lørdag 3. mai 2014
የቅማንት ብሔረሰብ ቅማንት ሆኖ በመቀጠሉ ምክንያት በደምና በአጥንት የተገነባውን የጎንደር ህዝብ አንድነት አደጋ ላይ አይጥለውም!
በሰ/አሜሪካ ከሚገኙ ውስን የቅማንት ብሔረሰብ ተወላጆች “ይድረስ ለጎንደር ህዝብ” በሚል ርዕስ ለተፃፈ ደብዳቤ የተሰጠ መልስ
ከጓሌ አለሙ
ጎንደር
gualealemu@gmail.com
እንደ መነሻ
ለዚህ ጹህፍ መነሻ ያደረኩት ኢትዮሚዲያ ድህረ- ገጽ ላይ “ይድረስ ለጎንደር ህዝብ” በሚል ርዕስ በሰ/አሜሪካ ከሚገኙ የቅማንት
ተወላጆች እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 17/2014 ዓ.ም. በድህረ-ገጹ ላይ የተጫነ (upload) ጹህፍ ነው፡፡
ጹሁፉን ማንበብ እንደጀመርኩ ዓላማው ትንሽ ግራ የሚያጋባ ስሜት ፈጠረብኝ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ የጹህፉ ጭብጥ በጎንደር አካባቢ
ስለሚኖሩ የህዝቦች ስብጥርና (አማራ፣ አገው፣ ቅማንት፣ ነገደ-ወይጦ ትግሬና ሌሎች) ሁሉም የየራሳቸው ቋንቋ፣ታሪክ፣ ባህልና ወግ
ያላቸው መሆኑን ያብራራና ‹‹ተዋህደዋል›› በማለት እነዚህን ህዝቦች ለመለያየት መሞከር ‹‹ የተደባለቀ ውኃና ወተትን የመለያየት ያክል
ይከብዳል›› ይላል፡፡ የቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ የተቃጣባትን ዘርን የማጥፋት ዘመቻ ለመከላከል የተጠየቀ መሆኑን ስረዳ ደግሞ
‹የምን ህዝብ ማለያየት?› በሚል ሀሳብ የበለጠ ግራ ተጋባሁ፡፡
ጉዳዩን በትክክል ለመረዳት ደጋግሜ አነበብኩትና የተረዳሁትን ያክል ከተረዳሁ በኋላ ለጹህፉ መልስ ሊሆን ይችላል ያልኩትን ሀሳብ
አሰባስቤ መጻፍ ሞክርኩ፡፡
በመጀመሪያ እነዚህ በሰ/አሜሪካ የሚገኙ የቅማንት ብሔረሰብ ተወላጆች ‹የህዝባችን ጉዳይ ጉዳያችን ነው ፤ የአገራችን ሰላም ለእኛም
ሰላም ነው› በሚል ስሜት ተነሳስተው እነሱ በተረዱት አግባብ፣ መጠንና በአገኙት መረጃ ልክ በቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ዙሪያ
አመለካከታቸውን በመሰንዘራቸው ለሰጡት አስተያየት ሙሉ አክብሮት አለኝ፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን በተናጠልም ሆነ
በጋራ ስለአንድ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሀይማኖታዊ ወይም ሌላ ጉዳይ የሚይዘው አሰተሳሰብና አቋም ግላዊ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ
‹ለምን እንዲህ ተባለ?› የሚል አቋም በፍጹም አይኖረኝም፡፡ ምን አልባት ይህን ጹህፍ ከጻፈው (ወይም ከጻፉት ) ሰው ጋር
የምንለያየው የተሰነዘረው ሀሳብ የተዛባ መረጃን መሰረት አድርጎ ወይም ደግሞ ከመረጃ እጥረተ አኳያ የተሰጠ ከሆነ ‹‹ አይ ጉዳዩ
እንደዚያ ሳይሆን እንዲህ ነው›› የማለት መብት ብቻ ነው የሚኖረኝ፡፡ ከዚያ ባለፈ የጹህፉ ባለቤት ከፈለገ (ከፈለጉ) የግል አቋሙን
(አቋማቸውን) የሌሎችን መብትና ፍላጎት በማይነካ መንገድ እስከምጻት ድረስ ሊያርምዱ ይችላሉ፡፡ እኔም ሀሳቤን በነጻ የመግለፅ
ተመሳሳይ መብት አለኝ ብየ አምናለሁ፡፡
ይህን ካልኩ በኋላ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ወደ ዝርዝር ሀተታየ እገባለሁ፡፡
የቅማንት ህዝብ ትናንት በዚህ ሥርዓት አማካኝነት እንደ እንጉዳይ ከመሬት የበቀለ ወይስ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ?
እውን በሰ/አሜሪካ የሚኖሩ የተወሰኑ የቅማንት ብሔረሰብ ለማለት እንደሞከሩት የቅማንት የማንነት ጥያቄ ለዘመናት ተዋህዶ የኖረውን
የጎንደር ክ/ሀገር ህዝብ ለመለያየት የተጠነሰሰ ድብቅ ሴራ ወይስ ደግሞ ከማንኛውም ጊዜ በባሰ መልክ በቅማንት ህዝብ ላይ በከፋ
መልኩ የተጋረጠውን የመጥፋት አደጋ ለመከላከል የተጀመረ እንቅስቃሴ?
የቅማንት ህዝብ ቅማንት ተብሎ መጠራትና መቀጠል ለሌላው አጎራባች ህዝብ አደጋው ምን ላይ ነው?
የአንድን ህዝብ ማንነት (identity) በሀይል በመድፈቅ እውነተኛ የአገርንና የህዝቦችን አንድነት ማረጋገጥ ይቻል ይሆን? በዚህ አይነት
አንዱ በሌላኛው ማንነት ተውጦ አብሮ የሚኖር ህዝብ ዘላቂ የህዝብ ለህዝብ አንድነት ያመጣል?
የቅማንት ጥያቄ ብቻውን ለምን አገርን የመገነጣጠል ድርጊት ተደርጎ ተቆጠረ?
የቅማንት ህዝብ በሌሎች ክልሎች የሚኖር ቢሆን ኑሮ ማንነቱ እንዳሁኑ አደጋ ላይ ይወድቃል ወይስ እንደሌሎች ኢትዮጵያዊያን ህገ-
መንግሥታዊ መብቱ ይከበርለት ነበር?
ያለፈው ታሪካችን
ሁላችን እንደምናውቀው ኢትዮጵያ ፈልገንም ሆነ ሳንፈልግ ከ80 በላይ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሀይማኖትና ወግ ያላቸው ህዝቦች በጋራ
ተከባብረው የሚኖሩባት አገር ናት፡፡ አነዚህ ህዝቦች በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር መልካሙንና ክፉውን ነገር አብረው አሳልፈዋል፡፡ ምን
አልባት በዘመኑ በነበሩ የገዥ መደቦች የሥልጣን ዘማናቸውን ለማራዘም ሲሉ አንዱ ህዝብ በሌላኛው ላይ በጥላቻና በግፍ እንዲዘምት 2
በማድረግ እርስ በእርስ በማናቆር በህዝብ መካከል የበቀልና የቂም ዘር ሲዘሩ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡ በመሆኑም ባለፉት ምዕተ ዓመታት
ሀገራችን ከፍተኛ የብሔር ጭቆናና የበደል ማዕከል ከመሆኗ በተጨማሪ በአክሱማዊያን እና በእነላሊበላ ዘመነ-መንግሥት ከደረሰችበት
ዕድገትና በዓለም ዘንድ ከነበራት መልካም ክብር ቁልቁል ወደታች በመወርወር የመጨረሻዋ መናጢ ደሀ ለመሆን በቃች፡፡ በተለይም
ባለፉት ሥርዓቶች የነበራት ታሪኳ ለተወሰኑ ገዥ መደቦች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሀይማኖትና የአስተዳደር የበላይነትን ያጎናፀፈና
የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ታሪክና ብዝሀነት ያልተቀበለና በሀይል የደፈጠጠ ነበር፡፡ በዚህ ድርጊታቸው በህዝቦች መካከል ጎሳንና
ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ ‹‹የከፋፍለህ ግዛው›› ዘይቢያቸው የተወሰነው የኅብረተሰብ ክፍል አንደኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊ ሌላኛው
ደግሞ የሁለተኛ ዜግነት ስሜት እንዲሰማው በማድረግ የአገዛዝ ዘመናቸውን ለማራዘም ተጠቅመውበታል፡፡
የቅማንት ህዝብም በእነዚህ ሥርዓቶች ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የሥነ-ልቦና ጫናን ከምንጩ እንዲጎነጭ
ተደርጓል፡፡ በሰሜን አሜሪካ ሁናችሁ ይህን ደብዳቤ የጻፋችሁትም ሆነ በሌሎቻችን ላይ በማንነታችን (በቅማንትነታችን) ምክንያት
የተቀበልነው የሥነ-ልቦና ጠባሳና መከራ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ያን ያለፈ ክፉ ዘመን ሰንኮፍ እያመነዠክን በወደፊት የአገራችንና
የህዝባችን አንድነት ላይ አሉታዊ ውጤት ሊያስከትል በሚችል እንቅስቃሴ በመሰማራት ህዝብን ከህዝብ የሚነጣጥል ተግባር
መሰማራት ለማንኛችንም አይጠቅምም፡፡ ፈረንጆች ሁለት ስህተቶች አንድ ትክክለኛ ነገር አይወጣቸውም (Two wrongs do not
make one right) እንደሚሉት ያለፈ ጊዜን በደል እያነሱ የዛሬ አብሮነታችን ላይ ማጨለም ተገቢ እንደማይሆን ጤናማ አዕምሮ ያለው
ሰው ሁሉ የሚረዳው ሀቅ ነው፡፡ የኔልሰን ማንዴላ አይነት የይቀር ባይነት ልብ በሁላችንም ዘንድ ሊኖረን ይገባል፡፡
የቅማንት ህዝብ ነባራዊ ሁኔታዎች
ወደተነሳሁበት ዋና ነገር ስመለስ የቅማንት ህዝብ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ ለመሆኑና መደበኛ ጎንደሬ ለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት
ይመሰክራሉ፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች ይህ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደ አንድ ራሱን የቻለ ነገድ የሚታወቅና የራሱ ቋንቋ፣
ታሪክ፣ ባህልና ወግ ያለው በሰሜንና በመካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍል ለዘመናት የኖረ ህዝብ መሆኑ በግልፅ ይታወቃል፡፡ በአጼው እና
በደርግ ሥርዓት ጭምር የሚታወቀውም በቅማንት ማንነቱ ነው፡፡ አጎራባች ህዝቦችም ቢሆኑ ይህን ህዝብ በግልፅ የሚያዉቁት
በቅማንት ማንነቱ ነው፡፡ በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ የብሔረሰብ ኢንስቲትዩት ባካሄደው ጥናት ቅማንት አንደ አንደ ብሔረሰብ ተካቶ
በህዝብ ብዛት ደረጃም በኢትዮጵያ በ10ኛ ደረጃ ይገኝ ነበር፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1976 ዓ.ም በተደረገው የህዝብና ቤቶች
ቆጠራ ‹ቅማንት ነኝ› ብሎ የተመዘገበው ህዝብ ብዛት (ማንነታቸውን የካዱትን ሳይጨምር) 169,168 ሲሆን ከዚህ ውስጥ 166,973
የሚሆኑት ቅማንተኛ ቋንቋን አጣርተው ይናገሩ ነበር፡፡ በተመሳሳይ በ1987 ዓ.ም (በዘመነ ኢህአዴግ) በተደረገው የህዝብና ቤቶች
ቆጠራ የቅማንት ህዝብ ብዛት 172,291 ነበር፡፡ በ1976 ዓ.ም የነበረውን 3.1% የህዝብ እድገት መጠን ወስደን በ10 አመታት ውስጥ
(አስከ1987 ዓ.ም ማለት ነው) የህዝቡ ብዛት ስንት ሊሆን እንደሚችል ማስላት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጅ በነበረው የሥነ-ልቦና ጫና
ምክንያት ከቅማንትነት ማንነቱ የሚሸሸዉ ህዝብ በመጨመሩ በአሥር ዓመታት ውስጥ የህዝቡ ብዛት የጨመረው በ3,123 ብቻ ነበር፡፡
የቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ መንሻ ምክንያቶችና ዓላማው
በ1999 ዓ.ም. በተካሄደው አገር አቀፍ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ቅማንት የሚባል ብሔረሰብ በቆጠራው ተሰርዞ አንድም በ‹አማራ› ሥም
እንዲቆጠር ይህን ማለት ካልፈለገ ደግሞ ‹ሌሎች› በሚለው ሥር እንዲቆጠር መመሪያ ተላለፈ፤ የሕዝብ ቆጠራ አዋጅም ወጣ፡፡
ልብ በሉ በአሥር ዓመታት ውስጥ የቅማንትን ህዝብ ከምድረ-ገፅ የሚያጠፋ ምን አይነት ሱናሜ ተፈጠሮ ነው ቅማንት የሚባል ህዝብ
ከኢትዮጵ ብሔረሰብ ዝርዝር እንዲወጣ የተፈረደበት? ስለዚህ በዋናነት የቅማንት ህዝብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ መነሻ
የቅማንት ህዝብ ከኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ዝርዝር ውስጥ በመሰረዙ ምክንያት ራስን የማዳን ትግል ነው፡፡
የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ የሽግግር መንግሥት በ1984 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 07/1984 በኢትዮጵያ ይገኛሉ ብሎ ከዘረዘራቸው 64 የተለያዩ
ብሔረሰቦችና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚገኙ ብሔረሰቦች ብሎ ከዘረዘራቸው 4 ብሔሮች (አማራን ጨምሮ) ዉስጥ
የቅማንት ህዝብ አልተካተተም፡፡ ይህም ሆኖ አስከ1999 ዓ.ም ድረስ ማለትም የቅማንት ህዝብ ከኢትዮጵያ የብሔረሰቦች መዝገብ
አስከተዘረበት ድረስ የቅማንት ህዝብ የራስ አስተዳደር ጉዳይ አይደለም የምንም አይነት ጥያቄ ሳያነሳ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ቀጥሏል፡
፡ ይህን ስል ህዝቦች ውስጣዊ የሆነ ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው ወንጀል ነው እያልኩ እንዳልሆነ ግንዛቤ ይያዝልኝ፡፡ በአሁኑ
የኢኮኖሚ እድገት አስተሳሰብ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ ይበልጥ አካባቢያዊ ልማትን ሊያፋጥኑ አንደሚችሉ የልማት
ባለሙያዎች አስረግጠው ይናገራሉ፡፡
ይህ የ1999 ዓ.ም ቅማንት የሚባል ህዝብ በኢትዮጵያ ሊቀጥል እንደማይችል በቆጠራው ከተረጋገጠ በኋላ የቅማንት ህዝብ የማንነትና
የራስ አስተዳደር ጥያቄ ህገ-መንግሥቱ በሚፈቀደው አግባብ ሁሉንም ባካተተ መልኩ እንዲጠየቅ ምክንያት ሆነ፡፡ የዚህ ጥያቄ መነሻም
በአዋጅ የተሰረዘውን ማንነት ማሰመለስ እንጅ ህዝብን ከህዝብ የመነጠል ምንም አይነት አጀንዳ አልነበረውም፤ የለውምም፡፡ ነገር ግን
ይህን ጥያቄ ማውገርገር የሚፈልጉ ጥቂት የመንግሥት አመራሮችና ድሮውንም ቢሆን ይህን ህዝብ በንቀትና የበታች እንደሆነ አድርገው
ሲመለከቱት ከነበሩና አሁንም ድረስ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከሚኖሩ አንዳንድ ግለሰቦች የተዛባ እይታ በመነጨ ምክንያት
የዚህን ህዝብ የማንነት ጥያቄ ከእውነተኛው ዓላማ ዉጭ ያልተፈለገ ስም እንዲለጠፍበት የተለያየ ሙከራ አድርገዋል አሁንም
በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምን አልባት እናንተ አሜሪካ ያላችሁ ወንድሞችና እህቶች አሜሪካ ሆናችሁ ራሳችሁን ቅማንት ብላችሁ
ልትጠሩ ትችሉ ይሆናል፤ያዉም በድፍረት የምትሉ ካላችሁ ማለቴ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ቅማንትነት በሄዳችሁበት አገር ተከትሎ
ለሁላችሁም የስድብ ስም (derogatory) እንደሚሆንባችሁ አልጠራጠርም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ምድር በተለይ ደግሞ ወደ አማራ ክልል
ስትመጡ ደግሞ ‹‹እኔ ቅማንት ነኝ›› ማለት ለጀምላ አስር ይዳርጋል፡፡ ቅማንት ማለት በአማራ ክልል መሪዎችና በአንዳንድ ጊዜው
ያለፈባቸው ፊውዳላዊ አስተሳሰብ በተጣባቸው ግለሰቦች ዘንድ ያልተፈቀደና ወንጀል ነው፡፡ ማደናገሪያቸው ደግሞ ሲፈልጉ አማራነትን 3
ከሀይማኖት ጋር በማያያ ‹‹ተጠምቃችሁ አማራ ሆናችኋል››፣ ሲፈልጉ ደግሞ የጋብቻንና የአበልጅነት ማህበራዊ ትስስርን የማንነት
መደመሰሻ መንገድ አድርጎ በማቅረብ ‹‹ከአማራ ጋር በማጋባታችሁ አማራ ሆናችኋል›› ሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹የአብዛኛው ቅማንት ህዝብ
ቋንቋ አማርኛ በመሆኑ ቅማንትነታችሁ አክትማሟል›› የሚሉትና ሌሎችን ጭምር በማፈራረቅ ይጠቀማሉ፡፡ በ2004 ዓ.ም በተደረገ
የማዕከላዊ ስታቲሰቲክስ የናሙና መረጃ በሚሰበሰብበት ወቅት ‹‹እኔ ቅማንት እንጅ አማራ አይደለሁም›› ያሉ የቅማንት ልጆች ለእስር
ተዳርገዋል፣ ተደብድበዋል፣ከሥራ ተባረዋል አለያም ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል፡፡ ይህን ያስፈፀሙ ጉጅለ አባላት ደግሞ
በሹመት ላይ ሹመት ተበርክቶላቸዋል፡፡
አገዛዙ ለከተሜው የቅማንት ልጆች ሁለት መሰረታዊ አማራጮች አስቀምጧላቸዋል፡፡ አንደኛው ቅማንትነትን ሙሉ በሙሉ
በማዉለቅና በመርሳት የሌላ ማንነት በመከናነብ የሚጣልለትን ጥራጥሬ እየተሻማ እንደዶሮ እየለቀመ መኖር ወይም ደግሞ ቅማንትነቱን
መርጦ ከመንግሥት የሥልጣን ዘካ (ፍርፋሪ) ራስን ማግለል ናቸው፡፡ ይህን ማወቅ ከፈለጋችሁ በዚህ ምክንያት ከስራ የተባረሩ፣ከደረጃ
ዝቅ የተደረጉና የተሻሩ ግለሰቦችን ሥም ዝርዝር (እነሱ ከፈቀዱ ማለቴ ነው) ልልክላችሁ እችላለሁ፡፡ የገጠሩ ነዋሪ ደግሞ ወደሌላ ቦታ
ተንቀሳቅሶ ሰርቶ እንዳይኖር ‹‹ሞፈር ዘመት›› የሚል ታርጋ ተለጥፎበት ከቀየው እንዳይወጣ በወረዳ ካድሬዎችና የፀጥታ ኃይሎች ወርች
ከእግር ታስሮ በድህነት እንዲማቅቅ ተፈርዶበታል፡፡ የገዠዎች ወገኖችና ቤተሰቦች ግን በሰፈራ፣ በኢነቨሰተትመንትና መሰል መንገዶች
ለም ወደሆኑ መሬቶች በመውሰድ ሀብት እነዲያፈሩ እድሉ ወለል ብሎ ተከፍቶላቸዋል፡፡ በቅማንት ህዝብ ላይ ይህን መሰል የለየለት
ዘረኝነት እየተካሄደበት ባለበት ሰዓት ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ የቅማንትን ህዝብ በዘረኝነትና በከፋፋይነት በመፈረጅ
ለማሳጣት ሲሞክሩ ትንሽ የሀፍረት ስሜት አይሰማቸውም፡፡ በቅማንት ላይ ይህ አይነት መከራ ሲደረስበት የትኛው የኅበረተሰብ ክፍል
ነው ይህን ድርጊት በመቃወም ከቅማንት ህዝብ ጎን የቆመው? ይባስ ብሎ የሆነ መረጃ ጨምሮና ቀጣጥሎ ለገዥዎች በማቀበል
የቅማንት ልጆች እንዲታሰሩ፣ ከስራ እንዲባረሩ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ከየካቲት 2006 ዓ.ም አስከአሁኑ ድረስ የሰሜን ጎንደር
የቅማንት ህዝብ ‹‹ጓንታናሞ›› በሆኑ እስር ቤቶች ከ300 በላይ የሚሆኑ የቅማንት ተወላጆች ወደስር ቤት የተጋዙት የሰው ልጅ ቋንጃ
ቆርጠው (የሰው ነብስ አጥፍተው) ወይም አገር በመክዳት ወንጀል ተከሰው ሳይሆን ራሳቸውን ቅማንት ብለው በመጥራታቸው ብቻ
‹ተደፋፈረን በሚል› የትምህክት አስተሳሰብ ምክንያት ብቻ የተፀፈመ ሰቆቃ ነው፡፡ እናንተ በውጭ አገር የምትኖሩ የቅማንት ልጆች
በገንዘብና በታክስ መልክ የምትከፍሉለት በአሜሪካ የሚገኙ ሚዲያዎች ጭምር በዚህ ህዝብ ላይ አየተፈፀመ ያለውን በደል ለዓለም
ማህበረሰብ ማሳወቅ እንኳ ተፀይፈዋል፡፡ ሆት ዶግና ሀምበርገር እየገሸለጡ ከብራዚልና ከኢትዮጵያ ተልኮ በስታርባክስ ተቀሽሮና ጣፍጦ
የቀረበ ቡናን እያጣጣሙ ስለአብሮነት መስበክና በህዝቡ ውስጥ ሆኖ በህዝብ ላይ የሚደረስን መከራና ሰቆቃ አይቶ እውነቱን መፍረድ
የሰማይና የምድር ያክል ይራራቃሉ፡፡ በተባራሪ ወሬና በስማ በለው የሚነፍሱ ተራ ወሬዎችን አጠረቃቅሞ እውነት አስመስሎ በማቅረብ
የተበደለን ህዝብ በደለኛ ማድረግ ለቅማነት ህዝብ ይጎዳው ካልሆነ በስተቀር ምንም አይበጀውም፡፡ ምን አልባት በተረት እንደሚነገረው
እግሩን ለጅብ እያስበላ ‹‹ዝም በል የእኔ እግር ነው በጅብ የሚበላው›› እንዳለው አይነት የፈሪው ሰውየ አይነት ምክር ከሆነ ለቅማንት
ህዝብ ጊዜው አልፎበታል፡፡ ይልቅ የወገናዊነት ስሜት ከተሰማችሁ የዚህን ህዝብ ግፍና የሰባዊ መብት ረገጣ በያላችሁበት አገር ሆናችሁ
ለሰባዊ መብት ድርጅቶችና ለዓለም መንግሥታት በታሰሙለት ከሚደረስበት ግፉ በመጠኑም ቢሆን እፎይ ባለ ነበር፡፡ እፎይ ባይልም
እንኳ የግፉን መጠን የዓለም ማህበረሰብ በቅጡ ይረዳለት ነበር፡፡
የተከበራችሁ በአሜሪካ የምትኖሩ የቅማንት ማህበረሰብ
አማራው ራሱን አማራ ካለ ኦሮሞው ኦሮሞ፣ ወላይታው ወላይታ ማለት ከቻለ የቅማንት ህዝብ ራሱን ቅማንት ብሎ መጥራት አገር
የመከፋፈልና ተዋህዶ የኖረውን ህዝብ ማለያየት የሚሆነው በምን አይነት ስሌት ነው? እራሱን አማራ ብሎ በመጥራቱ የሚኮራና የራሱ
የአስተዳደር ክልል ይዞ ያለ ህዝብ የቅማንት ህዝብ ቅማንት መባልና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ማንሳት በአገር መከፋፈልና በጎጠኝነት
የሚያስከሰስበት መነሻ ምክንያት ምንድነው? የጎንደር አንድነት ተጠብቆ እንዲኖር ቅማንት ማንነቱን የግድ ማጣት አለበት? የቅማንት
ማንነት ተጠብቆ የጎንደርን ህዝብ አንድነት ማስቀጠል አይቻል ይሆን? የጎንደር አንድነት የሚጠበቀው ቅማንትን ወደ አማራነት
በመቀየር ነው ወይስ ጎን ለጎን ቅማንትም ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር አንዱ የአንዱን መብት አክብሮና ተቀብሎ መኖር ሲጀምር? ህዝቦች
ህብረት የሚፈጥሩት ማንነታቸውን ለመሰረዝ ሳይሆን በማንነታቸው ኮርተው በህብረት ለመኖር ስለሆነ የአንዱ ማንነት ተከብሮ
የሌላው ማንነት ሊናቅ ወይም ሊንኳሰስ አይገባውም፡፡ የሁሉም ብሔራዊ ማንነት እኩል ሊከበር ይገባል፡፡ በአጭሩ አንድ ሰው
በኦሮሞነቱ፣ በቅማንትነቱ፣ በትገሬነቱ በሲዳማነቱ ወዘተ ማመኑና በዚህም መኩራቱ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያደናቅፍ ወይም የሚያቀጭጭ
ሳይሆን ለዘላቂና ሀቀኛ ኢትዮጵያዊነቱ መሰረት ነው፡፡ህዝቦች የየራሳቸው ማንነት ከተጠበቀላቸው የአንድን ገዥ መደብ ለመቀበል
ፈቃደኝነት አይኖራቸውም፡፡ ሌሎቹን እየረገጠ ራሱን በበላይነት ለማስቀጠል የሚፈልግ የአገዛዝ አስተሳሰብ ያለው የህብረተሰብ ክፍል
ካለ የተለያዩ ብሔረሰቦች በስማቸው መጠራት ኢትዮጵያዊነትን እንደሚፃረር አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡ የብሔሮችና የብሔረሰቦች ማንነት
ለመፋቅ ሲሞክር በተለምዶ የበላይነቱን የያዘው ገዥ መደብ የመጣበት ብሔር ማንነት የማይፋቅ መስሎ ይሰማዋል፡፡ በቅማንት
ህዝብም ላይ እየተደረገ ያለው ይህ ሀቅ ነው
የቅማንት ህዝብ በታሪኩ ስለጎጠኝነትና ሰለመንደራዊ አሰተዳደር መስበክ ይቅርና በከመንትነይ ቋንቋው ውስጥ የሰውን ዘር የሚያንቋሽሽ
ቃላት የለውም፡፡ የቅማንት ህዝብ ከማንም በላይ የኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ያሉ ህዝቦች አንድነት ለኢትዮጵያ ሊያሰገኝ የሚችለውን
ፋይዳ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ለዚህም ዓላማም ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመሆን አጥንቱን ከስክሶ ደሙን አፍሶ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር
አስከብሮ ኑሯል፤ ለወደፊትም ይኖራል፡፡ ይሁን እንጅ በዚህ ህዝብ ላይ ዛሬ የተቃጣበት ዘመቻ በአንድነት ስም ቅማንት የሚባልን
ህዝብ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ነው፡፡ ይህም በሰብዓዊ መብት ቋንቋ ያልተሰማ ዘር ማጥፋት (silent genocide) ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
ለዚህም የአማራ ክልል መንግሥት በተደጋጋሚ አጠናሁት ባለው ጥናት ‹‹ቅማንት የሚባል ህዝብ የለም ቋንቋውም ሙሉ በሙሉ
ሞቷል፤ አማርኛ በመናገሩ ምክንያት ወደ አማራነት ተቀይሯል›› እንጅ ያለው ኢትዮጵያዊ ሆኗል አይደለም፡፡
4
ማጠቃለያ
በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ህዝቦች ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ተጠፍጥፈው የተሰሩ ሳይሆኑ ድሮም የነበሩ አሁንም ያሉ
ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው፡፡ የቅማንት ህዝብ ጥያቄ በአደጋ ላይ ያለውን የቅማንት ህዝብ ማንነት ለማስቀጠል እንጅ የመንደር አጥር
ሰርቶ ‹‹አትድረሰብኝ አልደርብህም›› ለመባባል እንዳለሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡ ይህን ላድርግ ቢልም አይችልም፡፡ ምክንያቱም
እንደማንኛውም ሰው የቅማንት ብሔረሰብ በሁሉም በአገሪቱ ክልሎች ተዘዋውሮ የመስራት መብት እንዳለው ሁሉ ሌሎችም ቅማንት
በሚኖርበት አካባቢ መጥቶ የመኖርና የመስራት መብት ሙሉ መብት አለው፡፡
በአሜረካ የምትገኙ ወንድሞቻችን ምን አልባት በቅማንት ህዝብ ጥያቄ በቂ መረጃ ከሌላችሁ ወደ አገር ቤት መምጣት የምትችሉ ከሆነ
መጥታችሁ መረዳት፤ መምጣት ካልቻላችሁ ደግሞ አገር ቤት ያለው ሰው በራሱ ወጭ ወደ እናንተ መጥቶ እውነታውን ብትረዱ ምን
አልባት እንዳላችሁት ህዝቡ ተሳስቶ ከሆነ ታርሞ እናንተ የተሳሳተ ግንዛቤ ይዛችሁ ከሆነ ደግሞ ሀሳባችሁን በማስተካከል ለዚህ ህዝብ
በሚበጁ ነገሮች ላይ በጋራ መስራት የምንጀምርበት እድል ይኖረናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በተባራሪ ወሬና የዚህን
ህዝብ ማንነት እንዲቀጥል ከማይፈልጉ ወገኖች ጋር በማበር የዚህ ህዝብ ጎንደርን የመገነጣጠል ዓላማ ያልሆነውን በማራገብ በህዝቡ
ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዝ ማድረግ ከወገን የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ብታምኑም ባታምኑም በአጼ ተዎድሮስ ሁለተኛው ዘመን
እንዲከስም የተደረገው የዘመነ-መሳፍንት (Time of princes) አገዛዝ ሥርዓት በዚህ ህዝብ ላይ እየተፈፀመበት መሆኑን ልብ ብላችሁ
ይህን ህዝብ ከጥፋት በጋራ ልንታደገው ይገባል ፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት ግን በቅማንትና በሰፊው የአማራ ህዝብ ዘንድ ጥላቻ እንዲፈጠር የተወሰኑ አመራሮችና ጦር ጠማኝ ግለሰቦች
ለማነሳሳት ቢሞክሩም አንድም አይነት የጠላትነት ስሜት የሌለ መሆኑና በደምና በአጥንት የተገነባው የጎንደር ህዝብ አንድነት
መቸውንም ቢሆን ሊናጋ እንደማይችል ልትገነዘቡት ይገባል፡፡
ቸር ይግጠመን
ኢትዮሚድይ - Ethiomedia.com
April 27, 2014
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar