fredag 1. februar 2013

ከጉርዳፈርዳ ወረዳ ለተባረሩ በሺህ ለሚቆጠሩ ስዱዳን መታሰብ



ማሳሰቢያ:- ይህ ፅሁፍ አምና ድርጊቱ እንደተፈፀመ የተፃፈ ፅሁፍ ነበር። ብዙዎች በዜናነት ከማተት ባለፈ በተገቢው ያህል አልተናገሩለትም። ጉዳዩ ግን የመላው ኢትዮጵያውን በአንድቦታ የመኖር እና ንብረት የማፍራት መብቱን ስለሚንድ ከእርሱ ጋር ተያያዥ የሆኖ ሕጎችን በሙሉ ስለሚያፈርሳቸው ከሕግ እና ከፖለቲካ ጥያቄ በዘለለ ለመመልከት የሚያስገድድ ነው። በትናንትናው እለት ጥር 23/2005 ዓም ጉዳዩ እንደገና አለም አቀፍ ዜና ሆኖ ቀርቧል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ አንድ ወቅት በምክርቤት ስለጉዳዩ ተጠይቀው ሲናገሩ ”ማንም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት ቦታ የመኖር እና ንብረት የማፍራት መብት አለው” የሚለውን የህገመንግስቱን አንቀፅ ከመጥቀስ ይልቅ በደምሳሳው ”መሬቱን የደቡብ ክልል ነው የጠየቀው፣ ጉዳዩን ማራገቡ ማናችንንም አይጠቅምም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ይህን በሚናገሩበት ሰዓት ግን በሺ የሚቆጠሩ ከአካባቢው ለዘመናት የኖሩ ነዋሪዎች ”የተሰራብንን ግፍ መንግስት ይመልከትልን” ብለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤት እያሉ ነበር።

”ሃገሬ ስንት ነች?” የአቤል ጥያቄ (ከጉርዳፈርዳ ወረዳ ለተባረሩ በሺህ ለሚቆጠሩ ስዱዳን መታሰብያ)

አቤል ይባላል ደቡብ ኢትዮጵያ ከማጂ ዞን ጉርዳፋርዳ ወረዳ ተወልዶ ያደገ ከወረዳዋ በተለየ ሌላ ሀገር ያለ የማይመስለው የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ ነው። ደስተኛ ህይወቱን የመንደሩ
ECADF Ethiopian News
በሽፈራው ሽጉጤ ትዕዛዝ ከተፈናቀሉት የአማራ ብሄር ተወላጆች መካከል ጥቂቶቹ
ነዋሪ ሁሉ ይመሰክርለታል። ዛሬ ግን የደስታ ድባቡ ጠፍቶ በሃዘን የተዋጠ ልጅ ለመሆኑ በቂ ምክንያት ነበረው።
አቤልን የመንደሩ ነዋሪ በጋራ ያወጣለት ስም አለ። ‘ሮጦ የማይደክመው’ የሚል። ቀኑ ሙሉ ይሮጥበት የነበረው ሜዳ ዛሬ ወፍ ዝር አይልበትም ህዝቡ ንብረቱን ትቶ መሄድ ከጀመረ ወር ሊሞላው ነው። አቤል ከአራት የእድሜ አቻዎቹ ጋር ስለ ሰሞኑ ጉድ በልጅነት እግሩ ለአምስት ሰዓት ያህል ቆሞ ካወራ በኋላ እንኳን ለአንድ ደቂቃ ያወራ አልመስልህ ብሎት ስለመሸበት ብቻ ወደ ቤቱ ሄደ እንጂ ቤቱ አስጠልቶታል ። አሁን ግን መሸበት እናም እንዳቀረቀረ ወደ ቤቱ አመራ።
ማታ አባቱ የነገረው ነገር አሁንም እውነትነቱ አልገባ አለው። አባቱ ብቻ አደለም በአስር ሺ የሚቆጠር ህዝብ ”በቶሎ ሃገሩን ለቃችሁ ውጡ!” ተብለው ሰማይ ምድሩ ተደፍቶባቸው አይቷል።

አባት የመንግስት ትዛዝ ገርሞታል፣ ደንቆታል፣ ከሁሉ ያስለቀሰው ለብዙ ዓመት ያስቀደስበት ልጆቹን ሁሉ ክርስትና ያስነሳባት የቤተክርስትያኑ ጉዳይ ነው።” ከመድሃኔ ዓለም ታቦተ-ሕግ ርቀን ከክርስቶስም ሳንሆን ከለፋንበትም ንብረት ሳንሆን ሁለት ወር ‘ሁዳዴ’ ፆመን ሳንገድፍ ስደተኛ ሆን ማለት ነው?” ይልና ቀጥሎ ”ምን አይነት ሰዎች ምን አይነት ስብሰባ አርገው ከቀዬአችን ሊያስወጡን ወሰኑ አንተ? ምን አጠፋን? ሕግ ይሄን ያክል ተናቀ? መንግስት ምንም ግፍ ያልተፈፀመ ይመስል በራድዮና ቴሌቪዥኑ አለመናገሩ ምን ማለት ነው?” ይላል። ለአቤል ግን ”ምን አይነት ሰዎች ምን አይነት ስብሰባ አርገው ከቀዬአችን ሊያስወጡን ወሰኑ? ምን አጠፋን? ሕግ ይሄን ያክል ተናቀ? መንግስት ምንም ግፍ ያልተፈፀመ ይመስል በራድዮና ቴሌቪዥኑ አለመናገሩ ምን ማለት ነው? ” ሲል አባቱ ማታ የተናገረው ንግግር ጆሮው ላይ ይደውልበታል። አባቱ ድሮ ‘መንግስት’ የሚለው ቃል በጣም ያከብር የነበረ መሆኑን ያስታውሳል። አባቱ ብቻ አደለም። የስነ-ዜጋ ትምህርት መምህሩ ስለ አንድ መንግስት ‘ኃላፊነትና ግዴታ’ ብዙ አስረድተውታል። የመንግስትን ብቻ አደለም የአንድ ዜጋን ግዴታና መብትም ነግረውታል። በስነ-ዜጋ ትምርት ፈተናም ላይ ሁል ጊዜ ከዘጠና በላይ በማግኘቱ ሁለት ጊዜ በመምህሩ መሸለሙን አይዘነጋውም።
ሰሞኑን ጎረቤቱ ሁሉ ተሰብስቦ የሚነጋገርበት ጉዳይ አንድ ብቻ ነው :-
”ውጡ ተባልን” የሚል። አቤል ጎረቤቱ ስነጋገር ቀድም ብሎ ማውራት ልማዱ ነው ጎረቤቱ ቡና ላይ ”ሀገር ልቀቁ” ስለተባለው ወሬ ሲሰማ ነጠቅ ያረግና ”ሊሆን አይችልም… የአንድ መንግስት ግዴታ… ነው። ህገ መንግስቱ አንቀጽ.. ላይ… የሚል አለ” ብሎ ከስነ ዜጋ ትምርት የተማረውን ሊያስረዳ ይሞክር ነበር። በልበ ሙሉነት። ጎረቤቱም ሆነ ወላጆቹ በመጀመርያ እሱ የነገራቸውን የህገ መንግስት አንቀፅ ከወረዳው ሹሞች ጋር ሲነጋገሩ ይጠቅሷት ነበር። ቆይቶ ግን ጥቅስ እና ተግባር መለያየቱ ገባቸው።
ዛሬ ግን ከቤተሰቡ አልፎ አቤልም ያ! የስነ-ዜጋ መምህሩ የነገሩት ሁሉ ውሸት መሆኑን የተረዳው የመንግስት ወታደር አጎቱን ናአባቱን ቤተሰባቸውን ይዘው ከሌሎች በሺህ ከሚቆጠሩ ነዋሪዎች ጋር ለቀው እንዲወጡ የሚገልፅ ደብዳቤ ለመላው የጉርዳፈርዳ ሰፋሪ ሕብረተሰብ ከታደለ በኋላ ነበር።
ታላቅ ወንድሙ የዛሬ ሰባት ዓመት የስምንት ዓመት ልጅ ሳለ በ1997 ዓም በነበረው የ ‘ቅንጅት’ ምርጫ ተብሎ በሚጠራው ጊዜ ”ስነ-ዜጋ ትምህርትና የገሃዱ ዓለም አልጣጣም አለኝ” ብሎ ሲናገርና አባቱን በጥያቄ ሲያጣድፍ የነበረ መሆኑ ዛሬ ይበልጥ ትዝ አለው። አቤል ተገረመ በልጅነት አናቱ ላይ ጉዳዩ ሁሉ ፈላበት።
ድንገት ተነሳና ወደ አባቱ ሄደ ቤተሰቡ የሚይዘው ግራ ገብቶታል።
አባት ያሉትን በሬዎች በተገኘው ዋጋ ለመሸጥ ይጣደፋል። ልጆች ፍራሽ ያስራሉ።
እናት በርጩማ ላይ ራሷን በሁለት መዳፍዋ ደግፋ ተንሰቅስቃ ታለቅሳለች። አቤል አባቱን ሊጠይቅ የነበረውን ጥያቄ ተወው። እንባው አቀረረ በእንብርኩ ሆነና እናቴን ባፅናናት ብሎ ያሰበውን ቃላት መደርደር ጀመረ። ወድያው እንባውን ማቆም አቃተው። ቀጠለና :-
”እማ በቃሽ ስንት ቀን ታለቅሻለሽ? እኛ ልጆችሽ እስካለን ሁሉ ይተካል። ደግሞ ሌላ ምትክ ቦታ መንግስት ይሰጠን ይሆናል” ብሎ ከመናገሩ
እናቱ ‘እሳት ጎርሳ’ ተነሳችና በቁጣ አየችው ልጅ መሆኑን የረሳች ይመላል ቀጠለችና
”ካሁን በሁዋላ መንግስት መንግስት አትበል ከፊቴ…
ከአባትህ ጋር ከእዚህ ቦታ ስንመጣ አንድ ወፍ ዝር አይልም ነበር።
አባትህ ወደ እርሻ ሲሄድ ስንት ጊዜ ነብር የበላው ይሆን? እያልኩ ነፍስ እና ሥጋዬ ስትላቀቅ ከረምኩ? እመብርሃን ባማላጅነቷ ከለለችልኝ እንጂ… ተምርያለሁ ከምትሉት ከናንተ እኔው ደንቆሮዋ እሻላለሁ። መንግስት ለምንድነው ነፍስና ሥጋዬ እየተላቀቀ ካቀናሁት መሬት ናበፍቅር ከምኖርበት ሕዝብ የሚነጥለኝ? በል አስረዳኝ? የ እንጀራ ልጅ ነን እኛ ? ንገረኝ ያንተ ትምርት ለእዚህ መልስ ካለው አሁን ንገረኝ? በላ?… የዛሬ ሳምንት ለቀው የሄዱት እነ እማዋይሽ የት እንዳሉ ታውቃለህ? ከመንግስት አድርሱን አቤት የምንለው በደል አለ ብለው ቢሄዱ የሚያናግራቸው ጠፍቶ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ግቢውን ከፍቶላቸው ሰርቶ የሚበላ እጃቸው ያዲሳባ ሕዝብ ለማኝ መሆናቸውን አሁን አባትህ ነገረኝ። እረፈው! እናትህ ለማኝ ልትሆንልህ ነው!” ለቅሶው ባሰባት።
ቤተሰቡ ንብረቱን እየሰበሰበ ሁሉም ጆሮውን ጣል አርጎ ይሰማ ነበርና ሁሉም ይህን አዲስ ግን ደግሞ ሌላ መከራ ሲሰማ ስራውን አቁሞ ማልቀስ ጀመረ። መንደሩ ሰሞኑን ለቅሶና ‘ኡኡታ!’ ለምዷል የለቅሶው ምክንያት ስለሚታወቅ ማንም አዲስ ነገር ተፈጠረ ብሎ አይመጣም። ወደ ምሽቱ ላይ ሁሉም ተሰብስቦ ለወጉ ያህል ቡና ተፈልቶ ”የናንተ መቼ ነው ውጡ የተባላችሁት? የናንተስ መቼ ነው?” መባባል ልማድ ከሆነ ሰነበተ።
አቤል ግራ ገባው ለ እናቱ ማፅናኛ የሚለው ቃላት ሁሉ ማለቃቸውን ሙሉ በሙሉ አወቀ። እናቱ ብዙ የምትበልጠው ነገር መኖሩ ዛሬ ገባው። ከ ዛሬ በፊት ዳዊት መድገም ብቻ የምትችል ይመስለው ነበር። የእርሱ ስነ-ዜጋ ትምህርት ቢያንስ ለ ዛሬ የሚፈይደው ነገር አለመኖሩን ተረዳ።
”መንግስትና ሕዝብ……መንግስት ለ ዜጎቹ ያለበት ግዴታ……ዜግነት……የ ዜግነት መብቶች……ወዘተ” የሚሉት የ ስነ-ዜጋ ትምርት ላይ ያሉ ቃላት በ አይኑ ላይ ተርመሰመሱበት።
ቀና ሲል አባቱ በፍቅር ሲመለከተው አየ። ለመጠየቅ ድፍረት አገኘ። የ አባቱ አይኖች እንደዚህ የሚያዩት ከሆነ የጠየቀው ሁሉ እንደምደረግለት ያውቀዋል። እና ጠየቀ
” አባ” አለ አቤል።
”ወየ ልጄ” አለ አባት ተስፋ የቆረጠ ፊቱን ወደ ልጁ አዙሮ።
” ስነ-ዜጋ ትምርት ላይ ትቸር መንግስት ለ ህዝቡ ያስባል፣ህዝብን ይንከባከባል ያሉን ውሸት ነው ማለት ነው?ማነው የ ስነ-ዜጋ ትምርት ደብተሬ ላይ የተፃፈውን ከ ደረሰብን ጋር የምያስታርቅልኝ ?” አለው ሲፈራ ሲቸር።
አባት ለመልሱ ጊዜ አልወሰደበትም ” አንተው ነህ ልጄ አንተው ነህ! ስነ-ዜጋ ደብተርህ ላይ የተፃፈውን የሚያጣምሙትን የምታስተምር አንተው ነህ ልጄ ዓለም ይሄው ነች በ ዘረኞች፣በ ጥቅመኞች ፣ ህዝብን ከ ሕዝብ ጋር በ ማላተም ትርፍ ያገኙ በሚመስላቸው ሰዎች ተሞልታለች። ሆኖም ግን ፀረ-ዘረኞች፣ፀረ-ጥቅመኞች ና ህዝብን ከ ሕዝብ ጋር በሚያስማሙ ሃሳብ አፍላቂዎችና ፖለቲከኞች ብዙ ጊዜ ከ አደጋ ድናለች በ እያንዳንዱ የ ህዝቦች አደጋ ውስጥ አንዳንድ የ አደጋ አምካኞችን እግዝያብሔር ፈጥሮላታል።ለምሳሌ በ አሜሪካ የ ባርያ ፍንገላ ውስጥ አብርሃም ሊንከንን፣ በ ናዚና ፋሺዝም ክፉ ተግባር ውስጥ እነ ዊንስተን ቸርችልን እየፈጠረ ሰዎችን አድኗል። ማን ያውቃል ደብተርህ ላይ የተፃፈውን ከ ገሃዱ ዓለም ጋር የምታስታርቀው አንተ የማትሆንበት ምን ምክንያት አለ? ንገረኝ ምን ምክንያት አለ? ከ ቂም በቀል ነፃ ልቦና ብቻ ይዘህ እደግልኝ ልጄ አይዞህ !” አለ አባት ።
አቤል እንባውን አቅርሮ ዝም አለ።
አባት ቁጢጥ ብሎ ቁመቱን ከ ልጁ ቁመት ጋር አስተካከለና ” ልክ አደለም? ተሳሳትኩ ?” አለ።
አቤል ራሱን ግራና ቀኝ በማወዛወዝ አለመሳሳቱን ገለፀ አሁን ግን እንባው መውረድ ጀምሮ ነበር። አባት ወደደረቱ አስጠጋውና ”ታድያ ለምን ታለቅሳለህ? እኔ አባትህ እያለሁ ክንዴን ሳልንተራስ አይርብህም፣ አይጠማህም ሁሉን ሰርቼ ነው ያገኛሁት የሰው ላብ አልወሰድኩ ሁሉን መልሼ አገኘዋለሁ!” አለ።
አቤል ” ለ እዛ አደለም የማለቅሰው”
”ታድያ ሌላ ምን አዲስ ነገር መጣ የማላውቀው?”
አቤል ወደመሬት አቀርቅሮ ዝም አለ።
”ንገረኝ አይዞህ የኔ ጌታ ንገረኝ” አባት ግራ ተጋባ።
” ነገ ትምርት ቤት አልሄድም እነ ሰጠሄኝ፣እነ ግርማቸው ሁላችንም ባንድቀን መለያየታችን ነው ….ጓደኞቼን …..አስተማሪዬ ቲቸር አልማዝ…..ቲቸር አልማዝ አንድም ቀን ሲያለቅሱ አይቼ አልቅውቅም ነበር ትናንት ግን ውጡ ተብለናል ብለው መሬት አቀርቅረውሲያለቅሱ ነው የዋሉት……እህህህ ” አቤል ጧ ብሎ አለቀሰ።
አባት ለዚህ አይነቱ ነገር መልስ የለውም።ልጁን አቅፎ አብሮ ማልቀስ ጀመረ።በ ልጅነቱ ባንዲት ጀንበር ቀየውን ለቆ ብሄድ ለ አንድ ሕፃን ልጅ የሚፈጥረውን ስሜት አሁን ልብ አለው።አባትና ልጅ ተላቀሱ። በ መሃል አባትና ልጅን የለያያቸው የ መንግስት ታጣቂ ከ ቤት ገብቶ በጁ የያዘውን የ ስም ዝርዝር እያነበበ ”የናንተ ወረዳውን ለቃችሁ የምትወጡበት ቀን ነገ መሆኑን አውቃችኋል? ” ብሎ ሲደነፋና በ ቁጣ አይን ቤተሰቡን ስገላምጥ ነበር። ታጣቂው ቶሎ ከቤት መውጣቱ ነው አንጂ ትልቅ ፀብ ሊፈጠር የነበረ መሆኑ የ ቤቱ የ ዝምታ እና ሊገነፍል ያኮበኮበ የ ቁጣ መንፈስ ያስታውቃል።
ይህ ከ ሆነ ከ ሳምንት በኋላ አቤል ና ቤተሰቡ የተገኙት አዲስ አበባ በ አንድ መጋዘን ውስጥ ከ ብዙ ከነርሱ መሰል ስዱዳን ጋር ነበር። አቤል አሁንም የ ስነ-ዜጋው ደብተር ላይ የተማራት ስነ-መንግስት ምራፍ ሶስት ላይ ያሉት ፅሁፎች ትዝ ብለውት እረፍት ነሱት። ቢቸግረው ያገኘውን ሰው ሁሉ መጠየቅ ጀመረ። ቆይቶ ግን አጎቱ ”ልጄ ደብተርህን በጉያህ አርገው! እንዳታስፈጄን ” ያለው ንግግር ዝም አንዲል አረጉት።
አቤልን አጎቱ ”ደብተርህን በጉያህ!እንዳታስፈጄን” ያሉት ቀን አይረሳውም።ቀኑ የ አዲስ አበባ የ መጋቢት ወር ዝናብ መሬቷን ማራስ የጀመረበት ቀን ነበር።ድንገት ”ከ መንግስት የመጣን ነን መንግስት የወሰነውን ልናሳውቃችሁ ነው ” ያሉ ሰዎች ስደተኞቹ ወዳረፉበት መጋዘን መጥተው መንግስት ወደየ ክልላችሁ ግቡ በሏቸው ብሎናል” ብለው ሲናገሩ ።
አቤል በንዴት ተነስቶ
” ሃገሬ ስንት ነች? ኢትዮጵያ አንድ አይደለችም? እስከ ዛሬ የኖርኩባት የኔ ሀገር አደለችም ? የተወለድኩት ጉርዳፋርዳ ነው። ሌላ ሀገር አላውቅ?” አቤል በንባ የተሞሉ አይኖቹን ይዞ ፊቱን ከ ካድሬው ወደ አባቱ አዞረና ጥያቄውን ደገመው። በ አዳራሹ ውስጥ ያሉት ሁሉ ትንፋሻቸውን ውጠው ማዳመጥ ጀመሩ።አቤል ቀጠለ ” አባዬ ሃገረ ስንት ነች? ሀገራችሁ ግቡ የሚለን?”
ብሎ ሲናገር አዳራሹ ለቅሶ በለቅሶ ሆነ።
ከለቅሶው ቀጥሎ ግን ጥያቄው ጎረፈ በተለይ በትምህርት ገፋ ያሉት ጥያቄ ሊያባራ አልቻለም።
”በ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ መኖርያውን ትቶ መሰደድ የ ሀገር አደጋ አደለም? ቀይመስቀል የት ነው? የ አደጋ ጊዜና ዝግጁነት ኮሚሽን የሚባል መስርያበት በ ‘ብአዴን ‘ ተተካ? ይህ ሰው ሰራሽ አደጋ አይደለም?” ወዘተ ጥያቄ።
የ አቤልን የምታህል ከባድ ጥያቄ ግን አልተገኘችም የ ትውልዱ ጥያቄ ሆና ትኖራለችና።
” ሃገሬ ስንት ነች? ኢትዮጵያ አንድ አይደለችም? እስከ ዛሬ የኖርኩባት የኔ ሀገር አደለችም ?” የምትለዋ ጥያቄ።
አዎን ሀገራችሁ ግቡ ባዮች ከ አቤል የከበደ ጥያቄ ይገኝላችሁ ይሆን ? ሀገራችን ኢትዮጵያ በናንተ አቆጣጠር ስንት ነች? አሁን የምንኖርባት ሀገራችን አደለችም?
በ ጌታቸው በቀለ
መጋቢት 30/2004 ዓ.ም.
ኦስሎ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar