አሁንም በሳውዲ አረቢያ እና አካባቢው አገሮች የሚገኙ ወገኖቻችን የድረሱን ጥሪዎች እያሰሙ ነው። የወገኖቻችን ዋይታና ሰቆቃ አልበረደም። ዛሬም እህቶቻን እየተደፈሩ፣ እየተዋረዱ፣ እየተገደሉ ናቸው። በጥጋብ አገር ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያዊያን ሕፃናት በረሀብና በጥም እየሞቱ ነው። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ለከፋ የአዕምሮ ህመም እየተዳረጉ ነው።
በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ወገኖቻቸውን ሕመም እየታመሙ፤ ስቃያቸውን እየተሰቃዩ ይገኛሉ። አስቸኳይ እርዳታ ለማድረስም አቅማቸው የቻለውን ሁሉ ለማድረግ በመረባረብ ላይ ናቸው።
ባለፉት ጥቂት ሣምንታት ኢትዮጵያዊያን ባደረጓቸው ብርቱ ጥረቶች ጥቂት አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል። ከደረሰባቸው የመብት ረገጣ ጋር ፈጽሞ ተመጣጣኝ ባይሆንም ቢቢሲን ጨምሮ አንዳንድ የዓለም ዓቀፍ የዜና አውታሮች በወገኖቻችን ላይ ስለሚደርሰው በደል እንዲዘግቡ ማድረግ ተችሏል። እስካሁን ምን ያህል ወገኖቻችን እድሉን እንዳገኙ ማረጋገጥ ባይቻልም የሳውዲ መንግሥት ሙሉ የትራንስፓርት ወጪ ችሎ ወገኖቻችን ማጓጓዝ ጀምሯል። ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅቶች ለኢትዮጵያዊያን መብት መከራከር ጀምረዋል።
በአንፃሩ ግን አሁንም ሕሊናን የሚረብሹ ነገሮች እየተሰሙ ነው።
- ከሳውዲ እየታፈሱ የመን ድንበር ላይ የተጣሉ፤ የደረሱበት የማይታወቁ ኢትዮጵያን ቁጥር በየእለቱ እየጨመረ ነው። እነዚህ ወገኖቻችን በየመን በረሀ ላይ የሚደርስባቸው ሰቆቃ ሳውዲ ውስጥ ከነበረው የባሰ ነው።
- አሁንም በሳውዲ ተደብቀው የሚገኙ፤ “እጃቸውን ለመንግሥት ሰጥተው” እንደ ወንጀለኛ በእስር ቤቶች የሚማቅቁ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አሉ። እነዚህ ወገኖቻችን ያሉበት ሁኔታ ሕሊና ሊሸከመው ከሚችል በላይ ነው።
ከዚህ ሁሉ በላይ ኢትዮጵያዊያንን እየረበሸ ያለው የወያኔ ባህርይ ነው።
ወያኔ በእንዲህ ዓይነት የመከራ ወቅትም በወገኖቻችን ላይ ዘርፈ ብዙ ንግድ እያጧጧፈ ነው። በሳውዲ አረቢያ መንግሥት ወጪ የተመለሰሉትን ወገኖቻችን ለምርጫ ቅሰቀሳ ፕሮፖጋንዳ ሥራ እየተጠቀሙባቸው መሆኑ ሳያንስ ለእለት ጉርስ የሚሰጣቸው የእርዳታ ገንዘብ በወያኔ እየተዘረፉ ነው። ገንዘብ ባለበት ሁሉ ወያኔ አለ። ወያኔ ለተመላሽ ስደተኞች የእለት ጉርስ የተሰጠውንም እርዳታ እየቀማ የሚበላ እኩይ ኃይል ነው።
ድሆች ኢትዮጵያዊያን ወደ አረብ አገራት ሲሰደዱ ለወያኔ ድርጅቶች ገንዘብ ከፍለው ነው። እዚያ በነበሩበት ጊዜም ለወያኔ ገንዘብ እንዲከፍሉ ይደረግ ነበር። በግፍ ተፈናቅለው፤ ሀብታቸው ተዘርፎ ባዶ እጃቸውን ሲመለሱም ለወያኔ የእርዳታ ገንዘብ መለመኛ ሆነዋል። ወያኔ በድሆች ኢትዮጵያዊያን ድህነት የሚከብር በታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ስግብግብ ነው። ወያኔ ኢትዮጵያዊያን ፈጽሞ ሊጠየፉት የሚገባ ነው ስብስብ ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ከመርዳት ጎን ዓይኖቻችንን ከወያኔ እንዳንነቅል በአጽንዖት ያሳስባል። ወያኔ ከሥልጣን ሳይወገድ ችግሮቻችንን መፍታት አንችልም። የኢትዮጵያዊያን ችግሮች ለወያኔ የገቢ ምንጮች ናቸና ወያኔ እስካለ ድረስ ችግሮችን መፍጠሩና ማስፋፋቱ አይቀርም።
የኛ የኢትዮጵያዊያን ችግሮች የመፍትሔ ቁልፍ ያለው ወያኔን በማስወገድ ፍትሀዊ አመራር ማስፈን ላይ በመሆኑ የጋራ ትኩረታችን እዚያ ላይ እንዲሆን ግንቦት 7 ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar