onsdag 8. mai 2013

ታላቁ የህዳሴ ግድብና የግብፅ ስጋቶች

(በፀጋው መላኩ)
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚል ስያሜ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ በአፍሪካ ትልቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ከጀመረች አንድ ዓመት አልፎ ሁለተኛው ዓመት እየመጣ ነው። አንደኛው ዓመት እንደተጠናቀቀ የግንባታው ሰባት በመቶ መጠናቀቁ የተገለፀ ሲሆን፤ ትላንት ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምደሳለኝ ለፓርላማው በቀረቡት የመንግስት አቋም ግንባታው 11 በመቶ መድረሱን አመልክተዋል። 97 በመቶው የግብርና ምርቱን በአባይ ውሃ ላይ ጥገኛ ያደረገችው ግብፅ ከግድቡ መገንባት ጋር በተያያዘ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ አሉታዊ የሆነ ተፅዕኖን ሊፈጥር ይችላል በሚል ሥጋቷን በተለያየ
መንገድ ሥትገልፅ ቆይታለች። ኢትዮጵያ በአንፃሩ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት ከመጉዳት ይልቅ እንዳውም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በተደጋጋሚ ስትገልፅ ቆይታለች። በኢትዮጵያ በኩል ግድቡ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ባልተጠበቀ ጐርፍ እንዳይጥለቀለቁ፣ ግድቦቻቸው በደለል እንደይሞሉና የወሃ ትነቱንም ለመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ሲገለፅ ቆይቷል። ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በተለይ ግብፅና ሱዳን በግድቡ ግንባታ ላይ ሥጋት ካላቸው አጠቃላይ የግድቡን ሁኔታ የሚመረምር የኤክስፖርቶች ቡድን ተቋቁሞ የራሱን ሞያዊ ሪፖርት እንዲያቀርብ ፈቃደኝነቷን ገልፃለች።

በዚህም መሠረት International Panel of Experts በሚል አንድ ቡድን ተቋቁሞ በህዳሴው የግንባታ ቦታ በመገኘት የራሱን ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። ቡድኑ ስድስት አባላትን ያቀፈ ነው። ቡድኑ ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅና ከሱዳን ሁለት ሁለት ኤክስፐርቶችን ያቀፈ ሲሆን ከዚህ ውጪም አራት ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶችን እንዲይዝ የተደረገ ነው። የኤክሰፖርት ቡድኑ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ የመጀመሪያውን ጉብኝት በግድቡ አካባቢ በመገኘት ያደረገ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ስብሰባውንም በሰኔ ወር 2004 ላይ አድርጓል። ቡድኑ ከሰሞኑ የመጨረሻ የግድቡን የአንድምታ ተፅዕኖ ጥናቱን አጠናቆ የደረሰበትን ውጤት ለሦስቱም መንግሰታት የሚያቀርብ መሆኑን ገልጿል።
የቡድኑን የመጨረሻ ሪፖርትን ተከትሎ የሚኖሩትን ሂደቶች ጊዜው ሲደርስ የሚታይ ይሆናል። ግብፅም ሆነች ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን ሥጋት ለማጥራት ከኢትዮጵያ አንፃር የቡድኑ ጠቀሜታ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ነው የሚነገረው። በመሠረቱ ግድቡ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ውጪ ለመስኖ አገልግሎት የሚውልበት ሁኔታ የማይኖር መሆኑ በኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ስለተገለፀ የግድቡ ጉዳይ የአባይን ውሃ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመጠቀም ከሚያስችለው ስምምነት ጋር በቀጥታ የሚያገናኘው ነገር አይኖርም።
ያም ሆኖ ግን የአባይን ውሃ በተመለከተ ግብፅ በ1929 የነበረው የቅኝ ግዛት ውል በነበረበት እንዲቀጥል ፅኑ ፍላጐት ያላት መሆኑን በተደጋጋሚ ስትገልፅ ቆይታለች። በቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ በኩል ተረቅቆ በተግባር ላይ የዋለው ይህ የቅኝ ግዛት ስምምነት (Colonial Treaty) በአባይ ወንዝ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ግንባታዎች ከግብፅ ይሁንታ ውጪ እንዳይካሄዱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት እገዳን የሚጥል ነው። ከዚህም በተጨማሪ እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም 85 በመቶ የአባይን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጰያን በማግለል ግብፅና ሱዳን 90 በመቶውን የአባይ ውሃ በጋራ ለመጠቀም የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራርመው ሲተገብሩ ቆይተዋል።
ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተፋሰሱ ሥር የነበሩት ሀገራት የውስጥ ፖለቲካ የተረጋጋ አለመሆን እነዚህ ሁለት ስምምነቶች አንዳች ጥያቄ ሳይነሳባቸው እንዲቀጥሉ አድርጓቸው ቆይቷል። ጊዜው እየረዘመ በሄደ ቁጥርም ስምምነቶቹ በሌሎች ተፋሰስ ሀገራት ሳይቀር ተቀባይነት ያለው እንዲመስል አድርጐም የቆየበት ሁኔታም ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያም ሆነች ሩዋንዳ፣ ብሩንዲና ሌሎቹ ሀገራት ከጦርነት አዙሪት ወጥተው መረጋጋት ሲጀምሩ የአባይን ውሃ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በጋራ ለመጠቀም ጥያቄ ማንሳታቸው አልቀረም።
በዚህም መሠረት በተለይ ግብፅና ሱዳንን ባካተተ መልኩ ሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት በውሃው ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ለመወያየት አንዳንድ እንቅሰቃሴዎች ሲጀመሩ በተለይ ግብፅ በዚህ ዙሪያ ወደ ውይይት ለመግባት ብዙም ፈቃደኝነትን ያሳየችበት ሁኔታ አለነበረም። ሆኖም ከተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች በኋላ እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም ግብፅንና ሱዳንን ጨምሮ የዘጠኝ የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሀብት ሚኒስትሮች ኦፊሴላዊና መደበኛ በሆነ መልኩ በወንዙ ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል ላይ ተከታታይ ውይይቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። እነዚህ ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ብሩንዱ፣ ሩዋንዳና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኰንጐ ናቸው። ለተወሰኑ ዓመታትም ኤርትራ በታዛቢነት ስትሳተፍ ቆይታለች። በዚህም መሠረት የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ትብብር ተመስርቶ የቀድሞዎቹን ስምምነቶች በመሻር በአዲስና ዘመናዊ የውሃ ሀብት ክፍፍል ላይ አንድ አይነት መግባባት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድን በመቅረፁ ረገድ ከ10 ዓመት ያላነሰ ጊዜን ፈጅቷል። አብዛኛው ሂደትም ሲጓተት የቆየው በግብፅና በሱዳን እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት ሌሎቹን የላይኞቹን ተፋሰስ ሀገራት በማስተባበሩ ረገድ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራን በመስራቱ በመጨረሻ እ.ኤ.አ በ2010 የአባይን ውሃ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል በአምስት የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ትብብር ስምምነት (Cooperative Framework Agreement) ሊፈርም ችሏል። እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ በድርድሩ ላይ የነበሩት ግብፅና ሱዳን ከአስር ዓመት የድርድር ጊዜያት በኋላ ራሳቸውን ከስምምነቱ ከማግለል ባለፈ ሌሎች በጋራ ትብብር ሰነዱ ያልፈረሙ ሀገራት ሳይቀሩ ፊርማቸውን እንዳያኖሩ የራሳቸውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሲያሳድሩ ቆይቷል። ያም ሆኖ ይሄም ቢሆን ስኬትን ማግኘት ሳይችል ቀርቶ ፊርማውን በማኖሩ ሂደት ላይ የመቀዛቀዝ ሁኔታ አሳይታ የነበረችው ብሩንዲም በሰነዱ ላይ ፊርማዋን በማኖር የቀደመው የሱዳንና የግብፅ የሁለትዮሽ ስምምነት በአዲሱ ፍትሃዊ የውሃ ሀበት ክፍፍል መተካት ያለበት መሆኑን በአቋማ ገልፃለች።
በዚህ መልኩ የላይኞቹ የተፋሰስ ሀገራት የትብብር መንፈስ እየጠነከረ ሄዶ በግብፅና በሱዳን ላይ ጫና ማሳደር በጀመረበት ወቅት ግብፅ ከቀድሞው አገዛዝ ጋር በተያያዘ በውስጥ የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ በመግባቷ ሂደቱ ብዙም ወደፊት መሄድ ሳይችል የቆየበት ሁኔታ ነበር። ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ መሠረት የጣለችው የቀድሞውን የቅኝ ግዛት በመቀየር በአዲስ ስምምነት ለመተካት በኢንቴቤ የትብብር ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ ነው።
የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመሩን ተከትሎ ግብፅ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ስጋት የፈጠረባት መሆኑን በተለያየ መልከ ስትገልፅ ቆይታለች። ግብፅ ከዚህ ባለፈ ሱዳን በቀድሞው አቋማ እንድትፀና የማድረጉንም ስራ በሰፊው ስትሰራ መቆየቷ ነው የሚገለፀው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሁለቱ መንግስታት ከዚህም በኋላ አባይን በተመለከተ የጋራ አቀሟን ለማራመድ አንድ አይነት መግባባት ላይ መድረሳቸውንም በቅርቡ በይፋ ገልፀዋል። የዲፕሎማቲክ ሚስጥራዊ ሰነዶችን እየበረበረ ይፋ የሚያደርገው ዊክሊክስ (Wakileaks) በቅርቡ በለቀቀው መረጃ ደግሞ ግብፅና ሱዳን በኢትዮጵያ ድንበር በታላቁ ህዳሴ ግድብ ቅርብ ርቀት አካባቢ የአየር ኃይል ጣቢያ ግንባታን በማካሄድ በግድቡ ላይ የአየር ጥቃት ለማድረስ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ይገልፃል። ይህ መረጃ መለቀቁን ተከትሎ በርካቶች ዘንድ ስጋትንና ድንጋጤን የፈጠረ ሲሆን፤ የግብፅ መንግስት በበኩሉ መረጃውን “ከእውነት የራቀ ነው” በማለት በጠብቅ አስተባብሎታል።
ይሄንን መረጃ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት እንዴት ይመለከተዋል የሚል ጥያቄን ያነሳንላቸው የመንግሰት ኰሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሽመለስ ከማል፤ “በዊኪሊክስ በኩል የሚለቀቁት መረጃዎች ከእውነትነት ይልቅ በአሉባልታ፣ በመላምትና በግምት ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው የኢትዮጵያ መንግሰት መረጃውን መሠረት በማድረግ ያልሆነ ሰቀቀን የሚገባበት ሁኔታ የለም” በማለት መንግስት መረጃው ታአማኒ ነው ብሎ ስለማያምን ይሄንን መሠረት በማድረግ የሚወስደው እርምጃ ወይንም የሚይዘው የፖለቲካ አቋም የማይኖር መሆኑን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ መልኩ አስተያየታቸውን የሰጡት የኤዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ ሞሼ ሰሙ ግን የአቶ ሽመልስ በዊኪሊክስ መረጃ ላይ የሰጡትን አስተያየት አይቀበሉትም “ዊኪሊክስ እስከዛሬ የለቀቃቸው በርካታ የዲፕሎማቲክ ሚስጥራዊ መረጃዎች ሀሰት ሆነው አልተገኙም” ያሉት አቶ ሞሼ፤ ከዚህም በመነጨ መንፈስ የዊኪሊክስን መረጃ ትርጉም የለውም ብሎ በደምሳሳው ለመናገር አስቸጋሪ መሆኑን ነው የገለፁልን። እንደ አቶ ሞሼ ገለፃ እንዲህ አይነቱን መረጃ በዊኪሊክስ በኩል ይለቀቅም አይለቀቅም መንግስት በአባይ ላይ ፕሮጀክት ሲጀምር ሊኖር የሚችለውን ስጋት ግምት ውስጥ በማስገባት በመከላከያውና በኢንቴለጀንሱ ዘርፍ የራሱን ጠንካራ ስራ መስራት መቻል አለበት።
የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ግብፅና ሱዳን የተለየ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ የኢትዮጵያ መንግስት መረጃው ሊኖረው አይችልም የሚል እምነት የሌላቸው መሆኑን የገለፁት አቶ ሞሼ፤ ያም ሆኖ መንግስት ከኤርትራ ጋር በነበረው ጦርነት መረጃ መረዳት እንደሚቻለው የመንግስት ችግር መረጃውን ማግኘቱ ላይ ሳይሆን የመረጃ አተናተኑ ላይ መሆኑን ገልፀዋል። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት የኤርትራ መንግስት በአንድ ሺ ኪሎ ሜተር ድንበር ላይ የምሽግ ቁፋሮ ሲያካሂድና የጦር መሣሪያን ወደ ድንበር አካባቢ ሲያስጠጋ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት መረጃ አልነበረውም ማለት የማይቻል መሆኑን የገለፁት አቶ ሞሼ ያም ሆኖ ግን መንግስት ያገኘውን መረጃ የተነተነበት መንገድ ከኤርትራ መንግስት ጋር ደርግን ከመታገል ታሪክ ጋር የተያያዘ ስለነበር የመረጃው አተናተን ስህተት እንደነበር ገልፀዋል። ከመረጃ አተናተን ጋር በተያያዘ ችግር ሀገሪቱ ወረራውን ለመቀልበስ ከባድ መስዋዕትነትን ለመክፈል የተገደደችበት ሁኔታ መኖሩን በማስታወስ የህዳሴውንም ግድብ በተመለከተ መንግስት የሚያገኛቸውን ማናቸውንም መረጃዎች በመተንተኑ ረገድ ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርግ የሚገባው መሆኑን አቶ ሞሼ ይገልፃሉ።
በአባይ ዙሪያ በርካታ ትንታኔዎችን የሚሰጡት ሱዳናዊው ፕሮፌሰር ዓሊ አብደላ ዓሊ የአባይን የውሃ ክፍፍል በተመለከተ ግብፅ ሱዳንን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመችበት መሆኑን ይገልፃሉ። ግብፅና ሱዳን በአባይ ወንዝ ከመተሳሰራቸው በተጨማሪ ረዥም የጋራ ድንበርን የሚጋሩ ሀገራት ናቸው። የሁለቱን ሀገራት ታሪክ ወደ ኋላ ሄዶ ለተመለከተ ግብፃውያን ሱዳንን በኃይል ተቆጣጥረው ያስተዳደሩባቸው ረዥም ዘመናት አሉ። ይህ የታሪክ ሂደት የፈጠረው ስሜት ዛሬም ቢሆን የግብፃውያኑን የበላይነት ስሜት የሰበረው አይመስልም። ፕሮፌሰሩ በተለያዩ ጊዜያት በተለይ በሱዳን ትሪብዩን ድረገፅ ላይ በሚያሰፍሯቸው ጽሁፎች ሱዳናውያን ከግብፃውያን የታሪክ ሂደት አንፃር ሲታዩ በጉልህ የማይታዩ ህዝቦች (Low Profile People) ናቸው በማለት ያስቀምጡታል። ይህ በተለይ አባይን በተመለከተ ግብፅ የሱዳንን ፖለቲካ በፈለገችው አቅጣጫ እንድትቃኝ አድርጓታል። ፕሮፌሰሩ ከዚህ አንፃር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በመቃኘት በ2010 በ International Center for African Studies ሰሚናር ላይ ባቀረቡት አንድ ጥናታዊ ፅሁፍ ዓለም በከፍተኛ ደረጃ እየተለወጠ መሆኑን ገልፀው የቀደሙት ውሎች ጊዜ ያለፈባቸው መሆኑን በማመልከት ይልቁንም ሱዳን አዲሱን ውል እንድትፈርም ሀሳባቸውን የሰጡበት ሁኔታ ነበር። ከዚህ አንፃር ፕሮፌሰሩ ሌሎች ሀገራትን የአባይን ውሃ እንዳይነኩ ታሳቢ በማድረግ ብቻ የተመሰረተው የሱዳንና የግብፅ አንድ አይነት አቋም ባለበት የማይቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።
ግብፅ ቀደም ባሉት ዓመታት በተለይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ስታግዝ መቆየቷ በተደጋጋሚ ሲገለፅ የቆየ ሲሆን፤ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የሱዳን አንድነትና ሰላም ተጠብቆ እንዲቆይ በርካታ ስራዎችን ስትሰራ ቆይታለች። እንኳን ሌላ አለተሳካም እንጂ ደቡብ ሱዳን ሳይቀር ከሱዳን ተገንጥላ ነፃነቷን እንዳታውጅ ግብፅ የተቻላትን ሁሉ አድርጋለች።
የግብፅ የእጅ አዙር ተፅዕኖ ከዚህም ባለፈ በአባይ ዙሪያ በኢትዮጵያ ለሚሰሩ ፕሮጀክቶች የአበዳሪ አካላት ይሁንታ እንዳይኖር ከመከላከል ባሻገር በተለይ የህዳሴ ግድብ በታሰበለት ጊዜና እንዳይጠናቀቅ ተፅዕኖ የመፍጠር ሁኔታዎች እንዳሉ አንዳንዶች ይገልፃሉ። በቅርቡ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድረጅት (IMF) ኢትዮጵያ አኰኖሚዋን ለማረጋጋት የህዳሴውን ገንዘብ ግንባታ እንዳታቀዛቅዝ ሀሳብ የማቅረቡንም ጉዳይ ከዚሁ ጋር የሚያያይዙት ወገኖች አሉ።
ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ መገንባቷ በግብፅ የውሃው ፍሰት ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ የማይኖር መሆኑ በአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት ቢረጋገጥ እንኳን የግብፅ ስጋት ከዚህም ያለፈ ነው የሚሆነው። በአንድ መልኩ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ከፍተኛ ትርፍ የምታገኝበት ሁኔታ ስለሚፈጠር በቀጣይ በአባይ ወንዝ ፕሮጀክቶች ላይ በራሷ አቅም ግንባታዎችን እንድታከናውን እገዛ የሚፈጥር ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ከዚሁ የሚመነጨው አቅምም የሀገሪቱን የተደራዳሪነት አቅም የሚያጐለብት ነው የሚሆነው። ግብፅ እስከዛሬ ድረስ በተፈጥሮ ወንዞች የሚፈሱትን ውሃ በቀጥታ ስታገኝ የነበረ ሲሆን የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ግን በአብዛኛው በግድብ የሚያልፍን ውሃ (Managed Water) የምታገኝ ይሆናል። ይህም በራሱ ሌላኛው ስጋት ሆኖ የሚጠቀስ ነው። አቶ ሞሼ ግብፅ በተለያዩ መልኩ በአባይ ወንዝ ላይ ስጋቶች ቢኖራትም ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር የሚሰሩትን ግድቦች ለማስቆም የማትችልበት ጊዜ ስለመጣ ተባብሮ ከመስራት ባለፈ ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ ሁሉ ጊዜ ያለፈበት መሆኑን ይገልፃሉ። አቶ መለሰ ቀደም ሲል የሰጡትን ሀሳብ “Struggle over the Nile” በሚል ርዕስ ያስተናገደው የአልጀዚራ ዶክመንተሪም ይሄንኑ ሀሳብ የሚያጠናክር ነው።
ከዚህ ባለፈ ሌላኛው የግብፅ ስጋት እስራኤል ከላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር በግብርናው ዘርፍ በጋራ በመስራት ናይልን እንደ አንድ የፖለቲካ መሳሪያ ልትጠቀምበት ትችላለች የሚል ነው። ፕሮፌሰር ዓሊ አብደላ ዓሊ በተለያዩ ጊዜያት በሱዳን ትሪብዩን ድረገፅ ላይ ባሰፈራቸው ጽሁፎች ላይ በርካታ የእስራኤል የውሃ ኤክስፐርቶች ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ መጐብኘታቸውን ይገልፃሉ። ባለፈው ሳምንት ብቻ Struggle over the Nile የሚለውን ዘጋቢ ፊልሙን በአባይ ወንዝ ላይ ያለውን ውጥረት በማሳየት ከአምስት ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ በማስተላለፍ ሰፊ መረጃን ያቀረበው አልጀዚራ ቴሌዥንም ይሄንኑ የእስራኤልን ጉዳይ እንደ አንድ ስጋት የሚታይ መሆኑን ያመለክታል። በቀጣይ በተለይ ህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ (ግብፅና ሱዳን) የሚኖረው ተፅዕኖ የሚቀርበው የኤክስፐርቶቹ ሪፖርት በጉጉት ይጠበቃል።
ግብፅ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ከፖለቲካው ይልቅ በአብዛኛው በልማትና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ እንዲመሠረት እያደረገች ነው። በተለይ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ወቅት ጀምሮ በርካታ የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ በቅርቡም በምክትል ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማግዲ አሚር የተመራው ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ባደረገው ቆይታ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር የትብብር ልማትንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጐት ያላት መሆኗን ገልፀዋል። ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ በሚገኘው ግብፅ ኢምባሲ መግለጫ የሰጡት የግብፅ የጤና የልዑካን ቡድን አባላትም ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር በትምህርትና በጤናው ዘርፍ በስፋት በጋራ ለመስራት ሰፊ እቅድ ይዛ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ገልፀዋል። አንዳንዶች ይህ የግብፅ ማዘናጊያ ስትራቴጂ ይሆናል የሚሉ አስተያየቶችን እያሰሙ ሲሆን፤ አቶ ሞሼ በአንፃሩ በተለይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖረው መሆኑን ነው የሚገልፁት።
*Originally published on the Amharic weekly, Sendek, on Oct. 17, 2012, 

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar