mandag 4. november 2013
የሌለውን ፍለጋ - ክፍል አንድ
ዳንኤል ክብረት
ተስፋየ ገብረ አብ ‹የስደተኛው ማስተዋሻ› የተሰኘ መጽሐፍ ማውጣቱንና ባነበው መልካም እንደሆነ ገልጦ አንድ
ወዳጄ ‹ስስ ቅጅውን› ከሀገረ አሜሪካ ላከልኝ፡፡ ከዚህ በፊት ሌሎች መጻሕፍቱን አንብቤያቸዋለሁ፤ በአጻጻፍ
ችሎታው የምደሰተውን ያህል እንደ አበሻ መድኃኒት ነገሩን ሁሉ እርሱ ብቻ የሚያውቀው ምስጢር
ስለሚያደርገው፤ በአንዳንድ ጉዳዮችም ሆን ብሎም ሊያናጋቸው የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ያሉ
ስለሚመስለኝ፤ ተስፋዬ ለምን እንደዚህ ይጽፋል? እያልኩ የምጠይቃቸው ነገሮች ነበሩ፡፡
በዚህ መጽሐፉ ውስጥም ያንን ጥርጣሬየን አጉልቶ ሥጋ ነሥቶ እንዳየው የሚያደርገኝ ነገር ገጠመኝ፡፡ ተስፋየ በገጽ
306 ላይ ‹‹የፍስሐ ጽዮን ፖለቲካ› በሚል ርእስ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የማያውቀውን ነገር ጽፏል፡፡
ስለማያውቀው ነገር የጻፈው ባለማወቁ ብቻ አይመስለኝም፡፡ አንድም ለማወቅ ባለመፈለጉ፣ አለያም ሆን ብሎ የማፍረስ ዓላማ ይዞ
ይመስለኛል፡፡
ይህን የምለው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ ተስፋዬ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለመጻፍ ሲፈልግ ሊያነባቸው የሚችላቸው መጻሕፍት
በምድረ አውሮፓ እንደ ማክዶናልድ በዝተው ሞልተው ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ባልሆኑ ሰዎች የተጻፉ ናቸው፡፡
ሌላው ቢቀር ኤንሪኮ ቼሩሊ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔቶች ታሪክ(Gli Abbati di Dabra Libanos, 1945)፣ ኮንቲ ሮሲኒ ከሐተታ
ጋር ያሳተመውን ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣በዋልድባ ቅጅ (Il Gadla Takla Haimanot secondo la redazione
Waldebbana, 1896)፣ የዊልያም በጅን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወትና ተአምር (The Life and Miracles of Takla
Haymanot, 1906)፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጸሐፍትም ውስጥ የታደሰ ታምራትን Church and State in Ethiopia, ማንበብ
በተገባው ነበር፡፡
ከዚህም ዘልሎ ጥልቅ ጥናት አድርጌ ደረቴን ነፍቼ እናገራለሁ ለሚል ደግሞ እንግሊዝ ምቹ ናትና ሎንዶን ወደሚገኘው ብሪቲሽ
ሙዝየም ሄዶ በማይክሮ ፊልም የተነሡትንም ሆነ በአካል ያሉትን ብራናዎች ማየት ነው፡፡ እዚያም የማያደርሰው ከሆነ በዋና ከተማው
በሆላንድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙትን የጌታቸው ኃይሌን THE MONASTIC GENEALOGY OF THE LINE OF
TÄKLÄ HAYMANOT OF SHOA, (Rassegna di Studi Etiopici, Vol. 29 (1982-1983), pp. 7-38)፤
የተስፋዬ ገብረ ማርያምን A Structural Analysis of Gädlä Täklä Haymanot(African Languages and
Cultures, Vol. 10, No. 2 (1997), pp. 181-198)፤ የሐንቲንግ ፎርድን (G.W.B. Huntingford, "The Lives of
Saint Takla Haymanot," Journal of Ethiopian Studies, 4(1966), 34-35.) የአሉላ ፓንክረስትን Dabra
Libanos Pilgrimage Past and Present, The Mytery of the Bones and the Legend of Saint Takla
Haymanot,(the sociology ethnology Bulletin) 1,3 (1994), P. 14-26 ጥናቶችን ማየት ይቻል ነበር፡፡ ያም ካልሆነ
ወደ ቤልጅየም ሄዶ ፒተርስ አሳታሚ ከጥልቅ ጥናት ጋር የሚያሳትማቸውን የኢትዮጵያ ጥንታዊ መዛግብት ኅትመቶች ማገለባጥ ይቻል
ነበር፡፡
የገረመኝ ገድለ ተክለ ሃይማኖትን ያህል በኢትዮጵያ ታሪክ (History)ና የታሪክ አጻጻፍ(Historiography) ታላቅ ቦታ ያለው፣
በኢትዮጵያ ገድላት ጥናት(Hagiography) ቀዳሚ የሆነና በብዙ አጥኝዎች የተጠና ጉዳይ ያለ ምንም በቂ ማስረጃ አፈርሳለሁ ብሎ
መነሣቱ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከማይወጣበት የክርክር አዘቅት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡
ተስፋዬ ጽሑፉን የጀመረው በስድብ ነው፡፡ ኤርትራዊት እናቱ ‹ይዘምሩት ነበር‹ ብሎ ያቀረበው ጽሑፍ የራሱን ስድብ በእና ያሳበበበት
ነው፡፡ የኤርትራን ቤተ ክርስቲያንና ኤርትራውያን ክርስቲያን እናቶችን ከእርሱ በላይ አውቃቸዋለሁ፡፡ ተሰድደው በየሀገሩ ከተበተኑት
ጋር አብረን ቋንቋና ድንበር ሳያግደን አገልግለናል፡፡ አሥመራ ከተማ ከሚገኙት ታላላቅ አድባራት አንዱም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ
ክርስቲያን ነው፡፡ በምንም መልኩ አንዲት ኤርትራዊት እናት ተስፋዬ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ የተሳለቀውን ‹መዝሙር›
አትዘምርም፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደማቸው የፈሰሰው ሰባት ዓመት ሙሉ ለጸሎት የቆሙበት እግራቸው በጸሎት ብዛት በመቆረጡ
እንጂ ሰይጣን ‹ፈንግሏቸው› አለመሆኑን ኤርትራውያን እናቶች በሚገባ ያውቁታል፡፡ የሚገርመው ነገር ተስፋዬ በጆሮ ጠገብ የሆነ ቦታ
የሰማውን መዝሙር አጣምሞት እንጂ መዝሙሩ እንዲህ አይደለም፡፡
አቡነ ተ/ኃይማኖት
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar