September 19, 2013 | Filed underG7 Editorial,Slider Post | Posted by admin
የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በቅርቡ ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ዋነኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊና ዘላቂ ጥቅም ጠላት ወያኔ መሆኑን አስረግጦ ተናግሮ ነበር። ይህንን አባባል አንድ ተቃዋሚ ለተቃውሞ ያህል ወይም ስርዓቱን የሚጠላ አንድ ግለሰብ ስርአቱን ስለሚጠላዉ ብቻ እንደተናገረው አድርጎ አቃልሎ ማየት ትልቅ ስህተት ነው። ወያኔ ከፍጥረቱ ጀምሮ እስከአሁኑ ቅጽበት ድረስ በሀገራችን ላይ የፈጸመውን ደባ በቅጡ ያላዩ ሰዎች ይህ አባባል የተጋነነ ይመስላቸው ይሆናል። ኢትዮጵያ ዛሬም አንደ አገር የቆመችዉ በህዝቦቿ ታላቅነትና እንዲሁም ለታሪካቸው ባሳዩት ክብርና ብርታት ነዉ እንጂ እንደወያኔማ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ ከወደቀ ሰንብቷል።
ኢትዮጵያ የሚለውን ውብና ታሪካዊ የስም ለመጥራት እየተጸየፈ “የሀገራችን ህዝቦች” እያለ ሲጠራን የነበረው የወያኔዉ ሹም የንቀት አጣራር ወያኔዎች ከሀገሪቱ ስም ጋር ሳይቀር የገቡበትን ጠብ ያሳያል። ወያኔ አባቶቻችን ባቆዩልን ዳር ድንደር የሚደራር ብቻ ሳይሆን የአገራችንን መሬት ላብዕዳን እንካችሁ ያለ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ነዉ። በወያኔ እንደባሪያ ፈንግሎ የሚገዛት አገራችን ኢትዮጵያን የታሪክ አጋጣሚ እጁ ላይ ጥሎለት ነዉ እንጂ እሱ እንደሚነግረን ወያኔ ከራሱና ከጉጅሌዎቹ ጥቅም አስበልጦ ኢትዮጵያን አስቧት አያውቅም።
መገነጣጠል ግብ እንዲሆን በህገ መንግስት ደረጃ አንቀጽ ጽፎ ያስቀመጠው ወያኔ እሱ እንደሚለዉ ለብሔረሰቦች መብት አስቦ ሳይሆን ኢትዮጵያ አልዘረፍ ካለችን በትነናት ብንሄድስ ከሚል አላማ መሆኑን ሌናጤን ይገባል። ከምር ለብሄረሰቦች መብት በመቆርቆር ቢሆን ኖሮ ከጠመንጃና ከፍጅት በፊት የብሄረሰቦችን መብትና ነጻነት አክብሮ እራሳቸዉን በራሳቸዉ እንዲያስተዳድሩ ይተዋቸዉ ነበር።።
ወያኔ ኢትዮጵያን የሚፈልጋት ለርሱና ለጋሻ ጃግሬዎቹ የወርቅ እንቁላል የምትጥል ዶሮ ሆና ስላገኛት ብቻ ነው። ሀገሪቱን እያለማሁ፣ እያሳደግኩ ነው የሚለው ዲስኩር ለተራ መደለያ እንኳን የማይሆን ውሸት ለተራበው ህዝብ ምኑም እንዳልሆነ ያውቀዋል።
የሀገሪቱን ለም መሬት በሄክታር ባንድ ፓኮ ሲጋራ ዋጋ የሚቸረችረው ወያኔ እነዚህ ባእዳን በጎን የሚሰጡትን የሀገራችንን መሬት ዋጋ ኪሱ መክተቱን አረጋግጦ ነው። ዛሬ በመላ ሀገሪቱ የሚነዛው የኬሚካል ማዳበሪያ በጥቂት አመታት ውስጥ የሀገሪቱን አፈር ድራሽ እንደሚያጠፋ ወያኔ የአዋቂዎች ምክር ሳይሰማ ስለቀረ አይደለም። በአጥፊ ስራው የቀጠለው መዝረፍ የሚችለዉን ንብረት ካጋበሰና ከዘረፈ በኋላ ነገ ኢትዮጵያ እንደአለ ባድማ ብትሆን ቅንጣት ስለማይሰማዉ ነዉ። ለሀገር የሚያስብ መንግስት ቢሆን ኖሮ የአገሪቱ ወጣትና የተማረ የሰዉ ኃይል እንደ ጎርፍ ከአገሪቱ እየጎረፈ ሲወጣ ይቆረቆር ነበር። ወያኔ የተማረ ሰው ቢሰደድ፣ ዜጎች ቢራቡና በገዛ አገራቸዉ ቢዋረዱ ጉዳዩ አይደለም። በሰላማዊና ህገመንግስታዊ መንገድ ጥያቄ ያነሳን ዜጋ ሁሉ እንደአውሬ የሚቀጠቅጠውና ወህኒ ቤት የሚያጉረው ይህ በደል ነገ በሀገሪቱ ዘላቂ ህልውና ላይ የሚያመጣውን መዘዝ አጥቶት አይደለም። የአገራችን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ጉዳዩ ስላልሆነ እንጂ።
የኢትዮጵያን ብሄር ቤሄረሰቦች የሚያይዟቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአንድነት ክሮች እያንቋሸሸና እንደሌሉ እየሰበከ በሚለያዩንን ጥቃቅን ውጭያዊ የቋንቋና የዘር ግንዶች አጉልቶ የሚያሳየን አገራችንንና ህዝቧን እንደ አንድ ሀገር ሳይሆን እንደጊዚያዊ የዝርፊያ ቀጠና ስለሚመለከት ብቻ ነው።
ወያኔና ሎሌዎቹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ጠላቶቹ ናቸው እያሉ አንዴ የፈረሰችዉ ሶማሊያን፤ ሌላ ጊዜ ወደ ኤርትራና ግብጽ ጣቱን የሚጠነቁሉት አይናችንን ከወያኔ ላይ እንድናነሳ ነዉ እንጂ ከወያኔ በላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ጠላት የለም። ወያኔ በአካል እኛን ከሚመስሉ ኢትዮጵያውያን መሃል ይውጣ እንጂ፣ በተግባር ከቀን ጅብ ያልተናነሰ የዘረኞችና የዘራፊዎች ቡድን ነው። ብዙ ጊዜ ወያኔ ራሱ የጻፈውን ህግ ሲጥስ ለምን ብለን የምንገረም አለን። ወያኔ ሕግና ሕገ-መንግስት፣ ለአገራቸዉ የሚቆረቆሩ ምሁራንን የሚያፈሩ የትምህርት ተቋማት፣ በህዝብ የሚታመን ሰራዊት፣ ለህግ ብቻ የሚሰራ ፍርድቤትና የመሳሰሉት ዘላቂ ተቋማት እንዳይኖሩን የሚያደርገውና ያሉትንም የሚያፈርሰው ለኢትዮጵያ ብሄራዊና ዘላቂ ጥቅም ምንም ደንታ ስለሌለዉ ነዉመሆኑን የሚዘነጋ ኢትዮጵያዊ በእጅጉ የዋህ ነው። ወያኔ የኢትዮጵያ ጠላት ነው።
ስለዚህም እንላለን እኛ የግንቦት 7 ልጆችህ ሀገርህ ትውልድ ተሻግራ እንድትቀጥል አንተም የምትኮራባት ዜጋ እንድትሆናት የምትሻ የኢትዮጵያ ልጅ ሁሉ ሀገርህን ከወያኔ የቀን ጅቦችና ወራሪዎች አድን። አጎንብሰህ ሳይሆን ቀና ብለህ የምትሄድባት ሀገር እንድትኖርህ የምትሻ ሁሉ ለማይቀረው የጀመርነውን የአርበኝነትና የነጻነት ትግል ጉዞ ተቀላቀለን። እኛ የተባበርን እለት አብረን የተነሳንና በቃ ያልን እለት ታሪካዊቷ ሀገራችንና ታላቁ ሕዝባችን ዘላቂ ብሄራዊ ጥቅማቸው ይከበራል።
አዎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ዋነኛ ጠላት ወያኔ ብቻ ነው!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar