ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ
አዲስ እየተዘጋጀ ባለው ረቂቅ ሕግ በዋናነት የግል ዘርፍ አካላትን በሙስና ወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በተለይም በመቶ ሚሊዮኖች ገንዘብ የሚገመት ሀብት እያንቀሳቀሱ ያሉ፣ የሕዝብ ሀብት የሚያስተዳድሩ የግል ዘርፍ አካላት ላይ ረቂቅ ሕጉ አተኩሯል። እነዚህ አካላት በማንኛውም አግባብ ከአባላቶቻቸው ወይም ከሕዝብ የተሰበሰበ ወይም ለሕዝባዊ አገልግሎት እንዲውል የተሰበሰበ ገንዘብ፤ ንብረት ወይም ሌላ ሀብትን የሚያስተዳድሩ ወይም የሚያንቀሳቅሱ አክሲዮን ማኅበራት በማኑፋክቸሪንግ፣ በእርሻ፣ በንግድ፣ በኮንስትራክሽን፣ በትራንስፖርት፣ በፋይናንስ እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት መካከል በአክሲዮን የተቋቋሙ ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሐዋላ ተቋማት የሙያና የብዙሃን ማኅበራት ፌዴሬሽኖችና ኮንፌዴሬሽኖች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች፣ ኢንዶውመንቶችና የልማት ማኅበራት (ለምሳሌ አልማ፣ ኦልማ፣ ወዘተን) ያካትታል።
ሕጉን እንደገና ለማሻሻል ያስፈለገው ሙስናን የሚፀየፍ ኅብረተሰብ እንዲፈጠር የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም፤ በግል ዘርፍ የሚፈፀም ጉቦኝነትና ምዝበራ በሙስና ወንጀል የሚያስቀጣ በመሆኑ ሲሆን፤ አዲሱ ረቂቅ ሕግም ከሲንጋፖር፣ ከስዊዲንና ከደቡብ አፍሪካ ተመሳሳይ ሕጎች በመቀመር መዘጋጀቱም ታውቋል።
በአዲሱ ሕግ መሠረት ለሕዝብ ተብሎ የተሰበሰበ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ እና የሚያስተዳድሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በሙስና ወንጀል እንዲጠየቁ ማድረጉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን በሕጉ ያልተካተቱ ሲሆን፤ ሌሎች የሕዝብን ገንዘብና ሀብት የሚያስተዳድሩ ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት፣ እድር እና ተመሳሳይ ባህላዊ ወይም ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ማኅበራት አባላቱ እርስ በርስ የሚተማመኑና ለሙስና የመጋለጥ ዕድላቸው ዝቅተኛ በመሆኑ፣ በሙስናውም ቀጥተኛ ተጠቂ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥቂቶች በመሆናቸውና ከሚያንቀሳቅሱት ሀብት አነስተኛነት የተነሳ በሙስና ተጠያቂ በማድረግ ከሚድነው ሀብት ይልቅ ተጠያቂ ለማድረግ የሚባክነው ሀብት ከፍተኛ በመሆኑ ከሕጉ ውጪ ተደርገዋል።
በአዲሱ የሙስና ወንጀል ረቂቅ ሕግ በግለሰብ ባለሀብት ወይም ባለሀብቶች የተቋቋመ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በሙስና ወንጀል አይጠየቅም።¾
በእነ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ መዝገብ ስር የተዘረዘሩት 12 ተጠርጣሪዎች ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው
- በእነ መላኩ ፈንታ መዝገብ ያሉ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ዛሬ ይታያል
- አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር ድብደባ ተፈፅሞብኛል አሉ
በአሸናፊ ደምሴ
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ተጨማሪ ጊዜ በተጠየቀባቸው በእነ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ መዝገብ ስር የሚገኙ አስራሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀኑ ጊዜ ቀጠሮ ሲፀናባቸው፤ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ በሦስት የተለያዩ መዝገቦች የተዘረዘሩትን 22 ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ለመመርመር ደግሞ ዛሬን ጨምሮ ሐሙስና አርብ ተለዋጭ ቀጠሮዎችን ሰጥቷል።
ችሎቱ በዕለቱ ሲሰየም ኮሚሽኑ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት ለመስማት እንደሆነ ፍርድ ቤቱ አስታውሶ፤ ለፌዴራሉ ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ተወካዮች ሀሳባቸውን እንዲያስረዱ ዕድል በመስጠት ጀምሯል። በችሎቱ የተገኙት የመርማሪ ቡድኑ ተወካይም ቡድኑ ያሳካቸውንና ያላሳካቸውን የምርመራ ውጤቶች በሁለት ከፍለው ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል። በዚህም በዘጠኝ ተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት በመድረስ የኤሌክትሮኒስ መሳሪያዎችን፣ የተደበቁ ሰነዶችንና በህገወጥ መንገድ የተገኙ ገንዘቦችን (መኒ ላውንደሪ) መሰብሰቡን ጭምር ገልጿል። አክሎም የ28 ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጡን የሚያስረዱ ሰነዶችን፣ ስምንት በቫት ማጭበርበር ተጀምረው የተቋረጡ ክሶችን፣ ኦዲት ያልተደረጉ ሰነዶችን እና የ15 ምስክሮችን ቃል ስለመቀበሉ ካጠናቀቃቸው ውጤቶች አንኳሮቹ ናቸው ሲል አስረድቷል።
በአንፃሩ ደግሞ የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን አላጠናቀኳቸውምና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ጥያቄ ያቀረበባቸው ጉዳዮች መካከል፤ ተጨማሪ የሙስና ወንጀሎች የታገዱባቸው ሰነዶች፣ የታገዱ ንብረቶችን ማጣራት፣ ከአራጣ ብድር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማጥራት፣ የምርመራ ስራው ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ቦታዎች የሚካሄድም ጭምር መሆኑን እና በምርመራ ቡድኑ አማካኝነት የተገኙ ሰነዶችን መርምሮ ከክስ መዝገቡ ጋር እንዲያያዙ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ተጨማሪ 14 ቀናትን ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድ ጠይቀዋል።
ሰኞ ከሰዓት በኋላ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት በቀዳሚነት ጉዳያቸው በችሎቱ መሰማት የጀመረው በሁለተኛ የክስ መዝገብ ስር የተዘረዘሩት 12 ተጠርጣሪዎች ሲሆን፤ በዚህም ስር የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ ጨምሮ ሌሎችም ባለስልጣናት እና ነጋዴዎች በሙስና ወንጀሉ ተሳታፊ ሆነዋል የተባሉ ቤተሰቦች በችሎት ቀርበው በጠበቆቻቸው በኩል ጉዳያቸውን አስረድተዋል።
አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸው በኩል ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ጥያቄና አቤቱታ መሠረት፣ መርማሪ ቡድኑ በቂ ማስረጃዎችን ሰብስቤያለሁ ያለ መሆኑን በመጥቀስ፤ አንዳንድ ተጠርጣሪዎችም አሁን ድረስ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ክስ አለማወቃቸውን እና በጤናና በቤተሰብ ጉዳይ ላይ ተንተርሶ የዋስትና መብታቸው እንዲከብር ጥያቄ አቅርበዋል።
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ በጠበቃቸው አማካኝነት የምርመራ ቡድኑ አገኘሁት ያለው መረጃ በቂ ሆኖ ሳለ ሁለት ህፃናት ልጆቼ በችግር ላይ ስለሚገኙ የዋስ መብቴ ተጠብቆ ከእስር ልለቀቅ ይገባል የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።
አቶ ገብረዋህድ አክለውም፤ ሁለት ህፃናት ልጆቼ የሚንከባከባቸው በሌለበት መልኩ እንዲኖሩ ተገደዋል። ባለቤቴም ሆነች እህቷ የተመሠረተባቸው ክስ ሰነድ መደበቅ ቢሆንም ተደብቋል የተባለው ሰነድ ግን ቀድሞም በኮሚሽኑ እጅ የገባ መሆኑን በማስታወስ፤ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች በዚህ ክስ ስር መጠቃለላቸው አግባብ አይደለም ብለዋል። ይህም በመሆኑ ፍ/ቤቱ ሁለቱን የቤተሰብ አባላት በዋስ መብታቸው ተጠቅሞ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል።
በሌላም በኩል በተለይም በሁለተኛው የክስ መዝገብ ስር 5ኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር በምርመራ ወቅት ከፍተኛ ድበደባ እንደተፈፀመባቸውና ለሁለት ጊዜያት ያክል ራሳቸውን ስተው እንደነበር በማስታወስ፤ “በእስር ቆይታዬ አገሬ ምን እንደምትመስል አውቄያለሁ” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር የልብ፣ የደምና የስኳር ህመምተኛ መሆናቸውን ጭምር በማስረዳት የዋስትና መብት ጠይቀዋል። በዚሁ መዝገብ 3ኛ ተጠርጣሪ ሆነው የቀረቡት አቶ ጥሩነህ ባልቻ በበኩላቸው ሕገመንግስቱንና ሰብዓዊ መብትን በሚቃረን መልኩ በዱላ የታገዘ ምርመራ ተፈፅሞብኛል ሲሉ ቅሬታቸውን ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል።
በመዝገቡ ስር ሁለተኛ ተጠርጣሪ ሆነው የቀረቡት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣና ዋና ኦዲተር አቶ በላቸው በየነ፤ በጠበቃቸው አማካኝነት በቂ ማስረጃና ኤግዚቢት ይዘናል፤ ሠነድ ሰብስበናል ካሉ በኋላ የደንበኛዬን የዋስትና መብት በመገደብ ተጨማሪ የ14 ቀናት ቀጠሮ ሊጠይቅ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል። ለ27 ዓመታት በመንግስት መስሪያ ቤት ማገልገላቸውን ያስረዱት ተጠርጣሪው፤ እኔ የምተዳደረው በወርሐዊ ደመወዜ ነው ሲሉ በእርሳቸው መታሰር ምክንያት ቤተሰባቸው ችግር እንደገጠመው በመጥቀስ ፍርድ ቤቱን የዋስትና መብት ይከበርልኝ ሲሉ ጠይቀዋል።
በድምሩም በችሎቱ ለመርማሪ ቡድኑ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ፍርድ ቤቱ አፅንኦት የሰጡባቸው ሦስት አበይት ጉዳዮች ሲኖሩ፤ ይኸውም ቡድኑ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ሲጠይቅ ምንን እንደሚጠይቅ ቢታወቅም ማንን እንደሚጠይቅ በግልፅ አለመቀመጡን፣ የሚሰሙት ምስክሮች በማን ላይ ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ስለመሆናቸውና የትኛው ተከሳሽ በየትኛው ክስ ስር ተጠያቂ እንደሆነ በግልፅ አለመስፈሩ ተጠቁሟል።
የምርመራ ቡድኑ ተወካዮች በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ፤ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የተጠየቀው ወንጀሉ እጅግ ውስብስብና ሰንሰለታማ መሆኑን በመጥቀስ፤ ተጠርጣሪዎቹ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ከመሆናቸው አንፃር ከእስር በዋስ ቢለቀቁ ማስረጃዎችን ከማጥፋትም በላይ ምስክሮችን ሊያሸማቅቁ አሊያም ሊያግባቡ የሚችሉ ናቸው ሲል አስረድቷል።
በምርመራ ሂደት ውስጥ ተፈፅሟል ለተባለው ሕገ-መንግስቱን የጣሰ የሰብዓዊ መብት ችግር አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ፣ ጉዳዩ ለፍርድ ቤት ሲደርስ ተጠርጣሪዎቹ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ችግሮች ካሉ እናርማለን የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የህክምናና የቤተሰብ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡም፤ ታማሚዎች ካሉ ማረሚያ ቤቱ የራሱ የሆነ ክሊኒክ መኖሩን በመጥቀስ ከክሊኒኩ በላይ ለሆኑ ህመሞች በሪፈራል ደረጃና ከዚያም በላይ ለማሳከም የሚያስችል አቅም መኖሩን ጠቅሰዋል። ቤተሰብን በተመለከተ በተለይም 1ኛ ተጠርጣሪ በሰጡት አስተያየት ላይ ተመርኩዘው ሲያስረዱ ከቤተሰቡ የተገኘው ሰነድ እንዳለ ሆኖ መርማሪ ቡድኑ የሚፈልጋቸው ሌሎች ሰነዶችም ስለመኖራቸው በመግለፅ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ መብት ከእስር ቢለቀቁ አስቸጋሪ ይሆንብናል ብለዋል።
በጥቅሉም ለተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት መስጠትን በሚመለከት በወንጀለኛ ሕጉ ላይ፤ የተፈፀመው ወንጀል በሀገር ሀብት ላይ ከሆነና ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል መሆኑ ከግምት ከገባ ዋስትና እንደማይሰጥ ይደነግጋል ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱም፤ ተከሳሾቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከባድና ውስብስብ መሆኑን በመጠቆም የዋስትና መብታቸውን ውድቅ አድርጐ ለመርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ የ14 ቀናትን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል። አያይዞም በሰጠው ትዕዛዝ፤ የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብት በሚመለከት ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባው አሳስቦ የምርመራ ሂደቱም ግልፅ ይሁን ሲል ትዕዛዝ በመስጠት ለሰኔ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በተያያዘ ዜና በሙስና ወንጀል የተጠርጣሪዎቹን ቁጥር ወደ 54፤ የክስ መዝገቡን ደግሞ ወደ ሰባት ያደረሰው የእነመልካሙ እንድርያስ ጉዳይ በመርማሪ ቡድኑ የተጨማሪ ቀነ ቀጠሮ በመጠየቁ ለግንቦት 23 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል። በዚህ መዝገብ የተዘረዘሩት ግለሰቦች መልካሙ እንድርያስ የናዝሬት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ሰራተኛ፣ ወ/ሮ አልማዝ ከበደ የባሕር ትራንዚት ስራ አስኪያጅ፣ አቶ ዳዊት መኮንን ደላላ እና አቶ ዳዊት አብተው ሠራተኛ ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች የተጠረጠሩት ከትራንዚት ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር እቃዎች የጉምሩክን ስርዓት ባልጠበቀ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግና ያልተገባ ሀብትን ማካበት በሚሉ ወንጀሎች ነው።¾
ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ የረቡዕ ሚርይ 29 ዕትም አዲስ አበባ
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar