onsdag 8. mai 2013

“ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን እያፈረሰ የራሱን ይፈጥራል”

የመኢአድ ሊቀመንበር ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ስለገዢው ፓርቲ ምን ይላሉ?
“ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን  እያፈረሰ የራሱን ይፈጥራል”
  • “ከ97 ወዲህ ፍርሃት የተጠናወተው ፓርቲ ሆኗል”
  • “ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ሰላዮችን አሰማርቷል”
  • “ምርጫኮ የለም ፤ ያለተወዳዳሪ ምረጡኝ ይላል”
በአገራችን የምርጫ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ በሚሰጠው የ97 ምርጫ ቅንጅትን በከፍተኛ ደረጃ ይመሩ የነበሩት እና በአሁኑ ሰዓት የመኢአድ ሊቀመንበር የሆኑት ኢ/ር ኃይሉ ሻውል፤ መጽሐፍ ይጽፋሉ ተብሎ ከተጠበቀበት ጊዜ ዘግይተውም ቢሆን “ህይወቴና የፖለቲካ እርምጃዬ” የሚል መጽሐፍ ለንባብ ሊያበቁ ተቃርበዋል፡፡ መጽሐፉ 200 ገጽ ያለው ሲሆን ቀጣይነት አለውም ተብሏል። ኢ/ሩ በእንግሊዝኛም ሰፋ ያለ መጽሐፍ እየፃፉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በአዲሱ መጽሐፋቸው፣ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከኢንጂነር ሃይሉ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡
ኢንጂነር ኃይሉ፣ ስለገዢው ፓርቲ ምን ይላሉ? እስቲ በህትመት ላይ ስላለው መፅሀፍዎ ይንገሩኝ…. እንግዲህ የአንድ ሠው ታሪክ ብዙ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ የእኔ ዋናው ቅርንጫፍ በሙያዬ የተሠማራሁበት ሥራ ነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ችግር ሲመጣ ወደ ፖለቲካ ገባሁኝ፡፡ እናም በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ሰው እውነቱን እንዲያውቅ ቀለል ባለ መልኩ ፅፌዋለሁ፡፡ ብዙዎች በተለይ ፖለቲካውን በተመለከተ መጽሐፍ ለማውጣት እንደዘገዩ ይናገራሉ፡፡ የዘገዩበት ምክንያት ምንድን ነው? መፅሀፉ የዘገየበት ምክንያት የሚቀሩትን ላካትትበት ወይስ አሁን ያለቀውን ላሳትመው በሚለው ላይ ሳመነታ ነው፡፡ አሁን እየታተመ ያለውን ግን ከጨረስኩት ቆይቻለሁ፡፡

ግን ያለቀው ይውጣና ቀጣይ ክፍል አዘጋጅለታለሁ ብዬ ወሰንኩ። መቼም መፅሀፉ የ97ቱን ምርጫና የቅንጅትን ጉዳይ ማካተቱን አይቀርም፡፡ እስከዛሬ በቅንጅት ዙሪያ ከተፃፉት መፅሀፍት ምን የተለየ ነገር ይኖረዋል? እኔ እምናገረው እውነት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ የለም፡፡ እስከዛሬ ያየኋቸው መፅሀፍት ላይ ወገናዊነት አያለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ከሚገባው በላይ ዘለው የሄዱ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ የቅንጅት መፍረስ በቅንጅት መሪዎች ሲመኻኝ ነው የምሠማው፡፡ ነገር ግን የዚያ አይነት የፖለቲካ እመርታ ያመጣ ፓርቲ፤ በዚያ እሣት ውስጥ አልፎ የሄደ እንደመሆኑ መጠን ጥፋት ቢኖረው እንኳን ታይቶ ይታለፋል፡፡ አንዳንዶች ግን “እርስ በእርሣቸው ፈራረሱ” ይላሉ፡፡ ወያኔም እንዲህ ነው የሚለን፡፡ በጣም ያሣዝነኛል፡፡
እርስዎ ቅንጅትን ማነው ያፈረሠው ይላሉ?
እውነት ለመናገር ቅንጅትን ወያኔ ራሱ ነው ያፈራረሠው፡፡ አሁንም እያፈረሠ ነው፡፡ እያንዳንዱ ፓርቲ ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ አስርና አስራ አምስት ያህል ሠላዮች አሠማርቷል፡፡ እኛም ወስጥ ተሠማርተው ስራቸውን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ የእኛ ጥፋት ምኑ ላይ መሠለሽ፣ ዴሞክራሲ ብለን ስለተነሣን በየአካባቢው ያለው ሁኔታ ዴሞክራቲክ ነው በሚል ራስን በሚደልል ሁኔታ ግልፅ ሆንን እና ምስጢር የሚባል ነገር መያዝ አልቻልንም፡፡ በፊት ለፊት ስንሠራ ስለነበር ለወያኔ ተመቸነው፡፡
ተመቸነው ሲሉ እንዴት ነው?
የተመቸነውማ ውስጣችን ሆኖ እርስ በእርስ እንድናከስ አደረገ፡፡ የምንሠራውን ፕላን አስቀድሞ ማወቅ ቻለ፡፡ በውስጣችን እኛን የሚቃረን አዘጋጀ። አንድ ድርጅት ውስጡ ሆኖ የሚበትነው ወገን ሲኖር፣ ማን አፈረሰው ሊባል ነው! አፍራሾቹን ያሠማሯቸው አካል ነው ተጠያቂው፡፡ ራሣቸውን መስዋዕት አድርገው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የተሰለፉት አመራሮች ቅንጅትን አላፈረሱትም፡፡ ይህ በደንብ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ፡፡
አሁን የነገሩኝ ሀሣብ በመፅሀፍዎ ውስጥ ተካትቷል?
አዎ! አካትቸዋለሁ፡፡ መፅሀፉ ስለቅንጅት መፍረስ፣ በአጠቃላይ ስለ ፖለቲካው ሁኔታ የሚዳስስ እንደመሆኑ፣
ምን ምን አዲስ ነገሮችን ይፋ ያደርጋል?
ከመነሻው ጠቅላላ ሂደቱን ይተነትናል፡፡ መጀመሪያውኑ ቅንጅትን ስንመሠርት አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን ሳላስተውል ቀርቼ አልነበረም። ነገር ግን “ግዴለም አብረን ስንሠራ ቀስ በቀስ ይስተካከላል” በሚል አምኜ አብሬ ተጉዣለሁ። ያንን ጉዳይ አሁን ላይ ሆኜ ወደ ኋላ ሳየው “ለምን ሳናጣራ ሄድን” ብዬ እጠይቅና እቆጫለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ግዜው አይፈቅድም ነበር፡፡ ህዝብ ከእኛ ብዙ ይጠብቅ ነበር፡፡ የጋዜጦችም ግፊት ከፍተኛ ነበር፡፡ የዛን ጊዜ ወደ ኋላ ብንል ኖሮ “መኢአድ እንደልማዱ ቅንጅት አንፈጥርም ብሎ ነገር አበላሸ” ይባላል በሚል ነው የቀጠልነው፡፡ ምክንያቱም መኢአድ ባይኖር ቅንጅት አይፈጠርም ነበር፡፡ ይሄ ግልፅ ነው።
እንዴት?
ትልቅ ፓርቲ ተብሎ የተመሠረተው፣ ገጠሩንም ከተማውንም ያገናኝ የነበረው መኢአድ ብቻ ነበር። ሌሎቹ አብረውን የተጓዙት ፓርቲዎች አዳዲስ ነበሩ። አዲስ ተመስርተው ደግሞ ህዝብን ይዘን መጣን ማለት አይችሉም፤ አዲስ ከሆኑ ህዝብ የሚባል ነገር የላቸውማ! ይሁን እንጂ የእነርሱም ስራ ከፍተኛ እንደነበር አንክድም፡፡ ምክንያቱም ብዙው ምሁራን ስለነበሩ ህዝቡ በፓርቲው እምነት እንዲያገኝ በክርክሩ ጊዜ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በአጭር ጊዜም ውስጥ ቢሆን ገብተው ብዙ የለውጥ መንገዶችን ያስተካከሉ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን በውስጣቸው ምን አይነት ሠዎች እንደተሠለፉ አልመረመርንም፤ ለዚህ ነው መፍረሱ የመጣው፡፡ ከኢህአዴግ ሌላ በውስጣችሁ ለቅንጅት መፍረስ ተጠያቂ የሆነ ወገን ነበር እያሉኝ ነው? ኢዴፓዎች ችግር ነበረባቸው፡፡
ከገዢው ፓርቲ ጋር በጣም የተጠጋጋ አሠራር ነበራቸው፡፡ መጨረሻ ላይም የታየው ይሄው ነው፡፡ እውነተኛው ጊዜ ሲደርስ የማፍረስ ሁኔታ የፈጠረው ኢዴፓ ነው፡፡
እና ኢዴፓ አፍራሽ ነው ብለው ያምናሉ ማለት ነው?
አምናለሁ! ይህንን ጉዳይ ማንም የሚክደው አይደለም፡፡ ግን እኮ መኢአድ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በክፍፍልና በንትርክ ውስጥ ነበር፡፡ የንትርኮቹ መንስኤዎች እና የመፍትሄ ሀሣቦች በመፅሀፉ ተካተዋል? አ…ይ…እሱ … ዛሬ ያለው ሂደት ከድሮው የተለየ አይደለም፡፡ ጠበቅ አድርገን ቤቱን ባናፀዳው ኖሮ፣ ዛሬ መኢአድ የሚባል ድርጅት አይኖርም ነበር፡፡ ልክ እንደ ሌሎቹ ከገዢው ፓርቲ ጋር ተጨባብጦ የሚኖር ድርጅት ለመመስረት ነበር የተፈለገው። ይህ ማለት ደግሞ ከህዝብ ጋር የሚቆም ፓርቲ አይኖርም ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ያንን ለመቀየር ብዙ የውስጥ ትግል አድርገናል፡፡ ይህንን ጉዳይ በሁለት ዙር ትግል ያፀዳነው ይመስለኛል፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ ሁለቱ ቢራኮቱ ለእኛ ምናችንም አይደለም። እኛ የሚደበቅ ነገር የለንም እንጂ ሰላዮቹ ዛሬም አሉ፣ እናውቃቸዋለን፡፡
ዴሞክራቲክ ድርጅት እንደመሆናችን መሣሪያ በዚህ መጣ፣ ሠው በዚህ ተዋጋ የምንለው ነገር ስለሌለ የምንፈራው ነገር የለም፡፡ ሁሌ የሚሠልሉን ድንገት እነዚህ ሠዎች ወደ ሌላ ነገር ይገባሉ ብለው በመፍራት ይመስለኛል። በ97 ምርጫ በሠባ ምናምን እድሜዬ “ሠላማዊ ትግል ይዘን አሸነፍን፡፡ አቅማችንንም አወቅን። ከዚያ በኋላ ያለውን እኮ ለወጣቱ ትውልድ “ያውልህ” ብሎ ማስረከብ ነው፡፡ ወጣቱ ደግሞ የራሱን ስትራቴጂ አውጥቶ ይሄዳል፡፡
አሁን ያለው አጠቃላይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
የፖለቲካ እንቅስቃሴ አለ እንዴ? እኮ አለ እንዴ? እርስዎ ይንገሩኝ … እኔ እንግዲህ ያለውን ሁኔታ እንቅስቃሴ አልለውም፤ አይደለምም፡፡ ነገር ግን በእኛ በኢትዮጵያ አንፃር ከሆነ ትንሽ መንፈራገጥ ጀምሯል፡፡ ሚያዝያ ስድስትና አስራ ሶስት ስለተካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ ምን አስተያየት አለዎት? “ምርጫ” የሚለውን ቃል ለምን ተጠቀምሽበት? አባከንሺው እኮ፡፡
ለመሆኑ ምርጫ የሚባል ነገር ተደርጓል እንዴ?
አልተደረገም ነው የሚሉኝ?
አልተደረገም!! ድምፅ ሲሰጥ የምለውስ ሰው? ኢህአዴግ ወረቀት አሠባሠበ እንጂ ምንም ያደረገው ነገር የለም፡፡ ምርጫ ማለት ውድድር ሲኖር ነው፤ ከተወዳዳሪዎች መሀል ትመርጫለሽ። ዝም ብሎ “ኑ እኔን ምርጡኝ፤ ሌሎቻችሁ ዞር በሉ፣ ራሴ እመርጣለሁ፤ እራሴ እንደ ፈለግሁ አደርጋለሁ፤ ራሴ እናገራለሁ፤ ሌሎቻችሁ አፋችሁን ዝጉ” እየተባለ የሚደረግ ምርጫ በዓለም ላይ አይቼ አላውቅም፡፡ ከ97 ወዲህ ፍርሀት የተጠናወተው ፓርቲ ነው ስልጣን ላይ ያለው፡፡ ስለዚህ አንድም ፓርቲ እንዲነቃነቅ አይፈልግም፡፡ እኛም ደግሞ ወጣቱን ማስጨረስ አንፈልግም፡፡ ግዴለም ወቅቱ ሲደርስ ህዝቡ መልሱን ይሠጣል ፡፡ ከ2002ቱ ምርጫ ቀደም ብሎ በገዢው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የምርጫ ሥነ-ምግባር ኮድ ፊርማ ተካሂዶ ነበር፡፡ ኮዱን ከፈረሙት ፓርቲዎች መካከል መኢአድ አንዱ ነበር፡፡ በፊርማ ስነ-ሥርዓቱ ላይ እርስዎ ሲፈርሙ በቦታው ነበርኩኝ፡፡ የፊርማውን አስፈላጊነት በተመለከተ ጥያቄ ቀርብዎሎት የሰጡት መልስ ነበር፡፡ እስኪ አስታውሺኝ ልስማው… “እኛ ወደ ፊርማው የገባነው እየራቅን ነገሮች ከሚደበቁብን፣ ቀርበን የኢህአዴግን ልብ እና ሀሣብ ለማወቅ ነው፤ ጠላትን ወዳጅ መስሎ በመቅረብ እንጂ በመራቅ የሚገኝ ትርፍ የለም” ሲሉ ሠምቻለሁ፡፡ ከተፈራረሙና ከቀረቡ በኋላ ደግሞ ከስምምነቱ መኢአድ መውጣቱን አስታወቁ፡፡
ኢህአዴግን ቀርበውት የተማሩትና ያገኙት ቁም ነገር ምንድን ነው?
የምርጫ ስነ-ምግባር ኮድ መፈራረሙን በተመለከተ በመፅሀፍዎ ምን የሚነግሩን ይኖራል? መፅሀፏ መግለፅ ትገልፃለች፡፡ ኢህአዴግን በመቅረብ ምንም ያገኘነው ነገር የለም፡፡ ኢህአዴግ እስከ ዛሬ የኖረው ነገሮችን መደበቅ ስለሚችል፣ መሸፈን ስለሚያውቅበት ነው፡፡ እኛን መሣሪያ ለማድረግ ሞክሮ ነበር፡፡ እኛ አንቀጥልም ብለን ነው የወጣነው፡፡ ምክንያቱም እነሱ የሚያቀርቡት አጀንዳ እኛ ከምናቀርበው ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ እኛም እንድንናገር አይፈለግም፤ ራሱ ምርጫው የልጆች ጨዋታ ነበር ማለት ይቻላል። መጀመሪያውኑም አውቀነዋል፡፡ ነገር ግን “እነዚህ ሠዎች ሠው ለመሆን ፈልገዋል፤ እድል እንስጣቸው ብለን ነው የገባንበት፡፡” ለካ እነሱ ይህንን ሁሉ የቀመሙት ምንም ፋይዳ ለሌለው ነገር ነው። እነሱ በፊትም እንደጀመሩት ወጣቱን አሣደው ጨርሠዋል፤ በየቦታው አስረዋል፣ በዚያው ነው የቀጠሉት፡፡
ታዲያ እንድንፈራረም ለምን ፈለጉ ብዬ ራሴን ስጠይቅ ላገኝ የቻልኩት አንድ ምክንያት ብቻ ነው፡፡ ምንድነው ምክንያቱ? ምክንያቱ ምን መሠለሽ፤ የአውሮፓ ታዛቢዎች አንመጣም ሥላሉ ይህን አይነት ሥምምነት እንዲፈረም ተደረገ፡፡ ከተፈራረምን በኋላ መጡ። ነገር ግን የአውሮፓ ታዛቢዎች በመምጣታቸው ኢህአዴግን የበለጠ ትዝብት ላይ ጣለው እንጂ ያተረፈበት ነገር የለም፡፡
ምክንያቱም ገጠር ድረስ ሄደን ምርጫውን እንዴት እንደሚያጭበረብር አሣይተናል፡፡ አስቀድመው የተዘጋጁ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ሳጥን ውስጥ ያስገቡ ነበር፡፡ ስለዚህ ምንም ላይጠቅም ነው ግርግር ሲፈጥር የነበረው፡፡
እርስዎ የምርጫ ስነ-ምግባር ኮድ በመፈራረምዎ ተፀፅተዋል?
የለም! አልተፀፀትኩም፡፡ ምክንያቱም ያቺ አንድ እድል ቀርታ እድል ሳልሠጥ ብቀር ነበር የሚቆጨኝ። ባልፈርም ነበር የሚቆጨኝ፡፡ ለምን ቢባል ያቺን ዕድል ሠጥተናቸዋል፤ አልተጠቀሙበትም፤ በጠላትነት ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ ስለዚህ ይሄ መንግስት በእርግጥ ዴሞክራሲ በፈቃደኝነት እንደማያመጣ አይተናል፡፡ እነዚህን ሂደቶች እንዳልኩሽ በመፅሀፉ ለማካተት ሞክሬያለሁ፡፡
በመጽሐፉ የተካተቱ ሌሎች ጉዳዮች ይኖራሉ?
መፅሀፉ አጭር ነው፡፡ ሌሎች ጉዳዮች በቀጣዩ መፅሃፍ ይካተታሉ፡፡ እነዚህን ሌሎች ጉዳዮች ከሠው ልጅ ኑሮ ጋር አገናኝቼ እየፃፍኩ ነው ያለሁት። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገው ህዝቡን አደንቁሮ መግዛት ነው፡፡ ህዝብ ብዙ ጩኸት፣ ብዙ ወረቀትና ብዙ ግርግር ሲበዛበት፣ ዞር ዞር ብሎ አማራጭ ሲያጣ፣ ለጊዜው ኢህአዴግ ባመቻቸው መንገድ ብቻ ይሄዳል፡፡
በዛች መንገድ ሄዶ ግን መጨረሻው የማይበጀው መሆኑን ማወቁ አይቀርም፤ ያን ጊዜ ምን አይነት መልስ እንደሚሠጥ መገመት አያቅትም፡፡ ያ ጊዜ ደግሞ እየደረሠ ነው፡፡
የዚህች አገር የፖለቲካ እጣ ፋንታ ወዴት የሚያመራ ይመስልዎታል?
እኔ በአጠቃላይ ጥሩ ነገር አይታየኝም። የኢትዮጵያ ህዝብ ሠልችቶታል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ይሄ ህዝብ ወያኔ እድል ይሠጠኛል ብሎ እንደማይጠብቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የቀረው ሆ ብሎ መብቴን አስከብራለሁ ብሎ ሲነሣ፣ ያን ጊዜ ማን መልስ እንደሚሠጥ አናውቅም፡፡ በቃ ይሄው ነው፡፡ ይህን ሁሉ ፖለቲካ ፓርቲ የሚያራባው ማን ይመስልሻል፡፡ ዘጠና እና ዘጠና አምስት ፓርቲ አለ እኮ ነው የሚባለው፡፡
ለምሣሌ ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲ ሲመሰረት ሌላ አራት ይፈጠራል። ማን ነው የሚፈጥራቸው ካልሽ ራሱ ወያኔ ነው የሚፈጥራቸው፤ ደሞዝ እየከፈለ የሚያኖራቸው ፓርቲዎች አሉ አይደለም እንዴ፡፡
እነማን?
በስም ይጠቅሱልኛል? አልጠቅስም! ራሣቸውን ጠይቂያቸው፡፡ የመንግስት ደመወዝ ተከፋዮች ስም ዝርዝር አለ። እሱን አንቺ ፈትሺ፤ “ኢንቨስትጌቲቭ ሪፖርቲንግ” የሚባል ዘርፍ አለ፡፡ እሱን ተጠቀሚ፤ እንደውም ጐበዝ ትመስያለሽ፤ እንደምንም ተሹለክልከሽ ታገኝዋለሽ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በክልሎች ስለሚፈናቀሉ ዜጐች ብዙ እየተባለ ነው፡፡ ምን አስተያየትአለዎት?
በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡
አሁን ቤንች ማጂ ዞን ብትሄጂ አሠቃቂ ነገሮች አሉ፡፡ እኔ አሁን ጉዳዩን እንዲያጣሩ የላኳቸው፣ የአማራ ተወላጆች አይደሉም፡፡ ለምን ብትይ “አማራ ኬላ” የሚባሉ አምስት ቦታዎች አሉ፣ የአማራ ተወላጆች በነዚህ ኬላዎች አያልፉም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን እንዲያጣሩልኝ የደቡብ ሠዎች ነው የላኩት፡፡ መረጃ የደረሠኝም በደቡብ ተወላጆች በኩል ብቻ ነው፡፡ አማራ ቢሄድ በመታወቂያው ይያዛል፡፡
አምስቱም ኬላዎች ላይ ፖሊስ ቆሞ ይጠብቃል፡፡ምን ምን የሚባሉ ኬላዎች?
አሁን ዝርዝሩን አምጡልኝ አላልኩም ግን እነዚህ ኬላዎች አሉ፡፡ በእያንዳንዱ ኬላም ጠባቂ ሚሊሻዎች ቆመዋል፡፡ አንዳንድ አማራ ወደዛ የቢዝነስ ሥራ ኖሮት ለማለፍ ቢፈልግ “ አንድ ሺ ብር ክፈል” እንደሚባልም ደርሠንበታል፤ ጉቦ ነው እንጂ መቸስ ደረሠኝ አይሠጠውም እኮ፡፡ ህዝቡ ተስፋ ቆርጧል፣ ሠልችቶታል፣ ከኢህአዴግ ጥሩ ነገር አይጠብቅም ብለውኛል፡፡
እርሶም ቢሆኑ ጥሩ ነገር አይታየኝም እያሉ ነው፡፡የሰላማዊ ትግሉ ፋይዳ ታዲያ ምንድነው?
የእኛ ፋይዳማ ወቅቱ ሲደርስ ህዝብ እንዳይፋጅ መጠበቅ ነው፡፡ እንዴት ብትይ … በየወረዳው ኮሚቴዎች አሉን፡፡ ድሮ ቢሮ ውስጥ ነበር፤ አሁን ቢሮ አንጠቀምም፡፡ ምክንያቱም ቢሮ ያለበት ቦታ ወያኔ ሄዶ ያስራቸዋል፤ ያፈርሣቸዋል፡፡ ስለዚህ ያለ ቢሮ እንሰራለን፡፡ ሥራችንም ህዝቡ ከገደብ በላይ እንዳይወጣ “ተወው ይደርሣል” በሚል ከፍጅት ማዳን ነው፡፡ ይሄው ነው፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar