እኒህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር በስደት ያለውን፥ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራውን ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ፥ እኛ ስደተኞቹ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን፥ አመራሩን እንዳንቀበለው የሚያደርግ የጥሪ ደብዳቤ ጽፈው ፥በየድረ ገፆቹ ወጥተው በማየቴ የተሰማኝን መሪር ሃዘን የምገልጽበት ተመጣጣኝ በቂ ቃላት ባላገኝም ፥ የቻልኩትን ያህል ይችን አጭር መልስ ሳከብራቸውና ስወዳቸው ለነበርኩት አባቴ ለመስጠት ሌላ ሳይሆን ህሊናየ አስገደደኝ። እኒህ አዛውንት ምሑር ብዙ ነገር ስለቤተ ክርስቲያናችን ስለሚያውቁ በየጊዜው ለሕዝብ የሚያስተላልፏቸው መልክቶች ሊኖራቸው የሚችለው አሉታዊም ሆነ ኣወንታዊ ተጽእኖዎች በቀላሉ የሚገመቱ አይደሉም። አወንታዊ የሆኑት መልክቶቻቸው ላንድነታችን ጥንካሬ የማይናቅ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ሁሉ ፥ ባንጻሩም አሉታዊ መልክቶቻቸው ደግሞ አንድነታችንን ለማዳከምና ለመከፋፈል የሚጫወቱት ሚና እንዲሁ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ‘’ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እኮ እንዲህ ብለዋል’’ እያሉ ሊቀበሉ የሚችሉት ብዙዎች ናቸው። እኔም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንዱ ነበርኩ። ስለታሪካችን ፥ ስለቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናና ዶግማ ብዙ እውቀትን ከሚጽፏቸው መጻሕፍት ሸምቻለሁ ። ከጊዜ በኋላ ግን የሚሉትን ሁሉ ከመቀበሌ በፊት ጥንቃቄ ማድረግን መረጥኩ።
በዚህም የተነሳ ‘’ እናት ቤተ ክርስቲያናችን አልተከፈለችም’’ የሚል መልክታቸውን ፥ ሳይ ዛሬስ ምን ማለታቸው ነው ? ብየ መጠየቅ ጀመርኩ። መከፈል ወይም መካፋፈልን በነገረ መለኮት ብቻ ወስነውታል። በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጣስ ምክንያት ባስተዳደር በኩል ያለንን ልዩነት ቀደም ሳይሆን አሁን ለምን በቀላሉ እንዳዩት ግን እኔ ልረዳው አልቻልኩም። ፓትርያርክ በሕይዎት እያለ ሌላ ሰው በፓትርያርክ ሥልጣን መንበሩ ላይ መቀመጥ እንደማይችል ነግረውናል። አሁን በሕይዎት ያሉት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ መሆናቸውንም አልካዱም። እንዲያውም አንዴ ‘’ኢትዮጵያን ርጅስተር’’ ሲባል በነበረው መጽሔታቸው ፥ October 1997 ባወጡት እትም ላይ እንዲህ ብለው ነበር “ ፓትርያርኩ ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በስደት ላይ እንዳሉ የሚያስተላልፉዋቸው መልክእክቶች እንደሚያመለክቱት ስለጸድቅ ተሰደዱ እንጅ ክሥልጣናቸው አልወረዱም። በስደትና በድብቅ ለመኖር ቅዱስነታቸው የመጀመሪያው ፓትሪያርክ አይደሉም። የመንፈስ ቅዱስ አባታቸው አባ አትናቴዎስ በአራተኛው ምእት ዓመት የግብጽ ፓትርያርክ በነበረበት ጊዜ አርዮሳውያን ከዘመኑ ንጉሥስ ከከሐዲው ከቆስጠንጢኖስ ጋራ በመመሳጠር ከሀገር ወደሀገር ያሳድዱት ነበረ ።” ካሉ በኋላ እኒህ ታላቅ አዛውንት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ሃሳባቸውን በማጠናከር ፣ “ ..ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ናቸው። ዶ/ር ጳውሎስ በመንበሩ ላይ የተቀመጡት ከቤተ ክርስቲያን ሕግ ውጭ ስለሆነ እውቅና አይገባቸውም። ሁለተኛ ፥ ፓትርያርኩ ሲሰደዱ ሊቃነ ጳጳሳትም ተከታትለው ስለተሰደዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ በፓትርያርኩ ፈቃድ የሚሰበሰበው የሊቃነ ጳጳሳትና የጳጳሳት ጉባኤ ነው።”
አሁን ደግሞ እኒህ አባታችን ፕሮፌሰር ጌታቸው ያኔ የነበረውን በእውነት ላይ የተመሠረተውን ሀሳባቸውን ለውጠው ፤ “የአንድ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ማእከል ከሕዝቡ ማእከል መሆን እንዳለበት መካድ አይቻልም። ስለዚህ፥ በሕዝብ ማህል ያለውን የኢትዮጵያውን ጭቁን ሲኖዶስና የቤተ ክርስቲያንን አመራር ታግሎ፥ ከወያኔ እጅ ነፃ አውጥቶ፥ ከመውሰድ ይልቅ፥ ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ ሲኖዶስ ማቋቋም ሕጋዊ አለመሆኑን ሲኖዶስ አቋቋሚዎች ያውቁታል።” ይሉናል። ለ1600 ዘመን የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ የመራን በመንፈስ እንጅ በአካል ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ መካከል ሁኖ ነበር ?ለምን ይሆን ከኞቹ ላይ ሲሆን ይህ አሰራር የሚነቀፈው? ምሥጢሩ ምን ይሆን ? ፕሮፌሰሩ አዲስ አበባ ያለውን ጭቁን ሲኖዶስ ብለውታል። ያን ‘ጭቁን ሲኖዶስ’ ማን ነው እየገዛው ያለው ? አንድ አካል ራሱን ይጨቁናል እንዴ ? ሲኖዶስ ማለት የጳጳሳት ጉባኤ መሆኑን ከተስማማን ታዲያ በዚህ በአዲስ አበባ ውስጥ ባለው ሲኖዶስ የተሰባሰቡት ጳጳሳት ተጨቁነናልና ነፃ አውጡትን የሚል ጥሪ መች ለእኛ ለድያስጶራዎች የድረሱልን ጥሪ አቀረቡ ? ወገኖቻችን ድረሱልን መቸ አሉን? የተጣሰ ቀኖና ይስተካከል ፥ ለ2ኛ ጊዜ ቀኖና ጥሳችሁ 4ኛው በሕይዎተ ሥጋ ተቀምጠው 6ኛ ብላችሁ መንበሩ ላይ ሌላ ሕገ ወጥ ሰው አታስቀምጡ፤ የሚለውን ጥሪያችን አሻፈረን ብለው ሌላ የወያኔ ካድሬ ለመሾም ሸር ጉድ የሚሉትን ጳጳሳት ነው ጭቁኖች የሚሏቸው ? ወይስ በዚያ ሰብሰብ ውስጥ ፕሮፌሰር ጌታቸው በግል የሚያውቋቸው የአዲስ አበባ አካባቢ ተወላጆች ጥቂት ጳጳሳት ስላሉበት ነው ‘’ጭቁን’’ የሚል ቅጽል የለጠፉለት? እነ አቡነ ገሪማን ነው ጭቁን የሚሏቸው ? በምን መመዘኛ? ተቋሙን ነው ጭቁን ያልኩት ካሉንም መንግሥታዊ ተቅዋሙም እኮ በዚህ ስሌት ጭቁን ሊባል ነው። ሁለቱም ተቋማት ወያኔ የራሱ አድርጉኣቸዋል። በተቋሙ ውስጥ ያሉትም ፥ መሪዎቹም ሆኑ ተከታዮቹ ያው ወያኔዎች ናቸው። በጭቆና ቀንበር የሚኖረው ሕዝባችን እንጅ የተቋሙ መሪዎች አይደሉም። እነሱማ ራሳቸው ጨቋዋኞች ፥ አለያም የጭቆናው መሳሪያዎች ናቸው። ስደተኞቹ አባቶች አይሆኑም ወይ ግፉዐን ፥ ስዱዳንና ጭቁኖች ልንላቸው የሚገባው ? ምነው ፕሮፌሰር መጀመሪያ የነበራቸውን ብሩሕ ገጽታቸውን ዛሬ በነዚህ በግፍ በተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ላይ አጠቆሩባቸው? እነሱ የተወለዱበት መንደርም እኮ ቢሆን የርሳቸውም ነው። እርሳቸው የተወለዱበትም እንዲሁ የነርሱ ነው። የሁላችንም ነው። አሁን በዚህ መልክታቸውስ ማን ነው የሚደሰተውና የሚጠቀመው ? ማን ነውስ የሚከፋውና የሚጎዳው ? አዎ የሚጠቀመውና የሚደሰተው ጠላት የምንለው ወያኔ እንጅ ፥ በውጭም ሆነ በውስጥ ወያኔን እየታገለ ያለው ሕዝባችን እንደማይሆን ለርሳቸው ለታላቁ ምሑር አባት ይሰወራል ብየ ምንም አይነት ብዥታ የለኝም።
ራስ የሌለው ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን በቄሶች ብቻ መመሥረት እንደማይገባም እኒሁ አባታችን የዛሬን አያድረገውና በቀደመ አቋማቸው እንዲህ ብለው ነበር “ …ከኢትዮጵያ ካለውና በስደት ላይ ካለው አመራር (ሲኖዶስ) አንዱን መምረጥ ቤተ ክርስቲያንዋን መከፋፈል ይሆንብናልና ማንንም አንቀበልም ብለው በአንድ ካህን የበላይነት ብቻ የሚገለገሉ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች አሉ። ርእስ እንደሚያስፈልጋቸው ልብ አላሉትም። “ እነዚህን የመሳሰሉ እውነታውን የሚያረጋግጡ ሃሳቦች Ethiopian Register Vol. 4, no. 10, October 1997 page 60-61 ላይ አስፍረው ነበር። ታዲያ ዛሬ ምን የተለየ ነገር ተፈጥሮ ነው አባታችን ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ “ስለዚህ፥ የተሰደዱትን ካህናት የምጠይቃቸው፥ “የእኛን ሲኖዶስ ተከተሉ” እያሉ ሕዝብ ማስጨነቃቸውንና የመከፋፈል ምክንያት መሆናቸውን ትተው፥ የድዮስጶራው ሕዝብ ወያኔን ሲቃወም ተጨማሪ ኀይል እንዲሆኑ ነው። “ የሚሉን ? ካህናቱና ጳጳሳቱ ዋና ሥራቸውን በሃይማኖት አግልግሎት ሳይሆን ወያኔን በመታገሉ ላይ ያተኩሩ የሚለውን ሃሳብ ፥ ማለት የሃይማኖቱን ጉዳይ ትተው በፖለቲካው ሥራ ላይ እንዲያተኩሩ የሚያዘውን የመጽሐፍ ማስረጃ ግን አልሰጡንም። ታዲያ ይህ ከሆነ እውነተኛ እምነታቸው ለምን ከላይ በ1997 ዓ.እ የተጠቀሱትን ሃሳቦች እንዳሁኑ ሕዝብ እንዲያውቃቸው አያደርጉም ነበር ? ለምን ኣሁን ?
ዛሬ ከመቸውም በበለጠ በስደት ባሉት አባቶችና አዲስ አበባ ባሉት የወያኔ ወኪሎች በሆኑት፥ በስም ብቻ ጳጳሳት እየተባሉ በሚጠሩት መካከል ያለው ልዩነት ለሁሉም ቁልጭ ብሎ በርቶ በታየበት ወቅት ፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ልዩነቱን ሊያጨልሙት ሲሞክሩ እውነትን ከማንምና ከምንም በላይ ለምናይ ወገኖች ታላቅ አባታችን ስለሆኑ ብቻ ዝም ብለን የምናልፈው ነገር ሁኖ አላገኘሁትም። እርግጠኛ ነይ ገና ከኔ የተሻለ እውቀትና ችሉታ ፣ ምንልባትም ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ በሙያ የተደገፈ ችሎታ ያላቸው ብዙዎች ተገቢ መልስ ይሰጣሉ ብየም እጠብቃለሁ። ባሁኑ ወቅት በድያስጶራ የምንገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ፥ ባገር ቤት ሲኖዶስ ወይም ገለልተኛ በሚል ተከፋፍለን የቆየነው ሁላችንም በስደተኛው ሕጋዊ ሲኖዶስ አመራር ሥር ሁነን፥ በፍቅርና ባንድነት ሠንሠለት ተሳስረን፥ አገር ቤት ያለውን ሕገ ወጥ የወያኔ ወኪል ‘ሲኖዶስ’ ተብየው የሚሾመውን ሕገ ወጥ የካድሬ ‘ፓትርያርክ’ አናውቅህም ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መሪ ሳትሆን የጠላታችን የወያኔ አገልጋይ የሆንክ ፥ የባዕዳን እምነት ቅጥረኛ ነህ ብለን፥ እውነተኛ ማንነቱን በህብረት ቁመን ማጋለጥ በሚጠበቅብን ወቅት፤ በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራውን ቅዱስ ሲኖዶስ ትተን 3ኛ ሲኖዶስ ማቋቋምን እንደ አማራጭ እንድንወስድ እንደሚከተለው ጋብዘውናል ። ‘’የድዮስጶራው ሕዝበ ክርስቲያ የሚኖረው ኢትዮጵያ ካለው ሕዝበ ክርስቲያን የተለየ ችግር በሚያስከትል በተለየ የባህል አካባቢ ነው። ይኸ ልዩ የባህል አካባቢ የሚያመጣውን ችግር የሚረዱለት ካህናት ያስፈልጉታል። ስለዚህ፥ የድዮስጶራው ካህናት ድርጅት አቋቁመው፥ የሕዝቡን ችግር ለመረዳትና መፍትሔ ለመፈለግ በየጊዜው እየተሰበሰቡ መመካከር፥ እርስ በርሳቸው መማማር፥ ልምድ ካላቸው አብያተ ክርስቲያናት ተናጋሪ እየጋበዙ ልምዱን እንዲያካፍላቸው መጠየቅ ያስፈልጋቸዋል። ያንን ድርጅት “መካናዊ (ሀገረ ስብከታዊ) ሲኖዶስ”፥ ወይም “ረክበ ካህናት ጉባኤ” ሊሉት ይችላሉ። ቀኖና ነው። የሚከፋፍለንን ሲኖዶስ በዚህ በሚያስተባብረን ሲኖዶስ ስም ቢጠሩት፥ ያስከብራቸዋል። ሁላችንም እንከተላቸውና፥ “ከፋፋይ ” የሚለው አስከፊ ታሪካቸው ይፋቅላቸዋል።’’
እንዲህ ያለ ከፋፋይ እንቅፋት መፍጠር ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አይጠበቅም ነበር። እኔ እንዲያውም ስማቸውን ተጠቅሞ ሌላ ድብቅ አጀንዳ ያለው ግለሰብ መሆን አለበት የጻፈው እስከማለት ደርሸ ነበር መጀመሪያ ጽሑፉን ሳየው። ይህ ነው ከአንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር አባት የሚጠበቀው የተበተኑ ልጆቹን የመሰብሰብ ሥራ ? ይህን ነው ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የምንማረው የአንድነት ጥበብ ? ከሁለት አልፎ ከሦስት መከፈል ነው የመከፋፈልን ችገር የምንፈታበት ጥበብ ከፕሮፌሰሩ የምንማረው ? ‘’አይቴ ብሔራ ለጥበብ ? ወአይቴ ማኅደራ ? አይቴ ደወላ ? ወበአይቴ ተረክበ ዐሠረ ፍኖታ ?=የጥበብ አገርዋ ወዴት ነው ? ማደርያዋስ ወዴት ነው ? ቦታዋስ ወዴት ነው ? የጎዳናዋስ ፍለጋ በወዴት ተገኘ ? “ ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ዘደሴተ ቆጵሮስ።
በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ይላሉ ፤ “መዓቱ እስኪያልፍ ድረስ፥ ቅዱስ ገብርኤል “ንቁም፡ በበህላዌነ፡” እንዳለው፥ ባለንበት ነቅተን እንጽና። “ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በ1997 ዓ.እ ማን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መሪ እንደህነ እውቅና የሰጡት ፕሮፌሰር፥ እንደገና ዛሬ እንደማያውቁ ሁነው የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ጥቅስ ይጠቅሱልናል። ቅዱስ ገብርኤል ይህን የተናገረው በማኅበረ መላእክት መካከል ተፈጥሮ በነበረው ክፍፍል ጊዜ ነው። እግዚአብሔር የመላእክትን ታማኝነት ለመፈተን ለተወሰነ ጊዜ ተሰውሯ ቸው ነበር። ያኔ የመላእክት አለቃ የነበረው ሣጥናኤል (የስሙ ትርጉም የእግዚአብሔር ባለሥልጣን ማለት ነው) ‘’አነ ፈጠርኩክሙ ወአነ ገበርኩክሙ ፥ ስግዱ ለግብረ ዚአየ=እኔ ነኝ የፈጠርኳችሁና ለኔ ስገዱ፥ ተገዙልኝ/አምልኩኝ’’ በሚልበት ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በፍጥነት ተነስቶ ‘’ኦ አንትሙ ማኅበረ መላእክት ! ኢትእመኑ በዝንቱ መልአክ እስመ ውእቱ ፍጡር ከማነ ፤ ንቁም በበሕላዌነ እስከ ነአምር ፈጣሪነ = እናንት የመላእክት ማኅበር አባላት ሆይ ! በዚህ እንደኛ ፍጡር በሆነ መልአክ እንዳታምኑ ! ፈጣሪያችንን እስከምናየው ድረስ በያለንበት/በእምነታችን/በታማኝነታችን እንቁም !’’ የሚል ጥሪ በማሰማቱ 99ኙን ነገደ መላእክት ከክህደት ሲያድን ፤ በሣጥናኤል ያመነው አንዱ ነገድ በመካዱ ከብርሓን ወደ ጨለማ ወደቀ። በጨለማ የወደቀው የጥፋት ኃይል ብቻውን ወድቆ አልቀረም ፥ አዳምንና ሔዋንንም አስቶ ለ5500 ዘመን በዘመነ ፍዳ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። ዛሬም እንደ ወያኔና ተከታዮቹ ባሉት ሁሉ እያደረ የሚያውከን ፥ የሚከፋፍለን፥ የሚያጋጨን ፥ ነባር ሥርዓታችንና ባህላችን እያፈረሰ ያለው ጥንተ ጠላታችን ድያብሎስ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ይላሉ ፤ “መዓቱ እስኪያልፍ ድረስ፥ ቅዱስ ገብርኤል “ንቁም፡ በበህላዌነ፡” እንዳለው፥ ባለንበት ነቅተን እንጽና። “ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በ1997 ዓ.እ ማን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መሪ እንደህነ እውቅና የሰጡት ፕሮፌሰር፥ እንደገና ዛሬ እንደማያውቁ ሁነው የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ጥቅስ ይጠቅሱልናል። ቅዱስ ገብርኤል ይህን የተናገረው በማኅበረ መላእክት መካከል ተፈጥሮ በነበረው ክፍፍል ጊዜ ነው። እግዚአብሔር የመላእክትን ታማኝነት ለመፈተን ለተወሰነ ጊዜ ተሰውሯ ቸው ነበር። ያኔ የመላእክት አለቃ የነበረው ሣጥናኤል (የስሙ ትርጉም የእግዚአብሔር ባለሥልጣን ማለት ነው) ‘’አነ ፈጠርኩክሙ ወአነ ገበርኩክሙ ፥ ስግዱ ለግብረ ዚአየ=እኔ ነኝ የፈጠርኳችሁና ለኔ ስገዱ፥ ተገዙልኝ/አምልኩኝ’’ በሚልበት ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በፍጥነት ተነስቶ ‘’ኦ አንትሙ ማኅበረ መላእክት ! ኢትእመኑ በዝንቱ መልአክ እስመ ውእቱ ፍጡር ከማነ ፤ ንቁም በበሕላዌነ እስከ ነአምር ፈጣሪነ = እናንት የመላእክት ማኅበር አባላት ሆይ ! በዚህ እንደኛ ፍጡር በሆነ መልአክ እንዳታምኑ ! ፈጣሪያችንን እስከምናየው ድረስ በያለንበት/በእምነታችን/በታማኝነታችን እንቁም !’’ የሚል ጥሪ በማሰማቱ 99ኙን ነገደ መላእክት ከክህደት ሲያድን ፤ በሣጥናኤል ያመነው አንዱ ነገድ በመካዱ ከብርሓን ወደ ጨለማ ወደቀ። በጨለማ የወደቀው የጥፋት ኃይል ብቻውን ወድቆ አልቀረም ፥ አዳምንና ሔዋንንም አስቶ ለ5500 ዘመን በዘመነ ፍዳ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። ዛሬም እንደ ወያኔና ተከታዮቹ ባሉት ሁሉ እያደረ የሚያውከን ፥ የሚከፋፍለን፥ የሚያጋጨን ፥ ነባር ሥርዓታችንና ባህላችን እያፈረሰ ያለው ጥንተ ጠላታችን ድያብሎስ ነው።
ስለዚህ እኛ በስደት የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች፥ የቤተ ክርስቲያናችን ሕጋዊ ፓትርያርክ ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ቅዱስ ሲኖዶስ በመካከላችን ተደብቆ ሳይሆን በገሐድ አብያተ ክርስቲያናት እያቋቋመ ፥ በባዕድ አገር የሚወለዱ ልጆቻችንን እያጠመቀ ፤ ሃይማኖታቸውን ፥ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ጨርሰው እንዳያጠፉ እያሰተማረ፣ የክህነት ሥልጣን እየሰጠ ስላለ ፤ከመንደርተኝነት በሺታ ተላቀን አመራሩን እየተቀበልን ወደ ተስፋይቱ ምድር ፥ ቅድስት ኢትዮጵያ እስከምንመለስ ድረስ አብረነው ቁመን መቆየት አለብን። ለሀጋራችን ነፃነትም ከሦስት ተከፋፍለን ሳይሆን በአንድነት ባንድ አመራር ሥር ሆነን ስንታገል ነው ለድል የምንበቃው። እኛ ክርስቲያኖቹ በቤተ ክርስቲያን አመራር አንድ ሳንሆን በፖለቲካውም ባንድ ላይ መምጣት አንችልም። ያለውን እያፈረስን ሌላ በመገንባትም አይደለም። ዓለማውያኑ መንግሥታት ብቻም ሳይሆኑ እግዚአብሔርም ጭሆታችንን ሊሰማን የሚችለው ባንድነት ሁነን ‘’ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ = የአንተ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ አንድ እንሆን ዘንድ አንድነትን ስጠን’’ እያልን ስንጸልይ ብቻ ነው። ‘’በእንተ ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ መርቆሬዎስ ፥ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ፤ ወኩሉሙ ሊቃነ ጳጳሳት፥ ቀሳውስት ወዲያቆናት ፥ ወኩሎሙ ምዕመናን እለ ቆሙ ምስሌሁ በጊዜ ስደቱ’’ እያልን ነው መጸለይ የሚገባን። ይህ ነው ከእኛ የሚጠበቀው። እንደዚህ ያለ መልክት ነው እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከመሳሰሉት አዛውንት ምሁራን አባቶቻችን ለመስማት ጀሮዎቻችን መጠማት ያለባቸው። ‘ዐይኔን ሰው አማረው’ የምንልበት ጊዜ አሁን ነውና ፥ ምሁራን አባቶቻችን ሳትከፋፍሉን ወደ አንድ አቅጣጫ እንድንመጣ እርዱን። አሁን ባለንበት ሁኔታ ማንም ገለልተኛ ሊሆን አይገባም። ‘እነዚያም የኛ አይደሉም ፥ እነዚህም የኛ አይደሉም ‘ የሚል ነገር መቆም አለበት! ቀኖና አፍርሶ ግፍ በፈፀመውና በግፍ በተሰደዱት አባቶች መካከል የሞራል እኩልነት የለም።
እግዚአብሔር ዐይነ ህሊናችንን ያብራልን !
ከበደ አገኘሁ ዘውእቱ ስምአ ጽድቅ።
እግዚአብሔር ዐይነ ህሊናችንን ያብራልን !
ከበደ አገኘሁ ዘውእቱ ስምአ ጽድቅ።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar