onsdag 4. september 2013

ልማት ምንድነው? እውን የወያኔ መንግሥት ልማታዊ ነው?


ታደሰ ብሩ 
1. መግቢያ 
“ሰላም ምንድነው?” በሚል ርዕስ ለፃፍኩት መጣጥፍ ከደረሱኝ በርካታ አስተያየቶች ውስጥ “በነካ እጅህ ልማት ምን 
ማለት እንደሆነ ብትገልጽልን” የሚለው ጥያቄ ለዚህ ጽሁፍ ምክንያት ሆኗል። 
ከአሰልቺ የወያኔ ካድሬዎች ክርክሮች አንዱ “ልማታችን፣ ልማታችን” መሆኑ የማውቀውና በራሴም ላይ ከተራ 
ማሰልቸት በላይ የመብት ጥሰቶች ያደረሰብኝ ጉዳይ ነው። ወያኔ በአገራችን ላይ ላሰፈነው አገዛዝ ተቀባይነት 
(ligitimacy) ዋነኛ መከራከሪያው “ለኢትዮጵያ ልማትን ያመጣሁ፤ አሁንም በማምጣት ላይ ያለሁ መንግሥት ነኝ። 
ለወደፊቱም ኢትዮጵያን ለማልማት ከኔ የተሻለ የለም” የሚል ነው። በዚህ ክርክር ውስጥ (1) ከዚህ በፊት በአገሪቱ 
ውስጥ ልማት የሚባል ነበር አልነበረም፤ (2) እኔ ልማትን እያመጣሁ ነው፤ ሌላውን ቻሉት፤ እና (3) ለወደፊቱም ከኔ 
የተሻለ ኢትዮጵያን ማልማት የሚችል የሌለ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሲባል እኔ ለረዥም ጊዜ በስልጣን መቆየት አለብኝ 
የሚል መልዕክት አለው። 
በዚህ ጽሁፍ እነዚህን ሶስቱም መከራከራዎች ውሸት መሆናቸውን ለማስረዳት እሞክራለሁ። ከሁሉ አስቀድሞ ግን 
“ልማት” በተሰኘው ጽንሰ ሀሳብ ላይ የጋራ ግንዛቤ እንያዝ። 
2... የልማት ትርጉም 
በዛሬቷ ኢትዮጵያ መብራት ሲቋረጥ፤ ውሀ ሲጠፋ፤ ጤፍ ሲወደድ፤ መንደሮች ሲፈርሱ፤ የመኪና አደጋ ሲበዛ፤ ገበሬዎች 
ሲፈናቀሉ ሰበቡ ልማት ነው። ማናቸውም ችግር “እድገት ያመጣው ነው፤ ቻሉት” እየተባለ ይታለፋል። ለረሀብ፣ 
ለጥማት፣ ለበሽታ እና መሰል መጥፎ ነገሮች ልማት ምክንያት ሆኖ ሲቀርብ፤ “መብቴ ይከበርልኝ ብሎ መጠየቅ 
“በፀረ-ልማትነት” ሲያስከስስ “ለመሆኑ ልማት ምንድነው?” የሚል የጅል አልያም የልጅ የሚመስል ጥያቄ ለማንሳት 
እንገደዳለን። 
በቀላሉ ከሚገኝ የwikipidia የኢኮኖሚ ልማት (Economic Development) ትርጓሜ ልነሳ። 
... የኢኮኖሚ ልማት ... በሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት፣ በዋና ዋና መሠረተ ልማት አቅርቦቶች፣ 
በአካባቢው ገበያ በሚኖር ተወዳዳሪነት፣ በምቹ የተፈጥሮ አካባቢ (ኢንቫይሮመንት)፣ በማኅበራዊ 
መስተጋብር፣ በጤና፣ በደህንነት፣ በትምህርት እና በመሳሰሉ ነገሮች እድገት ማምጣትን ያካትታል
። 
1
Economic development ... refers to the sustained, concerned actions ... including development of human capital, critical 
infrastructure, regional competitiveness, environmental sustainability, social inclusion, health, safety, literacy, and 
other initiatives. (http://en.wikipedia.org/wiki/Economic_development accessed on 25/08/2013) accessed 31/08/2013 2 
የኢኮኖሚ ልማት የአንድ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊና ማኅበራዊ ደህንነት የሚሻሻልባቸው ሂደቶችና ፓሊሲዎችን 
ያካትታል2
። ልማት በቁጥር የሚለካ (Quatitative) ብቻ ሳይሆን በቁጥሮች መለካት የሚቸግር (Qualitative) ገጽታ 
አለው። እንዲያውም የልማት ዋነኛ ግብ በቁጥሮች ለመለካት አስቸጋሪ የሆነውን “ደስተኛ ማኅበረሰብን” መፍጠር ነው። 
ልማት የአብዛኛውን ሕዝብ የዛሬ ኑሮ እና/ወይም የነገ ተስፋው ላይ ተጨባጭ አዎንታዊ ለውጥ መፍጠር ነው። ይህም 
በአመጋገባችን፣ በጤናችን፣ በአለባበሳችን፣ በምናገኘው ትምህርት መጠንና ጥራት፣ በሚሰማን የራስ መተማመን ስሜት፣ 
በምናገኘው ፍትሃዊ ዳኝነት፣ በማኅበረሰቡ ባለው የመግባባት መጠን፣ በሚሰማን የነፃነት ስሜት ... ወዘተ መገለፅ 
አለበት። በመጨረሻም የልማት ዋነኛው ግብ የድሀውን ድህነት መቀነስ እንጂ ሀብታሙን ይበልጥ ሀብታም ማድረግ 
አይደለም። 
አሁን ወደ ትልቁ ጥያቄ እናምራ። የወያኔ መንግሥት ከላይ የተዘረዘሩትን የሚያደርግ መንግሥት ነው ወይ? 
3. ወያኔ እና ቀደምት መንግሥታት ከልማት አንፃር
የወያኔዎች ካድሬዎች ራሳቸውን ጻድቅ ለማስመሰል የቀደሙትን መንግሥታት መኮነን ይወዳሉ። እነሱ ሥልጣን እስከያዙ 
ድረስ በአገሪቷ ውስጥ አንዳችም ነገር ያልተሠራ አስመስለው ይናገራሉ። አገሪቷ መንቀሳቀስ የጀመረችው በእነሱ 
አስተዳደር እንደሆነ በድፍረት ያወራሉ። እውነታው ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነው። 
ከ1983 እስከ 1993 ያሉት 10 ዓመታት ወያኔ የቤተመንግሥትን ኑሮ በመለማመድ ላይ ስለነበር ስለልማት እውቀቱም 
ደንታውም አልነበረው። ከህወሓት መሰንጠቅ በኋላ አሸናፊው ወገን ቤተመንግሥት የመቆያ ምክንያት ሲፈልግ 
“ልማትን” አገኘ። በ1997 ደግሞ ከ1993ቱ የባሰ ክስተት ተፈጠረ - ምርጫ 97! ወያኔ ሕዝብን ማማለያ መሣሪያ ካላገኘ 
ሥልጣኑ አደጋ ላይ መሆኑ በተጨባጭ ተገነዘበ። አሁንም “ልማት” ለዚህ ሥራ ታጨ። ከምርጫ 97 ማግሥት ጀምሮ 
“ልማት” የወያኔ ዋነኛ የሥልጣን መከላከያ ምሽግ ሆነ። 
እንደ አጋጣሚም ጊዜው ዓለም ዓቀፍ ሁኔታዎች ለአፍሪቃ የተመቹበት ሆነ። እንዲያውም ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን 
(ከአውሮፓውያን 2000 ወዲህ) “የአፍሪቃ ጊዜ” እየተባለ ይጠራል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ አገሮች 
በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ነው። ቻይና ለጥሬ እቃ አቅርቦትና ገበያ ፍለጋ የአፍሪቃ ሸሪክ ሆነች። በአውሮፓና አሜሪካ 
በደረሰው የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት ሕንድን ጨምሮ አዳዲሶቹ አዳጊ አገሮች፣ ዓለም ዓቀፍ ኮርፓሬሽኖች እና ግለሰብ 
ባለሀብቶች ወደ አፍሪቃ ለመመልከት ተገደዱ። አፍሪቃ ትኩረት እየሳበች መጣች። ከዚህ በተጨማሪም ለጋሽ አገሮች 
ወያኔን የሚደግፉበት “ፀረ-ሽብር ጦርነት” የሚባል ድሮ ያልነበረ አዲስ ምክንያት ተፈጠረ። እነዚህ ሁሉ መልካም 
ነገሮች ለወያኔ ተሰብስበውለት መጡ። ወያኔ ግን አልተጠቀመባቸውም። በእንዲህ ዓይነቱ ምቹ ወቅት ብዙ መሠራት 
ሲኖርበት ባለመሥራቱ በመጠየቅ ፋንታ የሠራቸው ጥቂት ነገሮችን እያጋነነ በማውራት ሥራ ላይ ተጠምዷል። 

2
The scope of economic development includes the process and policies by which a nation improves the 
economic, political, and social well-being of its people.ibid 3 
ፕሮፖጋንዳውን ወደ ጎን ትተን ሀቁን ብንመረምር ወያኔ መሥራት ይችል የነበረው 1/100ኛ እንኳን ያልሠራ አንዳችም 
አዲስ የፕሮጀክት ሃሳብ ያላፈለቀ ድርጅት ነው። የአባይ ድልድይም ሆነ የአዲስ አበባ የከተማ ባቡር ፕሮጀክቶች ድሮ 
ታቅደው የነበሩ ናቸው። የወያኔን ያህል እድሜ፣ የተመቻቹ አገራዊና ዓለም ዓቀፍ ሁኔታ እና በየዓመቱ ከሶስት ቢሊዮን 
የአሜሪካ ዶላር ያላነሰ እርዳታ አግኝተው ቢሆን ኖሮ የቀድሞዎቹ ሥርዓቶች ከወያኔ የተሻለ ውጤት ያስመዘግቡ 
እንደነበር በበኩሌ ጥርጥር የለኝም። 
ይህ እምነት ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። አቅሜ በተቻለው መጠን ሶስቱንም ሥርዓቶች ለማጥናትና ለማወዳደር 
ሞክሬዓለሁ። በተለይም የሚከተሉትን ሶስቱን አስርት ዓመታትን ለማወዳደር ጥረት አድርጌዓለሁ። 
1ኛ. ከ1955 – 1965 የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ዘመን፣ 
2ኛ. ከ1970 – 1980 የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ፕሬዚዳንትነት ዘመን፣ እና
3ኛ. ከ1990 – 2000 የመለስ ዜናዊ የጠቅላይ ሚኒስትነርነት ዘመን 
እኔ እነዚህን ሶስቱን አስርት ዓመታትን አወዳድሬ የደረስኩበት ሀቅ ባጭሩ የሚከተለው ነው። 
በ1950ዎቹ መጨረሻ ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ላይ እንደነበረች የወቅቱ አቢይ ዜና ነበር። በእርግጥም ኢትዮጵያ በአየር 
ትራንስፓርት፣ በባህር ትራስፓርት፣ በዘመናዊ የመንግሥት አወቃቀር (ዘመን ተሻጋሪዎቹ የወንጀለኛ መቅጫ ህግና 
የመንግሥት ሠራተኛች አስተዳደር ደንብን ያስታውሷል)፣ በከተሞች ግንባታ (አዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ አዋሳ ...) ፈጣን 
እድገት የታየበት ጊዜ ነበር። አዲስ ዘመንና መሰል የመንግሥት ሚዲያዎች እነዚህን እያጋነኑ ይዘግቡ ነበር። 
በ1970ዎቹ የመንግሥቱ ኃይለማርያም አገዛዝም ኢትዮጵያ በአንዳንድ መስኮች መሻሻል ያሳየችበት ነበር። ለምሳሌ 
በመሠረተ-ትምህርት፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በመንግሥት እርሻዎች፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎችና ድልድዮች ግንባታ 
ረገድ የተወሰኑ መሻሻሎች ታይተዋል። የወቅቱ የመንግሥት ሚዲያዎች እነዚህን በጣም እያጋነኑ አገሪቷ በፈጣን እድገት 
ላይ እንዳለች አድርገው ይዘግቡ ነበር። 
በ1990 ዎቹ - በመለስ ዜናዊ ጊዜ - መንገዶችና ሕንፃዎች ተገንብተዋል። ት/ቤቶችና ክሊኒኮችም በተወሰነ መጠን 
ተገንብተዋል። የመንግሥት ሚዲያዎች እነዚህን እጅግ በጣም እያጋነኑ ማውራቱን ተያይዘውታል። 
በሶስቱም ጊዜዓት የተወሰኑ ለውጦች ነበሩ። በእነዚህ ጊዜዓት ውስጥ ያለው ትልቁ ለውጥ ግን የመንግሥት ሚዲያዎች 
ስኬትን አጋኖ በማውራት “ብቃት” ላይ የታየው ለውጥ ነው። የመንግሥታትን ስኬት አጋኖ በማውራት ብቃት ላይ 
የታየውን ያህል ፈጣን እድገት በየትኛውም መስክ አልታየም። 
ለማስረጃ ያህል ግብርናን ላንሳ። በአክሊሉ ሀብተወልድ አስተዳደር የኢትዮጵያ ግብርናን ለማዘመን የግብርና ኤክስቴሽን 
ፕሮግራም ተነድፎ በሥራ ላይ ውሎ ተዓምራዊ የተባለ ውጤት የተገኘበት ጊዜ ነበር። በተለይም የ60ዎቹ መጀመሪያ 
ዘመናዊ ግብርና በከፍተኛ ፍጥነት ያደገበት ጊዜ ነበር። የጭላሎ፣ የአርሲ፣ የወላይታ፣ የሰቲትና የሁመራ እርሻ ልማት 
ፕሮጀክቶች ዝና እስከዛሬም በባለሙያዎች ይታወሳል። 4 
በመንግሥቱ ኃይለማርያም የአገዛዝ ዘመን “መሬት ላራሹ” ተሰጥቶ፤ ገበሬውም በኅበረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅቶ 
በሶሻሊስታዊ የግብርና ፓሊሲ በመመራት ገጠሩ ወደ ከተማ ሊቀየር ደረሰ የተባለበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ በሺህ 
የሚቆጠሩ የገበሬዎች ማኅበራትና ከ200 በላይ ዩኒየኖች ነበሩ። ማልባ፣ ወልባ፣ ወላንድ የተሰኙ የዩኒየን እርከኖች 
ወጥተው ነበር። የየትኖራ የገበሬዎች የኅበረት ሥራ ማኅበርን የመሰሉ ሞዴልም ማኅበራት የወቅቱን ዜና አጣበውት 
ነበር። 
በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ዘመን ደግሞ የግብርና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እንደ አዲስ ተቀሰቀሰ። የወያኔ ካድሬዎች የግብርና 
ኤክስቴንሽን እነሱ የፈለሰፉት አዲስ ግኝት እንደሆነ አድርገው መስበክ ጀመሩ። አንዳችም የተለየ ቴክኖሎጂ ሆነ የእርሻ 
መሬት ስፋት ለውጥ ሳይኖር “ኤክስቴንሽን” በሚባል አስማት “ከድህነት ወጥተን ሚሊየነሮች ሆን” ብለው በቴሌቪዥን 
የሚናገሩ ሰዎች ተገኙ። 
እያደር ውሸት መረን አጣ። ኢቲቪን አምስት ቦታ ከፋፍሎ አምስት የቴሌቪዥን አገልግሎቶችን ከፈትኩ ማለት፤ የአዲስ 
አበባ ዩኒቨርስቲ ፋካልቲዎችን ዩኒቨርስቲ ብሎ በመሰየም የዩኒቨርስቲዎችን ቁጥር በሮኬት ፍጥነት አሳደግኩ ብሎ 
ማውራት የተቻለበት ዘመን ላይ ደረስን። 
4... ለምን በቁጥሮች አንናገርም? 
የወያኔ ካድሬዎች ስለ ልማት በቁጥር እና በምጣኔ (ፕርሰንት) ማውራት ይወዳሉ። ምርት በዚህን ያህል፤ አገልግሎት 
ደግሞ በዚህ መጠን አደገ ይሉናል። እነሱ የሚሉትን ለመቀበል ካቅማሙ “ባለሙያ ከሆንክ የቁጥር ማስረጃ አምጣ” 
ይላሉ። እውነት ነው ባለሙያ በማስረጃ መናገር አለበት - ማስረጃው ካለ። ሆኖም ግን ማስረጃ የለም። በአንድ በኩል 
እነሱ የሚጠቀሟቸው ቁጥሮች “በኢንኩቤተር የተፈለፈሉ” ቁጥሮች ናቸው። አንድ የነበረው ዩኒቨርስቲ 32 አደረስነው 
ሲባል ተዓምራዊ ይመስላል። ከእነዚህ ውስጥ 14ቱ የራሱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አካላት የነበሩ ሌሎቹ ደግሞ እንኳንስ 
ዩኒቨርስቲ “ኮሌጅ” ብሎ ለመጥራትም የሚያሳፍሩ መሆናቸው ቁጥሮች አይናገሩም። በጉራ የሚጠሯቸው ቁጥሮች 
የክሊኒኮች መብዛት ይነግረናል እንጂ ከዛሬው 10 የድሮዉ 1 የተሻለ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር አይነግሩንም። ይህ 
ያህል የኮንዶሚየም ቤቶች ተገነቡ ሲባል አንዳንዶቹ ከአሁኑ መፈራረስ መጀመራቸው ቁጥሮቹ ውስጥ አንዳችም ፍንጭ 
የለም። ቁጥሮች ብዛትን እንጂ ጥራትን አይናገሩም። 
በሌላ በኩል ደግሞ በቁጥሮቹም ላይ ከፍተኛ ችግር አለብን። የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መረጃዎችን እንዲሰበስብልን 
የተቋቋመው መሥሪያ ቤት - የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ጽ/ቤት - “የቁጥሮች መቀቀያ ቶፋ” የሚል ስም 
ወጥቶለታል። እንኳንስ ሌላ እኛን - ራሳችን - ቆጥሮ ስንት እንደሆንን ሊነግረን ያልቻለ መሥሪያ ቤት ነው። በአዲስ 
አበባ እና በአማራ የሕዝብ ብዛት ላይ የተነሳውን ክርክር ልብ ይሏል። ሰውን መቁጠር ያልቻለ መሥሪያ ቤት ምርቶችንና 
ምርታማነትን እንዴት ችሎ ይቆጥራል ብለን እናምናለን። 
ይህም ሆኖ ከግብርና ሚኒስቴር የምታገኙት የግብርና ምርት ዳታ ከስታትስቲክስ ጽ/ቤት ከምታገኙት በ20% ያህል 
የሚበልጥባቸው ጊዜዓት አሉ። በትምህርቱም በጤናውም ረገድ እንደዚሁ ነው። ሁሌም የሴክተር መሥሪያ ቤቶች 
የሚያወጧቸው ቁጥሮች የስታትስቲክ ጽ/ቤትም ከሚያወጣቸው የባሰ የተበላሹ ናቸው። ፓሊሲ የሚያስፈጽሙት 5 
ደግሞ የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ናቸው። ወያኔ የሚያስፈጽመው ፓሊሲ ካለው የሚያስፈጽመው በተሳሳተ መረጃ ላይ 
ተመሥርቶ ነው ማለት ነው። 
በአንድ ሥልጠና ወቅት የአዲስ አበባ አንድ ክፍለ ከተማ የጤና ቢሮ ኃላፊ “የዳታ ቅቀላ ልምዱን” እንደሚከተለው 
አወጋን። 
ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቴ በፊት በክልል የዞን የጤና ቢሮ ኃላፊ ነበርኩ። ከወረዳዎች የሚመጡልኝ 
ዳታዎች በጣም የተጋነኑ እንደሆነ ባውቅም ምርጫ ስለሌለኝ አሳልፋቸው ነበር። አንዱን ግን ለማሳለፍ 
በጣም ተቸገርኩ፤ ምክንያቱም ክትባት ተደርጎላቸዋል ተብሎ የቀረበው ከ6 ዓመት በታች ሕፃናት ቁጥር 
ከወረዳው ጠቅላላ ሕዝብ ብዛት ይበልጣል። በጣም አስጨነቀኝ ግን “ብናገር ራሴን ከማስጠመድ ወዲያ 
ምን ለውጥ አመጣለሁ” ብዬ ወደ ላይ ላኩት። 
በጉዳዩ ላይ ብዙ ተነጋገርንበት። መፍትሔ ግን አላገኘንለትም። “እዚህስ እንዲህ ነገር የለም?” የሚል ደፋር ጥያቄ
አነሳሁ። “በዚህ ጉዳይ ላይ መተባበር ያለተፃፈ Job Description ናችን ነው” የሚል ኪነጥበባዊ ምላሽ ሲሰጠኝ
የውይይቴን አርዕስት ቀየርኩ። በዚህ አጋጣሚ ለዚያ ወዳጄና ሌሎቹም ግልጽነት በጣም አመሰግናለሁ። ለኔ ግን ይህ
ብቸኛ አጋጣሚ አልነበረም። በመምህርነቴ፣ በአጫጭር ስልጠናዎች ሰጪነቴ፣ አንዳንዴም እራሴ በተሳተፍኩባቸው
ምርምር ነክ ሥራዎች ምክንያት በርካታ ዳታ ሰብሳቢዎችን፣ አጠናቃሪዎችንና ተርጓሚዎችን የማወቅ አጋጣሚዎች
ነበሩኝ፤ አሁንም አሉኝ።
ሶስት ሁነን የአንድ ተማሪን የማስተርስ የመመረቂያ ጽሁፍ ለመመዘን ተሰይመናል። ተማሪው በንድፈ ሃሳብ
ጥሩ ቢሆንም የተጠቀመበት ዳታ ስህተት የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ አድርሶታል። “እንዴት ይህንን
የማይመስል ዳታ ይዘህ ትነሳለህ?” ተማሪው ተጠየቀ።
“ምርጫ አልነበረኝም። ቁጥሮችን የሰጠኝ የቀበሌው ዲኤ (DA – Development Agent) ነው።
የዩኒቨርስቲው የትብብር ደብዳቤ አሳይቼም ራሴ መረጃ እንድሰበስብ ወረዳው አልፈቀደልኝም” ተማሪው
መለሰ።
“አትቸገር፤ ይኸ ግልጽ ነው። ለዲኤዎች ከምርጫ ድምጽ ጀምሮ የሚቆጠር ነገር ሁሉ መጭበርበር
አለበት” ሲል አንዱ መምህር አጉመተመተ።
በራሴ ወጪ ዳታ ልሰብስብ ቢሉ እንኳን ቢሮክራሲው አያፈናፍኖትም። ዲኤኦች ጫት ቤት ወይም ካቲካላ ቤት ቁጭ
ብለው የሞሏቸውን “ልማታዊ’” ዳታዎች ይሰጥዎታል።
ከክልል ማስረጃ ልጨምር። የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኦመር በአንድ ስብሰባ በቴሌቪዥን
ካሜራ እየተቀዱ የሚከተለው አስደናቂ ንግግር አደረጉ። 6
ልብ በሉ። በጣም እንዳደግን ጥሩ ደረጃ ላይ እንደረስን ነበር በየጊዜው ሪፖርት የሚቀርበው። ይህ ግን
ፍጹም ትክክል አይደለም፤ ውሸት ነው። ይህ አሁን የያዝኩት ሪፖርት ምን ያህል እውነት እንደሆነ
እርግጠኞች አይደለንም። ከዚህ በፊት ይቀርቡ የነበሩ ሪፓርቶችም እንዲሁ ናቸው። ግምገማ ለማለፍ
ተብሎ በውሸት የተሞሉ ሪፖርቶች ናቸው የሚቀርቡት። ምሳሌ ልስጣችሁ። አስር ሚሊዮን እንስሳት
እንደተከተቡ ተደርጎ ሪፖርት ቀርቧል። የግብርና ኃላፊው ሪፖርቱ ትክክል ነው ብሎ መማል አይችልም።
ሕዝቡ ይህ ሁሉ ሲከተብ አያይም ወይ? እንኳን አስር ሚሊዮን አምስት መቶ ሺም አልተከተበም።
በአስር ሚሊዮን እና በአምስት መቶ ሺህ መካከል ያለው ልዩነት ይታያችሁ!!! ይህ በጉባዬ የተናገሩት ነው3
። ይህ ንግግር
ኤዲት ሳይደረግ የተቀዳበት ቪዲዮ ከዚህም የባሰ ሚስጢራዊ ንግግር እንደያዘ ከቁጥጥራቸው ወጥቶ መበተኑ ለአቶ
አብዲ መሐመድ ኦመር ሥልጣናቸው ማጣት ተጨማሪ ምክንያት ሆኖባቸዋል። እንዲህ ዓይነት ነገር የሚሰማው
ከሶማሊ ክልል ብቻ አይደለም።
የአፋር ክልላዊ መንግሥትም በአንድ ወቅት አምስት ሚሊዮን ሕፃናት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ
እንደሆነ በክልላዊ መንግሥት ድረ-ገጽ ላይ አውጥቶ ጩኸት ሲበዛበት እንዳነሳው ይወራል። የሚገርመው በዚሁ ድረገጽ
የአፋር ክልል ሕዝብ ብዛት 3 ሚሊዮን አካባቢ እንደሆነ መገለፁ ነው። የሁሉም ክልሎች ዳታዎች በአንድ ወይም በሌላ
መንገድ የሶማሊውን ይመስላሉ።
የፌደራል መንግሥቱ ዳታዎች ችግር አለባቸው። የክልሎች ዳታዎች ደግሞ ከፌደራሎቹ የባሰ ችግር አሉባቸው። እናም
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የቅቅል ዳታዎች ክምር ተሸክሞ” ስለፈጣን ልማት ይደሰኩራል።
የስታትስቲክስ ጽ/ቤት ከሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር “ዳታ የማጣጣም” ሥራ ከጀመረ ወዲህ ልዩነቶች ጠበዋል። አሁን
የምናገናገኛቸው የስታትስቲክስ መረጃዎች በድርድር የተደረሰባቸው ቁጥሮች ናቸው።
“ዳታ የማጣጣም” ልምድ የተገኘው ደግሞ ከዓለም ባንክ ነው። የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀርብለት
የተጋነነ ዳታ ለመቀበል ሲቸገር ሶስት፣ አራት ሰዎችን አዲስ አበባ ይልክና በቁጥሮች ላይ ይደራደራል። ሁለቱም
ተደራዳሪዎች የየራሳቸው ግብ አላቸው። የመንግሥት ተደራዳሪዎች ለምን እንደሆነ አላውቅም ቁጥሮቹ ተደማምረው
የዓመቱን እድገት 11 % አካባቢ እንዲሆንላቸው ይጥራሉ። የዓለም ባንክ ሰዎች ደግሞ ለተጨማሪ ፈንድ ከ 4 - 8%
ይበቃቸዋል። በድርድር የፀደቁ ቁጥሮች የዓለም ባንክ ዳታ ሆነው ይቀርባለሁ። የወያኔ ካድሬዎች እነሱን እየጠሩ እኛ
ላይ ይዘባነናሉ።
ይህ ድራማ ቢመስልም እውነትም ነው። የድርድር ዳታ ጥቅምን የተረዱ የወያኔ “ምሁራን” እንዲህ ዓይነቱ ድርድር
በማዕከላዊ ስታትስቲክስና በሴክተር መሥሪያ ቤቶች መካከል እንዲካሄድ አድርገው አንድ ወጥ ዳታ “ለመፈብረክ”
እየጣሩ ነው። “ሥራው” ተጀምሯል ግን እንደ ዓለም ባንኩ የተሳለጠ አይደለም።
ይህንን አርዕስት በሚቀጥለው ቀልድ ልቋጨውና ወደሌሎች ጉዳዮች ልለፍ
3
. ለተጨማሪ መረጃ: https://www.youtube.com/watch?v=B-qttD_Z4jA&feature=youtube_gdata_player7
የመንግሥት የኢኮኖሚ አማካሪዎች ለሽርሽር ወጥተው መንገድ ጠፋቸው። ከፊሉ በግራ ሌላው
በቀኝ በኩል እንሂድ እያሉ እርስ በርሳቸው ተጨቃጨቁ። አለቃቸው ዋናው ኢኮኖሚስት
ትዕግስቱ አልቆ በቁጣ “እስኪ ካርታውን ወዲህ በል” ብሎ ጮከ። ካርታውን ተቀብሎ መሬት ላይ
ዘርግቶ በጥንቃቄ አጠናው። ቀና እያለም የአካባቢውን መልክዓ ምድር ከካርታው ጋር አገናዘበ።
በእንዲህ ዓይነት ጥልቅ ጥናት ዘለግ ያለ ጊዜ ከወሰደ በኋላ በድል አድራጊነት ስሜት ከፈካ
ፈገግታ ጋር “አሁን የት እንዳለን በትክክል ደርሼበታለሁ” ሲል የጥናቱን ውጤት ለባልደረቦቹ
አስታወቀ።
“አሁን የት እንዳለን በትክክል ደርሼበታለሁ!!! ይታያችኋል!? እዚያ ማዶ ያለው ተራራ!!!”
ሁሉም ወደ ወደ ተራራው አሻግረው ተመለከቱ፤ በአዎንታም አንገቶቻቸውን ነቀነቁ። “አሁን
ሁላችንም ያለነው እዚያ ተራራው አናት ላይ ነው” አለ ይባላል።
የወያኔ ኢኮኖሚስቶች ራሳቸው የፈጠሯቸው ቁጥሮች ከዓለም ባንክ ሲሰሟቸው የሚሰማቸው ፈንጠዚያ ሁሌ
ይገርመኛል። አንዳንዶቹ ቁጥሮቹ ትክክለኛ ናቸው ብለው የምር ከልባቸው የሚያምኑ ይመስሉኛል፤ እናም ከራሱ በላይ
ካርታውን ለዚያውም የተሳሳተ ንባብ አምኖ “እዚያ ማዶ ተራራ አናት ላይ ነው ያለሁት” ያለውን የቀልዱን ኢኮኖሚስት
ያስታወሱኛል።
5... ዘወርዋራ መለኪያዎችና መለኪያዎችና መለኪያዎችና ውጤቶቻቸው
በወያኔ መንግሥት ሥር ያሉ መሥሪያ ቤቶች የሚያወጣቸው የስታትስቲክስ መረጃዎች ላይ እምነት የለንም ማለት
ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም ማለት አይደለም። ወያኔ የፊት ለፊት መንገድ ሲዘጋብን በጓሮ በር ገብተን ጓዳችንን
መቃኘት አለብን። አንዳንዱን እንመልከት
5.1..... ድህነት
የወያኔ ቁጥሮች የሚሉትን ተቀብለን ካሰላን አትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ድህነትን አሸንፋ መካከለኛ ገቢ ካላቸው
አገሮች ተርታ ትገባለች። እንዲህ ዓይነቱ መደምደሚያ ላይ የምንደርሰው ግን መንግሥት “ሰጠሁ፣ አመረትኩ”
የሚለውን መረጃ እውነት አድርገን ስንቀበል ነው።
መንግሥት “አመረትኩ፣ ሰጠሁ፣ ...” በሚለው ፋንታ ሕዝብ የተቀበለውን ብንለካስ ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ
እንደርሳለን? በጭራሽ!!! እውነት በተከበረበት አገር አንድ ነገር በሰጪው በኩል ተለካ በተቀባዩ ለውጥ የለውም።
ሰጪው ውሸታም በሆነበት አገር ግን ተቀባዩን መጠየቅ ነው የሚሻለው። ልዩነቱ የሰጪው የውሸታምነት መጠን
መለኪያ ሊሆን ይችላል። 8
ኢትዮጵያ አገራችን ውስጥ የሰፈነውን የድህነት መጠን ለማወቅ እግረ መንገዱንም የወያኔ የውሸት መጠን ለመታዘብ
Multidimensional Poverty Index የሚባለው ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ ውጤትን መመልከት ይበቃል4

ድህነት ዘርፈ ብዙ ነው። ድህነት በምግብ እጦት፣ በትምህርት አገልግሎት እጦት፣ በጤና አገልግሎት እጦት፣ በማገዶ
እጦት፣ ... ወዘተ ይገለፃል። ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ እንዲህ ሰፋ ያለ የድህነት ትርጓሜን ይዞ የሚነሳ ሲሆን
በመረጃነት የሚጠቀመው መንግሥት አመረትኩ የሚለውም ሳይሆን ዜጎች በተጠቀሙት ምርትና አገልግሎት መጠን
ነው። የ2013 እ.አ.አ ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ የመጨረሻ አስር አገሮች ውጤት በአጭሩ በዚህ በታች በሰንጠረዥ
ቀርባል።
Country
Multidimensional poverty
Population in
severe poverty
(with intensity
higher than
50%)
Multidimensional
Poverty Index
(MPI = H*A)
Headcount ratio:
Population in
multidimensional poverty
(H)
Intensity of
deprivation
among the poor
(A)
Range 0 to 1 % Population
Average % of
weighted
deprivations
% Population
Sierra Leone 0.439 77.0 57.0 53.2
Liberia 0.485 83.9 57.7 57.5
Guinea 0.506 82.5 61.3 62.3
Mozambique 0.512 79.3 64.6 60.7
Somalia 0.514 81.2 63.3 65.6
Burundi 0.530 84.5 62.7 61.9
Burkina Faso 0.535 84.0 63.7 65.7
Mali 0.558 86.6 64.4 68.4
Ethiopia 0.564 87.3 64.6 71.1
Niger 0.642 92.4 69.4 81.8
ዘገባው እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ አገራችን አስከፊ ድህነት የተንሰራፋባት፤ በዓለም ሁለተኛዋ የመጨረሻ ድሃ አገር
ናት። በድህነት ከኢትዮጵያ የባሰች አገር ኒጀር ብቻ ነች። ጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ብቻ ሳይሆን ሶማሊያ እንኳ ከእኛ
ትሻላለች። በአገራችን 71 በመቶ ሕዝብ በአስከፊ ዘርፈ ብዙ ድህነት ውስጥ እየማቀቀ ነው።
ይህ መረጃ ወያኔ አመጣሁ ከሚለው ልማት ጋር ፈጽሞ የሚሄድ አይደለም። የልዩነቱ ምክንያት የወያኔ ውሸታምነት
ነው። ጥቂት የወያኔ ሹማምንት በከተሞች ውስጥ ድንቅ ፎቆችን ስለገነቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አልፎለታል ማለት
አይደለም። ከእነዚህ ፎቆች የሚወጣ ፍርፋሪ እንኳን ማግኘት እያቃተው በረሃብ በየእለቱ ሕይወቱ የሚያልፈው
ምስኪን ድሃ ቁጥሩ እጅግ ብዙ ነው።
4
 ሙሉው ሪፓርት http://www.ophi.org.uk/multidimensional-poverty-index/mpi-2013/ accessed 31/08/2013 9
ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ የድህንነት መንስኤ በመጠቆምም ረገድ የሚለው ነገር አለ። ከዚህ በታች ባለው ሰንጠረዥ
እንደሚታየው። ለኢትዮጵያውያን ድህነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረገው የኑሮ ደረጃ ማሽቆልቆል ነው። ይህም
በእጥረቶች ማለትም በምግብ እህል እጥረት፣ በኃይል እጥረት፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል
እጥረት .. ወዘተ ይገለፃል። የድህነታችን ግማሹ ያህል (46.5%) እነዚህ የእለት ተእለት ኑሮ ጋር በተቀጥታ የተገናኙ
ነገሮች በማጣት ምክንያት የመጣ ነው። ለድህነታችን በሁለተኛ ደረጃ አስተዋጽዖ ያደረገው የጤና አገልግሎት እጥረት
ነው። የተጓደለ የጤና አገልግሎት ለድህነታችን 28% ያህል አስተዋጽዖ አድርጓል። የተጓደለ ትምህርት ደግሞ 27%
አስተዋጽዖ አድርጓል። ወያኔ የትምህርትና የጤና አገልግሎት እያስፋፋሁ ነው በሚለው ፍጥነት ድህነት እየቀነሰ
አይደለም። ለምን? ከሚከተሉት ከሁለት አንዱ አሊያም ሁለቱም እውነት መሆን አለባቸው። ሀ) የወያኔ ሥርዓት
ለዜጎቹ የሚሰጠው ትምህርትና የጤና አግልግሎት ዓይነት ዜጎችን ሠራተኛ አድርጎ ከድህነት የሚያወጣቸው አይደለም፤
ወይም ለ) የወያኔ ሥርዓት ለዜጎች የትምህርትና የጤና አገልግሎች አስፋፋሁ የሚለው ውሸት ነው።
Country
Multidimensional
Poverty Index
(MPI)
Percentage contribution of
deprivations of each dimension to
overall poverty…
Education Health Living
standards
% Cont. % Cont. % Con.
Sierra Leone 0.439 31.5 19.3 49.2
Liberia 0.485 29.7 25.0 45.3
Guinea 0.506 35.5 23.0 41.5
Mozambique 0.512 23.9 36.2 39.9
Somalia 0.514 34.2 18.6 47.2
Burundi 0.530 31.5 22.4 46.1
Burkina Faso 0.535 36.2 27.9 35.9
Mali 0.558 34.5 26.2 39.3
Ethiopia 0.564 25.9 27.6 46.5
Niger 0.642 35.4 21.5 43.2
5.2. የተጨቆነ ኢኮኖሚ
በልማትና በኢኮኖሚ ነፃነት መካከል ቀጥተኛ ትስስር አለ። ይህንን ትስስር የፓለቲካ ነፃነትና የኢኮኖሚ ልማት ትስስር
የላቸውም የሚሉ አምባገነኖች እንኳን ይቀበሉታል። የኢኮኖሚ ነፃነት ሳይኖር የኢኮኖሚ ልማት የሚታሰብ አይደለም።
ሄሪተጅ ፋውንዴሽን በየዓመቱ በዓለም ላይ ያሉ የ183 አገሮችን ኢኮኖሚዎችን በጥልቀት በመመርመር የቱን ያህል ነፃ
መሆናቸውን ይለካል። ይህ መለኪያ የኢኮኖሚ ነፃነትን በአስር የነፃነት አይነቶች ከፋፍሎ ይገመግማል። እነዚህም ሀ)
የቢዝነስ ነፃነት፣ ለ) የኢንቬስትመንት ነፃነት፣ ሐ) የንግድ ነፃነት፣ መ) የበጀት ነፃነት፣ ሠ) የፋይናንስ ነፃነት፣ ረ) የንብረት
ነፃነት፣ ሰ) የመንግሥት ወጪ፣ ሸ) ከሙስና ነፃ መሆን፣ ቀ) የገንዘብ ነፃነት፣ እና በ) የሥራ ነፃነት ናቸው። 10
በያዝነው የአውሮፓውያን 2013 ከዓለም ከሁሉም የተሻለ ነፃ ኢኮኖሚ ያላት አገር ሆንግ ኮንግ ስትሆን ያገነችው
አጠቃላይ ነጥብ 89.3 ከመቶ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ 49.4 አጠቃላይ ነጥብ በማምጣት 146ኛ ደረጃ ይዛለች። ይህ
አጠቃላይ ውጤት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ “የተጨቆኑ” (repressed) ከሚባሉ ጋር አስመድቦታል5

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ነፃነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን በየዓመቱ በመሻሻል ፋንታ እየባሰበት የመጣ ነው። ከጥቂት ዓመታት
በፊት ከነበረበት “ባብዛኛው ነፃ ያልሆኑ” (mostly unfree) ምድብ ወደ የተጨቆኑ ምድብ የዘቀጠ ኢኮኖሚ ነው።
ለንጽጽር እንዲረዳን ከአፍሪቃ ቡርኪና ፋሶ በ59.9 ነጥብ 86ኛ፣ ሴኔጋል በ55.5 ነጥብ 87ኛ፣ ማላዊ በ55.3 ነጥብ
89ኛ፣ ናይጄሪያ በ55.1 ነጥብ 91ኛ፣ ጋምቢያ በ58.8 ነጥብ 122ኛ፣ ዛምቢያ በ58.7 ነጥብ 123ኛ፣ .... እያለ ይቀጥላል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ አገሮች የምትሻልበትን ነገር ፈልጎ ማግኘት የተሳነበት ጊዜ ላይ ነን።
5.3. ጭንጋፍ መንግሥት
ልማታዊ መንግሥት ለመባል በመጀመሪያ መንግሥት መሆን ይገባል። አንዳንድ መንግሥታት ቢኖሩም አሉ ለመባል
በማያስደፍር ሁኔታ ላይ ናቸው። እንዲህ ዓይነቶቹ መንግሥታት “የጨነገፉ መንግሥታት” (Faild States) የሚባል
መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል።
የውጭ ፓሊሲና የሰላም ፈንድ የዓለም አገሮች መንግሥታትን ድክመቶች በአስር ዋና ዋና መመዘኛዎች ይለካል።
እነዚህም ሀ) ፈጣን የሕዝብ ብዛት የሚፈጥረው ውጥረት፣ ለ) የሕዝብ ከመኖሪያ ቦታው መፈናቀል፣ ሐ) የቡድኖች
(የማኅበረሰብ) በሥርዓቱ መማረር፣ መ) ስደት፣ ሠ) አድልዖዓዊ የሆነ ልማት፣ ረ) የኢኮኖሚ ድቀት፣ ሰ) የመንግሥት
በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማጣት፣ ሸ) የመንግሥት አገልግሎት አናሳነት፣ ቀ) የፀጥታ ኃይሎች ብቃት ማነስ፣ በ)
የፓለቲካ ልሂቃን የእርስ በርስ መቆራቆስ፣ እና ተ) የውጭ ጣልቃ ገብነት ናቸው።
እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም (2013 እአአ) በጨነገፉ መንግሥታት መለኪያ ዓለምን የምትመራው ጎረቤታችን
ሶማሊያ ስትሆን ያገኘችው አጠቃላይ ነጥብ 113.9 ነው። ኢትዮጵያ በ98.9 አጠቃላይ ነጥብ 19ኛ ደረጃ ይዛ በቅርብ
ርቀት ትከተላታለች6
። ለማነፃፀር ያህል ብሩንዲ፣ ዩጋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ኤርትራ፣ ካሜሮን፣ ማውሪታኒያ፣ ሴራሊዮን ፣
ቡርኪና ፋሶ፣ ኮንጎ፣ማሊ፣ ሩዋንዳ፣ ማላዊ፣ ቶጎ፣ አንጎላ፣ ... ዝርዝሩ ብዙ ስለሆነ እዚሁ ላብቃ ... እነዚህ ሁሉ አገሮች
ከኢትዮጵያ የተሻለ አስተማማኝ መንግሥት አላቸው።
ኢትዮጵያ ከዓመት ዓመት ያመጣችው መሻሻል ይኖር እንደሆን ለማጣራትያለፉትን ተከታታይ ዓመታት ውጤት
ብናስተያይ በወያኔ መዳፍ ውስጥ ያለችው አገራችን በመሻሻል ፋንታ እየባሰባት እንደሆነ እናያለን። ወያኔ “ልማት፣
ሰላምና መረጋጋት” ፈጠርኩ ብሎ የሚመፃደቅባት ኢትዮጵያ በመውደቅ ላይ ካሉ መንግሥታት አንዷ ነች። ኢትዮጵያ
ውስጥ እንኳንስ ልማታዊ መንግሥት ተረጋግቶ የቆመ “መንግሥት” ለመባል የሚበቃ ተቋምም የለም።
5.4. በአፍሪቃ የመልካም አስተዳደር መለኪያ
5
. በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ይህንን ይጎብኙ። http://www.heritage.org/index/ accessed 31/08/2013
6
. ለተጨማሪ መረጃ http://ffp.statesindex.org/rankings-2013-sortable accessed 31/08/2013 11
የልማት አቢይ ገጽታዎች አንዱ መልካም አስተዳደር (Good Governance) ነው።
በአሁኑ ሰዓት በአፍሪቃ አገራት ላይ ያተኮረ በገለልተኛነቱና በጥራቱ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው የሞይ ኢብራሂም
የአፍሪቃ የመልካም አስተዳደር መለኪያ ነው። ይህ መለኪያ አምስት ዋና ዋና መመዘኛዎች አሉት። እነዚህም ሀ)
ደህንነት እና የህግ የበላይነት፣ ለ) የሕዝብ ተሳትፎ እና የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ሐ) ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ
እድገት፣ እና መ) ሰዋዊ እድገት (human development) ናቸው።
በየአመቱ 53 የአፍሪካ አገሮች በእነዚህ መመዘኛዎች ይለካሉ። የዚህ ዓመት ውጤት ገና አልወጣም። እስካሁን ያለን
የመጨረሻው ውጤት የአምናው የ2012 እኤአ ነው። አምና 82.4 ከ100 በማምጣት ሞሪሰሽ አንደኛ ሆናለች። ሞሪሸስ፣
ኬፐቨርዲ፣ ሲሺሊስ፣ ቦትስዋናና ደቡብ አፍሪካ በመልካም አስተዳደር አፍሪካን በመምራት በተከታታይ ከ 1- 5 ደረጃ
ወጥተዋል። በወያኔ አገዛዝ ሥር ያለችው ኢትዮጵያ ግን 46,7 ከመቶ በማምጣት 33ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች7

ለማነፃፀር ያህል ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሴራሊዮን፣ ሩዋንዳ፣ ጅቡቲ .... በመልካም አስተዳደር ረገድ ከኢትዮጵያ በጣም በተሻለ
ሁኔታ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ብቻ የሚሰማ ሰው በመልካም አስተዳደር የወያኔን መንግሥት የሚያህል በዓለምም የሚገኝ
ላይመስለው ይችላል። መራሩ ሃቅ ግን ከላይ የተገለፀው ነው።
የወያኔ “ልማት” ባዶ ጥሩምባ መሆኑን ለማሳየት ሌሎችም ተናጠል ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። የአንዳንድ
ኩባንያዎች ጉራ በጣም የሚያናድድ ነው። የኢትዮቴሌኮም ተልዕኮ ያነበበ ሰው እሱን የሚያህል ለደንበኞቹ የሚጨነቅ፤
ለሀገር ልማት የሚለፋ ድርጅት በዓለምም ያለ ላይመስለው ይችላል። ሆኖም ኢትዮቴሌኮም እንደ ስለላ ተቋምነቱ ደህና
ይንቀሳቀስ እንደሆነ እንጃ እንደ አገልግሎት ሰጭነት ሲታይ ቀሽም ነው። የአፍሪቃ አማካይ የሞባይል ቴሌፎን ሽፋን
70% ሲሆን የኢትዮጵያ ግን ገና 25 % አልደረሰም። (በነገራችን ላይ የአፍሪቃንም አማካይ ወደ 70 ያወረደው
የኢትዮጵያ ኋላቀርነት ነው)። 40 በመቶ የሆኑት ኬኒያዊያን የኢንተርኔት አገልግሎት ሲያገኙ ለዚህ የታደሉት
ኢትዮጵያዊያን 2.5 % ብቻ ናቸው። በመብራት ኃይል ሥርጭት ረገድ ያለው ልዩነት ከዚህ ይብሳል። በትምህርትና
በጤና አገልግሎት ዘርፍም እየተሠራ ያለው የሚያሳዝን ነገር ነው።
6... “““ኤፈርት “ መር ካፒታሊዝም””””?
መንገዶች ይሠራሉ፤ የከተሞች ሕንፃዎች ይረዝማሉ ግን አብሮ ድህነት ይስፋፋል፤ ድንቁርና ይፋፋል፤ በሽታ ሕዝቡን
ይጨርሳል። ጥቂት ሰዎች ይከብራሉ፤ ሚሊዮኖች ይደኸያሉ። ጥቂት ሰዎች በ100 ሺህ ሄክታሮች የሚለካ ለም መሬት
የሊዝ ሰርቲፊኬት ይይዛሉ፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ድንች መትከያ ተከልክለው “ወደ አገራችሁ ሂዱ” ተብለው
ይፈናቀላሉ። ይህ ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ሥርዓት ነው?
አንድ ሰሞን መለስ ዜናዊ እና አዲሱ ለገሠ “ግብርና መር ካፕታሊዝም” ማለት ያበዙ ነበር። ግብርናን እየገደሉ ግብርና
መር ካፒታሊዝም ሊኖር አይችልም። “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ለራሳቸው ለተናጋሪዎቹ ግልጽ ያልሆነ ድሪቶ ነው።
7
. ለተጨማሪ መረጃ ይህንን ድረገጽ ይጎብኙ http://www.moibrahimfoundation.org/ accessed 31/08/2013 12
ወያኔ ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ሥርዓት እየገነባ እንደሆነ ጥሩ ፍንጭ የሰጠን ስብሃት ነጋ ነው። ስብሃት በተለያዩ ጊዜዓት
በሰጣቸው “የአቶ እንደልቡ” መግለጫዎች የድርጅታቸው የኢኮኖሚ ፓሊሲ ግብ ካፒታሊዝም መሆኑን፤ ይህ
ካፒታሊዝም የሚመራው በኤፈርት መሆኑ እና የካፒታሊስቱ መደብ ሲጎለብት ኢህአዴግ ስልጣኑን አስረክቦ
እንደሚከስም ተናግራል8
፡፡ “ኤፈርት-መር ካፒታሊዝም” ብዙዎችን እያደኸየ ጥቂት የወያኔ ጎጠኞ ገዢዎችን ግን በሃብት
እያንበሻበሸ በመገስገስ ላይ ነው።
ለመሆኑ ኤፈርት ምንድነው? የማነው?
ኤፈርት /በትግርኛው ምህፃር “ትእምት” ወያኔ በረሃ እያለ ባንኮችን፣ የመንግሥት መኪናዎችን እና የግለሰቦችን ንብረት
በመዝረፍ ያቋቋመው ህገ-ወጥ የዘራፊዎች ድርጅት ነው፡፡ ወያኔ የሚኒሊክ ቤተመንግስትን ከተቆጣጠረ ወዲህም
ኤፈርት ራሱን በአስራ ሶስት ግዙፍ ኩባንያዎች አደራጅቶ በሁሉም አቅጣጫ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በመቦጥቦጥ የወያኔ
ሹማምንትን ኪስ እንዲያደልብ አደራ የተጣለበት ተቋም ነው።
በዚህም መሠረት መሶበ የኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረቻ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ አዲስ የመድሃኒት
ማምረቻ፣ ኢዛና የማዕድን ልማት፣ ጉና የንግድ ድርጅት፣ ሕይወት የግብርና ሜካናይዜሽን፣ ሳባ እብነ በረድ ማምረቻ፣
ሼባ የቆርቆሮ ፋብሪካ፣ ሱር ኮንስትራክሽን፣ አልሜዳ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ ኤክስፕረስ የትራንዚት አገልግሎት፣
ኢትዮጵያን እንወቅ አስጎብኚ ድርጅት እና ትራንስ ኢትዮጵያ የጭነት ማመላለሻ አገልግሎት የተሰኙ ግዛዙፍ
ኩባንያዎችን አቋቁሞ እንደ ተባይ ድሆች ኢትዮጵያንን የሚመጥ “ካፒታሊዝም” ኢትዮጵያ ውስጥ ለማንሰራፋት
ተንቀሳቀሰ። ከጥቂት ዓመታት ሥራ በኋላ የቁጥጥር አድማሱን በማስፋት ብሩህ ተስፋ ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ማይጨው
ፓርቲክል ቦርድ ፋብሪካ፣ ዲማ የማር ማጣሪያ፣ አላጌ ደንና የደን ውጤቶች፣ ናሽናል ጂኦ-ቴክስታይል እና አበርደሌ
የእንስሳት ማድለቢያና ኢክስፖርት ድርጅት የተባሉ ስድስት ኩባንያዎች የያዘው ደጀና ኢንዳውመንት ተጨመረለት።
ይህ በአደባባይ የሚታወቀው ኤፈርት ነው። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቅርበት የሚከታተሉ እንደሚያውቁት ሁሉ ኤፈርት
በኮንትሮባንድ ንግድ ጭምር የገባ “ወንበዴ ድርጅት” ነው። ኤፈርት ያሻውን ያህል ተበድሮ ያለመክፈል ልዩ ፈቃድ
ያለው ቅምጥል ድርጅት ነው፡፡ እስካሁን ከሶስት ቢሊዮን በላይ የባንክ እዳ እንደተሰረዘለት ይወራል፡፡ የህወሓት
ማዕከላዊ ኮሚቴ በተሰበሰ ቁጥር ከማይቀሩ አጀንዳች አንዱ ትዕምት (ኤፈርት) ነው። ለኤፈርት የቦርድ አባላትንም ሥራ
አስኪያጆችንም የሚሾምለት ህወሓት ነው። የአገሪቱ የፓርቲዎች ህግ ፓርቲዎች እንዳይነግዱ ይከለክላል። ህጉ ሕወሓት
ላይ አይሠራም። እርግጥ ኤፈርት ዘራፊ እንጂ ነጋዴ ስላልሆነ አዋጁ አይመለከተውም።
የኤፈርት ኢትዮጵያን የመዝረፍ ሕልም ትልቅ ነው። “በግል” ባንኮችም የአንበሳ ድርሻ አክሲዮን በመያዝ የፋይናንስ
ሴክተሩን ሊቆጣጠረው ደርሷል። በአገሪቱ ያሉ ያሉ ዋና ዋና የቢዝነስ ኮንትራቶችን የሚወስደው ኤፈርት ነው። ለሕዳሴ
ግድብ ግንባታም ዋና እቃ አቅራቢ ነው። የአገሪቱን 40 በመቶ የፒቪሲ (ፕላስቲክ ነክ ምርቶች) ገበያ ለመቆጣጠር
የሚያስችለውን ማምረቻ እየገነባ ነው። ኤፈርት የድሀውን ገንዘብ እየሰበሰ ለወያኔ ጄኔራሎችና ሹማምንት የሚያድል
አገርን ለማጥፋት የተቋቋመ ተቋም ነው። “የሙስና መርከብ” የኤፈርት የቤት ስሙ የሆነው ያለምክንያት አይደለም።
8
. አቶ ስብሃት ተመሳሳይ ንግግሮችን በተለያዩ ቦታዎች አድርጓል። በተለይ ለቢኦኤ የሰጠው ቃለ መጠይቅ “የተሟላ” ነው ብዬ አስባለሁ።
እዚህ ያገኙታል። http://www.youtube.com/watch?feature=player_detailpage&v=iPCg7zlMjQE accessed 31/08/2013 13
እናም ከተሞቻችን በኤፈርትና በኤፈርት ሰዎች ህንፃ ቢሽቀረቀር ለኛ ምናችን ነው?
7... ስለ ሕዝብ ብዛት እና ልማት በትንሹ
አንድ የእድሜ ባለፀጋ የሆነ ጨዋታ አዋቂ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ግትርነትን (Structural Rigidity) ለመግለጽ
“የተቀየረው የሕዝብ ብዛት ብቻ እንደሆነ ነግሬዓት የልጅ ልጄ Ethiopian Economy የተባለውን ኮርስ እኔ
የተማርኩበትን ደብተር ብቻ አጥንታ A አመጣች” አሉ።
በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ውስጥ ብዙ ሀቆች አሉ። ከጠቅላላው ምርት የግብርናው፣ የአገልግሎትና የኢንዱስትሪው
ዘርፎች ድርሻ በአለፉት አምሳ ዓመታት እጅግም አልተቀየረም። ለምሳሌ የኢንዱስትሪው ድርሻ (ያውም ባህላዊ ሽመና፣
አንጥረኝነትና ሸክላ ሥራ “ኢንዱስትሪ” ተብለው) የአጠቃላይ ምርቱ 15 % ነው ከተባለ አራት አስርታት አልፈዋል።
ከ85% በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በግብርና ይተዳደራል ከተባለ አምሳ ዓመት ሞላው። ሌላው ቀርቶ በከተማና በገጠር
ነዋሪ ድርሻ ላይ እንኳን የጎላ ለውጥ የለም። በሄክታር መሬት ላይ በአማካይ የሚመረተው የስንዴ ወይም የጤፍ
መጠንም (የግብርናው ምርታማነት) ላይ ለውጥ የለም። በነፍስ ወከፍ የካሎሪን ፍጆታ ላይ ለውጥ የለም። ...
ኃይለማርያም ደሣለኝ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለአክሊሉ ኃብተወልድ ሪፓርት ቢያደርጉ አክሊሉ ኃብተወልድ በአድናቆት
የሚያፏጩት የሕዝብ ብዛት ሲነገራቸው ብቻ ነው የሚሆነው።
ራሳቸው አክሊሉ ኃብተወልድን ጨምሮ በተለያየ መጠንም ቢሆን ስለ ትራስፎርሜሽን ያላወራ፣ ያላቀደ፣ ያልፎከረ
ጠቅላይ ሚኒስትር የለም። አሁንም እንደ አዲስ ዘፈንና ዳንኪራው ትራንስፎርሜሽን ሆኗል። በመፈክር ብዛት መዋቅራዊ
ትራንስፎርሜሽን አይመጣም።
ትንሽ እንኳን ሙያዊ ስነምግባር ያላቸው የወያኔ ኢኮኖሚስቶች በደንብ ሲሞገቱ መንግሥታቸው መዋቅራዊ
ትራንስፎርሜሽን አለማምጣቱን ያምናሉ። በዚህ ፍጥነት ተኪዶ በአጭር ጊዜ የሚመጣ አለመሆኑም ይቀበላሉ። ለዚህ
ሁሉ ምክንያቱ ግን የመንግሥት ድክመት ሳይሆን ፈጣን የሕዝብ ብዛት ነው ይላሉ። “ልፋታችንን ሁሉ ፈጣን የሕዝብ
እድገት በላው” ዓይነት መከራከሪያ ያቀርባሉ። የሕዝብ ቁጥር ስለበዛ ድሀና ድህነት በዛ፣ የቤት እጥረት ከፋ፣ የትምህርት
ጥራት ተጓደለ፣ መሬት ጠበበ፣ የሸቀጦች ዋጋ ናረ፣ .... ይቀጥላል ዝርዝሩ። ለተራ ካድሬዎች “ልማት” ለውድቀቶች ሁሉ
ሰበብ እንደሆነ ሁሉ በእውቀት ሻል ላሉት ደግሞ “የሕዝብ ብዛት” የውድቀቶች ሁሉ ሰበብ ነው።
ለመሆኑ የሕዝብ ብዛት ባለበት ቆሞ እንዲጠብቃቸው ነበር የፈለጉት? ደግሞስ በመጠን በላይ ፈጣን ለሆነ የሕዝብ
ብዛት መንግሥት ተጠያቂ አይደለምን?
“የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የልማት ስትራቴጂዎችና ስልቶች” የተሰኘው መጽሐፍ ቅዱሳቸው ኢትዮጵያ ያላት ሁለት ዋና
ዋና ግብዓቶች መሬትና የሰው ጉልበት ናቸው ይላል። ይኸ ትክክል ነው። የሚገርመው ይህንን ያለው ወያኔ እነዚሁኑ
ግብዓቶች ለባዕዳን በመሸጥ ላይ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ የምትተማመንበት ሀብቷ መሬቷ ነው ከተባለ ለምንድነው
ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች አስከፊ የመሬት እጥረት ውስጥ እያሉ ሰፋፊ ለም መሬቶች በገፍ ለባዕዳን ቱጃሮች በመሸጥ ላይ
ያሉት? ኢትዮጵያ በሰው ሀብቷ የምትመካ ከሆነ ለምንድነው ይህንን ሀብቷ ባልተቋረጠ ስደት የምታባክነው? አብዮታዊ
ዲሞክራሲ ያስገኘልን ውጤት በሚከተሉት ሁለት መስመር እንጉርጉሮ ተጠቃሏል። 14
አረብ ወደኛ - ለግብርና
እኛ ወደነሱ - ለግርድና
እንደ ብዙዎቹ ፓሊሲዎች የወያኔ የቤተሰብ ምጣኔ ፓሊሲም መስመሩን የሳተ ነው። ሴቶችን ማስተማርና ገቢ
በሚያስገኝ የሥራ መስክ ላይ ማሰማራትን የመሰለ ውጤታማ የቤተሰብ ምጣኔ የለም። እህቶቻችን ተምረውም ሆነ
ሳይማሩ ያለሥራ ከተቀመጡ ልጆች መምጣታቸው አይቀሬ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ ደረጃ ተፈላጊም ነው።
በአገራችን የደረሰው አስከፊ የኢኮኖሚው ድቀት ልጅ ወልዶ ማሳደግን ለድሆች የሚመች ብቸና አትራፊ “ሥራ”
አድርጎታል። በድሀ አገሮች ልጅን ማሳደግ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ነገር አይደለም። ትላልቆቹ ልጆች ትናንሾቹን
ያሳድጋሉ። ወላጆች ሥራ ከሌላቸው ደግሞ በልጆች ምክንያት የሚያጡት ገቢ የለም። እንደምንም አስር ዓመት
ከሞላቸው ልጆች ቤተሰብን ለመደጎም ይሯሯጣሉ። ጠና ሲሉ ደግሞ ከተቻለ ርቀው በመሄድ ካልቻለ ሴቷ አረብ አገር፤
ወንዱ ሱዳን ውስጥ ማሽላ ቆርጦ ቤተሰቡን ይጦራል። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በገጠር ብዙ ልጆች
ያላቸው ቤተሰቦች ከመንደሩ በኑሮ የተሻሉ የሆኑት። ውጤታማ የቤተሰብ ምጣኔ ፓሊሲ እንዲኖር ከተፈለገ ከዚህ ሀቅ
መነሳት ያስፈልጋል።
በዘመነ ወያኔ በቤተሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአገርም ደረጃም ሰው የኢትዮጵያ ትልቁ “ኤክስፖርት” ሆኗል። በውጭ
አገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በኦፊሲያላዊ መስመሮች የሚልኩት ገንዘብ ከቡና ቀጥሎ ትልቁ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ
ነው። አፊሴላዊ ባልሆነ መንገድ የሚገባው ሲታከልበት ኢትዮጵያዊያን የሚልኩት ከቡና ኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ
በጣም ይበልጠዋል።
ወያኔ ሌሎች የኤክስፓርት ሸቀጦችን ከማበረታታት በዚህ ላይ ማትኮር የተሻለ ሆኖ አግኝቶታል። በዚህም ምክንያት
ሙሉ የዲፕሎማሲ ትኩረቱን መከራን ሸሽቶ የወጣውን ኢትዮጵያዊ ገንዘብ ማለብ የሚቻልባቸውን መንገዶችን መቀየስ
ላይ አድርጓል። የአባይ ቦንድ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም ዲያስፖራው ነቅቶበት ውድቅ አድርጎታል። አሁን አዲሱ
ስልት ኮንዶሚኒየም ነው። የኮንደሚኒየም እቅዱ ከተሳካለት ከዲያስፖራው የሚያገኘው የውጭ ምንዝሬ ከቡና ንግድ
የሚያገኘውን ሶስት እጥፍ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል። ዲያስፖራው ገንዘቡ መበላቱ የሚያውቀው የዛሬ አስር ዓመት
ሊሆን ይችላል። እቅዱ እስከዚያው በተስፋ ማቆየት ነው።
የወያኔ ሥርዓት ኢሰብዓዊነት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ሕፃናትን ሳይቀር መሸጥ የፕሮጀክቱ አካል መሆኑ ነው።
የወያኔ ኢኮኖሚስቶች የሕዝብ ብዛትን ቢያማርሩም ውሸታቸውን ነው። እንዲያውም የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት
የቢዝነሳቸው መሠረት ሊሆን ተቃርቧል።
ይህንን ንዑስ አርዕስት ከመዝጋቴ በፊት አንድ አስደናቂ ነገር ላንሳ። ከሌሎች አገራት በተለየ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ
ብዛት በጣም ስሱ አይነኬ ፓለቲካ ሆኗል። ቁጥራችንን አናውቀውም። ለማወቅ መሞከር ደግሞ አደጋ አለው።
ኦፊሲያላዊ ቁጥራችንን የሚወስነው የወቅቱ ፓለቲካ ነው። በተለይም በኦሮሞና በአማራ ሕዝብ ቁጥር ላይ ወያኔ ትልቅ
የፓለቲካ ካልኩለስ ይሠራል። የአዲስ አበባ ነዋሪ ቁጥርም የሚወሰነው በፓለቲከኞች ነው። ከወያኔ ውጭም ያሉ ሰዎች 15
የሕዝብ ቁጥርን የስታትስቲክስ ሳይሆን የፓለቲካ ጉዳይ አድርገውታል። ቡድኖች ብዙ ነን ለማለት ቁጥር ወይም
ፕርሰንት ጨምረው ያወራሉ። እንዴት ነው ቁጥራችንን እንኳን ሳናውቅ የስነ ሕዝብ ፓሊሲ የሚኖረን?
8... ለዘላቂ ልማት ምን ዓይነት መንግሥት?
የወያኔ ካድሬዎች ኢትዮጵያን ለማልማት ከወያኔ ወዲያ ላሳር እንደሚሉ በመግቢያዬ ገልጫለሁ። የእኔ እምነት የዚህ
ቀጥታ ተቃራኒ ነው። ወያኔ ከዚህ በላይ በሥልጣን እንዲቆይ ከተፈቀደለት ኢትዮጵያችን ሊጠገኑ የማይቻሉ ቋሚ
ስብራቶች ይደርሱባታል። ስለዚህም ለኔ ኢትዮጵያን ለማልማት የወያኔ መወገድ ቅደመ ሁኔታ ነው።
እውቁ አሜሪካዊ ኢኮኖሚስት ማንኩር ኦልሰን “አምባነንነት፣ ዲሞክራሲና ልማት” (Dictatorship, Democracy and
Development) በሚል ርዕስ የፃፈው አጭር መጣጥፍ ውስጥ የሰጠው ስዕላዊ ገለፃ የወያኔን ታሪክ የሚያወራ እስከሚመስል
ድረስ ተቀራራቢ በመሆኑ እንድታነቡት አበረታታለሁ9

ኦልሰን እንዲህ ይላል
ዘላን ወንበዴዎች /roving bandits/ ነጥቀው ይሮጣሉ፤ መቼ እንደሚመለሱ አይታወቅም። እነዚህ
ወንበዴዎች ነጥቀው በሮጡ ቁጥር የማኅበረሰቡ ሀብት የማፍራት ፍላጎት ስለሚዳከም በሚቀጥለው
ዙር የሚዘርፉት ነገር እያነሰባቸው ይመጣል። ቀን ባለፈ መጠን ነጥቆ መሮጥ እንደሚጎዳቸው
ይገነዘቡና ራሳቸውን ከተዘዋዋሪ ወንበዴነት ወደ ቋሚ ወንበዴነት /stationary bandit/ ይቀይራሉ።
ለንጥቂያቸውም ሥርዓትና ልክ ያበጁለታል። ስሙንም “ግብር” ይሉታል። ራሳቸውንና ማኅበረሰቡን
ከሌሎች ተዘዋዋሪ ወንበዴዎች ይከላከላሉ። ይህ ሥርዓት ከሥርዓተ-አልበኝነት የተሻለ፤ የቅሚያውም
መጠን አስቀድሞ የሚታወቅ ከመሆኑ ጋር ማኅበረሰቡ ለሚከፍለው ተመጣጣኝ ባይሆንም የሚያገኘው
ጥቅም (ሰላምና ሌሎች ማኅበራዊ ምርቶች/ public goods) ስላሉ ምርት ይጨምራል፤ እድገትም
ይኖራል።
ይሁን እንጂ አምባገነን ሰፋሪዎች በተደላደሉ መጠን ፍጆታቸው እየናረ መሄዱ ፈጽሞ የማይቀር ነው።
ለጦር ሠራዊቱ፣ ለቤተመንግሥቱ፣ ለቤተመቅደሱ፣ ለማሰልጠኛው፣ ለመታሰቢያ ሀውልቶች ግንባታ፣
ለመሰብሰቢያ አዳራሾች ግንባታ፣ ለክብረ-በዓላት ማስጌጫ፣ በውጭ አገራት ባንኮች ለሚከማቸው
“መጠባበቂያ” ሂሳብ (ሞቡቱ 8 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ክምችት ነበረው ይባላል)፤ ለአምባገነኖቹና
ቤተሰቦቻቸው የክብር አልባሳትና ጌጣጌጦች መግዣ (ኤሜልዳ ማርቆስ 3000 ጥንድ ጫማዎች
ነበሯት)፤ ወዘተ ወጪ ማውጣት ያስፈልጋል። ይህንን ሁሉ ለማሟላት የሚጠየቀው ወጪ በጨመረ
ቁጥር ሕዝቡ በግብር አሊያም በሌላ መንገድ እንዲከፍል ስለሚገደድ ሥርዓት በመስፈኑ ምክንያት
9
 . Olson Mancure “Dictatorship, Democracy and Development” American Political Science Review Vol. 87 No. 3
 ለኦን ላይን ንባብ እዚህ ላይ ይሞክሩ
http://www.jstor.org/discover/10.2307/2938736?uid=3738032&uid=2&uid=4&sid=21102597375683 accessed 31/08/201316
አንሰራርቶ የነበረው የሥራ ፍላጎት እንደገና ያሽቆለቁላል። የሰፋሪ ወንበዴዎችን የሀብት ማጋበስ፣
ምቾትና እዩልኝ ፍላጎቶችን ማርካት አይቻልም።
ሰፋሪ ወንበዴዎች ከፍጆታቸው ከአቅም በላይ መናር በተጨማሪ ሌሎችም ችግሮች አሉባቸው። ከእነዚህ
ችግሮች አንዱ የሥልጣን ሽግግር /succession/ ችግር ነው። ልሁቁ ወንበዴ በደከመ ወይም ባረጀ ጊዜ
በማን እንደሚተካ ግልጽ መመሪያ ስለማይኖር ከአንድ አምባገነን ወደሌላኛው አምባገነን መሸጋገሪያ ላይ
ብጥብጥና አለመረጋጋት ይኖራል። ስለሆነም በዚህ መንገድ የሚመጣው ሰላም ከአንድ ሰው እድሜ በላይ
የመቆየቱ ነገር እጅግ አጠራጣሪ ነው ። ይህ ጥርጣሬ ራሱ የረዥም ጊዜ ኢንቬስትመንትን የሚገታ የእድገት
ማነቆ ነው።
ኦልሰን የፃፈውን ደጋግሜ ባነበብኩት ቁጥር የወያኔን ታሪክ የፃፈ ይመስለኛል። የአምባገነን ሥርዓቶች የባህርይ
ተመሳሳይነት የሚገርም ነው። የዚህ ንዑስ ክፍል ዋነኛው መልዕክቴ የሚከተለው ነው።
ወያኔና ወያኔ መሰል ሰፋሪ ወንበዴዎች /stationary bandits/ ዘላቂ የሆነ ልማት ማምጣት
አይችሉም። ለጥቂት ዓመታት ሞቅ ሞ ቅ ማድረግ ቢችሉ እንኳን የሚገነቡት ኢኮኖሚ “የሀብት
ማጋበስ፣ ምቾትና እዩልኝ” ፍላጎቶቻችውን ማርካት አይችልም።
ለዘላቂ ልማት የሚያስፈልገን ምን ዓይነት መንግሥት ነው?
ለዘላቂ ልማት ሰላምና ውሎችን ማስጠበቅ የሚችል እና ራሱን የሚቆጣጠር የአስተዳደር ሥርዓት መኖሩ ወሳኝ ነገር
ነው። ንብረት በግል የመያዝ መብት የሚያከብር፤ ራሱ ባለሀብት ለመሆን የማይጓጓ መንግሥት ያስፈልጋል። ወገናዊ
ያልሆነ የፍትህ ሥርዓት ከሌለ ውሎች አይረጉም፤ ቃልኪዳኖች አይከበሩም፤ በሰዎችና በተቋማት መካከል መተማመን
ይጠፋል። ይህ ሁሉ እድገትን ያቀጭጫል። እነዚህን አሟልቶ የሚገኝ የመንግሥት ሥርዓት ደግሞ ዲሞክራሲያዊ
ሥርዓት ነው።
9... መዝጊያ
የዚህን ጽሁፍ ገፆች ለመቀነስ ስል ብዙ የሚያነጋግሩ ሀሳቦችን በአጭሩ ቋጭቻለሁ። ያም ሆኖ ግን የተነሳሁበትን ሃሳብ
አሳክቻለሁ ብዩ አማናለሁ።
1. “ወያኔ ከኔ በፊት በአገሪቱ ውስጥ ልማት የሚባል ነበር አልነበረም” ይላል። ይህ ውሸት ነው። ከወያኔ በፊት
የነበሩት መንግሥታት የሠሩት በቂ ባለመሆኑ የሚተቹ ቢሆንም ጥቂት መልካም ነገሮችን ሠርተዋል።
2. ወያኔ “እኔ ልማትን እያመጣሁ ነው፤ ሌላውን ቻሉት” እያለን ነው። ይህ ውሸት ነው። ወያኔ ጥፋትን እንጂ
ልማት እያመጣልን አይደለም። ልማት አምጥቶልን ቢሆንም ኖሮ ለልማት ብላችሁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቼን
ታገሱ ማለት ትዕቢት ነው። 17
3. ወያኔ “ለወደፊቱም ከኔ የተሻለ ኢትዮጵያን ማልማት የሚችል የሌለ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሲባል እኔ ለረዥም
ጊዜ በስልጣን መቆየት አለብኝ” እያለ ነው። ሃቁ የሚያሳየው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ወያኔ በሥልጣን ላይ
በቆየ መጠን አገራችን ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየከፋ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም።
ስለሆነም ለአገራችንና ለወደፊቱ ትውልድ ደንታ ያለን ኢትዮጵያዊን ሁሉ ወያኔን አባረን በምትኩ ዲሞክራሲያዊ
ሥርዓት እንዲገነባ ለሚደረገው ትግል የበኩላችን አስተዋጽዖ ማበርከት ይጠበቅብናል። http://www.ethiomedia.com/2013report/what_is_development.pdf
አስተያየት ካለዎት: tkersmo@gmail.com

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar