የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበራትን የብዙ ዘመናት የበላይነትና የጠነከረ ቅርርብ መሠረት አድርገው በፖፕ ታዋድሮስ 2ኛ በኩል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ ግፊት ለማድረግና የግጭት መነሻ እንዳይሆን ጫና እንዲያሳድሩ በመሐመድ ሙርሲ በኩል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል የሚል ሰፊ ዘገባ ይዘው የወጡትን የግብጽ ጋዜጦች መነሻ በማድረግ የፓትርያርኩ ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥቷል። አናዶሉ የተባለው የዜና ወኪልም በቀጥታ ፖፕ ታዋድሮስ ጉዳዩን ያውቁት እንደሆነ በስልክ አነጋግሮአቸው በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት «የግብጽ ጋዜጦች ይህንን ዜና ከየት እንዳገኙት አላውቅም፤ ለእኔ በግሌ ከፕሬዚዳንት ሞርሲ በኩል የኢትዮጵያን ግድብ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ጋር የሽምግልና ድርድር እንዳደርግ የጠየቁኝ ምንም ዓይነት ነገር የለም» በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል ሲል ደጀ ብርሃን ብሎግ ዘገበ።
የደጀብርሃንን ዘገባ እንደወረደ ያንብቡት።
የፓትርያርኩ ጽ/ቤት ለዜና ወኪሉ በተጨማሪ እንደገለጸው ጥያቄው ቢቀርብላቸው የኮፕት ቤተ ክርስቲያን በጉዳዩ ላይ ለመሥራት ምንም ቅሬታ የሌላት ቢሆንም መታወቅ ያለበት ነገር ግን፤ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሀገሪቱ መንግሥት የውሳኔ ሰጪነት ሥልጣን ውስጥ ምንም ድርሻ የሌላት መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግ በመግለጫው ተመልክቷል። ለግብጽና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ጥቅምና ሰላም በሚበጅ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ነን፤ ይህንን በተመለከተም የኢትዮጵያው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ሐምሌ 19/2013 ግብጽ በሚመጡበት ወቅት ስለግድቡ ጉዳይ እናነሳላቸዋለን በማለት ጽ/ቤቱ ያለውን ሃሳብ በተጨማሪ አስረድቷል። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቀድሞ በነበራት ተደማጭነት በመንግሥት ላይ የምታሳድረው ተጽእኖ ባለመኖሩ በግድቡ ጉዳይ ላይ የጎላ ሚና ይኖራታል ተብሎ አይጠበቅም ሲል በዜና ዘገባው ላይ «አናዶሉ» የዜና ወኪል ያገኘውን ማብራሪያ መነሻ አድርጎ የራሱን ትንታኔ በመስጠት ስለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የወቅቱ አቅም እስከየት ድረስ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የደርግን የውድቀት ቀን ተጠግቶ ግንቦት 20 የመፍሰሻ አቅጣጫው መለወጡ ስለተነገረው ታላቁ ኅዳሴ ግድብ የግብጽ ሚዲያዎች የጩኸትና የጦርነት ዜማ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። የጃማአ አል ኢስላሚያ ሙፍቲ የሆኑት ሼክ አብደል አክሄር ሐማድ ለተከታዮቻቸው ባሰሙት ንግግር እንደተጠቆሙት «ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ አቅጣጫ መቀየሯ በግብጽ ሕዝብ ላይ ጦርነት እንዳወጀች ያህል ይቆጠራል» በማለት ጠጣር መልዕክት አስተላልፈዋል። «አል አረቢያ» ለተሰኘው ቴሌቪዥን ጣቢያም በቀጥታ ስርጭት ባደረጉት ንግግር «የኢትዮጵያን ድርጊት የግብጽ መንግሥት በትዕግስትና በዝምታ ሊመለከተው አይገባም፤ የኢትዮጵያ ድርጊት በግብጽ ላይ የተፈጸመ የጦርነት አዋጅ ነው፤ ይህንን ድርጊት በፍጹም አንታገስም፤ በሽምግልና ብቻ የሚፈታ ጉዳይ ስላልሆነ መብታችንን በኃይል እስከማስከበር መሄዳችን የግድ ወደሚል ሁኔታ ውስጥ እየገባን ነው» በማለት አቋማቸውን ለአድማጭ፤ ተመልካቹ በግልጽ ተናግረዋል። ግብጾች የሚጠብቀንን ግዴታ ሳንዘነጋ የዲፕሎማሲውን ጉዳይ ጎን ለጎን በማካሄድ ትኩረት መስጠት ይገባናል ማለታቸውም ተወስቷል።
በሌላ በኩልም በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወቅት የግብጽ ጦር አዛዥ የነበሩት ጀነራል ሞሐመድ አሊ ቢላል እንዳስገነዘቡት ግብጽ በዓባይ ግድብ ላይ የጥቃት እርምጃ ብትወሰድ ቀጣናውን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚቀይረው ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ የጋራ ጥቅም ያላት ቻይናና የግብጽ ባላንጣ የሆነችው እስራኤልን ወደጉዳዩ እንዲገቡ ሊያደርጋቸው ስለሚችል ግብጽ በምትወስደው የጥቃት እርምጃ ምንም ትርፍ አታገኝም ሲሉ ለአል አረቢያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ የረቡዕ 30/ 5/2013 ዕለት ስርጭት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሰሞኑ የግብጽ ሚዲያዎች እያራገቡ የሚገኙበትን ዘገባ ስንቃኝ ጦር፤ ጦር የሚሸት መንፈስን ባዘለ መልኩ መሆኑ ምናልባትም አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ባላቸው ዝቅተኛ ግምትና ለራሳቸው ጥቅም አብልጦ የማሰብ ራስ ወዳድነት ሲሆን አንዳንዶቹም በከፍተኛ ፖለቲከኞች በኩል ሆን ተብሎ በማስፈራሪያ ሰበብ የሚሰራጭና የግብጽ እርምጃ የት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ለኢትዮጵያ መንግሥት መልዕክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
በዚህም ተባለ በዚያ «አስቀድሞ ነበር መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ያደርጋል ድስትን ጥዶ ማልቀስ» እንዳይሆን አንዴ የገቡበትን ሥራ ቀድሞ ባልጀመርነው ኖሮ ከማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ከዲፕሎማሲው ጎን ለጎን ራሱን ማዘጋጀት ይገባዋል እንላለን። መንግሥት ልቡን ሰፊና እጁን ረጅም አድርጎ በፖለቲካ ያኮረፉትን በመጥራት በሀገር የጋራ ጉዳይ ላይ ማግባባት ወደሚችል የግል ሁኔታ ለመግባት የመድብለ ፓርቲውን ሥርዓት በር ከፈት ማድረግ አለበት። እንደኢትዮጵያ ባለና ውጥንቅጡ በወጣ አመለካከት ውስጥ ልማት ብቻውን ሀገር አይገነባም። አሸባሪ የተባለ ማንም ተነስቶ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ቢል አያስገርምም። ባራቅነውና በረገምነው ቁጥር መራቁ ባህሪያዊ ነውና። አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን በልማት ዜማ የማዳፈን ጉዳይ አኩራፊ ማበራከቱና ለጠላት በር መክፈቱ አይቀሬ ይሆናል። ግብጾች ራሳቸው መሥራት ያልቻሉትን የውጪ ሥራ በሌሎች እጅ ከማሰራት ይመለሳሉ ማለት የዋህነት ነው።
ዓለማችን በአየር ለውጥ የተነሳ ሙቀቷ እየጨመረና በረሃማነትም እየተስፋፋ እንደመሄዱ መጠን አንድ ዓባይን ብቻ በተስፋ የምትጠብቅ ግብጽ በሆነ አጋጣሚ አንድ ክረምት ዝናብ በበቂ ባይጥልና ወንዙ ጎድሎ በትነት መጠኑን ከቀድሞው ቢቀንስባት ወደአጥፍቶ መጥፋት አትገባም ማለት አይቻልም። ረጅም እሳቤ ያለው እቅድ ለዓባይ የዛሬው ግድብ አስፈላጊው ነው እንላለን።
እንዲያውም ስለዓባይ የተነገረው የግብጽ ሸክም የሚራገፍበት ዘመን ደርሶም ይሆን? የሚል የትንቢት ጥያቄም እናነሳለን።
«ግብጻውያንንም በጨካኝ ጌታ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ ጨካኝ ንጉሥም ይገዛቸዋል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦ ውኆችም ከባሕር ይደርቃሉ፥ ወንዙም ያንሳል ደረቅም ይሆናል። ወንዞቹም ይገማሉ፥ የግብጽም መስኖች ያንሳሉ ይደርቃሉም ደንገልና ቄጤማ ይጠወልጋሉ። በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ ይደርቃል፥ ይበተንማል፥ አይገኝምም። ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፥ በዓባይም ወንዝ መቃጥን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፥ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት ይዝላሉ»
ኢሳ 19፤ 4-8
Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=3825
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar