lørdag 5. januar 2013


ዛሬም ጽኑ መሆናችንን ያረጋገጠ ታላቅ የተቃውሞ እለት!!!

ድምፃችን ይሰማ
የመጀመሪያው ጁምአ በድል ተጠናቋል፡፡
ተጨማሪ ከተሞች ትግሉን ዳግም በይፋ እየተቀላቀሉ ነው፡፡
ዛሬም ለነጻነት ጠያቂዎች ምላሹ ጥይት ሆኗል፡፡
ከአንድ አመት በፊት የአወሊያ ተማሪዎች ጥያቄ ሰሚ በማጣቱ የተወለደው ህዝባዊ ንቅናቄ መላ ሃገሪቱን አዳርሶ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ መላው ህዝባችንም ‹‹365 ቀናት ለሃይማኖት ነፃነት›› በሚል በአራት ሳምንታት የተከፈለ ልዩ መርሃ ግብር መታደሙን ከጀመረ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል፡፡ ‹‹የአወሊያ ተማሪዎችና የጥያቄዎቻችን ሳምንት›› በሚል የተሰየመው የመጀመሪያው ሳምንት መርሃግብር አካል የሆነው የጁመዓ ውሎም በመላው ሃገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የዛሬው ህዝባዊ ተቃውሞ ከአንድ አመት በፊት በአወሊያ ግቢ ተወስኖ በነበረበት ይዘት ሳይሆን ከዋና ከተሞች እስከ ትናንሽ የገጠር ቀበሌዎች በአላማና በተግባር ባስተሳሰረ ከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ ነበር የተከናወነው፡፡ የጥያቄአችን መነሻውም፣ አካሄዱም፣ መድረሻውም ህዝባዊ ነውና ህዝባዊ ውበቱንና ጥንካሬውን ጠብቆ ይቀጥላል፤ ጥያቄዎቻችን እስኪመለሱ ድረስ::ዛሬም ጽኑ መሆናችንን ያረጋገጠ ታላቅ የተቃውሞ እለት!!!
የዛሬው የጁምአ ተቃውሞ በታላቅ ድምቀት ነበር በአገሪቱ በሚገኙ በርካታ ከተሞች የተካሄደው! ዛሬ በእርግጥም ለሚደርስባቸው ተከታታይ ግፍና በደል እጅ ላልሰጡት ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ታላቅ ትርጉም ያላት ቀን ሆና አልፋለች! በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በበርካታ የአገሪቱ መሳጂዶች በመገኘት መንግስት አመቱን ሙሉ ሲወስደው የነበረውን ህገ ወጥ እርምጃና የሰብአዊ መብት ጥሰት በተባበሩ ድምጾቻቸው አውግዘዋል፡፡ በአዲስ አበባው የአንዋር መስጊድ ተቃውሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ የተገኘ ሲሆን ለወትሮው ሁሉም ‹‹365 ቀናት ለሃይማኖት ነጻነት›› የሚለውን መፈክር በነፍስ ወከፍ በወረቀት፣ በጨርቅ እና በሌሎች ቁሶች ላይ አስፍሮ ነበር በቦታው የተገኘው፡፡ ምንም እንኳን ከየክፍለ ከተሞቹ በሺዎች የሚቆጠሩ የገዢው ፓርቲ አጎንባሾች የተቃውሞውን ድምቀት ለማደብዘዝ እና የጸጥታ እክል ለመፍጠር በቦታው ተገኝተው ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ያንን አስደማሚ የሕዝብ ማእበል ግን ተቃውሞውን ከማሰማት ያገደው ነገር አልነበረም! ተቃውሞውን አሰምቶም በሰላም ተመልሷል፡፡
በሳምንቱ ቀናት ታላላቅ ኢማሞቿ አይን ባወጣው የመንግስት እርምጃ እና በአፈሙዝ አስገዳጅነት የተባረሩባትና በአህባሽ አሰጋጆች የተተኩባት ደሴ ከተማም በተቃውሞ ደምቃለች፡፡ ሸዋበር መስጊድ እስከአፍንጫቸው በታጠቁ አድማ በታኝ ፖሊሶች መከበቧን ከቶውንም ያስተዋለች አትመስልም ነበር! በውስጧና በዙሪያዋ ያቀፈቻቸው፣ በጉያዋ የወሸቀቻቸው እልፍ አእላፍ አዛውንቶቿ፤ ሴቶቿ፣ ወንዶቿ፤ ወጣቶቿ ድምጻቸውን በጋራ አሰምተውባታል፡፡ ገና አዲሱ የአህባሽ ኢማም ኹጥባ ለማድረግ ወደ ሚንበሩ ሲያመራ ኹጥባውን አቋርጠው ከሚንበሩ እንዲወርዱ ያስገደደው እጅግ ጠንካራ ተቃውሞ ሀሰት በሐቅ ፊት ችሎ የሚቆምበት እግር እንደሌለው አረጋግጧል፡፡ ሙስሊሞች ያነገቧቸው ነጫጭ የወረቀት መሳሪያዎች ‹‹365 ቀናት ለሃይማኖት ነጻነት!›› በሚሉ የቀለም ጥይቶቻቸው የሚሊዮችን ቤት ያንኳኳው የትግልና የሶብር አመት ለምን ይህን ያህል ዋጋ እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡ በሰላምም ተበትነዋል፡፡ በቦታው የተገኘው ህዝበ ሙስሊም ‹‹መሳጂዶቻችን ይከበሩልን! ኢማሞቻችን ይመለሱልን! ጭቆናው ይብቃ! ባገራችን ሰላም አጣን!›› በሚሉ መፈክሮች ደሴን ንጧታል፡፡ በጥቂት የመንግስት ቅጥረኞች መርሀ ግብሩን ለመበጥበጥ የተደረገው ጥረትም በደሴ ህዝብ ሰላማዊነትና የበሰለ አንድነትና እርምጃ ከሽፏል፡፡
በዚያው በአማራ ክልል በወልዲያ ከተማ በመስጂድ አል ባሲጥ የተደረገው ከፍተኛ ተቃውሞም የትግሉን ዜማ ዳግም አድምቆታል፡፡ ምንም እንኳን ከዛሬው የጁምአ ሶላት መልስ በርካታ ሙስሊሞች በጸብ አጫሪዎቹ ፖሊሶች ቢታሰሩባትም ካሁን ቀደም ድንቅ የሶደቃና የአንድነት ፕሮግራም ያስተናገደችው ይህቺው ከተማ ዛሬም ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጋር አንድ ላይ መሆኗን ደምቆ በተሰማ ተቃውሞዋ አብስራለች፡፡ በርካታ ወጣቶቿ ከየቤታቸው ታፍነው ሲወሰዱባት ብትቆይም ‹‹አልበገርም!›› የሚል ቁርጠኝነቷን አሳይታለች፡፡ የወረባቦዋ ቢስቴማም እንደወልዲያ ሁሉ በታላቅ ተቃውሞ ደምቃ ውላለች፡፡
የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ በርካታ ተቃውሞዎችን ሲያስተናግድ ነበር የዋለው፡፡ የፍትህ ቀንዲል የነበረችው የአባ ጅፋሯ ጂማ ከተማ በፈትህ መስጊድ በተሰባሰቡት ጀግኖቿ የተሳሰረ ድምጽ እስካሁን 365 ቀናት የፈጀው የመብት ትግል ዳር ሳይደርስ ሙስሊሞች እጅ የማይሰጡ መሆናቸውን ያለማወላወል አረጋግጣለች፡፡ በኢሉባቦር ዞን በምትገኘው በደሌ ከተማም እንደ አሁን ቀደሙ ሁሉ በጣም የደመቀ ተቃውሞ ተስተናግዷል፡፡ በአዳማ ከተማ በጀሚአል ሐቢብ መስጊድ ቅጥር የተሰባሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በበኩላቸው ለሀይማኖታዊ በደል የሚያጎበድድ ትከሻና ጀርባ የሌላቸው መሆኑንና መንግስት እየፈጸመ ያለው ህገ ወጥ ውንብድና መቆም እንዳለበት በመፈክሮቻቸው ገልጸዋል፡፡ በሻሸመኔ ከሚገኘው አል ሂካም መስጊድ የወጣው ድምጽም ይኽው ነበር – ነጻነት፡፡
በኦሮሚያ ክልል በሚገኙት በዶዶላ እና በባኮ ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞ ከጁምአ በኋላ የተሰማ ሲሆን በመቱ ከተማ ነጃሺ መስጊድና በሃሮማያም እንዲሁ እጅግ በርካታ ማህበረሰብ የተገኘበት ተቃውሞ ተካሂዷል፡፡ አዎን! በኦሮሚያ ክልል የተደረጉት በርካታ ተቃውሞዎች ድምጽ ፍጹም አንድና አንድ ነው – ‹‹ድምጻችን ይሰማ! መብታችን ይከበር!›› የሚል! ሕዝብ ይህን ሰላማዊ መፈክር ቢልም ግን ለመተኮስ ሁሌም የሚቋምጡት የመንግስት ፌደራሎች በዛሬው ተቃውሞ ደም አፍስሰዋል፡፡ በሐረር ከተማ ኢማን መስጊድ ተቃውሞ በመደረግ ላይ ሳለ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የመስጊዱን አጥር በሀይል ጥሶ በመግባት ከፍተኛ ድብደባ መፈጸም ጀምረዋል፡፡ በመስጊዱና አቅራቢያው በሚገኘው ሕዝብ ላይ ፖሊሶች የጥይት ቃታ በመሳባቸው 3 ያህል ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በርካቶችም ቆስለዋል፡፡ ከተገደሉት ውስጥ አንዱ የሰባት አመት ሚስኪን ህጻን ልጅ መሆኑ ሲታወቅ ቀሪዎቹ ልጆን ወደ ሆስፒታል ለማድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ የሟች እጻን ልጅ እናት ልጇን ለመታደግ ባደረገችው ጥረት በጥይት ተመትታ ሆስፒታል የገባች መሆኗም ተነግሯል፡፡
አረንጓዴዋ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች መገኛ የሆነችው ደቡብ ክልል ለዛሬው የትግል ጥሪ በርካታ ተቃውሞዎችን አዋጥታለች፡፡ በውቢቷ ሐዋሳ ለከተማይቷ ከረጅም ጊዜ በኋላ የመጀመሪያ የሆነው ተቃውሞ በራህማ መስጂድ የተካሄደ ሲሆን ድምቀቱም በርካቶችን ያስገረመና ለቀጣይ ተሳትፎ የሚያነሳሳ ነበር፡፡ በአርባ ምንጭ ከተማም እንዲሁ የተካሄደው ተቃውሞ እጅግ የደመቀና የብዙዎችን ሞራል ከፍ ያደረገ ሆኖ አልፏል፡፡ በዚያው ለምለም ክልል የምትገኘው የንግድ ማእከል ወራቤ ከተማም ካሁን ቀደም በአንድነትና በሶደቃ ፕሮግራሞች የደመቀችውን ያህል ዛሬም በአቡበክር መስጂድ በተደረገው ደማቅ የተቃውሞ ፕሮግራም አመት የሞላውን የሙስሊሞች የፍትህ ጥሪ ከፍ አድርጋ አሰምታለች፡፡ ወልቂጤ ከተማ በሚገኘው ረቢእ መስጊድም እንዲሁ የደመቀ ተቃውሞ በውብ መፈክሮች ታጅቦ ተስተጋብቷል፡፡
በጥቅሉ ተቃውሞ የተካሄደባቸው ቦታዎች አዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ጅማ፣ በደሌ፣ አዳማ፣ መቱ፣ ሃረር፣ ዶዶላ፣ ባኮ፣ ሃሮማያ፣ ወልዲያ፣ አርባ ምንጭ፣ ሃዋሳ፣ ወራቤ፣ ወልቂጤ፣ ሻሸመኔ እና ቢስቴማ ከተሞች ነበሩ! የተቃውሞው ድምቀትም አመርቂ ሆኖ ታይቷል፡፡ በዚህ ታላቅ የትግል ዝክረ አመት ተቃውሟችን ህዝቡ ለ365 ቀናት ያልተመለሱ ጥያቄዎቹን በነፍስ ወከፍ በድምፅና በፅሁፍ ይዞ አደባባይ መውጣቱ ትግላችንን በየትኛውም አፍራሽ ስያሜ ለመጥራት የሚደረገውን እኩይ ሩጫ ከንቱ ያስቀረ ነበር፡፡ ‹‹ከ365 ቀናት በኋላ ድጋሚ የቀረበ ጥያቄ›› መባሉም ህዝብ የሚፈልገው መልስ በመሆኑ ዛሬም ጊዜው አለመርፈዱን የሚያመላክት ነው፡፡
በሰላማዊ የመብት ትግል ሂደት ውስጥ ህዝብን ጠልፎ መጣል የሚቻልባቸው ወጥመዶችን በሙሉ ህዝበ ሙስሊሙ እንዳከሸፋቸው ዛሬ ሁሉም ተረድቷል፡፡ ሩጫው እሾሃማ ተራራ ላይ ይሁን እንጂ ከተራራው ጫፍ ካለችው እውነት ከመድረስ ግን የሚገታው አይኖርም፡፡ ይህ ህዝብ በጊዜያዊ አጀንዳ አልተሰባሰበምና አላፊ ችግር አይበትነውም፡፡ አላማውን ጠንቅቆ በማወቁም የሚሄድበት አይጠፋውም፡፡ የህዝብን ልብ ለማሸሽ 365 ቀናት ጥፋት ከሚዶለትባቸው ስብሰባዎች ይልቅ ለህዝብና ለሃገር የሚበጀው መፍትሄ ቀላልነቱ እንዴት እንደተዘነጋ ለሰሚውም ለተመልካቹም ለእኛም ግራ ነው!
የዛሬውን የድምፃችን ይሰማ የተቃውሞ ውሎ ልዩ የሚያደርገው መላውን ህዝብ ማንቀሳቀሱ ብቻ ሳይሆን መንግስት ለህዝቡ ሊመልሳቸው ያልፈለጋቸው 3 ቀላል ጥያቄዎች 365 ቀናትን ያለ ምላሽ መሻገራቸው ነው፡፡ በተጨማሪም እስካሁን ተቃውሞ ያላስተናገዱ የነበሩ ከተሞች ሳይቀሩ ዛሬ በተቃውሞ መድመቃቸው የህዝቡ ጥያቄ ካልተመለሰ ተቃውሞው እየሞቀ እንጂ እየቀዘቀዘ እንደማይሄድ ያለማወላወል የሚያረጋግጥ ነው – ሰሚ ጆሮ እና ተመልካች አይን ላለው መንግስት! ከዚህም በላይ እልህ አስጨራሽ ጥያቄን የማስጣል ዘመቻ በመንግስት ሙሉ አቅም ተተግብሮ ሳለ በህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ ላይ የይዘት ቀርቶ የቅርፅ ለውጥ እንኳን ለመፍጠር አለመቻሉ ጥያቄዎቹ በህዝበ ሙስሊሙ ልቦና ምን ያህል መስረጻቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በአገራችን ለህዝብ የሚገባውን ክብር አለመስጠት ቢለመድ እንኳን ፖለቲካዊ ብልሃት መጥፋቱን ህዝብ እስከመጨረሻው እንዲረዳ ማድረግ ግን እንደ መንግስት የጤና ሊሆን አለመቻሉ ግልጽ ነው! ያለጥርጥር መንግስት ወደልቦናው ይመለስ ዘንድ ግድ ይላል! በጠብ መንጃ ሀይል በሰዎች እጅ ያለን ነገር ፈልቅቆ ማውጣት ይቻል ይሆናል!… በልባቸው ስምጥ ሸለቆ ጠልቆ የተቀበረን ብሶትና ተፈጥሮአዊ መብት ነቅሎ ያሚያወጣው መሳሪያ ይኖር ይሆን?
ከእለቱ የተቃውሞ መርሐ ግብር መጠናቀቅ በኋላ አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ፖሊስ ሙስሊሞችን ሲይዝ የነበረ መሆኑ የተሰማ ሲሆን አሁን ዘግይቶ በደረሰን መረጃም መንግስት በደሴ እና በሌሎች ከተሞች ቀን ተቃውሞ ሲያሰማ የዋለውን ሰላማዊ ሕዝብ ቤት ለቤት የማፈስ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ በቀን የመብት ጥያቄ ሲያሰማ የዋለውን ሕዝብ ከሰው እይታ ተከልሎ በምሽት ማሰር እና መግደል የኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ ይመስል የታሪካችን አካል እየሆነ ነው፡፡ ሰላማዊ ዜጎችን ከማሰር፣ ከመደብደብ፣ ከመግደል …… ለዜጎች የነጻነት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ይቅደም፡፡
አላሁ አክበር!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar