ባለፈው ዓርብ የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙርያ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ ስብሰባዎቹ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የተካሄዱ ሲሆን፣ የከተማው ነዋሪዎች አሉ የሚሏቸውን ችግሮች አቅርበዋል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ የተካሄደውን ውይይት የመሩት ቀጣዩ የአዲስ አበባ ከንቲባ ይሆናሉ ተብለው በፓርቲያቸው የታጩት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ድሪባ ኩማ ናቸው፡፡
በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ የተካሄደውን የአራዳ ክፍለ ከተማ ስብሰባ የመሩት ከአቶ ድሪባ ጋር ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ይመጣሉ ተብለው የሚጠበቁት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ናቸው፡፡
በብሔራዊ ቴአትር ቤት የተካሄደውን ስብሰባ የመሩት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና የመንግሥት ተጠሪ የሆኑት ወ/ሮ አስቴር ማሞ ናቸው፡፡
አብዛኛዎቹ የስብሰባ መድረኮች ላይ ኅብረተሰቡ ሥር የሰደዱ ናቸው የሚላቸውን ችግሮች አንስቷል፡፡ የኑሮ ውድነት፣ የመኖርያ ቤት እጥረት፣ ከመኖርያና ከንግድ ቦታ መፈናቀል፣ በዝቅተኛ እርከን ላይ የሚሠሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚፈጽሙዋቸው አስተዳደራዊ በደሎች፣ ሙስና፣ እሳት አደጋ በሚነሳበት ወቅት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ኤጀንሲ አደጋውን ለመቀነስ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ደካማነት፣ የትራንስፖርት ችግር፣ የንፁህ ውኃ አቅርቦትና ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮች በሰፊው ከተነሱት ችግሮች መካከል ናቸው፡፡
ይህ ስብሰባ የተካሄደው በአዲስ አበባ ከተማ በአጭር ጊዜ መፈታት ያለባቸውን የኅብረተሰቡን ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የተያዘው ዕቅድ አካል ነው፡፡ ከአንድ ወር በፊት ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የኅብረተሰቡን ችግር ለመፍታት መታቀዱን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ መሠረት በወረዳዎችና በክፍላተ ከተሞች እንዲሁም በማዕከል ደረጃ ሊፈቱ የሚገባቸውን አቤቱታዎች መፍትሔ ለመስጠት ይፋዊ ዘመቻ መጀመሩን ማሳያ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ይህ የተጀመረው ቅሬታ የመፍታት ሥራ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅና የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመፍታት በማሰብ ነው ከነዋሪዎች ጋር ስብሰባ የተቀመጡት ተብሏል፡፡ በዚህ ስብሰባ አቶ ድሪባ በአጭር ጊዜ፣ በመካከለኛ ጊዜና በረዥም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮች በቀጣይነት ተለይተው ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ለኅብረተሰቡ ቃል ገብተዋል፡፡ ጨምረው እንደገለጹትም ቀጣይ ስብሰባዎችን በየወሩ እያካሄዱ ችግሩን እንደሚፈቱ አስረድተዋል፡፡
ምንጮች እንደሚገልጹት አቶ ድሪባና አቶ ተፈራ ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከአዲስ አበባ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ሥራዎች ሲያከናውኑ የቆዩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ በቀጣይነት ለእነዚህ ባለሥልጣናት የከተማውን ቁልፍ ለመስጠት ያቀደ መስሏል ይላሉ ምንጮች፡፡ ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲገናኙ ማመቻቸቱን ይጠቅሳሉ፡፡
በሌላ በኩል ኢሕአዴግ ለአዲስ አበባ ከሚያቀርባቸው አምስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍንን አካቷቸዋል፡፡ ወ/ሮ አዜብ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚወዳደሩ ሲሆን፣ በዚህ ጣቢያ ከብቸኛው የኤዴፓ ዕጩ አቶ ወንድወሰን ተሾመ ጋር ይወዳደራሉ፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar