onsdag 18. september 2013

መነሻ ገጽ - ፓለቲካ - ‹‹ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረች አገር ነች›› ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

ርዕስተ
ዋና ዜና
15 SEPTEMBER 2013 ተጻፈ በ የማነ ናግሽ
‹‹ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረች አገር ነች››
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
-ኤርትራ በኢትዮጵያ ቅኝ ተገዝታ አታውቅም ይላሉ
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የዘመን መለወጫን በዓል ምክንያት በማድረግ ሰሞኑን በርከት ካሉ
የመንግሥት ጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ አካሂደዋል፡፡
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በቀጥታ በኤርትራ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈው ቃለ ምልልስ፣ ፕሬዚዳንቱ በአገሪቱ
ውስጥ ስላሉ ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ያብራሩ ሲሆን፣ የአካባቢውን
ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በዚህ ሰፊ ቃለ ምልልሳቸው ስለአገሪቱ የግብርና ልማት፣ ስለብሔራዊ አገልግሎት፣ የሕዝባዊ
ሠራዊት አስፈላጊነትና ግንባታ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ስላለው የድንበር ውዝግብ፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታትድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ስለተጣለባቸው ማዕቀብ ከጋዜጠኞቹ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ
ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ቃለ ምልልሳቸው አስገራሚ የሚባሉ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረች አገር ነች››
በዚሁ ቃለ ምልልስ የመንግሥት ጋዜጠኞች ፈራ ተባ እያሉ አንዳንዴም እየተሸማቀቁ ሐሳባቸውን ሳይጨርሱ
እያቆሙ ነበር ጥያቄያቸውን ለአቶ ኢሳያስ የሚያቀርቡላቸው፡፡ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተላለፈው ሰፊ ቃለ
ምልልስ፣ የመጨረሻው ክፍሉ የተጠናቀቀው የኤርትራ ውጭ ግንኙነት፣ የኢትዮ ኤርትራና የኤርትራና የጂቡቲ
የድንበር ውዝግቦች፣ እንዲሁም የአካባቢውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በመዳሰስ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከጋዜጠኞቹ
ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ከሰጡዋቸው ምላሾች አንዳንዳቹ የሚያስገርሙ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት አሁን
በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ የኤርትራ ተቃዋሚዎችና
ምሁራን ኢትዮጵያን ‹‹የጥቁር ቅኝ ገዥ›› አድርገው ሲመለከቱ ነበሩ፡፡ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው፣ ‹‹ኤርትራ
በኢትዮጵያ ተገዛች›› የሚባለው ዝም ብሎ ተደጋግሞ በመወራቱ እንደ እውነት መወሰዱን ይናገራሉ፡፡
‹‹ወያኔዎች እንዲኮሩ አድርጓቸዋል፤›› በማለት፡፡
‹‹ያው ለጂቡቲና ለሌሎች ሴራዎች ብዙም የማወራው አዲስ ነገር የለኝም፤›› ሲሉ ንግግራቸውን ጀምረው፣
‹‹ዋናው ነገር ብዙም ጊዜ የምለው ‘እነዚህ እነማን ናቸው?’ የሚለውን ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ኤርትራ
የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነበረች ተብሎ ተደጋግሞ ሲወራ እሰማለሁ፡፡ ውሸት ነው፡፡ ኤርትራ በኢትዮጵያ በቀጥታ
ተገዝታ አታውቅም፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ መቼ ነው የተፈጠረችው? ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት
መጠናቀቅ በኋላ የተፈጠረች አገር ነች፡፡ ሰው ግን የፈለገውን ማውራት ይችላል፤›› ብለዋል፡፡
ቀጥለውም ሰው የፈለገውን ቢያወራም እሳቸው የሚረዱትና ትክክለኛው ነው ያሉት፣ ‹‹ኢትዮጵያ በሁለተኛው
የዓለም ጦርነት አሸናፊዎች ለራሳቸው ጥቅም መሣሪያ እንድትሆን ሆን ተብሎ የተፈጠረች አገር ነች፡፡ ስለዚህ
ኤርትራን የእነሱ ወኪል ሆና ገዝታ ይሆናል እንጂ፣ ራሷ በቀጥታ ኤርትራን የገዛችበት አጋጣሚ አለ ማለት
አይቻልም፤›› በማለት፣ ከዚህ በፊት ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል የሆነችበት ታሪክ እንዳልነበረ በኤርትራ ሚዲያ
የሚነገረውን የተዛባ ወሬ አንድ ዕርምጃ ከፍ አድርገውታል፡፡
‹‹ሕዝባዊ ሠራዊት ለኤርትራ ሕልውና ብቸኛ ዶክትሪን ነው››
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል በጋዘጠኞች የቀረቡላቸው ‹‹ብሔራዊ ግዳጅ›› እና
‹‹የአገሪቱ ሕዝባዊ ሠራዊት›› ግንባታን የተመለከቱ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡
‹‹የዚህች አገር የዶክትሪን መሠረት ሕዝባዊ ሠራዊት ነው፤›› ሲሉ በጀመሩት ንግግራቸው፣ ‹‹አይ ከዚህ ውጪ
ሌላ መስፈርት አለ የሚል ካለ ይምጣ፤›› በማለት ቀጥለዋል፡፡ ኤርትራ እንድትፈጠርና እዚህ ደረጃ እንድትደርስ
ያደረጋት ብቸኛ ኃይል እሱ እንደሆነ በመግለጽ፡፡ ‹‹ሕዝብ ያልተሠለፈበት ምንም ዓይነት መስመር አይሳካም፤››
የሚለው በኢሕአዴግ ባሥልጣናት ተደጋግሞ የሚገለጸውን ደግመው የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ምናልባትም
በቅርቡ ወደ ሥራ የተገባበትን የአንድ ለአምስት ‹‹የልማት ሠራዊት›› አደረጃጀት ተመሳሳይ ይዘት ያለው
የሚመስል የልማት ሕዝባዊ ሠራዊት የማደራጀት ዓላማ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን አሁን ዘንግተናቸው
የቆዩ ሕዝባዊ አደረጃጀቶች አሉ፤›› ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ ሕዝባዊ ሠራዊት ለጦርነት ብቻ እንዳልሆነና በልማት ላይ
በማሳተፍ ተግባራዊ ለማድረግ ሕዝባዊ ኮንፈረንስ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
ኤርትራ በተለያዩ ጊዜያት ስትወረር ያዳናት ይኼው ሠራዊት መሆኑን ገልጸው፣ እንዲህ ዓይነት የልማት ሠራዊት
መፍጠርና መገንባት ደግሞ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም ይላሉ፡፡ ለዚህም ኤርትራ ከማንም የምታማረው ሳይሆን፣
ከራስዋ የታሪክ ተሞክሮ ያገኘችው መሆኑን ጠቅሰው እስራኤልን ግን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡
‹‹ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ትርጉም እንዳይሰጠው እንጂ፣ በዓለም ኃያል ሠራዊት ያላት አገር እስራኤል ናት፤››
በማለት፣ በተጠንቀቅ የቆመ ቁጥሩ ወደ 200 ሺሕ የሚጠጋ ጦር ያለ ቢሆንም፣ ኤርትራ 500 ሺሕ ሕዝባዊሠራዊት አላት ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ 700 ሺሕ ሕዝባዊ ሠራዊት እንዳላት በመጥቀስ፣ አምስት መቶ ሺሕ ለአገር
ልማት የተሠለፈ መሆኑን በማስታወስ፣ ሲፈለግም ወደ ጦርነት መግባት የሚችል ነው ብለዋል፡፡ በዚሁ አገራዊ
አገልግሎት ምክንያት አንዳንድ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችል የሰው ኃይል የላቸውም
በማለት ከጋዜጠኞች መካከል አንዱ ጠያቂ ያስቆጣቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ‹‹በስሚ ስሚ አይወራም፤ እንዲህ
የሚባል ተቋም በዚህ ምክንያት ሥራው ተስተጓጉሏል ብለህ ጥቀስልኝ፤›› ሲሉ አፍጥጠው ጋዜጠኛውን
ሲያስጨንቁት ተስተውሏል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከፍተኛ ትችት የቀረበበት
የኤርትራ መንግሥት የብሔራዊ አገልግሎት ግዴታ አሁንም የኤርትራ ሕልውና መሠረት መሆኑን እንደሚያምን
ጠቅሰው፣ በዚህ ላይ የሚነሱ ማናቸውም ቅሬታዎች የጠላት ወሬ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዛሬም የእያንዳንዱ
ዜጋ ግዴታ ነው፤›› በማለት፡፡
‹‹የፀጥታው ምክር ቤት እርቃኑን ቀርቷል››
ከስድስት ዓመታት በፊት በሶማሊያ የተቋቋመው የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት በዓለም አቀፍ
ማኅበረሰብ ዕውቅና የነበረውን ደካማውን የአገሪቱን የሽግግር መንግሥትን ለመበተን ተቃርቦ ነበር፡፡ ኅብረቱ
በወቅቱ ሶማሊያን በተለይም ደቡባዊ ክፍሉን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም
ላይ ጅሃድ ማወጁ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በሶማሊያ ሽግግር መንግሥት ጥሪ መሠረት የኢትዮጵያ
መንግሥት ለሁለት ዓመት የቆየ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለመፈጸም ተገዶ ነበር፡፡
ይኼው በዳሂር አዌይስ ይመራ የነበረው ቡድን ከአልቃይዳ ጋር ቀጥተኛ ትስስር የነበረው ሲሆን፣ በተለይ
ከመካከለኛው ምሥራቅ ለሚያገኘው ዕርዳታ መተላለፊያ ሆና የምታገለግለው ኤርትራ ነበረች፡፡ ከዚህም
በተጨማሪ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ የኤርትራ ወታደሮችንና ሰላዮችን በቁጥጥር ሥር አውለው ነበር፡፡
በመሆኑም ይህንን ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ዓላማ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቡድን ቀጥተኛ ፖለቲካዊና ወታራዊ
ሥልጠና የሚያገኘው ከኤርትራ እንደነበር ተመድ በወቅቱ ባሰማራው ተቆጣጣሪ ቡድን አረጋግጧል፡፡ በዚህም
መሠረት በጦር መሣርያ ዝውውር ላይ የመጀመሪያውን ማዕቀብ ጥሎ ነበር፡፡
የሶማሊያ የወቅቱ ቀውስ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እልባት ሳያገኝ ለቆየው የድንበር ግጭት የውክልና
ጦርነት ተደርጎ ነበር በብዙዎች የቀረበው፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስም በወቅቱ በአገራቸው ላይ ከተጣለው ማዕቀብ
ጀርባ የኢትዮጵያና የአሜሪካ መንግሥታት እጅ እንዳለበት ተናግረው ነበር፡፡ ኅብረቱ በኢትዮጵያ ወታደሮች
በመበታተኑ ምክንያት፣ አልሸባብ የተባለው ቡድን አንሰራርቶ አካባቢውን ያተራምስ ጀመር፡፡ አልሸባብም ቀጥተኛ
ድጋፍ ያገኝ የነበረው ከኤርትራ መሆኑን ተመድ በተመሳሳይ መንገድ አረጋግጦ ነበር፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል
የተጣለው ማዕቀብ ተጠናክሮ በአንዳንድ የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ዝውውር ላይና ከዳያስፖራ
በሚገኘው ገቢም ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ተጥሎ ነበር፡፡
ተመድ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ በሶማሊያ ላይ ባሰማራው ተቆጣጣሪ ቡድን አማካይነት የኤርትራ ጣልቃ ገብነት
እንዳልቆመ አረጋግጧል፡፡ በዚሁ አምስት መቶ ገጾች ባሉት ሪፖርት ውስጥ ኤርትራን በተመለከተ ብዙ ጉዳዮችን
አካቷል፡፡ በአሜሪካ ሐሳብ አቅራቢነትም የፀጥታው ምክር ቤት ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል አቅዶ ነበር፡፡ ሆኖም
በሪፖርቱ ውስጥ የቻይናና የሩሲያ ስም መልካም ባልሆነ መንገድ ተጠቅሷል በሚል ማዕቀቡ እስካሁን
አልተጣለም፡፡
በዚህም የኤርትራው ፕሬዚዳንት የልብ ልብ የተሰማቸው ይመስላል፡፡ ‹‹ቀድሞም ቢሆን በእኛ ላይ የተጣለው
ማዕቀብ ሕገወጥ ነበር፡፡ ውሳኔውን የምንቀበለው አይደለም፡፡ የማንቀበለው ግን በእኛ ላይ ስለተጣለ ሳይሆን
መሠረት የሌለው ፈጠራ ስለሆነ ነው፡፡ አሁን በቅርቡ የተዘጋጀው ሰነድም ደግሞ በጣም የሚያስቅ ነው፤›› ሲሉ
በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹የፀጥታው ምክር ቤት እርቃኑን ቀርቷል›› በማለት በተደጋጋሚ የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ሕግና ፍትሕ
የሚቀበርበት ከፀጥታው ምክር ቤት የበለጠ ሌላ ቦታ አይኖርም ብለዋል፡፡ የእነዚህ ተደጋጋሚ ማዕቀቦች ዋና
ዓላማ ምን እንደሆነ ማስታወስ አያስፈልግም የሚሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ሦስት መሠረታዊ ያሉዋቸውን ጉዳዮች
ግን አውግተዋል፡፡ የመጀመሪያው የኤርትራ እሴቶች ያሉዋቸውን ወጣቶችን እንዲበተኑ ማድረግ፣ የኤርትራን
ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማደናቀፍና ውጭ ከሚገኙ ዜጎች የሚገኘውን ገቢ መግታት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡አብዛኛዎቹ የኤርትራ ወጣቶች በ‹‹ብሔራዊ ግዳጅ›› ምክንያት አገር ለቀው በመንግሥታቸው ቀንደኛ ጠላት
ተደርጋ ወደምትቆጠረው ኢትዮጵያና ወደጎረቤት አገሮች እየኮበለሉ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የዚህ መንስዔው
በተመድ የተጣለው ማዕቀብ እንደሆነ ቢናገሩም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ግን ሁኔታው እውነት መሆኑን በግልጽ
አምነዋል፡፡ ‹‹ማዕቀቡ የኤርትራ ወጣቶችን በመበታተን ዓላማው ግቡን መትቶ ይሆናል፡፡ በተለያዩ አገሮች
የተበተኑት የኤርትራ ወጣቶች ግን ሥራ እንዳይሠሩ ተደርጎ ተበትነው ቀርተው ይሆናል፡፡ አንዳንዶቹ
እንደሚፈልጉት የእነርሱ መሣሪያ ግን አልሆኑም፤›› ይላሉ፡፡
በሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በዲሞክራሲያዊ መብቶች አፈናዎች ምክንያት በዓለም ስሟ በግንባር ቀደምነት
የሚነሳውን ኤርትራን የሚመራው ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ ሥርዓትን የሚቃወሙ የተለያዩ ተቃዋሚዎች
እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ አገራቸውን ጥለው የሚኮበልሉ ወጣቶች ተቃዋሚዎችን ይቀላቀላሉ የሚል
ግምት የነበራቸው ይመስላል፡፡
ለፀጥታው ምክር ቤት በቅርቡ በቀረበው ሪፖርት መሠረት በአገሪቱ ላይ ተጨማሪና ጠንከር ያለ ማዕቀብ ይጣላል
የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም፣ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት
እንዳይፀድቅ አድርገውታል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስም የምክር ቤቱ ገመና ተጋልጧል ያሉበት ምክንያት ይኼው
ነው፡፡ አንዳንዳቹ አባል አገሮች ቀድሞም ባደረጉት ነገር እንደተፀፀቱ በመግለጽ፡፡ በፕሬዚዳንቱ እምነት የአሁኑ
ዓላማ ማዕቀብ ለመጣል አልነበረም፡፡ ‹‹ዋናው ዓላማው ቀድሞ የተጣለው ማዕቀብ ይነሳ የሚል ሐሳብ
እንዳይቀርብ ለመከላከል ነው፤›› ይላሉ፡፡
በአገራቸው ላይ በተጣለው ማዕቀብ የኢትዮጵያ መንግሥት (እሳቸው ወያኔ ገለመሌ እያለ ነው የሚጠሩት) እጅ
እንዳለበት ግልጽ ነው ብለው፣ እዚህ ላይ ብዙም ጊዜ ሳያጠፉ ለማናቸውም ማዕቀቡን ተቋቁሙው በዚሁ ሴራ
ውስጥ ተሳትፈዋል ያሉዋቸው ኃይሎች ዓላማ እንዳይሳካ መንግሥታቸው መሥራቱን ይናገራሉ፡፡
‹‹ዓላማቸው በሕዝቡ ውስጥ መበታተንና ኹከት መፍጠር ነበር፡፡ አንድ ጤነኛ አዕምሮ ላለው ሰው አንድን ሰው
ደጋግሞ መተንኮስ ምን ይሉታል? የፀጥታው ምክር ቤት እርቃኑን ቀርቷል የምለው ለዚህ ነው፤›› ብለዋል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar