(አብርሃ ደስታ - ከፌስቡክ የተወሰደ)
ባለፈው እንዲህ ፅፌ ነበር፣
“… የትግራይ ህዝብ በሙሉ የህወሓት ደጋፊ ነው ማለት ኣይቻልም። ብዙ የሚቃወም ኣለ። ብዙ
የሚጨቆን ኣለ። በትግራይ የሌለው ጭቆናን የሚያጋልጥ ሰው ነው። በሌሎች ኣከባቢዎች (ከትግራይ
ውጭ) ሰው ሲታሰር ወይ ሲገደል የሚናገርለት ወይ የሚጮህለት ወገን ኣለው። በትግራይ ግን የለም።
ኣንዱ ሲታፈን ሌላው ኣብሮ ዝም ይላል። ይሄ ነው ልዩነቱ እንጂ በትግራይ ጭቆና ስለሌለ ኣይደለም።”
ከዚህ በመነሳት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም እንዲህ ጠየቁ:
“አብርሃ ደስታ፤ ያልከውን አምናለሁ፤ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅህና አንተ በተመቸህ መንገድ መልስልኝ፤
በትግራይ ሰዎች ሲበደሉና ሲጠቁ ሌላው ሰው ዝም የሚለው በምን ምክንያት ነው?”
መልስ
ኣብዛኛው የትግራይ ሰው የህወሓት መንግስት በዜጎች በደል ሲያደርስ ከመቃወም ይልቅ “ብኡ የሕልፎ” የሚል ብሂል (ወይ ኣባባል)
ተግባራዊ ያደርጋል። “ብኡ የሕልፎ” የትግርኛ ኣባባል ሲሆን Literally ‘በዛ ይለፍልን’ (ወይ ‘የባሰ ኣታምጣ’) ዓይነት ትርጉም ኣለው።
ለምንድነው የትግራይ ህዝብ ‘ብኡ የሕልፎ’ (የባሰ ኣታምጣ) በሚል የህወሓትን ጭቆና ‘ኣሜን’ ብሎ ለመቀበል የሚገደደው?
(1) ደርግ በትግራይ ህዝብ ብዙ ግፍ ያደረሰ ቢሆንም ህወሓት ከደርግ የባሰ ኣደገኛ ገዳይ መሆኑ የትግራይ ህዝብ በደምብ ያውቃል።
የህወሓት የኣገዳደል ወይ ጭቆና ስልት በጣም የረቀቀ ነው። በዚህ የረቀቀ መንገድ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ተገድለዋል ወይ እንዲጠፉ
ተደርገዋል። ስለዚ የትግራይ ህዝብ ‘ህወሓት ከደርግ የባሰ ኣደገኛ ነው’ ብሎ ያስባል፤ ይፈራልም። ለምሳሌ እኔ ህወሓትን ፊት ለፊት
ስቃወም ብዙ ጓደኞቼ ህወሓት ሊገድለኝ እንደሚችል ስጋታቸው ያካፍሉኛል። (የህወሓት ተግባር በደምብ ስለሚረዱ)። ይህም ሁኖ ግን
በኣሁኑ ሰዓት ብዙ የሚቃወም ኣለ። (ፓርቲውም እየተዳከመ ነው)።
(2) የትግራይ ህዝብ: ህወሓት ደርግን ማሸነፍ በመቻሉ (ደርግ ኣስፈሪ ነበር) ‘ሃይለኛ ነው’ የሚል የሃሰት ግምት ተሰጥቶታል። በዚ መሰረት
ህወሓት በሰለማዊ ተቃውሞ ስልጣን ሊለቅ ይችላል የሚል እምነት የለውም። የህወሓት ካድሬዎች (ፖሊት ቢሮ ኣባላትን ጨምሮ) ለህዝቡ
የሚናገሩት ይሄንን ነው። “ጫካ ገብተን፣ ብዙ መስዋእት ከፍለን ያመጣነው ስልጣን በምላሳቸው ለሚቃወሙን የደርግ ርዝራዦች ስልጣን
ኣሳልፈን ልንሰጥ ኣንችልም ይላሉ።
የትግራይ ህዝብ ታድያ እንዴት በሰለማዊ ተቃውሞ ስልጣን ሊለቅ የማይችልን ስርዓት ይቃወም? ህዝቡ ህወሓቶች ከስልጣን
እንደማይወርዱ ኣምኖ ከተቀበለ ፣ መቃወም ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን መረዳቱ ኣይቀርም። መቃወማቸው ዉጤት ካላመጣ
የሚቃወሙ ሰዎች ይገለላሉ፣ የባሰ በደል ይደርሳቸዋል። (የEDU ደጋፊዎች ነበሩ ተብለው የተፈረጁ ሰዎች እስከኣሁን ድረስ በመጥፎ ዓይን
ይታያሉ)።
ከተቃወሙ ስራ ኣያገኙም ወይ ከስራቸው ይባረራሉ። የመንግስት ኣገልግሎት (መብታቸው ቢሆንም) ይነፈጋሉ። ለምሳሌ ተቃዋሚ
ፓርቲዎችን የደገፉ ሰዎች፣ ከመንግስት ምንም ዓይነት ድጋፍ (የፖሊስ፣ ዳኝነት፣ የደህንነት ከለላ ባጠቃላይ) ‘ኣንፈልግም’ ብለው
እንዲፈርሙ (መቃወምን ከመረጡ ማለት ነው) የሚያስገድድ ማስፈራርያ ይደርሳቸዋል (በተለይ በገጠር ኣከባቢ)።
ስለዚ በትግራይ መቃወም ማለት የመንግስት (ፓርቲ) ለውጥ ለማምጣት መታገል (ከተሳካም ገዢው ፓርቲ መቀየር) ማለት ሳይሆን
የመንግስትን ኣገልግሎት ላለማግኘት መወሰን (በራስ ላይ ችግር መፍጠር) ማለት እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህ የምንረዳው ነገር
ቢኖር በትግራይ መቃወም ክፉኛ እንደሚጎዳ ነው። ለዚህ ነው ኣንዱ ሲታፈን ሌላው ኣብሮ ዝም የሚለው።
አብርሃ ደስታ
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar