ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ሶሻል ፓርቲና የደቡብ ህብረት ፓርቲ መሪ ናቸው። በግል የመድረክ መስራች ሲሆኑ፣ የሚመሩት ድርጅትም በመድረክ ጥላ ስር ከተሰባሰቡት ፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ይገኝበታል። ፕ/ር በየነን ጨምሮ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኢህአዴግን በመቃወም የሚታወቁ ፖለቲከኞች ተተኪ ፖለቲከኞች አላዘጋጁም በሚል ይወቀሳሉ። በዚህ ጉዳይ ስማቸው ከሚነሱት መካከል አንዱ ፕ/ር በየነ ናቸው። ፕ/ር በየነ አሜሪካ ለሥራ መምጣታቸውን ተከትሎ የ
ጎልጉል ዘጋቢ ቃለ ምልልስ አድርጎላቸዋል። ፕ/ር በየነ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት በተደጋጋሚ “እኔ የምናገረው ሰክነው ማዳመጥ ለሚችሉት ነው” በማለት ያሳስባሉ። ለምን?
ጎልጉል፡- ስለ መንግሥትና ተቃዋሚዎች እርቅ ጉዳይ ወሬ ይወራል የሰሙት ነገር አለ?
ፕ/ር በየነ፡- የለም። ምንም አልሰማሁም።
ጎልጉል፡- እርስዎ የሚመሩት ፓርቲ ጥያቄው አልቀረበለትም?
ፕ/ር በየነ፡- በፍጹም። በሚታወቅ ደረጃ ያነጋገረን አካል የለም። ማለቴ በድርጅት ወይም በአገር ደረጃ።
ጎልጉል፡- በግለሰብ ደረጃስ? ፖለቲካ የውትወታ (ሎቢ) ሥራ ነው ስለሚባል፤
ፕ/ር በየነ፡- በርግጥ በዚህ ደረጃ እንቅስቃሴ አለ። እኔ ሁሌም በሎቢ አምናለሁ። በ1997 ምርጫ ወቅት ያ ሁሉ እድል የተከፈተው በሎቢ ነው። በድካም ነው። እኔ ውስጡ ስለነበርኩ ሁሉንም አውቀዋለሁ። አስተውሎ መራመድና በሰከነ መንፈስ ከተሰራበት በሎቢ ብዙ ነገሮችን ማሳካት ይቻላል።
ፕ/ር በየነ፡- ቢሞላስ? ከእውነታዎች እንደምንረዳው በተለያዩ አገሮች 40ና 50 ዓመታት የፈጁ የትግል ተሞክሮዎች አሉ። ሎቢ በራሱ ብቻውን ትግል አይደለም። በሎቢ ብቻ ውጤት አይጠበቅም። ለሎቢ የሚያበቃና ሎቢ የምታደርጋቸውን ክፍሎች የምትማርክበት አግባብ ያስፈልጋል።
ፕ/ር በየነ፡- በየጠርዙ፣ በየጥጉ እየተፈለፈሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ እናውቅልሃለን፣ መፍትሄህ ነን የሚሉ ድርጅቶች አሉ። ድርጅቶች መሪያቸውንና መስራቾቻቸውን ይመስላሉ። ሎቢ ስታደርግ ወይ በድርጅት አለያም በመሪነት ነው። ሎቢ ከፍተኛ ስብዕናና ደረጃን ይጠይቃል። በዚህ ደረጃ ስንለካ ፈተናውን ማለፍ አለብን።
ጎልጉል፡- ለሎቢ ፖለቲካ እንኳ የማይመጥን ተቃዋሚዎች አሉ እያሉ ነው?
ፕ/ር በየነ፡- ሁሉንም ማለቴ አይደለም። እኔ የምናገረው አጠቃላይ ጉዳይ ነው።
ጎልጉል፡- በሎቢ የሚፈጠር አንድም ነገር የለም። አሜሪካኖቹ ኢህአዴግን ስለሚደግፉ ሎቢ ጉንጭ አልፋ ነው፣ ጊዜም ይገድላል የሚሉ አሉ፤
ፕ/ር በየነ፦ ተመሳሳይ እምነት ሊኖር አይችልም። ሁሉም በሚያዋጣው መንገድ መሔድ ይችላል። እኔ ግን በሎቢ አምናለሁ። ማንንም አላኮርፍም። በማንም ላይ ቂም ይዤ አላፈገፍግም። ተስፋ ሳልቆርጥ ድሮም እንደማደርገው እገፋበታለሁ። አሜሪካኖች ኢህአዴግን ወደዋል፣ ፈልገዋል በማለት ዳር ሆኖ በመሳደብና በማንጓጠጥ ትርፍ አይገኝም። አንድ እውነት አለ። አሜሪካኖቹ ኢህአዴግን ይረዳሉ። ይደግፋሉ። ይህንን አደረጉ ማለት ግን ኢህአዴግን ወደዱ ማለት አይደለም። በተለይ በኢህአዴግ ፖለቲካ ተሰላችተዋል። ፍርሃቻም አላቸው። የዘር ፖለቲካ መጨረሻው ወዴት እንደሚያመራ ደቡብ ሱዳን እያሳየቻቸው ነው። ኢትዮጵያን ከራሳቸው መሰረታዊ አቋም አንጻር መክሰርም አይፈልጉም። ችግሩ ያለው ከኢህአዴግ እሻላለሁ ሲባል በሚጨበጥና በሚታይ ማሳመኛ መሆን አለበት። ሎቢ የምታደርጋቸው ክፍሎች ሚዛናቸው ላይ ሲያስቀምጡ ሞልቶ መገኘት ያስፈልጋል። አማራጭ ነኝ ሲባል የሚዛኑን ክብደት ማንሳትን ይጠይቃል።የውጪ ኃይሎችን ድጋፍና ተቀባይነት ማግኘት ትልቅ ድል ነው። ብዙ ጉዳዮች አሉ።
ፕ/ር በየነ፡- አዎ ትንሽ ቆይቻለሁ።
ጎልጉል፡- የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ወደ አሜሪካ ሲመጡ ሚዲያዎች ላይ ይቀርባሉ። እርስዎ ግን ድምጽዎ አልተሰማም። ለምን?
ፕ/ር በየነ፡- መፈላለግን ይጠይቃል።
ፕ/ር በየነ፡- ነገር ከሚገባቸውና ብቃቱ ካላቸው ዜጎች ጋር ነው የምውልው የሚል እምነት አለኝ።
ፕ/ር በየነ፡- አስቀድሜ የገለጽኩ ይመስለኛል። የአዋዋልና የአረዳድ ጉዳይ ነው። ለኔ ቅርብ በሆኑ ሰዎች ሚዲያ ላይ እንድቀርብ ተጠይቄያለሁ። ግን ጥያቄ ያቀረቡት ክፍሎች በሚሄዱበት መስመር ለመሄድ ስለማልፈልግ ጥያቄው ለጊዜው እንዲቆየኝ አድርጌያለሁ።
ጎልጉል፡- ጥያቄ ቀርቧል እያሉ ነው? ለመሆኑ ከየትኛው ሚዲያ ነው?
ፕ/ር በየነ፡- በተለያዩ መንገዶች ጥያቄዎች ቀርቦልኛል። ያው በመተዋወቅ መንገድ። ይህንን ስል ክፍተት ልዩነት አለ በሚል ደረጃ የሚታይ አይደለም። በቃ የእምነት ጉዳይ ነው።
ጎልጉል፡- አንዳንድ ገለጻዎችዎ ማብራሪያ የሚጠይቁ ናቸው?
ፕ/ር በየነ፡- አስቀድሜ የገለጽኩ መሰለኝ። እኔ የምናገረው በሰከነ መንፈስ ለሚያዳምጡ፣ ከንዴትና ከስሜት ፖለቲካ ራሳቸውን ላቀቡት ነው። ለነዚህ ዜጎች መልዕክቴ ግልጽ ነው።
ፕ/ር በየነ፡- እስከ ሐምሌ (ጁላይ) እዚህ ነኝ።
ጎልጉል፡- አገር ቤት ያለውን ፖለቲካ ለጊዜው አቁመውታል ማለት ነው? የፖለቲካ እረፍት ወጡ?
ፕ/ር በየነ፡- ድርጅታችን መዋቅርና በየደረጃው ያሉ አመራሮች አሉት። በተቀመጠ እቅድ መሰረት ያከናውኑታል። በሳምንት ሲያስፈልግም በየቀኑ እንገናኛለን።
ጎልጉል፡- ዶ/ር ነጋሶ “በቃኝ” ብለዋል ሰምተው ከሆነ? እርስዎስ?
ፕ/ር በየነ፡- አንተ አረጀህ ካልከኝ እንጂ እኔ አላረጀሁም። ጤነኛ ነኝ። በደንብ አስባለሁ። እድሜዬም የዶ/ር ነጋሶን ያህል አይደለም። ራሴንም በግል መርጬ ወይም አስመርጬ አላውቅም። ርምጃን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የማውቅ ሰው እንደሆንኩ እረዳለሁ።
ጎልጉል፡- ስለዚህ ራስዎን ከፖለቲካ ስለ ማግለል አያስቡም ማለት ነው?
ፕ/ር በየነ፡- እኔ በቀላሉ ራሴን ከፖለቲካ ሰውሬ ገዳም ለማኖር መወሰን አልችልም። የምትታገልለትን ህዝብ ቃል ገብተህለት ለማን ጥለኸው ነው የምትሄደው? ልክ እኮ እንደ አንድ የሰራዊት መሪ ማለት ነው። ሰራዊቱን በትኖ ወደ ቤቱ የሚገባ!! 22 ዓመት ከታገልኩበት ህዝባዊና አገራዊ ዓላማ ለመገለል ራሴን ጡረታ የማወጣበት ምክንያት የለኝም።
ጎልጉል፡- 22 ዓመታት የተጓዘው የተቃዋሚዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ አድሮ ቃሪያ ነው እየተባለ ነው። ተስፋ ሰጪ ነገ የለም። እንዲያውም ኢህአዴግን ለማጀብ የተፈጠራችሁ እንደሆነ ተደርጎ አስተያየት ይሰጣል፤ እየተሰጠም ነው፣ ለዚህ ዋናው ምክንያት ምንድነው ይላሉ?
ፕ/ር በየነ፡- ተጨባጩ እውነታ ነው።
ፕ/ር በየነ፡- ወያኔ/ኢህአዴግ የሚባለው ቅድመ ዝግጅት ያደረገ ሃይል የአገሪቱን ሃብት፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት፣ መከላከያ፣ አጠቃሎ ተቆጣጥሮ ከእኔ ሌላ ማንም ብቅ ካለ አጠፋለሁ ብሎ በመወሰን አገሪቱን ረግጦ መያዙ አንዱና ዋናው መሰረታዊ ችግር ነው። እንግዲህ …
ጎልጉል፡- ይህ የሚታወቅ ነው። ከናንተ በኩል ያለውን ችግር ቢነግሩኝ?
ፕ/ር በየነ፡- መነሻውን ለማስጨበጥ ነው። በገንዘብ፣ በጦር መሳሪያ፣ በቁሳዊ ነገር ይህንን ኃይል መብለጥና ማሸነፍ አይቻልም። ግን በሰብዓዊ ብቃት በልጦ መገኘት ይቻላል። በስዕብና ጥራት፣ በዓላማ ጽናት፣ ለራስ በመታመን፣ ቃል የገቡለትን ህዝብና መጪ ትውልድ በማሰብ ትግሉን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማጠንከር አልተቻለም። ኢህአዴግን እንፎካከራለን የምንለው ክፍሎች መሰረታዊ የስትራቴጂና የታክቲክ ጉዳዮችን መለየት አቅቶን የምንፈረካከስ፣ እርስ በርስ በመጋጨት ጊዜ የምንገድል፣ ቀላል ጉዳይ እንኳ ማለፍ የማንችል መሆናችን ለኢህአዴግ አመችቶታል። የሚያሳዝነው ከዚህ ተደጋጋሚ ጥፋት ትምህርት መውሰድ አለመቻሉ ነው። የመንቦጫረቅ ችግር አለ። አገራችን አንድ ተረት አለ።“ለአውራነት/ለኮርማነት የታሰበው በሬ ተመልሶ እናቱን ጠባ“ ህዝብ ከሚጠብቀን ደረጃ ስንወርድ በተለያየ መልኩ ኪሳራችን ይበዛል ማለት ነው።
ፕ/ር በየነ፡- ትንንሽ ጠርዝ በመያዝ የሚደረግ ትግል የትም አያደርስም። ይህን ማወቅ ያልቻሉ አሉ። ኢህአዴግ ትንንሽ ሲመሰረት ደስታው እጠፍ ድርብ ነው። ኢህአዴግ ስትደራጅና ስትገዝፍበት አይወድም። እኛ ደግሞ ለመግዘፍና ተደራጅቶ ለመቀጠል አልቻልንም። ቅድም የተነሳው ጥያቄ እዚህ ጋር ይመጣል። የፖለቲካው ስራ የዘመኑን ፖለቲካ መጫወት የሚችሉትን ክፍሎች ይፈልጋል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ፖለቲካው አመራር አልባ ሆኗል። ሰው የለውም። ልሂቃኑ ዳር ቆመዋል። በአገራቸው ፖለቲካ መሳተፍ ሲገባቸው እኛን ይተቻሉ። የሞከርነውን ያወግዛሉ። ዳር ቆመው እኛን ከመተቸት ያለፈ አስተዋጽኦ የላቸውም። አገር ቤት በስፋት ያለው ችግር የተማረውና ዘመናዊውን ፖለቲካ ማራመድ የሚችለው ክፍል ዳር እንደቆመ መቅረቱ ሲሆን፣ ዲያስፖራውም በተመሳሳይ ተመሳሳይ ችግር አለበት።
ጎልጉል፡- ዲያስፖራው ንቁ ተሳታፊ እንደሆነ ነው የሚነገረው?
ፕ/ር በየነ፡- ችግሩ አገር ቤት ጎልቶ ቢታይም በውጪ አገር በሚኖሩ ወገኖች ዘንድም በተመሳሳይ ይስተዋላል። ስሜታዊነት ትልቁ ችግር ነው። ከስሜት ብዛት መሰረታዊ ጉዳዮችን መለየት አለመቻልና ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ ይታያል። ግለሰቦችን በጀት መድቦና ጊዜ ሰውቶ ስማቸውን የማጥፋት ስራ ላይ መጠመድ አለ። ይህንን ተናገርክ ወይም አሰብክ ብሎ ሰውን ለመስደብና ሰብዕናውን ለማቆሸሽ ጊዜ ሰጥቶ በዘመቻ ይሰራል። ይህ ትልቁ በሽታ ነው። ለዚህ ሁሉ መፍትሄው መስከን ነው። ከስሜት ፖለቲካ መለየት ነው። አገር ልትበተን ነው፣ አገር ልትደማ ነው፣ ኢትዮጵያ አለቀላት፣ ወዘተ በሚል ተስፋ መቁረጥን በራሳችን ላይ በማወጅ ተጠቃሚ አንሆንም። መጥፎውን ብቻ በማሰብ የምንታገል ከሆነ ሩቅ ማየት ይሳነናል። ብስጩ ሆነን እንቀራለን።
ፕ/ር በየነ፡- ፖለቲካ በባህሪው ክፍተትን አይወድምና አካኪ ዘራፍ ከማለት በመቆጠብ አብረን የምንሰለፍበትን መንገድ ለይተን ማወቅ ይገባናል። አለበለዚያ የፖለቲካው ሥራ እየተንቦጫረቀ ኢህአዴግን ከመጥቀም የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም። በግሌ ቀድሞውንም እንደማደርገው የሰከነ ፖለቲካ ከሚስባቸው፣ ከስሜታዊነት በጻዳ፣ ከተስፋ መቁረጥ በዘለለ ከሚሰሩት ጋር አጠናክሬ እሰራለሁ። መጪውን ምርጫ …
ጎልጉል፡- ስለ ምርጫው እናቆይና ስለመደራጀት ባነሱት ላይ የሚሰማ ተቃውሞ አለ። አብራችሁ መስራት አልቻላችሁም ትባላላችሁ። ቅንጅት ፈረሰ፣ አሁን ደግሞ መድረክም …
ፕ/ር በየነ፡- በርግጥ በመድረክ ደስተኛ አይደለሁም።
ጎልጉል፡- ይቅርታ ስላቋረጥከዎት፣ ግን መድረክ አለ?
ፕ/ር በየነ፡- መድረክ አለ። አመራርም አለው። ስምንት ድርጅቶች ነበሩበት። ከ2010 (እኤአ) ምርጫ በኋላ ሁለቱ መቀጠል አልቻሉም። አሁን ስድስት ድርጅቶችን በአባልነት አሉበት።
ፕ/ር በየነ፡- በህብረትና በቅንጅት ስብስብ ውስጥ መፍረክረክርክ ተፈጠረ። ህዝብን አሰባስቦ የማታግል ጉዳይ ዋጋ አጣ። ጉዳዩ አሳሳቢ ስለነበር እንዴት እናድርግ በሚል ለጉዳዩ ትኩረት የሰጥን ወገኖች መጀመሪያ በግል፣ ቀጥሎ በድርጅት ደረጃ መድረክን ፈጠርን። ከሁለት ዓመት በላይ የተደከመበት ስራ ነው። ህብረትና ቅንጅትን ካገጠሟቸው ችግሮች በቂ ግንዛቤ ተወስዶ ነበር መድረክ የተቋቋመው። ከዚያ ሁሉ ድካም በኋላ አሁን የተፈጠረውን ሳስብ ያሳዝነኛል። እገረማለሁም።
ፕ/ር በየነ፡- ከቀድሞው ስህተት ተምረን ትልቅ አገራዊ ዓላማ እናራምዳለን፣ ታግለን እናታግላለን፣ በማለት ተስማምተው በህግ ለመተዳደር ፊርማቸውን ያኖሩ ድርጅቶች ለገቡት ውል ተገዢ አንሆንም አሉ። የፈረሙበትን ውል አናውቀውም አሉ። አንድ ድርጅት ለህግ አልገዛም፣ ለፈረመበት ደንብ አልታዘዝም ካለ ጨዋታው ፈረሰ ማለት ነው። መድረክ ሲቋቋም ከ65 ገጽ በላይ የሚሆን ፕሮግራም ተቀርጾ ሁሉም አባል ድርጅቶች በራሳቸው ጉባኤ አጽድቀውት የተቀበሉት ነው። አንዳንዶቹ ላረቀቁት፣ ለተቀበሉትና በጉባኤ ወስደው ላጸደቁት ደንብ አንገዛም፤ አገር ግን እንመራለን እያሉን ነው።
ጎልጉል፡- እየከሰሱ ያሉት አንድነትን ነው?
ፕ/ር በየነ፡- አዎ። ምስጢር አይደለም። ችግር ፈጣሪው አንድነት ነው። በአደባባይ ችግራችንን ተነጋግረን የመድረክ የበላይ አመራሮች የወሰኑባቸውን ሰነዶች ይፋ አደረጉ። ይህ አግባብ አይደለም።
ጎልጉል፡- ስለዚህ ከአንድነት ምንም አልጠብቅም እያሉ ነው?
ፕ/ር በየነ፡- ራሳቸውን አስተካክለው ለመስራት ከፈለጉ ከአንድነት ሌላ የምመርጥበት ምክንያት የለኝም። ዋናው ለህግና ለደንብ መገዛት ነው። ከመድረክ የተሻለ ህዝባዊ አመኔታ ያለው ፓርቲ ያለ አይመስለኝም። በውስጡ ስላለሁ ሳይሆን እውነት ነው። ሌላ የተሻለ ድርጅት ካለ ሊገለጽ ይችላል።
ጎልጉል፡- ሕዝብ ተስፋ ይቆርጣል ብለው ያስባሉ?
ፕ/ር በየነ፡- ሕዝብ በመውደቅና በመነሳት ማመን አለበት። ሕዝብ ዓላማ ሊኖረው ይገባል። ተቃዋሚዎች ጥፋት ብናጠፋም ስልጣን ላይ ሆነን ህዝብን የበደልን አይደለንም። ወይም ስልጣን ላይ ተቀምጠን ክህደት አልፈጸምንም። ወደ ተስፋ መቁረጥ የሚያመራ ሁኔታ የለም። የልሂቃኑ ወደ ፓለቲካው አለመግባትና ባገራቸው ጉዳይ ዳር ቆመው ለመኖር መወሰናቸው ሊታሰብበት ይገባል። ኢትዮጵያና ልጆቿ ከነሱ ብዙ ይጠብቃሉ።
ጎልጉል፡- ኢህአዴግ በተለያዩ ሚዲያዎችና በመሪዎቹ ህዝብ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መንገሽገሹን እየገለጹ ናቸው፤
ፕ/ር በየነ፡- ይህ የኢህአዴግ አሉባልታ ውድቅ ነው። የሚያስተናግደውም ያለ አይመስለኝም። ወያኔ በራሱ ከተማመነ ምርጫውን ክፍትማድረግ ነው። ህዝቡ ተቃዋሚዎችን የማይመርጥ ከሆነ የአንድ ለአምስት አደረጃጀት ለምን አስፈለገ? ቤተሰብ ድረስ ዘለቀ የደህንነት ሰንሰለት ለምን ዘረጉ? ህዝብን በስለላ ማስጨነቅን ምን አመጣው? ሚዲያዎቹ እግረ መንገዳቸውን እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቅ ቢችሉ መልካም ነበር። የተፈጠሩበት ባህሪ ስለማይፈቅድላቸው እነሱን ጨምሮ ለውጥ ፈላጊዎች ናቸው። ህዝብ እኮ መምረጥ እንደሚችል ሲነገረው ማንን እንደሚፈልግ አሳይቶ ድምጹን በኃይል ነው የተነጠቀው። ምርጫ ሲመጣ ህዝብ ድምጹን የሚሰረቀው ለምንድነው? እንዲህ ያለውን የኢህአዴግ አሉባልታ ዋጋ የሌለው ተራ ነገር ነው።
ጎልጉል፡- እርስዎ እንዳሉት ኢህአዴግ የመፎካከሪያ መንገዱን ስለዘጋ፣ በተቃዋሚዎች በኩል አገር ቤት ያለው ትግል ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ የኃይል አማራጭ ይሻላል? በማለት የተነሱ አሉ። ምን አስተያየት አለዎት?
ፕ/ር በየነ፡- በስሜታዊነትና አገር ውስጥ ባለው የፖለቲካ ምህዳር ጠበበ በሚል አሁን ባለንበት ወቅት ለአገሬ ጦርነት አልመኝም። እኔ የምመራቸው ድርጅቶችም አይቀበሉትም። በጦርነት ለውጥ ሊመጣ ቢችልም አስተማማኝ አይደለም። ጦርነት የሁለት የጎበዝ አለቆች ጸብ ነው። ወያኔ ነፍጥ ይዞ በረሃ ገባ። ስልጣን ሲይዝ የገባውን ቃል አላከበረም። የኢትዮጵያ ህዝብ ካለው ልምድ የተነሳ ነፍጥ አንስተው የሚታገሉትን የሚያምን አይመስለኝም። በነፍጥ ስልጣን ይዞ ለህዝብ ያስረከበ የለም። በብዙ መልኩ ብክነት ነው።
ጎልጉል፡- በሰላማዊ መንገድ ኢህአዴግን ማስወገድ ካልተቻለ ምን ይደረግ? የሰላማዊ ትግሉን ቁልፎች ኢህአዴግ ብቻውን ይዞታል። እድሜ ከመቁጠር የዘለለ የሚገኝ ነገር የለምና ጦርነት ወቅታዊው አማራጭ ነው የሚሉ አሉ፣
ፕ/ር በየነ፡- አስቀድሜ ባግባቡ የመለስኩ መሰለኝ። ፈጥኖ ተስፋ የመቁረጡ ችግር ወደ አካኪ ዘራፍ ትግል ያዛውራል። ከስሜት በመራቅ በርጋታ ለሚያስቡት ነው የምናገረው ያልኩት ለዚህ ነው። የሰላማዊውን ትግል ለራሳችን ክብር በመስጠት፣ ስብዕናችንን ዝቅ ሳናደርግ፣ ህዝብና መጪውን የልጅ ልጅ ትውልድ እያየን በጽናት ብናከናውነው ውጤታማ ነው። ኢህአዴግም የሚፈራው ይህንን ትግል ነው።
ጎልጉል፡- ከመጪው ምርጫ ለውጥ ይጠብቃሉ?
ፕ/ር በየነ፡- እንግዲህ እኛ ለውጥ እንዲመጣ እየሰራን ነው። ወደ ምርጫ ከመግባታችን በፊት የ1997 ዓ.ም. ዓይነት ሁኔታ እንዲፈጠር እየሰራን ነው። ከምዕራብ አገሮችና ከአሜሪካ ጋር በቀጣዩ ምርጫ የዲፕሎማሲ ስራ ጀምረናል። ከኢህአዴግም ጋር ለመደራደር እንፈልጋለን። ቀጣዩ ምርጫ የተሻለ እንዲሆን እንጥራለን። ለውጥ የሚኖረው ይመስለናል። መጀመሪያ ላይ እንደገለጽኩት በኢህአዴግ የውስጥ ፖለቲካ ምቾት የሌላቸው ተበራክተዋል። ይህንን እንደ ዕድል ለመጠቀም በሎቢ ስራ ላይ ነን። ይህንን ካመቻቸን የደጋፊና የመራጭ ችግር የለብንም።
ጎልጉል፡- ኢህአዴግ በተለይም ህወሃት ውስጥ ከመለስ ሞት በኋላ ውስጡ ችግር ነግሷል። ሊፈራርስ ነው ይባላል? እንደ አንድ ታዛቢ ምን መልስ አለዎት?
ፕ/ር በየነ፡- ከስሜት የሚመነጭ ግምት ልክ አይሆንም። ግምት ሲበላሽ ትግልም መስመሩን ይስታል። በስሜት የተነሳ የትግሉ መስመር ከሳተ አደጋው ዘመንን ሊሻገር ይችላል። በስሜት ፖለቲካና ትግል ውስጥ የሚከሰተው ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ከባድ ነው። በመለስ ሞትና በህወሃት ጉዳይ የየዋህነት ፖለቲካ ባንከተል የተሻለ ነው። በማንኛውም የፖለቲካ ስራ ውስጥ ውይይትና ንግግር አለ። ክርክሮችንና ውይይቶችን ወደ መሐል የሚያመጣ ሰው ሊኖር ይችላል። ከዚህ አንጻር መለስ ቀዳሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ያ ማለት አሁን ሰው የለም ማለት አይደለም። ህወሃቶች አሁን ያላቸውን የኢኮኖሚ የበላይነት ማስጠበቅ የሚችሉት ሲስማሙ ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ። አሁን ያሉበት ደረጃና ስሜታቸው ጨምሯል። ከፍተኛ ሃብት አላቸው። ህወሃት ይህንን ሃብት ይዞ ለመቆየት የፖለቲካው የበላይነት ያስፈልገዋል። ስለዚህ የፖለቲካውን የበላይነት አሳልፎ ለመስጠት እርስ በርስ ይጣላሉ ብሎ መገመት ለኔ የዋህነት ነው። ራስን ማታለል ነው። የመከላከያ ሃይሉ ህዋሃት የሚገጥመውን ማንኛውን ችግር ለመታደግ ተቋጭቶ የተሰራ ነው። የወታደራዊ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ጡንቻ አለው። የደኅንነቱንና የፖሊሱን ኃይል በተመሳሳይ በሚያመቻቸው መልኩ ገንብተውታል። ስለዚህ ዝም ብሎ ኢህአዴግ በጉምጉምታ ይናዳል ብሎ ማሰብ አግባብ አይመስለኝም። ያሳስተናል። የተሳሳተ ግምትና መረጃ ጉዳቱ ለራስ ነው።
ጎልጉል ፡- ወደ ፊት የሚያስፈራዎት ነገር አለ?
ፕ/ር በየነ፡- በኢትዮጵያ ነጻ ምርጫ እንዳይካሄድ አፍኖ መያዝ ተስፋ የሚያስቆርጣቸውን ክፍሎች እያበዛ አገሪቱ ሙሉ በሙሉ ችግር ውስጥ እንዳትገባ እፈራለሁ። በአገሪቱ የፖለቲካ አካሄድ ውስጥ የሚገፉና የሚታፈኑ በበረከቱ ቁጥር እምቢተኛነት ይነሳል። እንዲህ ያለው ነገር ከተነሳ አደገኛ ነው።
ጎልጉል፡- ምን መልዕክት አለዎት? ለማን?
ፕ/ር በየነ፡- በአገራችን ዘመናዊውን ፖለቲካ የመምራት ብቃት ያላቸው ወገኖች ዳር ቆመው መመልከታቸውን እስካላቆሙ ድረስ ለውጥ ለማምጣት ቀላል አይሆንም። የሰላማዊው ትግል ብቃት ያላቸውን ክፍሎችና ልዩ ቃል ኪዳን የተላበሱ አገር ወዳዶችን ያሻዋል። አገሪቱ እንዲህ አይነት ስብዕና ያላቸው ሰዎች ድሃ አይደለችምና ልጆቿ ሊታደጓት ይገባል። ጡረታ እንድንወጣ የሚወተውቱን፣ ጥለን የት እንሂድ በሚል ተቸግረን እንደሆነ በመረዳት እነዚህ ወገኖች /ልሂቃኑን/ ወደ ፖለቲካው ተሳትፎ ፊታቸውን እንዲያመሩ ሊገፋፉዋቸው ያስፈልጋል። ሚዲያውም ላዲስ ሃሳብና ላዳዲስ ባለ ራዕዮች ልዩ ትኩረት በመስጠት ሊሰራ ይገባዋል። አልሰማም ያሉትንም የማሳሰብና የመውቀስ ተግባር ከሚዲያ ይጠበቃል። ዲያስፖራውም ድጋፍ ሲያደርግ በስሜት ሳይሆን በሰከነ አእምሮ በማሰብ ሊሆን ይገባዋል። ከንዴትና ከብሶት የጸዳ ፖለቲካ የሚያራምዱ ክፍሎች እንዲበዙ መስራት ይገባዋል። ስለ ድጋፍ ሲነሳ ዲያስፖራው የሚሰጠውን እገዛ ማንሳት ተገቢ ነው። የዲያስፖራው ድጋፍ ሚዛን በማይደፉ መስፈርቶችና ወገንተኛነት ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል። ይህ መለወጥ አለበት።
ጎልጉል፡- ኸርማን ኮኽን በቅርቡ ይፋ ስላደረጉት የኢትዮጵያና የኤርትራ እርቅ ጉዳይ ምን ይላሉ?
ፕ/ር በየነ፡- እርቅ ደግ ነው። ከኤርትራ ጋር የሚደረገው እርቅ ግን የፖለቲካ መሪዎች ተራ መጨባበጥና የነሱን ፍላጎት ብቻ ያሟላ መሆን የለበትም። እርቁ የአልጀርስን ስምምነት በቅድሚያ ተግባራዊ ከማድረግ እንደሚጀምር ነው ኮኽን የተናገረው። በደብዳቤ ውስጥ ከዚህ ዘለለ ቁም ነገር አላየሁበትም። የአልጀርስ ስምምነት ሲባል ባድመን አሳልፎ የሚሰጥ፣ ኢትዮጵያን በርካታ መሬት እንድታጣ የሚያደርጋት ነው። ከዚህ አንጻር ስጋት አለኝ። ፓርላማ በነበርኩበት ወቅት እንዳልኩት ጉዳዩ ጥንቃቄ ያሻዋል። ስለዚህ አዲስ ድርድር ከተደረገም ሰጥቶ በመቀበል መርህ አትራፊ በሚያደርግ መልኩ ሊሆን ይገባል።
ጎልጉል፡- በሰጡት አስተያየት ላይ ተቃውሞ እንደሚገጥምዎት ያስባሉ?
ፕ/ር በየነ፡- በመጀመሪያ ለማን እንደምናገርና አውቃለሁ። እኔ የተናገርኩት በግል የማምንበትንና በድርጅት አቋማችን የሆነውን ነው። ሃሳብ ላይ ተንተርሶ መከራከርና መነጋገር ይቻላል። ሃሳብ ላይ ያላተኮረ ተራ ዘለፋና ትችት ዋጋ የለውም። ከዚህ ሌላ በየነ ይህንን አለ በማለት የዘመቻ ወቀሳ ከተሰነዘረ የምለው ነገር የለም። በጨዋነት ለሚቀርብ የሃሳብ ተቃውሞ ግን የሚቀርበውን ሃሳብ ሰምቼ መልስ ልሰጥ እችላለሁ። ይሄ አሁን የተለመደው አይነት ተራ የስም ማጥፋትና ማቆሸሽ ዘመቻ ግን የመጨረሻው እድገታችን መሆኑ ያሳዝነኛል። ብዙ ነገር እያየን ነው። ሰው ለማቆሸሽና ስም ለማጥፋት ጊዜና ገንዘብ እየባከነ ነው።