበግባችሁ ዜጎች ሁሉ አሁን ወቅቱ የሚሻው የትግል ጊዜ ላይ በመሆናችን፤ የድል አጥቢያ አብሳሪ የሆኑ ወጣት የነጻነት ታጋዮችን በመቀላቀል ራሳችሁን፤ ወገናችሁንና አገራቸሁን ታደጉ።
ግንቦት 7 የፍትህ፤ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህ የወያኔ የመተካካትና ወንጀለኛን በወንጀለኛ የመለዋወጥ ስልት ህዝብን ለማታለል፤ የስልጣን ዘመንን ለማራዘምና የትግልን አቅጣጫን ለማሳት ሆን ተብሎ የሚደረግ ሴራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ተረድቶ ከወዲሁ ትግሉን እንዲያፋፍም በአደራ ጭምር ያስጠነቅቃል። ስለሆነም ንቅናቄያችን አሁንም በንቃት በመከታተል የስርአት ለውጥ በሃገራችን ለማምጣት አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ማናቸውም የትግል ስልቶች በመጠቀም ህወሃት/ኢህአዴግን ለማስገደድ ወይም ለማስወገድ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠን ተነስተናል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar