• ‹‹ሰማያዊ ሳይጠብቁት በመላ አገሪቱ ዕጩ በማቅረቡ ደንግጠዋል›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
(ነገረ-ኢትዮጵያ) ምርጫ ቦርድ በየወረዳው ለሚገኙ የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች ‹‹ከቦርድ የሚጠበቅ ውሳኔ ስላለ፣ ሰኞ ተሰብስበን እስክንወስን ድረስ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎቹን ወደ ቅጽ 4 እንዳታዘዋውሩ›› የሚል መልዕክት ማስተላለፉን እና ሰማያዊ ፓርቲ ያቀረባቸውን ዕጩዎች ከመቀነስ ጀምሮ ፓርቲውን ከምርጫው ለማገድ ፍላጎት እንዳለው ከምርጫ አስፈጻሚዎች መረጃዎች ደርሰውናል ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ፓርቲው ከትግራይ፣ እስከ ሞያሌ ጫፍ ዕጩ ማቅረቡ ለገዥው ፓርቲ ያልተጠበቀና አስደንጋጭ ሆኖበታል ያሉት ኢ/ር ይልቃል በህጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ ላይ የሚደረጉት ጫናዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሰማያዊ ሰይጠብቁት በመላ አገሪቱ ዕጩ በማቅረቡ ደንግጠዋል፡፡ በአዲስ አበባ 23 ዕጩዎችን አቅርበናል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ዕጩ ያቀረቡ ፓርቲዎች ሳይቀር በሚዲያ ሲነገርላቸው ሰማያዊ ፓርቲ ያቀረባቸውን ዕጩዎች ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ዛሬ ጠዋት ደግሞ የምርጫ ቦርድ ባለስልጣናት በቴሊቪዥን ቀርበው ‹ሰማያዊ በተደጋጋሚ ብንነግረው አልሰማም፣ በመሆኑም ሰኞ ቦርዱ ተሰብስቦ ውሳኔ ያስተላልፋል› ብለዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ሰማያዊ በምርጫው እንዳይሳተፍ ችግር መፍጠር እንደሚፈልጉ ነው፡፡›› ሲሉ ፓርቲው ላይ እየተፈጠረበት ያለውን ጫና ገልጸዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ በዛሬው ዕለት በኢቢሲ ቀርበው ሰማያዊ ይቅርታ ባለመጠየቁና ማስጠንቀቂያዎችን ባለመቀበሉ ነገ ሰኞ ጥር 9/2007 ዓ.ም ውሳኔ ያስተላልፋል ብለዋል፡፡
ከሌሎች ፓርቲዎች ሰማያዊን በመቀላቀል በፓርቲው ምልክት ለመወዳደር የወሰኑ ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንዲሰረዙ መደረጉና በሌሎች ዕጩዎች ላይም ከፍተኛ ወከባ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ነገረ ኢትዮጵያ መዘገቧ ይታወሳል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረሲት ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ የሆነው አቶ ግርማ ቢተው በፈረሲት ወረዳ ፖሊሶች መያዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በገዥው ፓርቲ ደህንነቶችና ፖሊስ ወከባ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ተገልጾአል፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar