ሚዲያ ከስሜታዊነት፣ ከስጋና ደም ድምር፣ ከችኩል ውሳኔና ግብታዊነት ነጻ ለመሆን ሌት ተቀን መስራት እንዳለበት ባለሙያዎች አበክረው የሚናገሩት ዓቢይ ጉዳይ ነው። ሚዲያ ስንል ደግሞ ሁሉንም ነው – የኅትመት፣ የምስል፣ የድምጽ፣ የድረገጽ፣ የዲጂታል፣ የማኅበራዊ ድረገጽ፣ … ። ሁሉም ሚዲያዎች አሻግሮ በማየት ህዝብንና አገርን የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው። ጋዜጠኞች ወይም እንደ ጋዜጠኛ የሚሠሩ ሁሉ ከየትኛውም ሙያተኛ በላይ ሃላፊነት ሊሰማቸውም ግድ ነው። ለዚህም ነው በጋዜጠኝነት ሙያ “አመጣጥን፣ አሁንም አመጣጥን፣ አሁንም አመጣጥን … “ባላንስ” አድርግ” የሚባለው!!
ከኢህአዴግ ዓይነ ያወጣ ውሸትና ዝግነት የተነሳ ሁሉንም መረጃዎች የማመጣጠኑ ሙያዊ ሃላፊነት ለመወጣት ፈተና ቢያጋጥምም በከፍተኛ ደረጃ ጥንቃቄ ልንወስድባቸው የሚገባን ጉዳዮች አሉ። ከነዚህ ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋናው የሃይማኖት ጉዳይ ነው። እውነት ለመናገር አሁን ባለው የሃይማኖት ውዝግብ ህዝብ ግራ ተጋብቷል። መሰላቸቱንም እየገለጸ ነው። ሲመረው “አረ መግዱ” ሊል ይችላል። ይህንን የሚለው ደግሞ የማይደግፈው ብቻ ሳይሆን እየተደገፈና እየተሞካሸ ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉም ወገን!!
እንደሚታወቀው አገራችንን ሊጠብሳት እያዘጋጃት ያለው የ”ጎሳ ፖለቲካ” ደራሲውና ቀማሚ በሞት ቢለዩም የሚያበርደው አስተዋይ መሪ አልተገኘም፡፡ በማስተዋል ማርከሻውን ለሚቀምሙም በቂ ጆሮ አልተሰጣቸውም – ጩኸቱ እጅግ ያደነቁራልና። ከውጪም ከውስጥም የሚረጨው የጎሳና የ”ደም” መርዝ ሳያንስ አሁን ደግሞ በሃይማኖት ተንተርሶ የተጀመረው አለመግባባት አስደንጋጭ ይዘት እንዳለው አያጠያይቅም። ተወደደም ተጠላም ያስፈራል። ኢህአዴግ ባቀናበረው “የድርሰት” ፊልም መነሻ ሳይሆን በበርካታ መረጃዎች የተደገፈ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል።
ሁሉም ችግሮች በሰለጠነ መንገድ መፈታት የሚችሉ ቢሆንም ኢህአዴግ በሚከተለው “የደንቆሮና ድንቁርና የወለደው (አስፈሪ) የፍርሃት ፖለቲካ” ሳቢያ ነገሮች እየተካረሩ አገርና ህዝብ ላይ ሲያነጣጥሩ ማየት ተለምዷል። በሌላ አነጋገር በኢህአዴግ ግትርነትና “ያለ እኔ” በሚል በሚከተለውና ራሱም ባመነበት “የበሰበሰ አስተሳሰብ” የተነሱ ችግሮች ተጠራቅመው መጨረሻቸውን ህዝብና አገር ላይ አድርገዋል። በተለያዩ ቦታዎች የደረሰውን አሰቃቂ መከራ፣ ግድያና መፈናቀል አንዘነጋውም። ኢህአዴግ አልሰማ ብሎ ኤርትራን ከኢትዮጵያ በላይ አፍቅሮ የማይረሳ የታሪክ ዋጋ አሳጥቶናል። ተቆጥሮ የማያልቅ የኢኮኖሚ ኪሳራ አድርሶብናል። በወንድሞቻችንና በጭቁን ህዝብ ደምና አጥንት ፈርዷል። ብዙ፣ ብዙ፣ እጅግ ብዙ፣ … ኢህአዴግ ክፋቱና አረመኔነቱ ተዘርዝሮ አያልቅም። በበርካታ ምክንያቶች ኢህአዴግን እንቃወማለን፤ አጥብቀን እናወግዛለን፤ ለሥርዓቱ መለወጥ እና ለፍትሕ እንታገላለን። በኢትዮጵያችን ግን አንጫወትም። በኢህአዴግ መወገድና ማስወገድ ሰበብ ግን በጭፍን በኢትዮጵያችን ላይ አንቀልድም። ኢህአዴግ ሌላ፤ ኢትዮጵያችን ሌላ!!
ከላይ የዘረዘርናቸው ችግሮች ደጋግመን እንደምንለው፣ ሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት በቀናነትና በመቻቻል ሊፈቱ የሚችሉ ነበሩ። በገዢውም ሆነ በተቃዋሚዎች ውስጣዊ አደረጃጀትና ውስጠደንብ የተለየ አመለካከት ማራመድ ወንጀል ባይሆን ኖሮ፤ በልዩነት ላይ በመከራከር ምርጫው ገና ድሮ የህዝብ እንዲሆን በተደረገ ነበር። ግን አልሆነም። ተጀምሮ ነበር፤ ከሸፈ። በመጨረሻም አሁን ለሰለቸንና ላንገፈገፈን “የጋለሞታ ፖለቲካ” ተዳረግን። እንዘርዝረው ቢባል ስፍራውም ጊዜውም አይበቃምና አሁን አሳሳቢ ስለሆነው ጉዳይ እንቀጥል፡፡
“መብታችን ይከበር” በሚል የተነሱት የእስልምና እምነት ተከታዮች ጉዳይ አንገብጋቢ እንደሆነ ከሚሰማቸው ክፍሎች ተርታ ነን። “ድምጻችን ይሰማ” በሚል የተጀመረው ትግል ዓመት ቢሞላውም ከመርገብ ይልቅ የመወሳሰብ አዝማሚያ እየያዘ ነው። አዳዲስና የከረሙ፣ ዓመት ያስቆጠሩ መረጃዎችም እየተሰሙበት ነው።
በእኛ እምነት የፖለቲካዊ፣ የሃይማኖታዊ፣ የማኅበራዊ፣ የጾታዊ፣ … “ድምጻቸው እንዲሰማላቸው” የጠየቁም ሆነ መጠየቅ የሚፈልጉ “ድምጻቸው ሊሰማ” ይገባል ብለን በአጽዕኖት እናምናለን። አሜሪካዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ “በአንዲት ቦታ የሚፈጸም ኢፍትሃዊነት በሁሉም ቦታ ለሚገኝ ፍትሃዊነት አደጋ ነው” ብለው የተናገሩትን ቃል በሙሉ ልብ ተቀብለን የምናስተናግደው ብቻ ሳይሆን በአገራችን ተግባራዊ እንዲሆንም የምንታገልለት ነው፡፡ እንዲሁም “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ ሊሆን አይችልም” የሚለውን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መሪ መፈክር እኛም በሚቻለን ሁሉ ከፍ አድርገን የምንፈክረውና የምንሟገትለት ነው፡፡ ሆኖም የሰው ልጅ መብት ሊገፈፍ እንደማይገባ ስናምንና ለዚሁም ተግባራዊነት እገዛ ስንሰጥ ግን እስካሁን እንዳደረግነው አሁንም ጥንቃቄ እናደርጋለን። ይህም ለመብት መከበር ካለን የጸና እምነት ባልተናነሰ ዋጋ የምንከፍልበት አቋማችን ነው። ግልጽ እናድርገው፡፡
የሙስሊም ወንድሞችና እህቶች ጥያቄ በፊት ለፊት የተቀመጡት ሶስቱ ጉዳዮች ከሆኑ ከየአቅጣጫው እንደሚባለው ችግር የለውም። “መብቴ ይከበርልኝ፣ እርዱኝ” ተብሎ የሌላውን መብት የመጎሸም አዝማሚያ ካለ ግን “ጠርጥር ከገንፎ ውስጥም አለ ስንጥር” እንላለን፤ ካስፈለገም “ወራጅ አለ” እንላለን፤ ካለብን ኃላፊነት በመነሳት ሌሎችም እንዲወርዱ እንመክራለን። ቆም ብለን እንድናስብ እንገደዳለን።
በተለያዩ መገናኛዎች ኢትዮጵያ ላይ በአምላክ (ስሙን በየትኛውም ሃይማኖት በመጥራት) ሲዛት እየሰማን ነው። ኢትዮጵያን በመቆጣጠር ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ወይም ኢህአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ያስምል እንደነበረው በዚያ መልክ መንግስት ለመመሥረት ዓላማ እንዳላቸው ባደባባይ የሚናገሩትን እያዳመጥን ነው። ጉዳዩ በዴሞክራሲና በህዝብ ፈቃድ ቢሆን ባልከፋ ነበር። አሁን የሚሰማው ፉከራ “ድምጽን አሰምቶ መብትን በማስከበር” አቀባባይነት “እንትኖችን … እናጠፋለን” የሚሉና ለዚህ ዓላማ መሳካት ሁሉም ዓይነት ዝግጅት ያደረጉ የመኖራቸው ጉዳይ ነው። ይህንን ከሚሰብኩት አንዳንዶቹ እስከመመለክም ደርሰዋል። ምንም እንኳ ይህ አመለካከት “የጥቂቶች ወይም የተወሰኑ ግለሰቦች ነው” የሚል መከራከሪያ ቢሰጥበትም፣ “የግለሰቦች” አስተያየት ውስጥ ካለው የክፋት መጠን የተነሳ አገርና ህዝብ ላይ በሚያነጣጥሩ ጉዳዮች ላይ ዝምታን መምረጥ የክህደት ያህል ሆኖ ይሰማናል። አንድም ሰው ቢሆን አገራችን ላይ ሲዝት ማረቅ ይጠበቅብናልና። የጠላነው የሃይልና የማስፈራራት መንገድን ነውና!! በዛቻ፣ በመሃላ፣ … መብትን ማስከበር ወይም ለማስከበር መነሳት ውጤቱ ምን እንደሚሆን ኢህአዴግ ለ21 ዓመታት አሳይቶናል፤ አሁንም እያየን ነው፡፡ በየትኛውም መልኩ ይሁን እንዲደገም አንፈልግም!
ሃይማኖት ያላቸውም ሆኑ ሃይማኖት የሌላቸው … ተደራጅተው አገር ለመምራት የህዝብና የፓርቲያቸውን ፈቃድ ካገኙ እሰየው ነው። ሁሉም ዜጎች የሚናፍቁት ነው፡፡ ከዚህ መንገድ ውጪ ኢህአዴግን ስለምንጠላ በሚል የሳሳ ስሌት አገርንና ህዝብን ታሳቢ ሳናደርግ መጋለብ አንመርጥም። ኢህአዴግን መቃወምና አገርን መጥላት ለየቅል ናቸው። ኢህአዴግ ሌላ፤ ኢትዮጵያችን ሌላ!!
(ፎቶ፡ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ)
|
lørdag 16. februar 2013
ኢህአዴግ ሌላ፤ ኢትዮጵያችን ሌላ!!
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar