November 4, 2013
ይሄይስ አእምሮ
ምን ብዬ ከየት እንደምጀምር አላውቅም፡፡ ሁሉም ነገር ተምታትቶብኛል፡፡ መፈጠሬ ራሱም አስጠልቶኛል፡፡
ግንቦት ሰባት ሆይ! እንደሰውም እንደድርጅትም ልብ ብለህ ስማኝ! በቃ፤ በቃ ማለት በቃ ነው፡፡ ከሰሞነኛ አንድ ኢትዮጵያዊ ውርደት በኋላ አቋሜን ሙሉ በሙሉ ለውጫለሁ፡፡ እናም በስሜት ግንቦት ሰባት ሆኛለሁ፤ በተግባርም እሆናለሁ፡፡ ያበጠው ይፈንዳ፡፡ ማንም በኔ አያገባውም፡፡ ግንቦት ሰባት የማይሆንን ተቋምም ይሁን ግለሰብ አወግዛለሁ – የማወግዘው የኔም የቤተሰቤም ውርደት እንዲቀጥል ፈቃደኛ መሆኑን ከመገንዘብ አኳያ ነው፡፡ በወጡ ሳይወጠወጥ የሥልጣን ጥማቸውን የውይይት መድረክ ላይ ፊጥ የሚያደርጉ ዜጎች ከአሁን በኋላ አንደበት የላቸውም፡፡ መድረክ ላይ መደስኮር ሌላ ነው – እኛ ያለንበትን መከራና ስቃይ ማጤን ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ግንቦት ሰባትን የሚቃወም የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት እንደሆነ አድርጌ እወስዳለሁ፡፡ አሁን የራሴ እንጂ የማንም አፈቀላጤ አይደለሁም፡፡ ብርሃኑ ነጋን በግል መጥላት ይቻላል፡፡ አንዳርጋቸው ጽጌን በግል መጥላት ይቻላል፡፡ ኤፍሬም ማዴቦን በግል ማጥላት ይቻላል፡፡ ሌሎቹንም የድርጅቱን ሰዎች መጥላትና ሲያጠፉም መገሰጽ ይቻላል፡፡
ግንቦት ሰባት አንግቦት የተነሣውን ዓላማ ማውገዝና መጥላት ግን የወያኔ አባል – ደጋፊ አላልኩም – የወያኔው ቀንደኛ አባል መሆንን በጉልህ የሚያመለክት ነው፡፡ እዬዬም ሲዳላ ነው፤ ዕንባም የሚመጣው ሲመች ነው፡፡ ምርጫም አማራጭ ሲኖር ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ቀልድ አብዝተናል፡፡ በተለይ በስደት ዓለም እየተንፈላሰስን የምንኖር ኢትዮጵያውያን በሕዝብ ቁስል እንጨት ብቻ ሣይሆን ጨውና ሚጥሚጣ እየጨመርን በሚመር ቀልድ መዝናናት ቀጥለናል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን የቄሣርን ለቄሣር የእግዜርን ለእግዜር ብለን እንነሳለን፤ አላጋጮችንና አምቧታሪዎችን እናጋልጣለን፡፡ በሕዝብ ስቃይ ደስታን የሚገዙ ሀዘን አምላኪዎችን ዝም ማለት ለተጨማሪ ሰቆቃ ከመዳረግ በስቀር አይጠቅመንምና ዝም አንበላቸው፡፡ የተከፋፈለች መንግሥት አትጸናም፡፡ እውነት ነው፡፡ መከፋፈላችን ከየት ወደየት እንዳመጣን እያየን ነው፡፡ ስለዚህ በረት በጥባጭ ኮርማዎችንና ወይፈኖችን በተቻለ መጠን አውግዘን እንለያቸው፡፡ በሕዝብ ስም የዐዞ ዕንባ ማንባት ሊቀር ይገባዋል፡፡
ማን ነው ግንቦት ሰባትን ማጥላላት የሚቻለው? ግንቦት ሰባት ከሻቢያ ጋር በመሥራቱ አይደለም እንዲህ የተጠመደው? እሰይ! እንኳን ከሻቢያ ጋር የሠራ! እልልልልልልል…..! አሁንም ከሻቢያ ጋር አይደለም ከሰይጣን ከራሱ ጋርም ቢሆን ተደራድሮ ይሥራ! እኔም ባገኘሁት አጋጣሚ ከሰይጣን ጋርም ቢሆን ለመሥራት አሁን ቃል ገባሁ፡፡ እንደኔ በንዴት ሳትንተከተኩ በጥሞና የምለውን ስሙልኝ፡፡
ወያኔ ሁላችንንም ወደጨለማ እያወረደ ወንዱን በወንድ ሴቷን በሴት እስኪደፍር ጠበቅነው፤ የለመኑትን የማይነሣው ወያኔም ይሄውና በጥይት መግደሉን እንደኋላቀርነት ቆጥሮት በቁማችን በሚያሣፍር መሣሪያ ከኋላችን እየገለበ ሊጨርሰን ተያይዟል፡፡ እምናገረው ሃቅና ሃቅ ብቻ ነው፤ የተራ ጉዳይ እንጂ ሁላችንም ተደፍረናል፡፡ በቀደም ዕለት ይህን ዜና ስሰማ በኔ የደረሰ ያህል ነው የተሰማኝም ያለቀስኩትም፡፡ ደግነቱ መጽናናት አለና አሁን መለስ ብሎልኛል እንጂ ወደያውማ ማንም ሊያጽናናኝ አልቻለም ነበር፡፡ ለኔው ነው ያለቀስኩት፤ ለልጆቼ ነው ያለቀስኩት፤ ለሁሉም ምሥኪን ህዝብ ነው ያለቀስኩት፤ ለሀገሬ እዚህ የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረስ ነው ስቅስቅ ብዬ ያለቀስኩት፡፡ ሁላችንም ለፈጣሪ ከልብ እናልቅስ፡፡
ኢሳይያስ አፈወርቂ በሥልጣንና በኤርትራ ሲመጡበት ጭራቅ ሊሆን ይችላል – ግን ዜጎቹን በግብረሶዶም በቁማቸው የሚገድሉለት የደኅንነት አባላትን አሰልጥኖና ኦሬንቴሽን ሰጥቶ በሙሉ ስንቅና ድርጅት አያሰማራም – በጭራሽ፡፡ ኢሳይያስ አፈወርቂ በአስተዳደር ይትበሃሉ ጭራቅ ሊሆን ይችላል – ግን በዘረኝነት ልክፍት ታውሮ የሚገዛውን ሕዝብ እርስ በርስ አያባላም፤ ኤርትራንም እየሸነሸነ ለባዕድ ዓሣማና ጅቦች አይሸጥም፡፡ የኤርትራ መንግሥት ጨካኘ ሊሆን ይችላል ግን የሀገሪቱን ሕዝብ ባህልና ሃይማኖት ደምስሶ በመላዋ ሀገር ሶዶማዊነትንና ሌዝቢያኒዝምን ባቋቋማቸው የሴኪዩሪቲና የአፈና ተቋማቱ አማካይነት በኃይል ድርጊት አያስፋፋም፡፡ ኢሳይያስ የፈለገውን ያህል ጨካኝ ቢሆን ወያኔ እያደረገው እንዳለው ተቃዋሚዎችን እያፈነ መናገር እንኳን የሚዘገንን ድርጊት እንደማይፈጽምባቸው አምናለሁ፡፡ ስለዚህ አሁን ግንቦት ሰባት ያልሆንኩ መቼም አልሆንም፤ አሁን ኢሳይያስ አፈወርቂን ቢያንስ በሰውነቱና በሰብኣዊነቱ ያልወደደኩ መቼም ልወደው አልችልም፡፡ ፈጣሪን በዚህች ቅጽበት የምለምነው ኢሳይያስ ሳያውቀኝና ሳላውቀው እንዳንሞት ነው፡፡ ይህ ግርዶሽ ተገፍፎ ለአንዲት ቀን እንኳን አዋርቼው የልቤ ቢደርስ ምኞቴ ነው፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ከሀገሩ እየወጣ እየተሰደደ ያለው እንደኔ ግምት ሻጥረኛ የውጪ መንግሥታትና ተባባሪዎቻቸው ኤርትራ ላይ በፈጠሩት ጫና ምክንያት በተፈጠረ የኢኮኖሚ ድህነት እንጂ የኛን የመሰለ በደልና ግፍ በገዛ መንግሥታቸው ተፈጽሞባቸዋል ብዬ አልገምትም፡፡ የኛ ችግር የአምባገነንት ችግር አይደለም፡፡ አምባገነን መንግሥት እኮ አንዳንዴ ለሕዝብ ይጨነቃል፤ ያስባል፡፡ ግፋ ቢል ሥልጣኑን ላለመሻማት ነው መጠንቀቅ የሚኖርብህ፡፡ የወያኔዎች ነገር ከአምባገነንነት በላይ ነው – የምልህ ከገባህ፡፡
ለምለው ሁሉ ምክንያት አለኝ፡፡ ለምን እንዲህ እንደምልም ታውቃላችሁ፡፡ የደላው ሙቅ ያኝካልና ስሜቴ ያልገባው ወይም በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ዜጋ ወይም የወያኔ ደጋፊ የሆነ ሰው ምን ሊለኝ እንደሚችል አውቃለሁ – ለምለው ነገር ሁሉ ሪስኩን ሁሉ እወስዳለሁ፤ ደግሞም የለመድኩት ነው፡፡
ቀደም በሚል አንድ ወቅት ስለወያኔ እሥረኞችንና ከእሥር ተፈቺዎችን አፍ መሸበብ በተመለከተ በጽሑፍ የተናገርኩት ነገር ነበር፡፡ ሰሞኑን ፈጥጦ የወጣው ያ ነው፡፡ የወያኔ እሥረኛ አያያዝ በየትም ሀገር የለም፡፡ የወያኔ ‹ብላክሜል› በየትም ሀገር ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ አሁን በገሃድ እንዲህ አይነገር እንጂ ወያኔዎች ተስፋ ከቆረጡበት በተለይ ከግንቦት ሰባት 97 ወዲህ ሰዎችን ከተቃውሞ ጎራ ለማስወጣትና እንዳይገቡም ለማድረግ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ በፊትና አሁንም በጥቅም ለመያዝ ይሞክራሉ፡፡ በብዙ መልኩ እሱ እየተሳካላቸው ይመስላል፡፡ የአሁነኛው ግን ከበድ ያለና ኅሊናችን ችሎ የሚሸከመው አይደለም፡፡
ይህ ተግባራቸው ከዕብድም አይጠበቅም፡፡ መግደል ያባት ነው፡፡ መግረፍ ያባት ነው፡፡ በወጉ ማሰቃየት ወግ ነው፡፡ ወፌላላና በዘይት መጠበስ፣ ጥፍር በጉጠት መገንጠል ከደርግ ጀምሮ የለመድነው ነው፡፡ የአሁኑ ግን የመጨረሻቸው ይመስላል የተለዬ ሆኗል፡፡ እባካችሁን ወደሰማይ እንጩህ፤ እባካችሁን ሁላችን ግንቦት ሰባትን በቻልነው ተቀላቅለን ወይም ሌላ መስከረም ሁለትም ይሁን ሐምሌ 19 የትግል ግምባር መሥርተን ይህን የብዔል ዘቡል መንግሥት እንጣል፡፡ ከዚህ በላይ ምን ያድርጉን? እነሽመልስ ማዘንጊያ እጮኞቻችንን እየቀሙ ነበር የሚያገቡብን፤ እነመላኩ ተፈራ ሚስቶቻችንን እየቀሙ ነበር የሚያገቡብን፣ እነመንግሥቱ ኃይለ ማርያም በሣንጃ ነበር መቀመጫችንን እየወጉ የሚገድሉን፡፡ የአሁኑ እኮ በታሪካችን እጅግ የተለዬ ነው፡፡ እግዚኦ በሉ፤ ወዮ ለመጪው ጊዜ! ዕልቂት ከፊታችን ይታየኛል! ሰማይ ተከፍቶ የመርገምት እሳት በሀገራችን ሲዘንብ ይታየኛል፡፡ አቤት እንበል፡፡
ወያኔዎች የሚፈጽሙት ግፍ የተለዬ ነው፡፡ እነ እንትና ከእሥር ከተፈታ(ች) በኋላ በስማም እንደተባለበት ሰይጣን እንዲህ ጭጭ ያሉበትን ምክንያት ለመረዳት በግድ መታሠር አያስፈልግም፡፡ ሁሉን እናውቀዋለን፡፡ ይህን መንግሥት ለመጣልና ቢያንስ በሰውነትህ የሚያምን የራስህ የሆነ ጨቋኝ መንግሥት ለማምጣት ደግሞ ሁሉም መታገል ይኖርበታል፡፡ ዴሞክራሲ ለኔ የቧልታይ ድንቃይ ኤዞፓዊ ድራማ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቴ ውዬ በደህንነት ጋንጎች ተጠልፌ አይሆኑ ሆኜ ራሴን ሆስፒታል የማገኝባት ሀገር ካለችኝ ጥንቅር ትበል ወይም ሀገር እንዲኖረኝ መታገል ነው የሚኖርብኝ፡፡ ዴሞክራሲው፣ ምርጫው፣ ቢሮክራሲው ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ አስተዳደራዊ በደሉ፣ ቅጥ ያጣው ዘረኝነቱ፣ ፍትህ ማጣቱ… ይሄ ይሄ ቀልድ ነው አሁን፡፡ ስለነዚህ አንስቶ ለመወያየት መጀመሪያ ሰው መሆኔ መታወቅ አለበት፡፡ ሰው መሆኔ ብቻም አይደለም፡፡ እንስሳ መሆኔም መታወቅ አለበት፡፡ አሁን ከሰውም፣ ከእንስሳም፣ ከግዑዝም ነገሮች በታች ነኝ፡፡ እኔ በኢትዮጵያ ምድር ምንድነኝ? ሰው እንዳልሆንኩ እኔም አውቃለሁ – እናስ ምን ነኝ ልበል? የፋሲካው በግ በገናው በግ እንደሳቀ ጀምበር ትጥለቅብን ወገኖቼ? የት ሄደ ያ ኢትዮጵያዊ ወኔና ጀግንነት? ወይንስ የሚወራው ሁሉ የውሸት ነበር ማለት ነው? ምንድነው የምንሰማውና የምናየው ሁሉ?
አንድ ወንድ ጅብ የሚጠላውን ወይም በትግል ያሸነፈውን ሌላ ወንድ ጅብ አስገድዶ ሲደፍረው በየትም ሀገር አልታየም፡፡ አንድ አንበሣ ያሸነፈውን አንበሣ በኃይል ጥሎ ወይም ማስከሪያ ነገር በግዳጅ ግቶ ወንዱን ወንዱ ሲገናኘው በየትም ሀገር ታሪክ አልተመዘገበም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በወያኔ እየተካሄደ ያለው ጉድ በቀጥታ ምፅዓትን የሚጣራ ነው፡፡ በዘመነ ሎጥ እንዲህ ተደርጎ ነበር ይባላል፡፡ ቅጣቱም የማይችሉት ሆነና ከሰማይ የድኝ እሳት ዘነበ፡፡ የኢትዮጵያም ነገር ምን አለ በሉኝ እንደዚያው ነው፡፡ በቀልድ የምንሰማው የ“ወጊርናዮም፣ ነፊእናዮም” መፈክር በይፋ እውን ሆኖ ሲታይ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት መፍለቂያነት ከምትታወቀው ሀገራችን ትግራይ የመጡ ጉዶች ወይም ሥልጡን ጋሻጃግሬዎቻቸው ይህን የመሰለ ወንጀል በበሉበትና በጠጡበት በበለጸጉበትም ሕዝብ ላይ ይፈጽማሉ ብሎ ማንም ሊገምት አይችልም፡፡ ይህን ያደረጉ ዜጎች ከምን ዘረመል ወይም ጄኔቲክ ማቴሪያል እንደተሠሩ ለማወቅ እንድንችል ከነጻነት በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለው ዲኤንኤያቸው እንዲመረመር ማስታወሻ ይያዝልኝ፡፡ የመለስና የአዜብም፡፡ ሰው የፈለገውን ያህል ከሰውነት ተራ ቢወጣ እንዴት እስከዚህ በወገኑ ላይ ይጨክናል???
ወያኔዎች እንዲህ የሚያደርጉት ሴት አጥተው አይደለም – በያይነቱ ሞልቷቸዋል፤ ከትንሽ እስከትልቅ ሁሉም የነሱው ነው፡፡ ወያኔዎች በጥላቻ ስለተሞሉ ብቻም አይደለም እንዲህ የሚያደርጉት፤ የሚጠሉትን ሰው ያስሯል ይገርፏል እንዲያም ሲል ይገድሏል እንጂ በወሲብ አስገድዶ መድፈር የሚያስቡት አይደለም – ወላድ በድባብ ትሂድ እንጂ ምን ጠፋና? ወያኔዎች ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት አላቸው፡፡ መገመት እችላለሁ፤
እንድም የሴቴኒዝም እምነት ተከታዮች ሊሆኑ ይችሉና አባታቸውን ሰይጣንን ለማስደሰት ነው፡፡ ሴቴኒዝም በሁለት ይከፈላል – ደግ ሰይጣን፤ ክፉ ሰይጣን፡፡ ወደዝርዝር አንገባም፡፡ እነዚህኞቹ የመጥፎው ሰይጣን፣ የአውሬው ተከታዮች መሆን አለባቸው፡፡
አንድም ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ ተስፋ ሲቆርጡ ደግሞ ለሥልጣናቸውና ለሀብታቸው ምንጭ አስጊ ነው ያሉትን ወገን ቅስም መስበር አለባቸው፡፡ ያን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ ሌሎች ተቀባይነት ያላቸውን የማሰቃያ መንገዶች ሁሉ ተጠቅመው አልሠራ ሲሏቸው ጊዜ ወደዚህኛው ተስፋ የቆረጡ ተስፋ አስቆራጮች ወደሚጠቀሙባቸው የዘቀጠ ሥልት ወርደዋል ማለት ነው፡፡ ይህም ሞታቸውን ያፋጥነው እንደሆነ እንጂ በዘለቄታዊ እስትራቴጂነት አያዋጣቸውም ብቻ ሣይሆን የካርማ መዝገባቸውን ይበልጥ በወንጀልና በኃጢኣት እያጨቀዬ ለበለጠ ሥጋዊና መንፈሳዊ መከራ ይዳርጋቸዋል፡፡ እርግጥ ነው – አሁን ኀረሊናቸው በጥቅምና በክፋት ስለታወረ የሚሠሩትን አያውቁትምና ይህ የምለው ነገር የኋላ ዳፋ አይሰማቸውም፡፡ በስቶክሆልም ሲንድረምነት አይያዝብኝ እንጂ ለነሱም እኮ ማዘን አለብን – ምክንያቱም ያን ወንጀል ሠርተው በሰላም አይተኙም፤ይጨነቃሉ፣ ይጠበባሉ፤ ለመርሳትም በመጠጥ ውስጥ ይደበቃሉ - በጠጡ ቁጥር ደግሞ የወንጀል ሱሳቸው እየገፋፋቸው ሌላ ወንጀል ለመሥራት የአለቆቻቸውን ትዕዛዝ አቆብቁበው ይጠባበቃሉ፡፡ አሣራችን ብዙ መንገዳችን ረግረጋማ ነው፡፡ ተያይዘን ከመጥፋታችን በፊት ቀም ብለን እናስብ ጎበዝ፡፡
አንድም በማሠርና በመግደል ብቻ ዓላማቸውን ማሳካት ስላቃታቸው ይህን የመሰለ ዘግናኝ ድርጊት በመንግሥት ቀጥተኛ ስፖንሰርነት ማካሄዳቸው ሌሎች የነጻነት ታጋዮችን በአበስገበርኩ ከትግሉ ሜዳ ለማሰወጣት ነው፡፡ ይህን የሚሰማ ሰው “እንዴ! ምን አዳረቀኝ? ለምንስ እዋረዳለሁ? አፌን በዳቦ ብዬ ያለኝን እየበላሁ ብኖር ምን እሆናለሁ?” በሚል በፍርሀት ተሸብቦ እየተንቀጠቀጠ እንዲኖር ወይም እንዲሰደድ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ለጊዜው ስኬታማ የሆኑ ይመስላሉ፡፡
ይሄ ሰላማዊ የሚሉት ትግል ደግሞ ለኔ ላግጣ ነው፡፡ በሀገር እንደማላገጥ እወስደዋለሁ፡፡ ስንተዋወቅ አንተናነቅ ወገኖቼ፡፡ ወያኔን በሰላማዊ ትግል አንበረክካለሁ ብሎ መቃዠት የወያኔን ባሕርይ ካለመረዳት የሚመነጭ ጅልነት ነው – አዎ ንፍልል ያለ ጅልነት፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ለ27 ዓመታት ታስሮ በትግሉ ግለት አፓርታይድ እንዲገረሰስ አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ አደራችሁን ጥረቱን ለማጣጣል አይደለም – አንዷለም አራጌ ግን 27 አይደለም 273 (27 cubed) ለ19683 ዓመታት ቢታሠር ኢትዮጵያ ከወያኔ አገዛዝ ነጻ አትወጣም፡፡ የሚያዋጣው ጉልበትና ጉልበት ብቻ ነው፡፡ ከዝንጀሮ ተፈጥሮ ያልወጣን የወያኔ ቡድን እነጋንዲ እንዳደረጉት በሰላማዊ ትግል የወያኔን መንጋ ከአራት ኪሎ አባርሬ ሀገሬን እይዛለሁ ብሎ መመኘት ቅዠት እንጂ ቅጥ ያለው ህልም እንኳን ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ሰላማዊ ትግልን አንጋጥጣችሁ የምትጠብቁ ዜጎች ተስፋችሁን ቁረጡ፤ ይልቁን የወያኔ መሣሪያ አትሁኑ፡፡
ስለዚህ ግንቦት ሰባት የጀመረው መንገድ የጽደቅ መንገድ እንደሆነ በበኩሌ ዐውጃለሁ፡፡ ይህን መንገድ የሚነቅፍ የወያኔው ዘረኛ መንግሥት ተባባሪ ነውና እግዚአብሔር ከወያኔዎቹ ጋር ደርቦ ተገቢ ዋጋውን ይክፈለው – ከእንግዲህ በሕዝብ መቀለድ መቅረት አለበት – እያለቅን ነው፤ የተመቸው የሚመስለው እንኳ የሰላም እጦት እንደነቀዝ ቦርቡሮ ፈጅቶት አካሉ ብቻ ነው ወንከር ወንከር ሲል እምታዩት – ሰው የለም፤ በቁም አልቀናል ወገኖቼ – በላህ አልበላህ፣ ጠጣህ አልጠጣህ ሂሳብ ውስጥ አይገባም ፤ ባጭሩ በቁም ሞተናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ችግራችን መብላት መጠጣት አይደለም – እሱ የቆዬ ችግራችን ነው – ተላምደነውማል፡፡ የአሁኑ ችግራችን የትኛው ወይም የትኞቹ ደህንነቶች መንገድ ላይ አስቁመው ወደጨለማ ቦታ በመውሰድ ይደፍሩን ይሆን የሚለው ነው፡፡ የትኞቹ ደህንነቶች አፍነው ወስደው እነሱው የገደሉት የሰው በድን ሥጋ ራሳችን እየቆረጥን እንድንበላ ያስገድዱን ይሆን የሚለው ነው፡፡ ከዚህ ደግሞ በጥይት መግደል የበለጠ ግርማ ሞገሣማ ነው፡፡ እነሱ ግን በዚህ አይገድሉንም – አዋርደው መግደልን ነው የሚመርጡት፡፡ በአናታቸው ላይ ግን ከፍለው የማይጨርሱት ዕዳ እየቆለሉ ናቸው – ይህን ሁላቸውም ይረዱት፡፡
ኢትዮጵያ ወደዚህ ደረጃ መድረሷ ግና ኃጢኣቷ ምን ቢበረታ ይሆን ? በዚህ መልክ ከመኖር በታች ሆነን እያለን ታዲያ ዓለመኛ ምንትስ ራስ ላይ እዘሉኝ ይላል እንዲሉ በሥልጣን ሽኩቻ የቺንዋ አቼቤ መጽሐፍ ዓይነቶቹ “men of the people” በእኔ እቀድም እኔ እቀድም የታሪክና የሥልጣን ሽሚያ ባልተገኘ መንበር ሲወራከቡ ይገኙልናል፡፡ መረገም ነው፡፡ ትልቅና አመክሮ የሌለው መረገም፡፡
ጠብ ያላችሁ ታርቃችሁ፣ ሰላም ያጣችሁ ሰላም አውርዳችሁ፣ በከንቱና በግል ቂም በቀል የታወራችሁ ለተዋረደውና ለተናቀው ሕዝብ ስትሉ ያንን ጥላችሁ … ተባብራችሁ ካልደረሳችሁልን በውነቱ ዘር አይውጣላችሁ፡፡ መጥፎ ባሕርያችሁን አርቃችሁ(2)፣ ሆዳችሁን ሰብስባችሁ፣ የተምቦረቀቀ ፍላጎታችሁን አጥብባችሁ፣ ዐመላችሁን አስተካክላችሁ፣ ልዩነታችሁን አጥብባችሁ በመለስተኛ ፕሮግራሞቻችሁ ተባብራችሁ ካልመጣችሁልን እኛን እየፈጀ ያለው እሳት በያላችሁበት ይፍጃችሁ፡፡ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ ብላችሁ ዛሬ በዚህ ጭንቃችን ወቅት ያልመጣችሁ የነጻነት ፋኖዎች መቼም ልትመጡልን እንደማትቸሉ የዜግነት መብቴን በመጠቀም ላረዳችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ልብ በሉ – ይህ ጊዜ ያልፋል፡፡ የማያልፈው ግን ትዝብቱና የምታሣርፉብን ጠባሳ ናቸው፡፡ ያኔ እንተያያለን! ያ ቀን ደግሞ የማይመጣ እንዳይመስላችሁ፡፡ የዮዲት ጉዲትን፣ የግራኝ አህመድንና የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ጉግማንጉግ ዘመናት ጠቅልሎ ወደታሪክ መዝገብነት የለወጠ የኢትዮጵያ አምላክ ይህንንም ዘመን አይሸበልለውም ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው፡፡
ከአሁን በኋላ የምናገረው ነገር ባይኖረኝ እመርጣለሁ፡፡ ወሬን ቢያወሩት ፋይዳ የለውም፡፡ ወንድ የሆነ ሰው በአድራሻዬ የክተት ጥሪ ያሰማኝ፤ ወደየትም እሄዳለሁ፡፡ ሞቼ መኖር ሰልችቶኛል በውነት፡፡ የሰሞኑ ጉዳይ አእምሮየን ነክቶታል፡፡ ሄለን የተባለች ሴት ልጅ በዘሀበሻ የጻፈችውን ማንበቤ አሁን ትዝ አለኝ፤ እግዜር ይሽጥሽ ልበልሽ በዚህ አጋጣሚ፡፡
ኤርትራ፡- ውድ የኤርትራ ልጆች! ይህን የኢትዮጵያ ውርደት እየሰማችሁ ነው፡፡ ሀገሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር ስለሆነች ከአሁን በፊትም በተደጋጋሚ ከሞት እንዳስነሳት ሁሉ ዛሬና አሁንም ከወደቀችበት እንደሚያነሣት የታመነ ነው፡፡ እናንተም ለዚህ ውድቀቷ ታላቅ አስተዋፅዖ እንደነበራችሁ ማንም ደብቆ ሊያስቀረው የማይቻለው እውነት ነው፡፡ አሁን ግን በብዙ መንገድ ከወያኔ ይልቅ እናንተ የተሻላችሁ ሆናችሁ ተገኝታችኋል፡፡ በማን መሥፈሪያ የሚለው ለጊዜው አያነጋግርም፡፡ ነገር ግን ቢያንስ የኤርትራ ችግር የኢኮኖሚ እንጂ እንደዚህ በጠራራ ፀሐይ ዜጎቹን ለአስከፊ ውርደት የሚዳርግ የመንግሥት መዋቅር በኤርትራ መሬት አለመኖሩ ብቻ ለነጻነት ትግል መደላድልነት ያስመርጣችኋል፡፡ እናንተም ከአሁን በፊት ላደረሳችሁት ጥፋት ሕዝብን የምትክሱበትና ኢትዮጵያን በጋራ እያለማን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በጋራ የምንጠቀምበት ዕድል ፊት ለፊታችን ይገኛል፤ ይህን ዕድል ሁለታችንም ብንጠቀምበት ከአፍሪካ እጅግ የበለፀገች ሀገር ባለቤቶች መሆን እንችላለን፡፡
ተመልከቱ ኤርትራዎች! በደርግ ዘመን ከወያኔም ከእናንተም ጋር በተካሄደ ጦርነት ከ40 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጦርነቱ ሰበብ እንደወደመ ሰምቻለሁ፤ ከዚህ በበለጠ ደግሞ የአፍሪካን ቀንድ ቢያስተባብሩ ሌላ ሲንጋፖርንና ማሌዥያን ሊፈጥሩ ይችሉ የነበሩ የአንዲት እናት ልጆች በከንቱ መስዋዕት ሆኑ፤ ከዚያም ወዲህ በጦርነትና በሙስና የሀገር ሀብት በአካፋና በላይዳ እየተዛቀ የጥቂቶች መፈንጪያ ሆነ፤ አሁንም የሀገር አንጡራ ሀብት እየተመዘበረ ለወያኔዎችና አሽከሮቻቸው የግል ብልጽግና እየዋለ ነው፡፡ በማይረባ ግጭትና መሠረት በሌለው ጥላቻ ምክንያት የተቀሰቀሱ ጠቦችን ተከትሎ ለግምት የሚያዳግት ሀብትና ንብረት ወደመ፤ ሕዝብም አለቀ – ታዲያ አሁን የመቆጨት ጊዜ ሊኖረን አይገባምን? ማን ተጠቀመ? ማንስ ተጎዳ? …
ሰው ሟች ነው፡፡ ሀገራት ግን አይሞቱም፡፡ ሕዝብም እንዲሁ ቢለፋ ቢሰቃይም እየተተካካ ኅያው እንደሆነ በዘላለማዊነት ይኖራል፡፡ አንድ ወቅት በሆነ ታሪካዊ ሰበብ የተለያየ ሕዝብ በሆነ ሌላ ታሪካዊ አጋጣሚና ሰበብ እንደገና ተገናኝቶ የጋራ ኑባሬውን የሚያድስበት ሁኔታ አለ – የዓለማችን ታሪክም ይህን እውነት አስረግጦ የሚያስረዳባቸው አብነቶችን መዝግቦ ይዟል፡፡ ሰው ሆኖ መሳሳት አለ – በዚህም በዚያም፡፡ ስህተትን ለማረም ፈጣሪ ጊዜና ዕድል ሲሰጥ ያን መጠቀም ደግሞ የብልሆች ድርሻ ነው፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወርቃማ ዕድል እፊታቸው ተቀምጣ እንቁልልጭ እያለቻቸው እንደሆነ ያህል ይሰማኛል – ሞታቸው እውን እንዲሆን የሚጥሩ ኃይላት መኖራቸው እርግጥ እስከሆነ ድረስ ላለመሞት ቢንፈራገጡ መለኮታዊም ምድራዊም ቡራኬና ቅድስና የሚያገኙ ይመስለኛል፡፡ የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባየ ነው መባሉ ሊለወጥ ይገባል፡፡ የተዘጉና ጨለማ የሚመስሉ ቤቶች ሲከፈቱ ሕይወትን የሚያለመልም ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሰማያዊ ወምድራዊ መና ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት ይገባል – ከጽልመታዊና አሉታዊ አስተሳሰብ ርቀን ደግ ደጉን ካሰብንና ከተመኘን ይሆንልናል – ጥሩ ተመኝ ጥሩ እንድታገኝ አይደል የሚባል? እስኪ ያልሞከርነውን እንሞክረው – ቢያንስ እንደማያከስረን በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ እዚህ ላይ ብዙ መናገር አልችልም – አልፈልግምም፡፡ … ስድብ ሰልችቶኛልና ማንም ስድብ እንዳይሰድልኝ አደራ፡፡ ትክክለኛና የሚያስተምር ሃሳብ ግን በደስታ እቀበላለሁ፡-yiheyisaemro@gmail.com
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar