lørdag 25. mai 2013
ወያኔ ኢትዮጵያን እጅግ በሚጎዳ መልኩ ከሱዳን ጋር የድንበር ስምምነት ተፈራርሟል
- አቶ አገኘሁ መኮንን
የኢሕአዴግ ምንግሥት በትረ ስልጣኑን ከጨበጠበት ቀን ጀምሮ እንደ መንግሥት ለሚመራት
ሀገር ጥቅምና ሉዐላዊነት ከመቆም ይልቅ በተቃራኒው በመቆም ኢትዮጵያን የጎዳባቸው ድርጊቶች
ብዙ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ደብቆና ሕገወጥ በሆነ ሁኔታ ለሱዳን
የሰጠው ከፍተኛ መሬት ነው።
ኢሕአዴግ ራሱ የቀረፀውና እመራበታለሁ የሚለው ሕገመንግሥት አንቀፅ 86 ቁጥር 3፦
“የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በጋራ ጥቅምና በዕኩልነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን
እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ
መሆናቸውን ማረጋገጥ።” ቢልም፣ ወያኔ ግን የሚሠራው ከዚህ ፍፁም ተቃራኒውን ነው። የሌለ
ስምምነትን ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያን ጥቅም እጅግ በሚጎዳ መልኩ ከሱዳን ጋር ስምምነት
ተፈራርሟል።
ወያኔ ዋቢ የሚያደርገው ስምምነት አፄ ምኒልክ በ1902 ከእንግሊዝ ጋር ያደረጉትን ስምምነት እና
እርሱን ተከትሎ ሻለቃ ጉዊን የተባለ የእንግሊዝ ሞኮንን በ1903 ያደረገውን ክለላ ነው። ይህ
ሻለቃ ጉዊን ያደረገው ክለላ ግን እርሱ ራሱ በሪፖርቱ “ከተሰጠኝ ስልጣን በላይ ሄጀ የስምምነቱን
መሥመር አዛብቻለሁ” ብሎ መሥክሯል። ስምምነትን ጥሶ የተደረገ ክለላን ደግሞ ኢትዮጵያ እንድትቀበል የሚያስገድዳት ምንም
ዓይነት ዓለማቀፋዊ ሕግ የለም። በዚህም ምክንያት አፄ ምኒልክ ጉዊን እርሳቸው ከተስማሙበት የድንበር ወሰን እያለፈና
ኢትዮጵያን በጎዳ ሁኔታ በመከለሉ ክለላውን አልቀበልም ብለው ከክለላው በኋላ የተሠራው ካርታ ላይ እንግሊዞች ፊርማቸውን
አስቀምጠው አፄ ምኒልክም ማህተማቸውን እንዲያሳርፉበት ሲጠይቋቸው ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው የእርሳቸው ማህተም
ሊደረግበት የነበረው ቦታ እስከአሁን ድረስ ክፍት ሆኖ ይታያል። በዚህ ሁኔታ በአፄ ምኒልክ ውድቅ የተደረገውን የጉዊን የክለላ
ነው ወያኔ አፄ ምኒክ የጉዊንን ክለላ ተቀብሏል እያለ ሕዝብን የሚያወናብደው።
ወያኔ ቀጥሎ የሚጠቅሰው ስምምነት ደግሞ በ1972 (እ.አ.አ.) በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜ ከሱዳን መንግሥት ጋር
ተደረገ የተባለን የደብዳቤ ልውውጥ ነው። በዚህ የደብዳቤ ልውውጥም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሥት የጉዊንን የወሰን መሥመር
በፍፁም አልተቀበለም። የአፄ ኃይለ ሥለሴን መንግሥት የተካው የደርግ መንግሥትም ቢሆን ይህንን ከስምምነት ውጭ የተከለለ
የጉዊን መሥመር የተቀበለበት አንድም መረጃ የለም። ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ግን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን የሱዳን
ጠበቃ በሚያስመስልባቸው የፓርላማ ንግግር የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት “የጉዊንን መሥመር ተቀብሏል” እያሉ በሃሰት
ተናግረዋል። ኢትዮጵያን እመራለሁ የሚሉት አቶ መለስ ዜናዊ በዚያን ቀን ንግግራቸው እንኳን የደብዳቤ ልውውጡን ይዘት
ተረድቶ በትክክል ሊያቀርቡ ይቅርና ስለየትኛው ስምምነት እንኳን እንደሚያወሩ አያውቁትም ነበር። በተደጋጋሚ የሚናገሩት
“በ1907 እንደተፈረመው፣ በ1909 እንደተከለለው” እያሉ የሌለ ፊርማና ክለላ ነበር የሚያወሩት። በአድናቂዎቻቸው ሊቅ ይባሉ
የነበሩት አቶ መለስ ቀደም ብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፓርላማ ይዘውት የቀረቡት መልስ የሌለ ስምምነትና ክለላ ነበር። ኢትዮጵያ
ከሱዳን ጋር በ1907 ምንም ዓይነት ውል አልተፈራረመችም፤ በ1909ኝም ምንም ዓይነት የድንበር ክለላ አላካሄደችም። ውሉ
የተፈረመው በ1902 ሲሆን ክለላውም ምንም እንኳን (ከላይ እንደጠቀስኩት) በአፄ ምኒልክ ባይፀድቅም በ1903 ነው። የራሱን
ሕገመንግሥት ጥሶ የጉዊንን የወሰን መሥመር የተቀበለው አንዱና ብቸኛው መንግሥት የኢሕአዴግ መንግሥት ብቻ ነው። ይህም
በእኛ በኢትዮጵያውያን ሳይሆን በወዳጁ በሱዳን መንግሥትም ኖቬምበር 19 2007 በሱዳን ትሪቡን በወጣ ጽሑፍ እንደሚከተለው
ተረጋግጧል፦ “The relations between Sudan and Ethiopia were empoisoned by the issues of border
demarcations in the past. The government of the ruling EPRDF is the first Ethiopian government to be willing
to talk with Sudan on the border issue.”
ከወያኔ መንግሥት በፊት የነበሩትን መንግሥታት የሱዳን መንግሥት የሚገልፃቸው በዚህ መልኩ ነበር። ምክንያቱም የኢትዮጵያን
ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ መንግሥታት ስላልነበሩ! የወያኔ መንግሥት የፈፀመው ግን የሀገር ክህደት ወንጀል በመሆኑ የዚህ
ወንጀል ፈፃሚዎች መቸም ይሁን መቸ አንድ ቀን ለፍርድ ይቀርባሉ።
የታሪክ ተመራማሪው አገኘሁ መኮንን የሚኖሩት በእንግሊዝ ሀገር ነው።
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar