“ቆብ ቀዶ መስፋት የስንፍናና ሥራ ፈትነት እንጂ የችሎታና የብቃት ማሳያ ተግባር ሊሆን አይችልም”
ከጥላሁን እንደሻው (የመድረክ ሊቀመንበር)
በአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት አባላት በመድረክ ላይ ሰሞኑን የተከፈተውን አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ በሚመለከት የቀረበ ማብራራሪያ፡-
በቅድሚያ በመድረክ ላይ ሰሞኑን በየሚዲያዎቹ እየተካሄደ ያለው አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ በአንድ ግለሰብና በሌሎች ደጋፊዎች አማካኝነት ቢመስልም በመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአንድነት ተወካዮች የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና አቶ አሥራት ጣሴ ግንቦት 7 ቀን 2005 ዓ.ም በተካሄደው የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እውነቱን አውጥተው ተናግረዋል። በዚሁም መሠረት አቶ ሃብታሙ አያሌው የሚባለው ግለሰብ በየሚዲያዎቹ መድረክን ስለማፍረስ ፕሮፓጋንዳ የጀመረው በራሱ ተነሳሽነትና ውሳኔ ሳይሆን የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት አመራሮች በተለይም የም/ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን ና የግምገማ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ በላይ ፈቃደ በሰጡት ፈቃድና ትዕዛዝ መሆኑን ገልፀዋል።
አሁንም ቢሆን የብሔራዊ ም/ቤቱ ግለሰቡ የሚያካሂደውን አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ የሚያስተባብል መግለጫ ለማውጣትም ሆነ የእርማት እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆኑን ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት በመድረክ ሥ/አ/ኮ የአንድነት ተወካዮች በስብሰባ ላይ በግልጽ አስረድተውናል። ስለዚህ ሁሉም የብሔራዊ ም/ቤት አባላት ይህንን አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ይደግፋሉ ብሎ ማጠቃለል የማይቻል ቢሆንም ነገሩ የግለሰብ ጉዳይ አለመሆኑንና በብሔራዊ ም/ቤት መሪዎች ግለሰቡ የጀመረውና የቀጠለበት ጉዳይ መሆኑን አንባቢያንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳልኝ እፈልጋለሁ። እውነቱን ለነገሩን የአንድነት ፓርቲ ተወካዮች በወቅቱ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ምስጋናዬን ያቀረብኩ ሲሆን አሁንም ደግሜ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ። እኔም ነገሩ የግለሰብ ይሆን እንዴ? ብዬ በትዕግሥት ስከታተል ከቆየሁ በኋላ በብሔራዊ ም/ቤት አመራር ደረጃ እጃቸውን ያስገቡበት ጉዳይ መሆኑን ስለተረዳሁ በመድረክ ውስጥ የተሠራውን እውነተኛ ሥራ በማስረዳት ሕብረተሰቡን በሐሰትና አፍራሽ በሆነ ፕሮፓጋንዳ ለማወናበድና ለማሳሳት እየተንቀሳቀሱ ያሉትን እነዚህ ግለሰቦች የሚያካሂዱትን መሠረተ ቢስ ፓሮፓጋንዳዎች ለመከላከል እንደመድረክ ሊቀመንበርነትም ሆነ እንደ አንድ እውነትን ደጋፊ ዜጋ የበኩሌን ድርሻ መወጣት ግዴታ ስለሆነብኝ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ብዕሬን ማንሳቴን ለአንባብያን በቅድሚያ መግለጽ እፈልጋለሁ። እውነት እስኪታወቅ ድረስ ሐሰት እውነት መስላ ብዙ ሰዎችን ልታሳስት ስለምትችል ሁሉም ስለመድረክ ትክክለኛውን እውነታ የሚያውቅ የመድረክ አባልም ሆነ ደጋፊ ሁሉ በመድረክ ላይ የተከፈተውን አፍራሽና ጐጂ ፕሮፓጋንዳ በማጋለጥ የድርሻውን እንዲያበረክትም በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። በመቀጠል ወደ ርዕስ ጉዳይ እገባለሁ።
በሀገራችን ሰነፎችና ሥራ ፈቶች የሚሠሩትን ፋይዳቢስ ሥራ ለመግለጽ ሕዝባችን በድሮ ጊዜ የሚጠቀመው ምሳሌአዊ አነጋገር “ሥራ የፈታ መነኩሴ ቆብ ቀዶ ይሰፋል” የሚል ነበር። ይህ አባበል በአሁን ጊዜ መነኩሴዎቻችን ሥራ ፈቶች መሆናቸው ቀርቶ ሥራ አክባሪዎችና ብርቱ ሠራተኞች ሆነው በየገዳማቱ በሚያመርቱት ምርት ለሌላውም ሕብረተሰብ ጥሩ አርአያ እየሆኑ ስለመጡ ከመነኩሴዎቻችን ጋር የማይገናኝ ተረትና ምሳሌ ሆኖአል። ምክንያቱም መነኩሴዎቻችን እጅግ በጣም ብዙ ሥራዎችን በየገዳማቱ በመፍጠር በሥራ እየተጠመዱ ጥሩ ጥሩ የሥራ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ስለሆኑ በአሁኑ ጊዜ ቆብ ቀደው የሚሰፉበት ጊዜ ስለሌላቸው ነው::
ይሁን እንጂ ይህ መጥፎ የሥራ ፈትነትና ስንፍና ባህርይ በጠቅላላው ከሕብረተሰባችን ጠፍቷል ማለት ግን አይደለም። እንዲያውም አንዳንድ ፖለቲከኞች ነን ባዮች ለራሳቸው ሥራ መፍታትና የስንፍና ባሕሪ ማሳየት ብቻ ሣይሆን በሥራ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚጥሩትን ዜጎችንም በሥራቸው ላይ እንዳያተኩሩ በፋይዳቢስ ፕሮፓጋንዳቸው ለማስተጓጎል ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያውቀው በሀገራችን የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ፓርቲዎቹ በፖለቲካ አመለካከትና የአደረጃጀት ቅርፅ መለያየት ብቻ ሣይሆን በርካታ የሚጋሩዋቸው ጉዳዮችም አሉዋቸው። በብሔርም ሆነ በሕብረ ብሔር ቢደራጁም የሚታገሉት ለአንዲት የጋራ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ስለሆነና ሀገራቸውም ደግሞ በውስጡዋ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉዋት በመሆንዋ ለሀገራቸው ሲያስቡና ሲታገሉ በውስጡዋ ለሚገኙና የየራሳቸው ባህልና ቋንቋ እንዲሁም የማንነት መግለጫ ላላቸው ሕዝቦች መብት አብሮነትና የጋራ ዕድገትም ያስባሉ፤ ይታገላሉም። ስለዚህ በብሔር ወይም በሕብረ ብሔር የመደራጀት ጉዳይ የአደረጃጀት ቅርጽ እንጂ የዓላማ ልዩነት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም።
አንዳንድ ይህንን እውነታ በሚገባ ያልተረዱ ወይም ሆን ብለው በመከላከላቸው ያለውን ግንኙነት ለማሻከርና ለገዢው ፓርቲ የከፋፍለህ ግዛ ተልኮ መሳካት አስተዋጾአቸውን ለማበርከት የተሰለፉ ግለሰቦች በብሔር ብሔረሰብ የተደራጁ ፓርቲዎች ለራሳቸው ብሔር ወይም ብሔረሰብ ብቻ የቆሙ፣ ለኢትዮጵያ ሕልውናና አንድነት የማይጨነቁ፣ እንዲያውም ሀገርን ለመገነጣጠል የተሰለፉ አድርገው በሌላ በኩል በሕብረ ብሔር የተደራጁት በአደረጃጀት ቅርጻቸው ምክንያት ብቻለሀገር ሕልውናና አንድነት ብቸኛ ጠበቆችና ባለአደራራዎች እንዲሆኑ አድርገው ከተጨባጩ እውኔታ ውጭ በሆነ አቀራረብ ሲዘባርቁ ይታያሉ። አንዳንዶች ደግሞ በሕብረ ብሔር የተደራጁት ሁሉ የብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን መብቶች በጭራሽ እንደማይቀበሉ አድርገው ይፈርጃሉ። አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንም እነዚህኑ ቁንጽል አስተሳሰቦች በማስተጋባት በብሔር ብሔረሰብ የተደራጁና በሕብረብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች ጭራሽ ሊያገናኛቸው የሚችል ጉዳይ በመካከላቸው እንደሌለ በመቁጠር አብሮ ለመሥራት የሚያደርጉት እንቅስቃሴና የጋራ ትግላቸውን ሲያጥላሉ ይታያሉ።
ከዚህ በላይ የተገለጹት የተዛቡ አመለካከቶች ትክክል አለመሆናቸውን የተረዱት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አባል የሆኑ በብሔር ብሔረሰብ የተደራጁና ሕብረ ብሔር የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተዛባውን አስተሳሰብ በመስበር ተቀራርበው በመወያየት የሚያስማማቸውንና የሚለዩበትን ጉዳዮች በሰከነ ውይይት በመለየትና ከሚለያያቸው ጉዳዮች ይልቅ በሚያግባባቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር በጋራ ተቀናጅተውና ግንባር ፈጥረው ለሀገራችን የዴሞክራራሲ ሥርዓት ግንባታና ለልማቱዋ የጋራ ዓላማዎችን በጋራ ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። በዚህም ጥረታቸው ከ2000 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ “መድረክ ለዴሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ” በሚል የጋራ የውይይት መድረክ ከፍተው ውይይታቸውን ለአንድ ዓመታት ያህል ጊዜ አካሂደው በመጀመሪያ የጋራ መርሖችን አውጥተው በነዚሁ መርሖዎች የሚሰማሙ ሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በመድረኩ እንዲሳተፉ በመጋበዝ ተንቀሳቅሰዋል።
በመጀመሪያ እንቅስቃሴውን የጀመሩት በብሔር የተደራጁት የኦሮሞ ሕዝቦች ኮንግረስ፤ አረና ትግራይና የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት፤ በክልልና ሕብረ ብሔር አደረጃት የተደራራጀው ደቡብ ሕብረትና በሕብረብሔርና ሀገር አቀፍ አደረጃጀት የተደራጁት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከሁለት ታዋቂ ግለሰቦች ጋር በመሆን ነበር። መድረኩን ከፈጠሩበት መሠረታዊ መርሖዎች አንዱና ዋነኛውም “ትግላችንን በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ሥር እናካሂዳለን” የሚል ነበር።
እንግዲህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት አካላት በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ሥራ ለመታገል የተስማሙባቸው በርካታ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መርሖዎች የሳባቸው ሌሎች ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ማለትም የኢትዮጵያ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የሚባሉ ፓርቲዎችም በመድረኩ የተቀላቀሉ ሲሆን መድረኩን ከውይይት መድረክ ወደ ሕጋዊ የቅንጅት አደረጃጀት ለማሸጋገር ከስምምነት ስለተደረሰ ለዚህ አደረጃጀት የሚያበቃንን የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም የጋራ የስምምነት ሰነድ ለማዘጋጀት ይህንኑ የሚያዘጋጅ ግብረሃይል በማቋቋም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሰፊና እጅግ አድካሚ ውይይቶችን አካሂደናል። በሳምንት ከሶስት እስከ አራት ቀናት ስብሰባዎችን በማካሄድና በእያንዳንዱ ቀናትም ከሶስት እስከ አምስት ሰዓታት ያህል ሳናቋርጥ በውይይት ላይ እየቆየን ነው ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ያሳለፍነው። ግብረሃይሉ የሚያካሂዳቸውን ውይይቶች በየ15 ቀናት ለጋራ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሪፖርት እያደረገ ከየድርጅቶቹ የተወከሉትን ሁለት ሁለት ግለሰቦች ያቀፈው የመድረክ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እየገመገመው ቀጣይ ውይይቶች በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንዲካሄዱ በማድረግ ስፋትና ጥልቀት ያላቸው የፖሊስ ጉዳዮች ላይ በመወያየት አጠቃላይ የፖለቲካ የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ጉዳዮች ብቻሳይሆኑ ዝርዝር የሴክተር ፖሊሲዎች ላይ ጭምር ከስምምነት ላይ ሊደረስባቸው ችሎአል። ውይይቶቹ በተወካዮች አማካኝነት ብቻ ሣይሆን ለድርጅቶችም እየተላኩ በየድርጅቶቹ የአመራር አባላትና አካላት ጭምር ውይይቶች እየተካሄዱ አቋም ይወሰድባቸው ነበር።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሁኔታ የሚዳስስ መግቢያ፤ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከስምምነት የተደረሰባቸው አጠቃላይ መርሖችና አቋሞች ፖለቲካዊ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጉዳዮችን በሚመለከትና የኤኮኖሚና ማሕበራዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ያሉትን በርካታ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት የመፍትሔ ሀሳቦችን የሚያስቀምጡ አንቀጾች በግልጽ የተቀመጡባቸው ባለ 65 ገጽ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ በጋራ ጉባኤ ሊጸድቅ ችሎአል። በወቅቱ የኢትዮጵያን አንድነትም ሆነ በኢትዮጵያ አንድነት ሥር ሊከበር ስለሚገባው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት አከባር ላይ በጋራ ስምምነት በርካታ አንቀጾች ያለልዩነት የጸደቁ መኖራቸውን አንባቢያን ፕሮግራሙን ራሱን በማንበብ ሊረዱ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ።
ለምሳሌ በፕሮግራሙ አጠቃላይ መርሖዎች መጀመሪያ ላይ “ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት በጽናት እንቆማለን፣ በቀድሞ የነበሩትንና አሁንም ያሉትን ኢፍትሐዊና አድሎአዊ አሠራሮች የተወገዱበት በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲጠናከር በጽናት እንቆማለን፤ በመሆኑም መገንጠልን አንደግፍም” የሚል መርሖ ቅድሚያ ተሰጥቶ ሰፍሮ ይገኛል።
የመድረክ አባል ድርጅቶች ብሔራዊም ሆኑ ሕብረ ብሔራዊ በምንም ሳይለያዩ ስለኢትዮጵያ አንድነትና ስለሕዝቦቿ አብሮነት ያላቸው ጽኑ አቋም ከዚህ በላይ የጠቀስኩት ሆኖ ሳለ አንዳንድ የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት አባላት የሆኑ ግለሰቦችና አንዳንድ ሚዲያዎች በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ አንድነትና በሕዝቦች የመብት ጥያቄ ላይ የሰፋ ልዩነት በመድረክ አባል ድርጅቶች መከላከል እንዳለ በማስመሰል የራሳቸውን የፈጠራ ወሬ ከማስተጋባታቸውም በላይ ውይይት ያልተካሄደበትና አቋም ያልተወሰደበት ጉዳይ ያለ ይመስል የመድረኩ አባል ድርጅቶችን ግንኙነት አፍራሽ በሆነ መልኩ ደጋግመው ሲተቹ ታይቷል።
መድረክ ወደ ግንባር የተሸጋገረብትን ሂደት አስመልክተውም በመድረክ አባል ድርጅቶች መሪዎች ብቻ በችኮላ እንደተፈጸመ አስመስለው ከእውነት የራቀ አሉባልታ ሲያስተጋቡ ይደመጣሉ። ይህንን ከሀቅ የራቀ ፕሮፓጋንዳቸው” ለገዥው ፓርቲ ፕሮፓጋንዲስቶች በማቀበልም በመድረክ አባላትና ደጋፊዎች የትግል ሞራል ላይ ጥቃት የሚያደርስ ዘመቻ እንዲያካሂድበት በማድረግ ለገዥው ፓርቲ አገልጋይነታቸውን በተግባር በማሳየት ላይ ይገኛሉ። እውነቱ ግን ከመጀመሪያውኑ የፕሮግራሙና የደንቡ ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ሰነዶቹ ከቅንጅት አልፎ ለግንባር ምስረታም ቢሆን በቂ የሆኑ ሰነዶች መሆናቸው በሁሉም የመድረክ አባል ድርጅቶች ታምኖበት የነበረ ቢሆንም በሀገራችን ባላው የግንባር ምሥረታ ሕግ መሠረት የሚመሠረተው ግንባር ከሆነ ሰነዶቹ በእያንዳንዱ አባል ድርጅት ጉባኤ ጭምር መጽደቅ ያለበት ስለሆነ ሁሉም ድርጅቶች በአመራር አካላት ብቻ ሣይሆን ጉባኤ ጠርተው በየጉባኤዎቻቸው እንዲያፀድቋቸው ተደርጐአል። ታዲያ ከእነዚህ የሁሉም አባል ድርጅቶች አባላት በስፋት ከተሳተፉባቸው ጉባኤዎች በኋላ ሁሉም ድርጅቶች የተስማሙበት የጠቅላላ ጉባኤዎች ቃለ ጉባኤና የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ የሰነዱ አጸዳደቅ በአመራር አባላት ብቻ እንዳልሆነና በዴሞክራሲያዊ አሰራር የድርጅቶቹን አባላት በበቂ ሁኔታ በማሳተፍ የተሰራ ለመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው።
የግለሰብና የብሔር ብሔረሰብና ቡድን መብቶች አከባበር በሚመለከትም ጉዳዩ ከስምምነት ያልተደረሰ አይደለም። በዚህና በሌሎችም የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በመጀመሪያ ለውይይት መነሻ የሆኑ ጥናታዊ ጽሑፎች በግብረ ሃይሉ አባላት እኔም ራሴ በተሳተፍኩበት ተዘጋጅተው ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ከመድረክ አባል ድርጅቶች አባላት ጋር ጭምር ሰፊ ውይይት ከመደረጉም በላይ የግብረ ሃይሉ አባላትም በጥልቀት ተወያይተው “የግለሰብ፤ የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦችና ቡድኖች መብቶች እኩል እንዲከበሩ ሳንታክት እንሰራለን።” በሚለው መርሕ ላይ ካለአንዳች ልዩነት ተስማምተን በፕሮግራሙ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። በዚህም መሠረት የግለሰብና የቡድን መብቶች አንዳቸው ሳይከበር ሌላው ሊከበር ስላማይችሉ ሳይነጣጠሉ በተግባር እንዲውሉ ነው የተስማማነው። በወቅቱ ከቡድን መብት ይልቅ የግለሰብ መብት ቅድሚያ ይኖረዋል የሚል አቋም የነበራራቸው የአንድነት አባላትም በውይይቱ በቀረቡት ሀሳቦች በማመናቸው ወደ ጋራ ሃሳብ ማለትም ሁለቱም በእኩልነት ሳይነጣጠሉ በተግባር ላይ እንዲውሉ እናደርጋለን፣ ወደሚለው ሃሳብ መጡ እንጂ ማንም ያስገደዳቸው ወይም ያሳሳታቸው የለም። ወደዚህ ሃሳብ መምጣታቸውንና ፕሮግራሙን መቀበላቸውንም በፊርማቸውና በማሕተማቸው አረጋግጠዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች መብትን እስከመገንጠል በፕሮግራሙ አስቀምጦ የነበረው አረና ትግራራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነትም ይህንን ሀሳብ ከፕሮግራራሙ ለማስወጣት በራሱ ፈቃድና ተነሳሽነት በጉባኤው አጽድቆ “መገንጠልን አንደግፍም” ከሚለው የመድረክ ሀሳብ ጋር ተመሳሳይ አቋም መያዙን በመግለጹ ሁላችንም በመድረክ ፕሮግራም የተቀመጠውን የግለሰብና የቡድን እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦችን መብቶች ካለልዩነት ተስማምተን ነው ያሰፈርነው። ይህ ወደ ሚያቀራርብ መካከለኛ ሀሳብ መሰባሰብና መስማማት ደግሞ ትክክለኛና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የዴሞክራሲያዊ ድርድር ሂደት መግለጫ ነው ብዬ አምናለሁ።
ከዚህ በላይ በተጠቀሱና በመሳሰሉ በርካታ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያለልዩነት ከስምምነት የተደረሰበት ቢሆንም በሁለት ጉዳዮች ላይ ግን ብዙ ጊዜ ወስደን ብንወያይም ስምምነት ለመድረስ አልቻልንም። እነዚህም ሁለት ጉዳዮች የመሬት ጉዳይና የፌዴራላዊ ክልሎች አከላለልን የሚመለከቱ ነበሩ። በመሬት ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ አርሶ አዶሮችና የከተማ ነዋሪዎች መሬት በባለቤትነት የመያዝና የመጠቀም፤ የሚከራዩትና ለፈለጉት ሰው በውርስ በማስተላለፍ መብቶች ላይ ከስምምነት ተደርሶ በፕሮግራሙ ተካትቷል። አርብቶ አደሮችም መሬትን በጋራ ባለቤትነት በመያዝ የመጠቀም መብታቸው በፕሮግራሙ ተካቷል። መሸጥን በሚመለከት ግን አንድነት ለዴሞክራሲያዊና ለፍትህ ፓርቲ መሸጥን ሲደግፍ ሌሎች ፓርቲዎች ግን በአሁኑ የሀገራችን የኤኮኖሚ ዕድገትና ተጨባጭ ሁኔታ መሬትን መሸጥ በተለይም አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ከመሬታቸው ውጭ ሆነው ሌላ የሥራ መስክ ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ ወደ ጭሰኝነት ተመልሰው መሬትን በስፋት ለሚገዙ ሰዎች የሥራ ውጤታቸውን እየገበሩ እንዲኖሩ ሊያደርግ ስለሚችል በሕዝቦች ትግል የተወገደውን ፊውዳላዊ ሥርዓት የመመለስ አደጋ ስላለው አንደግፈውም በማለታችን ሳንስማማ ቀርተናል። ስለዚህም ይህ ጉዳይ በልዩነት ተቀምጦ ከተቻለ ወደፊት በውይይት ለመቀራረብና በፕሮግራማችን ለማካተት፣ መቀራራረብ ካልቻልን ደግሞ ሥልጣን በምንይዝበት ወቅት ቅድሚያ ተሰጥቶት ከሌሎች የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ሀሳቦች ጋር ለሕዝባችን ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ ለማድረግ ተስማምተናል። ሕዝቡ የሚሰጠውን ውሳኔ በፀጋ ለመቀበልም ተስማምተናል።
የፌዴራል ክልሎችን ማካለል በሚመለከትም አንዳንዶች በመልክዐ ምድር ላይ እንዲመሠረት ሲሉ፤ አንድንዶች ደግሞ በሕዝቦች ቋንቋ፣ ባሕላዊና ማህበራዊ ገጽታዎች ላይ የሚል ሌሎች ደግሞ ሁሉንም ማለት መልከዓ ምድራዊ፣ ባህላዊና ማሕበራዊ እንዲሁም ለአስተዳደር ያለውን አመቺነት ባገናዘበና የሕዝቦችን ፈቃደኝነትም ባረጋገጠ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል የሚሉ አማራጮችን በማቅረብ ሰፊ ውይይቶች ተካሂደው ከስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቀርተዋል። ይህንንም ጉዳይ ከመሬት መሸጥ ጉዳይ ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ከተቻለ ወደፊት በሚደረግ ውይይት በማቀራረብ ወደ ስምምነት ለመድረስና በፕሮግራም ለመካተት ካልተቻለ ግን ለሕዝብ ውሳኔ ለማቅረብ ከስምምነት ተደርሷል። ይህ ሲባል ግን የመንግሥት አወቃቀርን በሚመለከት ምንም ስምምነት አልተደረሰም ማለት አይደለም። በበርካታ የመንግሥት አወቃቀር ጉዳዮችም ላይ ከስምምነት ላይ ተደርሶአል። ለምሳሌም በፕሮግራሙ አንቀጽ 7 ላይ “ሀገራችን የምትከተለው የመንግሥት አወቃቀር በፌዴራልና በክልል መንግሥታት የተመሠረተ ፌዴራላዊ አወቃቀር እንደሚሆን፤ መድረክ በፌዴራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል የሚኖረው የሥልጣን ክፍፍል እና ግንኙነት ትክክለኛውን የፌዴራሊዝም መርሕ የተከተለና በትክክልም ሥራ ላይ የሚውል እንዲሆን ያደርጋል፤ የፌዴራል መንግሥት የሕግ አውጭ አካል በሁለት ም/ቤቶች (Bicameral) ይሆናል፤ በዚህም መሠረት የሕግ መምሪያ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና የሕግ መወሰኛ የፌዴሬሽን ም/ቤት የሚባሉ አካላት ያሉት በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎና በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች እንዳቋቋሙ ይደረጋሉ፤ የፌዴሬሽን ም/ቤት ከሚሠራቸው ሥራዎች አንዱ በተወካዮች ም/ቤት የሚወጡ ሕጐች ሕግ ሆነው ከመውጣታቸው በፊት በሕገ-መንግሥቱ መሠረት የወጡ መሆናቸውን መርምሮ ማጽደቅ ይሆናል፤ በዚሁም መሠረት በሕግ ማውጣቱ ሥራ የሚሳተፍ አካል ይሆናል፤ ሕገ-መንግሥቱን የመተርጐም ሥራ ከፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ሥራ ይወጣል። በምትኩ ይህንኑ ሥራ የሚሠራ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ይደራጃል የሚሉና የመሳሰሉ በርካታ አሁን ያለውን ሕገ-መንግሥትና አሠራሮችን የሚያሻሽሉ የመንግሥት አወቃቀርን የሚመለከቱ ሀሳቦች ቀርበው በሙሉ ስምምነት በፕሮግራማችን ውስጥ ተካተዋል።
የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች መብት በሚመለከትም ከተደረሰባቸው ስምምነቶች የሚከተሉት ይገኛሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔር ሀገር ነች ቀደምት የሀገራችን አገዛዞች የብሔር ብሔረሰባችን ሕልውና ባለመቀበልና ባለማክበር አምባገነናዊ አሃዳዊ አገዛዝ በማስፈናቸው አገዛዞቻቸው ለሀገራችን ሰላም መታጣትና አለመረጋጋት አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢሕአዴግ አገዛዝም በአፋኙ አሃዳዊ አገዛዝ ፋንታ መገንጠልን ጨምሮ የብሔር ብሔረሰቦች መብቶች የሚከበሩበት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ እውን አደርጋለሁ ቢልም በተግባር ግልጽ ሆኖ የታየው ግን ሥርዓቱ እውነተኛ ፌዴራላዊም ዴሞክራሲያዊም አለመሆኑ ነው፤ በብሔር ብሔረሰብ መብት መከበር ሽፋን ተግባራዊ እየሆነ ያለው ከፋፍሎ መግዛት ነው፤ በዴሞክራሲ ስም በሀገሪቱ ሰፍኖ ያለውም የዜጎች መብቶች አፈና ነው፤ ቀደምቶቹም ሆኑ የአሁኑ የአፈና አገዛዞች የብሔር ብሔረሰቦች መብት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን እንዳይኖር ማድረጋቸው የሀገራችን አንድነት ስጋት ላይ እንዲወድቅ አድርገዋል፤ በመሆኑም በዚህ መድረክ የተሰበሰብነው ሃይሎች እስካሁን ከታዩት አካሄዶች በመማር እና የታዩትን ስህተቶች በማረም በሀገራችን የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና መከባበር የሰፈነበት ዘላቂ አንድነት ይረጋገጥ ዘነድ እንታገላለን የሚሉና የብሔር ብሔረሰቦች ማንነታው ቋንቋቸውና ባህላቸው እንዲሁም ታሪካቸው በእኩልነት የሚከበሩባቸው መርሖዎች እንዲሁም በአካባቢያቸው ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር ያላቸው መብት የሚከበር መሆኑን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲንም ጨምሮ ያለአንዳች ልዩነት በሙሉ ስምምነት አጽድቀነዋል። በዚህ ላይ ከስምምነት ሳይደርስ የቀረ አንድም ነጥብ የለም። ምናልባት አሁን ከተስማማንበት አቋም ለመንሸራተትና የአቋም ለውጥ ለማድረግ ካልታሰበ በስተቀር።
ታዲያ እውነቱ ከዚህ በላይ እንደተገለፀው በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሰፊና ጥልቅ ውይይቶች ተደርገው ስምምነት የተደረገበት ሆኖ ሳለ እጅግ በርካታ መሠረታዊ በሆኑ የሀገራችን ጉዳዮች ላይ በስምምነት ተግባብተው ለመሥራት የወሰኑ ብሔራዊና ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲዎችን ተስማምተው ሊሠሩ የማይችሉ “ውሃና ዘይት ናቸው” በማለት ለአንድነት ለዴሞክራሲያዊ ለፍትሕ ፓርቲ ይጠቅማል ብለው አንዳንድ የፓርቲው የብሔራዊ ም/ቤት አባላት ከመድረክ የመውጫ (Exit) ስትራራቴጂ ሚያዝያ 12 ቀን 2004 ዓ.ም በታተመው የፍትሕ ጋዜጣ “የመድረክ ከየት ወዴት” በሚል አርእስት ሥር በተዘጋጀው ፅሁፍ ጠቁመው ነበር። በወቅቱ ጋዜጣውን ፎቶ ኮፒ አድርጌ ለአንድነት ተወካዮች ሰጥቼ ነበር። ሚያዝያ 23/2005 በታተመው የሰንደቅ ጋዜጣ ደግሞ ስለመድረክ መፍረስ ከንቱ ሕልም በማለም እንዲሁም ሰሞኑን በታተሙት የቆንጆ መጽሄት ላይና በኢትዮ ምሕዳር ጋዜጣ እትሞች መድረክ መፍረስ አለበት እያሉ የባጥ የቋጡን በማውራራት ላይ ይገኛሉ። የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የብሔራዊ ም/ቤት አባላት አዲስ የጥናት ግኝት ያገኙ ይመስል ለገዥው ፓርቲ ለኢሕአዴግ ካልሆነ በስተቀር ለመድረክ፣ ለአንድነትም ሆነ ለሀገራችን ሕዝቦች በአጠቃላይ የማይጠቅም ወሬ ሲያናፍሱ እየተመለከትናቸው ነው። እርግጥ መድረክ ሁሉም አባል ድርጅቶች በፈቃዳቸው አባል የሆኑበት ግንባር ስለሆነ ማንኛውም አባል ድርጅት አንድነትንም ጨምሮ ከመድረክ ለቆ መውጣት ከፈለገ መብቱ የተጠበቀ ነው። ከዚህ አልፎ ግን “መድረክ መፍረስ አለበት” ብሎ ማቅራራታቸው “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ያለችው እንሰሳ አይነት አስተሳሰብ ይመስላል። ሚያዝያ 2004 ዓ.ም የጠቆሙትና ከሚያዝያ 2005 ዓ.ም ጀምሮ ሰሞኑን በማካሄድ ላይ ከሚገኙት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ግልጽ የሆነው ነገር የመውጫ ስትራቴጂያቸው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሥርዓት ባለው መልኩ በሰላም ከመድረክ የመሰናበት ሳይሆን በእኩልነት ተደራድረን ከደረስንባቸው ስምምነቶች ውጭ ልክ እንደ ሕወሐት የራሳቸውን ሙሉ ፕሮግራም በመድረክ አባል ድርጅቶች ላይ መጫን ካልተሳካላቸው መድረክን አፍርሰው ለመሄድ በፍጹም የማይሳካላቸውን ምኞት እየተመኙ እንደሆነ ነው። ይህ መቼም ምን ያህል ትዕቢት የተሞላበት ብልግና እንደሆነ አንባቢያን ይረዱታል ብዬ አምናለሁ።
መድረክ እንደ ኢሕአዴግ አንድ አምባገነን የፖለቲካ ፓርቲ ሕወሐት ከሥሩ ተቀጥላ ፓርቲዎችን ፈጥሮ የራሱን የፖለቲካ ፕሮግራም ከሀ እስከ ፐ አስገልብጦ በመስጠት ለጋራ ግንባራቸውም የዚያው አምባገነን ፓርቲ ትክክለኛ ግልባጭ ከስሙ በስተቀር ማለት ነው በማስጨበጥ የተፈጠረ ግንባር አለመሆኑና ነፃና የየራሳቸው አደረጃጀትና አመለካት ያላቸው ፓርቲዎች በራሳቸው ነፃ ፍላጎት ተቀራርበው በሚስማሙባቸው ፖሊሲዎችና የጋራ ሀገራችን ጉዳዮች በጋራ ለመሥራት የፈጠሩት ግንባር መሆኑን መቼም አንዳንድ የትናንትናዎቹ የኢህአዴግ የወጣት ክንፎችና የአሁኖቹ የአንድነት ለዴሞክራሲ ለፍትሕ ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት አባላት ሳይቀሩ በሚገባ ያውቃሉ ብዬ አምናለሁ። ታዲያ ከገዥው ፓርቲ ወደ ተቃዋሚ ፓርቲ መግባት መብታቸው መሆኑን ሚያዝያ 30 ቀን 2005 ዓ.ም በታተመው በሰንደቅ ጋዜጣ የገለጹትና እኛም ይህንኑ መብታቸውን በጥብቅ የምናከብርላቸው እነዚህ ሰዎች ሊያውቁት የሚገባቸው መሠረታዊ መብት እኛም ከኢህአዴግ የተለየ ማለትም ፕሮግራምን ከአንድ አምባገነን ፓርቲ ሙሉ ቅጂ ያልወሰደ ግን የምንስማማባቸውን አብዛኛዎቹን ጉዳዮች ያካተተና የተለያየንባቸውን ጥቂት ጉዳዮች ደግሞ በተመቸን ጊዜ በዴሞክራሲያዊ“ እኩልነታችንና ነፃነታችን በተከበረ መልኩ በረጋ ሁኔታ ተወያይተን ከተቻለን ለመስማማቱ ካልተቻለን ደግሞ ለሕዝብ ውሳኔ አቅርበን ሕዝቡ በሚወስነው ለመገዛት ተስማምተን ሕብረ ብሔራዊና ብሔራዊ ፓርቲዎችን ያቀፈ ከኢህአዴግ በይዘትም ሆነ በቅርጽ የተለየ ግንባር ለመፍጠር ዴሞክራሲያዊ መብት ያለን መሆናችንን ነው። ስለዚህ ይህንን ነፃ መብታችንን በመጣስ በኢህአዴግ የግንባር ምሥረታ ሞዴል እንድንመራ ሊያስገድዱንና ከኢሕአዴግ ሞዴል የተለየ የግንባር ምሥረታ ሁሉ ስህተት እንደሆነ በማስመሰል በሚያወሩት መሠረተ ቢስ ፕሮፓጋንዳቸው ሕብረተሰቡን ለማሳሳት መሞከር የለባቸውም ብዬ አምናለሁ። እነርሱ በኢሕአዴግ ሞዴል ለመምራት ፍላጎት ካላቸው ግን ለራሳቸው ብቻ ሊመርጡትና ሊጠቀሙበት መብታቸው ነው። በአለም ዙሪያ ተደራጅተው የሚንቀሳቁ ፓርቲዎች ግንባር ሲፈጥሩ የሚስማሙባቸውንና የሚለያዩባውን ጉዳዮች ለይተው ያልተስማሙባቸውን ወደጎን በመተው የተስማሙባቸው” ጉዳዮች በጋራ ሥራ ላይ ለማዋል እንደሚንቀሳቀሱ ግንዛቤ የሌላቸው ወይም ሆን ብለው ሕዝብን ለማሳሳት የመድረክ ግንባርነትን የሚተቹ እነዚህ ሰዎች መድረክ ለምን እንደ ኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና ግንባር በሁሉም ነገር አንድ ግልባጭ ፕሮግራም አይኖረውም? ይህ ካልሆነ ወደ ግንባር መሸጋገሩ ስህተት ነውና መፍረስ አለበት በሚል አስተሳሰብ ስለግንባር አመሠራረት ባላቸው ቁንጽልና የተሳሳተ ግንዛቤ ሕዝባችንን ግራ ለማጋባት ያዙን ልቀቁን ሲሉ ይታያሉ። በዚህ አስተሳሰብና አቀራራረባቸው ከሚወሰኑ ይልቅ የኢህአዴግን ብቻሣይሆን በተለያዩ ሀገሮች ፓርቲዎች የሚፈጥሩዋቸውን ግምባሮች በሚመለከት ሰፊ ጥናት አድርገው ሰፋ ያለ ዕውቀት ለራሳቸውም ሆነ ለሕዝባችን ለማቅረብ ቢዘጋጁ የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ሰለ ግንባር ምንነት ያላቸውን ግንዛቤ ትንሽ ሰፋ ቢያደርጉ የኢህአዴግን የመሰለ ግንባር ካልፈጠራችሁ መፍረስ አለባችሁ ከሚለው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አቋማቸው ይታረማሉ ብዬም እገምታለሁ።
ግንባር መመሥረት የሚያሳየው መጀመሪያውኑም ቢሆን የተወሰኑ ከስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች መኖርን ነው እንጂ በሁሉም ጉዳዮች መስማማትን አይደለም። በሁሉም ነገሮች ከተስማሙ በኋላ መነሳት ያለበት የውሕደት ጥያቄ ነው። የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት አባላትም ሆኑ መላው ሕዝባችን እንደሚያውቀው የመድረክ አባል ድርጅቶች በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ተስማምተን በጥቂት ጉዳዮች ላይ አሁንም ልዩነታችንን እስከያዝን ድረስ መመሥረት ያለብን ትክክለኛው ጥምረት ግንባር ነው መሆን ያለበት። የተስማማንባቸው ጉዳዮች በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ተሠርተው የሚጠናቀቁ ሥራዎች ሳይሆኑ ላልተወሰነ ጊዜ በጋራ ተሰልፈን እንድንታገል የሚጠይቁን ስለሆነ ከቅንጅት ይልቅ የግንባር አደረጃጀትን የሚሹ ናቸው። እኛም በዚህ እውነታ ላይ ተመሥርተን ነው ከቅንጅት ይልቅ የግንባር አደረጃት ለጋራ ዓላማዎቻችን መሳካት የሚመጥን ስለሆነ ግንባርን የፈጠርነው። ስለዚህ መድረክ በተወሰኑ ጥቂት ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ሳይደርስ ግንባር መሆኑ ትክክለኛና ከኢሕአዴግ በስተቀር ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችም የሚያረጋግጡት የግንባር አደረጃጀት ጉዳይ ነው። ሙሉ በሙሉ በምንስማማበት ወቅት ወደውሕደት እንደምንደርስና ለዚህም ደረጃ በደረጃ እየሠራራን እንደምንቆይ የመድረክ አባል ድርጅቶች እምነት ነው። በእኛ በኩል “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል።” እንደሚባለው በችኮላ ሳይሆን ቅድሚያ የሚሰጡ የጋራ ሥራዎችን ቅድሚያ እየሰጠን በዚህም ጉዳይ ላይ በሰከነ መንፈስ መወያየታችንን አልተውንም። የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት አባላትም እንደሚያውቁት በቅርቡ የተካሄደው የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ትኩረት ሰጥቶ ከተወያየባቸውና ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መመሪያ ከሰጠባቸው አበይት ጉዳዮች ዋነኞቹ የሀገራችን መሠረታዊና ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ተዘጋጅቶ የቀረበውን ማነፌስቶ አጠናቆ ሕዝቡን በማወያየት የትግል እንቅስቃሴ እንዲደረግበትና ከዚህ ጐን ደግሞ በሚገኘው ጊዜ ውስጥ ባልተጠናቀቁ የፕሮግራም ልዩነቶችም ላይ ውይይት እየተደረገ ለማቀራረብ ሙከራ እንዲደረግ ነው።
መተዳደሪያ ደንባችንን በሚመለከት ሰፊና ጥልቅ ውይይት ተካሂዶባቸው ከስምምነት ላይ የተደረሱ ጉዳዮች ተካተውበት ደንቡ በጉባኤው ውሳኔ መሠረት እንዲሻሻል ተደርጐ ለምርጫ ቦርድ ከገባ የተወሰኑ ወራቶችን አስቆጥሮአል። ለወደፊትም በሚካሄዱ ውይይቶች ተጨማሪ ማሻሻያዎች ይደረግበታል የሚል እምነት አለኝ። በሰከነ ውይይት ለመፍታት የምንሞክራቸውን ልዩነቶች አሁኑኑ በጥብጠው በማጠጣት ሊያስወጡን ስሜታዊና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ፉከራ የሚያሰሙት የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት አባላት የሆኑ “አለን አለን” ባዮች ስሜታዊ ሩጫዎች አፍራሽ እንጂ ገንቢ አይደለምና ከአፍራሽ ተግባራቸው ሊታቀቡ ይገባል። የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የተግባር ኮሚቴዎች ይህንን የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ ደፋ ቀና በሚሉበት ጊዜ ውስጥ እኛና ሕዝባችን በማኒፌስቶአችን ሀሳቦች ላይ አተኩረን እንዳንቀሳቀስ ለማድረግ አዲስ የጥናት ግኝት ያገኙ ይመስል ጋዜጦችንና መጽሄቶችን እኛ ለብዙ ጊዜ ስንወያይበት በቆየነውና አሁንም ባላቋረጥነው ጉዳይ በመሙላት የአደናቃፊነት መራወጥ ማሳየት ቆብ ቀዶ ከመስፋት ያለፈ ፋይዳ ያለው ሥራ አይደለምና ዓላማውም መድረክ ከተያያዘው ወሳኝ የትግል ምዕራፍ ላይ የሕዝብን አመኔታ ለመሸርሸርና ለማደናቀፍ የማይሳካ ሙከራ ማድረግ ብቻነው የሚመስለኝ።
በበኩሌ እኔ መድረክ ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ በአመራርውስጥ ያለሁና በተለይም ፕሮግራሙን ያዘጋጀው ግብረሃይል ፀሐፊ ሆኜ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ቃለ-ጉባኤዎች” በመያዝ በውይይት ወቅት የተከናወኑ ሥራዎችን ስለሚያውቅ እነዚህ የተረሱ ጉዳዮችን ያስታወሱን ይመስል ዛሬ “መድረክ መፍረስ አለበት” እያሉ ቡራ ከረዩ የሚሉ የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት አባላት የሚያነሷቸው ጉዳዮች ስሰማ በጣም ይገርመኛል። ምክንያቱም ጉዳዮቹ በቂና ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው በስምምነትና ልዩነት የተቀመጡ እንጂ ዝም ብለው ወይም ተረስተው የተዘለሉ አይደሉምና ነው። ከላይ እንደ ጠቆምኩትም በመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ተገምግመው ውሳኔ የሰጠባቸውና ቀጣይ የአፈጻጸም ጥረት ብቻ የሚጠይቁ እንጂ ምንም አዲስ ግምገማና ጥናት የሚያስፈልጋቸውም አይደሉም። ምክንያቱም የታወቁና በጠቅላላ ጉባኤም የተገመገሙ ናቸውና። ሳይገመገም የቀረ ነገር አለ እንኳ ቢባል በተወካዮቻቸው አማካይነት ለሚመለከተው የመድረክ አካል በማቅረብ የሌሎችም አባል ድርጅቶች ተወካዮች ባሉበት በጋራ ማስገምገም ሲገባ ከመድረክ ጀርባ ግምገማ ለምን ያስፈልጋል? ታዲያ ተገቢውን የመድረክ የግምገማ አሰራር ሳይከተሉና ሳይገመግም የቆየ አንዳች ጉዳይ እንኳ ሳይዙ ሚዲያ ላይ በመውጣት በመድረክ ላይ አፍራሽ ትችቶችን እያስተጋቡ እዩኝ እዩኝ ማለት ቆብ ቀዶ በመስፋት የሥራ ችሎታንና ብቃትን ለማሳየት የሚቻል መስሎአቸው የሚያደርጉት ከንቱ ሙከራ ነውና ፋይዳ የሌለውና ገንቢ ሊሆን የማይችል ሥራ ነው።
ይልቁንም እነዚህ ሰዎች የራሳቸውንና የእኛንም ወርቃማ ጊዜ በከንቱ ከሚያባክኑብንና ሕዝባችንንም ግራ በማጋባት ሥራ ላይ ከሚሠማሩ በጋራ ጠቅላላ ጉባኤአችን የፀደቀውን የትግል አቅጣጫ አመላካች ማኒፌስቶአችንን ለሕዝባችን አቅርበን ለማወያየትና ሥራ ላይ ለማዋል ገዥው ፓርቲ ከፊታችን የደቀነብንን መሰናክሎች ተባብረን በመጋፈጥ ተጨባጭ የትግል ውጤት በሚያመጡ ሥራዎች ላይ የሚሰማሩበት ወኔ ቢኖራቸውና ለዚህም ቢዘጋጁና ቢሠማሩ ቁም ነገር መሥራት ይሆናልና ለዚሁ ቀና ሥራ እንዲሰለፉ የበኩሌን ሀሳብ አቀርብላቸዋለሁ:: ይህንን ቀና ሀሳብ የማትቀበሉና ከአፍራሽ ፕሮፓጋንዳችሁ የማትታቀቡ ከሆነ አገልግሎታችሁ ለማን እንደሆነ ግልጽ ነውና ምርጫችሁን ብታስተካክሉና ግልጽ ብታደርጉ ጥሩ ይመስለኛል የመድረክ ትግል በእኛ መኖር አለመኖር ይወሰናል ብላችሁ ገምታችሁ ከሆነ በጣም ተሳስታችኋል:: መድረክ ያለእናተም ቢሆን የያዘውን ሕዝባዊ ዓላማ ይዞ በጽናት ትግሉን እንደሚቀጥል በፍጹም ጥርጥር ሊገባችሁ አይገባም። ምክንያቱም አንድ ድርጅት ከውስጡ የሚታረሙ ቦርቧሪዎችን በጸዳ ቁጥር የበለጠ እየተጠናከረ ይሄዳል እንጂ አይዳከምምና። መድረክም ዓላማውንና ፕሮግራሙን እናንተ ብትለዩት ሜዳ ላይ ጥሎ የሚጠፋ ድርጅት አይደለምና።
ይህንን የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት አባላት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ስላገኛችሁ ሰሞኑን ልባችሁ ቅቤ ጠጥቶ መድረክ አይሰነብትም በማለት ጮቤ እየረገጣችሁ የማይሳካ ሟርታችሁን በማሰራጨት ላይ ያላችሁ የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዲስቶችም የራሳችሁ ድርጅት በየጊዜው የገባበትን ከዚህ ችግር እጅግ የባሰ ማጥና ከዛ ለመውጣት ያደረጋቸውን መፍጨርጨሮች ብታስታውሱ እንደዚህ አይነት ጉዳዮች በናንተም ሆነ በማንኛውም ድርጅት የሚከሰት መሆኑን ትረዳላችሁ። በአምባገነንነተና በአንድ ድርጅት የበላይነት የሚፈጠር የእናንተ አይነት ግንባር ካልሆነ በስተቀር ሌላው ሁሉ የሚፈርስ መስሏችሁ ከሆነ ሟርታችሁ መና ሲቀርና መድረክ የበለጠ ተጠናክሮ ጉዞውን ሲቀጥል ተገቢውን ትምህርት ትቀስማላችሁ ብዬ እተማመናለሁ። ከተጨባጭ ሁኔታ መማር የምትችሉ ከሆነ ማለቴ ነው። እስካሁን ያልተረዳችሁትና በዚህ አጋጣሚ በሚገባ የምትረዱት ይሆናል ብዬ የማስበው ነገር ቢኖር መድረክ ለተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ከተሰባሰቡት የኢሕአዴግ አባላት እጅግ የላቀ የዓላማ ጽናትና የሞራል ጥንካሬ ያላቸው ታጋዮች ባለቤት የሆነ ድርጅት መሆኑን ነው። ስለዚህ እናንተ እንደምትገምቱትና እንደምታሟርቱበት ሳይሆን ዓላማቸውን በሰላማዊ ትግል ከግብ ለማድረስ ፀንተው በመታገል በእንደነዚህ አይነት ክስተቶች የማይበገሩ አባላት ያሉበት ድርጅት ችግሮች ሲያጋጥሙት የበለጠ ይጠናከራል ባትሳሳቱ ጥሩ ነው። ስለዚህ መድረክ አይሰነብትም በማለት የማይሆን ሟርት በማሰራጨት ጊዜአችሁን ብታባክኑም አይሳካላችሁምና ሌላ ሥራ ብትሠሩ ይሻላል እላለሁ።
ሌላው እነዚሁ የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት አባላት በመድረክ ላይ የከፈቱት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ስለግንባሩ መተዳደሪያ ደንብና ስለአመራሩ ዴሞክራሲያዊ አለመሆን ነው። እንዲያውም “ኢዴሞክራሲያዊ ነው” በማለት የሚያናፍሱት ፕሮፓጋንዳም ውስጡ ባዶ የሆነ ፕሮፓጋንዳቸው ነው። በመድረክ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የግንባሩ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ከየድርጅቶቹ የሚወከሉ አሥር አሥር አባላት የሚሳተፉበት ሲሆን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ደግሞ ከየድርጅቶቹ የሚወከሉ ሁለት ሁለት ሰዎች የሚሳተፉበት ነው።
የጉባኤውና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ቁጥር ለወደፊቱ ቢያንስ በእጥፍ እንዲጨምር ለማድረግም እየተወያየንበት ነው። ከዚህ የበለጠ ለማድረግ በሁላችንም በኩል ፍላጐቱ ያለ ቢሆንም ችግራችን ጉባኤአችን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ መሆኑን ብቻነው። አባል ድርጅቶች በማንኛውም ወቅት ተወካዮቻቸውን መቀየር ይችላሉ። የግንባሩ ሊቀመንበር ብቃትና ችሎታን መሠረት ባደረገና የአባል ድርጅቶችን እኩል ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ በየዓመቱ ይመረጣል ይላል። ደንቡ አንድ ሊቀመንበር ጉባኤው ከፈቀደለት ለአንድ ዓመት ለአንድ ጊዜ ብቻ ኃላፊነቱን ይዞ ሊቀጥል ይችላል። ከዚያ በላይ ሊቀመንበር ሆኖ መቆየት አይችልም። መጀመሪያውንም ብቃቱ በራሱ ድርጅት ተገምግሞ በድርጅቱ አማካይነት በዕጩነት ይቀርባል። ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ ቆይቶ አምባገነን ሊሆን የሚችልበት ዕድልም በደንቡ ውስጥ በጭራሽ የለም። ታዲያ ይህ ከዚህ በላይ የተገለጸው አሰራር በምን ተአምር ነው ፀረ -ዴሞክራሲያዊ ተብሎ የሚነገረው። እነዚህ ተችዎች በድርጅታቸው ውስጥ በሚያሳዩት ሐቀኛና ቅን ተሳትፎ በራሳቸው ድርጅት አማካኝነት ብቁ ናቸው ተብለው በዕጩነት ሳይቀርቡ የመድረክ ሊቀመንበር ወይም ሥ/አ/ ኮሚቴ አባል ሊሆኑ የሚችሉበት አድል በእርግጥ የለም። በመጀመሪያም ሐቀኛና ቅን ታጋዮች መሆናቸውን በተግባራዊና ቅን ተሳትፎ በድርጅታቸው ውስጥ ማሳየት የተሳናቸው ሰዎች በአቋራጭ ሊቀመንበር ወይም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለመሆንና ለረጅም ጊዜም በአመራር ላይ ለመቆየት ተመኝተው ከሆነ መንገዱ የትግል እንጂ በብልጣብልጥነት ሥልጣን ላይ ወጥተው የሚኮፈሱበት አይደለም። ሥልጣን ይዘው ለረጅም ጊዜ ለመቆየትና አምባገነናዊ አመራር ለመፍጠርም ዕድል አይሰጥም። ይህንን መንገድ መከተልን ኢ-ዴሞክራሲያዊነት ነው፤ እንደ ኢህአዴግ መሪዎች ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ አይቆይም የሚሉ ከሆነ ስለዴሞክራሲያዊ ግንባር አደረጃጀትም ሆነ አመራር ተገቢ ግንዛቤ የሚጎድላቸው ስለሆነ ራሳቸውን ሊያስተካክሉና በትክክለኛው የታጋይነት አቅጣጫ ሊመጡ ይገባል። በትክክለኛው አቅጣጫ ከመጡና የድርሻቸውን አበርክተው ለሌላ ለማስረከብ ከተዘጋጁ ግን በሩ ለእነርሱም ቢሆን ክፍት ነው።
ከዚህ አልፈው ደግሞ በመድረክ ውስጥ ያልታየና የማይታወቀውን በልመና ሊቀመንበር ስለመሆን በሰንደቅ ጋዜጣ አንስተዋል። ይህ መቼም ሊከሰት የሚችልበት ሁኔታ በትክክል በመድረክ ውስጥ ቢኖር ኖሮ እውነት ሊመስል ይችል ነበር። ነገሩ ግን የመድረክን ሁኔታ በትክክል የሚያውቁትን ሰዎች ለማጭበርበር ተብሎ የቀረበ መሠረተ ቢስ ወሬ ነው። ምክንያቱም የመድረክ አመራር አባልነት ወይም ሊቀመንበርነት ታጋዮች ለቆሙለት ዓላማ ዕውቀታቸውን ጉልበታቸውንና ጊዜአቸውን ገንዘባቸውንም ጭምር መስዋዕት የሚያደርጉበት በተለይም ድርጅቶቻቸው የሚሰጡአቸውን የውዴታ ግዴታ ውክልና መወጣት ግዴታቸው ሆኖ የሚቀበሉት ጉዳይ እንጂ ቅንጣት ታህል የራራሳቸው ጥቅም የሚያገኙበት ቦታ አይደለም። ስለዚህ ካለአንዳች ክፍያ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡበት እንጂ የሚቀራመቱት ጥቅም ኖሮ አንዱ ለማኝ ሌላው ተለማኝ የሚሆንበት ቦታ አይደለም። ለመሆኑ ማን ማንን ይለምናል? ለምንስ ብሎ ይለምናል? የሚለመነውስ ምን ሊሰጥና ሊጠቅም ወይም ምን ስለሆነ ነው? የሚለመነው? አንዳች የጥቅም መቀራመት በሌለበት ቦታ ፈቃጅና ከልካይ የሆነ የተለየ ስልጣን ወይም ሃይል ያለው አካል በሌለበት ቦታ ለማኝም ሆነ ተለማኝ በፍጹም ስለማይኖር መድረክ ውስጥ እንደዚህ አይነት ነገር በፍጹም ሊኖርም አይችልም። የለምም። ከዚህ ሌላ አንድም ለሊቀመንበርነት የታጨ ሰው እርሱ ብቃት የለውም ተብሎ “እባካችሁ ምረጡኝ” ብሎ የላመነበት ጊዜ የለም። እኔ በተመረጥኩበት ዕለት ስለመተዳደሪያ ደንቡ መሻሻል ቤቱ በስፋት ከመነጋገሩ በስተቀር በግለሰብ ደረጃ ስለእኔ ብቃት ተነስቶ የተተቸበት ሁኔታ በፍጹም አልነበረም። ለመተቸት ግን የሚከለክል ነገር አልነበረም። ከዚህም ሌላ አንድ ሊቀመንበር በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በአመራሩ ደካማ ሆኖ ከተገኘ በዓመቱ አጋማሽ ላይ በሚደረግ ጠቅላላ ጉባኤ ተገምግሞ በሌላ ሊተካ ይችላል። የአንድነት ም/ቤት አባላት ይህንን ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ ቢጠቀሙበት እንጂ በጋዜጦች ላይ መሠረተቢስ ወሬ ቢያወሩ ብቃት ያላቸውም ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ሊያሰኛቸው አይችልም። በዕለቱ የተተቸው መተዳዳሪ ደንቡ ስለነበር በራሱ ሰብሳቢነት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከጠቅላላ ጉባኤው በተሰጠው መመሪያ መሠረት አሻሽሎት በዓመቱ አጋማሽ ላይ ለተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ ማሻሻያው ሊፀድቅና ለምርጫ ቦርድም ሊተላለፍ ችሎአል። ደንቡን ለወደፊቱም ጉባኤው ለማሻሻል የሚያግደው ነገር የለም። በዚህ መሠረት በመድረክ ውስጥ የመተዳዳደሪያ ደንብ የአመራርውክልና አመራረጥም ሆነ አሰራር ኢ-ዴሞክራሲያዊነት ችግር ሳይሆን እነዚህ ግለሰቦች የሚያወሩት የራሳቸውን ሕልምና ቅዠት ነው።
ሌላው የድርጅት አባልነትን በሚመለከት በአባል ድርጅቶች ሙሉ ስምምነት የሚለው ሀሳብም እስካሁን ሐቀኛና ብቃት ያለው ተቃዋሚ ድርጅት አባል ሆኖ ለመመዝገብ ሲጠይቅ አንድ ድርጅት ብቻውን ውድቅ ያደረገበት አሰራርና ወቅት እስካሁን በፍጹም አልተከሰተም። ፎርማል የሆነ የአባልት ጥያቄ ጠይቆና የአባልነት መመዘኛዎችን አሟልቶ ከላይ በተጠቀሰው የድምፅ አሰጣጥ ምክንያት አባል ሳይሆን የቀረ ድርጅት በሌለበት ዝም ብሎ ለወሬ ብቻ ይህ ደንብ መድረክ በአንድ ድርጅት ድምፅ መወሰን አቅቶት አባላትን እንዳይጨምርና እንዳያድግ አድርጓል ብሎ ማውራት “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ነውና አሁንም እነዚህ ሰዎች ወደተጨባጩ ዓለም መጥተው ቁም ነገር ላይ በማተኮር ተጨባጭ የሆኑ የመድረክም ሆነ የአባል ድርጅቶች ችግሮች የሚቀረፍበት ሁነኛ ስራ ላይ ቢሠማሩ ይጠቅማቸዋል ብዬ አምናለሁ። በዚህ ረገድ በተጨባጭ ችግር በሥራ ላይ ቢያጋጥም ግን ችግሮችን ገምግመን ደንቡን ለማሻሻል የሚያግዳቸው ነገር የለም። ስለዚህ በተግባር ያልታየን ችግር አየር በአየር ማውራቱ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።
የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት አባላት ሰሞኑን የግምገማ ሪፖርት ብለው ባዘጋጁት ሰነድም ቀደም ብሎ ድርጅቱ በድርድር የተስማማባቸውን ሀሳቦች ሁሉ የሚንዱና ስምምነቶቹን ሁሉ በሚያፈራርሱ መከራከሪያዎች የታጨቀ የመድረክ የግምገማ ሪፖርት የሚባል ሰነድ ከመድረክ አባል ድርጅቶች በስተጀርባ ሠርተው ካጠናቀቁ በኋላ ይፋ አድርገዋል። መድረክ ራሱ አንድነትም በሚሳተፍባቸው አካላቶቹ አማካይነት የሚገመግምበት አሰራር እያለ ያንን መጠቀም ትተው ለብቻቸው ለመገምገም የፈለጉበት ምክንያት ከሰዎቹ የግልጽነት ጉድለትና በራስ ያለመተማመን ችግራቸው የመነጨና ለገዥው ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ለማቀበል ከመጣደፋቸው ጋር የተያዘ ነው። ስለዚህ ከመድረክ በስተጀርባ ተሠርቶ “ቆብ ቀዶ የመስፋት” አይነት ወሬ ከሚዘበዝበው ሪፖርታቸው ፋይዳ ያለው አዲስና ገንቢ ሀሳብ ስለማይገኝ መድረክ እስከአሁን ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ ለወደፊቱም እራሱን የሚገመግምበት አሰራር ሥራ ላይ በማዋል ያሉበትን ጠንካራ ጐኖች በማጐልበት ደካማ ጐኖችን ደግሞ በማረም የተያያዘውን የዴሞክራራሲና የፍትሕ ሥርዓት የመገንባት ትግል አጠናክሮ ይቀጥላል። የመድረክ ግምገማ ባሉት ሪፖርቸው ውስጥ ስለታጨቁት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች ወደፊት በዝርዝር ስለሚጻፍበት ለዛሬው በጋዜጦችና መጽሔቶች ሰሞኑን በመድረክ ላይ ስለተነዛው መሰረተ ቢስ ወሬ ብቻ በማብራራት ጽሑፌን ለማብቃት እፈልጋለሁ።
የተከበራችሁ አንባቢያንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ በእነዚህ ግለሰቦች አማካይነት መድረክ በሕዝባችን ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ለመሸርሸር በማለም በመድረክ ፕሮግራሞች መተዳደሪያ ደንብና በአመራሩ ላይ እየተካሄደ ያለውን መሠረተቢስ ፕሮፓጋንዳ ብናወግዝም በመድረክ ላይ የሚታዩትን ትክክለኛና ተጨባጭ የሆኑትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመለየት ድክምታችንን እንድናርም በጥንካሬአችንም እንድንበረታ የሚሰጠንን ገንቢ አስተያየት በአክብሮት የምንቀበል መሆናችንን እየገለጽኩ እንደዚህ አይነት አፍራሽ ሥራዎች ላይ የሚሰማሩ ሰዎችና ሥራቸው በትግል ሂደት የሚከሰቱ ጉዳዮች ስለሆኑ በፕሮፓጋንዳቸው ግራ ሳትጋቡ መድረክ የሀገራችንን መሠረታዊና ወቅታዊ ችግሮች የመፍቻ አቅጣጫዎች ማኒፌስቶ ላይ ያስቀመጣቸውን የመፍትሔ ሀሳቦች ከግብ ለማድረስ የየበኩላችሁን አስተዋጽኦ ማበርከታችሁን በጽናት እንድትቀጥሉበት በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
ሕዝባዊ ትላችን ግቡን ይመታል
ጥላሁን እንደሻው
የወቅቱ የመድረክ ሊ/መንበር¾
( ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 402 ረቡዕ ግንቦት 14/2005 )
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar