søndag 3. november 2013

የተበተኑ የኢትዮጵያ ፍርስራሾች

October 31, 2013

ዳኛቸው ቢያድግልኝ
አገር ማለት ሕዝብ ነው ሕዝብም የሰዎች ስብስብ፡፡ መልክዐምድሩና የተፈጥሮ ሀብት ደግሞ የሰዎችን አኗኗርና አስተሳሰብ የሚቀርጽና ማንነትንም የሚያላብስ ነው። በየመንደሩና አካባቢው ያለው የተለያየ የአኗኗር ሁኔታ የቋንቋና የባህል መስተጋብር ደግሞ ትብብርንና አንድነትን የሚያወርስ እኔነትንና የእኔነትን የሚሰጥ ይሆናል። ኢትዮጵያዊነትም እንደዚያ ነው።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ግን በሁሉም አቅጣጫ ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ያቺ የሰውን ዘር ትልቅ የመሆን ተስፋን የሰነቀች ምንጭ ትደርቅ ዘንድ የራስዋ ልጆች እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እያሉ በፉክክር ሊያጠፏት ይሽቀዳደማሉ። የቀጨጨ ትውልድና የጫጨ አእምሮ ያለው ዘር ይጠፋ ዘንድ እውነት ነውና ኩራታችንን ተቀምተን አናሳና ሁዋላ ቀርነታችንን ተቀብለን እንድንጠፋ ተፈርዶብን መጥፋትንም ተለማምደን በዚህም ዳር እንቁም በዚያኛው እግር በእግር እየተጠላለፍን እንዘጭ እንዘጭ የምንልም በርካቶች ሆነናል። ከትናነንት በመማር ፈንታ በትናንቱ እያማረርን ቂም አርግዘን ሞት የምናምጥ በየጎጡ የሰፈርንም ብዙ ነን። “ለመጥፋት መጋፋታችን መቆም አለበት! መኖር ይገባናል! እኛ እኮ ምንጮች፤ የሰው ዘር፣ የእህል ዘርና የስልጣኔ ፈር ቀዳጆች ነን!” ብለን በነበረን ላይ ያለችንን አክለን “የነገን ተስፋ ብሩህ አድርገን ማለፍ የሚገባንና ጮክ ብለን የማሰብ ሃላፊነት ያለብን የኢትዮጵያ ልጆች ነን” የሚል መነሳሳት ያስፈልገናል። ኮሎኒያሊስቶች ባሻቸው ቀጣጥፈው የሰሯቸው አገሮች እንኳን አገር ነን ብለው በሚኮሩበት በዚህ ዘመን የፈረንጅ የእውቀት ቃርሚያ የቀመሱቱ የኛው ልጆች  ኢትዮጵያ የምትባል አገር እኮ አልነበረቺም እያሉን መቃብራችንን ሊያስቆፍሩን ይውተረተራሉ። ለመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት ይሆን? ኢትዮጵያዊነት ለኔ እንዲህ ይገለፃል ወይም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል የሚሰማኝ ስሜት እንዲህ ነው።
“ከኢትዮጵያ አፈር ውሀና አየር የተሰራሁ፣ ማለትም የበላሁት የጠጣሁት፣ የተነፈስኩት አየርና የሞቅሁት ፀሀይ ያለኝን ተክለ ሰውነት እውነት ያደረገ፤ አስተሳሰቤን፣ ወግና ልማዴን ስነልቦናዬን ጭምር ያወረሰኝ፣ ሀሳቤን እግለጽበት ዘንድም አፍ የፈታሁበትን ቋንቋ የሰጠኝ የምንነቴ መገለጫ ነው”
ግን በዚህም አላበቃም ከዚህ በላይ የማንነቴ መገለጫ ትልቅ እውነትም አለና። ኢትዮጵያዊ ነኝ እንድል የሚያደርገኝ ሌላው እውነት ከውልደቴ በሁዋላ የተማርኩት ብቻ ሳይሆን በውርስ የተቀበልኩትምእኔነት ነው እላለሁ። ይህም ውርስ….
ከእናቴና አባቴ እኩል በእኩል በተቀበልኩት ክሮሞዞም ይት ድርና ማግ የተሸመንኩ ‘ጂን’ በሚሉት ዝንጉርጉር የዘርማንዘሮቼ አሻራ  ጥበብ የደመቅሁ አንድም ብዙም ሰው መሆኔም ጭምር ነው። አያቶቼን፣ ቅም አያቶቼን ከዚያም በፊት የነበሩትና የመጀመርያው ለተከታዩ ሲያወርሱት የቆዩት አሻራቸውን ሁሉ መረከቤና የዚያም ነጸብራቅ መሆኔ ነው ኢትዮጵያዊነቴ።  ከኔ ጋር በአካል ምንም ግንኙነት ሳይኖራቸው ሳላያቸው ሳያዩኝ ግን እነሱን እንድመስል የሚያደርጉኝን መሰረታዊ የሆኑ ባህርያት የተረከብኩበት መገለጫዬ ነው ኢትዮጵያዊነቴ።”
ስለዚህ እያንዳንዳችን የተሸከምነው ጓዝ ብዛቱ የትየለሌ በመሆኑ ግለሰብም ሕዝብን (ያሉትንና የነበሩትን) ይወክል ዘንድ እውነት ነው።  ዘር ከልጓም ሲሉ፣ የእናት ሆድ ዥጉርጉር ሲሉም ያንን ትልቅ እውነት በሀገራዊ ብሂል የሚገልጹበትና ሳይንሱም ይህንን እውነት የሚመሰክርበት ነው። ለዚህም ነው በሌላ ሀገር ተወልደው፣ የሌላ አገር ማንነትን ይዘው ነገር ግን ምንነታቸውን በሰጣቸው የጂን አሻራ ምክንያት ኢትዮጵያዊ የሚያስብሉ ባህርያትን የሚያንጸባርቁ ወገኖችን የምንመለከተው።
እንዲያም ሆኖ ግን እኔ የተሰራሁበት አፈር፣ ወሀና አየር የኢትዮጵያው ስለሆነ ዛሬ በዐለም ዙርያ በመዞሬ ያካበትኩት እውቀትና ልምድም ተጨምሮበት እንኳን ኢትዮጵያ ከውስጤ ከወጣች ባዶዬን የምቀር ነኝ። መሰረቴ ሀገሬ በመሆንዋ ያለሀገሬ ባዶ ነኝ። ብዙዎች ላይ የሚነበበውና ምትሀታዊ ሀይል የሚመስለው እውነትም ይኸው ነው። ስለዚህ ሀገራችን ከሌለች ሀገርም ከሌለን የኛ መኖር ካለመኖራችን ጋር አንድ ነው። ጎዶሎ ስሜት ያልተሟላ ማንነት ይዞ መንገታገት! በስደት አካላዊ ምቾት እንኳን ቢኖር የተሰበረ ቅስም የመያዛችን ትልቁ ምክንያትም ይኸው ይመስለኛል። ለዚህ ነው አገር አልፈረሰችም ሲሉኝ ስብርባሪዎችዋን ተበታትነው እያየሁ እንደምን አልተነካችም ልበል? አገር ሕዝብ ከሆነ ሕዝብ ሲበተን አገር እየፈረሰ ነው ማለት ምን ውሸት አለው? የሚያሰኘኝ።
የኢትዮጵያ ጠላት ኢትዮጵያን ካስተዳደረ፣ የኢትዮጵያ ምሁራን ለሕዝባቸውና ለወገናቸው ማገልገል ተስኗቸው በስደት ለአፍሪካ ሀገሮች፣ አውሮፓና አሜሪካ እውቀታቸውን የሚሰጡ ከሆነ፣ የነገ ሀገር ተረካቢዎች የሆኑ ወጣቶች በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ “በሀገር ተዋርዶ ከመኖር እየሄዱ መሞት” ብለው የሚሰደዱ ከሆነ፤ ወይዛዝርቶች  ወደ አረብ ሀገር ለባርነትና፣ ለግርድና ሲያቀኑ ባዕድ ሀገራት ለም መሬታችን እየተሰጣቸው ሕዝባቸውን ሲመግቡ እንደሞኝ እየተመለከትን እድሜ የምንገፋ ከሆነ አገር ምንም አልሆነች ማለት እንደምን ይቻለናል? እንደ መለስ ዜናዊ “መሬቱ እኮ እዚያው ነው ሱዳኖች መጥተው አረሱት እንጂ” አይነት አባባል እኛም “ኢትዮጵያ እኮ አለች ሕዝብዋ እየተሰደደና እየተፈናቀለ ነው እንጂ …” ብለን በራሳችን ካልቀለድን በቀር እየፈረሰች ያለች አገር ናት።
ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ስንደረደር የካፒቴን ተሾመ ተንኮሉን ቃለመጠይቅ ኢሳት ላይ እየተመለከትኩ ነበር። የደረሰበት በደል በጫካ ሕግ ላይ የተመሰረተ የጠላትነትና የማንአለብኝነት ተግባር ነበር። ለማመንም ለመቀበልም እጅግ የሚያዳግት ነው። እስከዛሬው ቀን ድረስ ለተቀበለው ስቃይ ምክንያት ምን እንደሆነ አልተነገረውም። ሀገሩን ማፍቀሩና ማገልገሉ በወያኔ ዘንድ እንደ ከባድ ጥፋት ከመቆጠሩ በስተቀር። ከዚያ በደል ሁሉ በሁዋላ ደግሞ አገርህ ትፈልግሀለች መባሉ ይበልጥ የሚያቆስል ነው። እንደ ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ አይነት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪ ያስተማረቻቸውና የሀገር መከታ የሆኑት ሁሉ ተሰደው የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የተገኘውን ስራ እየሰሩ ተበትነው ይኖራሉ። በሙያቸው እየሰሩ ያሉትም ቢሆኑ ለመኖር እንጂ ሀሴትን ለማግኘት እንዳልታደሉ ይታወቃል። በ42 ፕሮፌሰሮች መባረር የተጀመረው ዘመቻ ዛሬ ከየተቋማቱ አገር ጥለው የሚኮበልሉ ምሁራን ቁጥር ከግምትም በላይ ነው። የመውጫ ቀዳዳ አበጅተው አገሬን የሚለውን በርካታ ወገን ከሀገሩ አስጨንቀው አስወጥተውታል እያስወጡም ነው የምንል ከሆነ በዚያች አገር መኖር የሚችለው መከራን ለመቀበልና ለመጋፈጥም ዝግጁ የሆነና ባርነትን በግዱና ምርጫ በማጣት የተቀበለው ነው ማለት ነው። ባለሀገር ነን ባዮቹና የሀገሪቱን ጸጋ እየተቀራመቱ ያሉት ጥቂት የወያኔ አባላትና ተላላኪዎቻቸው ብቻ ናቸው። እነርሱም የቆቅ እንቅልፍ የሚተኙና ሀብት የሚያሸሹቱ ይበዙባቸዋል።
ትውልድን የሚያንጽና የሚቀርጽ አካል ከሌለ የሚጠብቀን ለባርነትና ለውርደት የተመቸ ዜጋን መተካት ግድ ይሆናል።ሀገረገዢዎቹ ደግሞ ከነርሱ የተሻለ የሚያስብ እንዲኖር አይሹም እንዲሁ እየተንገታገቱ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘመኑ የሚመጥን እውቀትና ሀብት ይዘው የሚፈነጩበትን አገር እየሰሩ ነው። በቁም መፍረስና መሞት ማለትም ይኸው ነው። በተለያየ የሙያ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ወገኖች በውጭው አለም ከእውቀታቸውና ከልምዳቸው ጋር የማይመጣጠን ስራ ሲሰሩ ማየት ትልቅ የሀገር ሀብት ከንቱ መቅረቱን መመስከር ስለሆነ ያማል። በሙያቸው የሚሰሩትም ቢሆኑ ለሀገርና ለወገን የሚገባውን ማድረግ ካልቻሉ በደሉ ያው ነው። በጥቂት የወያኔ ባለስልጣኖች ባለንብረትነት የሚገነባው ሕንጻ ሽቅብ ሲወጣና ወደ ጎን ሲሰፋ ኢትዮጵያዊነት ግን ቁልቁል ሲሄድና የሃገሪቱም ጠረፍ ወደጎን ሲጠብ ማየትስ ምንኛ አሳዛኝ ነው?
ያለው መንግስት ባመነው መሰረት ብቻ እንኳን በሁለት አመት ውስጥ አራት መቶ ሺህ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ተሰደዋል የሚል ዜና ሰምተናል። ምናልባትም ተመሳሳይ ቁጥር በህጋዊ መንገድ ከሀገር ለቀው ወጥተዋል ይህ ከቶ ምንን ያመለክታል? የኢትዮጵያ ወጣቶች ደም የሰሃራ በረሃን እያጠጣው ነው፣ የውቅያኖስ አሳዎችን እየቀለበ ነው። በየመን ሞት ነው፣ በሊቢያም ሞት ነው። በኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ማላዊ፣ ዚምባብዌ፣ ሞዛምቢክ የኢትዮጵያ ወጣቶች እስርቤቶችን አጨናንቀውታል። የአለም ደቻሳ የጣር ድምጽ ዛሬን ድረስ ይሰማል። በፈላ ውሃ የተቃጠለችው ሸዋዬ ሞላ ምስል አሁንም አለ፤ የሚደርስላት ጠፍቶ አስፋልት ላይ ደሟ የተነዠቀዠቀው ወጣት ምስል በሃሳባችን ወስጥ ትኩስ ሀዘን አስፍሯል። ኤምባሲዎቻችን ሱቅ በደረቴዎችና ሰላዮችን እንጂ ኢትዮጵያን ጉዳዬ የሚሉ ሰዎችን አልያዘም። ወደ ሞታቸው እየተጋፉ መርከብ ወይም ጀልባ የተሳፈሩ ወጣቶች በላምባዱዛ መርገፋቸው አንገት ያስደፋል። በአንድ ዘመን አረቦች በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰደው እየኖሩ የእለት ጉርሳቸውን ያገኙ እንዳልነበር ዛሬ አረቦች በጋጠወጥ ድርጊት ልጆቻቸንን እህቶቻቸንን ሚስቶችንም ጨምሮ እንደ አሻንጉሊት እየተጫወቱባቸው ነው። ቀኑን በስራና በችጋር ለሊቱን በመደፈር እያሳለፉት መጨረሻቸው እብደትና ሞት ሆኗል። በዚህ አይነት መከራ የሚመጣ ገንዘብን የሚጠብቁ ተጧሪዎች ደግሞ ልጆቻቸውንህቶቻቸውን ወንደሞቻቸውን እና ሚስቶቻቸውን ለዚህ መከራ አሳልፈው ከሰጡ በርህራሄና በመተሳሰብ የሚታወቀው ኢትዮጵያዊነት አብቅቶለታል።  መከታነት አጋርነትም በችጋር ምክንያት ተሟጥጦ ሄዷል፣ ክብርም እንዲሁ። ወጣቶቻችን እንደ ባርያ እየተሸጡ ነው፣ የኛው ጉዶችም ባርያ ፈንጋይና ደላሎች ሆነው ወገኖቻቸውን  ያሻሽጣሉ። እንዲህ ከዘቀጥን እውነት ኢተዮጵያ የምንላት ሀገር አልፈረሰችምን? በትክክል እየፈረሰች ነው የሚያሰኘኝ የተበታተኑ የኢትዮጵያ ፍርስራሾች በመላው አለም መበተናቸውን መመስከሬና አንዱም እኔው መሆኔ ነው።
ወድቀናል መነሳት ግን ይቻለናል። ፈርሰናል መልሰን የመጠገን አቅም ግን አለን። ስለዚህ በዚህች በምንወዳት አገራችን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ከየተበተንበት ጉድባ ከየወዳደቅንበት ቀዬ ደልቶን ከምንኖርበት የሰው አገርም ቢሆን ቀና ብለን ተስፋችንን ልናለመልም ቃልኪዳናችን ልናድስ ይገባል። ሀገር የሌለው፣ መሸሻ፣ ማኩረፊያና ማረፊያ የሌለው ሰው ያበቃለት ነው። የተቀበልነው ፓስፖርትና የያዝነው ዜግነት አገሮች በመልካም ፈቃድ የሰጡንን ባልፈቀዱ ጊዜም የሚነጥቁን መሆኑን ልናስተውል ይገባል። ባይነጥቁንም ሁለተኛ ዜጎች ጥገኞችም ነን።
በኢትዮጵያ ተስፋ እንዳንቆርጥ ማንነታችንን አሽቀንጥረን እንዳንጥል የሚያደርጉ ክስተቶች ስንመለከት ደግሞ ታላቅ  ብርሃን ይሆንልናል። ኢትዮጵያችንን በዚያም በዚህም ቢቀጠቅጧትና እያንዳንዱ ሰው ሀገሩን እንዲጠላ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በቀን በቀን ቢገጥሙት፣ ምርር ብሎት በሰሃራ በረሃም ቢያቋርጥ፣ በኬንያ ቢፈተለክ በሱዳን ቢያቀጥን በቦሌም ቢከንፍ ሃሳቡ አረፍ ሲልለት ኢትዮጵያዊነቱ ይነግስበታል፤ በረሃውን ሲያቋርጥ ድህነት ቢያሸማቅቀውም እንኳን ኢትዮጵያዊ ኩራቱን ይዞ ቀን እስኪያልፍ እያለ የጭለማውን ጊዜ ይገፋዋል። ሰው እንጂ ሀገር አይሞትም የሚል የተስፋ ደወል አድማስ እየሰነጠቀ ግም ድው ኳ ሲል ይሰማዋል። ሰለዚህም ነው ባንዲራውን ሲያሳንሱበት ለብሶት፣ ቆብ አድርጎት፣ የአንገት ልብስ አሰርቶት ጉንጭና ሌላም የሰውነት ክፍሉን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀብቶት አደባባዩን የሚያደምቀው። ሀውልቱን ሲያፈርሱበት ታሪኩን አስውቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ መጽሃፍ አድርጎ ያወጣዋል። በሃይማኖቱ ሊያናክሱት ሲፈልጉ ተቃቅፎ ይሳሳማል። ይህን ስሜት እንደ ምርኩዝ ይዞ ኢትዮጵያን ማዳን ይቻለናል። መንደርደርያና ማኮብኮብያውን ግብ አድርገው ነገር የሚወናጨፉቱ ይህንን ታላቅ ነገርም ሊገነዘቡ ይገባል። የምቾት ፖለቲካ ለማሻመድ ጊዜው የለንም፣ አገር የማዳን ጥድፊያ እንጂ የምርጫና የድምጽ ብልጫ ጊዜ ላይ አይደለንምና ቀዳሚውን ቀዳማይ ዓላማ አድርገን እንጀግን። ወደ ድል ለሚወስደው ጎዳና መንገድ ጠራጊ እንሁን ያም ቢያቅተን እንቅፋት መሆናችን ይብቃ በማለት ኢትዮጵያችን በነጻነት ለዘለዐለም ትኖርልን ዘንድ ጀግነው የተነሱትን እናበረታታ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁን!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar