ከበደ ኃይሌ
በዓለም ዙሪያ በደረሰው የኢኮኖሚ መንኮታኮት ምክንያት እንኳን በድህነት የላሸቁ አፍሪካ አገሮች ቀርቶ በሃብት የዳበሩ የምዕራቡ አሁጉራትን ጨምድዶ በመያዙ ህዝባቸው በኑሮ ውድነትና ከስራው ተፈናቅሎ የመንግስት፤ የማህበረሰብ፤ ...
በዓለም ዙሪያ በደረሰው የኢኮኖሚ መንኮታኮት ምክንያት እንኳን በድህነት የላሸቁ አፍሪካ አገሮች ቀርቶ በሃብት የዳበሩ የምዕራቡ አሁጉራትን ጨምድዶ በመያዙ ህዝባቸው በኑሮ ውድነትና ከስራው ተፈናቅሎ የመንግስት፤ የማህበረሰብ፤ ...
... የበጎ አድራጎት ተቋማትና የተረዳድቶ የመኖር ሰለባ ለመሆን በመብቃቱ የህዝቡን የኑሮ ችግር እንደሁናቴው ለመቋቋም መንግስታቸው ለሕዝቡ አላሰባችሁለትም ተብለው በህግ እንዳይጠየቁና ፓርቲያቸው እንዳይወቀስ የመንግሥት ወጪ የሚቀነስበትና ሕዝባቸው ልዩ ልዩ የመንግስት ዕርዳታ እያገኘ የሚኖርበትን መንገድ በመቀየሰ ላይ ይገኛሉ።
ኢኮኖሚው እስከሚሻሻል ድረስ በችግር ላይ የወደቀውን ሀዝባቸውን በተቻለው ሁሉ ለመርዳት የምዕራቡ መንግስታት ሊቋቋም የቻለው በአገር መስተዳደር ውስጥ ለህዝብ ግልጋሎት ለሚሰጡ ንብረቶች ማስተዳደሪያና ግልጋሎት ሰጪ ድርጅቶች መተዳደሪያ እንዲውል ሰርቶ የሚኖረው ህዝብ ከገቢው ታክስ እያሰቆረጠ ገቢ ማድረግና የወር ገቢውን ማሳቀወቅ ግዴታ ስላለበት ነው። ለዚህም አይነተኛ ምሳሌ/ሞዴል ሆኖ ለመገኘት ከፍተኛ የአገር መሪዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣኖች የፖለቲካ ስልጣን ኮርቻ ላይ ከመውጣታቸው አስቀድሞ በቀደምት ስራቸው ላይ ምን ያህል ደመወዝ ይከፈላቸው እንደነበረ፤ ታክስ መክፈላቸውንና የንብረታቸውን መጠን በማሳወቅ ግንባር ቀደም ሲሆኑ ይታያሉ።
እንኳን ሰለታክስ ክፍያው ገንዘቡን ከየት እንዳመጡት፡ በፈቃዳቸው ተነሳስተው ስላደረጉት የበጎ አድራጎት ችሮታና ስላበረከቱት የነጻ አገልግሎትና ህግ ለማክበራቸው ተመስግነው ለዕጩነት ይቀርባሉ ብሎም ስልጣን ላይ ይወጣሉ። ካላቸው ገቢ በላይ/በታች ከፍለው/ቸረው ሲገኙም በህግ ከመጠየቃቸውም በላይ ለአመለከቱበት የከፍተኛ ሥልጣን ስራ ቦታ ዕጩነትነ ይሰረዛሉ። ለህበረተሰቡ አገልግሎትና ለአገር እድገት የሚውለውን ታክስ ተቆራጭ ሳየውቁም ሆነ አውቀው ህግ ጥሰው ከተገኙ ስማቸው ለመቀጣጫ ጎድፎ መቀመቅ እንዲገቡ ይደረጋሉ። በዚህ ምክንት ህጉን ተከትሎ ሃላፊነቱን መወጣቱን ማረጋገጥ በህዝቡ ዘንድ እንደ ባህል ስለሚቆጠር ታክስ ያልከፈለ ነዋሪ ልጆቻቸው ት/ቤት አይገቡም፤ የረዘመ ህክምና አገልግሎት አያገኙም፤ በመንግስት መ/ቤት ያለ ጉዳያቸው አይፈጸምላቸው። ይህም በመሆኑ እንኳን ከፍተኛ ባለስልጣናት ስደተኛው የነዋሪነት ፈቃድ ለማውጣት ጥያቄ ሲያቀርብ ታክስ ለመክፈሉ ማረጋገጫ አምጣ ተብሎ የሚጠየቀው በዚህ ምክንያት ነው።
የአፍሪካ አገር መሪዎችና ባለሥልጣናት ግን የህዝብ ተገዥ ስላልሆኑ ካላቸው የስራ ዋስትናም በላይ በሥልጣን ላይ እያሉ ምን ያህል የወር ደመወዝ እንደሚከፈላቸውና የመንግስት ታክስ ይክፈሉ አይክፈሉ ለህዝብ ይፋ የሚሆንበት ስርዓት የለም። ከዚህም ሌላ መንግስታዊ/ኦፌሴላዊ የስልጣን ደረጃቸውን ጠብቀው ስራቸውን እንዲያከናውኑ እየተባለ ከደመወዛቸው በተጨማሪ የመንግስት መኪናና የኑሮ ድጎማ እየተሰጣቸው ሲኖሩ የህዝቡን ኑሮና አገራቸውን ለማሻሻል የሚያሳዩት ጥረት አጥጋቢ አይደለም። በየምክንያቱ በመንግስት ወጪ የሚደረገው የእንግዳ ማስተናገጃ ግብዣ ስፍር ቁጥር የለውም። ያላቸውን ሥልጣን በመጠቀም ፓርቲያቸው በግድም ሆነ በውድ ለረዥም ጊዜ በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን መንገድ ማዘጋጀቱ ላይ ትኩረት ይሰጣሉ እንጂ የሕዝብ መተዳደሪያ ደንቡን በመተግበር ሕዝቡን በቅንነት ሲያገለግሉ አይታዩም።
የአፍሪካ አሁግራት ህዝብና አገር ጥቅም ሲባል መሪዎች ለተወሰነ ጊዜ ስልጣን ላይ መቆየት፤የደመወዝ እርከን መቅረጽና በአግባቡ ታክስ ከደመወዛቸው ተቆራጭ እንዲሆን መመሪያ ማውጣት ወይም እነሱ ፈጽመውት ምሳሌ ሆኖ መገኘት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ደራሲው እስከሚያውቀው ድረስ (ማንም ስው ፍጹም ባሆንም) ለአገራቸውና ለህዝህብ ዕድገት በማሰብ የተቻላቸውን ግልጋሎት ለአገራቸው አበርክተው በፈቃዳቸው ሥልጣን የለቀቁ ብርቅዬ የአፍሪካ መሪዎች ቢኖሩ የታንዛንያው መሪ ጁሊየስ ኔሬሬና የሳውዝ አፍሪካው ማንዴላ ናቸው።
የአፍሪካ ህዝብ ግን የሚያስብለት መሪ ስለሌለው የኑሮ ማካካሻ ሳይሰጠው በዝቅተኛ ደመወዝ ቤተሰብ እያሰተዳደረና አልፎ ተርፎም መንገድ ላይ ቆሞ ተመጽዋች ህዝብና ለሚሄድበት ጸሎት በት አገልጋዮች ደመወዝ ክፍያ እንኳ ካላው ገቢ ላይ ቀንሶ እየመጸወተ ኑሮውን የሚገፋ ህዝብ ነው። ይህንን ለማድረግ ወደ ስራ ለመሄድ ለረጅም መንገድ የሚከፍለውን የመመላለሻ ገንዘብ ለመቆጠብ በእግሩና በከብት ጀርባ እየተመላለሰ ሰርቶ ጦም አዳሪ ነው። የግል መኪና ያለውም የነዳጅ ዋጋ ስለተወደደበት መኪናውን በእረፍቱ ቀን ብቻ ለመጠቀም ይገደዳል። ከዕለት ኑሮ ወጪው ተርፎት ተቀማጭ ገንዝብ ማስቀመጥ አይታሰብም። ደመወዙ ከወር ወር አላደርስ እያለው በአዳቫንስ/ቅድሚያ ክፍያ እየወሰደ ኑሮውን የሚገፋ ሕዝብ ነው።
በመሰረቱ ከፍተኛ ደመወዝ ለሰራተኛ እንዲከፈል የሚደረገው ሠራተኛው ጠንክሮ እየሰራ ለህዝቡ ምሳሌ ሆኖ እንዲገኝና ሌላው ዜጋ ለአገሩ እንዲያገለግል ለመሳብ ነበር። ከፍተኛ ባለሥልጣኑ ግን ከዳበረ ደመወዝ ሌላ ተጨማሪ ድጎማ እየተከፈለው የሚሰራ ባለስልጣናትና ተራው ሰራተኛ የሚከፈለው ደመውዝ ባላቸው የትምህርት ደረጃና የስራ ልምድ ተመጣጣኝ ነው ለማለት አያስደፍርም። አገራቸውን ከኢኮኖሚ ውድቀት ለማውጣትና ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ለባለሥልጣናት ከደመወዝ ሌላ የሚወጣው ጥቅማጥቅምና ድጎማ ይቁም ቢላበልም ደንቡ በስራ ላይ እንዲውል መሪዎች እራሳቸው ካልሆኑ በቀር ተራው ባለስልጣንማ የት ቆሞ። የዚህ ተጠቃሚው የፖለቲካ ዘር ተክሎ እያለመለሙ የሚጠቀሙ ጥቂቱ የበላይ መሪዎች ብቻ ናቸው።
ለመንግስት ባለስልጣናት ስለሚከፈል ደመወዝ ጉዳይ በአንድ ወቅት በጋዜጣ ላይ የወጣውን ልጥቀስ። ለመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን በወር የሚከፈለው የደመወዝ ክፍያን በተመለከተ የተጻፈ ርእስ ያዘለ ጋዜጣ አዝዋሪው መ/ቤታቸው በራፍ ላይ ቆመው ጫማውን ለሚያስጠርጉ ባለስልጣን የእለቱ ጋዜጣ ጥሩ ዜና ስለአለው ግዙ እያለ ሲወተውት መልስ የሚሰጠው ቢያጣ ይህንን ርዕስ አይተውታልን ብሎ ጋዜጣውን ወደ የፖለቲካ አባል ባለስልጣኑ ፈት ላይ ሲያቀርብ እኔ መሰሎቼን መስዬ ለማደር እጥራለሁ ይህ የሚመለከተው የሂሳብ ስራተኞችንና አዛዦቻቸውን ይመስለኛል ለእኔ ከምታሳየኝ ለኦዲተሩ ብታሳየው ስራውን እንዲሰራ ያደርገዋል ሲሉ መለሱለት ይባላል። ለነገሩ በስራ ላይ የተመደው ኦዲተርም ሆነ የሂሳብ ሠራተኛ ስራውን አጥተውት ሳይሆን ስራቸውን የሚያከናውኑት በተሰጣቸው የስራ ዝርዝር መሠረት ስለሆነና እሰተያየት ቢሰጡም ተቀባይነት እንደሌለው ስለሚገነዘቡት ነው እንጂ ስህተቱን አጥተውት አይደለም።
በከፍተኛ የሥራ መድብ ላይ ተመድበው የሚሰሩ መሪዎች ታክስ ከከፈሉ ሌላው ህዝብ የማይከፍልበት ምክንያት አይኖርም። ከፍተኛ ባለስልጣናትና ነጋዴው ታክስ በየዓመቱ መክፍል እንደሚገባው ቢታውቅም ያለተሰበሰበ፤ ህዘቡ እንደግዴታ አድርጎ ሰለማይወስደውና ውዝፍ ታክስ በወቅቱ ገቢ መሆኑ የሚረጋገጥበት ሥርዓት ስለሌለ ታክስ እሰከፋዩ በቀላሉ ይታለላል፤ስለዚህም የአፍሪካ መሪዎችና ባለስልጣናት ከህግ በላይ ስለሆኑ ባይከፍሉም አይፈረድባቸውም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኢኮኖሚ መውደቅና የውጭ ዕርዳታ መቀነሰ መንግስታትን ክፉኛ አሳሰቦ ለወታደር፤ ለጸጥታ አስከባሪውና የባለስልጣኑን የወር ገቢ መሸፈኛ የሚውል የታክስ መክፈያ መሰብሰቢያ የወጣው ህግ በሥራ ላይ ቢውልም ታክስ ከፋዩ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለው ሰርቶ አደርና ምስኪን ነጋዴው ነው። በአፍረካ አህጉራት ውስጥ በተለይ ከፍተኛ ነጋዴና ሃብታሞች ታክስ በወቅቱ ከፍለው መገኘት ሲገባቸው እኔ አልከፈልኩም ወይም ትንሽ ከፈልኩ ብሎ መናገር እንደ ጀብደኝነት ይታያል።
አነስተኛ ደመወዝ የሚከፈለው የመንግስት ሰራተኛው ኑሮውን ለመቋቋም ጉቦ ቢበላ አያስገርምም። ምክንያቱም ታክስ ሰብሳቢው/አስከፋዩም ሰራተኛ ደመወዙ አነስተኛና ችግረኛ ዜጋ ስለሆነ በኑሮው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ካላደረገ በቀር ጉቦ መብላቱ ስለማይታወቅበት ነው። ነገር ግን በስልጣን ላይ ተቀምጦ በከፍተኛ ደመወዝ የሚሰራው ባለስልጣናት ሃብት ለማካበት ጉቦ ይቀበላል። ጉቦ መቀበሉ የሚያስጠይቀው ጉዳይ ቢሆንም ይህንን የሚከታተለው መ/ቤት ባለስልጣናትን ሳሆን ቁጥጥሩ በተራው ሰራተኛ ላይ ስለሚጠነክር ታክስ ባለመክፈል የሚወቀሰውና የሚታሰረው ተራው ሰርቶ አደሩ፤ የፖለቲካ ተቀናቃኙና ጉቦ አልስጥም ባይ ባላሃብት ህዝብ ነው።
የአፍሪካ ከፍተኛ መሪዎች ታክስ መክፈል ቀርቶ ያፈሩትን የግል ሃብት ይፋ ለማድረግ ሲጠየቁ በማንገራገር የቃላት ጦርነት ይከፍታሉ። ጠያቂው ተራ ሰራተኛም በስራ ላይ የመቆየቱ ጉዳይ ያጠራጥራል። ታክስ ቫት (VAT) ላለመክፈል መቻል እራሱን የቻለ የፈጠራና የመመሳጠር ችሎታ በአፍሪካ አህጉራት እንደጉብዝና ስለሚቆጠር፤ታክስ ብቻ ሳይሆን የመብራት፤ የውሃና ምግብ ማብሰያ ጋዝ ላለመክፈል በስልጣናቸው ይጠቀማሉ፤ ለደግስና ቤት ስሰሩ የህዝብ እራዳታና የመስሪያ ቤታቸውን መሳሪያ ሲጠቀሙበት ይታያሉ፤ከስራ ሲሰናበቱም ሃብታም ሆነው ይወጣሉ፤ለስራ ጉዳይ ከአገር ውጭ ሲወጡ በውጭ አገር ያሉ ኢምባሲ መኪናና ቤት በነጻ መገልገል የሚገርም ሰው ካለ ለስርዓቱ አዲሰ ወይም ይልኙታ የያዘው ባለስልጣን ብቻ ነው።
በሠለጠነው አገር ተምረው የአገር አስተዳደር ሙያ ያላቸው፤ዕድል ገጥሟቸው በውስጡ ያለፉ፤ ያዩና የሰሙ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ስልጣን የሚይዙ የአፍሪካ መሪዎች የተማሩትንና በአይናቸው የተመለከቱትን ለአገራቸው ጥቅም ላይ ማዋል ሲገባቸው የተማሩትን ሳይጠቀሙበት ሲቀሩና እንዳልተማረ ሰው ሆነው ሃላፊነታቸውን የማይወጡት ከፍተኛ ባለስልጣናት ተጠያቂ መሆን ሲገባቸው ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ይዘው ሕዝባቸውንና የአገራቸው ሃብት ሲበዘብዙ ይታያሉ። የአፍሪካ ባለስልጣናት የቤት ኪራይና የመሪት ግብር መሰብሰብ እንጂ ለህዝብ ግልጋሎት የሚውል ታክስ ለመክፈል አይፈቅዱም እንዲያውም ታክስ እንዳይከፍሉ ወይም ከገቢያቸው እንዳይቀንስባቸው ይመሳጠራሉ፤ በተራው ህዝብ ላይ ቁጥጥሩ እንዲጠናከርበት ግፊት ያደርጋሉ።
በአጠቃላይ ስለአመታዊ ግብር ክፍያ የአፍሪካ ህዘብ ያለው አመለካከትና ንቃተ ሂሊናው ዝቅተኛ ነው። የተማሩ መሪዎች መክበርና ስልጣን ላይ መቆየት ስለሚፈልጉ ህዝቡ እንዲያውቅና ታክስ መክፈል ግዴታውና ባህሉ አድርጎ እንዲወስደው አያስተምሩትም ብሎም ያለውን ህግ በሥራ ላይ አያውሉትም፤የአገራቸው ህግ የሚሰራው የሥልጣን ተቀናቃኞችን ለመወንጀል ብቻ ነው። በተለምዶ ህዙቡ ታክስ የሚከፍለው ከደመወዙ ነው። ነጋዴው በፍላጎቱ ሄዶና ሲበዛበትም ተመሳጥሮ ገቢውን አሳንሶ ስለሚያቀርብ የሚከፍለው ዝቅተኛ ስለሆነ ለህዘብ ግልግሎት ለሚውል በቂ ገንዘብ ማሰተዳደሪያ ስሌለው አገሩ/የህዝብ ግልጋሎት አይዳብርም፡ ባይከፍሉም የሚያስገድደው ባለስልጣን የለም፤የታክስ ሰብሳቢዎቺ ሲመጡበትም ተደብቆ ያሳልፈዋል። እንዲህም ሲባል ይልኙታ ያለውና ነገ ያሰወቅሳል ብሎ የተነሳ የፖለቲካ መሪ/ባለሙያ የብሔራዊ ግዴታውን የሚወጣ ሰው የለም ማለት አይደለም። ካለ እንዲወገዝ መንግድ ይፈለግለታል፤በጥቅም ይያዛል፤ አሊም ሕይወቱን ያጣታል እንጂ ለአገር ጥቅም የሚያስብ የአፍሪካ ባለስልጣን ቁጥሩ ጥቂት ነው ቢባል አያሰገርምም።
የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ አሰተዳዳሪዎቻቸው ስር በነበሩበት ወቅት አገራቸውን ነጻ ለማውጣት የትግል ስልት የሚያሳይበት አንዱ ዜዴያቸው ታክስ መክፈል አይገባንም እያሉ ማመጽ ነበር። ቅኝ ገዥ አህጉራትም ንቅናቄውን ለማክሸፍና ህዝቡን ታክስ ማሰከፈል እንደድህነት ይመለከቱት ስለነበር ህዝቡን ታክስ ክፈሉ ብሎ ማስገደድ እንደተጸእኖ ታይቶ አቤቱታ ሰለሚሰማበት መ/ቤቶችና ግልጋሎት ሰጪ ድርጅቶች በመንግስት በጀት የሚተዳደሩ ናቸው። ከአገራችን አኳያ ብነመለከት ለምሳሌ በአጼ ኃይለሥላሴ አስተዳደር ዘመነ-መንግስት ጊዜ የጎጃም ባለዕርስት የመሬት ዓመታዊ ግብር/ታክስ ክፈል ተብሎ ቢጠየቅ የአመጽ ባህርይ ከአሳየበት ጊዜ አንስቶ ህዝብ በመንግስት ላይ የማጉረምረም ባሕርይ እየከረረ መምጣት የተጀመረበት ወቅት ነው ሲባል ይሰማል።
የአፍሮካ አሁግራት ከቅኝ አገዛዝ ሲላቀቁ በቂ ሞያተኛ ስለሌላቸው ለመንግስታት ነጻ አማካሪዎች ይመደብላቸዋል። ያልተደራጁት መሪዎች አገራቸውን የሚያስተዳድሩበት የውስጥ መመሪያ/ህግ ለይስሙላ ተሻሻሎ የሚወጣው ባለስልጣናትን የሚጠቅም ነው። በተግባር እንዲተረጎም አማካሪዎች ግፊት አያደርጉም። በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ስም ገብተው የአገሪቱን ጥሬ አንጡራ ሃብት ከባለስልጣን ጋር እየተመሳጠሩ ለመበዝበዝ እንዲያመቻቸው የሚተባበራቸውን መሪ ለማስቀመጥ በመሪዎች ምርጫ ላይ የታዛቢ አባል ይሆናሉ። በአገር ውስጥ ጉዳይ እጃችንን አናስገባም በሚሉት ስልታቸው እየተጠቀሙ እነሱን የሚቃረነውን የውስጥ መመሪያ በስራ ላይ እንዳይተረጎም እየተከላከሉ አፍሪካ ከውጭ መንግስታት ተረጂነት እንዳትላቀቅ ለጋሸ አገሮች ይጥራሉ።
ይህ ሕገ ወጥ አሰራሩ እንደባህል ተወስዶ ህዝቡ ታክስ ላለመክፈል እንደመሳሪያ እያየው ለብሄራዊ እድገት የተጣለበትን ሃላፊነት ላለመወጣት ስለሚታገል አህጉራቱም ከውጭ ችሮታ/እርዳታ እጅ ከማይት መላቀቁን እንደጦር ይፈራል። ባለስልጣናቱም ቢሆን ህግ አወጡ ለመባል ነው እንጂ ስራ ላይ ካልዋለ ህግ ቢወጣ ዋጋ የለውም፤ የሚከፈለውም/የሚሰበሰበው ታክስ በህዝብና በአገር እድገት ላይ ይዋል አይዋል ካለአድልዎ የሚቆጣጠር አስከባሪ ሰራተኛ/ድርጅት የለም። ይሁን እንጂ ስለታክስ ክፍያ የወጣውን መመሪያ በስራ ላይ ከማዋል በፊት ከፍተኛ የአገር መሪዎች በስራ ላይ እያዋሉ ምሳሌ ሆነው ካልተገኙ ተራውን ህዝብ ታክስ ክፈሉ ብሎ ማሳቸገሩ እንደፖለቲካ ተጽእኖ ተደርጎ ይወስደዋል እንጂ ለአገር ጥቅም አድርጎ ሰለማይመለከተው ላለመክፈል ሁሉም ይሸሻል። በዚህ ምክንያት ግለሰቡ ስልጣን ላይ ከወጣ በኃላ መስሎ ያድራል እንጂ ከሌሎቺ ተለይቶ መታየትን ስለማይፈልግ የተማረውን በስራ ላይ አያውልም፤እንኳን ታክስ መክፈል ለሥልጣን ሲታጭ ታክሰ መክፈሉ አይጣራም። የሚገርመው ብዙ የአፍሪካ መንግስታትና ባለስልጣናት ህዝብ የሚያወናብዱበትን ስልት ከምዕራብ አገሮች እየኮርጁ ሲጠቀሙበት ለአገር የሚጠቅም ነገር አይኮርጁም።
የአፍሪካ አካል የሆነቸው ኢትዮጵያም ለመሪዎቿና ለባላሥልጣናት የሚከፈለው የወር ደመወዝ ምን ያህል እንደሆነና ታክስ ለመክፈላቸው ህዝቡ እንዲያውቅ ይፍ አይደረግም። በኢኮኖሚ መቆርቆዝና ለህዝቡ ደህነት እስተዋጽዎ ካደረገው አንዱ ይኸው የኋላ ቀር ታክስ አሰባሰብ ሥርዓትና የወጪ ቁጥጥር ያለመኖር፤ የውጭ ባለሃብት ተረጂ ከመሆን እንድትርቅ ስለማይፈለግ ነጋዴውና ባለስልጣኑ እየተመሳጠረ አገር ከመበዝበዝ ስለማይቆጠብ ነው። ግንባር ቀደም ቢኖር አካሄዱ ወደ ፖለቲካ ሂዳሴው ተቃዋሚ ነህ ተብሎ ስለሚጠየቅ በፍራቻ ይኖራል፤ ብሎም ነጻ የብሄራዊ መብት ለመግለጽ ነጻነት የለውም። በአጠቃላይ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ መሪዎችና የከፍተኛ ባለሥልጣናት የህግና የዲሞክራሲ ተገዢ ካልሆኑና ህዝብ አቀፍ በሆነ አመራር አገራቸውን ካለመሩ አህጉራቱና ህዝቡ ከችግር አይላቀቅም፤የኢኮኖሚ ዕድገት አያሳይም፤ ብሎም ምን ጊዜም የውጭ ዕርዳት ጠባቂ ነው።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar