“ሙሰኞቹ” ፍርድ ቤት ቀረቡ፤ ሌሎችም ታሰሩ!
(EMF) ከመለስ ዜናዊ ጀርባ ይቀመጥ የነበረው የህወሃት አባል፤ አስመላሽ ወልደማርያም ዛሬ ከቀድሞ የጉምሩክ ዳይረክተር አቶ መላኩ ፈንታ ጋር ዛሬ 2ኛ የፌዴራል ወንጀል ችሎት ቀርበው ነበር። ከነሱም ጋር አቶ እሸቱ፣ አቶ ማርክነህ፣ አቶ ከተማ፣ አቶ ስማቸው እና አቶ ፍቅሩ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የአቃቤ ህግ ክስ እንደሚያስረዳው “ግለሰቦቹ ህግ እና ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ የሌሎችን ቢዝነስ በድለዋል” የሚል ይዘት ያለው ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የህወሃት አባል እና የጉምሩክ ም/ል ዳይረክተር የነበሩት አቶ ገብረዋህድ በተመሳሳይ መልኩ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ችሎት ቀርበው ነበር። ፖሊስ በጠቅላላ ተከሳሾች ላይ፤ ለተጨማሪ መረጃ የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል። ሆኖም ተከሳሾች ቢሮ እና ቤታችን ተበርብሮ መረጃ ስለተወሰደ ተጨማሪ ጊዜ መሰጠት የለበትም፤” ሲሉ ተቃውመዋል። በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ መረጃውን እስከነገ ጨርሶ ነገ እንደገና እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል።
“ተከሳሾች ከሃይማኖት አባቶች፣ ከጠበቆች እና ከቤተሰባችን ጋር እንዳንገናኝ ተደርጓል። ህገ መንግስታዊ መብታችን ተገፏል።” በማለት ቅሬታ አሰምተዋል። ከዳር ሆኖ ሁኔታውን ለሚታዘብ ሰው፤ የእነዚህ ሰዎች ጥያቄ ትንሽ ፈገግ ሊያሰኝ ይችላል። እነ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ አንዷለም አራጌ፣ ርዕዮት አለሙና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ሃሳባቸውን በነጻ ስለገለጹ ብቻ “አሸባሪዎች” ተብለው መብታቸው ተገፎ ሲሰቃዩ በሞቀ ቤታቸው ተንደላቀው ተኝተው ነበር። አሁን ግን በሙስና ወንጀል ተከሰው ውሎ እና አዳራቸው እስር ቤት ሆኗል።
በቅርቡ እስክንድር ከቃሊቲ በላከው የእንግሊዘኛ ደብዳቤ ላይ የጻፈውን እዚህ ላይ ማስታወሱ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። “አሳሪዎቼ በሞቀ አልጋቸው ውስጥ ከሚስቶቻቸው ጎን በቤታቸው ይተኛሉ። እኔም ቅማልን ብቸኛ ጓደኛዬ አድርጌ፤ በእስር ቤት ውስጥ ለሊቱን አሳልፋለሁ – የህሊና ሰላም ግን አለኝ።” ብሎ ነበር። እነዚህ ሰዎች… የእስክንድር ነጋን አባባል ሊጋሩት ይችላሉ። ሆኖም ህሊናቸው ነጻ ስላልሆነ፤ ስቃያቸው የበዛ ነው። ትላንት በሌላው ሲዛበቱ እና ሲስቁ፤ በሙስና ወንጀል ሲራቀቁና ሲሰርቁ ነበርና ዛሬ የህሊና ሰላም የላቸውም። ወደፊት በህግ ከተፈረደባቸው ደግሞ፤ የእስር ቤት ቅማል ገላቸውን ብቻ ሳይሆን ህሊናቸውንም ይበላዋል። ለሁሉም ግን የፍርድ ሂደቱን ተመልክተን ወደፊት የምንለው ይሆናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የናዝሬቱ ጉምሩክ ሃላፊ ተመስገን ጉልላት ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በጋምቤላ በኩል አድርጎ ሊጠፋ ሲል ተይዟል። የጋምቤላ ጉምሩክ ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋም የናዝሬቱን ሃላፊ በመርዳቱ አብሮ ታስሯል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar