በእስከ ነጻነት
ዛሬ ብዕሬን ሳነሳ ስለጂሃዳዊ ሐረካት የከሰረ ድራማ ጥቂት ለማለት ነበር፡ ግን የምለውን ሳስብ ወንድሜ ዳኛቸው ቢያድግልኝ “ጂሃዳዊ እንምጃን በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩ ሲጋለጡ”በሚል አርእስት ባማር አገላለጽ ከሽነው አቅርበውታል፡ ሌሎችም ብዙዎች ብዙ ብለውበታል፡ ነገሮችን ረጋ ብለው የማየት፤ ሁኔታዎችን የማገናዘብ እና የማቀናጀት ተሰጥኦ ያላቸው ብዕረኛ ወንድሜ ሮቤል አባ ቢያም እየቀመሩ እንደሆነ ይስማኛል፡ በየሳምንቱ የሰኞ ድግስ አቋዳሻችን ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማርያምም ጅሃዳዊ ሐረካትን ከናዚዎች ስነልቦና እና ጭካኔ ያምባ ገነኖች የመጨረሻው ሰአት የውር ድንብር ጉዞ ምን እንደሚመስል፡ ይህም አኪል ዳማ፤ ጅሃዳዊ ሐረካት እና የመሳሰሉት ደራማዎች የመጨረሻው የቁለቁለት ጉዞ መሆኑን ያሰቃኙናል ብዬ አጠብቃለሁ፡ ስሞኑን ድምጿ የራቀኝ እህቴ ስላም በየነም ጀባ ትለናለች በዬ በጉጉት እጠብቃለሁ፡ ወንድማችን ኦባንግ ጅሃዳዊ ሐረካትም ሆነ አኪል ዳማ፡ ከስብአዊ መብት ረገጣ ጋር ያላቸውን ቁርኝት፡ ሐይማኖተኞችን ማጥፋት እንዴት ከዘር ማጥፋት፡ ጋር እንደሚገናኝ እና በምን መልኩ ለፍርድ ማቅረብ እንደሚቻል፡ ከኛ የወደፊቷን የሁላችን የሆነች ኢትዮጵያን የምንመኝ ዜጎች ማድረግ የሚጠበቅብንን እንደወትሮው ምክር አዘል መልእክታቸውን ያስተፍልናል ብየ ኣጠብቃለሁ፡ ጥልቅ መልእክታቸውን በስንኝ ቋጥረው እንደ ጥቅምት ውሃ ኮለል አያረጉ የሚያፈሱልን ወንድሞቼ ወለላዬ፤ የዋርካው መንግሰቱ፤ ቤልጅግ አሊ፤ ሄኖክ የሺጥላ እና ሌሎችም ለጊዜው ስማቸውን የዘነጋሁት ወንድምና እህቶቼ በተባ ብዕራቸው፡
- በነስብሃት ነጋ የጭካኔ ሴራ እና በነ ለገሰ አስፋው ደደብነት የመስዋእት በግ ሆነው የሃውዜንን ገበያ በደማቸው ያጨቀዩትን የሃወዜን አካባቢ ሰማእታት፡ ወያኔ ለሰራዊት ማሰባሰቢያ የተጠቀመበትን የተሳካ ድራማ፡
- ወያኔ ገና አዲስ አበባ ሳይደርስ በአሶሳ የታረዱ ከ500 በላይ የሚሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎች ወያኔ ኦነግ አረዳቸው የሚል አማርኛ እና ኦሮምኛ ተናጋሪ ዜጎችን ለማጋጭት የጀመረበትን ከፍል አንደ ድራማ፡
- በታምራት ላይኔ ቀስቃሽነት አን በወያኔ ሰራዊት ተባባሪነት በበደኖና ከነ ህይወታቸው ገድል የተወረወሩትና ኦነግ ፈጸመው ተብሎ መለስ ዜናዊ ራሱ ማናፈስ ይቻላል ያለበትን ድራማ፡
- በአርባ ጉጉ የተፈጸመውን አረመኔያው ድርጊት ወያኔ እንኳ ሊተውንበት ያልደፈረውን ጭፍጨፋ፡ ምናልባትም እዚህ ላይ ሊጠቀስ የሚገባው ያርባ ጉጉ ግጭት የአማርኛ ተናጋሪዎች እና የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ገጭት ተደርጎ የሚወሰደው ያው ሁለቱን ቋንቋ ተናጋዎች ለማቃቃር ካለው ወያኔያዊ ተልእኮ እንጅ ሃቁ ግን መጤ እና ነዋሪ የሚል መሆኑን መጠቀስ ያለበት ይመስለኛል፡ ከሸዋ በተለይ ከሰላሌ የተሰደዱና አርሲ ለዘመናት የኖሩ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ከአማርኛ ተናጋሪው ጋር ተፈርጀው እኩል ተጨፍጭፈዋል፡ ደማቸው ተደባለቆ የአርባጉጉን መሬት አጨቅይቶታል፡ ስጋቸው እኩል የአርሲን አሞሮችና አራዊቶች መግበዋል፡
- በአኪል ዳማ እና በጂሃዳዊ ሐረካት ድራማዎችን ይተነትናሉ ብዬ አጠብቃለሁ።
ብዙ ጸሓፊዎችን ሳነሳሳ እንዴ እነ ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው፡ እን ዶ/አክሎግ፤ እና ልሎችንም ለምን ረሳሃቸው ትሉኝ ይሆናል፡ አልረሳሗቸውም ለሌላ ጉዳይ እየቆጠበኳቸው ነው፡
እኔ ዛሬ ማንሳት የፈለኩት እኔና የኔ የምላቸውን የተመለከተ ይሆናል፡ ዛሬ የማቀርበው ራሱን የቻለ ጽሑፍ አይደለም፡ ለመነሻነት በተለይም የመስኩ ባለሙያዎች እንዲያዳብሩት፡ እንዲወያዩበት፤ እኔ ካነበብኩት እና እኔ መስሎ የተሰማኝን ብቻ ስለሆነ የማቀርበው፡ ሃሳቡን ለማዳበር፡ ለማጎለበት፤ እንዲያም ሲል ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር በመስኩ የዳበረ ልምድና ተመክሮ ያላችሁ ኢትዮጵያንን ሁሉ በትህትና እጋብዛለሁ፡በዚህም ረገድ ዶ/ረ አበባ ፈቃደ፡ ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው፡ እና ሌሎቻችሁም እንድታዳብሩት የአክብሮት ግብዣዬን እንደምትቀበሉኝ ተስፋ አረጋለሁ፡
የዛሬ ጽሑፌ የሚያተኩረው ባለፉት አምስት አሰርት አመታት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እኔን ጨምሮ የተለያየ የግፍ ቀንበር ሲፈራረቅበት ኖሯል፡ ከዚህም ለመላቀቅ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ስም የተሰጣቸው ድርጅቶች ተቋቁመዋል እየተቋቋሙም ነው፡ ግን አንዳቸውም ለፍሬ ሳይበቁ ወይ ይመክናሉ ወይ ባሉበት እየረገጡ ለስም ብቻ አለን ይላሉ።
ለምን ይሆን?
ይህ ጥያቁ ብዙዎችን ያሰጨነቀ፤ ያሳሰበ ጉዳይ ነበር፤ ነው፤ ይሆናልም፡ መፍትሄ ግን አለተገኘም፤ መፍትሄው የሚታያቸውም ደፍረው የችግሩን ስርና መሰረት መናገር አልቻሉም። እኔም የዚሁ ችግር ምንጭ ምን ይሆን እያልኩ ስወጣ ስወርድ፤ “አምስቱ የቡድን እንቅፋቶች”፡ በሚል ርዕስ በፓትሪክ ሌንቺዮኒ ከተደረሰ መጽሐፍ ዋናውን ቁም ነገር ቀንጭቤ ከኛ ወግና ባህላዊ ተጽዕኖ ጋር እያጣቀስኩ መግልጽ አሞክራለሁ። ከላይ እንደገለጽኩት ግርድፍ ሃሳብ ስለሆነ ባለሙያዎች እንድታዳብሩት ጥሪየን በድጋሜ አቀርባለሁ፡
የፖለቲካም ይሁን የሲቪክ ተቋማት ዞሮ ዞሮ የቡድን ስራ፡ የሚጠይቁ ናቸው፡ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ የሲቪክ ተቋማት ስኬት በቀጥታ ከአባላቱ የስራ ስኬት ጋር የተያያዘ ለመሆኑ ጥያቄ የሚቀርብበት ጉዳይ አደለም።
ይህ ከሆነ ለቡድን ስኬት እንቅፋቶች ምንድናቸው?
እንደ ሌንቺዮኒ አገላለጽ፡ የቡድን እንቅፋት
ቁጥር 1. አለመተማመን
በቡድን አባላቱ መካከል፡ በኛ ሁኔታ በፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ ማህበራዊ ድርጅት አባላት መካከል መተማመን ከሌለ የትም አይደረስም፡ ታሪካችንም ሆነ ባህላችን ደግሞ መተማመንን የሚያበረታታ አደለም፡ ከተረቶቻችን ብንነሳ፡ ጠርጥር፡ ከገነፎም አለው ስንጥር። ሰውን ማመን ቀበሮ ነው፡ ሰውን ውደደው እንጂ አትመነው፡ የሚባል ወንጋላዊ ቃልም ይጠቀሳል፡ እዚህ ላይ ግን “አትመነው” የሚለው ቃለ ምን ማለት ነው? በእንግሊዘኛው አገላለጽ (believe in, trust) ተብለው በግልጽ ተቀምጠዋል፡ ያማርኛው ትርጉም ግን አሻሚ ነው፡ እኔ እንደሚገባኝ አትመነው ማለት እንደ አመላክህ አታምልከው፤ እንደ ፈጣሪ አትምልከተው ለማለት እንጂ የሚያደርገውን ሁሉ በጥርጣሬ ተከታተለው ለማለት አይመስለኝም፡
በነገራችን ላይ ወንበር ጠባቂ ሚንስቴር ሃይለማርያም እናንተ ባታምኑ እኔ አምነዋለሁ ብሎ ይሆን እንዴ ዘላለማዊ ክብር ለመለስ ዜናዊ ያለው? ለነገሩ ቀፎውን እግዚአበሄር ሰራው እንጂ አስተሳሰቡ፤ አነጋገር ዘይቤው፤ ቃላቱ፤ ሃረጎችና አረፍተ ነገሮች ሳይቀሩ የተሞላው በመለስ ስለሆነ ቢያመልከውም አይፈረድበትም፡
ወደቁም ነገሩ ልመለስና በቡድን መካከልም ይሁን በማህበረ ሰብ ስብስብ አባላት መካከል መተማመን ከሌለ፡ እያንዳንዱ አባል የሚናገረውን፤ የሚያደርገውን በጥርጣሬ የመመልከት፡ ከሗላው ሌላ ነገር ይኖረዋል ብሎ ማሰብ፡ የራስንም ሃሳብ በነጻ ለመግለጽ መታቀብ፡ ቂም መያዝ፡ የጓደኛን ወይም ያባሉን ጥሩ ምግባር ወይም ተግባር ከማድነቅ ይልቅ ማደናቀፊያ መንገድ መፈለግ፡ ባጠቃላይ ጊዜን ትርጉም ባለው ተግባር ከማሳለፍ ይልቅ በመወቃቀስ፤ በመካሰስ ግፋ ሲልም በመራራቅ እና በመወነጃጀል መጠመድ ከዛም ድርጅቱን ማፍረስ ይከተላል፡ ይሄ አብሮን የኖረ፤ አሁንም የሚኖር ችግራችን ነው፡
ቁጥር 2. የግጭት ፍራቻ፡ የሃሳብ ግጭት ጭምር መፍራት
በባህላችን ከአውነት ይልቅ ይሉኝታ የገነነበት፡ ከነተረቱ፡ ከነገሩ ጾም እደሩ፡ ስምቶ መቻል፡ ንቆ ማለፍ፡ ዝም አይነቅዝም፡ ዝምታ ወርቅ ነው፡ እና የመሳሰሉት አውነትን አፍረጥርጦ ተነጋግሮ ወደ መፍትሄ ከመሄድ ይልቅ፤ የሆድን በሆድ ይዞ ጊዜ ይፈጀው፤ ይህንን ብናገር እገሌን ይከፋዋል፡ እገሊት ቅር ልትሰኝ ትችላለች፡ በሚል፡ ይሉኝታ ታጥሮ፡ እውነታውን ህሊና እያወቀው አለባበሶ ማለፍ የተለመደ ነው፡ የዚህ ውጤት ደግሞ አጨቃጫቂ ግን አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን አንሰቶ ከመወያየት መሸሽ፡ ፊት ለፊት መነጋገር ቀርቶ ሹክሹክታ፤ ሃሜት ማብዛት፡ የአባላቱን ሃሳብ አለመቀበል፤ መናናቅ፤ ከዚያም መፈራራት እና መጠላላት ጊዜን ለቁም ነገር ከማዋል ይልቅ ራስን በመደበቅና ያልሆኑትን ለመምሰል በመሞከር ሃይልን ማባከን፤ የተለማማጭነት እና የአድርባይነት ጸባይ ቁራኛ መሆን ይሆናል።
ቁጥር 3. የሃሳብ ጽናት ጉድለት፡
ባህላችንም ይሁን ሃይማኖታችንም ችግራችንን ሁሉ ጊዜ ይፈታዋል፤ ሁሉ ለበጎ ነው፡ የሚሰቃዩ ብጹአን ናቸው፡ የሚታሰሩ፤ የሚገረፉ፤ የሚበደሉ ብጹአን ናቸው በሚለው እምነት የታሰርን ይመስለኛል፡ በሃሳባችን ጸንተን ከመታገል ይልቅ ጊዜ ይፈታው፤ ብለን የመንፈሰ ደካማነት አቋም እንወስዳልን፡ ሓይማኖትን ተቸህ እንደማትሉኝ ተስፋ አረጋለሁ፡ ምክንያቱም የቀድሞ የሃይማኖት አባቶች ቀኙን ስጠኝ ብለው መብታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስከበር ጦራቸውን ስበቀው ይዘምቱ ነበር፡
የሃሳብ ጽናት አለመኖር ግራ መጋባት፤ አቅጣጫን ያለማውቅ፤ ግብንና የግብ አላማን መጠራጠር አንድን ሃሳብ አብስሎ ወደ ውሳኔ ከመድረስ ይልቅ አንድ ሃሳብ መልሶ መላልሶ ማኘክን ያስከትላል፡ የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል እንደሚባለው ማለት ነው፡ ይህም ግልጽ ያለ አቋምና የአቋም ጽናት ያለመኖር፡ በጥቃቅን ጥቅማ ጥቅም መደለል እና አላማን የመሳት ችግሮች በሰፊው ይታዩብናል፡
ቁጥር 4. ሓላፊነትን መሸሽ፡ የሃላፊነት ድርሻን አለመቀበል፡
ሌላው ትልቁ ችግራችን ደግሞ ለሰራነው ስራ ሃላፊነትን መውሰድ፤ እኔ ነኝ ይህንን ያጠፋሁት ብሎ ሃላፊነት የመውሰድ እና ለጥፋቱ ይቅርታ መጠየቅ እንደ ጦር የሚፈራ ነገር ነው፡ ለአንድ ተግባር ሃላፊነትን ወስዶ የተጣለበትን ሃላፊነት የመወጣት ቁርጠኝነት ይጎለናል፡ ይህ ደግሞ የበታችነትን አምኖ የመቀበል፡ ጎመን በጤና ብሎ አንገት ደፍቶ የመኖር አባዜ መጠናወትን ያመጣል፡ ይህ ሃላፊነትን መሸሽ ሌላው ችግራችን ነው። በመጨረሻም
ቁጥር 5. ለውጤት ትኩረት አለመስጠት፡
ሌላው ትልቁ ችግር ደግሞ የጋራ ውጤትን አሻግሮ ከማየት ይልቅ የራስን ማንነት የማሳደግና ራስን በማግነን አባዜ መጠመድ ነው፡ በጋራ የጋራ ጥቅም የሚከበርበትን አቅጣጫ ከመተለምና ለግቡ ከመታገል ይልቅ የራስን ሚና ከፍ አርጎ ማሳየት የሚቻልበትን መንገድ እና ስልት ማውጠንጠን፡ማሰቀደም፡ እዘህ ላይ ትንሽ ከረር ያለ አስተያየቴን ላክልና አንዳንዶቻችን እንቱ አንቱ የሚለንና አጀብ አጀብ የሚያረገን ስብስብ እሰካገኝን ድርስ አገሪቷ ብትጠፋ ስሜት የማይሰጠን ብዙ ሰዎች አለን።
ለፖለቲካም ይሁን ማህበራዊ ድርጅቶቻችን ወደፊት አለመራመድ እንቅፋቶች ብየ የዘረዘረኳቸው ጠቅልል ብለው አንደሚከተለው ተቀምጠዋል፡
አሁን ችግሮቸን ሰማን መፍተሄው ምንድነው ታዲያ የሚል ጥያቄ ሊጠየቅ ይችላል፡ ለዚህ መልስ ፈለጋ ከመሄዳችን በፊት ችግሩ ላይ መስማማት አለብን፡ ለዚህም የባለሙያዎችን አስተያየት
እና ማዳበሪያ ስለሚያሰፈልግ ሁላችሁንም አስተያየት እንድትስጡበት እንድታዳብሩት አደራ እያልኩ የዛሬን እዚህ ላይ አበቃለሁ።
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይጠብቅ
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar