November 6, 2013
ከተስፋዬ ዘበነ(ኖርዌይ በርገን)
ሃገርና ሕዝብ በውጥረት በታመሰበት አምባገነን የህውሃት/ኢአዴግ/ ዘረኛ ስርዓት ከምስራቅ እስከ ምህራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ሃገሪቱን እንደ ብራና ወጥሮ የሕዝቡን ኑሮ ሲያከብድበት እያየንና እየተመለከትን ስርኣቱን ለመታገል በየትኛውም መልኩ የተዋቀርን ድርጅቶች ሳንጀምር እየጨረስን ወይም እራሳችን ስላዋቀርነው ፓርቲ፣ ድርጅት ወይም ሸንጎ ሳንመረምር ሌሎች ስለሚደክሙበትና ስለሚለፉበት ትግል መፃዪ እድል እየተነበይን እርስ በእርስ ስንናከስና ስንጣረዝ የዘረኛውን የህውሃት እድሜ አበርክተን እዚህ አድርሰነዋል፡፡
በዚህ እኩይ የህውሃት ስርዓት መጀመሪያ ጀምሮ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በራስ ተነሳሺነት ተዋቅረው እየተንቀሳቀሱ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች አላማና ግባቸውን ለማስፈፀም የሰላማዊ ትግል መርሆችን ተግባራዊ ለማደረግ አንድም በራሳቸው የውስጥ ችግር ምክንያት፣ በዋነኝነት ግን ስርዓቱ ካለው ተፈጥሮዊ ባህሪ አንፃር ከሕዝብ ጋር ያለው ትስስርና በሕዝብ ላይ የሚፈፅመው የመልካም አስተዳደር ችግርም ሆነ የሰብሃዊ መብት አያያዝ እንዲሁም ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ስላሉበት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ለተደራጁ ፓርቲዎች ነፃነት ሰጥቶ ሞቱን ማፋጠን አይፈልግም፡፡ ስለዚህም ነው በሰላማዊ መንገድ የመታገያ መንገዶችን ሁሉ ዘግቶ በጥቂት ቁርጠኛ ታጋዮች ላይ እርምጃ እየወሰደ ትግሉን እያሽመደመደ ያለው፡፡ በሰላማዊ መንገድ እታገላልሁ የሚል ድርጅት አባላቱን አሰባስቦ አላማውን ማስረፅ ካልቻለ፣ በህዝብ ላይ የሚፈፀመውን ማንኛውንም በደል በመቃወም የሕዝብን ድምፅ ለማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ ካላካሄደ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን የሚያዘጋጅበት ቦታ ማግኘት ካልቻለና ይህንንና ይህንን የመሳሰሉ ህገ-መንግስታዊ የሰላማዊ ትግል መብቶቹን በወያኔ ስርዓት ከተቀማ እንዴት ነው ትግሉን ጫፍ ማድረስ የሚቻለው የሚል ጥያቄ ማሰነሳቱ አይቀርም፡፡
ዘረኛው የወያኔ ቡድን በሃገርና በሕዝብ ላይ ከሚፈፅመው ግፍና በደል አንፅር ኢትዮጲያችን ውስጥ ላለፉት ሃያ ሁለት አመታት የተደረገው ትግል እምብዛም አመርቂ ሳይሆን ይልቁንም ለህውሃት ቡድነ ሽፋንና ከለላ በመስጠት በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ በትንሹም ቢሆን አወንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ የረዳው የትግል ስልት ነበር፡፡ እንደሚታወቀው በህገ- መንግስቱ ላይ የሰፈሩ የሰብሃዊ መብት ድንጋጌዎች አሉ መሬት ላይ አይታዩ እንጂ ለምሳሌ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዳለ ተደርጎ የሚቆጠረውና በአካል ግን ከገዢው ፓርቲ ህውሃት(ኢአዴግ)ውጪ ለውጥ ማምጣት እንዳይችሉ ተደርገው ሕዝባዊ መዋቅራቸውን እያሽመደመደ የሚበትናቸው ድርጅቶች እስካሉ ድረስ ለዘረኛው ስርዓት ሽፋን ከመሆን በዘለለ ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሲታገሉና ሕዝብን ሲያታግሉ መመልከት በጣት ከሚቆጠሩት ፓርቲዎች ውጪ እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡
በአጠቃላይ እስካሁን ሲደረግ የነበረው የነፃነት ትግል ያስከፈለንን ዋጋ ያህል የምናጣጥመው ድል ሳይኖረን ከሁለት አስርተ አመታት በሗላም ገዢዎቻችን የጫኑብን ቀንበር ከብዶን እንፍገመገማለን፡፡ ወያኔን ለማስወገድ እስካሁን በተደረገው ትግል ውስጥ ለውጥ ማምጣት የቻለ ባይኖርም ለኢትዮጲያና ለሕዝቧ መልካም በማሰብ ከዘረኛው ስርዓት መንጋጋ ነፃ ለማውጣት የሚደረግ ትግል ከየትም ይነሳ ከየትም መደገፍ ባንችል እንኳን መንቀፍ ግን የለበትም፡፡
ከያዙት የትግል ስልት ውጪ ያለን አመለካከትና እንቅስቃሴ ሁሉ በመቃወምና በማብጠልጠል የህውሃትን ዘረኛ ቡድን አደብ ማስያዝ አይቻልም፡፡ በአሁን ሰዓት ለሃገርና ለሕዝብ የሚያስፈልገው ከህውሃት ማነቆ ነፃ የሚያወጣ እንጂ ነፃነቱ የሚገኝበት ሃገርና ቦታ አይደለም፡፡ የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጲያ ጋር ጠላትነት የጀመረው አሁን ለነፃነት በሚታገሉ ወገኖች ዘመን ሳይሆን ከኤርትራ ጋር ሲጀመር ወዳጅ በመቀጠልም ጠላት ሆኖ የሃገራችንን ቤሔራዊ ክብር በዋረደው የኢትዮጲያ ብቸኛ ጠላት በሆነው የህውሃት የእድሜ መጀመሪያ ነው፡፡
የግንቦት ሰባት ዋና ፀሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንደተናገሩት ለኢትዮጲያም ሆነ ለሕዝቧ አሁን ባለንበት ሁኔት ቀንደኛው ጠላት ህውሃት መሆኑን በተደጋጋሚ አሳስበዋል፡፡ ይህንን እውነታ ለመቀበል የሚቸግራቸው ወገኖች ህውሃት በኢትዮጲያና በሕዝቧ ላይ እየፈፀመ ያለውን በደል መረዳት የቸገራቸው ወይም በአሁን ባለንበት ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ማለቂያ የሌለው ሰሞነኛ የትግል ስሌት ውስጥ ክብርና ዝና የሚፈልጉ ለመሆናቸው አማራጭ የማያቀርቡበት ተራ ተቃውሟቸው አንድ ማሳያ ነው፡፡
ትግል በመስዋትነት ይሰፈራል ስለሆነም የተመቻቸ የግል ኑሮዋቸውን ትተው በዛች ሃገር የምናልመው የሕዝቦች ሰብአዊ መብት የተከበረበትና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ምስረታን እውን እንዲሆን በተግባር ዋጋ ለሚከፍሉ ቁርጠኛ የሕዝብ ልጆች ክብር በመስጠትና አጋርነታችንን በመግለፅ የወያኔ የእድሜ ዘመን እናሳጥር፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ በደም የሚከፈል መስዋትነትን ከመንቀፍ እንቆጠብ፡፡
ድል ለኢትዮጲያ ሕዝብ!!!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar