የፖለቲካው ስር ቁማርተኞች!
(ተመስገን ደሳለኝ)
በሀገራችን መንግስታዊ አስተዳደር የ‹‹ቁማር ህግ››ን ችግር መፍቻ አድርጎ መጠቀም የጀመረበትን ጊዜ
ለማስላት ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ምንሊክ እንደ"ተበሉበት" ከሚነግረን የሽኩሹክታ ታሪካችን አንስቶ አንድ፣
ሁለት፣ ሶስት… እያልን ለመቁጠር እንገደዳለን፡፡ ይሁንና ባለሙያ (በንባብ የደረጀ) ቁማርተኛ ፖለቲከኛ እንደ
ሰማይ ከዋክብት የበዛበት ድንገቴ ክስተት የ1966ቱ አብዮት ዋዜማ ነው ቢባል ወደ እውነታው ይጠጋል፡፡
ከመንግስቱ ኃ/ማሪያም ‹‹ለምሳ ያሰቡንን፣ ቁርስ አደረግናቸው›› እና የአጥናፉ አባተ ፍፃሜን ጨምሮ
የእነተስፋዬ ደበሳይና ብርሃነ መስቀል ረዳ፤ የእነኃይሌ ፊዳና አለሙ አበበ፤ የእነሌንጮ ለታና ባሮ ቱምሳ፤ የእነ
አባይ ፀሀዬና አረጋዊ በርሄ፤ የእነታምራት ላይኔና ያሬድ ጥበቡ… ከትግል መድረክ መገለል ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ደግሞ በእነመለስ ዜናዊና ስዬ አብርሃ፤ በእነኃይሉ ሻውልና ቀኝ አዝማች ነቅዐ ጥበብ፤ በእነብርሃኑ ነጋና
ልደቱ አያሌው፤ በእነመረራ ጉዲናና አልማዝ ሰይፉ፤ በእነግዛቸውና ያዕቆብ ኃ/ማርያም… መካከል የተፈጠሩ የሃሳብ ልዩነቶች የተፈቱበት
መንገድ በዚሁ የጨዋታ ህግ የተስተናገደ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ተጨባጭ ሁነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ልዩነቶች የተቋጩት ከመተዳደሪያ
ደንብ ውጪ፣ የተሻለ ዕድል ያለውን ካርታ ቀድሞ በመዘዘ ብልጣ ብልጥ አሸናፊነት ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ የምናየው ‹መልክአ ቁማር›ም
ከእንዲህ አይነቱ የጥሎ ማለፉ ጨዋታ በተጨማሪ የመንፈስ ልዕልናቸውን ያረከሱትንም የሚያካትት ይሆናል፡፡
ቁማርተኞቹ…
የተለመደውን ‹‹ፖለቲካ፣ ቆሻሻ ጨዋታ ነው›› ፈረንጅኛ አባባል እንደፈጣሪ ትዕዛዝ በልባቸው ያሳደሩ ፖለቲከኞች እንደአሸን የፈሉት
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ነው፤ የሀገሬንም ‹ዕድል ፈንታ› በመዳፋቸው የጨበጡ መሪዎች ከዚሁ መልክአ ምድር መብቀላቸው ይመስለኛል
አስከፊ ድህነት፣ ተደጋጋሚ ድርቅ (ችጋር)፣ ሀገር ለቆ መሰደድ፣ የነፃነት እጦት፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ… በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ
እንደ ምርጊት የተጣባን፡፡ ይሁንና ‹ይህ ለምን ሆነ?› የሚለው ጥያቄ የባለሙያ ጥናት የሚሻ ጉዳይ ቢሆንም በአይን የሚታየውን፣ በጆሮ
የሚሰማውን አንድ ምክንያትን ግን መጥቀስ ይቻላል፡- ‹‹ባለስልጣናቱ ከሚያስተዳድሩት ህዝብ በላይ፣ ለሹመት ያበቃቸውን ድርጅት
አጥብቀው መፍራታቸው››ን፡፡
በእኔ አተያይም ይህ ስር የሰደደ ፍርሀት ከህግና መርህ ይልቅ፣ የጥቂት ወሳኝ ሰዎችን ፍላጎት እንዲያስፈፅሙ፤ ከሀገር ይልቅ ድርጅትን፣
ከድርጅት ይልቅ ሥልጣንንና የግል ጥቅምን እንዲያስቀድሙ አስገድዷቸዋል፤ ወደዚህ አይነቱ ቅጥ ያጣ ፍርሃት ለመገፋታቸውም ሁለት
ምክንያት መጥቀስ ይቻላል፤ የመጀመሪያው ከብቃትና አቅም ጋር በተያያዘ (ከትምህርት ዝግጅትም ሆነ ከፖለቲካ ብስለታቸው ጋር
በማይመጣጠን ከፍተኛ ሥልጣን ላይ እንዲቀመጡ መደረጉ) ሲሆን፤ ሌላኛው በሥልጣን ዘመናቸው የስግብግብ ነጋዴ ባህሪ
የተጠናወታቸው ዘራፊ መሆናቸውን ነው፡፡ እነዚህ ኩነቶች ደግሞ ለከፍተኛ ስልጣን ላበቋቸው አንጋፋ ታጋዮች ለጥ-ሰጥ ብለው የሚገዙ
‹ትጉህ ባሪያ› እንዲሆኑ ተፅዕኖ አድርገውባቸዋል፤ ታማኝነታቸውን ያጎደሉ ዕለት ደግሞ ወደ ወህኒ ሊያስወረውር የሚችል ‹ጥቁር
መዝገብ› (ሙስኛነታቸውን የሚያጋልጥ) መጠባበቂያ ተደርጎ መቀመጡን ማወቃቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲን እንደ ‹የግል አዳኝ› አድርጎ
ከመቀበል በቀር አማራጭ አሳጥቷቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ብሔራዊ ጥቅምንና ህዝብን የሚጎዳ ትዕዛዝ ሲሰጣቸው ‹ለምን?› ብለው
መከራከር አይችሉም፡፡ በርግጥ ስልቱ ቃል-በቃል የተቀዳው ጨቋኝ ገዥዎችን ምክር ይለግስ ከነበረው ኒኮሎ ማኪያቬሊ ‹‹ዘ ፕሪንስ››
ከተሰኘ መፅሀፍ ነው፡-
‹‹የሚሾማቸውን ባለሥልጣናት በሚጠቅመው መልኩ መቅረፅ የሚሻ ገዥ፣ ባለስልጣናቱን መንከባከብ፣ ለክብር ማብቃትና በሀብት
ማበልፀግን መዘንጋት የለበትም፤ ከዚህም በላይ ክብሩንና ስልጣኑን ከእነርሱ ጋር በመጋራት ባለውለታው ሊያደርጋቸው ይገባል፤ ይህ
ሲሆንም የገዥው ፍፁማዊ አገልጋይ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡››
በእንዲህ አይነት ሁኔታ ሰብዕናው ‹ፈርሶ የተሰራ› ተሿሚም በሥልጣን ዘመኑ ሀገር፣ ህዝብ፣ ህገ-መንግስት፣ ህሊና… እያለ የሚጨነቅበት
ሁናቴ አይኖርም፡፡ ፍትህ ቢዛባ፣ ንፁሀን በጥይት ቢደበደቡ፣ ሚሊየኖች በረሀብ ቢረግፉ… አይቆረቁረውም፤ የእርሱ ጭንቀት ለሿሚዎቹ
ያለውን ታማኝነት ሳያጓድል በስልጣን መቀጠሉ እና ከለታት አንድ ቀን ‹ይመጣል› ብሎ ለሚሰጋበት ክፉ ቀን ራስን አዘጋጅቶ መጠበቁን
አለመዘንጋት ነው፤ የትዳር አጋር እና ልጆችም አሜሪካና አውሮፓን የሙጢኝ የማለታቸው መግፍኤ ይህ ይመስለኛል፡፡ መቼም ስንት
ሚኒስትር፣ ስንት ጄነራል ያችን የቀን ጎደሎ ‹ታጥቦና ታጥኖ› እየጠበቀ መሆኑን ‹‹ጊዜ ይቁጠረው›› ከማለት ውጪ ስም ዝርዝሩ ውስጥ
መግባቱ አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም፡፡ የገዥዎችን ስነ-ልቦና ጠልቆ የተረዳው ማኪያቬሊም ቢሆን ሰዎቹ በእንዲህ አይነት ወቅት
የሚወስዱትን እርምጃ ገና ድሮ እንደሚከተለው ገልፆት ነበር፡-
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar