tirsdag 17. februar 2015

የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አባላት በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ


የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አባላት በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ ጥር ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም :-<<ብሄራዊ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በወሰኑብን ፖለቲካዊ ውሳኔ ምክንያት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ተነጥቀናል>> ያሉ የአንድነት ፓርቲ አባላት› በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን ሰማያዊ ፓርቲ አስታውቋል፡፡ በእነ በላይ ፍቃዱ አመራርነት አንድነት ፓርቲን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲመሩ የነበሩ አመራሮች ዛሬ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፤ ከቀድሞ ፓርቲያቸው አንድነት ጋር የፕሮግራምም ሆነ የስትራቴጂ ተመሳሳይነት ወዳለው ሰማያዊ ፓርቲ ተቀላቅለው ሰላማዊ ትግላቸውን ለመቀጠል መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ሌሎችን የ አንድነት አባላትን በመወከል  መግለጫውን የሰጡት፦ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አፈ ጉባዔ  አቶ አበበ አካሉ፣ ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ ፀጋዬ አላምረው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፋረደኝ እና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ናቸው፡፡
‹‹የምናምነው በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ ይህን ሰላማዊ ትግል ለመምራት ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ብቁ ነው ብለን በማመን ፓርቲውን ተቀላቅለናል›› ብለዋል የቀድሞዎቹ የአንድነት አመራሮች።  በዚህም መሰረት በርከት ያሉ  የአንድነት አመራሮችና አባላት በይፋ የሰማያዊ ፓርቲን የአባልነት ፎርም መሙላታቸው ተመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል የአንድነት አባላት ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን አስመልክቶ መግለጫ ለመስጠት ወደ ሰማያዊ ቢሮ ባቀኑበት ወቅት ፖሊስ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ድረስ በመግባት፦ ‹‹በሰማያዊ ስም መግለጫ የሚሰጡ አካላት እንዳሉ ሰለሰማን ነው›› በሚል ለፓርቲው አመራሮች ጥያቄዎችን ማቅረባቸውን ከሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።፡፡ ይህ  በእንዲህ እንዳለ-“በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ስልጣን ይያዛል ብሎ ማመን ህዝቡን ማታለል ነው” ሲል አንድነት ፓርቲ አስታወቀ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ  ስርዓቱ ለመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ የሚመች የአስተሳሰብ ለውጥ እስካላመጣ ድረስ ፣ በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ስልጣን ይያዛል ብሎ ማመን ህዝቡን ማታለል ነው ብሎአል።  የምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ለማፍረስ የወሰደውን እርምጃ አጥብቆ የኮነነው አንድነት፣ አሁን ባለው ሁኔታ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ተቀበረዋል የሚል ድምዳሜ ላይ  መድረሱን አስታውቋል።  አባሎቹ ይህን ህገወጥ እርምጃ በፅኑ እየተቃወሙ ለነፃነትና ለኢትዮጵያዊነት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመከፍል ዝግጁ መሆን እንደሚኖርባቸው አሳስቧል፡፡  ምርጫን በተመለከተ ፓርቲው አቋሙን ሲገልጽ፣ በአምስት ዓመት የሚደረግ ክብረ በዓል አድርጎ ለማድመቅ እና የህዝብ ሀብት ለማባከን በሚደረግ ሂደት ተሳታፊ ለመሆን አዲስ ፓርቲ መመስረትም ሆነ አሁን ካሉት ፓርቲዎች ጋር ተቀላቅሎ መታገል የሚያመጣው ለውጥ የለም ብሎአል፡፡ በመድብለ ፓርቲ ሰርዓት ስልጣን ይያዛል ብሎ ማመን ህዝቡን ማታለል ነው የሚል ፅኑ እምነት መያዙን የሚገልጸው አንድነት፣   የፓርቲ ፖለቲካ አላበቃም ብለው የሚያምኑ የአንድነት አባላት ካሉ በራሳቸው ነፃ ውሳኔ ወደ ፈለጉት ፓርቲ ተቀላቅለው የመታግል መብታቸው መጠበቁንም አስታውሷል።  ህዝቡ የትግሉ ባለቤት ሆኖ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ  የፓርቲው አባላት ሀገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ቁርጠኞች መሆናቸውንም መግለጫው ጠቅሷል። አንድነት ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ እንዲፈርስ መደረጉ ብዙ ኢትዮጵያውያንን አበሳጭቷል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar