søndag 16. desember 2012

ከአእምሮ ባርነት ነጻ እንውጣ!


ከአእምሮ ባርነት ነጻ እንውጣ!

(መክብብ ማሞ)
emancipation from mental slavery
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በተደጋጋሚ የተሃድሶን አስፈላጊነት በሚያወጡት ርዕሰአንቀጽ ላይ አስነብበውናል፡፡ ባለፈው ጊዜ “ከፖለቲካ ተሃድሶ በፊት [የእውቀት] ተሃድሶ በአስቸኳይ!!” በሚል ርዕስ የተሃድሶን ጥቅምና አስፈላጊነት አስታውቀውናል፡፡ በቅርቡ ደግሞ “የተሃድሶ ያለህ!!!” በማለት በድጋሚ የሰሚ ያለህ ብለውናል፡፡ እኔም ይህንን በሙሉ ልብ የማምንበትን ሃሳብ በማንሳታቸው ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ በዚሁ ርዕስ ዙሪያ “ከአእምሮ ባርነት ነጻ እንውጣ” በሚል ሃሳቤን እንደሚከተለው አቅርቤአለሁ፡፡
ከአእምሮ ባርነት ነጻ እንውጣ
የሰውን ልጅ “ሰው” ከሚያሰኙት መካከል ማንነቱን የሚወስኑት የአካላዊ፣ የአእምሯዊና የመንፈሣዊ ኃይላት ውጤት መሆኑ በዋንኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡ እነዚህ ዕድገታቸውን በተመጣጠነ መልኩ ካልተጠበቀ የሰው ልጅ “ሰው” ተብሎ ቢጠራና ራሱንም “ሰው ነኝ” እያለ ቢኖርም ከ“ሰው”ነት ተራ የወጣ ለመሆኑ ራሱ ምስክር ነው፡፡
የእነዚህ ኃይላት ተመጣጥነው አለማደግ ሰውን ለብዙ ዓይነት ችግር ይዳርጉታል፡፡ ተምሮ ለድንቁርና፤ ባለጸጋ ሆኖ ለመንፈሣዊ ድህነት፤ ነጻ ሆኖ ለባርነት፤ … ይዳርጉታል፡፡ ከባርነትም የአእምሮ ባሪያ መሆን ትልቁ ጭቆናና ውርደት ነው፡፡
የአእምሮ ባሪያ የሆነ ነጻነቱን የሚጎናጸፍበት በርካታ መንገዶች ቢኖሩም የዕውቀት ተሃድሶ ማድረግ ቀዳሚው ነው፡፡ የዕውቀት ተሃድሶ ለማድረግ ትምህርት ቤት መግባት አያስፈልግም – እዚያ የሚሰጥ ትምህርት አይደለምና፤ የዲፕሎማና የዲግሪ ክምችት አይሻም – በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የተቀረጸ ኮርስ አይደለምና፤ … የዕውቀት ተሃድሶ ለማድረግ ከሁሉ በላይ ቅንነት እና እውነተኛነት ያስፈልጋል፡፡
ቅንነትን መመሪያው የሚያደርግ “እሺ” እያለ የሚታዘዝ ብቻ ሳይሆን “እምቢ” የማለትን ምርጫ በነጻነት የሚመርጥ ይሆናል፡፡ እምቢባይነቱን የሚያሳየው ሌሎች “ስህተት ነው! ጥላው!” ስላሉት ሳይሆን ኅሊናው ስለሚጸየፈው ነው፡፡ በሚጠላው ቡድን ብቻ ሳይሆን አምኜ እከተለዋለሁ በሚለውም ዘንድ ውሸት፣ ቅጥፈት፣ አምባገነንነት፣ … በየትኛውም መልክና ቅርጽ ሲመለከት እምቢባይነቱን ያለአንዳች ፍርሃትና ተጽዕኖ ይገልጻል፡፡ ምክንያቱም ከአእምሮ ባርነት ነጻ ነው፡፡ በሚያደርገው ምርጫ የሚከተለው ሌሎችን ሳይሆን የራሱን አእምሮ ይሆናል፡፡ የዕውቀት ተሃድሶ ያደረገና በዚያ የሚመራ የሚያስበው በቅንነት ስለሆነ የሚወስነው ውሳኔ ትክክል ከሆነ “ካለኔ ላሳር” ብሎ በትዕቢት አይወጠርም፡፡ ምርጫው ስህተት ቢሆን ደግሞ “ተሳስቻለሁ” ብሎ ከስህተቱ  ለመማር አይከብደውም፡፡ ምክንያቱም ከአእምሮ ባርነት ነጻ ወጥቷልና፡፡
በእውቀት ተሃድሶ የሚመራ መመሪያው እውነት ስለሆነ ለውሸትና ለተንኮል ቦታ የለውም፡፡ የሌሎችን ሃሳብ ቢያከብርም በሌሎች አእምሮ ግን አይመራም፡፡ የሌሎችን ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ ቢሆንም “እነርሱ ካልባረኩት የተረገመ ነው” በማለት የራሱን የአስተሳሰብ ነጻነት ለሌሎች አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ከአእምሮ ባርነት ነጻ ወጥቷልና! የዘር፣ የጎሣ፣ የጎጥ፣ የቡድን፣ … ጉዳይ ሳይሆን መጀመሪያ የግለሰብ ጉዳይ በዋነኝነት የሚያሳስበው ይሆናል፡፡ የአእምሮ ነጻነትን ያልተጎናጸፈ ሰው እታገልለታለሁ የሚለው ቡድን “ነጻ ቢወጣ” እንኳን እርሱ ግን በአእምሮ ባርነት ውስጥ ስላለ የነጻነትን ብርሃን ማየት አይችልም፡፡ የሬጌው ንጉሥ እንዳለው “ራሳችሁን ከአእምሮ ባርነት ነጻ አውጡ፤ ሌላ ማንም ሳይሆን ራሳችን ነን አእምሯችንን ነጻ ማድረግ የምንችለው”፡፡
ባለፉት በርካታ ዓስርተ ዓመታት አገራችን ከጭቆና ነጻ የምትወጣበትን ስናልም፣ ተስፋ ስናደርግ፣ “ስንታገል”፣ ውል የሌላቸውን ፍልስፍናዎችን ስንከተል፣ ሌሎች እንዲከተሉን ስንመራ፣ በሌሎች ስንመራ፣ … ቆይተናል፡፡ የናፈቅነው ለውጥ ግን ብቅ እንኳን አላለም፡፡ ያለፈው ትውልድ ለሰራው ጥፋት ግልጽ ይቅርታ ጠይቆ ለመጪው ትውልድ ብሩህ ተስፋን ከማስተላለፍ ይልቅ “በጭራሽ አልተሳሳትኩም” በሚል ብልጣብልጥነትና ድርቅና ጥፋትን በሌላው አካል ላይ እየከመረ ራሱ በጭለማ ውስጥ ሆኖ መጪው ትውልድ በጭለማ እንዲኖር ውርስ ያስተላልፍለታል፡፡ ዓይን ያወጣ ውሸት፣ ከአገር ይልቅ የራስን ስምና ዝና በ“ትግል” ስም በመሸፈን ሕዝብ ሲታለል ስንት ትውልድ አለፈ!?
ፕሮፌሰር መስፍን “የክህደት ቁልቁለት” በሚለው መጽሐፋቸው ከሚጠቅሷቸው እጅግ ድንቅ ሃሳቦች መካከል ስለ እውነትና እውቀት በሰፊው ያብራራሉ፡፡ “የአንድ ሕዝብ የክስረት ምልክቱ እውነትን ከውሸት መለየት ሲሳነውና ሰብዓዊ ባህርዩን ለእንስሳ ባህርዩ ሲያስገዛ ነው” ይሉናል፡፡ (ገጽ 14) ቅንነት ሲጠፋና ውሸት ሲነግስ ነጻነት ሩቅ ይሆናል፡፡
እየደረሰ ያለውን ጥፋት እና ከበስተጀርባ የሚሸረበውን ተንኮል እያወቅን “ወያኔ ላይ ጠጠር የሚወረውር …” በሚል አጉል ፈሊጥ ውሸትን የምናባብል ከሆነ ራሳችን ከአእምሮ ባርነት ነጻ አልወጣንምና ለሕዝብ ነጻነት ማምጣት አንችልም፡፡ ለራሣችን ዝናና ክብር እየታገልን “ሕዝብን ነጻ ለማውጣት ነው የምታገለው” ማለት ከአእምሮ ባርነት ነጻ ያለመውጣት ምልክት ስለሆነ በሕዝብ ያልተመሠረተ ድርጅት እየመሠረትን ትግሉን “ሕዝባዊ” ብንለው ሕዝባዊ ሊሆን አይችልምና ከአእምሮ ባርነት ነጻ እንውጣ! ቀደምት እናቶቻችን እና አባቶቻችን በአካል ብቻ ሳይሆን በአእምሮና በመንፈስም ነጻ ነበሩ፡፡ ያስረከቡንም እንደዚህ ያለ ነጻነትን ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት ትርጉምም ይኸው ነው፡፡
ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፍ ገጽ 15 ላይ ፕ/ር መስፍን ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ኃይለሥላሴ ዘመን ድረስ የተካሄዱትን የውጪ ወረራዎች ለየት ካለ አንጻር ያስረዳሉ፡፡ እንግሊዝ አጼ ቴዎድሮስን ሊወጋ ሲመጣ የጦር መሣሪያውን ያጓጓዘው በእንስሳት ነበር፤ የቴዎድሮስም ጦር በተመሳሳይ መልኩ በእንስሳት ነበር የተጓጓዘው፡፡ በአጼ ምኒልክም ዘመን ጣሊያን አምባላጌ ለመድረስ መጓጓዣው አጋሰስና አህያ ነበር፤ የምኒልክም ጦር ለውጊያ የደረሰው ከጣሊያን ባልተለየ መልኩ ተጓጉዞ ነበር፡፡ ከአርባ ዓመታት በኋላ ጣሊያን ኢትዮጵያን በአውሮፕላን፣ በታንክና በጦር መኪና ሲወጋ “የአጼ ኃይለሥላሴ ጦር ወደ ማይጨው የዘመተው ያው እንደተለመደው አህያ እየነዳ ነበር”፡፡ ይህ ሁሉ ካለፈ ከስድስት ዓስርተ ዓመታት በኋላ ሕዝብ ሳይጠይቃቸው “የሕዝብ ብሶት የወለደው” በማለት ራሳቸውን “ነጻ አውጪ” ብለው የሾሙት የወያኔ ልጆች “የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻ ያወጡት” አህያ እየነዱ ነበር ይላሉ፡፡ ሃሳባቸውንም በሚከተለው ዓርፍተነገር ያጠቃልላሉ  “ … በአእምሮና በመንፈስ ኃይሉ የማይጠቀም ሕዝብ አህያ ከመንዳት ሊወጣ አይችልም::”
አሁንም በእውቀት ተሃድሶ ያልተገነቡ መሪዎች ቅንነት ሳይኖራቸውና ከአእምሮ ባርነት ነጻ ሳይወጡ ነጻነትን በአጋሰስ ጭነው ሊያመጡልን “ሕዝባዊ ትግል እያካሄድን ነው” ይሉናል፡፡ ጎበዝ ልብ እንበል የተታለልነው በወያኔ ብቻ እኮ አይደለም፡፡ በነጻነት ተስፋ ስንጦዝ ሁለት ዓስርተ ዓመታትን ሲጥ አደረግን፡፡ ከዚህ በኋላ ስንት ተጨማሪ ዓመታትን ነው የምንጠብቀው? ችግሩም ሆነ መፍትሔው ያለው እኛው ዘንድ ነው፡፡ ሕዝብ እምቢ ማለት ይችላል፡፡ ምክንያቱም በእውቀት ተሃድሶ የታነጸ ሕዝብ፣ የአእምሮ ነጻነት የተጎናጸፈ ሕዝብ፣ ከአእምሮ ባርነት ነጻ የወጣ ሕዝብ “ነጻ አውጪ” አይፈልግም፡፡ በእውቀት ተሃድሶ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar